የቁርኣን ግጭቶች
ሙስሊም ወገኖቻችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በርካታ ስህተቶችና ግጭቶች መኖራቸውን ሲነገሩን ኖረዋል፡፡ እነ አሕመድ ዲዳትን የመሳሰሉት ሰባኪያን እንዲያውም የስህተቶቹን ብዛት ከሃምሳ ሺህ እስከ መቶ ሺህ ያደርሱታል፡፡( መቶ ሺህ ስህተቶች ማለት በግምት በእያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ውስጥ ወደ ሦስት ስህተቶች ማለት ነው!) ለእንደዚህ አይነቶቹ መሠረት የለሽ ክሶች ክርስቲያን ሊቃውንት በበቂ ሁኔታ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ነገር ግን ሙስሊም ሰባኪያን በሚችሉት አቅም ሁሉ የሌላውን የእምነት መጽሐፍ እያብጠለጠሉና እየወረፉ የራሳቸውን ግን እንደ አይነኬ መቁጠራቸው በሃቀኝነታቸው ላይ ጥርጣሬን ያጭራል፡፡ እነዚህ ወገኖች ቁርኣን እርስ በርሱ የተስማማና ምንም ዓይነት ግጭት እንደሌለበት በመመጻደቅ ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ ቁርኣንም ስለራሱ በሱራ 4፡82 ላይ እንዲህ በማለት ይናገራል፡-
“ቁርኣንን አያስተነትኑምን? ከአላህ ሌላ ዘንድ በነበረ ኖሮ በርሱ ውስጥ ብዙ መለያየትን ባገኙ ነበር፡፡”
በዚህ ጥቅስ መሠረት በቁርኣን ውስጥ ብዙ መለያየት የለም፡፡ ይህም ከአላህ ዘንድ ለመሆኑ ማረጋገጫ ነው፡፡ በመሠረቱ በአንድ መጽሐፍ ውስጥ ተጣርሶ መኖሩ ያ መጽሐፍ ሁሉን አዋቂ ከሆነው አምላክ ዘንድ እንደልሆነ ቢያረጋግጥም በአንጻሩ ግን አንድ መጽሐፍ እርስ በርሱ አለመጋጨቱ ለመጽሐፉ መለኮታዊ ምንጭነት ማረጋገጫ ሊሆን እንደማይችልም መታወቅ አለበት፡፡ ብዙ ውስጣዊ ግጭት የሌላቸው የልብ ወለድ መጽሐፍት በዓለም ላይ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን ተቃርኖ በውስጣቸው አለመኖሩ እውነት እንዲሆኑ አያደርጋቸውም፡፡ በኸሊፋ ዑሥማን ዘመንና በ1924 ዓ.ም. በግብፅ አገር የእርማት ሥራ የተሠራለት ቁርኣንም ተቃርኖ በውስጡ ባይገኝ አስደናቂ አይሆንም፡፡ እርስ በርሱ ባለመጋጨቱም እንደ ፈጣሪ ቃል አንቀበለውም፡፡ ነገር ግን ቁርኣን ውስጥ ተቃርኖ የለም የሚለው አባባል በገሃዱ ዓለም ሲፈተሽ የንግግርን ያህል ቀላል እንዳልሆነና ሙስሊም ወገኖች ጊዜ ወስደው ሊመለከቷቸው የሚገቡ ነጥቦች መኖራቸውን ለመጠቆም እንወዳለን፡፡ ይህንንም ስንናገር ሙስሊም መዳጆቻችን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ላነሷቸው ክሶች አፀፋ ለመመለስ አይደለም፡፡ ቀጥሎ ለሚቀርቡት የመጽሐፋቸው ችግሮች ምላሽ ሊኖሯቸው አይችልም ከሚል አስተሳሰብ በመነሳትም አይደለም፡፡ እነዚህን ችግሮች መፍታት ቀላል እንደማይሆኑላቸው ብንገምትም ነገር ግን መልስ እንዳላቸው እንደሚያምኑ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ እነርሱም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለሚያነሱአቸው ጥያቄዎች ክርስቲያኖች በቂ ምላሽ እንዳላቸው ይገነዘቡ ዘንድ በፍፁም ቅንነት እንጠይቃለን፡፡ ሙስሊም ወገኖች ሆይ እኛ ክርስቲያኖች ትችቶቻችሁን በበጐ መልኩ ተቀብለን በማስተናገድ ለጥያቄዎቻችሁ በተገቢው መንገድ ምላሽ እንደምንሰጥ ሁሉ እናንተም ለእነዚህ በመጽሐፋችሁ ውስጥ ለሚገኙት አመክንዮአዊ ግጭቶች ተገቢውን ምላሽ እንደምትሰጡ ተስፋ እናደርጋለን፡፡
- አጋሪ ሴቶችን (ከአላህ ውጪ ሌላ ነገር የሚያመልኩትን) ማግባት ተፈቅዷል ወይስ አልተፈቀደም?
