የጳውሎስ ወይስ የሙሐመድ ኩረጃ? – የሙስሊም ሰባኪያን ቅጥፈት ሲጋለጥ – ዙር ሁለት

የጳውሎስ ወይስ የሙሐመድ ኩረጃ? 

የሙስሊም ሰባኪያን ቅጥፈት ሲጋለጥ

ዙር ሁለት


ከዚህ ቀደም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስን በኩረጃ የሚከሱ ሁለት ጽሑፎችን የተመለከተ ምላሽ በዌብሳይታችን ላይ ማስነበባችን ይታወሳል። መልስ ከተሰጣቸው ሙስሊሞች መካከል አንዱ ውሎ ሳያድር በከፍተኛ የብስጭትና የቁጣ ስሜት አጸፋዊ ምላሽ ለመስጠት ሞክሯል። ከአጻጻፉ እንዳስተዋልነው ሙስሊሙ ወገን ጠንካራ ነው ብሎ ያሰበው ሙግቱ መፈረካከሱ ያስከፋው ይመስላል። በዚህም ምክንያት “እስላማዊ ስነ ምግባሩን” በሚያሳብቅ ሁኔታ የስድብ ናዳ ሲያዘንብ ታዝበናል። ይህ አብዱል ለኛ ምላሽ ለመስጠት ከሚሞክር ስህተቱን አምኖ ቢቀበልና የተወጋውን የእውነት መርፌ ቢያጣጥም ይሻለው ነበር። ነገር ግን በአመክንዮአዊ ህፀፆችና በተሳከረ መረጃ የተሞላ ሌላ ጽሑፍ በማዘጋጀት እንደገና ስህተት ሠርቶ እጃችን ላይ ወድቋል። አብዱል እንዲህ ሲል ይጀምራል፦

ጳውሎስ ሲኮርጅ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ቢሆን ኖሮ በትክክል ማስቀመጥ ያቅተዋልን? ይህንን ስል አንዱ ወጠጤ አሳብን ከመሞገት ይልቅ እንደ ወጠጤ የሰው ስብዕና ላይ እንጠጥ እንጠጥ በማለት እንደ ውርጋጥ መራገጥ በለመደበት አፉ ጳውሎስ “ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው” የሚለው ከየት እንዳገኘው ለመመለስ ቢሞክርም ምንም ምንጭ ሳያስቀምጥ ጭራሽ መልስ ላይሆነው ነገር ስለ ራዕየ ኤልያስ ሲዳክር እና ሲነፍር ታይቷል።

በዚህ የተወናገረ አረፍተ ነገር ውስጥ የተሰገሰጉት አይረቤ ቃላት ከኛ ይልቅ የሙስሊሙን ማንነትና ባሕርይ የሚገልጹ ናቸው። እኛ ሙስሊሙ ጸሐፊ ካዘጋጀው ጽሑፍ በመነሳት ባደረግነው ግምገማ ክርስትናን ለመተቸትም ሆነ እስልምናን ለማስተማር ብቃት የሌለው አላዋቂ መሆኑን መናገራችን ሃቅ ነው። ስብዕናው እንደተነካ ስሞታ ያቀረበው ይህ ሰው በዚህ መንገድ ሊገለጽ የማይገባው በጨዋነት የተገነባ ስብዕና ቢኖረው ኖሮ የኛ ምላሽ ምንም ያህል ቢያስከፋው እነዚህን ሁሉ “ጠ”ዎች በማባከን እንዲህ የስድብ ናዳ ባላወረደ ነበር። ይህ ምላሹ ምን ያህል የዘቀጠ ስነ ምግባር እንዳለው በማሳየት በአንባቢያን ፊት ትዝብት ላይ እንዲወድቅ ከማድረጉም በተጨማሪ የስነ ጽሑፍ ክህሎቱ ደካማ መሆኑን ያሳያል። እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ አጻጻፍ የማሰብያ ሚዛኑ በተናጋ ወይም በዕድሜ ጨቅላ በሆነ ህፃን የተዘጋጀ እንጂ ራሱን “ዐቃቤ እምነት” ብሎ በሰየመ ሰው የተጻፈ አይመስልም። ከስድቡ በመለስ አብዱል እንዲህ ሲል “ምላሹን” ያቀርባል፦

ጳውሎስ “ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው” ብሎ ዐውዱ ላይ የሚናገረው ስለ ክርስቶስ እንጂ ስለ ጀነት በፍጹም አይደለም፦

1ቆሮንቶስ 2፥7 ነገር ግን እግዚአብሔር አስቀድሞ ከዘመናት በፊት ለክብራችን የወሰነውን፥ ተሰውሮም የነበረውን የእግዚአብሔርን ጥበብ በምሥጢር እንናገራለን።

ተሰውሮም የነበረውን የእግዚአብሔርን ጥበብ እና ከዚችም ዓለም ገዦች አንዱ እንኳ ይህን ጥበብ ያላወቁት ክርስቶስ ሲሆን ክርስቶስ የተዘጋጀ ሰው ነው፦

