የቁርኣን ግጭቶች – አላህ ሁሉን አዋቂ ነው ወይንስ አይደለም?

16. አላህ ሁሉን አዋቂ ነው ወይንስ አይደለም?

ማሳሰብያ፡- በሰማያዊ የተጻፈው የኛ ሲሆን በጥቁር የተጻፈው የእርሱ ነው፡፡

ሁሉን አዋቂ ነው፦

49:16 አላህ በሰማያት ውስጥ ያለውንና በምድር ውስጥ ያለውን ሁሉ የሚያውቅ ሲኾን አላህን በሃይማኖታችሁ ታስታውቁታላችሁን? በላቸው፤ አላህም በነገሩ ሁሉ ዐዋቂ ነው።

ሁሉን አዋቂ አይደለም፦

47:31 “ከናንተም ታጋዮቹንና ታጋሾቹን እስከምናውቅ ወሬዎቻችሁንም እስከምንገልፅ ድረስ በእርግጥ እንሞክራችኋለን።”

ኦሪጅናል ጥያቄያችን ውስጥ የተዘረዘሩት ጥቅሶች እነዚህ ብቻ አይደሉም፡፡ ቆርጠህ ያስቀረሃቸውን እንመልከትና ከዚያ መልስህን እንሰማለን፡፡

አላህ ሁሉን አዋቂ ነው ወይንስ አይደለም?

ሁሉን አዋቂ ነው;- ለምሳሌ ቁርኣን 2፡59፤ 2፡96፤ 49፡18፤ ይመልከቱ

ሁሉን አዋቂ አይደለም –

በግምት ይናገራል 53:1 “በኮከብ እምላለሁ በወደቀ (በገባ) ጊዜ። ነቢያችሁ፣ (ሙሀመድ) አልተሳሳተም፤ አልጠመመምም። ከልብ ወለድም አይናገርም። እርሱ (ንግግሩ) የሚወረድ ራዕይ እንጂ ሌላ አይደለም። ኀይሎቹ ብርቱው (መልአክ) አስተማረው። የዕውቀት ባለቤት የሆነው (አስተማረው በተፈጥሮ ቅርጹ ሆኖ በአየር ላይ) ተደላደለም። እርሱ በላይኛው አድማስ ሆኖ። ከዚያም ቀረበ፤ ወረደም። (ከርሱ) የሁለት ደጋኖች ጫፍ ያህል፣ ወይም (ከዚህ) ይበልጥ የቀረበ ሆነም።” “And was at a distance of two bow lengths or nearer.”

ይጠራጠራል 11:12 “በርሱ ላይ የገንዘብ ድልብ ለምን አልተወረደም ወይም ከርሱ ጋር መልአክ ለምን አልመጣም ማለታቸውንም በመፍራት ወደ አንተ ከሚወርደው ከፊሉን ልትተው በርሱም ልብህ ጠባብ ሊኾን ይፈራልሃል፤ አንተ አስፈራሪብቻ ነህ፤ አላህም በነገሩ ሁሉ ተጠባባቂ ነው።”

18:6 “በዚህም ንግግር (በቁርኣን) ባያምኑ፣ በፈለጎቻቸው ላይ በቁጭት ነፍስህን አጥፊ ልትሆን ይፈራልሃል።” “Then perhaps you would kill yourself through grief over them, [O Muhammad], if they do not believe in this message, [and] out of sorrow”

26:3 “አማኞች ባለ መሆናቸው፤ (በቁጭት) ነፍስህን ገዳይ መሆን ይፈራልሃል፤” “Perhaps, [O Muhammad], you would kill yourself with grief that they will not be believers.”

እርግጠኛ ለመሆን ጊዜንና ሁኔታዎችን መጠበቅ ያስፈልገዋል 72:25-28 “የምትስፈራሩበት ነገር ቅርብ፣ ወይም ጌታየ ለርሱ የተወሰነ ጊዜን የሚያደርግለት (ሩቅ)፣ መሆኑን አላውቅም በላቸው። (እርሱ) ሩቁን ሚስጢር ዐዋቂ ነው፣ በሚስጢሩ ላይ አንድንም አያሳውቅም። ከመልክተኛ ለወደደው ቢሆን እንጅ (ለሌላ አይገልጽም)፤ እርሱም ከስተፊቱም ከስተኋላውም ጠባቂዎችን ያደርግለታል። እነሱ ዘንድ ባለው ነገር ዕውቀቱ የከበበና ነገሩንም ሁሉ በቁጥር ያጠቃለለ ሲሆን፣ የጌታቸውን መልክቶች ያደረሱ መሆናቸውን ያውቅ ዘንድ (ጠባቂ ያደርጋል)።

“That he may know that they have conveyed the messages of their Lord; and He has encompassed whatever is with them and has enumerated all things in number.”

