የጳውሎስ ወይስ የሙሐመድ ኩረጃ? የሙስሊም ሰባኪያን ቅጥፈት ሲጋለጥ

የጳውሎስ ወይስ የሙሐመድ ኩረጃ?

የሙስሊም ሰባኪያን ቅጥፈት ሲጋለጥ


ሰሞኑን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስን በኩረጃ የሚከሱ በሙስሊሞች የተዘጋጁ ሁለት ጽሑፎችን አንብቤ ነበር። ሁለቱንም አንብቤ ከጨረስኩ በኋላ ለጸሐፊያኑና ለአንባቢዎቻቸው ከልቤ አዘንኩላቸው። የጽሑፎቹ አዘጋጆች የዕውቀታቸው ልክ በጽሑፎቹ ውስጥ የሚታየው ከሆነ የማስተማር ብቃት እንዳላቸው ራሳቸውን በመቁጠር ለመጻፍ መድፈራቸው፤ አንባቢያናቸውም እንዲህ ያሉ ወገኖችን በመስማት መሳሳታቸው የሚያሳዝን ነው። እስኪ ሁለቱንም ጽሑፎች አከታትለን እንገምግም። የመጀመርያው ጸሐፊ እንዲህ ሲል ይጀምራል፦

የጳውሎስ ኩረጃ

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

371 «የመጽሐፉ ሰዎች ሆይ! እውነቱን በሐሰት ለምን ትቀላቅላላችሁ? እውነቱንም እናንተ የምታውቁ ስትኾኑ ለምን ትደብቃላችሁيَا أَهْلَ الْكِتَابِ لِمَ تَلْبِسُونَ الْحَقَّ بِالْبَاطِلِ وَتَكْتُمُونَ الْحَقَّ وَأَنتُمْ تَعْلَمُونَ

ይህ ጸሐፊ እንኳንስ ክርስትናን የተመለከቱ አርዕስት ላይ ሊጽፍ ይቅርና የገዛ መጽሐፉን እንኳ በቅጡ የማያውቅ ሰው መሆኑ ግልጽ ነው። ቁርአን አይሁድና ክርስቲያኖችን “የመጽሐፉ ሰዎች” በማለት አክብሮ ይጠራቸዋል፤  እነርሱ ጋር እውነት መኖሩን ቅድመ ግንዛቤ በመያዝ “እውነትን እንዳይደብቁ” ይናገራቸዋል እንጂ ከእነርሱ ጋር ያለው መጽሐፍ እንደተለወጠ አይነግራቸውም። አንድ ሰው እውነትን መደበቅ የሚችለው እውነት እጁ ላይ ካለ ብቻ ነው። እውነት እጁ ላይ በሌለበት ሁኔታ ምኑን ነው ሊደብቅ የሚችለው? የቁርአን ደራሲ በአይሁድና በክርስቲያኖች እጅ እውነት እንዳለ ስለሚያውቅ ይህንን እውነት በመደበቅ ወቀሳቸው እንጂ አንድም ጊዜ እጃቸው ላይ ያለው መጽሐፍ እንደተበረዘ አልነገራቸውም። አልፎ ተርፎም የእርሱ ቁርአን “በመጽሐፉ ሰዎች እጅ” የሚገኘውን መጽሐፍ ለማረጋገጥ እንደመጣ በተደጋጋሚ ተናግሯል (የላም ምዕራፍ 2፡40-41፣ 89፣ 91፣ 101)። አይሁድና ክርስቲያኖች በገዛ መጻሕፍታቸው መተዳደር እንደሚገባቸውም አጥብቆ ይናገራል (የማዕድ ምዕራፍ 5፡43-44፣ 47)። እውነታው ይህ በሆነበት ሁኔታ የቁርአን ጥቅሶችን ያለ ርእስና አውድ መጥቀስ የደራሲውን ዕውቀት አልባነት ያሳያል። አብዱል ቀጥሎ እንዲህ ይለናል፦

ጥንት የነበሩት የፈጣሪ ነቢያት በአምላክ ተልከው ትንቢት ሲመጣላቸው የሚናገሩት በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ነበር፦

2 ጴጥሮስ 121ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፥ ዳሩ ግን በአምላክ ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ።

በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩእንጂበመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ጻፉአይልም፥ ብዙ ሰዎች ጳውሎስ የጻፋቸውን አሥራ አራት ደብዳቤዎች“letters” “በመንፈስ ቅዱስ ተነድቶ ነውይላሉ። ቅሉ ግን በመንፈስ ቅዱስ ተነድቶ የተጻፈ ጽሑፍ የለም፥ ባይሆን በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው የተናገሩት ንግግር አለ። ይህም ከአምላክ ተልከው ትንቢት እንጂ ታሪክ አይደለም፥ ከመነሻው ይህ ጥቅስ ስለ ነቢያት እንጂ ስለ እነ ጳውሎስ ሽታው የለውም።

ሙስሊሙ ሰባኪ ለገዛ ውርደቱ እየቀጠፈ ነው። እውን ይህ ጥቅስ በንግረት ደረጃ ስላለ ትንቢት ብቻ እየተናገረ ነው ወይንስ በቃል ተነግሮ በጽሑፍ ስለሰፈረ ትንቢት እየተናገረ ነው? ሙስሊሙ ሰባኪ ቆርጦ ያስቀረውን የጥቅሱን ቀዳሚ ክፍል ጨምረን እንጥቀስ፦

