ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስና የኢየሱስ ብቻ (Only Jesus) አስተምህሮ

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስና የኢየሱስ ብቻ (Only Jesus) አስተምህሮ

አማን እንዳለ


“የኢየሱስ ብቻ” ሐሳውያን መምህራን በሥላሴ የሚያምኑ ክርስቲያኖችን ከሚወቅሱባቸውና የነገረ-ሥላሴን ትክክለኛነት ከሚቃወሙባቸው ጉዳዮች መካከል ዋነኛው እውነተኛው አምላክ ራሱን በሦስት አካላት ገልጧል የሚለው ክርስቲያናዊ አስተምህሮ ነው። መጽሐፍ ቅዱሳዊውና ታሪካዊው ክርስትና አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ የአንዱ መለኮት ሦስት አካላት/ማንነቶች እንደሆኑ በአፅናዖት ያስተምራል። እነዚህ ወገኖቻችን ብዙ ጊዜ “አካል” የሚለው የቃል አገባብና ትርጉም ላይ ግራ ሲጋቡና መምህራኖቻቸው ደግሞ ሆነ ብለው “ሦስት አካላት” በማለት የምንጠቀመውን ጽንሰ ሐሳብ ወደጎን በማድረግ “ብዝሃ አማላክትን ታመልካላችሁ” ብለው ሲከሱን ይደመጣሉ። እንደ እውነቱ ከሆነ በክርስትና ታሪክ ወይንም በጥንታዊው ነገረ-ክርስትና ውስጥ ልክ እንደ “ውግዝ ከመ አርዮስ ወ ሰባሊዮስ” ሁሉ ከተወገዙት ትምህርቶች መካከል ብዝሃ-አምላክ (polytheism) ይገኝበታል። ስለዚህ እኛኑ መልሶ በዚያው ክስ መክሰሱ የነገረ-ሥላሴን መሠረታዊ ትምህርትና ትንታኔ በአግባቡ ያልተረዱ መሆናቸውን ከማሳየት የዘለለ ትርጉም የሌለው የሐሰት ክስ ነው።

በዚህ ጽሑፍ የዚህ ኑፋቄ ቡድን አባላት “መሠረታዊ” በማለት ከሚያምኗቸው አስተምህሮዎች መካከል አንዱን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በጻፋቸው መልእክታት ሚዛን እንፈትሻለን። ትምህርታቸውን የምንቃኘው አሁን በሕይወት የሌሉት በኢትዮጵያ የቤተ እምነቱ መሥራችና ዋና አስተዳዳሪ የነበሩት ቄስ ተክለማርያም ገዛኸኝ “ኢየሱስን ማን ይሉታል” በሚል ርእስ ያዘጋጁትን መጽሐፍ መነሻ በማደርግ ይሆናል። ደራሲው እንዲህ ይላሉ፦

“ክርስቶስ ከዘላለም ከአብ ተወልዶ ከአብ አካል ውጪ የኖረ ሁለተኛ አምላክ ነው የሚሉ ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ምንም ማስረጃ የላቸውም። እግዚአብሔር እግዚአብሔርን አይወልድም፣ በልደት የሚፈጠሩ እግዚአብሔሮች የሉምና። እግዚአብሔር ግን በመገለጫ መንገዶቹ ራሱን ለሕዝቡ ይገልጻል። እግዚአብሔር በሥጋ እንደሚገለጽ ከጥንት በነቢያት አፍ ሲናገረው የቆየው ትንቢትና ቃል ኪዳን ነበር” (ቢሾፕ ተከለማርያም ገዛኸኝ። ኢየሱስን ማን ይሉታል። የመጀመሪያ እትም፣ 1978፣ ገጽ 54 )።

በተጨማሪም፦

“እግዚአብሔር አብ የላከልን ልጅ ሰማያዊ ስለሆነ የባሕርይ ልጁ ነውና በአካል ከአብ የተለየ አይደለም። ወልድ የአብ መልክ ነው። <<እኔና አብ አንድ ነን>> ብሎ በድፍረት መናገር የሚችለው አብና ወልድ በውሕደት በአንድ አካል ውስጥ ስላሉ ብቻ ነው” (ገፅ 68)።