ሉቃስ 2፥30 ዓይኖቼ በሰዎች ሁሉ ፊት “ያዘጋጀኸውን” ማዳንህን አይተዋልና።

የሐዋርያት ሥራ 17፥31 ቀን ቀጥሮአልና፥ በዚያም ቀን “ባዘጋጀው ሰው” እጅ በዓለሙ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው።

በቀደመው ምላሻችን እንዲህ ማለታችን ይታወሳል፦ “ከአውዱ እንደምንረዳው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ ለአማኞች የተገለጠ መገለጥ እንደሆነ የሚናገረው ክርስቶስን ማወቅ ነው። እግዚአብሔር ማንነቱን፣ ፍቅሩንና ክብሩን በአንድያ ልጁ በኩል ስለገለጠ ክርስቶስን ያወቁቱ ዓለም ያላገኘችውን ይህንን ታላቅ መገለጥ አግኝተዋል። በዚህ መሠረት ሐዋርያው እየተናገረ ያለው ነቢዩ ኢሳይያስ የተናገረውን ነው፤ ማለትም እውነተኛውን አምላክ በማወቅ የሚገኘውን ትሩፋት ስለመቋደስ ነው።” ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በዚህ ቦታ ላይ ክርስቶስ ራሱ የተዘጋጀ ነው የሚል ንግግር እየተናገረ አይደለም ነገር ግን በክርስቶስ በኩል ለሰው ልጆች የተገለጠውን የማዳን ምስጢር ታላቅነት እየተናገረ ነው፤ ይህም የእግዚአብሔር የተስፋ ቃሎች ሁሉ ማጠቃለያ ነው። አውዱን እናንብብ፦

“በበሰሉት መካከል ግን ጥበብን እንናገራለን፥ ነገር ግን የዚችን ዓለም ጥበብ አይደለም የሚሻሩትንም የዚችን ዓለም ገዦች ጥበብ አይደለም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር አስቀድሞ ከዘመናት በፊት ለክብራችን የወሰነውን፥ ተሰውሮም የነበረውን የእግዚአብሔርን ጥበብ በምሥጢር እንናገራለን። ከዚችም ዓለም ገዦች አንዱ እንኳ ይህን ጥበብ አላወቀም፤ አውቀውስ ቢሆኑ የክብርን ጌታ ባልሰቀሉትም ነበር፤ ነገር ግን፦ ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው ተብሎ እንደተጻፈ፥ እንዲህ እንናገራለን። መንፈስም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ስንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራልና ለእኛ እግዚአብሔር በመንፈሱ በኩል ገለጠው” (1ቆሮ. 2:6-10)።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እየተናገረ ያለው ስለ ክርስቶስ የሰበከውን ስብከት ነው፤ ይህም ስብከት ክርስቶስን በማወቅ በመስቀሉ በኩል ያገኘነው መዳን ነው። “ተዘጋጀልን” የተባለው ይህ እንጂ የክርስቶስ ማንነት የተዘጋጀ ነው የሚል ትርጉም የለውም።

አብዱል በሌሎች ጊዜያት ግሪክ የሚችል ለማስመሰል እንደሚሞክረው ሁሉ በዚህ ቦታ የጠቀሳቸውን ጥቅሶ በአዲስ ኪዳን ግሪክ ቢመለከት ኖሮ ለዚህ ስህተት ባልተዳረገ ነበር። በ1ቆሮንቶስ 2:9 ላይ የተጠቀሰው የግሪክ ቃል ἡτοίμασεν “ሄቶይማሴን” የሚል ሲሆን “ሄቶይሞስ” የሚለው እግዚአብሔር አምላክ ለአማኞች ያዘጋጀውን የወዲያኛውን ዓለም መልካም ነገሮች ለማመልከት በተለያየ አገባብ ጥቅም ላይ ውሏል፦ (ማቴ. 22:4፣ 25:34፣ ማር. 10:40፣ ዮሐ. 14:2፣ 14:3፣ ዕብ. 11:16)። አረጋዊው ስምዖን ሉቃስ 2፡30 ላይ “ዓይኖቼ በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን ማዳንህን አይተዋልና” ብሎ ሲል ይኸው ቃል ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን ክርስቶስ በመምጣቱ ምክንያት በእርሱ በኩል የሚመጣው ተስፋ እውን መሆኑን ለማመልከት የተናገረው እንጂ የክርስቶስን ማንነት የተመለከተ ንግግር አይደለም፤ ንግግሩ ስለ አዳኝ (Savior) ሳይሆን የተዘጋጀውን ማዳን (Salvation) የተመለከተ ነው። ነገር ግን የሐዋርያት ሥራ 17፡31 ላይ “…ባዘጋጀው ሰው እጅ በዓለሙ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው” ብሎ ሲል የተጠቀመው ቃል ὥρισεν “ሆሪሴን” የሚል ነው። “ሆሪዮን” የሚለው ቃል ስለ አንድ ጉዳይ አስቀድሞ መወሰንን የሚያመለክት እንጂ ከመፍጠር ወይም የሌለውን ወደ መኖር ከማምጣት ጋር ተያይዞ አንድም ጊዜ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ጥቅም ላይ አልዋለም። ለናሙና ያህል ተከታዮቹን ጥቅሶች እንመልከት፦