“ይህን በመጀመሪያ እወቁ፤ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም፤ ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ።” (2ጴጥ. 1:20-21)

በግልጽ እንደሚታየው ጥቅሱ እየተናገረ ያለው የብሉይ ኪዳን ነቢያት በቃል ተናግረው በመጽሐፍ ስለ ሰፈረው ትንቢት እንጂ በቃል ተነግሮ ስለቀረ ትንቢት አይደለም። ትንቢት መጀመርያ በነቢያት አማካይነት ለሕዝቡ ይነገራል ከዚያም በጽሑፍ ይሰፍራል። ደፋሩ አብዱል ግን “በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ” እንጂ “በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ጻፉ” አይልም”  በማለት የድፍረቱንና ያለማወቁን ጥግ አሳይቶናል። የአላዋቂነት አንዱ መጥፎ ነገር ደፋር ማድረጉ ነው። እንዲህ ያሉ ሰዎችን በሚመጥናቸው ንግግር ልክ ተናግሮ ቦታ ማስያዝ ተገቢ ቢሆንም ለአንባቢያን ካለን አክብሮት አንጻር ሊገባቸውና ሊመጥናቸው የሚችለውን ንግግር አንጠቀምም። አንባቢያን እንዲህ ካሉ ራሳቸውን እንደ አዋቂ ከሚቆጥሩ አላዋቂዎች እንዲጠበቁ ብቻ በመምከር እናልፋለን።

ሙስሊሙ ሰባኪ ይህ ጥቅስ የጳውሎስን መልእክታት እንደማይመለከት ሊነግረን ሞክሯል። ያላስተዋለው ነገር ቢኖር ሐዋርያው ጴጥሮስ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ስለሚገኙት ትንቢቶች በዚህ ሁኔታ በተናገረበት መልእክቱ ውስጥ የጳውሎስን ጽሑፎች በነዚሁ ትንቢታዊ መጻሕፍት ደረጃ ላይ ማስቀመጡን ነው። አንድ ምዕራፍ ወደ ፊት አልፈን ስናነብ እንዲህ የሚል ቃል እናገኛለን፦

“የጌታችንም ትዕግሥት መዳናችሁ እንደ ሆነ ቍጠሩ። እንዲህም የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስ ደግሞ እንደ ተሰጠው ጥበብ መጠን ጻፈላችሁ፥ በመልእክቱም ሁሉ ደግሞ እንደ ነገረ ስለዚህ ነገር ተናገረ። በእነዚያ ዘንድ ለማስተዋል የሚያስቸግር ነገር አለ፥ ያልተማሩትና የማይጸኑትም ሰዎች ሌሎችን መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ እነዚህን ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ። እንግዲህ እናንተ፥ ወዳጆች ሆይ፥ ይህን አስቀድማችሁ ስለምታውቁ፥ በዓመፀኞቹ ስሕተት ተስባችሁ ከራሳችሁ ጽናት እንዳትወድቁ ተጠንቀቁ” (2ጴጥ. 3:15-17)።

ሐዋርያው ጴጥሮስ የቅዱስ ጳውሎስን መልእክታት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በሚጠቀሱበት አጠቃቀስ γραφὰς (ግራፋስ – Scriptures) ብሎ አብሮ ቆጥሯቸዋል። በመልእክታቱ ውስጥ ለማስተዋል የሚያስቸግሩ ነገሮች መኖራቸውን ከተናገረ በኋላ ያልተማሩና የማይጸኑም ሰዎች ልክ በሌሎች መጻሕፍት ላይ እንደሚያደርጉት እነዚህንም ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው እንደሚያጣምሙ ይነግረናል። ይህ አብዱል በዚህ ጽሑፉ ይህንን እያደረገ ይገኛል። የመልእክቱ ጸሐፊ ጴጥሮስ ራሱ የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስን መልእክታት በዚህ ልክ አክብሮ ተናግሮላቸው ሳለ ከተመሳሳይ መጽሐፍ በዚያው ጸሐፊ የተጻፈን አንድ ጥቅስ ቆንጥሮ በመውሰድ ጸሐፊው የማያምነውን ሐሳብ ለማስተላለፍ መሞከር ራስን ማሞኘት ነው። ይህ ሙስሊም ሰባኪ በጴጥሮስ ፊት የጳውሎስን መልእክታት ለማጣጣል ቢሞክር “ያልተማርክና የማትጸና … ለገዛ ጥፋትህ ቅዱሳት መጻሕፍትን የምታጣምም … የተሳሳትክ አመጸኛ” ብሎ በዚህ ጥቅስ ውስጥ በተጻፉት ቃላት እንደሚገስጸው ጥርጥር የለውም።

አብዱል ዲስኩሩን ይቀጥላል፦

ጳውሎስ ብዙ ጊዜ ከጥንት ነቢያት ሲጠቅስ ስለሚሳሳት የሚጽፈው በመንፈስ ቅዱስ በጭራሽ አይደለም፦

1 ቆሮንቶስ 29 ነገር ግን፦ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው አምላክ ለሚወዱት ያዘጋጀውተብሎ እንድተጻፈ፥ እንዲህ እንናገራለን።

በብሉይ ኪዳንዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀውተብሎ የተጻፈ በባትሪ ብትፈልጉ አታገኙም፥ ጥቅሱን የወሰደበት ቦታ አምላክ ስላዘጋጀው ነገር ሳይሆን አሐዳውያን ባዕድ አምላክን መስማት፣ መቀበል እና ማየት እንዳልፈለጉ የሚያስጨብጥ ነው፦

ኢሳይያስ 644 ሰዎች ከጥንት ጀምሮ ለሚጠብቁህ ከምትሠራላቸው ከአንተ በቀር ሌላ አምላክን አልሰሙም በጆሮአቸውም አልተቀበሉም ዓይንም አላየችም።

ጳውሎስ ሲኮርጅ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ቢሆን ኖሮ በትክክል ማስቀመጥ ያቅተዋልን?

