የቁርኣን ግጭቶች – ዒሳ እንደ ማንኛውም ሰው የሆነ ሰው ወይንስ የአላህ ቃልና መንፈስ ብቻ?

35. ዒሳ እንደ ማንኛውም ሰው የሆነ ሰው ወይንስ የአላህ ቃልና መንፈስ ብቻ?

ማሳሰብያ፡- በሰማያዊ የተጻፈው የኛ ሲሆን በጥቁር የተጻፈው የእርሱ ነው፡፡

እንደ ማንኛውም ሰው የሆነ ሰው፡-

5፡75 “የመርየም ልጅ አልመሲሕ ከበፊቱ መልክተኞች በእርግጥ ያለፉ የሆነ መልክተኛ እንጅ ሌላ አይደለም፤ እናቱም በጣም እውነተኛ ናት፤ (ሁለቱም) ምግብን የሚበሉ ነበሩ፤ አንቀጾችን ለነርሱ (ለከሐዲዎች) እንዴት እንደምናብራራ ተመልከት፤ ከዚያም (ከውነት) እንዴት እንደሚመለሱ ተመልከት።”

የአላህ ቃልና መንፈስ ብቻ፡-

4፡171 “እናንተ የመጽሐፉ ሰዎች ሆይ! በሃይማኖታችሁ ወሰንን አትለፉ፤ በአላህም ላይ እውነትን እንጂ አትናገሩ፤ የመርየም ልጅ አልመሲሕ ዒሳ፣ የአላህ መልክተኛ፣ ወደ መርየም የጣላት (የሁን) ቃሉም ከርሱ የሆነ መንፈስም ብቻ ነው፤ …”

መልስ

ከላም” كَلَٰم የሚለው ተባታይ ቃል “ከለመ” كَلَّمَ ማለትም “ተናገረ” ከሚል ግስ የመጣ ሲሆን “ንግግር” ማለት ነው፤ “ከሊማህ” كَلِمَة ደግሞ የከላም አንስታይ ነው፤ የከሊማህ ብዙ ቁጥር “ከሊመት” ِكَلِمَةٍ ሲሆን “ቃላት” ማለት ነው። አላህ “ሲፋቱል ከላም” صفات الكلام ማለትም “የመናገር ባህርይ” አለው፤ አምላካችን አላህ “ሙተከለም” مُتَكَلِّم ማለትም “ተናጋሪ”speaker” ነው፤ የራሱ “ከላም” كَلَٰم ማለትም “ንግግር”speech” የራሱ ባህርይ ነው፤ “ከላም” እራሱ “ሐርፍ” حَرْف ማለትም “ሆሄ” ነው።

አላህ “አል-ኻሊቅ” الخَٰلِق ማለትም “ፈጣሪ” ሲሆን ነገር ሁሉ “መኽሉቅ” مَخْلُق ነው፤ አላህ ነገርን የሚፈጥርበት ንግግሩ ደግሞ ፈጣሪም ፍጡርም ሳይሆን የራሱ ባህርይ ነው፤ አምላካችን አላህ ደግሞ የሁሉ ነገር ፈጣሪ ነው፤ ነገር ማስገኘት በሻ ጊዜ “ኹን” ይለዋል፤ ወዲያው ይኾናልም፦

39፥62 አላህ የነገሩ ሁሉ ፈጣሪ ነው፡፡ እርሱም በነገሩ ሁሉ ላይ አስተናባሪ ነው፡፡

36፥82 ነገሩም አንዳችን በሻ ጊዜ “ኹን” ማለት ነው፡፡ ወዲያው ይኾናልም፡፡

40፥68 እርሱ ያ ሕያው የሚያደርግ የሚገድልም ነው፡፡ አንዳችን ነገር በሻም ጊዜ ለእርሱ የሚለውን «ኹን» ነው፤ ወዲያውም ይኾናል፡፡