አልተፈቀደም:- ሱራ 2፡221 “(በአላህ) አጋሪ የሆኑ ሴቶችን እስኪያምኑ ድረስ አታግቧቸው፡፡”
ተፈቅዷል:- ሱራ 5፡5 “ከነዚያ ከናንተ በፊት መጽሐፍን ከተሰጡት ሴቶች ጥብቆቹም ዘማዊዎችና የሚስጢር ወዳጅ ያዢዎች ሳትሆኑ ጥብቆች ሆናችሁ መህሮቻቸውን በሰጣችኋቸው ጊዜ (ልታገቧቸው የተፈቀዱ ናቸው)”
ነገር ግን የመጽሐፉ ሰዎች (ክርስቲያኖችና አይሁድ) አጋሪዎች እንደሆኑ ቁርኣን በብዙ ስፍራዎች ላይ ይናገራል፡፡ ለምሳሌ ክርስቲያኖች ኢየሱስን በማምለካቸው ሳቢያ አጋሪዎች እንደሆኑ ሱራ 4፡17፤5፡72-73፤5፡116 ላይ ተጽፏል፡፡ እንዲሁም አይሁድ ዕዝራን የአላህ ልጅ በማለት ስለሚጠሩት አጋሪዎች እንደሆኑ በሱራ 9፡20 ላይ ተጽፏል (እንዲህ ያለ እምነት በአይሁድ ታሪክ ተሰምቶ አለመታወቁ በቁርኣን ላይ የታሪካዊ ትክክለኝነትን ጥያቄ የሚያጭር ቢሆንም)፡፡ ይህንን ዐይን ያወጣ ግጭት ለመረዳት የሚከተለውን ሲሎጂዝም ልብ ይበሉ፡-
አጋሪ ሴቶችን ካላመኑ በስተቀር አታግቡ፡፡
ክርስቲያኖችና አይሁዶች አጋሪዎች ናቸው
ክርስቲያኖችና አይሁዶችን አግቡ፡፡
ይህ ማብራሪያ የማይሻ ግጭት ነው፡፡ ለዚህ ጥያቄ በሙስሊሞች የተሰጠ መልስ
- ጋኔንና ሰው የተፈጠሩት ለምንድ ነው?
- ለአላህ ሊገዙ ብቻ:- ሱራ 52፡56 “ጋኔንና ሰው ሊገዙኝ እንጂ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም”
– ለገሃነም መሙያ:- ሱራ 7፡179 “ከጋኔንና ከሰው ብዙዎችን ለገሃነም በእርግጥ ፈጠርን፡፡” እንዲሁም ሱራ 23፡13፤ 11፡119 ላይ ተመሳሳይ ሐሳብ እናገኛለን፡፡ በሁለቱ ጥቅሶች መካከል ያለውን ተቃርኖ በግልፅ ማየት ለማንም የሚያስቸግር አይመስለንም፡፡ ለዚህ ጥያቄ በሙስሊሞች የተሰጠ መልስ
- ሰዎችን የሚያጠመው አላህ ወይንስ ሰይጣን?