ከአፍታ በኋላ እንደምንመለከተው ይህ ደፋር አባባል ይህንን አብዱል የማይወጣበት ጸጸት ውስጥ ይከተዋል፤ የእርሱን ሐሰተኛ ነቢይ ሙሐመድን የምንመታበትን ጥሩ ብትር አቀብሎናልና! ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን አገላለጽ ከኢሳይያስ 64:4 እንደወሰደ ብዙዎች ይስማማሉ፤ ነገር ግን ይህ አባባል በኢሳይያስም ሆነ በሌላ ከቅዱስ ጳውሎስ በሚቀድም በማንኛውም ምንጭ ውስጥ በዚህ ሁኔታ ተጽፎ አይገኝም። ተመሳሳይ አባባል የተዘገበበት “ራዕየ ኤልያስ” የተሰኘ መጽሐፍ ያለ ሲሆን ኦሪጎን ሐዋርያው ጳውሎስ አባባሉን ከመጽሐፉ እንደወሰደ ተናግሯል። ነገር ግን ጀሮም ይህንን ሐሳብ ይቃወማል። በሊቃውንት መሠረት መጽሐፉ ከሁለተኛው ክፍለ ዘመን በኋላ በተለይም ከሦስተኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ በኋላ የተጻፈ ሲሆን ቀዳሚ የእጅ ጽሑፍ የሚባለው በአራተኛው ክፍለ ዘመን የተዘጋጀ ነው (O. S. Wintermute. (1983). Apocalypse of Elijah. In James Charlesworth. The Old Testament Pseudepigrapha Volume 1, pp. 729-730)። የተጠቀሰውም አባባል አሁን በሚገኘው በየትኛውም የመጽሐፉ ቅጂ ውስጥ አልተገኘም። መጽሐፉ ድህረ ክርስትና የተጻፈ መሆኑ ስለተረጋገጠ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ከዚህ ምንጭ ሊቀዳ እንደማይችል ግልጽ ነው። ይህንንም የሚቀበል ምሑር የለም።

አውዱን ስንመለከት ሐዋርያው የአማኞችን የወደፊት ተስፋ ብቻ ሳይሆን አሁን ስላሉበት ሁኔታም ጭምር የሚገልጽ ነው፤ ምክንያቱም በክርስቶስ ያሉቱ ቅዱሱን መንፈስ ስለተቀበሉ መንፈሳዊ ምስጢር ተገልጦላቸዋልና፦

“በበሰሉት መካከል ግን ጥበብን እንናገራለን፥ ነገር ግን የዚችን ዓለም ጥበብ አይደለም የሚሻሩትንም የዚችን ዓለም ገዦች ጥበብ አይደለም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር አስቀድሞ ከዘመናት በፊት ለክብራችን የወሰነውን፥ ተሰውሮም የነበረውን የእግዚአብሔርን ጥበብ በምሥጢር እንናገራለን። ከዚችም ዓለም ገዦች አንዱ እንኳ ይህን ጥበብ አላወቀም፤ አውቀውስ ቢሆኑ የክብርን ጌታ ባልሰቀሉትም ነበር፤ ነገር ግን፦ ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው ተብሎ እንደተጻፈ፥ እንዲህ እንናገራለን። መንፈስም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ስንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራልና ለእኛ እግዚአብሔር በመንፈሱ በኩል ገለጠው። በእርሱ ውስጥ ካለው ከሰው መንፈስ በቀር ለሰው ያለውን የሚያውቅ ሰው ማን ነው? እንዲሁም ደግሞ ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር ለእግዚአብሔር ያለውን ማንም አያውቅም። እኛ ግን ከእግዚአብሔር እንዲያው የተሰጠንን እናውቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም” (1ቆሮ. 2:6-12)።

ከአውዱ እንደምንረዳው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ ለአማኞች የተገለጠ መገለጥ እንደሆነ የሚናገረው ክርስቶስን ማወቅ ነው። እግዚአብሔር ማንነቱን፣ ፍቅሩንና ክብሩን በአንድያ ልጁ በኩል ስለገለጠ ክርስቶስን ያወቁቱ ዓለም ያላገኘችውን ይህንን ታላቅ መገለጥ አግኝተዋል። በዚህ መሠረት ሐዋርያው እየተናገረ ያለው ነቢዩ ኢሳይያስ የተናገረውን ነው፤ ማለትም እውነተኛውን አምላክ በማወቅ የሚገኘውን ትሩፋት ስለመቋደስ ነው። ይህ ዕውቀት አሁናዊና መጻዒ ገጽታዎች አሉት። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የኢሳይያስን አባባል መሠረት በማድረግ ቅዱሳት መጻሕፍት አማኞች ስላላቸው ተስፋ የተናገሩትን ሐሳብ ጠቅልሎ እንዳስቀመጠ መደምደም እንችላለን። ሐዋርያው በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ ባለ ሥልጣን በመሆኑ ሳብያ የእግዚአብሔር መንፈስ በገለጠለት መጠንና ሁኔታ መጻፍ ይችላል። ይህ ጳውሎስ በእግዚአብሔር የተሾመ እውነተኛ መልእክተኛ በመሆን አለመሆኑ ላይ የሚመሠረት እንጂ ከዚህች አንድ ነጥብ ብቻ በመነሳት የሚወሰን አይደለም።