16፥40 ለማንኛውም ነገር መኾኑን በሻነው ጊዜ ቃላችን ለእርሱ “ኹን” ማለት ብቻ ነው፤ ወዲውም

“ቃላችን” የሚለው ሃይለ-ቃል ይሰመርበት፤ “ሸይዕ” شَىْء ማለት “ነገር’thing” ማለት ሲሆን “ነገር” በሚለው ቃል ውስጥ ፍጥረት ይካተታል፤ የሚፈጥበት የይኹን ቃል ግን ከነገር ውጪ የፈጣሪ ባህርይ ነው፤

ሱራ 4፡171 ላይ በቅንፍ የገባው (የኹን) የሚለው ቃል የተርጓሚዎች ጭማሬ እንጂ በኦሪጅናል አረብኛው ውስጥ አይገኝም፡፡ ከዚህ ቀደም ሌላ ቦታ ላይ እንዳብራራነው፡- ሙስሊም ወገኖች እዚህ ጋ በትኩረት ሊመለከቷቸው የሚገቡ ሁለት ነገሮች አሉ፡፡ የመጀመርያው ይህ መጠሪያ ለኢየሱስ ብቻ መዋሉን ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሱራ 4፡171 ላይ ከአላህ የኾነ ቃል ሳይሆን የእርሱ (የአላህ) ቃል (ከሊመቱሁ) መባሉን ነው፡፡ ኢየሱስ የአላህ ቃል የተባለው በቃል በመረገዙ ምክንያት ከሆነ አዳምም የአላህ ቃል ሊባል ይገባዋል፡፡ ምክንያቱም እንደ ቁርኣን አስተምህሮ ሁለቱም በተመሳሳይ አፈጣጠር ነው የተፈጠሩት፡፡ እዚህ ጋ ሙስሊም ወገኖች አጣብቂኝ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ምክንያቱም ኢየሱስ “ሁን” በሚለው ቃል መፈጠሩ የአላህ ቃል ነው ካስባለው ሰማይ፣ ምድር፣ ዛፍ፣ ድንጋዩ፣ እንስሳት፣ እኛ ሰዎች፣ ሰይጣንን ጨምሮ ሁላችንም የአላህ ቃል ነን ማለት ነው፡፡ ሰይጣን “ሁን” በሚለው ቃል ተፈጥሯልና የአላህ ቃል ልንለው ነው? እንዲህ የሚያምን ሙስሊም ይኖራል?

ክርስቲያኖች ፈጣሪ ልጅ አለው ሲሉ አምላካችን አላህ፦ “ነገርንም ማስገኘት በሻ ጊዜ ለእርሱ የሚለው “ኹን” ነው፤ ወዲያውም ይኾናል” የሚል ምላሽ ሰጠ፦

2፥116 አላህም ልጅ አለው አሉ፡፡ ከሚሉት ጥራት ተገባው፡፡ አይደለም በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉ የእርሱ ነው፡፡ ሁሉም ለእርሱ ታዛዦች ናቸው፡፡

2፥117 ሰማያትንና ምድርን ያለብጤ ፈጣሪ ነው፤ ነገርንም ማስገኘት በሻ ጊዜ ለእርሱ የሚለው፡- «ኹን» ነው፤ ወዲያውም ይኾናል፡፡

19፥35 ለአላህ ልጅን መያዝ አይገባውም፡፡ ከጉድለት ሁሉ ጠራ፡፡ ነገርን በሻ ጊዜ ለእርሱ የሚለው «ኹን» ነው ወዲያውም ይኾናል፡፡

ለአላህ ልጅ መውለድ አያስፈልገው፤ ነገርን ማስገኘት ሲፈልግ በንግግሩ “ኹን” ይላል ይሆናል፤ መርየምም”ዐ.ሰ.”፦ “ጌታዬ ሆይ! ሰው ያልነካኝ ስኾን ለኔ እንዴት ልጅ ይኖረኛል?” ስትል፤ መለኮታዊ ምላሽ፦ “አላህ የሚሻውን ይፈጥራል፤ አንዳችን በሻ ጊዜ ለእርሱ ኹን ይለዋል፤ ወዲውኑም ይኾናል” የሚል ምላሽ ነው፦

3፥47 ፡-ጌታዬ ሆይ! ሰው ያልነካኝ ስኾን ለኔ እንዴት ልጅ ይኖረኛል? አለች፡፡ ነገሩ እንዳልሽው ነው፡፡ አላህ የሚሻውን ይፈጥራል፤ አንዳችን በሻ ጊዜ ለእርሱ ኹን ይለዋል፤ ወዲውኑም ይኾናል አላት፡፡