47:31 “ከናንተም ታጋዮቹንና ታጋሾቹን እስከምናውቅ ወሬዎቻችሁንም እስከምንገልፅ ድረስ በእርግጥ እንሞክራችኋለን።”

3:140 “ቁስል ቢያገኛችሁ ሰዎቹንም መሰሉ ቁስል አግኝቷቸዋል፤ ይኽችንም ቀናት በሰዎች መካከል እናዘዋዉራታለን፤ (እንድትገሠጹና) አላህም እነዚያን ያመኑትን እንዲያዉቅ (እንዲለይ)፣ ከናንተም ሰማዕታትን እንዲይዝ ነዉ፤ አላህም በዳዮችን አይወድም።”

በመጀመርያዎቹ ጥቅሶች ውስጥ አላህ ሁሉን አዋቂ መሆኑ ሲነገረን በሁለተኛዎቹ ውስጥ ግን አላህ ሲጠራጠር በግምት ሲናገር እና ስለ አንዳንድ ጉዳዮችም እርግጠኛ ለመሆን ልክ እንደ ሰው ጊዜንና ሁኔታን መጠበቅ ሲያስፈልገው እናያለን፡፡

ይህንን ሁሉ ማስረጃ ቆርጠህ አስቀርተህ ለአንዷ ጥቅስ ብቻ ምላሽ መስጠትህ አስገራሚ ነው፡፡

መልስ

በቁርኣን ከተገለፁት የአላህ ስሞች መካከል “አል-ዐሊም” الْعَلِيم ወይም “አል-ዓሊም” الْعَٰلِم ሲሆን “ሁሉን ዐዋቂ” ማለት ነው፤ አላህ ሁሉን ነገር ዐዋቂ ነው፦

49:16 አላህ በሰማያት ውስጥ ያለውንና በምድር ውስጥ ያለውን ሁሉ የሚያውቅ ሲኾን አላህን በሃይማኖታችሁ ታስታውቁታላችሁን? በላቸው፤ አላህም በነገሩ ሁሉ ዐዋቂ ነው።

24:64 ንቁ፣ በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉ የአላህ ብቻ ነው፤ እናንተ በርሱ ላይ ያላችሁበትን ኹኔታ፣ በእርግጥ ያውቃል፤ ወደርሱ የሚመለሱበትን ቀንም ያውቃል፤ የሠሩትንም ሁሉ፣ ይነግራቸዋል፤ አላህም ነገሩን ሁሉ ዐዋቂ ነው ።

33:54 ማንኛውንም ነገር ብትገልጹ ወይም ብትደብብቁ በእርሱ ይመነዳችኋል፤ አላህ ነገሩን ሁሉ ዐዋቂ ነውና።

ችግሩ ሁሉን አዋቂ አለመሆኑን የሚያሳዩ የቁርኣን ጥቅሶች መኖራቸው ነው፡፡

“ዒልም” عِلْم ማለት “ዕውቀት” ማለት ሲሆን የአላህ ዕውቀት የአላህ የራሱ ባህርይ ነው፤ ይህ የአላህ ዕውቀት በመሃይምነት ተቅድሞ መነሻ እና በመሃይምነት ተደምድሞ መዳረሻ የለውም፤ የአላህ ዕውቀት በጊዜ እና በቦታ እንደ ፍጡራን አይገደብም፤ ዕውቀቱ አይሻሻልም አይለወጥም። ይህ የአላህ ዕውቀት በቁርኣን ውስጥ የተገለፀው በሁለት መልኩ ነው፤ አንደኛው “ዒልሙል ገይብ” ሲባል ሁለተኛው “ዒልሙዝ ዛሂር” ይባላል፦

ነጥብ አንድ

“ዒልሙል ገይብ”