“በኢየሱስ ብቻ” አስተምህሮ መሠረት አብና ወልድ ሁለት የተለያዩ አካልት/ማንነቶች ሳይሆኑ ከላይ እንዳነበብነው በአንድ አካል ተዋሕደው ያሉ አንድ አካል ናቸው (በእርግጥ ግልጽነትና የእርስ በርስ ተቃርኖ ቢኖረውም)። አሁንም ነገሩ ግልጽ እንዲሆንልን እነዚህ የኢየሱስ ብቻ ሰባኪያን ወልድ የእግዚአብሔር አብ ቃል ነው ብለው ሲያምኑ ይህንን ቃሉን ሥጋ አድርጎ በዚያ ሥጋ ውስጥ አብ ተገለጧል እያሉን ነው። አንባቢ በቀላሉ እንደሚያስተውለው ጥቅሶች ከአውዳቸው ውጪ ተጠቅሰዋል፤ ይህንንም በሰፊው እያየን እንሄደለን። ለአሁን ግን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ምድር ከመምጣቱ በፊት ከአብ በተለየ ማንነት አይኖርም የሚለውን ግልጽ የሆነ ክህደት በሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ጽሑፎች እንመልከት፦

“በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ያ አስተሳሰብ፣ በእናንተም ዘንድ ይሁን፤ እርሱ በባሕርዩ አምላክ ሆኖ ሳለ፣ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን ሊለቅቀው እንደማይገባ አድርጎ አልቈጠረውም፤ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ፣ በሰውም አምሳል ተገኝቶ፣ ራሱን ባዶ አደረገ፤ ሰው ሆኖ ተገልጦም፣ ራሱን ዝቅ አደረገ፤ እስከ ሞት፣ ያውም በመስቀል ላይ እስከ መሞት ድረስ ታዛዥ ሆነ። ስለዚህ እግዚአብሔር እጅግ ከፍ አደረገው፤ ከስምም ሁሉ በላይ የሆነውን ስም ሰጠው፤ ይኸውም በሰማይና በምድር፣ ከምድርም በታች፣ ጕልበት ሁሉ ለኢየሱስ ስም ይንበረከክ ዘንድ፣ ምላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።” (ፊልጵስዩስ 2፡5-11 አ.መ.ት)።

በዚህ ስፍራ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች በወንጌሉ የዳኑ ሰዎች እንዴት መመላለስ እንዳለባቸው መመሪያዎችን እየሰጠ ነው። በመጀመሪያው ምዕራፍ (ም-1) የፊልጵስዩስ ሰዎች ስለ ወንጌል በሚደርስባቸው መከራ እንዳይሸበሩ ይነግራቸዋል (1፡28)። በዚህ ዓለም ሳሉ አማኞች የክርስቶስ መሆናቸው የሚታወቅበት አንደኛው ሁኔታ ክርስቶስ እንደተሰደደው እነርሱም መሰደዳቸው እንደሆነና ይህም ለቅዱሳን ከእግዚአብሔር የተሰጠ ምልክት እንደሆነ ይነግራቸዋል (1፡28)። በዚህ ሳያበቃ በወንጌሉ በማመን የዳኑበትን እምነት የተቀበሉት በጸጋ አማካኝነት እንደሆነ ካሳሰባቸው በኋላ ይህም ስለ እርሱ መከራ እንዲቀበሉ ጭምር እንደሆነ ያስገነዝባቸዋል። በፊልጵስዩስ አማኞች ላይ የሚደርሰው መከራ ሁሉ ስለወንጌል ነውና ለአንዱ ወንጌል ሁሉም እንደ አንድ ሰው እየተጋደሉ መሆኑን ያወሳል (ቁ-27)።

በማስከተልም አማኞች ከማያምኑ ሰዎች ዘንድ መከራ ቢደርስባቸውም ሁሉንም እየታገሱ ይልቁኑ በክርስቲያናዊ ባሕርይ አንዳቸው ከሌላቸው ጋር እንዲመላለሱ ያሳስባቸዋል። ይህም ትህትና ይሰኛል። የሁለተኛው ምእራፍ ጭብጥ አማኞች በማንኛውም ሕይወት ውስጥ የክርስትናን ሕይወት መኖርና መለማምድ ይገባቸዋል የሚል ነው። ምእራፍ 2 ቁጥር 3 ላይ “በራስ ወዳድነት ምኞት ወይም ከንቱ ውዳሴ ለማግት አንዳች አታድርጉ” የሚለው ሐዋርያዊ ትዕዛዝ አማኞች አንዳቸው ከሌላቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት እያንዳንዱ ሌላውን የሚጠቅመውን እንጂ የራሱን ብቻ አይመልከት በሚል ሐሳብ ተጠናክሯል። እንደዚህ ያለ የሕይወት ምልልስ ትህትህና ተብሎ በዚህ ስፍራ የተጠቀሰው ነው። ትህትና ሌሎች ከእኛ እንደሚሻሉ እንድንቆጥር ያደርገናል (ቁ 3)።