አላህ:– ሱራ 7፡186 “አላህ የሚያጠመውም ሰው ለርሱ ምንም አቅኚ የለውም፡፡”
ሱራ 16፡93 “አላህ በሻም ኖሮ አንዲት ህዝብ ባደረጋችሁ ነበር ግን የሚሻውን ሰው ያጠማል የሚሻውንም ሰው ያቀናል፡፡ ትሰሩት ከነበራችሁትም ሁሉ ትጠየቃላችሁ፡፡”
ሰይጣን:– ሱራ 4፡119-120 “በእርግጥም አጠማቸዋለሁ ከንቱም አስመኛቸዋለሁ… የማይፈፀመውን ተስፋ ይሰጣቸዋል ያስመኛቸዋልም፡፡ ሰይጣንም ለማታለል እንጂ አይቀጥራቸውም”
ሱራ 7፡202 “ወንድሞቻቸውም (ሰይጣናት) ጥመትን ይጨምሩላቸዋል ከዚያም እነሱ አይገቱም”
ሰይጣንም ራሱ “ጌታዬ ሆይ እኔን በማጥመምህ ይሁንብኝ” በማለት ለራሱ ጠማማነት አላህን ተጠያቂ ሲያደርግ በሱራ 15፡39 ላይ እናነባለን፡፡ እንዲሁም ሱራ 16፡93 ላይ እንደምናነበው አላህ ራሱ ሰዎችን አጣሟቸው የፈጠረ ሲሆን ነገር ግን “በሥራችሁ እጠይቃችኋለሁ!” ብሎ ሲዝትባቸው እናያለን፡፡ ራሱ አጣሞ ከፈጠረ በኋላ “ስለ ጠመማችሁ እጠይቃችኋለሁ” ማለት በራሱ ትልቅ ኢ-ፍትሃዊነት ነው፡፡ ለእኛ እስከሚገባን ድረስ ሰዎችን ማጥመም የጠማማው የዲያቢሎስ ሥራ እንጂ የጻድቁ የእግዚአብሔር ሥራ ሊሆን ከቶ አይችልም፡፡ ለዚህ ጥያቄ በሙስሊሞች የተሰጠ መልስ
- አማላጆች አሉ ወይስ የሉም?
አሉ፡- ሱራ 42፡5 “… መላእክትም ጌታቸውን እያመሰገኑ ያወድሳሉ፤ በምድርም ላለው ፍጡር ምህረትን ይለምናሉ…” እንዲሁም ሱራ 33፡43፤ 4፡7 ይመልከቱ፡፡
የሉም፡- “…ከርሱ ሌላ ረዳትም አማላጅም ምንም የላችሁም አትገሠፁምን?”
መላእክት በምድር ላለው ፍጡር ምህረትን የሚለምኑ ከሆነ ከአላህ ሌላ አማላጅ የላችሁም የሚለው ሐሳብ ከባድ ተቃርኖን ያስከትላል፡፡ ከአላህ ሌላ አማላጅ የላችሁም ማለትስ ምን ማለት ነው? አላህ ራሱ ከራሱ ምህረትን ይለምናል ማለት ነውን? ከሆነ አላህ በባህሪም በአካልም አንድ (ነጠላ) ነው ከሚለው የእስልምና አስተምህሮ ጋር እንዴት ይሄዳል? ሱራ 39፡44 ላይ የሚገኘው ቃል አላህ አማላጅ እንደሆነ የሚናገረውን ሐሳብ ያጠናክራልና ያንብቡት፡፡ ለዚህ ጥያቄ በሙስሊሞች የተሰጠ መልስ
- አላህ ያለሚስት ልጅ ሊኖረው ይችላል ወይስ አይችልም?
ይችላል፡- ሱራ 39፡4 “አላህ ልጅን መያዝ በፈለገ ኖሮ ከሚፈጥረው ውስጥ የሚሻውን ይመርጥ ነበር ጥራት ተገባው፡፡”
አይችልም፡– ሱራ 6፡101 “… ለርሱ ሚስት የሌለችው ሲሆን እራዴት ልጅ ይኖረዋል?”