“የሰው ልጅስ እንደ ተወሰነው (ሆሪስሜኖን) ይሄዳል፥ ነገር ግን አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት” (ሉቃስ 22:22)።

እርሱንም በእግዚአብሔር በተወሰነው (ሆሪስሜኔ) አሳቡና በቀደመው እውቀቱ ተሰጥቶ በዓመፀኞች እጅ ሰቅላችሁ ገደላችሁት (ሐዋ. 2፡23)

“ለሕዝብም እንድንሰብክና በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ በእግዚአብሔር የተወሰነ (ሆሪስሜኖስ) እርሱ እንደ ሆነ እንመሰክር ዘንድ አዘዘን” (ሐዋ. 10:42)።

ይህ ቃል በየትኛውም የአዲስ ኪዳን ክፍል ከመፍጠር ጋር ተያይዞ አልተጠቀሰም። በዚህ ክፍል“ማዘጋጀት” የሚለው ሐሳብ አስቀድሞ መወሰን የሚል እንጂ መፍጠር የሚል አይደለም። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ የተገለጠ መለኮት ነው። ሰብዓዊ ባሕርይ ቢኖረውም በማንነቱ መለኮት እንጂ ፍጡር አይደለም። ሰብዓዊ ባሕርይ ስላለው ሰው ተብሎ ተጠርቷል፤ ነገር ግን አንድ ዘላለማዊ ማንነት አለው፤ ይህም አንድ ማንነት የተፈጠረ አይደለም። በዚህ ቦታ የተጠቀሰው ቃል በ1ቆሮ. 2:9 ላይ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ከተጠቀመው ጋር አንድ አይደለም፤ ስለዚህ ስለ አንድ ጉዳይ የሚናገሩ አይደሉም። አብዱል ይቀጥላል፦

ይህ ሆኖ ሳለ በመቀጠል ነቢያችን ከ 1ቆሮንቶስ 2፥9 ላይ እንዶኮረጁ ለማስመሰል ሲቃጣው ይህንን ሐዲስ ይጠቅሳል፦

ኢማም ቡኻሪይ መጽሐፍ 65, ሐዲስ 302

አቢ ሁረይራህ”ረ.ዐ.” እንደተረከው፦ ነቢዩም  እንዲህ አሉ፦ “የላቀው አሏህም እንዲህ አለ፦ “እኔ ለደጋግ ባሮቼ ዓይን ዓይቶት የማያውቅ፣ ጆሮ ሰምቶት የማያውቅ እና በሰው ልብ ውልብ ብሎ የማያውቅ ጸጋን አዘጋጅቻለው”ከዚያም እርሳቸው፦ “ይሠሩትም በነበሩት ለመመንዳት ከዓይኖች መርጊያ ለእነርሱ የተደበቀላቸውን ጸጋ ማንኛይቱም ነፍስ ዐታውቅም” የሚለውን አንቀጽ አነበቡ”

ሲጀመር እዚህ ሐዲስ ላይ እንደ ጳውሎስ “ተብሎ እንድተጻፈ” የሚል የለም፣

፨ሲቀጥል ተወዳጁ ነቢያችን ሐዲሱ ላይ ያሉን፦ “ጳውሎስ አለ” ብለው ሳይሆን “አሏህ አለ” ብለው ነው፥ አሏህን ደግሞ የግልጠት ባለቤት ስለሆነ ከማንም ወሰደ አይባልም።

፨ሢሰልስ ሐዲሱ ላይ አሏህ፦ “እኔ ለደጋግ ባሮቼ ዓይን ዓይቶት የማያውቅ፣ ጆሮ ሰምቶት የማያውቅ እና በሰው ልብ ውልብ ብሎ የማያውቅ ጸጋን አዘጋጅቻለው” ያለው ስለ ጀነት ነው፦