ይህ አብዱል በዚህ ቦታ በድፍረት እንደ ጻፈው ሐዋርያው ጳውሎስ እውን ከተሳሳተ የእስልምና ጀማሪ የሆነው ሙሐመድ ቅዱስ ጳውሎስ የጻፈውን ይህንኑ ቃል ከጠቀሰ በኋላ የአላህ ቃል መሆኑን  በመመስከር የተናገረውን ምን ሊያደርገው ነው?

حَدَّثَنَا مُعَاذُ بْنُ أَسَدٍ، أَخْبَرَنَا عَبْدُ اللَّهِ، أَخْبَرَنَا مَعْمَرٌ، عَنْ هَمَّامِ بْنِ مُنَبِّهٍ، عَنْ أَبِي هُرَيْرَةَ ـ رضى الله عنه ـ عَنِ النَّبِيِّ صلى الله عليه وسلم قَالَ ‏ “‏ قَالَ اللَّهُ أَعْدَدْتُ لِعِبَادِي الصَّالِحِينَ مَا لاَ عَيْنٌ رَأَتْ، وَلاَ أُذُنٌ سَمِعَتْ، وَلاَ خَطَرَ عَلَى قَلْبِ بَشَرٍ ‏”‏‏.‏

Narrated Abu Huraira:

the Prophet (ﷺ) said, “Allah said, “I have prepared for My righteous slaves (such excellent things) as no eye has ever seen, nor an ear has ever heard nor a human heart can ever think of.’ “

“አቡ ሁረይራ እንዳስተላለፈው ነቢዩ እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹አላህ እንዲህ አለ ‹እኔ ለታማኝ ባርያዎቼ ዓይን ያላየችውን፣ ጆሮ ያልሰማውን የሰው ልብ ሊያስበው የማይችለውን (አስደናቂ ነገሮች)› አዘጋጅቻለሁ፡፡››” (Sahih Al-Bukhari, Vol. 9, Book 93, Number 589)

እስኪ ይህንን በሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ መልእክት ውስጥ ከተጻፈው ጋር እናነጻጽር፡-

“ነገር ግን፦ ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው ተብሎ እንደተጻፈ፥ እንዲህ እንናገራለን” (1ቆሮንቶስ 2፡9)፡፡

ቀደም ሲል እንዳልነው ይህ አባባል ሐዋርያው ጳውሎስ የኢሳይያስን አገላለጽ መሠረት አድርጎ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የተጠቀሱትን የእግዚአብሔርን ተስፋዎች በራሱ አባባል ጨምቆ ያስቀመጠበት ዓረፍተ-ነገር ሲሆን ከእርሱ በሚቀድም በየትኛውም ምንጭ ውስጥ በዚህ መልኩ ተጽፎ አይገኝም፡፡ ይህንኑ ቃል ሙሐመድ “አላህ እዲህ አለ…” በማለት ከአላህ የሰማው መገለጥ በማስመሰል አቅርቦታል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስን እንዲህ በከረሩ ቃላት ለመዝለፍ የደፈረው ይህ አብዱል የገዛ ነቢዩ ይህንን አባባል ኮርጆ አምላኩ የተናገረው በማስመሰል ማቅረቡን ሲሰማ ምን ይል ይሆን? ጳውሎስ ከተሳሳተና ኮራጅ ከተባለ ሙሐመድ ደግሞ ይህንኑ “ስህተት” ከጳውሎስ ኮርጆ ማቅረቡ ሐሰተኛ ነቢይ አያስብለውምን? ሙሐመድ በዚህ ጉዳይ ላይ ትክክል ነው ከተባለ ለሙሐመድ የኩረጃ ምንጭ የሆነው ጳውሎስም ትክክል ነው ማለት ነው። ዳሩ ግን ሙሐመድ ከጳውሎስ የኮረጀውን አላህ የተናገረው በማስመሰል ማቅረቡ ሐሰተኛ ነቢይ መሆኑን በገሃድ የሚያሳይ አጋጣሚ ነው። ከእርሱ ከሚቀድም ከሌላ ምንጭ ቃል በቃል ያመጣውን ተናገረ እንጂ ከአምላክ ሰምቶ አይደለምና። ሙሐመድ ሐሰተኛ ነቢይ መሆኑን እንዲህ እንድናጋልጥ እድል ስለፈጠረልን ይህንን አብዱል ልናመሰግነው እንወዳለን። ቅሌት የማይሰለቸው ሙስሊሙ ሰባኪ አሁንም እንዲህ በማለት ዲስኩሩን ይቀጥላል፦

ጳውሎስ ከኢሳይያስ ጠቅሶ እንዲህ ይሳሳታል፦

ሮሜ 1126 እንደዚሁም እስራኤል ሁሉ ይድናል፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፦መድኃኒት ከጽዮን ይወጣል፥ ከያዕቆብም ኃጢአተኛነትን ያስወግዳል።