ቀጥሎ ያቀረብከው በሙሉ ጥያቄውን የማይመለከት አላስፈላጊ ሐተታ ነው፡፡ “መልሴን ቆረጡብኝ” እንዳትል ግን እንዳለ ወስደነዋል፡፡

“ዒልሙል ገይብ” عِلْمٌ الْغَيْب ማለት “ስውር ወይም እሩቅ አሊያም ረቂቅ ዕውቀት”subjective knowledge” ማለት ነው፤ “ገይብ” غَيْب ማለት “ባጢን” بَاطِن “ስውር” ወይም “እሩቅ” ማለት ሲሆን አላህ አንድ ነገር ከመከሰቱ በፊትና በኃላ እና ከህዋስ ባሻገር ያለውን ዕውቀት ነው፦

2፥255 ከፍጡሮች በፊታቸው ያለውንና ከኋላቸው ያለውን ሁሉ ያውቃል፡፡

21:28 በፊታቸው ያለውንና በኋላቸው ያለውንም ሁሉ ያውቃል፤

19፥64 «በጌታህም ትእዛዝ እንጅ አንወርድም፡፡ ”በፊታችን ያለው፣ በኋላችንም ያለው በዚህም መካከል ያለው” ሁሉ የርሱ ነው፡፡ ጌታህም ረሺ አይደለም፡፡

“ገይብ” በሶስት ይከፈላል፦

አንደኛው “አል-ገይቡል ማዲ” الغيبه المادي ሲሆን ያለፈ ክስተት ነው፤ ይህም ድርጊቱ ከዚህ በፊት አላፊ የሆነ ነገር ነው፤ ከፍጡራን በፊት ያሉትን የሩቅ ወሬዎች አላህ ብቻ ነው በትክክል የሚያውቃቸው።

ሁለተኛው “አል-ገይቡል ሙዷሪዕ” الغيب المضارع ሲሆን እየተፈጸመ ያለ ክስተት ነው፤ ይህም ድርጊቱ በአሁኑ ሰዓት ቀጣይነት ያለው ነገር ነው፤ አላህ በመካከል ማለትም ከህዋስ ባሻገር ለምሳሌ በልብ ውስጥ ያለውን ሁሉ ያውቃል።

ሦስተኛው “አል-ገይቡል ሙስተቅበል” الغيب المستقبل ሲሆን መጪው ክስተት ነው፤ ይህም ድርጊቱ ገና ያልተፈጸመ ወደፊት የሚሆን ነው፤ ከፍጡራን በኃላ ወደ ፊት ምን እንሚከሰት ያውቃል።

እንደርሱ ከሆነ ታድያ ሱራ 72:25-28 ላይ ለምን እንዲህ ይላል? እነሱ ዘንድ ባለው ነገር ዕውቀቱ የከበበና ነገሩንም ሁሉ በቁጥር ያጠቃለለ ሲሆን፣ የጌታቸውን መልክቶች ያደረሱ መሆናቸውን ያውቅ ዘንድ (ጠባቂ ያደርጋል)።”

ፈጣሪ መልእክቱ መድረስ አለመድረሱን ለማወቅ መረጃ አቀባይ ያስፈልገዋልን? የፈጣሪ ዕውቀት በመረጃ አቀባዮች ላይ የተመሠረተ ነው ማለት ነው?

“አል-ገይቡል ሙስተቅበል” ሁለት ደረጃ አለው አንዱ አላህ ብቻ የሚያውቀው ሲሆን “ገይበል ሙጥለቅ” الغيب المطلق ሲባል፣ ሁለተኛው ደግሞ አላህ ለሚልከው ነብይ ሲያሳውቅ ያ የሚያሳውቀው የሩቅ ነገር ምስጢር “ገይቡን ኒስቢይ” الغيب النسبي ይባላል፤ አላህ ወደፊት የሚከሰተውን ክስተት አስቀድሞ ለሚወደው ነብይ ይገልጥለታል፦

72፥26-27 «እርሱ ”ሩቁን ምስጢር” ዐዋቂ ነው፡፡ በምስጢሩም ላይ አንድንም አያሳውቅም፡፡»

ከመልክተኛ ለወደደው ቢኾን እንጅ ለሌላ አይገልጽም፡፡

ስለዚህ አንድ ነገር ከመከሰቱ በፊት ያለው ዕውቀት “ዒልሙል ገይብ” ሲባል ከተከሰተ በኃላ የሚገልጠው ዕውቀት “ዒልሙዝ ዛሂር” ይባላል፤ እስቲ “ዒልሙዝ ዛሂር” እንይ፦

ነጥብ ሁለት

“ዒልሙዝ ዛሂር”

