የቁርኣን ግጭቶች – ሙሐመድ ቢሳሳት የሚጐዳው ማነው?

10. ሙሐመድ ቢሳሳት የሚጐዳው ማነው?

ማሳሰብያ፡- በሰማያዊ የተጻፈው የኛ ሲሆን በጥቁር የተጻፈው የእርሱ ነው፡፡

እስኪ የሚከተለውን የቁርኣን ጥቅስ በአንክሮ ያጢኑ፡-

ሱራ 34፡50 “ብሳሳት የምሳሳተው በራሴ ላይ ብቻ ነው ብመራም ጌታዬ ወደኔ በሚያወርደው ነው፡፡”

መልስ

34፥50 «ብሳሳት የምሳሳተው በራሴ ላይ ብቻ ነው፡፡ ብመራም ጌታዬ ወደ እኔ በሚያወርደው ነው”፡፡ እርሱ ሰሚ ቅርብ ነውና» በላቸው፡፡

ይህ ጥያቄ የግጭት ጥያቄ ሳይሆን የብዥታ ጥያቄ ነው።

የጥያቄያችንን ነጥብ ቆርጠህ በማስቀረት ወደ መልስ መዝለል ትክክል አይደለም፡፡ በኦሪጅናል ጽሑፋችን ውስጥ ያነሳነው ጥያቄ እንዲህ የሚል ነው፡-

ሙሐመድ “እኔ ያመንኩትን እመኑ ተከተሉኝ” እያለ መለስ ብሎ ደግሞ “ብሳሳት የምሳሳተው በራሴ ላይ ብቻ ነው” ማለቱ በእጅጉ ያስገርማል፡፡ ይህ ጥቅስ በአረብኛና በእንግሊዘኛ የቁርኣን መጽሐፍት ይበልጥ ግልፅ ሆኖ ይነበባል፡፡ ሐሳቡም ሙሐመድ ትክክል ካልሆነ (ከተሳሳተ) የሚጐዳው እርሱ ብቻ እንደሆነ ነው፡፡  ሙስሊሞች ከአለባበስ ጀምሮ እሰከ ጢም አቆራረጥ ድረስ ሙሐመድን መምሰል ወሳኝ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ሙሐመድ ልክ ከሆነ የእርሱን ትምህርት የተቀበሉና የተከተሉት ሰዎች ሊድኑ ይችላሉ፡፡ እርሱ ትክክል ካልሆነ ግን ይጠፋሉ፡፡ ምክንያቱም ሐሰተኛ ነቢያትና ሐሰተኛ አስተማሪዎችን የሚከተሉ ሰዎች ሁሉ ይጠፋሉና፡፡ ሙሐመድ ትክክለኛ ነቢይ ሆነም አልሆነም ይህ ዓይነቱ ንግግር ስህተት እንደሆነ ለማንም ግልፅ ነው፡፡ ምክንያቱም እርሱ ቢሳሳት የሚጐዳው እርሱን የተከተለ ሰው ሁሉ እንጂ እርሱ ብቻ ስላልሆነ ማለት ነው፡፡

ጥያቄውን መመለስ የሚኖርብህ ጥያቄውን በትክክል ካስቀመጥክ በኋላ ነው፡፡

ነቢያችን ቁርኣን ወደ እርሳቸው መወረዱን ተስፋ ሳያደርጉ ከቁርኣን በፊት ምንም ሳይሉ ማለትም፦ “ነብይ ወይም መልእክተኛ ነኝ” ሳይሉ ብዙ ዕድሜ ማለትም 40 ዓመት በእርግጥ ኖረዋል፦

28፥86 መጽሐፉ ወደ አንተ መወረዱን ተስፋ የምታደርግ አልነበርክም፡፡ ግን ከጌታህ ችሮታ ተወረደልህ፡፡ ለከሓዲዎችም በፍጹም ረዳት አትኹን፡፡

10፥16 አላህ በሻ ኖሮ በእናንተ ላይ ባለነበብኩትም፤ አላህ እርሱን ባላሳወቃችሁም ነበር፡፡ በእናንተም ውስጥ ከእርሱ በፊት ምንም ሳልል ብዙን ዕድሜ በእርግጥ ኖሬአለሁ፤ አታውቁምን? በል።

ከቁርኣን መውረድ በፊት በአርባ ዓመት ውስጥ በነበራቸው ቆይታ መጽሐፍን የሚያነቡ በቀኛቸውም የሚጽፉ አልነበሩም፤ አላህ ምንም የማያውቁ ሆነው ሳሉ ቁርኣንን በማውረድ መራቸው፦