32፥17 ይሠሩትም በነበሩት ለመመንዳት ከዓይኖች መርጊያ ለእነርሱ የተደበቀላቸውን ጸጋ ማንኛይቱም ነፍስ ዐታውቅም፡፡

ከላይ ያለው “ምላሽ” እንደ እውነቱ ከሆነ በእጅጉ አስቂኝ ነው። አንድ ሰው ከእርሱ በፊት የተነገረ ነገር ደግሞ ከተናገረ በኋላ “አምላክ ነው የተናገረኝ” ማለቱ ላለመኮረጁ እንዴት ዋስትና ይሆናል? እንዲህ ያለ ሰው የታወቀ የሌላ ሰው አባባል ቃል በቃል ከደገመ በኋላ ፈጣሪ እንደተናገረው በመናገሩ በፈጣሪ ስም የሚቀጥፍ ሐሰተኛ እንጂ እውነተኛ ሊባል አይችልም። ሙሐመድ “አላህ ተናገረኝ” ከማለት ይልቅ “ጳውሎስ እንደተናገረው” ብሎ ቢጀምር ወይም “ተብሎ እንደተጻፈው” ቢል ኖሮ የኩረጃ ክስ ባልቀረበበት ነበር፤ ምክንያቱም እየጠቀሰ እንጂ እየኮረጀ አይደለምና። ሙሐመድ ከእርሱ በፊት የተነገረ የታወቀን ንግግር “አላህ ተናገረኝ” ብሎ መናገሩን ይህ አብዱል ኩረጃ ላለመሆኑ እንደ ማስረጃ ካቀረበ በኋላ ከሌላ ምንጭ ጠቅሶ ቢናገር ግን ኩረጃ እንደሚሆን ይነግረናል። በምንኛ እያሰበ ይሆን? በቀደመው ጽሑፋችን እንደገለጽነው ይህ ሰው በጥቅስና በኩረጃ መካከል ያለውን ልዩነት የሚያውቅ አይመስልም። ሙሐመድ ጠቅሶ ቢናገር ኖሮ ከኩረጃ ክስ በዳነ ነበር ነገር ግን ከሌላ ቦታ የቀዳውን ሐሳብ በሐሰት የአላህ ንግግር አስመስሎ በማቅረቡ ምክንያት ሐሰተኛ ነቢይ ነው፤ ምናልባት ሙስሊሞች ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ አላህ ነው ብለው ካላመኑ በስተቀር! ቀጥሎ አብዱል እንዲህ ይለናል፦

ይኸው ቀጣፊ አሏህ እንደኮረጀ ለማስመሰል ሲዋትር አምላካችን አሏህ ጥንት በተውራት፦ “ነፍስ በነፍስ ዓይንም በዓይን አፍንጫም በአፍንጫ ጆሮም በጆሮ ጥርስም በጥርስ ይያዛል” የሚል ሕግ ተናግሮ የነበረው ይጠቅሳል፦

5፥45 በእነርሱም ላይ በውስጧ፦ “ነፍስ በነፍስ ዓይንም በዓይን አፍንጫም በአፍንጫ ጆሮም በጆሮ ጥርስም በጥርስ ይያዛል፤ ቁስሎችንም ማመሳሰል አለባቸው” ማለትን “ጻፍን”፡፡

“ከተበ” كَتَبَ ደግሞ “ቃለ” قَالَ ማለትም “አለ” ወይም “ከለመ” كَلَّمَ ማለትም “ተናገረ” በሚል ስለሚመጣ “ከተብና” َكَتَبْنَا የሚለው ቃል “ቁልና” قُلْنَا ወይም “አውሐይና” َأَوْحَيْنَا በሚል የመጣ ነው። ያ ሆኖ ሳለ በ 9ኛው ክፍለ ዘመን ከቁርኣን 200 ዓመት በኃላ ከተዘጋጀው ከማሶሬት ቅጂ ተጠቅሶ “በትክክል አልተቀመጠም” ማለት እንጥል መቧጠጥ ነው፦

ዘጸአት 21፥24-25  ዓይን በዓይን፥ ጥርስ በጥርስ፥ እጅ በእጅ፥ እግር በእግር፥ መቃጠል በመቃጠል፥ ቍስል በቍስል፥ ግርፋት በግርፋት ይከፈል።

ማሶሬት የቶራህ ቀዳማይ ሥረ መሠረት”orginal autography” አይደለም፥ ቅሉ ግን አሏህ ተናግሮት የነበረው አሳቡ በመለኮታዊ ቅሪት እንዳለ ጉልኅ ማሳያ ነው። ቁርኣን ላይ አሏህ የተናገረው “ነፍስ በነፍስ ዓይንም በዓይን አፍንጫም በአፍንጫ ጆሮም በጆሮ ጥርስም በጥርስ ይያዛል” የሚለው ቃል በቃል ዘጸአት 21፥24-25 መቀመጥ ነበረበት ብሎ መሞገት በባዶ ሜዳ አቧራ ከማስነሳት የዘለለ ነገር የለውም።

በመጀመርያ ደረጃ ይህንን ጥቅስ የጠቀስነው “አላህ ኮረጀ” በሚል እሳቤ አይደለም። የቁርአን ደራሲ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጠቅሶ የጻፈው በጥቂት አጋጣሚዎች ቢሆንም ጥቅሶቹን ሲጠቅስ ግን አንድም ጊዜ አስተካክሎ እንዳልጠቀሰ ለማሳየት ነው። ይህም ጳውሎስ ከኢሳይያስ አስተካክሎ አልጠቀሰም የሚለው የአብዱል ክስ ተቀባይነት ካገኘ ሙሐመድስ ምን ሊባል ነው? ለማለት እንጂ እኛ እንደ አብዱል በጥቅስና በኩረጃ መካከል ያለውን ልዩነት የማናውቅ ሆነን አይደለም።  በራሱ ያላዋቂ ሚዛን ሊመዝነን እየሞከረ ነው።