“ዒልሙዝ ዛሂር” عِلْمٌ الظَهِير ማለት “ግልፅ ወይም ቅርብ አሊያም ተጨባጭ ዕውቀት”objective knowledge” ማለት ነው፤ “ዛሂር” ظَهِير ማለት “ሸሀደት” شَهَٰدَة “ግልፅ” ወይም “ቅርብ” ማለት ሲሆን አንድ ነገር ከተከሰተ በኃላ ያለውን አላህ ሲገልጥልን “ዐወቀ” እና “እስኪያውቅ” ይለናል፦

2፥187 በጾም ሌሊት ወደ ሴቶቻችሁ መድረስ ለናንተ ተፈቀደላችሁ፡፡ እነርሱ ለእናንተ ልብሶች ናቸው፤ እናንተም ለእነርሱ ልብሶች ናችሁ፡፡ አላህ እናንተ እራሳችሁን የምትበድሉ መኾናችሁን “ዐወቀ” عَلِمَ ፡፡

73:20 አላህም ሌሊትንና ቀንን ይለክካል፣ ሌሊቱን የማታዳርሱት መኾናችሁን “ዐወቀ” عَلِمَ ፤

8:66 አሁን አላህ ከእናንተ ላይ አቀለለላችሁ፤ በእናንተ ውስጥም ድክመት መኖሩን “ዐወቀ” وَعَلِمَ ፤

“ዐወቀ” ተብሎ የተቀመጠው ቃል “ዐሊመ” عَلِمَ ሲሆን “ዐልለመ” عَلَّمَ ማለትም “ዓሳወቀ” “ገለጠ” “ለየ” በሚል ቃል ይመጣል፦

በዚህ ቦታ ላይ የገባው ቃል “ዐሊመ” (ዐወቀ) የሚል እንጂ “ዐለመ” (ዓሳወቀ) የሚል አይደለም፡፡ ከአውዱም እንደምንረዳው አላህ አንድ ትዕዛዝ ከሰጠ በኋላ ሙስሊሞች መተግበር ሲሳናቸው ሐሳቡን መለወጡንና ይህም ዕውቀቱ ፍፁም አለመሆኑን አመላካች ነው፡፡ ሙሉ አውዱን ለማስቀመጥ ያህል፡-

የጥቅሱ አውድ የሚናገረው ሙስሊሞች ከስንት “ከሃዲያን” ጋር መዋጋት እንዳለባቸው ሲሆን የተለያዩ ትዕዛዛትን ይሰጣል፡-

“አንተ ነቢዩ ሆይ! ምእምናንን በመዋጋት ላይ አደፋፍራቸው፡፡ ከእናንተ ውስጥ ሃያ ታጋሾች ቢኖሩ ሁለት መቶን ያሸንፋሉ፡፡ ከእናንተም መቶ ቢኖሩ ከእነዚያ ከካዱት እነሱ የማያውቁ ሕዝቦች ስለኾኑ ሺህን ያሸንፋሉ፡፡” (ሱራ 8፡65)

በዚህ ጥቅስ መሠረት ሃያ ሙስሊሞች ሁለት መቶን፣ መቶ ደግሞ አንድ ሺህን ይገጥማሉ፡፡ የዚህ ምጥንጥን አንድ ለአሥር ነው፡፡ ቀጥሎ እንዲህ የሚል ትዕዛዝ ይገኛል፡-

“አሁን አላህ ከእናንተ ላይ አቀለለላችሁ፡፡ በእናንተ ውስጥም ድክመት መኖሩን ዐወቀ፡፡ ስለዚህ ከእናንተ መቶ ታጋሾች ቢኖሩ ሁለት መቶን ያሸንፋሉ፡፡ ከእናንተም ሺህ ቢኖሩ በአላህ ፈቃድ ሁለት ሺህን ያሸንፋሉ፡፡ አላህም ከታጋሾቹ ጋር ነው፡፡” (ሱራ 8፡66)

በዚህ ጥቅስ መሠረት ደግሞ መቶ ሙስሊሞች ሁለት መቶን፣ አንድ ሺህ ደግሞ ሁለት ሺህን እንደሚገጥሙ ተነግሯል፡፡ የዚህ ምጥንጥን አንድ ለሁለት ነው፡፡