29፥48 ከእርሱ በፊትም መጽሐፍን የምታነብ በቀኝህም የምትጽፈው አልነበርክም፡፡ ያን ጊዜ አጥፊዎቹ በእርግጥ በተጠራጠሩ ነበር፡፡

93፥7 የሳትክም ኾነህ አገኘህ መራህም፡፡

“የሳትክ” የሚለው ቃል “አዷል” أَضَلّ ሲሆን “ምሪት አልባ” ማለት ነው፤ “ምሪት አልባ” ነበርክ ማለት “መጽሐፉም ምን እንደኾነ የምታውቅ አልነበርክም” ማለት ነው፤ “መራንህ” የሚለው “የምንሻውን ሰው በእርሱ የምንመራበት ብርሃን አደረግነው” በሚል መጥቷል፦

42፥52 እንደዚሁም ወደ አንተ ከትእዛዛችን ሲኾን መንፈስን አወረድን፡፡ መጽሐፉም እምነቱም ምን እንደኾነ የምታውቅ አልነበርክም፡፡ ግን ከባሮቻችን የምንሻውን ሰው በእርሱ የምንመራበት ብርሃን አደረግነው፡፡ አንተም ወደ ቀጥተኛው መንገድ በእርግጥ ትመራለህ፡፡

ስለዚህ የሳትክ ነበር ማለት መጽሐፉም ምን እንደኾነ የምታውቅ አልነበርክም ማለት ሲሆን ቁርኣንን የሚመራበት ብርሃን አድርጎ መራቸው ማለት ነው።

እኛ የጠቀስነው ጥቅስ ግን ስለ ቀደመው ሕይወቱ ሳይሆን በወቅቱ ስለነበረው ሕይወቱ ነው እየተናገረ ያለው፡፡ ሙሐመድ በወቅቱ ለነበሩት አድማጮቹ “ብሳሳት ማንንም አልጎዳም” እያለ ነው፡፡ “ብሳሳት ኖሮ” በማለት በአላፊ ጊዜ ሳይሆን “አሁን የተሳሳትኩ ብሆን” በሚል መንፈስ “ብሳሳት የምሳሳተው በራሴ ላይ ብቻ ነው” እያለ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የተሳሳተ ንግግር ነው፡፡

ይህ ቁርኣን ወደ ቀጥተኛ መንገድ ይመራል፦

17፥9 ይህ ቁርኣን ወደዚያች እርሷ ቀጥተኛ ወደ ኾነችው መንገድ ይመራል፡፡

አንቀጹ ይቀጥልና፦ “ድኻም ኾነህ አገኘህ አከበረህም” ይላል፤ ሃብት ሙሉነት ሲሆን ድህነት ባዶነት ነው። እውነተኛ ሃብት ደግሞ የነፍስ ሃብት ቁርኣን ነው፤ ስለዚህ የሳትክ  ነበርክ ማለት የቁርኣን ዕውቀቱ አልነበረክም ደሃ ነበርክ፤ መራንህ ማለት የነፍስ ሃብት በሆነው ቁርኣን አከበርንህ ማለት ነው፤ ታላቁ ሙፍሲር ኢብኑ ከሲር በዚህ መልኩ ነው ያስቀመጠው፦

93፥8 ድኻም ኾነህ አገኘህ አከበረህም፡፡

ኢማም ቡኻርይ: መጽሐፍ 81, ሐዲስ 35

አቢ ሁረይራህ”ረ.ዐ” እንደተረከው ነብዩም” አሉ፦ ”ሃብት ማለት መጠነ ሰፊ ንብረት መያዝ አይደለም። ነገር ግን ሃብት ማለት የነፍስ ሃብት ነው።

ስለዚህ “ደለልቱ” ضَلَلْتُ የሚለው ቃል “አዷል” أَضَلّ ማለትም “ምሪት አልባ” ከሚል የስም መደብ የመጣ ሲሆን  “ባላውቅ” “ባልገነዘብ” “ምሪት አልባ ብሆን” ጉዳቱ በራሴ ላይ ነው፥ ብመራም ጌታዬ ወደ እኔ በሚያወርደው ቁርኣን ነው ማለት ነው።

ቁርኣን ወደ ቀጥተኛ መንገድ ይመራል፦

17፥9 ይህ ቁርኣን ወደዚያች እርሷ ቀጥተኛ ወደ ኾነችው መንገድ ይመራል፡፡

ምሪት አልባ ባዶ ሰው እራሱን ይጎዳል እንጂ ሌላውን አይጎዳም። የሌለውን ከየት ይሰጣል?