በመጀመሪያው ጥቅስ ውስጥ አላህ ከፍጡራን መካከል የሚፈልገውን በመምረጥ (በምርጫ) ብቻ ልጅ መያዝ እንደሚችል ሲናገር ሁለተኛው ጥቅስ ደግሞ ሚስት የሌለችው ሲሆን እንዴት ልጅ ይኖረዋል? በማለት የመጀመሪያውን ሐሳብ ያፈርሳል፡፡ በተጨማሪም ሁለተኛው ጥቅስ በአላህ ሁሉን ቻይነት ላይ ከባድ ጥያቄን ያስነሳል፡፡ ምክንያቱም አላህ ያለሚስት ልጅ ሊኖረው የማይችል ከሆነ ሁሉን ቻይ ስለማይሆን፡፡ ለዚህ ጥያቄ በሙስሊሞች የተሰጠ መልስ
- አላህ ብቸኛ ረዳት ወይስ ሌሎች ረዳቶችም አሉ?
ብቸኛ ረዳት፡– ሱራ 9፡116 “አላህ የሰማያትና የምድር ንግስና የርሱ ብቻ ነው፡፡ ህያው ያደርጋል ይገድላልም፤ ለናንተም ከርሱ በቀር ጠባቂም ረዳትም የላችሁም”
ሌሎች ረዳቶችም አሉ፡– ሱራ 5፡55 “ረዳታችሁ አላህና መልክተኛው እነዚያም ያመኑት ብቻ ናቸው…” እንዲሁም ሱራ 9፡71
በነዚህ ጥቅሶች ውስጥ “ረዳት” የሚለው ቃል በአረቢኛ “ዋሊ” ሲሆን ከዘጠና ዘጠኙ የአላህ መጠሪያዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ እነዚህን መጠሪዎች ደግሞ ለሌላ ፍጡር መስጠት በእስልምና የተውሂድ አስተምህሮ መሠረት ከባድ ኃጢኣት ነው፡፡ ሱራ 5፡55 ላይ የሚገኘው ቃል ይህንን መጠሪያ ለሌሎች ከመስጠቱም በላይ ከመጀመሪያው ጥቅስ ጋር በግልፅ ይጋጫል፡፡ በሌላም ስፍራ ላይ እንደዚሁ ሐዋርያት ራሳቸውን “የአላህ ረዳቶች” ብለው መጥራታቸውን እናነባለን ሱራ 3፡53፡፡ ታዲያ አላህ ብቸኛ “ዋሊ” ነው ወይስ አይደለም? ለዚህ ጥያቄ በሙስሊሞች የተሰጠ መልስ
- የመላእክት ስግደት ለማን?
ለአላህ ብቻ፡– ሱራ 7፡206 “እነዚያ እጌታህ ዘንድ ያሉት (መላዕክት) እርሱን ከመገዛት አይኮሩም ያወድሱታልም ለርሱ ብቻ ይሰግዳሉ፡፡”
ለሰው ሰግደዋል፡–ሱራ 2፡34 “ለመላዕክት ለአደም ስገዱ ባልን ጊዜ (አስታውስ) ሁሉም ወዲያውኑ ሰገዱ ኢብሊስ (ዲያቢሎስ) ብቻ ሲቀር እምቢ አለ ኮራም ከከሐዲዎቹም ሆነ፡፡” በተጨማሪም ሱራ 17፡61፤ 15፡30 ያንብቡ
በእስላማዊ አስተምህሮ መሠረት ስግደት የሚገባው ለአምላክ ብቻ ነው፡፡ ማንኛውም ፍጡር መስገድ ያለበት ለፈጠረው አምላክ እንጂ ለሌላ ፍጡር መሆን እንደሌለበት እስልምና አጥብቆ ያስተምራል፡፡ ከዚህ ሐሳብ ጋር የማይስማማ ሙስሊም የሚኖር አይመስለንም፡፡ ሙስሊም ወገኖች ቀደም ሲል በተጠቀሱት ጥቅሶች መካከል አመክንዮአዊ ግጭት እንደሌለ ሊያስረዱን ይችሉ ይሆናል፡፡ ነገር ግን እውነተኛው አምላክ መላእክት ለሰው ይሰግዱ ዘንድ ቀጭን ትዕዛዝ በመስጠት አንዱ ፍጡር ለሌላው ፍጡር ይሰግድ ዘንድ እንዳስተማረ የሚናገረውን ጥቅስ ከአጠቃላይ የቁርኣንና የእስልምና አስተምሕሮ ጋር እንዴት ያስታርቁት ይሆን? ለዚህ ጥያቄ በሙስሊሞች የተሰጠ መልስ
- የአላህ ቃል ይለወጣል ወይስ አይለወጥም?