በዚህ ቦታ ላይ ሐዋርያው ስለ ትህትና የሚነገረንን ከተረዳን ዘንዳ ከታች ካለው ምንባብ አንጻር እንዴት ያለ ስነ-መለኮታዊ ጭብጥ እንዳለው መገንዘብ ከባድ አይሆንም። ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ  የሕያው የእግዚብሔር ልጅ እንደሆነ ስናምን ሁላችንም በአንድነት የእግዚአብሔር ልጆች የመሆንን መብት አግኝተናል (ዮሐ. 1፡12)። እኛ ሁላችንም የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባል የመሆንን የከበረ ስጦታ ተጎናጽፈናል (ኤፌ. 2፡19)። እንግዲያውስ እኛ ሁላችንም በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል የእግዚአብሔር ልጆችና የቤተ ሰብ አባላት ከሆንን አንዳችን ከሌላው ያነስን ወይም ሌላው ወንድማችን ከእኛ የተሻለ እንደሆነ የምንቆጥረው እንዴት ባለ ሁኔታ ነው? ምላሹ በትህትና የሚል ነው። ትህትና እኩል የሆነ መብትና ሥልጣንን በተጎናጸፉ ሁለት አካላት መካከል ያለን ግንኙነት ህብራዊ (Harmonize) የሚያደርግ ግሩም ቅመም ነው።

ለዚህ ድንቅ ማሳያ የሚሆን ከጌታችንና ከመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የላቀ ማን ሊኖር ይችላል? ማንም! ለዚህም ነው ሐዋርያው ትህትናን ለአማኞች ለማስረዳት ኢየሱስ ክርስቶስን መነሻ ያደረገው። ለመሆኑ ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ መልዕክት ውስጥ በምን ዓይነት መንገድ ተገለጸ?

  1. በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ አስተሳሰብ አለ
  2. እርሱ በባሕርዩ አምላክ ነው
  3. ከእግዚአብሔር አብ ጋር መተካከልን ሊለቀው እንደማይገባ አልቆጠረም
  4. የባሪያን መልክ የያዘው እርሱ ነው
  5. በሰው አምሳል የተገኘው እርሱ ነው
  6. በዚህም ራሱን ዝቅ አደረገ
  7. እስከ ሞት ድረስ የታዘዘ ሆነ
  8. በእግዚአብሔር ከፍ ከፍ ተደርጎ ከስም ሁሉ በላይ የሆነ ስም የተሰጠው እርሱ ነው
  9. ጉልበት ሁሉ በስሙ ተንበርክኮ ምላስ ሁሉ ለአብ ክብር ጌትነቱን የሚያውጅለት እርሱ ነው
  10. በብሉይ ኪዳን ስለ ያሕዌ የተነገረው ጥቅስ ስለተጠቀሰለት እርሱ እግዚአብሔር (ያሕዌ) ነው።