ሁለተኛ አብዱል “ከተበ” የሚለው የአረብኛ ቃል “ተናገረ” ተብሎ ሊተረጎም እንደሚችል እየነገረን ነው። ይህ ቃል በተለይም በዚህ አውድ በዚህ መንገድ እንደሚተረጎም የሚጠቁም ማስረጃ አለመጥቀሱ እንደተጠበቀ ሆኖ የጥቅሱን አውድ እንኳ ሳያነብ የቁርአን ደራሲ ስለ ጽሑፍ ሳይሆን ስለ ንግግር እየተናገረ እንዳለ ማስመሰሉ የአላዋቂነቱን ጥግ ያሳያል። እስኪ አንድ ጥቅስ ከፍ ብለን እንጥቀስ፦

እኛ ተውራትን በውስጥዋ መምሪያና ብርሃን ያለባት ስትኾን አወረድን፡፡ እነዚያ ትዕዛዝን የተቀበሉት ነቢያት በእነዚያ አይሁዳውያን በኾኑት ላይ በርሷ ይፈርዳሉ፡፡ ሊቃውንቱና ዐዋቂዎቹም ከአላህ መጽሐፍ እንዲጠብቁ በተደረጉትና በርሱም ላይ መስካሪዎች በኾኑት (ይፈርዳሉ)፡፡ ሰዎችንም አትፍሩ፡፡ ፍሩኝም፡፡ በአንቀጾቼም አነስተኛን ዋጋ አትለውጡ፡፡ አላህም ባወረደው ነገር ያልፈረደ ሰው እነዚያ ከሓዲዎቹ እነርሱ ናቸው፡፡ በእነርሱም ላይ በውስጧ «ነፍስ በነፍስ ዓይንም በዓይን አፍንጫም በአፍንጫ ጆሮም በጆሮ ጥርስም በጥርስ (ይያዛል)፡፡» ቁስሎችንም ማመሳሰል አለባቸው ማለትን ጻፍን፡፡ በእርሱም የመጸወተ (የማረ) ሰው እርሱ ለርሱ (ለሠራው ኃጢአት) ማስተሰሪያ ነው፡፡ አላህም ባወረደው ነገር የማይፈርድ ሰው፤ እነዚያ በደለኞቹ እነርሱ ናቸው” (ሱራ 5:45)።

በግልጽ እንደሚታየው የቁርአን ደራሲ እየተናገረ የነበረው ስለ ተውራት ነው። ይህ ደግሞ በዘመኑ በነበሩት ሊቃውንት እጅ እንደነበረና ሊቃውንቱ በመጽሐፉ እንደሚፈርዱ ይናገራል። ይህንን ካለ በኋላ ነው “በእነርሱም ላይ በውስጧ «ነፍስ በነፍስ ዓይንም በዓይን አፍንጫም በአፍንጫ ጆሮም በጆሮ ጥርስም በጥርስ (ይያዛል)፡፡» ቁስሎችንም ማመሳሰል አለባቸው ማለትን ጻፍን” በማለት የጠቀሰው። ተፍሲራቱንም ስንመለከት ከዚህ የወጣ ሐሳብ የላቸውም። የቁርአን ደራሲ እየተናገረ የነበረው በወቅቱ በአይሁድ እጅ ስለነበረ ተውራትና በውስጡ ስለ ተጻፈ ሐሳብ እንጂ በንግግር ስላለ ጉዳይ አይደለም።

ሦስተኛ አብዱል ስለ ማሶሬቲኩ ቅጂ ደጋግሞ ቢናገርም ምን እንደሆነ እንኳ እንደማያውቅ ግልጽ ነው። የማሶሬቲክ ቅጂ ከስድስተኛው እስከ አስረኛው ክፍለዘመን ባለው መካከል ከቀደምት የብሉይ ኪዳን ኮፒዎች ላይ የተገለበጠና በአይሁድ ሊቃውንት የእብራይስጥ አናባቢ ምልክቶች (diacritical marks) የተጨመሩበት የእብራይስጥ ጽሑፍ ሲሆን የብሉይ ኪዳን ቀደምትና ብቸኛ ጽሑፍ አይደለም። ከማሶሬቲክ የእጅ ጽሑፎች የሚቀድሙ አያሌ የብሉይ ኪዳን ጽሑፎች አሉ። ከማሶሬቲክ በእጅጉ በሚቀድሙት የሰብዓ ሊቃናት የእጅ ጽሑፎችና በማሶሬቲክ መካከል በዚህ ክፍል ላይ ልዩነት የለም። ሌላው ከማሶሬቲክ በእጅጉ የሚቀድሙ ዕድሜያቸው እስከ ቅድመ ክርስቶስ ድረስ ወደ ኋላ የሚሄድ በርካታ የእብራይስጥ የእጅ ጽሑፎች ተገኝተዋል። ይህ በሆነበት ሁኔታ የብሉይ ኪዳን የእጅ ጽሑፎች ታሪክ የሚጀምረው ከማሶሬቲክ ቅጂ ማስመሰል አላዋቂነት ነው። የሆነው ሆኖ በቀደመው ጽሑፋችን ሙሐመድ አሳስቶ የጠቀሰው ከአዲስ ኪዳንም ጭምር እንደሆነ ባሳየንበት ሁኔታ ያኛውን ችላ ብሎ ስለ አንዱ ብቻ ማውራት እንዴት መልስ ሊሆን ይችላል? ምናልባት የብሉይ ኪዳን የእጅ ጽሑፎች ከማሶሬቲክ ዘመን በኋላ ብቻ ያሉ መስሎት የአዲስ ኪዳን ደግሞ ከእስልምና በብዙ ክፍለ ዘመናት እንደሚቀድሙ ስለሚያውቅ ይሆን በብሉይ ኪዳኑ ላይ ብቻ ያተኮረው? ሙስሊሙ ወገናችን ማላመጥ ከሚችለው በላይ እንደጎረሰ ግልጽ ነው። አብዱል ይቀጥላል፦