ይለወጣል፡– ሱራ 2፡106 “ከአንቀፅ ብንለውጥ ወይም እርሷን ብናስረሳህ ከርሷ የሚበልጥን ወይም ቢጤዋን እናመጣለን፡፡ አላህ በነገሩ ሁሉ ላይ ከሃሊ (ቻይ) መሆኑን አታውቅምን?”
ሱራ 13፡39 “በአንቀፅ ስፍራ አንቀፅን በለወጥን ጊዜ አላህ የሚያወርደውን ነገር አዋቂ ነው፡፡ አንተ ቀጣፊ እንጂ ሌላ አይደለህም ይላሉ በውነቱ አብዛኞቻቸው አያውቁም፡፡”
አይለወጥም፡- ሱራ 18፡27 “ለቃላቱ ለዋጭ የላቸውም፡፡”
ሱራ 33፡26 “ለአላህ ድንጋጌ ፈፅሞ መለወጥን አታገኝም፡፡”
ሱራ 10፡64 “የአላህ ቃል መለወጥ የላትም፡፡”
እንዲሁም ሱራ 6፡115 እና 6፡34 ያንብቡ፡፡ በአማርኛው ቁርኣን የተወሰኑ ገፆች ላይ አንዱ አንቀፅ (ጥቅስ) በሌላው መሻሩን የሚያሳስቡ የተለያዩ የግርጌ ማስታወሻዎች ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ፡- ገፅ 18, 26, 53, 55, 123, 297 ይመልከቱ፡፡
መሰሉን የቁርኣን እርስ በርስ መሻሻር ሙስሊም ሊቃውንት በአረብኛ ናሲክ ወልመንሱክ በእንግሊዘኛ ‘Abrogation’ በማለት ይጠሩታል፡፡ ሁኔታን ተመልክቶ ትላንት የተናገረውን ቃል የሚያጥፍና የሚለዋውጥ ደካማ የሆነው የሰው ልጅ እንጂ እውነተኛው አምላክ እንዴት ሊሆን ይችላል? እንኳንስ አእማሬ ኩሉ የሆነው ሃያሉ ጌታ ይቅርና ከሰው ልጆች መካከል ጨዋ የሚባለው እንኳ ትላንት ለተናገረው ቃል ታማኝ የሚሆን ነው፡፡ ለዚህ ጥያቄ በሙስሊሞች የተሰጠ መልስ
- በገሃነም ውስጥ የተጣሉ ሰዎች ምግብ አንዱ ብቻ ወይስ ሁሉም?
ዶሪዕ የሚባል ዛፍ ብቻ፡– ሱራ 86፡6 “ለነሱ ዶሪዕ ከሚባል (እሾሃም) ዛፍ እንጂ ሌላ ምግብ የላቸውም፡፡”
የዘቁም ዛፍ የሚባል፡– ሱራ 37፡62-68 “በመስተንግዶ ይህ ይበልጣልን ወይስ የዘቁም ዛፍ?… እርሷ በገሃነም አዘቅት ውስጥ የምትወጣ ዛፍ ናት፡፡ እንቡጧ ልክ የሰይጣናት ራሶች ይመስላል፡፡ እነርሱም ከርሷ በይዎች ናቸው…” እንዲሁም ሱራ 56፡52 ያንብቡ
የቁስል እጣቢ ብቻ፡– ሱራ 69፡36 “ምግብም ከእሳት ሰዎች ቁስል እጣቢ (እዥ) በስተቀር የለውም”
በገሃነም የተጣለ ሰው ምግብ ዶሪዕ ብቻ? የቁስል እጣቢ ብቻ? ወይስ የዘቁም ዛፍ? እንዲሁም ቁርኣን በገሃነም የተጣለ ሰው የፈላ ውሃ እንደሚጠጣ ይናገራል (ሱራ 56፡54-56፡፡) ለዚህ ጥያቄ በሙስሊሞች የተሰጠ መልስ
- ሙሐመድ ቢሳሳት የሚጐዳው ማነው?