ኢሳይያስ 5920 ለጽዮን ታዳጊ ይመጣል፥ በያዕቆብም ዘንድ ከኃጢአት ለሚርቁ፥ ይላል ያህዌህ። וּבָ֤א לְצִיֹּון֙ גֹּואֵ֔ל וּלְשָׁבֵ֥י פֶ֖שַׁע בְּיַֽעֲקֹ֑ב נְאֻ֖ם יְהוָֽה

ለጽዮን ታዳጊ ይመጣልማለት እናመድኃኒት ከጽዮን ይወጣልማለት ሁለት የተለያየ ቃላት ነው፥በያዕቆብም ዘንድ ከኃጢአት ለሚርቁማለት እናከያዕቆብም ኃጢአተኛነትን ያስወግዳልማለት ሁለት የተለያየ ቃላት ነው። መንፈስ ቅዱስ ይህ ጠፍቶት ነው? ጳውሎስ የኮረጀው ከዕብራይስጡ ሳይሆን ከግሪክ ሰፕቱጀንት ነው፦

καὶ ἥξει ἕνεκεν Σιὼν ῥυόμενος καὶ ἀποστρέψει ἀσεβείας ἀπὸ ᾿Ιακώβ.

ግሪክ ሰፕቱጀንት የዕብራይስጥ ቅጂ ሳይሆን ከዕብራይስጥ ወደ ግሪክ የትርጉም ሥራ ነው፥ ጳውሎስ ከትርጉም ሥራ ላይ እየኮረጀየአምላክ መገለጥ ነውብሎ መቅጠፉ ጥሩ አይደለም። ጳውሎስ እንዲህ ዓይነት የኩረጃ ስህተቶችን የተሳሳተባቸው በቁና ማቅረብ ይቻል ነበር፥ ቅሉ እና ጥቅሉ ግን አንባቢያንን ማሰልቸት ነው።

ይህ አብዱል የሚያውቃቸውን ክሶች ሁሉ እጅ እጅ በሚል አጻጻፉ ካቀረበ በኋላ ሌሎች ብዙ እንዳሉ ማስመሰሉ ንግግር ከማሳበጥ የዘለለ ፋይዳ የለውም። ይህ ጸሐፊ በመጀመርያ ደረጃ “ኩረጃ” እና “ጥቅስ” ልዩነቱ ምን እንደሆነ ማወቅ ያስፈልገዋል። አንድ ሰው ሐሳቡን ለማጠናከር ማስረጃ ከሌላ ጽሑፍ ቢጠቅስ ኮረጀ አይባልም። ኩረጃ ማለት አንድ ሰው ልክ ሙሐመድ ሲያደርገው እንደነበረው ከእርሱ በፊት የሚታወቁ ሐሳቦችን የራሱ በማስመሰልና ከምንጮቹ ያላገኛቸው ነገር ግን ከሰማይ የተገለጠለት መገለጥ በማስመሰል ሲያቀርብ እንጂ ከሌላ ምንጭ መጥቀስ ማለት አይደለም። የኩረጃና የጥቅስ ልዩነት የማያውቅ ሰው ገና ብዙ ይቀረዋል።

በሁለተኛ ደረጃ የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ አጠቃቀስና የሰፕቱጀንት ጥቅስ ልዩነት ያሳያል። የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት እንደሚናገሩት የዚህ ምክንያቱ ሐዋርያው የተለያዩ ጥቅሶችን አንድ ላይ በማቀናጀት መጥቀሱ ነው። ጥቅሱን እናንብበው፦

“እንደዚሁም እስራኤል ሁሉ ይድናል፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፦ መድኃኒት ከጽዮን ይወጣል ከያዕቆብም ኃጢአተኛነትን ያስወግዳል። ኃጢአታቸውንም ስወስድላቸው ከእነርሱ ጋር የምገባው ኪዳን ይህ ነው” (ሮሜ 11:26)።

በማቲው ፑል ሐተታ መሠረት እነዚህ ዓረፍተ ነገሮች የሦስት ጥቅሶች ውጤቶች ናቸው Romans 11 Matthew Poole’s Commentary የመጀመርያው ክፍል ከኢሳይያስ 59:20 ላይ የተወሰደ ነው። ይህ ክፍል መሲሃዊ ትንቢት መሆኑን የጥንት አይሁድ ያምኑ ስለነበር (አ.መ.ት ማጥኛ ገጽ 1725 ይመልከቱ) ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ጥቅስ ለመጥቀስ የመጀመርያው አይደለም። ክፍሉ እንዲህ ይላል፦

“ለጽዮን ታዳጊ ይመጣል፥ በያዕቆብም ዘንድ ከኃጢአት ለሚርቁ፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡” (ኢሳ. 59:20)

ሁለተኛው ክፍል ደግሞ ከተከታዩ ጥቅስ የተቀነጨበ ነው፦

“ስለዚህም የማምለኪያ ዐፀዶችና የፀሐይ ምስሎች ዳግመኛ እንዳይነሡ የመሠዊያውን ድንጋይ ሁሉ እንደ ደቀቀ እንደ ኖራ ድንጋይ ባደረገ ጊዜ፥ እንዲሁ የያዕቆብ በደል ይሰረያል፥ ይህም ኃጢአትን የማስወገድ ፍሬ ሁሉ ነው።” (ኢሳ. 27:9)