በመጨረሻም የምለው ነገር ጳውሎስ “ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው” ተብሎ የተጻፈበት ጽሑፍ በብሉይ ኪዳን 39 መጻሕፍት ውስጥ በባትሪ ብትፈልጉት አታገኙትም። ከዚህ ይልቅ ጳውሎስ ኮረጀ ከተባለ ከ 46 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቀኖና መካከል ከሚገኘው ከመቃቢያን ሊሆን ከቻለ ነው፦

1መቃቢያን 14፥20 በወዲያኛው ዓለም ለደጋግ ሰዎች የተዘጋጀች ደስ የምታሰኝ ገነትን “ዓይን ያላየውን፣ ጆሮም ያልሰማውን፣ በሰው ልቡና ያልታሰበውን እግዚአብሔር በሕይወት ሳሉ ደስ ላሰኙት ለሚወዱት ለአብርሃም፣ ለይስሐቅ፣ ለያዕቆብ ያዘጋጀውን” ይሰጣቸው ዘንድ በሥራቸው ደስ እንዳሰኙት ለምእንደ አብርሃም፣ እንደ ይስሐቅ፣ እንደ ያዕቆብ አደሉም።

ጳውሎስ “ያዘጋጀውን” የሚለው ክርስቶስን ሲሆን የመቃብያን ተናጋሪ እና ጸሐፊ ደግሞ “ያዘጋጀውን” የሚለው ገነትን ነው። ስለዚህ ጳውሎስ “ተብሎ እንደተጻፈ” ብሎ የጻፈውን ከታሪክ መጽሐፍ ከመቃቢያን ከሆነ “ከአምላክ ነው” ብሎ ማለትም “ወዮላቸው” የሚያስብል ወንጀል ነው፦

አብዱል የመጀመርያውን ጽሑፍ ሲያዘጋጅ ጳውሎስ “ከኢሳይያስ ሲኮርጅ አሳስቶ ኮርጇል” የሚል ክስ ነበር ሲያቀርብ የነበረው። አሁን ደግሞ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቀኖና መካከል አንዱ ከሆነው ከመጽሐፈ መቃብያን “ኮርጇል” እያለ ነው። እስካሁን ድረስ የጥቅስና የኩረጃ ልዩነት ምን እንደሆነ አልተገነዘበም። የእውነት ሐዋርያው ከመጽሐፈ መቃብያን ላይ ጠቅሶ ከሆነ የኩረጃ ክስ ሳይሆን መቅረብ ያለበት መጽሐፈ መቃብያን ቀኖናዊ የመሆን ያለመሆኑ ጉዳይ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ከመጽሐፈ መቃብያን ጠቅሶ ከሆነ መጽሐፉን በቀኖናዊነት የተቀበሉት የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አማኞች ትክክል ይሆናሉ፤ ጳውሎስ ከኢሳይያስ “አሳስቶ ጠቅሷል” የሚለው አባባል ደግሞ ሌላ ምላሽ ሳያሻው በዚያው ሥርዓተ ቀብሩ ይፈጸማል ማለት ነው። ሙሐመድም ደግሞ ይህንን አባባል ሲጠቅስ ከመቃብያን ጠቅሶ “አላህ የተናገረው” እንደሆነ ስለገለጸ ሙስሊሞች ወይ መቃብያንን እንደ ቀኖና መጽሐፍ መቀበል አለባቸው አለበለዚያ ሙሐመድ ዋሽቷል ማለት ይሆናል። የሙስሊሙ ምላሽ ሙሐመድን ከኩረጃ ወንጀል በጭራሽ ነፃ አያደርገውም። የሆነው ሆኖ አሁን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኘው የመጽሐፈ መቃብያን ትርጉም በካቶሊክና በሌሎች የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ከሚታወቀው የተለየ ነው። የግሪኩንም ስንመለከት ከአማርኛው ትርጉም ጋር አንድ አይደለም፤ ይህንንም ጥቅስ በውስጡ አናገኝም። ለዚህ ነው አንድም የመጽሐፍ ቅዱስ ሐታች ቅዱስ ጳውሎስ ከመቃብያን እንደጠቀሰ ሲናገር የማናየው። ከዚህ የተነሳ ቅዱስ ጳውሎስ ከመቃብያን ጠቅሷል የሚለው አባባል በጥናት ሊረጋገጥ የሚገባው እንጂ እንደ ድምዳሜ ሊያዝ የሚገባው አይደለም። የመጽሐፈ መቃቢያን የአማርኛ ትርጉም በትክክል ዋናውን ጽሑፍ የሚወክል መሆኑ ባልተረጋገጠበት ሁኔታ ይህንን ማለት አይቻልም። በእኛ በኩል የማጣራቱን ሥራ ስለ ጉዳዩ ዕውቀት ላላቸውና ለሚመለከታቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሊቃውንት የምንተው ይሆናል። 

