የቁርኣን ግጭቶች – ዓድ የጠፋችው በስንት ቀን ነው?

12. ዓድ የጠፋችው በስንት ቀን ነው?

ማሳሰብያ፡- በሰማያዊ የተጻፈው የኛ ሲሆን በጥቁር የተጻፈው የእርሱ ነው፡፡

በአንድ ቀን

54:19 እኛ በነርሱ ላይ ዘወትር መናጢ በኾነ ቀን በኃይል የምትንሻሻ ነፋስን ላክንባቸው::

B, በብዙ ቀን

41:16 በቅርቢቱ ሕይወት የውርደትን ቅጣት ልናቀምሳቸውም፣ በነሱ ላይ የሚንሻሻን ብርቱ ነፋስ መናጢዎች በሆኑ ቀናት ውስጥ ላክንባቸው፤

በሰባት ቀን

69:6-7 ዓድማ በኀይል በምትንሻሻ ብርቱ ነፋስ ተጠፉ። ተከታታይ በሆኑ ሰባት ሌሊቶችና ስምንት መዓልቶች ዉስጥ በነሱ ላይ ለቀቃት ሕዝቹንም በዉስጧ የተጣሉ ሆነዉ ልክ ክፍት የሆኑ የዘንባባ ግንዶች መስለው ታያቸዋለህ።

መልስ

“ዘወትር” መናጢ በኾነ “ቀን” ይላል ልክ ነው፦

54:19 እኛ በእነርሱ ላይ ዘወትር መናጢ በኾነ ቀን” በኀይል የምትንሻሻ ነፋስን ላክንባቸው፡፡

እዚህ ጥቅስ ላይ በአንድ ቀን የሚል ቃል የለውም፣ ባይሆን “የውም” يَوْم ማለትም “ቀን” የሚለው ቃል የግድ የሃያ አራት ሰዓት እርዝማኔ ብቻ ሳይሆን ጥቅላዊ ቀናትን ዐቅፎ ሊጠራ ይችላል። ለምሳሌ የትንሳኤ ቀን፣ የሂሳቡ ቀን፣ የፍርዱ ቀን ወዘተ…። ነገር ግን ይህ ቀን በውስጡ ቀናት መያዙን የምናውቀው “ሙሥተሚር” مُّسْتَمِر ማለትም “ዘወትር” የሚል ሃይለ-ቃል አለ።

“ዘወትር” ማለት ገደብ የሌለው የቀናት ድግግሞሽ እንጂ ጥቂት ቀናት ብቻ ማለት አይደለም፡፡ በዚያ ትርጓሜ መሠረት የምትሄድ ከሆነ ንፋሱ በአድ ላይ የነፈሰው ለዘወትር ማለትም ገደብ ለሌለው ጊዜ ነው፡፡ ስለዚህ “ዘወትር” የምትለዋን ቃል ልብ እንድንላት በመጠቆምህ ግጭቱን ከአንዱ ዓይነት ወደ ሌላው ዓይነት ለወጥከው እንጂ አላስወገድከውም፡፡ እንግዲያውስ ያንተን ምላሽ ይዘን እንዲህ ስንል እንጠይቅሃለን፤ በአድ ላይ ንፋስ የነፈሰው ለዘወትር (ማለትም ገደብ ለሌለው የቀናት ድግግሞሽ) ወይንስ ለሰባት ሌሊቶችና ስምንት መዓልት ብቻ? የቱ ነው ትክክል?

ሰው፦ “ቀን ወጣልኝ” ሲል 24 ሰአት እርዝማኔ ያለውን መአልት እና ሌሊት ማመልከቱ ሳይሆን “ያልተወሰነ ጊዜን” ለማመልከት ነው። “ዘወትር” የያዘ መናጢ ቀን በውስጡ ብዙ መናጢዎች ቀናትን እንደያዘ ይህ አንቀጽ ያስረዳል፦

ምላሽህን ተቀብለናል፤ ስለዚህ አዲሱን ግጭት አስታርቅልን፡፡ ባንተው አባባል መሠረት በዚህ ቦታ “ቀን” ሲል የ24 ሰዓት ርዝማኔን ሳይሆን “ያልተወሰነ ጊዜን” ለማመልከት ከሆነ፤ ይህም “ዘወትር” በሚል ያልተገደበ የቀናት ድግግሞሽን በሚገልፅ ቃል ከተጠናከረ በአድ ላይ ነፋስ የነፈሰው ለዘወትር ወይንስ ለሰባት ሌሊቶችና ስምንት መዓልት ብቻ?