እስኪ የሚከተለውን የቁርኣን ጥቅስ በአንክሮ ያጢኑ፡-
ሱራ 34፡50 “ብሳሳት የምሳሳተው በራሴ ላይ ብቻ ነው ብመራም ጌታዬ ወደኔ በሚያወርደው ነው፡፡”
ሙሐመድ “እኔ ያመንኩትን እመኑ ተከተሉኝ” እያለ መለስ ብሎ ደግሞ “ብሳሳት የምሳሳተው በራሴ ላይ ብቻ ነው” ማለቱ በእጅጉ ያስገርማል፡፡ ይህ ጥቅስ በአረብኛና በእንግሊዘኛ የቁርኣን መጽሐፍት ይበልጥ ግልፅ ሆኖ ይነበባል፡፡ ሐሳቡም ሙሐመድ ትክክል ካልሆነ (ከተሳሳተ) የሚጐዳው እርሱ ብቻ እንደሆነ ነው፡፡ ሙስሊሞች ከአለባበስ ጀምሮ እሰከ ጢም አቆራረጥ ድረስ ሙሐመድን መምሰል ወሳኝ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ሙሐመድ ልክ ከሆነ የእርሱን ትምሕርት የተቀበሉና የተከተሉት ሰዎች ሊድኑ ይችላሉ፡፡ እርሱ ትክክል ካልሆነ ግን ይጠፋሉ፡፡ ምክንያቱም ሐሰተኛ ነቢያትና ሐሰተኛ መምህራንን የሚከተሉ ሰዎች ሁሉ ይጠፋሉና፡፡ ሙሐመድ ትክክለኛ ነቢይ ሆነም አልሆነም ይህ ዓይነቱ ንግግር ስህተት እንደሆነ ለማንም ግልፅ ነው፡፡ ምክንያቱም እርሱ ቢሳሳት የሚጐዳው እርሱን የተከተለ ሰው ሁሉ እንጂ እርሱ ብቻ ስላልሆነ ማለት ነው፡፡ ለዚህ ጥያቄ በሙስሊሞች የተሰጡ ምላሾችን ለማንበብ እዚህ ጋ እና እዚህ ጋ ጠቅ ያድርጉ
- ማርያም የተገለጡላት ስንት መላእክት ነበሩ?
ማርያም ጌታ ኢየሱስን ስትወልድ በመልአክ ለእርስዋ መልክት የተነገረባቸው ቢያንስ ሁለት ቦታዎች በቁርኣን ውስጥ ይገኛሉ፡፡ እነዚህም፡-
ብዙ መላእክት፡– “መላእክትም ያሉትን (አስታውስ)፡- መርየም ሆይ! አላህ በእርግጥ መረጠሸ አነጻሽም በዓለማት ሴቶችም ላይ መረጠሸ” (ሱራ 3.42)፡፡ እንዲሁም “መላእክት ያሉትን (አስታውስ) …” (ሱራ 3.45)፡፡
አንድ መልአክ:- “ከእነሱም መጋረጃን አደረገች መንፈሳችንንም (ጂብሪልን) ወደ እርሷ ላክን ለርሷም ትክክለኛ ሰው ሆኖ ተመሰለላት፡፡ …. እኔ ንፁህን ልጅ ለአንቺ ልሰጥሽ የጌታሽ መልክተኛ ነኝ አላት” (ሱራ 19.17-19)፡፡
በእነዚህ ጥቅሶች መሠረት ምን ያህል መላእክት ናቸው ወደ ማርያም የመጡት? በ3፡42 እና 45 መሠረት መላእክቱ በብዙ ቁጥር ነው የተገለጹት፤ ማለትም በአረብኛ ቋንቋ የብዙ ቁጥር አተረጓጎም ከሦስት ያላነሱ መላእክት እንደነበሩ ነው፡፡ ነገር ግን አሁንም በአረብኛ አካሄድ አራት መላእክት ወይንም ሺ ወይንም ሚሊዮንም ማለትም እንኳን ሊሆን ይችላል፡፡ በ19፡18 ላይ እንደተገጸው ደግሞ ማርያም ከአንድ መልአክ ጋር ብቻ ነው የተነጋገረችው፡፡ አንዱን መልአክ ብቻ መፍራቷም የታያት አንድ መልአክ ስለመሆኑ ሌላው ማረጋገጫ ነው፡፡ ስለዚህ የቱ ነው ትክክል? ለዚህ ጥያቄ በሙስሊሞች የተሰጠ መልስ
- ዓድ በተባለችው ከተማ ላይ የቅጣት ነፋስ ለስንት ቀን ነው የነፈሰው?
