31. ዮናስ በምድረ በዳ ተጥሏል ወይስ አልተጣለም?
ማሳሰብያ፡- በሰማያዊ የተጻፈው የኛ ሲሆን በጥቁር የተጻፈው የእርሱ ነው፡፡
አልተጣለም፡-
ሱራ 68:49 “ከጌታው የሆነ ጸጋ ባላገኘው ኖሮ፣ በምድረ በዳ ተወቃሽ ሆኖ በተጣለ ነበር።”
ተጥሏል፡-
ሱራ 37፡145 “እርሱ በሽተኛ ሆኖ በቃይ በሌለው በባሕር ዳርቻ ላይ ጣልነውም፡፡”
መልስ
የዓሳውንም ባለቤት ዩኑስ ዓሳም ዋጠው፥ በዓሳው ሆድ ጨለማዎች ውስጥ ኾኖ አላህን፦ “ከአንተ በቀር ሌላ አምላክ የለም፡፡ ጥራት ይገባህ፡፡ እኔ በእርግጥ ከበዳዮቹ ነበርኩ” በማለት ተጣራ። አላህም ጥሪውን ተቀበለው፥ ከጭንቅም አዳነው፦
21፥87 የዓሳውንም ባለቤት ተቆጥቶ በኼደ ጊዜ አስታውስ፡፡ በእርሱም ላይ ፈጽሞ የማንፈርድበት መኾናችንን ጠረጠረ፡፡ ዓሳም ዋጠው፥ በጨለማዎችም ውስጥ ኾኖ ከአንተ በቀር ሌላ አምላክ የለም፡፡ ጥራት ይገባህ፡፡ እኔ በእርግጥ ከበዳዮቹ ነበርኩ በማለት ተጣራ፡፡
21፥88 ”ለእርሱም ጥሪውን ተቀበልነው፡፡ ከጭንቅም አዳነው”፡፡ እንደዚሁም ምእመናንን እናድናለን፡፡
ዩኑስ ከዓሳው ሲወጣ በሽተኛ ሆኖ በቃይ በሌለው በባሕር ዳርቻ ላይ ጣለው፦
37፥145 ”እርሱ በሽተኛ ሆኖ በቃይ በሌለው በዳርቻ ላይ ጣልነውም”፡፡
ልብ አድርግ ምን ሆኖ “በሽተኛ” ሆኖ። የት ላይ ነው የተጣለው? “በባሕር ዳርቻ” አስተውል! ከጌታው የኾነ ጸጋ ባላገኘው ኖሮ በምድረ በዳ ተወቃሽ ኾኖ በተጣለ ነበር፦
68፥49 ”ከጌታው የኾነ ጸጋ ባላገኘው ኖሮ በዳርቻ ተወቃሽ ኾኖ በተጣለ ነበር”፡፡
“ዐራ” عَرَآء ማለት “ዳርቻ” ማለት ነው። የባሕር ዳርቻ ከጌታው የኾነ ጸጋ ባላገኘው ኖሮ በሽተኛ ሳይሆን ተወቃሽ ኾኖ በተጣለ ነበር። ነገር ግን በሽተኛ ኾኖ ተጣለ። ስለዚህ ቁርኣንን ከመተቸት በፊት “በሽተኛ” እና “ተወቃሽ” የሚሉትን ሃይለ-ቃል አጥኑ። “መዝሙም” مَذْمُوم ማለት “ተወቃሽ” ማለት ሲሆን በራስ ስህተት የሚመጣ ወቀሳን ያሳያል፥ ተወቃሽነት ተውበት ካልታከለበት ያስቀጣል፦
17፥18 ቸኳይቱን ዓለም በሥራው የሚፈልግ ሰው ለእርሱ በርሷ ውስጥ የሻነውን ጸጋ ለምንሻው ሰው እናስቸኩልለታለን፡፡ ”ከዚያም ለእርሱ ገሀነምን መኖሪያ አድርገንለታል፡፡ “ተወቃሽ” ብራሪ ኾኖ ይገባታል”፡፡
“ሠቂም” سَقِيم ማለት ግን “በሽተኛ” ማለት ሲሆን በሽታ የጤና መታወክ እንጂ የሚያስቀጣ የሚያስጠይቅ ነገር አይደለም።