41፥16 በቅርቢቱ ሕይወት የውርደትን ቅጣት ልናቀምሳቸውም በእነርሱ ላይ የሚንሻሻን ብርቱ ነፋስ መናጢዎች በኾኑ ቀናት ውስጥ ላክንባቸው፡፡

እነዚህ መናጢ ቀናት ሰባት ሌሊት እና ስምንት መዓልት የያዙ ቀናት ናቸው፦

69፥7 “ተከታታይ በኾኑ ሰባት ሌሊትና ስምንት መዓልት ውስጥ በእነርሱ ላይ ለቀቃት”፡፡ ሕዝቦቹንም በውስጧ የተጣሉ ኾነው ልክ ክፍት የኾኑ የዘንባባ ግንዶች መስለው ታያቸዋለህ፡፡

በመዓልት የሚጀምር እና የሚያልቅ ስምንት መአልት በውስጡ ሰባት ሌሊት ሲኖረው ሰባት ቀናት ይሆናል።

ስለዚህ ቀናቱ ውሱን ከሆኑ ቀደም ሲል “ዘወትር” ከሚለው ጋር ይጋጫል ማለት ነው፡፡

“ቀን” የሚለው ነጠላ ቃላት ለብዙ ቀናት ቃሉ አገልግሎት ላይ እንደሚውል ከራሳችሁ ባይብል በአንድ ናሙና ልሞግት፦

ዘጸአት 31፥17 እግዚአብሔር  ሰማይንና ምድርን “በስድስት “ቀን” ስለ ፈጠረ”፥

ዘጸአት 20፥11 እግዚአብሔር “በስድስት “ቀን” ሰማይንና ምድርን፥ ባሕርንም፥ ያለባቸውንም ሁሉ ፈጥሮ” በሰባተኛው ቀን ዐርፎአልና፤

ስድስት ተብሎ “ቀን”  አይባልም፣ ባይሆን “ቀናት” እንጂ፣ ነገር ግን ባይብል የተጠቀመበት ቃል ነጠላ ሲሆን “ዮውም” י֔וֹם ማለትም “ቀን” እንጂ “ያሚም” לְיָמִ֖ים ማለትም “ቀናት” አይደለም፣ አይ “ዮውም”  የሚለው “ያሚም” የሚለውን ጠቅልሎ ይይዛል ከተባለ እንግዲያውስ የቁርኣኑን አናቅጽ በዚህ ሒሳብ ተረዱት። ጉንፋን ይዞክ ሰውን ጉንፋናም ብለክ ትፎትታለህ እንዴ? ከአንሰሪንግ ኢሥላም ላይ አምጣችሁና አላምጣችሁ ያመጣች ኮፒ እንዲህ ድባቅ ይገባል።

ፉከራውንና ሽለላውን አቆየውና ሐሳብህን ሰብሰብ አድርግ፡፡ በአማርኛም ሆነ በእብራይስጥ ቁጥርን ገልጸን “ቀን” ማለት እንችላለን፤ ለምሳሌ ሁለት ቀን፣ ስድስት ቀን፣ ሰባት ቀን፣ ወዘተ.፡፡ ይህንን ዘወትር የምንጠቀምበት አነጋገር በመሆኑ በዚህ ማንም ግር የሚሰኝ የለም (እግረ መንገድህን የዘወትርን ትርጉም ልብ እያልክ)፡፡ ነገር ግን አንድን ክስተት ጠቅሰን “ቀን” የሚል ነጠላ ቃል ካስከተልን ክስተቱ በአንድ ቀን ለመከሰቱ ማሳያ ነው፡፡ مُسْتَمِرٍّ (ሙስዕታምሪን) ለሚለው የአረብኛ ቃል የአማርኛ ቁርኣን ተርጓሚዎች የሰጡትን “ዘወትር” የሚለውን ትርጓሜ ተቀብለህ የቀናቱን ርዝማኔ ከአንድ ቀን ወደ ኢ-ውሱን ቀናት በመለወጥህ የግጭቱን ዓይነት ለወጥክ እንጂ ግጭት አልፈታህም፡፡ እስከ አሁን ድረስ እንደታዘብነው ግጭት ከመፍታት ይልቅ ግጭት በመፍጠር የተካንክ ነህ፡፡

የቁርኣን ግጭቶች