እነዚህን ትዕዛዛት ከግጭት ለመቁጠር የሚያበቃ ምክንያት አለ፡፡ ኢብን ኢስሐቅ የተሰኘው ዘጋቢ እንደተናገረው አላህ ይህንን ትዕዛዝ በሰጠበት ዕለት ሙስሊሞች ትዕዛዙ ስለከበዳቸው መደናገጣቸውንና አላህ ትዕዛዙን በሌላ ትዕዛዝ በመሻር ሁለተኛውን “መገለጥ እንዳወረደ” ዘግቧል፡፡ (Guillaume, The Life of Muhammad; p. 326)፡፡ አላህ ሁሉን አዋቂ ከሆነ ትዕዛዙ እንደሚከብዳቸው አስቀድሞ በማወቅ ትክክለኛውን ትዕዛዝ ከማውረድ ይልቅ ተግባራዊ ሊሆን የማይችለውን አውርዶ እንደገና መሻር ለምን አስፈለገው? ይህ ትዕዛዝ ከፈጣሪ ሳይሆን ከሙሐመድ አእምሮ የመነጨ መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡

ሁለተኛው ጥቅስ “አሁን አላህ ከእናንተ ላይ አቀለለላችሁ፡፡ በእናንተ ውስጥም ድክመት መኖሩን ዐወቀ” በማለት የአላህን ሁሉን አዋቂነት ከጥርጣሬ ውስጥ ይጨምራል፡፡ አላህ በሙስሊሞች ውስጥ ድካም መኖሩን ያወቀው ትዕዛዙን ከሰጠ በኋላ እንደሆነ ያስመስላልና፡፡

ስለዚህ በቦታው ላይ የሌለ ቃል ከመተካትህም በላይ ሐሳብህ ከአውዱ ጋር የሚሄድ አይደለም፡፡

2፥143 ያችንም በርሷ ላይ የነበርክባትን አቅጣጫ መልክተኛውን የሚከተለውን ሰው ወደ ክህደት ከሚመለሰው ሰው ”ልናውቅ” لِنَعْلَمَ እንጅ ቂብላ አላደረግናትም፡፡

“ልናውቅ” የሚለው ቃል “ሊነዕለማ” لِنَعْلَمَ ሲሆን “ልንገልጽ” ማለት ነው፦

3፥167 እነዚያንም የነፈቁትን እና ለእነርሱ «ኑ፤ በአላህ መንገድ ተጋደሉ፤ ወይም ተከላከሉ፤» የተባሉትን ”ሊገልጽ” وَلِيَعْلَمَ ነው፡፡

ሱራ 8፡66 የገባው “ወ-ዐሊመ” የሚል ቃል ሲሆን “ዐወቀ” የሚል ትርጉም ነው ያለው፡፡ የአላህ ዕውቀት ውሱን መሆኑንም አመላካች ነው፡፡ ከዚህኛው ሱራ ጋር ተመሳሳይ ትርጉም የለውም፡፡

አላህ አንድ ነገር ከመከሰቱ በፊትም ያውቃል ከተከሰተ በኃላም ያውቃል፤ ይህንን የተከሰተ ነገር ግልፅ ስለሆነ ሰዎች ያውቁታል፤ ግን ወደፊት የሚከሰተውን አያውቁም፦

30:7 ከቅርቢቱ ሕይወት ግልጹን ብቻ ያውቃሉ፤ እነርሱም ከኋይለኛይቱ ዓለም እነርሱ ዘንጊዎች ናቸው።

አላህ ግን ግልፁን ማለትም ቅርቡን ዕውቀት እና ስውሩን ማለትም ሩቁን ዕውቀት ሁሉ ያውቃል፦

59:22 እርሱ አላህ ነው፤ያ ከርሱ በቀር ሌላ አምላክ የሌለ፣ ”ሩቁንና ቅርቡን ዐዋቂ የሆነው”፤ እርሱ እጅግ በጣም ርኅሩኅ በጣም አዛኝ ነው።

62:8 ያ ከርሱ የምትሸሹት ሞት እርሱ በእርግጥ አግኛችሁ ነው፤ ከዚያም ”ሩቁንና ቅርቡን ዐዋቂ” ወደ ሆነው ጌታ ትመለሳላችሁ፤

64:18 ”ሩቁን ሚስጢር ግልጹንም ሁሉ ዐዋቂው” አሸናፊው ጥበበኛው ነው።

32:6 ይህንን የሠራው ”ሩቅንም ቅርቡንም ሁሉ ዐዋቂዉ”፣ አሸናፊው፣ አዛኙ ነው።

13:9 ”ሩቁንና ቅርቡን ዐዋቂ” ታላቅ የላቀ ነው።

39:46 ሰማያትንና ምድርን የፈጠርክ፣ ”ሩቁንም ቅርቡም ዐዋቂ” የኾንክ አላህ ሆይ! አንተ በባሮችህ መካከል በዚያ በርሱ ይለያዩበት በነበሩት ነገር ትፈርዳለህ፤ በል።