ከአንድ ቀን በላይ:- 69:6-7 “ዓድማ በኀይል በምትንሻሻ ብርቱ ነፋስ ተጠፉ። ተከታታይ በሆኑ ሰባት ሌሊቶችና ስምንት መዓልቶች ዉስጥ በነሱ ላይ ለቀቃት ሕዝቹንም በዉስጧ የተጣሉ ሆነዉ ልክ ክፍት የሆኑ የዘንባባ ግንዶች መስለው ታያቸዋለህ።”
41:15-16 “ዓድም በምድር ላይ ያለ አግባብ ኮሩ፤ ከኛ ይበልጥ በኀይል ብርቱማ ነው? አሉም፤ ያ የፈጠራቸው አላህ እርሱ በኀይል ከነርሱ ይበልጥ የበረታ መሆኑን አያዩምን? በታምራታችንም ይክዱነበሩ። በቅርቢቱ ሕይወት የውርደትን ቅጣት ልናቀምሳቸውም፣ በነሱ ላይ የሚንሻሻን ብርቱ ነፋስ፣ መናጢዎች በሆኑ ቀናት ውስጥ ላክንባቸው፤ የመጨረሻይቱም (ዓለም) ስቃይ በጣም አዋራጅ ነው፤ እነርሱም አይረዱም።”
ለአንድ ቀን:- 54:18-19 “ዓድ አስተባበለች ቅጣቴና ማስጠንቀቂያዎቼም እንዴት ነበሩ! እኛ በነርሱ ላይ ዘወትር መናጢ በኾነ ቀን በኀይል የምትንሻሻ ነፋስን ላክንባቸው::” “For We sent against them a furious wind, on a Day of bitter ill-luck”
በመጀመርያዎቹ ጥቅሶች መሠረት በከተማዋ ውስጥ በሚኖሩ ህዝቦች ላይ የአላህ ቅጣት የሆነችው ነፋስ የተላከችው ከአንድ ቀን በላይ ለሆነ ጊዜ እንደሆነ ሲናገር በሁለተኛው ጥቅስ መሰረት ግን ለአንድ ቀን (“ቀን” የሚለው ነጠላ መሆኑን ልብ ይሏል) እንደሆነ እናያለን፡፡ ታድያ የትኛው ነው ትክክል? ለዚህ ጥያቄ በሙስሊሞች የተሰጠ መልስ
- አንዱ የሌላውን ኃጢኣት ይሸከማል ወይንስ አይሸከምም?