ስናጠቃልል በዚህ “ምላሹ” አብዱል ሐዋርያው ጳውሎስን የከሰሰበትን የኩረጃ ክስ በማስረጃ ማስደገፍ ካለመቻሉም በላይ በሙሐመድ ላይ የቀረበውን የኩረጃ ማስረጃ ማስተባበል አልቻለም። ለዚህ ሙስሊም ሰባኪ አስደንጋጭ በሆነ ሁኔታ ሙሐመድ የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስን ሐሳብ በመቅዳት ሲያቀርብ የመጀመርያው አይደለም። ለምሳሌ ያህል ተከታዩን እንመልከት፡-

“ኑዕማን ቢን በሺር እንዳስተላለፈው የአላህ መልእክተኛ እንዲህ ብለዋል፡- የአማኝ ፍቅር፣ መዋደድና መተሳሰብ ልክ እንደ አንድ አካል ነው፡፡ አንዱ የአካል ክፍል እንቅልፍ በማጣትና በትኩሳት ምክንያት ሲታመም መላው አካል አብሮት ይታመማል፡፡” (ሳሂህ ሙስሊም መጽሐፍ 45፣ ሐዲስ ቁጥር 84)

የአማኞች ፍቅርና አንድነት በአካል በመመሰል አስቀድሞ የተናገረው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ነው፡-

“ክብር ያላቸው ብልቶቻችን ግን ይህ አያስፈልጋቸውም። ነገር ግን ብልቶች እርስ በርሳቸው በትክክል ይተሳሰቡ ዘንድ እንጂ በአካል መለያየት እንዳይሆን፥ ለጎደለው ብልት የሚበልጥ ክብር እየሰጠ እግዚአብሔር አካልን አገጣጠመው። አንድም ብልት ቢሣቀይ ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሣቀያሉ፤ አንድ ብልትም ቢከበር ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ደስ ይላቸዋል። እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ እያንዳንዳችሁም ብልቶች ናችሁ።” (1ቆሮ. 12፡24-27)

ከዚህ በተጨማሪ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ንግግሮች በመቅዳት አላህ የተናገረው ንግግር በማስመሰል አቅርቧል። ለምሳሌ ያህል ጌታ በምፅዓቱ ዕለት የሚሰጠውን ፍርድ በተመለከተ የተናገረውን ሙሐመድ በመቅዳት ለአላህ አድርጎታል። በሐዲስ ቁድሲ ውስጥ እንዲህ ሲል ተጽፏል፡-

“አቡ ሁረይራ የአላህ መልእክተኛ እንዲህ ማለታቸውን ተናግሯል፡- በዕለተ ትንሣኤ አላህ እንዲህ ይላል፡- የአዳም ልጅ ሆይ፣ ታምሜ አልጠየቅኸኝም፡፡ እርሱም እንዲህ ይለዋል፡- ጌታዬ ሆይ አንተ የዓለማቱ ጌታ ስትሆን እኔ አንተን ጥየቃ እንዴት እመጣለሁ? እርሱም ይለዋል፡- እገሌ የተባለው ባርያዬ በታመመ ጊዜ እንዳልጠየቅኸው ታስታውሳለህን? ብትጎበኘው ኖሮ እኔን እርሱ ዘንድ ታገኘኝ እንደነበር ታውቃለህን? የአዳም ልጅ ሆይ ምግብ ለምኜህ አላበላኸኝም፡፡ ጌታዬ ሆይ አንተ የዓለማቱ ጌታ ስትሆን እኔ ላበላህ እንዴት እችላለሁ? እርሱም ይለዋል፡- እገሌ የተባለው ባርያዬ ምግብ ለምኖህ እንዳላበላኸው ታስታውሳለህን? ብታበላው ኖሮ ምንዳህን ከእኔ ዘንድ ታገኝ እንደነበር ታውቃለህን? የአዳም ልጅ ሆይ እንድታጠጣኝ ለምኜህ አላጠጣኸኝም፡፡ እርሱም እንዲህ ይለዋል፡- ጌታዬ ሆይ አንተ የዓለማቱ ጌታ ስትሆን እኔ የሚጠጣ ነገር ልሰጥህ የምችለው እንዴት ነው? እርሱም ይለዋል፡- እገሌ የተባለው ባርያዬ የሚጠጣ ነገር እንድትሰጠው ለምኖህ ከልክለኸዋል፡፡ ብታጠጣው ኖሮ ምንዳውን ከእኔ ዘንድ ታገኝ ነበር፡፡” (ዘገባው የሙስሊም ሲሆን 40 ሐዲስ ቁድሲ ቁጥር 18 ላይ ይገኛል)

