የቁርኣን ስሁት አመክንዮ

የቁርኣን ስሁት አመክንዮ

በወንድም ትንሣኤ


ሙሐመድ ከፈጣሪ የተላከ ነቢይ መሆኑን ለማሳየት ከተጠቀማቸው ስሁት ሙግቶች መካከል አንዱ በአራተኛው ሱራ ላይ የሚገኘው “የአላህ ንግግር” አንዱ ሲሆን በዚህ ዘመንምን ጭምር ሙስሊም ወገኖቻችን ያስተጋቡታል።

“ቁርኣንን አያስተነትኑምን ? ከአላህ ሌላ ዘንድ በነበረ ኖሮ በርሱ ውስጥ ብዙ መለያየትን ባገኙ ነበር…” (ሱራ 4:82)።

የቁርኣን ሙግት በአጭሩ የሚከተለውን ይመስላል፦

“ቁርኣን ከፈጣሪ ባይሆን ኖሮ ብዙ ግጭቶች ይገኙበት ነበር። ቁርኣን ምንም ግጭቶች የሉበትም። ስለዚህ ቁርአን ከፈጣሪ ዘንድ ነው።”

ቁርኣን ግጭቶች አሉበት ወይስ የሉበትም? የሚለውን ጥያቄ ለጊዜው ወደ ጎን እናድርገውና ይህ ሙግት ትክክለኛውን የአመክንዮ ሕግ የተከተለ ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን እንመልከት።

አያውን በአንክሮ ያላስተዋለ ሰው ሙግቱ በተለምዶ Modus Tollens ብለን የምንጠራውን የሙግት ዓይነት የተከተለ ትክክለኛ ሐሳብ ሊመስለው ይችላል፤ ነገር ግን ቁርኣን የተጠቀመው አመክንዮ በፍጹም ከ Modus Tollens ሊመደብ የሚችል አይደለም።

መታወቅ ያለበት ቀዳሚው ጉዳይ ይህ የሙግት ዓይነት የሚሠራው የመጀመሪያው ቅድመሁኔታ (Premise) ውሸት የመሆን ዕድል ከሌለው ብቻ መሆኑ ነው። ለምሳሌ አንድ ሰው “ንስር ብሆን ኖሮ መብረር እችል ነበር። መብረር አልችልም፤ ስለዚህ ንስር አይደለሁም” ብሎ ቢናገር ትክክለኛ Modus Tollens የተከተለ አመክንዮ መጠቀሙ እሙን ነው፤ ሰውየው ንስር ከሆነ የግድ መብረር መቻሉ ስለማይቀር ማለት ነው። አላህ በሙግቱ ያስቀመጠው የመጀመሪያው ቅድመሁኔታ (ቁርኣን ከፈጣሪ ባይሆን ኖሮ ግጭቶች ይኖሩበት ነበር የሚለው) ግን ውሸት የመሆን ዕድል ያለው ሐሳብ ነው። አንድ መጽሐፍ ከፈጣሪ ስላልሆነ ብቻ የግድ ግጭቶች ይኖሩበታል ማለት አይቻልም፤ ቁርኣን ከአላህ አለመሆኑም ግጭት እንዲኖርበት ሰበብ ይሆናል ብለን ለመደምደም አያስችለንም።

ስለዚህ አንድ ሰው የቁርኣንን ሙግት እቀበላለሁ የሚል ከሆነ የመጀመሪያው ቅድመሁኔታ (Premise) የግድ እውነት ነው ብሎ መውሰድ ይኖርበታል። ይህ ከሆነ ደግሞ ሰውየው “ከፈጣሪ ያልሆነ መጽሐፍ ሁሉ ግጭት አለበት” የሚለውን ሐሳብም ሊቀበል ዘንድ ግድ ይለዋል።

ስናጠቃልል ሙስሊሞች ቁርኣን ግጭት ስለሌለው ከፈጣሪ ነው የሚለውን ሐሳብ ማስረገጥ ከፈለጉ ሌሎች ከፈጣሪ ያልሆኑ መጽሐፍት በሙሉ ግጭት እንዳለባቸው የማሳየት ግዴታ አለባቸው። በተቃራኒው ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎች ደግሞ ከፈጣሪ ያልሆነ ግጭት አልባ መጽሐፍ/ት በማቅረብ ብቻ ቁርኣንን መርታት ይችላሉ ማለት ነው። እውነተኛው አምላክ ሁሉን አዋቂ ስለሆነ እንዲህ ባለ ስሁት አመክንዮ ላይ የተመሠረተ “ማስረጃ” ለቃሉ እውነተኛነት ማረጋገጫ አድርጎ አያቀርብም፤ ስለዚህ ቁርኣን ከፈጣሪ ዘንድ አይደለም።

ቁርኣን