ምላሹ ባጠቃላይ ዮናስ ንስሐ ባይገባ ኖሮ ለዘላለም ጥፋት በሚዳርግ ወቀሳ ውስጥ ሆኖ በባሕሩ ዳርቻ በተጣለ ነበር ነገር ግን ንስሐ ስለገባ በሽተኛ ሆኖ ተጣለ የሚል ነው፡፡ ይህንን ግጭት ለማስታረቅ የሞከረው ሰው “ተወቃሽ” (መዝሙሙን) የሚለውን ቃል በዚህ መንገድ ማብራራቱ ሌላ ግጭት ያስከትላል፡፡ ሱራ 37፡142-145 ላይ እንደተመለከተው ዮናስ ንስሐ ባይገባ ኖሮ አላህ እስከ ዕለተ ትንሣኤ ድረስ በዓሣው ሆድ ውስጥ እንዲቆይ ባደረገው ነበር፡-
“እርሱም ተወቃሽ ሲሆን ዐሳው ዋጠው፡፡ እርሱ ለጌታው ከአወዳሾቹ ባልሆነም ኖሮ፤ እስከሚቀሰቀሱበት ቀን ድረስ በሆዱ ውስጥ በቆየ ነበር፡፡ እርሱ በሽተኛ ሆኖ በቃይ በሌለው (በባሕር) ዳርቻ ላይ ጣልነውም፡፡”
በዚህ ጥቅስ መሠረት ዮናስ በዓሣ ከተዋጠ በኋላ በተግባሩ ተፀፅቶ ወደ አምላኩ ባይመለስ ኖሮ በዓሣው ሆድ ውስጥ እስከ ዕለተ ትንሣኤ ድረስ ይቆይ ነበር፡፡ ሱራ 21፡87 ዮናስ በዓሣው ሆድ ውስጥ ሆኖ ስላቀረበው ንስሐ እንዲህ ተብሏል፡-
“የዐሣውንም ባለቤት ተቆጥቶ በኼደ ጊዜ (አስታውስ)፤ እርሱም ላይ ፈጽሞ የማንፈርድበት መሆናችንን ጠረጠረ፤ (ዐሳም ዋጠው)፤ በጨለማዎችም ውስጥ ሆኖ ፦ ከአንተ በቀር ሌላ አምላክ የለም፤ ጥራት ይገባህ፤ እኔ በእርግጥ ከበዳዮቹ ነበርኩ በማለት ተጣራ፡፡”
ከዚህ በተጻራሪ ሱራ 68:49 “ከጌታው የሆነ ጸጋ ባላገኘው ኖሮ፣ በምድረ በዳ ተወቃሽ ሆኖ በተጣለ ነበር” ይላል፡፡ ስለዚህ ወቀሳ የተባለው ንስሐ ገብቶ የኃጢአት ይቅርታን አለማግኘት ተብሎ ከተተረጎመ ዮናስ ለኃጢአቱ ንስሐ ገብቶ ይቅርታን ባያገኝ ኖሮ አላህ ምን ያደርገው ነበር? ለሚለው ጥያቄ ጥቅሶቹ እርስ በርሳቸው የተጣረሱ ምላሾችን ነው የሚሰጡት፡፡ በመጀመርያው ጥቅስ መሠረት በዓሣ ሆድ ውስጥ እስከ ዕለተ ትንሣኤ የሚቆይ ሲሆን በሁለተኛው ጥቅስ መሠረት ተወቃሽ ሆኖ በባሕሩ ዳርቻ ይጣል ነበር፡፡ የቱ ነው ትክክል? ስለዚህ ቁርኣን ሱራ 37፡142-145 ላይ ዮናስ ንስሐ ባይገባ ኖሮ በዓሣው ሆድ ውስጥ እስከ ዕለተ ትንሣኤ እንደሚኖር ስለነገረን (እንዴት ሆኖ የሚለው በራሱ ሌላ ጥያቄ ቢሆንም) “ተወቃሽ ሆኖ በተጣለ ነበር” የሚለውን ንስሐ ባይገባ ኖሮ የሚደርስበት ቅጣት አድርጎ መተርጎም ትክክል አይደለም፡፡ አለበለዚያ ግጭት በመፍታት ፋንታ ሌላ ግጭት መፍጠር ይሆናል፡፡ ይህም ጥያቄ እንደ ሌሎቹ ሁሉ ምላሽ አላገኘም፡፡