28. ሙስሊሞች ከክርስቲያኖች ጋር እንዲወዳጁ ተፈቅዷል ወይስ አልተፈቀደም?
ማሳሰብያ፡- በሰማያዊ የተጻፈው የኛ ሲሆን በጥቁር የተጻፈው የእርሱ ነው፡፡
ተፈቅዷል፡-
ሱራ 5:82 “ይሁዶችንና እነዚያን ያጋሩትን፣ ለነዚያ ለአመኑት በጠላትነት ከሰዎች ሁሉ ይበልጥ የበረቱ ሆነው በእርግጥ ታገኛለህ፤ እነዚያንም እኛ ክርስቲያኖች ነን ያሉትን ለነዚያ ለአመኑት በወዳጅነት በእርግጥ ይበልጥ የቀረቧቸው ሆነው ታገኛለህ፤ ይህ ከነሱ ውስጥ ቀሳውስትና መነኮሳት በመኖራቸውና እነሱም የማይኮሩ በመሆናቸው ነው።”
አልተፈቀደም፡-
ሱራ 5:51 “እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ይሁዶችንና ክርስቲያኖችን ረዳቶች አድርጋችሁ አትያዙ፤ ከፊላቸው ለከፊሉ ረዳቶች ናቸው፤ ከናንተም ውስጥ ረዳቶች የሚያደርጋቸው ሰው እርስ ከነርሱ ነው፤ አላህ አመጠኞችን ሕዝቦች አያቀናም።”
መልስ
“ጠላትነት” እና “ወዳጅነት” ሁለት ጠርዝ ነው። እዚህ አንቀጽ ላይ አይሁዶችና እነዚያን ያጋሩት ለአማንያን ጠላትነት አላቸው አለ እንጂ አይሁዶችና እነዚያን ያጋሩት ጥሉ አይልም። እንዲሁ ክርስቲያኖች ለአማንያን ወዳጅነት አላቸው አለ እንጂ ክርስቲያኖች ውደዱ አይልም። “ሙስሊሞች ከክርስቲያኖች ጋር እንዲወዳጁ ተፈቅዷል” የሚል እሳቤ ጭራሹኑ የለም።
“አይሁድን ጥሉ ተብሏል፤ ክርስቲያኖችን ውደዱ ተብሏል” ያለው ማን ነው? ለምን ያልተባለውን ትላለህ? ወዳጅነትና ጠላትነት የፍቅር ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የእስትራቴጂም ሊሆን ይችላል፡፡ ሲጀመር እስልምና ፖለቲካ በመሆኑ እንዲህ ያሉ ቃላትን በፖለቲካዊ ትርጉማቸው እንደሚጠቀማቸው አይጠፋንም፡፡ “ሙስሊሞች ከክርስቲያኖች ጋር እንዲወዳጁ ተፈቅዷል የሚል እሳቤ ጭራሹኑ የለም” ያልከውን በቀጣዩ አንቀፅ አፍርሰኸዋል፡-
“መወዳህ” مَّوَدَّة ማለት “ፍቅር” ማለት ነው። ይህ አንቀጽ የወረደበት ምክንያት ንጉሥ ዐርማህን እና ባልደረቦቹን በተመለከተ ነው። እርሱ ጋር ቀሳውስትና መነኮሳት በመኖራቸውና እነርሱም የማይኮሩ በመኾናቸው ነው። ወደ መልክተኛውም የተወረደውን ቁርኣን በሰሙ ጊዜ እውነቱን ከማወቃቸው የተነሳ ዓይኖቻቸው እንባን የሚያፈሱ ነበሩ፦
5፥83 “ወደ መልክተኛውም የተወረደውን ቁርኣን በሰሙ ጊዜ እውነቱን ከማወቃቸው የተነሳ ዓይኖቻቸው እንባን ሲያፈሱ ታያለህ”፡፡ «ጌታችን ሆይ! አመንን ከመስካሪዎቹም ጋር ጻፈን » ይላሉ፡፡ እነዚህ ቁርኣንን አምነው ከመስካሪዎቹ የሆኑት ናቸው።