ስለዚህ አላህ ዐወቀ ማለት የአማርኛችን ዘዬ ላይ እጥረት ስላለው ከዚህ በፊት ያላወቀውን አሁን ዐወቀ ይመስላል፤ ግን አላህ ዐወቀ ማለት የተከሰተውን ነገር ስለገለጠው ታወቀ ዐሳወቀ ማለት “ዒልሙዝ ዛሂር” ማለት ሲሆን ከመከሰቱ በፊት ደግሞ አላህ ብቻ የሚያውቀው ሩቁ ዕውቀት “ዒልሙል ገይብ” ማለት ነው።

“ዐወቀ” እንዲሁም “ዓሳወቀ” ለሚሉት ቃላት የአረብኛ ቋንቋ የተለያዩ ቃላት ስላሉት ምንም የሚያምታታ ነገር የለውም፡፡ የትኛውንም መዝገበ ቃላት ብንመለከት عَلِمَ (ዐሊመ) የሚለው ቃል “ዓወቀ” ተብሎ እንደሚተረጎም ማረጋገጥ እንችላለን፡፡

ከላይ የሚገኘው ከሞላ ጎደል ከጥያቄያች ጋር ግንኙነት የሌለው ሐተታ ነው፡፡ ጥያቄው አጭርና ግልፅ ነው፤ ቁርኣን በአንድ ወገን አላህ ሁሉን አዋቂ እንደሆነ ይናገራል፤ በሌላ ወገን ደግሞ ሁሉን አዋቂ እንዳልሆነ ይናገራል፡፡ የቁርአኑ አላህ፡-

በግምት ይናገራል

53:1 “(ከርሱ) የሁለት ደጋኖች ጫፍ ያህል፣ ወይም (ከዚህ) ይበልጥ የቀረበ ሆነም“And was at a distance of two bow lengths or nearer.”

አላህ ጂብሪል ወደ ሙሐመድ ምን ያህል እንደቀረበ እርግጠኛ መሆን አልቻለም፤ ልክ እንደ ሰው “የሁለት ደጋን ጫፍ ያህል ወይም ከዚያ ይበልጥ” ብሎ ግምቱን ያስቀምጣል፡፡

ይጠራጠራል

11:12 “በርሱ ላይ የገንዘብ ድልብ ለምን አልተወረደም ወይም ከርሱ ጋር መልአክ ለምን አልመጣም ማለታቸውንም በመፍራት ወደ አንተ ከሚወርደው ከፊሉን ልትተው በርሱም ልብህ ጠባብ ሊኾን ይፈራልሃል፤ አንተ አስፈራሪብቻ ነህ፤ አላህም በነገሩ ሁሉ ተጠባባቂ ነው።”

18:6 “በዚህም ንግግር (በቁርኣን) ባያምኑ፣ በፈለጎቻቸው ላይ በቁጭት ነፍስህን አጥፊ ልትሆን ይፈራልሃል።” “Then perhaps you would kill yourself through grief over them, [O Muhammad], if they do not believe in this message, [and] out of sorrow”

26:3 “አማኞች ባለ መሆናቸው፤ (በቁጭት) ነፍስህን ገዳይ መሆን ይፈራልሃል፤” “Perhaps, [O Muhammad], you would kill yourself with grief that they will not be believers.”

አላህ ሙሐመድ ተቀባይነትን በማጣቱ ምክንያት መጥፎ እርምጃ እንዳይወስድ መጠርጠሩን ይነግረዋል፡፡ መጠርጠር የሁሉን አዋቂ አካል ባሕርይ አይደለም፡፡

እርግጠኛ ለመሆን ጊዜንና ሁኔታዎችን መጠበቅ ያስፈልገዋል

“እርሱም ከስተፊቱም ከስተኋላውም ጠባቂዎችን ያደርግለታል። እነሱ ዘንድ ባለው ነገር ዕውቀቱ የከበበና ነገሩንም ሁሉ በቁጥር ያጠቃለለ ሲሆን፣ የጌታቸውን መልክቶች ያደረሱ መሆናቸውን ያውቅ ዘንድ (ጠባቂ ያደርጋል)።”

“That he may know that they have conveyed the messages of their Lord; and He has encompassed whatever is with them and has enumerated all things in number.”