ሦስተኛው ክፍል ከተከታዩ ክፍል የተወሰደ ነው፦

“ከእነዚያ ወራት በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነውና፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፥ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል” (ኤር. 31:33)።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በተለያዩ ክፍሎች ውስጥ የሚገኙትን ተመሳሳይ ሐሳብ ያላቸውን ጥቅሶች የሰብዓ ሊቃናቱን ትርጉም መሠረት በማድረግ አንድ ላይ አቀናጅቶ አቀረበ እንጂ ኢሳይያስ 59:20 ላይ የሚገኘውን ጥቅስ ብቻ ነጥሎ አልጠቀሰም። በመጀመርያው ክፍለ ዘመን የተለያዩ የብሉይ ኪዳን ጥቅሶችን አንድ ላይ አቀናጅቶ ውሱን የሆነ ነገረ መለኮታዊ አስተምህሮ ማስተላለፍ የተለመደ ነበር። ለአብነት ያህል ይህንን ጽሑፍ ያንብቡ። በሌላ ወገን ደግሞ የሐዋርያው አጠቃቀስ ጥቅሶቹ የሚያስተላልፉትን ሐሳብ መሠረት ያደረገ እንጂ ቃላትን መሠረት ያደረገ አይደለም። ኢሳይያስና ሌሎች ነቢያትን ያነሳሳቸው ያው አንዱ ቅዱስ መንፈስ ጳውሎስንም ካነሳሳው ሐሳቡን ሳይለውጥ አባባሉን ለተደራሲያኑ በሚገባ መንገድ እንዲያስቀምጥ ሊመራው የማይችልበት ምክንያት የለም። አሁንም ቀደም ሲል እንዳልነው ጉዳዩ የሚወሰነው በዚህች አንድ አጋጣሚ ሳይሆን ጳውሎስ እውነተኛ የጌታ ሐዋርያ በመሆን አለመሆኑ ላይ ነው። እውነተኛ የጌታ ሐዋርያ ከሆነ ቅዱሳት መጻሕፍትን መንፈስ ቅዱስ በወደደው መንገድ ቢጠቅስ ትክክል ነው።

በማስከተል አብዱል እንዲህ ይላል፦

የመጽሐፉ ሰዎች ሆይ! ከአምላክ የመጣውን እውነት ከኩረጃ ንግግር ጋር ለምን ትቀላቅላላችሁ? ይህ ሥራ ዋጋ ያስከፍላል።

በዙርያው ከነበሩ የተለያዩ ማሕበረሰቦች ታሪኮችንና ሐሳቦችን እየለቃቀመ ከሰማይ ተገለጠልኝ ሲል የነበረውን ሙሐመድን የሚከተል ሰው እንዲህ ያለ ንግግር የመናገር ሞራሉ ሊኖረው አይችልም። ይህንን አብዱል አንድ የምንጠይቀው ጥያቄ ቢኖር ሙሐመድ የትኛውን የቅዱሳት መጻሕፍት ጥቅሶች አስተካክሎ ጠቅሶ እንደሚያውቅ እንዲያሳየን ነው። ሙሐመድ በቀጥታ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጠቀሰ የሚባለው ሦስት ጊዜ ሲሆን ሦስቱንም አሳስቶ ነው የጠቀሰው። እስኪ እንመልከታቸው፦

“በእነርሱም ላይ በውስጧ «ነፍስ በነፍስ ዓይንም በዓይን አፍንጫም በአፍንጫ ጆሮም በጆሮ ጥርስም በጥርስ (ይያዛል)።» ቁስሎችንም ማመሳሰል አለባቸው ማለትን ጻፍን። በእርሱም የመጸወተ (የማረ) ሰው እርሱ ለርሱ (ለሠራው ኃጢአት) ማስተሰሪያ ነው። አላህም ባወረደው ነገር የማይፈርድ ሰው፤ እነዚያ በደለኞቹ እነርሱ ናቸው” (ሱራ 5:45)።

የቁርአን ደራሲ የጠቀሰው ከተከታዮቹ ክፍል ነው፦

“ዓይን በዓይን፥ ጥርስ በጥርስ፥ እጅ በእጅ” (ዘጸ. 21:24)።

“ስብራት በስብራት ፋንታ፥ ዓይን በዓይን ፋንታ፥ ጥርስ በጥርስ ፋንታ፥ ሰውን እንደ ጐዳ እንዲሁ ይደረግበት” (ዘሌ. 24:20)።

የቁርአን ደራሲ “አፍንጫም በአፍንጫ ጆሮም በጆሮ” የሚል የቱ ጋር አንብቦ ይሆን ይህ እንደተጻፈ የነገረን?