ኦንላይን የሚገኘውን የአረቢክ ቁርኣን ኮርፐስ የተመለከትን እንደሆን ቃሉ በሁሉም አገባብ error, astray, mislead, lost እየተባለ እንደሚተረጎም ያሳያል http://corpus.quran.com/qurandictionary.jsp?q=Dll#(34:50:3) ፡፡ ዞሮ ዞሮ ከፈጣሪ የሆነ ምሪት ማጣት በስህተት ጎዳና ላይ መገኘትን እንጂ ከስህተትም ከትክክልም ነፃ (neutral) መሆንን አያመለክትም፡፡ ስለዚህ “ምሪት አልባ ባዶ ሰው እራሱን ይጎዳል እንጂ ሌላውን አይጎዳም” የሚለው አባባል ሐሰት ነው፡፡ ከፈጣሪ የሆነ ምሪት የሌለው ሰው በተሳሳተ ጎዳና ላይ ስላለ የሚጎዳው ራሱን ብቻ ሳይሆን በዙርያው የሚገኙትንም ሰዎች ጭምር ነው፡፡ በዚህች ምድር ላይ የሚኖር ሰው ምናልባት ለብቻው ተነጥሎ በአንድ ደሴት ላይ ካልኖረ በስተቀር በተሳሳተ ጎዳና ላይም ይሁን በመልካም ጎዳና በዙርያው በሚገኙት ሰዎች ላይ ተጽዕኖ ማምጣቱ የማይቀር ነው፡፡

በሌላ ወገን ስናየው ሙሐመድ አንተ ስህተትን በተረጎምከው መንገድ የተሳሳተ ቢሆን ኖሮ (ምሪትን ባያገኝ ኖሮ) የሚሳሳሳተው እርሱ ብቻ አይደለም፤ በእርሱ አማካይነት ምሪት ሊመጣላቸው የተገቡት ሰዎች ሁሉ ተሳስተው ይቀራሉ፡፡ ስለዚህ የእርሱ ምሪትን አለማግኘት የሚጎዳው እርሱን ብቻ ሳይሆን ምሪቱን በእርሱ አማካይነት መቀበል የተገባቸውን ሰዎች በሙሉ ነው፡፡ ስለዚህ ያንተ አመክንዮ በእጅጉ ደካማ ነው፡፡

ሲቀጥል መሳት እና ማሳሳት ሁለት ለየቅል ዐረፍተ-ነገር ይሰራሉ። መሳሳት ጉዳቱ በራስ ላይ ነው፥ ቀጥሎ ሌላውን ማሳሳት ጉዳቱ በሌላውም ጭምር ነው፦

10፥108 «እናንተ ሰዎች ሆይ! እውነቱ ከጌታችሁ በእርግጥ መጣላችሁ፡፡ በእርሱ የተመራም ሰው የሚመራው ለራሱ ነው፡፡ የተሳሳተም ሰው የሚሳሳተው ጉዳቱ በራሱ ላይ ነው፡፡ እኔም በእናንተ ላይ ተጠባበቂ አይደለሁም» በላቸው፡፡

17፥15 የተመራ ሰው የሚመራው ለራሱ ብቻ ነው፡፡ የተሳሳተም ሰው የሚሳሳተው ጉዳቱ በእርሷ ላይ ነው፡፡ ተሸካሚም ነፍስ የሌላይቱን ኃጢኣት አትሸከምም”፡፡ መልዕክተኛንም እስከምንልክ ድረስ የምንቀጣ አይደለንም፡፡

ሙሐመድን የመሰለ ነቢይ ነኝ ባይ ሰው ቢሳሳት እርሱ ብቻ ተሳስቶ አይቀርም ነገር ግን የተከተሉትን ሁሉ ያሳስታል፡፡ ስለዚህ በሙሐመድ ሁኔታ መሳትና ማሳሳት መነጣጠል አይችሉም፡፡

የተሳሳተ ሰው ጉዳቱ በራሱ ላይ ሲሆን ያሳሳተ ሰው ግን ሌላውን በማሳሳቱ ያሳሳተው ሰው የሚቀጣበትን ቅጣት ከሚቀጣው ሰው ላይ ሳይጨመር ሳይቀነስ በማሳሳቱ ይቀጣል፦

16፥25 ይህንንም የሚሉት በትንሣኤ ቀን ኀጢኣቶቻቸውን በሙሉ ”ከእነዚያም ያለ ዕውቀት ኾነው ከሚያጠሟቸው ሰዎች ኀጢአቶች ከፊሉን ሊሸከሙ ነው”፡፡ ንቁ! የሚሸከሙት ኃጢኣት ምንኛ ከፋ!