47:31 “ከናንተም ታጋዮቹንና ታጋሾቹን እስከምናውቅ ወሬዎቻችሁንም እስከምንገልፅ ድረስ በእርግጥ እንሞክራችኋለን።”

3:140 “ቁስል ቢያገኛችሁ ሰዎቹንም መሰሉ ቁስል አግኝቷቸዋል፤ ይኽችንም ቀናት በሰዎች መካከል እናዘዋዉራታለን፤ (እንድትገሠጹና) አላህም እነዚያን ያመኑትን እንዲያዉቅ (እንዲለይ)፣ ከናንተም ሰማዕታትን እንዲይዝ ነዉ፤ አላህም በዳዮችን አይወድም።”

በነዚህ ጥቅሶች መሠረት ደግሞ አላህ አንድን ነገር ለማወቅ ጊዜ እንደሚወስድበትና ዕውቀትን ለማግኘትም ልክ እንደ ሰው ጊዜንና ሁኔታን መጠበቅ እንደሚያስፈልገው እናያለን፡፡

ስለዚህ ቁርኣን በአንድ ወገን አላህ ሁሉን አዋቂ መሆኑን ከተናገረ በኋላ በሌላ ወገን ደግሞ በሁሉን ቻይነቱ ላይ ጥርጣሬን የሚያጭሩ ነገሮችን ይናገራል፤ ይህም ግልፅ ግጭት ነው፡፡ ለዚህ  ነው ግጭቱን በአጭሩ እንደመመለስ አላስፈላጊ ሐተታ ውስጥ በመግባት የአንባቢን ሐሳብ ለመበተን የጣርከው፡፡

እስቲ ይህንን ሙግት ይዘን ለንፅፅር ወደ ባይብል እንግባ፤ አንድ ነቢይ ወይም ሕልም አላሚ ቢነሣ፥ ምልክትም ተአምራትም ቢሰጥህ፥ እንደ ነገረህም ምልክቱ ተአምራቱም ቢፈጸም፥ እርሱም። ሄደን የማታውቃቸውን ሌሎች አማልክት እንከተል እናምልካቸውም ቢል፤ ትወድዱት እንደ ሆነ ያውቅ ዘንድ እግዚአብሔር ሊፈትናችሁ ነውና ተብሏል፤ አምላክ የሰውን መውደድ ለማወቅ ይፈትናል? “ዒልሙዝ ዛሂር” ነው ካላችሁ የቋንቋ ሙግት አሊያም የሰዋስው ሙግት ማቅረብ ይጠበቅባችኃል፦

ዘዳግም 13፥1-3 በመካከልህም ነቢይ ወይም ሕልም አላሚ ቢነሣ፥ ምልክትም ተአምራትም ቢሰጥህ፥ እንደ ነገረህም ምልክቱ ተአምራቱም ቢፈጸም፥ እርሱም። ሄደን የማታውቃቸውን ሌሎች አማልክት እንከተል እናምልካቸውም ቢልህ፥ አምላካችሁን እግዚአብሔርን በፍጹም ልባችሁ በፍጹምም ነፍሳችሁ ትወድዱት እንደ ሆነ ያውቅ ዘንድ አምላካችሁ እግዚአብሔር ሊፈትናችሁ ነውና የዚያን ነቢይ ቃል ወይም ያን ሕልም አላሚ አትስማ።

አምላክ እንዴት ትእዛዙን ይጠብቃል ወይም አይጠብቅም ብሎ 40 ዓመት ይመራል?፦

ዘዳግም 8፥2 አምላክህ እግዚአብሔር ይፈትንህ ዘንድ፥ በልብህም ያለውን ትእዛዙን ትጠብቅ ወይም አትጠብቅ እንደሆነ ያውቅ ዘንድ፥ ሊያስጨንቅህ በእነዚህ በአርባ ዓመታት በምድረ በዳ የመራህን መንገድ ሁሉ አስብ።

የምጣዱ እያለ የእንቅቡ ተንጣጣ ወይንም ቅቤ አንጣሪዋ እያለች ጎመን ቀንጣሽዋ ምች መታት ይላል ያገሬ ሰው፤ ይህ ሂስ እያለ ቁርኣን ላይ መጠንጠል ምን አመጣው? በሰፈሩት ቁና መሰፈር እንዲህ ነው።