አንድ ጊዜ ነጅራኖች ማለትም የየመን ክርስቲያኖች፦ “ዒሣ የአላህ ልጅ ካልሆነ እንግዲያውስ አባቱ ማን ነው? ብለው ጠየቁ፤ አምላካችን አላህም ይህንን አንቀጽ አወረደ፦

3፥59 አላህ ዘንድ የዒሳ ምሳሌ እንደ አዳም ብጤ ነው፡፡ ከዐፈር ፈጠረው፡፡ ከዚያም ለእርሱ «ኹን» አለው፤ ኾነም፡፡

አላህ አደምን ከዐፈር ቅርጹን ካበጀ በኃላ በቃሉ “ኹን” አለው ሰው ሆነ፤ በተመሳሳይም ዒሣን ከመርየም “ኹን” አለው ሰው ሆነ፤ “ወከሊመቱል ቃሃ ኢላ መርየም وَكَلِمَتُهُ أَلْقَاهَا إِلَىٰ مَرْيَمَ ማለትም “ወደ መርየም የጣላት የይኹን ቃል ነው” የሚለው ለዛ ነው፦

4:171 እናንተ የመጽሐፉ ሰዎች ሆይ! በሃይማኖታችሁ ወሰንን አትለፉ፤ በአላህም ላይ እውነትን እንጂ አትናገሩ፤ የመርየም ልጅ አልመሲሕ ዒሳ፣ የአላህ መልክተኛ፣ ወደ መርየም የጣላት የሁን ቃሉም ነው፤ ከእርሱ የሆነ መንፈስም ብቻ ነው”።

በኢብን ከሢር ተፍሲር መሠረት ምስጢራዊ ወይም ስውር ከሚባሉ የቁርኣን ጥቅሶች መካከል ሱራ 4፡171 አንዱ ሲሆን ተከታዩ አያ “የወረደው” እርሱንና መሰል ጥቅሶችን አስመልክቶ ነው፡-

“እርሱ ያ በአንተ ላይ መጽሐፉን ያወረደ ነው፡፡ ከእርሱ (ከመጽሐፉ) ግልጽ የኾኑ አንቀጾች አልሉ፡፡ እነሱ የመጽሐፉ መሠረቶች ናቸው፡፡ ሌሎችም ተመሳሳዮች አልሉ፡፡ እነዚያማ በልቦቻቸው ውስጥ ጥመት ያለባቸው ሰዎች ማሳሳትን ለመፈለግና ትችቱን ለመፈለግ ከርሱ የተመሳሰለውን ይከታተላሉ፡፡ (ትክክለኛ) ትችቱንም አላህ ብቻ እንጅ ሌላ አያውቀውም፡፡ በዕውቀትም የጠለቁት «በርሱ አምነናል፤ ሁሉም ከጌታችን ዘንድ ነው» ይላሉ፡፡ የአእምሮ ባለቤቶችም እንጅ (ሌላው) አይገሰጽም፡፡” (ሱራ 3፡7)

ሙሐመድ ኢየሱስን የአላህ ቃልና መንፈስ ብሎ ከጠራውና የኢየሱስን መለኮታዊነት የሚጠቁሙ የተለያዩ ቃላትን ከተናገረ በኋላ ክርስቲያኖች በገዛ ቃሉ እንደሚያጠምዱት ስላስተዋለ “ትርጉሙን ከአላህ ውጪ ማንም አያውቅም” የሚል የማምለጫ ሰበብ መፍጠሩ ግልፅ ነው፡፡ የነጅራን ክርስቲያኖች ወደ እርሱ በመጡ ጊዜ የቁርኣን ጥቅሶችን ተጠቅመው እንዳፋጠጡት የተለያዩ እስላማዊ መጻሕፍት ይናዘዛሉ፡፡ ይህ የሙሐመድ ግራ መጋባት ከተፍሲርና ከሲራ መጻሕፍት በግልፅ የሚታይ ቢሆንም ዛሬ የሚገኙት ሙስሊሞች ነቢያቸው ግራ የተጋባበትን ጉዳይ ከእርሱ ተሽለው ሊያብራሩልን ይሞክራሉ፡፡ Tafsir Ibn Kathir Juz’ 3 (Part 3): Al-Baqarah 253 to Al-I-‘Imran 92; 2nd Edition; By Muhammad Saed Abdul-Rahman, p. 108-109 እንዲሁም Guillaume, The Life of Muhammad, p. 257