አንድ ሰው ሌላውን ሰው ሲያሳስት አሳሳቹ በማሳሳቱ ምክንያት የተሳሳተው ሰው የሚያገኘውን ቅጣት ከሚሳሳተው ላይ ቅጣቱ ሳይቀነስ ሳይጨመር የተሳሳተውን ሰው ቅጣት አሳሳቹ ይቀበላል፤ አንድ ሰው ሌላውን ሰው ከመራ መሪው በመምራቱ ምክንያት የተመራው ሰው የሚያገኘውን አጅር ከሚመራው ላይ አጅሩ ሳይቀነስ ሳይጨመር የተመራውን ሰው አጅር መሪው ይቀበላል፤ ከላይ ያለው መልክእት ይህ ነው፤

ይህ በቀጥታ የሙሐመድን ሁኔታ ያመለክታል፡፡ ስለዚህ “ብሳሳት እራሴን እንጂ ሌላውን አልጎዳም” ማለቱ ስህተት ነው፡፡

ኢብኑ ከሲር ይህንን አንቀፅ በሐዲስ እንዲህ ይፈስረዋል፦

ሱነን ኢብኑ ማጃህ መጽሐፍ 1, ሐዲስ 210

አነስ ኢብኑ ማሊክ እንደተረከው፤ የአላህ መልእክተኛ” እንዲህ አሉ፦ “ማንም ጠሪ ሰዎችን ወደ ጥመት የሚጣራ የተከተሉት ሰዎች የሚሸከሙትን ኀጢአት ከእነርሱ ላይ ሳይጓደል ይሸከማል፤ ማንም ጠሪ ሰዎችን ወደ ምሪት የሚጣራ የተከተሉት ሰዎች የሚያገኙትን ምንዳ ከእነርሱ ላይ ሳይጓደል ያገኛል”።

ስለዚህ ሙሐመድ ራሱ ወደ ጀመረው የእስልምና ሃይማኖት ሰዎችን እየጠራ “ብሳሳት የምሳሳተው በራሴ ላይ ብቻ ነው” ብሎ ማለቱ ትክክል አይደለም፡፡ ሙሐመድ ቢሳሳት የተከተሉት ሰዎች ሁሉ ይሳሳታሉ፤ ትክክል ቢሆን የተከተሉት ሰዎች ትክክል ይሆናሉ፡፡ ሙሐመድ ትክክለኛ መንገድ ላይ ቢሆን እንኳ ይህ ንግግሩ ስህተት ነው፡፡ ቢሳሳት የተከተሉትን ሁሉ ያሳስታል እንጂ እርሱ ብቻ እንዴት ይሳሳታል?

ነፍስ የሌላይቱን ኃጢአት አትሸከምም ማለት ለምሳሌ መቶ ኪሎ ጤፍ ተሸክሜ ከነበረ ሌላ ሰው ለእኔ ጤፉን ከተሸከመልኝ እኔ ላይ መቶ ኪሎ ጤፍ የለም ማለት ነው፤ ግን አጥማሚ የጠመመውን ሰው በእርሱ ምክንያት ነውና ከእርሱ ቅጣት ሳይጓደል ይቀጣል።

ስለዚህ ሙሐመድ ባሳሳታቸው ሙስሊሞች ሁሉ ኀጢአት ተጠያቂ ስለሚሆን ቅጣቱ ምንኛ ከፋ!

መልሱ ኢንሻላህ ይቀጥላል…

እስከ አሁን አንድም መልስ ስትሰጥ አላየንህም፡፡ ገና ትጀምር እንደሆን እንጠብቃለን፡፡ እኛ ግን፡-

በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ኃይል መልሳችን ይቀጥላል…

 

ለተመሳሳይ ጥያቄ የተሰጠ ሌላ ምላሽ ለማንበብ እዚህ ጋ ጠቅ ያድርጉ

የቁርኣን ግጭቶች