ከላይ ቢሾፑ አብና ወልድ በአንድ አካል ውስጥ ተዋኸደዋል (በአዲስ ኪዳን) በብሉይ ኪዳን ደግሞ ወልድ የአብ ቃል ነበር ብለው የጻፉትን ላስታውሳችሁና ይህንን ሐሳባቸውን በዚህ ምንባብ መነጽር እንፈትሽ። ኢየሱስ ክርስቶስ በፊልጵስዩስ መልዕክት ውስጥ በሐዋርያው ጳውሎስ አገላለጽ ቅድመ ሕላዌ (preexistence)  የነበረው ነበር፤ በዚህ ቅድመ ሕላዌው ደግሞ በባሕርዩ አምላክ የነበረ ነው። ጌታችንንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ምንም እንኳን ከእግዚአብሔር ጋር የተካከለ ቢሆንም በቁጥር 7 እና 8 ላይ የተገለጹትን ነገሮች መሆንን እንደማይገባ አድርጎ አልቆጠረም። ከዚህ ገለጻ ውስጥ ሁለት ነገሮች ግልጽ ናቸው። አንደኛ ቃል ወይም ንግግር ሆኖ ሳይሆን የነበረው በባሕርዩ አምላክ ሆኖ እንዲሁም ከእግዚአብሔር ጋር በተካከለ ሁኔታ ይኖር ነበረ። ሁለተኛ በንቃተ ህሊና ረገድ ካየነው ደግሞ የራሱ የሆነ ንቃተ ሕሊና (consciousness) የነበረው ሲሆን ምን እየተደረገ እንደነበር ያውቅ ነበር (መተካከልን ሊለቀው እንደማይገባ አልቆጠረውም)። ስለዚህ የቢሾፕ ተክሌ ትምህርት እንደዚህ ግልጽ በሆነ መንገድ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ይጋጫል። ቢሾፑ ምንም እንኳን እግዚአብሔር የራሱን ቃል ሥጋ አድርጉ በሥጋው ውስጥ የተገለጠው አብ ነው ቢሉም ለዚህ የሚሆነ አንድ እንኳን የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ ማቅረብ አይችሉም። ከዚህ ይልቅ በተሳሳተ ቅድመ ልባዌ (with wrong presupposition) እኚህ የሐሰት መምህር ክርስቶስ ኢየሱስን አምላክ ነው ካልን ሁለተኛ አምላክ እንደምንፈጥር ይነግሩናል። ሆኖም ይህ አባባል ከራሱ ከሐዋርያው ጳውሎስ አጻጻፍ እንዴት ትክክል እንደማይሆን እንመልከት።

ከቁጥር 9 እስከ 11 ባለው ውስጥ “…በሰማይና በምድር፣ ከምድርም በታች፣ ጕልበት ሁሉ ለኢየሱስ ስም ይንበረከክ ዘንድ፣ ምላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው” ሲል ይህንን ምንባብ ሐዋርያው የጠቀሰበት ክፍል የሚገኘው በነቢዩ ኢሳይያስ መጽሐፍ 45:23 ነው፦ “ጕልበት ሁሉ በእኔ ፊት ይንበረከካል፤ አንደበትም ሁሉ በእኔ ይምላል፤ ብዬ በራሴ ምያለሁ፤ የማይታጠፍ ቃል፣ ከአፌ በጽድቅ ወጥቷል።” በሚገርም ሁኔታ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የጠቀሰው ምንባብ እግዚአብሔር አምላክ ራሱን በእንጨት ከተሠሩት የአሕዛብ አማልክት ጋር በንጽጽር በማቅረብ ከእርሱ ሌላ አምላክ እንደሌለና እርሱ ብቸኛ አምላክ መሆኑን በአፅንዖት የገለጸበት ክፍል ነው። ነገር ግን ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን ክፍል ከጠቀሰ በኋላ ሁለት አካላትን/ማንነቶችን እንዴት እደገለጸ አስተውሉ። በባሕርዩ አምላክ የሆነና ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን ሊለቀው እንደማይገባ ያልቆጠረው ጉለብት ሁሉ የሚንበረከክለት ጌታ ኢየሱስ በራሱ አንድ ማንነት ሲሆን እግዚአብሔር ተብሎ የተጠራው አብ ደግሞ ለእርሱ ክብር እንዲሆን ተብሎለታል። ያም ቢሆን ሐዋርያው ደጋግሞ በመልዕክቱ እንደጻፈው አንድ እውነተኛ አምላክ መኖሩ ግልፅ ነው። አብና ወልድ በአንድ መለኮታዊ ባሕርይ በአንድ አምላክነት የሚጠሩ ልዩ ማንነቶች (Distinct Persons) እንጂ አንድ ማንነት አይደሉም። መጽሐፍ ቅዱስ ግልጽ በሆነ ሁኔታ የሚነግረን ይህንን ነው። ከዚህ እውነታ ያፈነገጠ አስተምህሮ ሁሉ በቃሉ ላይ የሚፈጸም ግልጽ ክህደት ነው።

ይቀጥላል…


መልስ ለሰባልዮሳውያን