የቁርኣን ግጭቶች – ህፃናት ጡት እንዲጥሉ አላህ ያዘዘው ከምን ያህል ጊዜ በኋላ ነው?

32. ሕፃናት ጡት እንዲጥሉ አላህ ያዘዘው ከምን ያህል ጊዜ በኋላ ነው?

ማሳሰብያ፡-በሰማያዊ የተጻፈው የኛ ሲሆን በጥቁር የተጻፈው የእርሱ ነው፡፡

ከ30 ወራት በኋላ፡-

ሱራ 46:15 “ሰውንም በወላጆቹ በጎ መዋልን በጥብቅ አዘዝነው እናቱ በችግር ላይ ሆና አረገዘችው በችግርም ወለደችው፥ እርግዝናውና ከጡት መለያውም ሠላሳ ወር ነው።

ከሁለት ዓመት (ከ24 ወራት) በኋላ፡-

ሱራ 31:14 “ሰውንም በወላጆቹ (በጎ እንዲያደርግ ) በጥብቅ አዘዝነው፤ እናቱ ከድካም በላይ በሆነ ድካም አረገዘችው፤ ጡት መጣያውም በሁለት ዓመት ውስጥ ነው፤ ለኔም ለወላጆችህም አመስግን በማለት (አዘዝነው)፤ መመለሻው ወደኔ ነው።”

መልስ

46፥15 ሰውንም በወላጆቹ በጎ መዋልን በጥብቅ አዘዝነው፡፡ እናቱ በችግር ላይ ኾና አረገዘችው፡፡ በችግርም ወለደችው፡፡ ”እርግዝናው እና ጡት መለያውም ሠላሳ ወር ነው”፡፡

“ሠላሳ ወር” ማለት “ሁለት ዓመት ከስድስት ወር” ነው፥ “እርግዝና” እና “ጡት መለያው” ሁለት ዑደት ነው። እርግዝና በአማካኝ ዘጠኝ ወር ሲሆን ሠላሳ ወሩ የሚቆጠረው ከእርግዝናው ሲሆን ጡት መጣያውን ለማግኘት ከሠላሳ ወር ላይ ዘጠኝ ወር መቀነስ ነው። ውጤቱ “ሃያ አንድ ወር” አሊያም አንድ ዓመት ከዘጠኝ ወር ይሆናል ማለት ነው። አንድ ዓመት ከዘጠኝ ወር ደግሞ በሁለት ዓመት ውስጥ ያለ ቁጥር ነው፦

31፥14 ሰውንም በወላጆቹ በጎ እንዲያደርግ በጥብቅ አዘዝነው፡፡ እናቱ ከድካም በላይ በሆነ ድካም አረገዘችው፡፡ ”ጡት መጣያውም በሁለት ዓመት ውስጥ ነው”፡፡ ለእኔም ለወላጆችህም አመስግን በማለት አዘዝነው፡፡ መመለሻው ወደ እኔ ነው፡፡

“ፊ” ማለት فِي “ውስጥ” ማለት እንጂ “በኃላ” ማለት አይደለም። “በኃላ” የምትለዋ የሚሽነሪዎች ቅጥፈት ናት። እንደውም እናት ወተት ኖሯት ማጥባት ከቻለች ሁለት ዓመታት ሙሉውን ታጠባለች፦

2፥233 ”እናቶችም ልጆቻቸውን ሙሉ የኾኑን ሁለት ዓመታት ያጥቡ፡፡ ይህም ማጥባትን መሙላት ለሻ ሰው ነው”፡፡

“አንድ ዓመት ከዘጠኝ ወር ጡት መለያውም” የተባለው እና “ጡት መጣያውም በሁለት ዓመት ውስጥ ነው” የተባለው ትእዛዛዊ መርሕ ሳይሆን አብዛኛው ላይ ያለውን ጥቅላዊ ደንብ ነው። “ሙሉ የኾኑን ሁለት ዓመታት ያጥቡ” ግን ቀመራዊ መርሕ ነው። ይህም ማጥባትን መሙላት ለፈለገች እናት ነው።

ጥቅሶቹን እንመልከታቸው፡-

ሱራ 46:15 “…እርግዝናውና ከጡት መለያውም ሠላሳ ወር ነው” – በዚህ ጥቅስ መሠረት የእርግዝና ጊዜ ሲደመር ጡት የመጥባት ጊዜ ሠላሳ ወር ነው፡፡ “ሠላሳ ወር ነው” ሲል ያው ሠላሳ ወር ማለት ነው፡፡ ሃያ ዘጠኝ አይደለም፤ ሰላሳ አንድ አይደለም፤ ሠላሳ ወር ነው፡፡ ስለዚህ ከሠላሳ ወር ላይ ዘጠኝ የእርግዝና ወራትን ስንቀንስ (በጸሐይ አቆጣጠር ማለት ነው) ሃያ አንድ ወራትን፣ ማለትም ዓመት ከዘጠኝ ወር እናገኛለን፡፡ ቆጠራው በእስልምና ካሌንደር ከሆነ ደግሞ የእርግዝና ጊዜ በጨረቃ አቆጣጠር አሥር ወራት ነው የሚሆነው፤ ስለዚህ የጥቢ ገደብ ዓመት ከስምንት ወር ይሆናል ማለት ነው፡፡

ሱራ 31:14 “…ጡት መጣያውም በሁለት ዓመት ውስጥ ነው,..” – በዚህ ጥቅስ መሠረት ጡት የመጣያ ገደብ ሁለት ዓመት ነው፡፡ በሁለት ዓመት ውስጥ ማለት በሁለት ዓመት የጊዜ ገደብ ውስጥ ማለት ነው፡፡ ሁለት ዓመት ትልቁ የጥቢ ጣርያ መሆኑ በተከታዩ ጥቅስ ተጠናክሯል፡-

ሱራ 2፡233 ”እናቶችም ልጆቻቸውን ሙሉ የኾኑን ሁለት ዓመታት ያጥቡ፡፡ ይህም ማጥባትን መሙላት ለሻ ሰው ነው”፡፡

ስለዚህ ጥቢ ሙሉ የሚባለው ሁለት ዓመት ሲሞላ ሲሆን ከዚያ በታች በሆነ ጊዜ ጡት ማስጣል ይቻላል፡፡ ሁለት ዓመት ገደብ እንጂ ግዴታ አይደለም፡፡ ይህ ግልፅ ከሆነልን ግጭቱ የት ጋር እንዳለ ማስተዋል አይቸግረንም፡፡ ለዚህ ግጭት መልስ ለመስጠት የሞከረው ሰው ዓመት ከዘጠኝ ወር በሁለት ዓመት ውስጥ ስለሚገኝና ጥቅሱ በሁለት ዓመት ውስጥ ስለሚል አይጋጭም የሚል ማብራርያ ሰጥቷል፡፡ ነገር ግን ጥቅሶቹ ስለ ጥቢ ገደብ የሚናገሩ መሆናቸውን አላስተዋለም፡፡ ሱራ 46:15 ገደቡን በዓመት ከዘጠኝ ወር የወሰነ ሲሆን ሱራ 31:14 እና ሱራ 2፡233 ደግሞ በሁለት ዓመታት ገደብ ወስነዋል፡፡ ስለዚህ የቱ ነው ትክክል? መልስ ያላገኘ ጥያቄ ነው፡፡

የቁርኣን ግጭቶች