ጌታችን ኢየሱስ እንዲህ ማለቱ በማቴዎስ ወንጌል ውስጥ ተጽፏል፡-

“የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ፥ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል፤ አሕዛብም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛም በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል፥ በጎችን በቀኙ ፍየሎችንም በግራው ያቆማቸዋል። ንጉሡም በቀኙ ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል፦ እናንተ የአባቴ ቡሩካን፥ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ። ተርቤ አብልታችሁኛልና፥ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛልና፥ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛልና፥ ታርዤ አልብሳችሁኛልና፥ ታምሜ ጠይቃችሁኛልና፥ ታስሬ ወደ እኔ መጥታችኋልና። ጻድቃንም መልሰው ይሉታል፦ ጌታ ሆይ፥ ተርበህ አይተን መቼ አበላንህስ? ወይስ ተጠምተህ አይተን መቼ አጠጣንህ? እንግዳ ሆነህስ አይተን መቼ ተቀበልንህ? ወይስ ታርዘህ አይተን መቼ አለበስንህ? ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ አይተን መቼ ወደ አንተ መጣን? ንጉሡም መልሶ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት ለእኔ አደረጋችሁት ይላቸዋል። በዚያን ጊዜ በግራው ያሉትን ደግሞ ይላቸዋል፦ እናንተ ርጉማን፥ ለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘላለም እሳት ከእኔ ሂዱ። ተርቤ አላበላችሁኝምና፥ ተጠምቼ አላጠጣችሁኝምና፥ እንግዳ ሆኜ አልተቀበላችሁኝምና፥ ታርዤ አላለበሳችሁኝምና፥ ታምሜ ታስሬም አልጠየቃችሁኝምና። እነርሱ ደግሞ ይመልሱና፦ ጌታ ሆይ፥ ተርበህ ወይስ ተጠምተህ ወይስ እንግዳ ሆነህ ወይስ ታርዘህ ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ መቼ አይተን አላገለገልንህም? ይሉታል። ያን ጊዜ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ለአንዱ ስላላደረጋችሁት ለእኔ ደግሞ አላደረጋችሁትም ብሎ ይመልስላቸዋል። እነዚያም ወደ ዘላለም ቅጣት፥ ጻድቃን ግን ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ።” (ማቴ. 25፡31-46)

በሌላ ጊዜ ደግሞ ጌታችን ያስተማረውን ጸሎት አስልሞ አቅርቧል፦

“አቡ ደርዳ እንዳስተላለፈው፡ የአላህ ምልእክተኛ (ሰላም በርሳቸው ላይ ይሁንና) እንዲህ ሲሉ ሰምቼዋለሁ፤ ከናንተ መካከል የሚታመም ቢኖር ወይንም ወንድሙ የሚታመም ቢኖር እንዲህ ይበል:- በሰማይ የምትኖር ጌታችን አላህ ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ፤ ትእዛዝህ በሰማይና በምድር የበላይ ሆኖ ይገዛል፤ ምህረትህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁም በምድር ትሁን፤ ኃጢኣታችንንና ስህተቶቻችንን ይቅር በለን፤ አንተ የመልካም ሰዎች ጌታ ነህ፤ ይህ በሽታ እንዲፈወስ ከምህረትህ ምህረትን ከፈውስህ ፈውስን አውርድ፡፡” (ሱናን አቡ ዳውድ መጽሐፍ 28፣ ቁጥር 3883)

እስኪ ይህንን ጌታችን ኢየሱስ ካስተማረው ጸሎት ጋር አነጻጽሩ፡-

“እንግዲህ እናንተስ እንዲህ ጸልዩ፡- በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፥ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን፤ የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን፤ እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን፤ ከክፉም አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን፤ መንግሥት ያንተ ናትና ኃይልም ክብርም ለዘለዓለሙ፤ አሜን።” ማቴዎስ 6፡9-13

ሙሐመድን ከኩረጃ ወንጀል ነጻ ለማድረግ ከመሞከር ወተት ጥቁር ነው ብሎ መከራከር ይቀላል!


ተጨማሪ ንባቦች


ለእስልምና ሙግቶች ምላሽ