ልብ አድርግ “ከሊመት” ِكَلِمَةٍ ማለት ብዙ ቁጥር ሲሆን “ቃላት” ማለት ነው፤ በተጨማሪም ሙአነስ ነው፤ ዒሣን ነጠላ ነው፤ በተጨማሪም ወንድ እንጂ ሴት አይደለም፤ “የይኹን ቃል” መንስኤ ሲሆን ዒሣ ውጤት ነው። ሲቀጥ “ብቻ” የሚለው የዐረቢኛ ቃል “ወሒድ” وَاحِد ነው፥ “ወሒድ” የሚል ቃል አንቀጹ ላይ የለም።

“ቃል” ወይም “ቃላት” መባሉ የሚያመጣው ለውጥ የለም፡፡ ለምሳሌ ያህል ቁርኣን የአላህ ቃል ነው ስትሉ አንዲት ቃል ብቻ ነው እያላችሁ አይደለም፤ የአላህ ቃላት ነው ስትሉትም ብዙ መጽሐፍ ነው እያላችሁት አይደለም፡፡ በነጠላ ወይም በብዙ መጠራቱ ለውጥ አያመጣም፡፡ ይልቅ “ብዙ ቁጥር ነው” የሚል ሙግት ማቅረብህ “ኹን” በምትለዋ አንዲት የአላህ ቃል የተፈጠረ ስለሆነ ነው “ከሊመቱሁ” የተባለው የሚለውን ሙግትህን ውድቅ ያደርግብሃል፡፡ ደግሞም የታወቁት የቁርኣን ትርጉሞች በሙሉ “ከሊመቱሁ” የሚለውን በነጠላ እንጂ በብዙ አልተረጎሙም፡፡

ስለ ቋንቋ የምታውቅ ከሆነ የቃላት ፆታዎች የቃላትን ድምጸት የሚገልጹ እንጂ የአንድን አካል ፆታ የሚገልጹ እንዳልሆኑ አይጠፋህም፡፡ በዚህ ጥቅስ ውስጥ “ከሊመት” የሚለው ቃል አንስታይ ፆታ ሲሆን “ወሩሁን” (መንፈሱም) የሚለው ተባዕታይ ነው፡፡ ቃልም መንፈስም ፆታ አልባ ቢሆኑም በአረብኛ ቋንቋ ግን የሚነበቡበት ድምጸት ፆታ አለው፡፡ በግሪክ ቋንቋም ተመሳሳይ ፅንሰ ሐሳብ አለ፡፡ ይህ ከወንድነት ወይም ከሴትነት ጋር የተገናኘ አይደለም፡፡ በአረብኛ ሰማያትና ምድር (ሰማዋት ወል አርድ) አንስታይ ፆታ ናቸው፡፡ ስለዚህ ሴቶች ናቸው ማለት ነው?  በአማርኛ እንኳ “ነፍስ” በሴቴ ፆታ ነው የምትገለጸው፡፡ ስለዚህ አንተ “ነፍስ” ስትባል ሴት ሆንክ ማለት ነው? ይህ በጣም ስሁት ሙግት ነው፡፡

ጥቅሱ ኢየሱስን “ከሊመቱሁ” (የእርሱ ቃል) ይለዋል እንጂ “የእርሱ ቃል ውጤት” አይለውም፡፡ “የእርሱ ቃል” ሲል ቃሉ ራሱ ኢየሱስ መሆኑን አፅንዖት የሚሰጥ ነው፡፡ “የእርሱ ቃል” ተብሎ በግልጽ የተቀመጠውን “የእርሱ ቃል ውጤት” ብሎ ማንበብ የሚገርም ማጣመም ነው፡፡

