ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስና እስልምና

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስና እስልምና

ህሱ ሰላም

የእስልምና እምነት ተከታይ ወንድምና እህቶቻችን የኢድ አል ፈጥር (የፆም ፍቺ በዓል) እያከበሩ ይገኛሉ። ይህንን መነሻ አድርገን በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ከሚሰነዘሩ በርካታ ጥያቄዎች መካከል አንዷን አንስተን እንድናወጋት ወደድኩ። በእርግጥ ርእሱ አንድ ቢሆንም በርካታ ጉዳዮችን ይጠቀልላል የሚጠቀልል ነው።

በቅርብ የተነሱ የእስልምና ምሁራን የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ጉዳይ ትልቁ አጀንዳቸው እየሆነ መጥቷል። በፍልስፍናና በሥነ እስልምና ጉዳዮች የሚታወቀው ቡርሃን ሐዲስ (ሙሐመድ አሊ) በ NBC ETHIOPIA የነፀብራቅ መርሐግብር ላይ ሐዋርያው ጳውሎስን የመጀመሪያው የክርስትና “የተሐድሶ” አንቀሳቃሽ ብሎ ሲያነሳው መስማቴ የቅርብ ትውስታ ነው።

የእስልምና ምሁራን በሐዋርያው ጳውሎስ ላይ የሚሰነዝሯቸው መሠረታዊ ትችቶች የሚመነጩት እስልምና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚያነሳቸውን በርካታ ስሁት ሐሳቦች የሚቃወሙ መልእክታትን (የኢየሱስ አምላክነት፣ ስቅለትና ሞት፣ የክርስትና እውነተኝነትና የብል ምሳሌዎች ትርጓሜዎች) አስቀድሞ በመጻፉ በነዚህ ጉዳዮች ላይ የሚያነሱት ጥያቄዎች ውኅ መቋጠር ባለመቻላቸው የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስን ማንነት በማጉደፍ የሐሳባቸውን ተገቢነት ከማሳየት አንፃር ነው።

መሰረታዊ ትችቶች

  1. ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የክርስቶስ ደቀመዝሙር ባለመሆኑ ሐዋርያ መባሉ ልክ አይደለም።
  2. የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ አስተምህሮዎች ከቅዱስ ወንጌል ጋር የማይገጥሙ ናቸው።

 

1. በመሰረታዊ ደረጃ ትችት 1 የኢየሱስ ክርስቶስን የወንጌል አስተምህሮ በቅጡ ካለመረዳት የመነጨ ስህተት ነው። በቅዱስ ወንጌል አስተምህሮ መሠረት የክርስቶስ ደቀመዝሙርነት ከዋሉበት ተውሎ ካደሩበት ታድሮ ከእግሩ ስር በመማር ብቻ ሳይሆን እርሱ ካስተማራቸው ሐዋርያትና ተከታዮቻቸው (በሐዋርያት ቅብብሎሸ በተማሩ) ዘንድ በመማር፣ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም በመጠመቅ የሚገኝ ሐብት ነው። (ማቴ 28:19-20)

ከእዚህ አንፃር ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በሐዋርያት ሥራ ፀሐፊ በሆነው በወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ስለደቀመዝሙርነቱ በተመሠከረለት (ሐዋ 9:10) አናንያ በተባለ ሰው ተምሮና ተጠምቆ ደቀመዝሙር የሆነ በመሆኑ (ሐዋ 9: 17-19) ከላይ የተጠቀሰውን የወንጌል ትዕዛዝ ሙሉ ለሙሉ ያሟላ መሆኑን ማንሳት ይቻላል።

ከዚህ ባሻገር በልዩ መንገድ የተጠራ መሆኑ (ሐዋ 9:3-8)፣ ክርስቲያን ተብለው በአንፆኪያ ከተጠሩት ጋር አብሮ ነበር። (ሐዋ 11:25-26)፣ የመጀመሪያው ጉባኤ ተሳታፊ ነበር (ሐዋ 15:22-29)፣ በመንፈስ ተሞልቶ ነበር (ሐዋ 13:9)፣ ተዓምራት ያደርግ ነበር (ሐዋ 14:11) ከሐዋርያትና ከአርድእት ጋር ያገለግል ነበር። (ሐዋ 15:35)፣ የሐዋርያት አለቃ ሆኖ የተሾመው ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ስለትምህርቱ በመልዕክቱ መስክሮለታል (2ኛ ጴጥ 3:15)

2. የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት ከሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ አስተምህሮ ጋር ይጋጫል የሚለው ጥያቄ ምንም እንኳን ከላይ በተሰጡት ምላሾች አንጻር መመለስ የሚቻል ቢሆንም በይበልጥ የወንጌል ዋና አላማን መነሻ በማድረግ የተወሰኑ ተጨማሪ ነጥቦች ማንሳቱ ይበልጥ ነጥቡን ግልፅ ስለሚያደርገው በዛ መልኩ እንመልከተው።

መሠረታዊ የቅዱስ ወንጌል አላማ ከእግዚአብሔር ሦስቱ አካላት አንዱ የሆነው ወልድ በተለየ አካሉ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ የህይወት ውሐ የሆነን ትምህርት አስተምሮና የሰውን ልጅ ከአምላክ ጋር የሚያገናኙ ሥርዐቶችን ሠርቶ በዕፀ መስቀል ላይ በከፈለው ፍፁም ዋጋና በትንሳኤው የሰውን ልጅ ከዘላለማዊ የሐጢያት ባርነት ነፃ አውጥቶ ወራሽ የሆንበትን መንገድ መተረክ ነው።

  • በቅዱስ ወንጌል ክርሰቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ በተደጋጋሚ የተገለፀ ሲሆን /ማቴ 3:15፣ ማር 1:1፣ሉቃ 1:35፣ ዮሐ 1:34/ በተመሳሳይ ጳውሎስም ይህን ያስተምር ነበር። ሐዋ 9:20
  • ወንጌል መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ እያለ መመለስን ሲያስተምር (ማቴ3:2፣ ማር 1:15) በተመሳሳይ ሐዋርያው ጳውሎስም ይህን ያስተምር ነበር ( ሐዋ 28:31፤ 1ኛ ተሰ 1:9)
  • ስለቅዱስ ቁርባንና ስለመስዋዕቱ ሐዋርያው ጳውሎስ የማቴ 26:28 ትረካ በመዋስ በ1ኛ ቆሮ 11:25 ላይ ጽፏል
  • ስለትንሳኤው በ1ኛ ቆሮ 15:1-7 ሐዋርያው የፃፈው ታሪክ በማቴ 28፣ በሉቃ 24፣ በማር 16ና በዮሐ 20 የተገለጠው ታሪክ ጋር ህብረት ያለው ነው።

ይህን እንደማሳያ አነሳነው እንጂ የሐዋርያው መልዕክትና በሐዋርያት ሥራ የተገለጠው አገልግሎቱ በወንጌልና በኢየሱስ ክርስቶስ አስተምህሮ የተመሰከረ ነው።

እኒህን ሁሉ ማስረጃዎች ወደጎን አድርገን የእነሱን አመክንዮ ብንቀበል እንኳን የእስልምናው የቀደመ የሙግት ሐሳቦችን ውድቅ የሚያደርግና ቢያንስ ሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ ተበርዟል ከሚለው አስተምህሯቸው ወጣ ብለው ወንጌል ልክ ነው የሐዋርያው የቅዱስ ጳውሎስ መልእክት እንጂ ወደ ሚል ሙግት ስለሚያንሸራትታቸው ለምን ቢያንስ ወንጌሉን አላመናችሁበትም ያስብለናልና እንጠይቃለን።

ነገር ግን ሐዋርያውን በዚህ መጠን ለሚተቹት ሁሉ ከእርሱ ጋር አንድ በምንሆንባት የክርስቶስ አካሉ በሆነችው ቤተክርስቲያን የእርሱን ቃል ተውሰን እንዲህ እንላለን።

“ዳሩ ግን ማንም ሊከራከር ቢፈቅድ፥ እኛ ወይም የእግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያናት እንዲህ ያለ ልማድ የለንም።” 1ኛ ቆሮንቶስ 11፥16