ስለዚህ ጥቅሱ ወደ አክሱም ስለተሰደዱት ሙስሊም ስደተኞች እና ክርስቲያኖች ስለ ነበሩት ስለ ንጉሡና በዙርያው ስለነበሩት ሰዎች ከተናገረ “ሙስሊሞች ከክርስቲያኖች ጋር እንዲወዳጁ ተፈቅዷል የሚል እሳቤ ጭራሹኑ የለም” እንዴት ልትል ትችላለህ? የጥቅሱ ታሪካዊ ዳራ የሚነግርህ የመጀመርያዎቹ ሙስሊሞች ክርስቲያኖችን ተወዳጅተው ከጥፋት ስለመዳናቸው ሆኖ ሳለ “ሙስሊሞች ከክርስቲያኖች ጋር እንዲወዳጁ ተፈቅዷል የሚል እሳቤ ጭራሹኑ የለም” ብሎ ማለት ትርጉም አይሰጥም፡፡
እስላማዊ ትውፊቶች እንሚናገሩት ወደ አክሱም የመጡት ሙስሊሞች እስልምና ስለ ኢየሱስ ማንነት የሚያስተምረውን ትምሕርት ከፊሉን እንጂ ሙሉውን አልነገሯቸውም፡፡ ኢየሱስ ከድንግል ስለመወለዱ፣ የአላህ ቃልና መንፈስ ስለመሆኑ፣ ወዘተ. ነው የነገሯቸው፡፡ ያነበቡትም የቁርኣን ጥቅስ ገብርኤል የተናገረውን ብስራት የሚያትተውን ነው፡፡ ይህንን የሰማ ማንኛውም ሰው ከክርስቲያናዊ አስተምሕሮ ጋር ተስማሚ ሆኖ ሊያገኘው ይችላል፡፡ ስለዚህ ንጉሡና አጃቢዎቹ ማልቀሳቸው እስልምናን በመቀበላቸው ምክንያት ሳይሆን ሙስሊሞቹ ከክርስቲያናዊ አስተምሕሮ ጋር የሚስማማ ነገር በመናገር ስላታለሏቸው ነው፡፡ (Martin Lings, Muhammad, His Life Based on the Earliest Sources, p. 83) (Alfred Guillaume, The Life of Muhammad, A Translation of Ibn Ishaq’s Sirat Rasul Allah, 1995, p. 152)
እንዲህ ያለ የማታለል ታሪክ ይዘህ ክርስቲያኖች እንደሰለሙ ለመናገር መድፈርህ የሚገርም ነው፡፡
በተረፈ አይደለም ክርስቲያን እና አይሁድ ማንንም ከምእምናን ሌላ ረዳቶች አድርገን አንይዝም፦
3፥28 “ምእምናን ከሓዲዎችን ከምእምናን ሌላ ረዳቶች አድርገው አይያዙ፡፡ ይኼንንም የሚሠራ ሰው ከአላህ ሃይማኖት በምንም ውስጥ አይደለም”፡፡ ከእነርሱ መጥጠበቅን ብትጠበቁ እንጂ፡፡ አላህ እራሱ ያስጠነቅቃችኋል፡፡ መመለሻም ወደ አላህ ብቻ ነው፡፡
ሙሐመድና የመጀመርያዎቹ ሙስሊሞች ግን ክርስቲያኖችን ረዳት አድርገው ከመያዛቸውም በላይ ጠላቶቻቸው ሲያሳድዷቸው ወደ እነርሱ ሸሽተው ተጠልለዋል፡፡
5፥51 እናንተ ያመናችሁ ሆይ! “አይሁዶችንና ክርስቲያኖችን ረዳቶች አድርጋችሁ አትያዙ፡፡ ከፊላቸው ለከፊሉ ረዳቶች ናቸው፡፡ ከእናንተም ውስጥ ረዳቶች የሚያደርጋቸው ሰው እርሱ ከእነርሱ ነው”፡፡ አላህ አመጸኞችን ሕዝቦች አያቀናም፡፡