“ብቻ የሚል ቃል የለም” ያልከው ቅጥፈት ነው፡፡ በአረብኛ “ብቻ” ለማለት “ወሒድ” ከሚለው ቃል ውጪ የተለያዩ ቃላትና አገላለፆች አሉ፡፡ በዚህ ጥቅስ ውስጥ “ኢነማ” የሚል ቃል ስላለ ነው ተርጓሚዎቹ “ብቻ” የሚለውን ቃል ያስገቡት፤ ደግሞም ትክክል ናቸው፡፡ “ማ” በአረብኛ ገዳቢ ቃል ሲሆን “ብቻ” (Only) ተብሎ ይተረጎማል፡፡

ሢሰልስ ከአላህ የሆነው መንፈስ ነው ማለት የዒሣ መንፈስ ከአላህ የሆነ ነው ማለት ነው፥ “ሩሑ ሚንሁ” رُوحٌۭ مِّنْهُ የሚለው ሃይለ-ቃል ይሰመርበት። ከመርየም አካል ሲሆን “ከእርሱ (ከአላህ) የሆነው መንፈስ ነው፥ የማንኛውም ሰው አካል ከወላጆቹ ሲሆን ሩሕ ግን ከአላህ ነው፦

17፥85 ከሩሕም ይጠይቁሃል፡፡ «ሩሕ ከጌታዬ ነገር ነው ከዕውቀትም ጥቂትን እንጂ አልተሰጣችሁም» በላቸው፡፡

ስለዚህ ሰው የሩሕ እና የአካል ውሕደት ከሆነ የመርየም ልጅ ዒሣ ልክ እንደ እናቱ ምግብ የሚበላ ሰው ነበር፦

5፥75 ”የመርየም ልጅ አልመሲሕ ከበፊቱ መልክተኞች በእርግጥ ያለፉ የኾነ መልክተኛ እንጅ ሌላ አይደለም፡፡ እናቱም በጣም እውነተኛ ናት፡፡ ሁለቱም ምግብን የሚበሉ ነበሩ”፤ አንቀጾችን ለነርሱ ለከሓዲዎች እንዴት እንደምናብራራ ተመልከት ከዚያም ከእውነት እንዴት እንደሚመለሱ ተመልከት፡፡

“ሩሑን ሚንሁ” (ከርሱ የሆነ መንፈስ) የሚለው አባባል በሌላ አነጋገር የአላህ መንፈስ መሆኑን የሚገልጽ ነው፡፡ ኢየሱስ ከአላህ የሆነ መንፈስ ከሆነ የማን መንፈስ ነው? የአላህ መንፈስ ነው፡፡ በሌሎች ጥቅሶች ላይ ደግሞ አላህ መንፈሱን ወደ ማርያም እንደተነፈሰባት ይናገራል፡- “የዒምራንን ልጅ መርየምንም ያችን ብልቷን የጠበቀችውን (ምሳሌ አደረገ)፡፡ በእርሱም ውስጥ ከመንፈሳችን ነፍፋን… ” (አል -ተህሪም 12)፡፡ “ያችንም ብልቷን የጠበቀቺውን በርሷም ውስጥ ከመንፈሳችን የነፋንባትን …” (አል -አንቢያእ 91)፡፡ በነዚህ ጥቅሶች ላይ “ከመንፈሳችን” የሚለው በአረብኛ “ሚን ሩሒና” የሚል ሲሆን አንደኛ መደብ ባለቤት ተውላጠ ስም ሲሆን መንፈሱ የአላህ የራሱ መሆኑን ያሳያል፡፡

ሱራ 17፡85 ላይ “ሩህ” የተባለው የሰው ነፍስ ይሁን ወይም ጂብሪል ይሁን ለመወሰን የሚያስችል ቁርአናዊ አውድ የለም፡፡ ነፍስ በአረብኛ “ነፍስ” በመባል የምትታወቅ ሲሆን “ሩህ” ነፍስ ይሁን ወይም ከነፍስ የተለየ ሌላ ነገር በሙስሊም ሊቃውንት መካከል ክርክር አለ፡፡ ስለዚህ “ሩህ” የሰው ነፍስ ይሁን ወይም ደግሞ በሰው ውስጥ ነፍስን የሚፈጥር የአላህ መንፈስ ይሁን ከዚህ ጥቅስ በመነሳት ማረጋገጥ አይቻልም፡፡ ጥቅሱ ግራ አጋቢ ነው፡፡