ሌላ ጥቅስ እንመልከት፦

“ምድርንም መልካሞቹ ባሮቼ ይወርሷታል ማለትን ከመጽሐፉ (ከተጠበቀው ሰሌዳ) በኋላ በመጽሐፎቹ በእርግጥ ጽፈናል” (ሱራ 21:105)።

በሙስሊም ምሑራን መሠረት ይህ ጥቅስ የተወሰደው ከመዝሙረ ዳዊት መጽሐፍ ላይ ነው። ኢብን አባስ፣ ጃለላይንና ኢብን ከሢርን የመሳሰሉት ተፍሲራት ይህንኑ ይላሉ https://quranx.com/tafsirs/21.105

ነገር ግን በመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው ጥቅስ ይህንን አይልም፦

“ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፥ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ” (መዝሙር 37:29)።

በግልጽ እንደሚነበበው “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ” ይላል እንጂ “መልካሞቹ ባሮቼ” አይልም። ሌላኛው ጥቅስ የሚከተለው ነው፦

“… ምልክታቸው ከስግደታቸው ፈለግ ስትኾን በፊቶቻቸው ላይ ናት፡፡ ይህ በተውራት (የተነገረው) ጠባያቸው ነው፡፡ በኢንጂልም ውስጥ ምሳሌያቸው ቀንዘሉን አንደአወጣ አዝመራና፣ (ቀንዘሉ) እንዳበረታው፣ እንደወፈረምና፣ ገበሬዎቹን የሚያስደንቅ ኾኖ በአገዳዎቹ ላይ ተስተካክሎ እንደ ቆመ (አዝመራ) ነው…”

ሰይድ አቡል ዓላ ማውዱዲ የተሰኙ ሙስሊም ሐታች ይህ አባባል ከተከታዮቹ የአዲስ ኪዳን ክፍሎች እንደተወሰደ ይነግሩና፦

“ሌላ ምሳሌ አቀረበላቸው እንዲህም አለ፦ መንግሥተ ሰማያት ሰው ወስዶ በእርሻው የዘራትን የሰናፍጭ ቅንጣት ትመስላለች፤ እርስዋም ከዘር ሁሉ ታንሳለች፥ በአደገች ጊዜ ግን፥ ከአታክልቶች ትበልጣለች የሰማይም ወፎች መጥተው በቅርንጫፎችዋ እስኪሰፍሩ ድረስ ዛፍ ትሆናለች” (ማቴ. 13:31-32)

“እርሱም አለ፦ በምድር ዘርን እንደሚዘራ ሰው የእግዚአብሔር መንግሥት እንደዚህ ናት ሌሊትና ቀን ይተኛልም ይነሣልም፥ እርሱም እንዴት እንደሚሆን ሳያውቅ ዘሩ ይበቅላል ያድግማል። ምድሪቱም አውቃ በመጀመሪያ ቡቃያ ኋላም ዛላ ኋላም በዛላው ፍጹም ሰብል ታፈራለች። ፍሬ ግን ሲበስል መከር ደርሶአልና ወዲያው ማጭድ ይልካል” (ማር. 4:26-29)።

እነዚህ ጥቅሶች በሐሳብም ሆነ በአገላለጽ ፈጽሞ ከቁርአን ጋር አይስማሙም። የቁርአን ደራሲ ሲጠቅስ አሳስቷል ስለዚህ ይህ አብዱል ባስቀመጠው መስፈርት መሠረት ሙሐመድ እውነተኛ ነቢይ ሊሆን አይችልም።



ሌላ አንድ ጀማሪ ሙስሊም ጸሐፊ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስን እንዲህ በማለት ይከሰዋል፦

ወንጌላውያን ከግሪኮሮማዊያን አፈታሪኮች የተለያዩ ንግግሮችና አባባሎችን በመገልበጥ የአምላክ መገለጥ ብለው ይጽፉት ነበር። እስኪ ከቀደምት ሮማውያን ፈላስፋዎችና ጸሐፊዎች ተኮርጀው በባይብል የተቀመጡትን አባባሎች እንመልከት:-

ይህኛው አብዱል ደግሞ ከዚያኛው የባሰ አላዋቂ በመሆኑ በቅዱስ ጳውሎስ ጽሑፎችና በወንጌላት ጸሐፊያን መካከል ያለውን ልዩንት እንኳ አያውቅም። ከጠቀሳቸው ነጥቦች መካከል አንዱንም ከወንጌላውያን ያልጠቀሰ ሲሆን ሁሉም አባባሎች በቅዱስ ጳውሎስ የተነገሩ ናቸው። ይህንን መሠረታዊ እውነት የማያውቅ ሰው እንዲህ ላለ ትችት መንጠራራቱ አስቂኝ ነው። በማስከተል እንዲህ ይለናል፦

1- አፒሜንዲስ (Epimenides 600 BC)

የምንኖረውና የምንንቀሳቀሰው፣ ያለነውም በእርሱ ነውና for in thee we live and move and have our being¹

Copied Bible verse

በእርሱ ሕያዋን ነንና እንንቀሳቀሳለን እንኖርማለን።

  — ሐዋርያት 1728

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን የተናገረው በአቴና ከተማ በአርዮስፋጎስ አደባባይ ሲሆን ለግሪካውያን ፈላስፎች ነበር። ሐዋርያው ኤፒሜኔዴስ የተሰኘውን በግሪኮች ዘንድ የታወቀ የቀርጤስ ባለ ቅኔ አባባል እየጠቀሰ እንጂ የሌላውን ሐሳብ የራሱ አስመስሎ እያቀረበ አይደለም። እየተናገረ የነበረው በባለጉዳዮቹ ፊት ሆኖ ሳለ ይህንን የማድረግ ዕድልም ሊኖረው አይችልም። አድማጮቹ የሚያውቁትን የታወቀ ንግግር ለመግባባት ሲል መጥቀሱ ኮፒ አደረገ አያሰኘውም። በዚህ ጉዳይ ሐዋርያው ጳውሎስን በግልበጣ የከሰሰ አንድም ሊቅ የለም፤ የንግግሩን አውድ ያልተገነዘቡ እንደዚህ ሙስሊም ጸሐፊ ያሉ አላዋቂዎች ካልሆኑ በስተቀር። ሐዋርያው በንግግሩ አባባሉ ከየት እንደመጣ ገልጿል፦ ከእናንተ ከባለ ቅኔዎች አንዳንዶች ደግሞ፦ እኛ ደግሞ ዘመዶቹ ነንና ብለው እንደ ተናገሩ፥ በእርሱ ሕያዋን ነንና እንንቀሳቀሳለን እንኖርማለን” (ሐዋ. 17:28)። ሐዋርያው ራሱ የሌላውን አባባል እየጠቀሰ እንዳለ ግልጽ አድርጎ ሳለ ኮፒ አድርጓል የሚል ክስ ማንሳት ለትዝብት የሚዳርግ ነው። አብዱል ይቀጥላል፦