ሙሐመድና የመጀመርያዎቹ ሙስሊሞች ክርስቲያኖችን ረዳት አድርገው ይዘዋል፡፡ አንተም ይህን አልካድክም፡፡
እዚህ አንቀጽ ላይ “አውሊያ” أَوْلِيَاءَ በብዜት የመጣው “ወሊይ” وَلِىّ ለሚለው ብዙ ቁጥር ነው፥ “ወሊይ” ማለት “እረዳት” ማለት ነው። በመልካም በማዘዝ በመጥፎ በመከልከል ለአማኞች ወሊይ እራሳቸው አማኞች እንጂ ከሃድያን ወሊይ አይደሉም፦
“በመልካም በማዘዝ በመጥፎ በመከልከል” የሚል ሐረግ ማስገባትህ የቁርኣን ደራሲ በደፈናው “አይሁዶችንና ክርስቲያኖችን ረዳቶች አድርጋችሁ አትያዙ” ብሎ ማለቱ ከእውነታ ያፈነገጠ፣ ተግባራዊ ሊደረግ የማይችል ከንቱ ትዕዛዝ መሆኑ ስለገባህ ይመስለኛል፡፡ ሙስሊሞች በየትኛውም ዘመን በይሁድና በክረስቲያኖች ላይ ጥገኛ ሳይሆኑ ኖረው አያውቁም፡፡ የመጀመርያዎቹ ሙስሊሞች ሕልውናቸውን ለማስቀጠል በክርስቲያኖች ላይ ጥገኞች ነበሩ፡፡ እስከ ዛሬ ድረስም በንግድና በወታደራዊ አሰላለፍ ሙስሊም አገራት በክርስቲያኖችና በአይሁድ ላይ ጥገኛ ሆነው እናያቸዋለን፡፡ ይህ የሙሐመድ ትዕዛዝ እንኳንስ በሌሎች ሙስሊሞች ሊተገበር ይቅርና በራሱ በሙሐመድ እንኳ ሊተገበር ያልቻለ ከንቱ ትዕዛዝ ነው፡፡
9፥71 “ምእምንና ምእምናትም ከፊሎቻቸው ለከፊሉ ረዳቶች ናቸው፡፡ በደግ ነገር ያዛሉ፤ ከክፉም ይከለክላሉ”፡፡ ሶላትንም ይሰግዳሉ፡፡ ዘካንም ይሰጣሉ፡፡ አላህንና መልክተኛውንም ይታዘዛሉ፡፡ እነዚያን አላህ በእርግጥ ያዝንላቸዋል፡፡ አላህ አሸናፊ ጥበበኛ ነውና፡፡
ይህ ወደ ሺክር የሚያመራ ወዳጅነት በትንሳኤ ቀን፦ “ዋ ጥፋቴ! እገሌን ወዳጅ ባልያዝኩ ኖሮ እመኛለሁ” የሚያስብል ጸጸት ነውና እንጠንቀቅ፦
25፥28 «ዋ ጥፋቴ! “እገሌን ወዳጅ ባልያዝኩ ኖሮ እመኛለሁ”፡፡
ቁርኣን በአንዱ ቦታ ላይ አይሁድና ክርስቲያኖችን መወዳጀት ኃጢአት መሆኑን ይናገራል በሌላ ቦታ ላይ ግን መወዳጀት እንደሚቻል ይናገራል፡፡ ሙሐመድና ተከታዮቹም ተወዳጅተዋል፡፡ ቁርኣን ሙስሊም ወንዶች አይሁድና ክርስቲያን ሴቶችን እንዲያገቡ መፍቀዱንም ማስታወስ ያስፈልጋል (ሱራ 5፡5)፡፡ ከትዳር የበለጠ ወዳጅነት ምን አለ? ይህ ግልፅ ግጭት ነው፡፡ ሙስሊሞች ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር ሳይወዳጁ መኖር አለመቻላቸውን አእምሮ ያለው ሰው ሁሉ ሊስተው የማይችለው እውነታ ነው፡፡ ይህ የቁርኣን ትዕዛዝ እርባና ቢስ ነው፡፡ የዘመናዊቷ ቱርክ መሥራች ሙስጠፋ ከማል አታቱርክ ቁርኣንን በመስኮት ወደ ውኀ መወርወሩ ያለምክንያት አልነበረም፡፡