ስናጠቃልል ቁርኣን በአንድ ቦታ ላይ ዒሳን እንደ ማንኛውም ሰው መሆኑን ከተናገረ በኋላ በሌላ ቦታ ላይ የአላህ ቃልና መንፈስ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ይህ አጠራር በቁርኣን ብቻ ሳይሆን በሐዲሳትም የተጠቀሰ ነው፡፡ ከዒሳ ውጪ በነዚህ ማዕርጋት የተጠራ አንድም ሰው የሌለ ሲሆን አዳም የሰው ልጆች አባት፣ አብረሃም የአላህ ወዳጅ፣ ሙሴ አላህን ፊት ለፊት ያናገረው፣ ሙሐመድ የአላህ መልእክተኛ እንደተባሉት ሁሉ ኢየሱስ “የአላህ ቃልና የአላህ መንፈስ” ተብሏል፡፡ ሳሂህ ሙስሊም ሐዲስ ውስጥ እንዲህ ተጽፏል፡-

እነሱም ወደ አዳም መጥተው እንዲህ ይሉታል፡- አባታችን ሆይ የገነትን በር ክፈትልን፡፡ እርሱም ይላቸዋል፡- ከገነት ያወጣችሁ ምንድነው? የአባታችሁ ኃጢአት አይደለምን? እኔም ይህን የሚያደርግ ስልጣን ላይ አይደለሁም፡፡ የአላህ ወዳጅ (ጓደኛ) ወደ ሆነው ወደ አብርሃም ሂዱ፡፡ ቅዱሱ ነቢይም እንዲህ አለ፡፡ አብርሃምም እንዲህ አለ፡– እኔ ይህን በሚያደርግ ስልጣን ላይ አይደለሁም፡፡ ከምንም በላይ እኔ ለአላህ ወደጁ ነበርኩ፤ ነገር ግን አላህ ፊት ለፊት ወዳናገረው ወደ ሙሴ ሂዱ፡፡ እነሱም ወደ ሙሴ መጡ፡፡ ነገር ግን እሱም እንዲህ አለ፡- እኔ ይህንን የሚያደርግ ስልጣን ላይ አይደለሁም፡፡ የአላህ ቃል እና የአላህ መንፈስ ወደ ሆነው ወደ ኢየሱስ ሂዱ… (ሳሂህ ሙስሊም መጽሐፍ 001 ቁጥር 0380)

የአላህ ቃልና የአላህ መንፈስ ተብሎ የተጠራ ሌላ ሰው በቁርኣንም ሆነ በእስላማዊ ሐዲሳት አለመታወቁ እነዚህን ሁለቱን ማዕርጋት በትኩረት እንድንመለከታቸው ያስገድደናል፡፡ በተለይም “የአላህ ቃል” የሚለውን በመጽሐፍ ቅዱስ መነፅር ለተመለከተ ሰው ትርጉሙ እጅግ የተለየ ነው፡-

በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ዮሐ 1:1-2

በዚህ ክፍል ኢየሱስ በፍጥረት ጅማሬ በቃልነት ይኖር የነበረ እንደሆነ፣ በፍጡርነት ሳይሆን ሙሉ መለኮትነትን በመላበስ የነበረ እንደሆነ እናያለን፡፡ ወደ እርሱ ቃል አልተላከም፤ ያ ቃል ራሱ ነው ሥጋ የሆነው፡-

ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፡፡ ዮሐ 1፡14

ሙሐመድ ትርጉሙን ሳያውቅ የኢየሱስን አምላክነት የሚያረጋግጥ ማዕርግ የሰጠው ሲሆን ይህንን ለማብራራትና ለማስተባበል የጨማመራቸው ሌሎች ሐሳቦች በቁርኣን ውስጥ ግጭት እንዲኖር ሰበብ ሆነዋል፡፡



የቁርኣን ግጭቶች