በመግቢያችን ላይ እንዳልነው እነዚህን የግጭት ዝርዝሮች ስናቀርብ ዓላማችን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የምታቀርቡት የገዛ ሙግታችሁ በቁርኣን ላይ ሲተገበር ምን እንደሚፈጠር ዐይታችሁ በአባይ ሚዛን መጠቀም እንድታቆሙ ማሳሰብ ነው፡፡ መሰል ጥያቄዎችን አስቀድማችሁ ያነሳችሁት እናንተ በመሆናችሁ ከቁርኣን ውስጥ ተመሳሳይ ነገር ስናሳያችሁ መልሳችሁ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ጥቅሶችን የምታሳዩን ከሆነ ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች መቼም ቢሆን ከክርክር አዙሪት ላይወጡ ነው፡፡

ለማንኛውም በዚህ ቦታ “ያውቅ ዘንድ” ተብሎ የተተረጎመው የእብራይስጥ ቃል የእስትሮንግ ቁጥር 3045 ላይ የሚገኘው “ያዳዕ” የሚል ሲሆን በስትሮንግ መዝገበ ቃላት መሠረት ተከታዮቹ ትርጉሞች አሉት፡-

3045 yada` yaw-dah’ – a primitive root; to know (properly, to ascertain by seeing);
used in a great variety of senses, figuratively, literally, euphemistically and inferentially (including observation, care, recognition; and causatively, instruction, designation, punishment, etc.) (as follow):–acknowledge, acquaintance(-ted with), advise, answer, appoint, assuredly, be aware, (un-)awares, can(-not), certainly, comprehend, consider, X could they, cunning, declare, be diligent, (can, cause to) discern, discover, endued with, familiar friend, famous, feel, can have, be (ig-)norant, instruct, kinsfolk, kinsman, (cause to let, make) know, (come to give, have, take) knowledge, have (knowledge), (be, make, make to be, make self) known, + be learned, + lie by man, mark, perceive, privy to, X prognosticator, regard, have respect, skilful, shew, can (man of) skill, be sure, of a surety, teach, (can) tell, understand, have (understanding), X will be, wist, wit, wot. (Source: Iota Bible Software)

ከላይ የሚገኘውን የመዝገበ ቃላት ትርጉም ያስቀመጥነው ቃሉ ምን ያህል ጥልቅና ሰፊ ትርጉም እንዳለው ለማሳየት ያህል ነው፡፡ በቀይ ቀለም ደምቀው የሚታዩት አማራጭ ትርጉሞች በሙሉ የእግዚአብሔር ሁሉን አዋቂነት ለጥያቄ ሳይቀርብ የሚተረጎምባቸው መንገዶች ናቸው፡፡ ነገር ግን አብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ባስቀመጡት መንገድ እንኳ ቢሆን በእግዚአብሔር ሁሉን አዋቂነት ላይ ጥያቄ ሊያስነሳ አይችልም፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ጊዜ በሰውኛ ዘይቤ (Anthropomorphism) ራሱን ሲገልጥ እንመለከታለን፡፡ ይህም የሰው ልጆችን የመግባቢያ መንገዶች በመጠቀም በሰውኛ ዘይቤ ይናገራል፡፡ እንዲህ ያለው ንግግር ዘይቤያዊ ወይንም ተምሳሌታዊ ብቻ ሲሆን የእግዚአብሔርን ሁሉን ቻይነትና ሁሉን አዋቂነት ለጥያቄ ለማቅረብ የታለመ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር አምላክ በፍጥረት ቋንቋና ምህዳር ራሱን ከሚገልጥባቸው መንገዶች መካከል አንዱ ሲሆን ተምሳሌታዊ ወይም ዘይቤያዊ ብቻ ናቸው፡፡

የቁርአኑ አላህ ንግግር በዚህ መንገድ ሊታይ አይችልምን? አዎ አይችልም፤ ምክንያቱም ሙስሊሞች (በተለይም አክራሪ ሰለፊስቶች) አላህ በፍጥረት ዘይቤና ምሕዳር መገለጥ መቻሉን አይቀበሉምና፡፡ አላህ ከሰው እጅግ የራቀ፣ ወደ ሰው የማይቀርብ፣ ከሰው ጋር ሕብረት የሌለው አምላክ ነው፡፡ ስለዚህ ሰውኛ ዘይቤዎችን (Anthropomorphism) ተጠቅሞ መናገር አይችልም፡፡

የቁርኣን ግጭቶች