2- ፐብሊዮስ ቴራንትዮስ 159 BC

ማንም ባልቴት ግን ልጆች ወይም የልጅ ልጆች ቢኖሯት፥ እነርሱ አስቀድመው በቤታቸው ቅድስናን (እግዚአብሔርን መምሰል) ይማሩ But if any widow have children or nephews, let them learn first to show piety at home²

Copied Bible verse

ማንም ባልቴት ግን ልጆች ወይም የልጅ ልጆች ቢኖሩአት፥ እነርሱ አስቀድመው ለገዛ ቤተ ሰዎቻቸው እግዚአብሔርን መምሰል ያሳዩ ዘንድ፥ ለወላጆቻቸውም ብድራትን ይመልሱላቸው ዘንድ ይማሩ፤ ይህ በእግዚአብሔር ፊት መልካምና የተወደደ ነውና።

  — 1 ጢሞቴዎስ 54

“But if any widow have children or nephews, let them learn first to shew piety at home,

  — 1 Timothy 5:4 (KJV)

ይህ አብዱል ያቀረበውን ክስ የሚያረጋግጥ ምንም ዓይነት ማስረጃ ከተዓማኒ ምንጮች ማግኘት አይቻልም። አንድ ሁለት የሙስሊም ብሎጎች ላይ ስለተጻፈ ብቻ ገልብጦ አመጣ እንጂ በግሉ ምንም ዓይነት የማጣራት ሥራ እንዳልሠራ ግልጽ ነው። ሙስሊሞች መጽሐፍ ቅዱስን ለመተቸት የሚያቀርቧቸው ክሶቹ አብዛኞቹ እንዲህ ያሉ ማስረጃ የሌላቸው ገለባ ክሶች ናቸው። የግልበጣ ክስ የሚቀርበው ደግሞ እንዲህ ባሉ በአጋጣሚ ሊመሳሰሉ በሚችሉ የተለመዱ ንግግሮች ዙርያ አይደለም። ምን ዓይነት ይዘቶች ከግልበጣ ሊቆጠሩ እንደሚችሉ ማወቅ ቀዳሚ ጉዳይ ነው። የሆነው ሆኖ ይህ አብዱል ስለ ጉዳዩ የሚያወራ ተዓማኒ ማስረጃ አላቀረበም። ትርጉሙ ምን እንደሆን የማያውቀውን ከአንድ ብሎግ ያገኘውን ምንጭ ዝም ብሎ ጠቀሰ እንጂ ምን እንደሚል አንብቦና ተረድቶ አይደለም። አብዱል እንደተለመደው እየቀጠፈ ነው።

3- አራቱስ (Aratus 240 BC)

እኛም ደግሞ ልጆቹ ነን (for we are indeed his offspring³

Copied Bible verse

 ‘እኛም ደግሞ ልጆቹ ነን/for we are also his offspring.

  — ሐዋርያት 1728 (አዲሱ .)

ይህ አባባል ከቅዱስ ጳውሎስ ቀደም ብሎ በኪልቅያው ባለቅኔ አራጠስ (315-240 ዓ.ዓ) እና በቅሊንጦስ (331-233 ዓ.ዓ) የተነገረ ሲሆን ሐዋርያው ስለ ጉዳዩ በሚያውቁት ግሪካውያን ፈላስፎች ፊት የተናገረው ነው። ሲናገርም እንደ ሙሐመድ “አሁን ከሰማይ ተገለጠልኝ” በሚል ውሸት ሳይሆን መልእክቱ ለአድማጮቹ በሚገባ መንገድ የገዛ ምንጮቻቸውን እየጠቀሰ ነበር። ከእናንተ ከባለ ቅኔዎች አንዳንዶች ደግሞ፦ እኛ ደግሞ ዘመዶቹ ነንና ብለው እንደ ተናገሩ…” ብሎ ምንጩን በተናገረበት ሁኔታ ጥቅሱን ቆርጦ በመጥቀስ የኩረጃ ክስ ማቅረብ ጸሐፊው የማስተዋል ችግር እንዳለበት ግልጽ ያደርጋል።

እስካሁን እንደ ተመለከትነው ሙስሊም ሰባኪያኑ ለኩረጃ ክስ የሚበቃ ምንም ዓይነት ማስረጃ አላቀረቡም። ኩርጃ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ለማወቅ ተከታዮቹን ጽሑፎች እንዲያነቡ እንጋብዛቸዋለን።

ተጨማሪ ንባቦች


ለእስልምና ሙግቶች ምላሽ