አይሸከምም:- 35:18 “ኀጢኣትን ተሸካሚም (ነፍስ)፣ የሌላዋን ሸክም አትሸከምም፤ የተከበደችም (ነፍስ) ወደ ሸክሟ ብትጠራ (ተጠሪው) የቅርብ ዝምድና ባለቤት ቢሆንም እንኳ ከርሷ አንዳችን የሚሸከምላት አታገኝም። የምታስጠነቅቀው፣ እነዚያን ጌታቸውን በሩቅ የሚፈሩትን፣ ሦላትንም አስተካክለው ያደረሱትን ብቻ ነው፤ የተጥራራም ሰው፣ የሚጥራራው ለራሱ ብቻ ነው፤ መመለሻም ወደ አላህ ብቻ ነው።”
53:37-42 “በዚያም (የታዘዘውን) በፈጸመው በኢብራሂም ጽሑፎች ውስጥ ባለው አልተነገረምን?) (እርሱም ኃጢአት) ተሸካሚ ነፍስ የሌላይቱን ነፍስ ኃጢአት አትሸከምም። ለሰውም ሁሉ የሠራው እንጅ ሌላ የለውም። ሥራውም ሁሉ ወደፊት ይታያል። ከዚያም ሙሉውን ምንዳ ይመነዳዋል። መጨረሻውም ወደ ጌታህ ብቻ ነው፡፡”
ይሸከማል:- ሙሐመድ በእርሱ ዘመን የነበሩትን አይሁድ አባቶቻቸው በሠሯቸው ኃጢኣቶች ሳብያ ሲወቅሳቸው በብዙ የቁርኣን ክፍሎች እንመለከታለን፡፡ ለምሳሌ ቁርኣን 2:50-52 እንዲህ ይላል:- “በናንተም ምክንያት ባሕሩን በከፈልን ጊዜ (አስታውሱ)፡፡ ወዲያውም አዳንናችሁ፡፡ የፈርዖንንም ቤተሰቦች እናንተ የምትመለከቱ ኾናችሁ አሰጠምናቸው፡፡ ሙሳንም አርባን ሌሊት በቀጠርነው ጊዜ (የኾነውን አስታውሱ)፡፡ ከዚያም ከርሱ (መኼድ) በኋላ እናንተ በዳዮች ስትኾኑ ወይፈንን (አምላክ አድርጋችሁ) ያዛችሁ፡፡ ከዚያም ከዚህ በኋላ እናንተ ታመሰግኑ ዘንድ ከናንተ ምሕረት አደረግን፡፡”
የወርቁን ጥጃ ያመለኩት አባቶች ሆነው ሳሉ ነገር ግን ልጆች ተወቃሾች ሆነዋል፡፡ ታድያ አንዱ የሌላውን ኃጢኣት ይሸከመል ወይንስ አይሸከምም? የቱን እንቀበል? ለዚህ ጥያቄ በሙስሊሞች የተሰጠ መልስ
- ሙሐመድ የሚያስጠነቅቀው ያመኑ ሰዎችን ብቻ ወይንስ ያላመኑ ሰዎችንም ጭምር?
ያመኑትን ብቻ:- 35:18 “[…]የምታስጠነቅቀው፣ እነዚያን ጌታቸውን በሩቅ የሚፈሩትን፣ ሦላትንም አስተካክለው ያደረሱትን ብቻ ነው፤ የተጥራራም ሰው፣ የሚጥራራው ለራሱ ብቻ ነው፤ መመለሻም ወደ አላህ ብቻ ነው።”
36:11 “የምታስጠነቅቀው ግሣጼን የተከተለንና አልረሕማንን በሩቅየፈራን ሰው ብቻ ነው ፤ በምሕረትና በመልካም ምንዳም አብስረው።”
ያላመኑ ሰዎችንም ጭምር:- 41:13 “(ከእምነት) እንቢ ቢሉም እንደ ዓድና ሠሙድ መቅሠፍት ብጤ የሆነን መቅሠፍት አስጠነቅቃችኋለሁ፣ በላቸው።”
34:46 “የምገሥጻችሁ ባንዲት ነገር ብቻ ነው፤ (እርሷም) ሁለት ሁለት፣ አንድ አንድም፣ ኾናችሁ ለአላህ እንድትነሱ፣ ከዚያም በጓደኛችሁ(በሙሐመድ) ምንም ዕብደት የሌለበት መሆኑን መርምራችሁ እንድትረዱ ነው፤ እርሱ ለናንተ ከብርቱ ቅጣት በስተፊት አስጠንቃቂ ነው እንጂ ሌላ አይደለም፣ በላቸው።”
በፊተኞቹ ጥቅሶች ውስጥ እንደተመለከተው ሙሐመድ የሚያስጠነቅቀው ያመኑትን ሰዎች ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን ከነርሱ ቀጥለው በሚገኙ ጥቅሶች መሰረት ሙሐመድ ላላመኑ ሰውችም ጭምር አስጠንቃቂ እንደሆነና ሲያስጠነቅቃቸውም እናነባለን፡፡ ታድያ የቱ ነው ትክክል? ለዚህ ጥያቄ በሙስሊሞች የተሰጠ መልስ
- መልዕክተኞች የተላኩባቸው ከተሞች በሙሉ ክደዋል ወይንስ ያልካዱ አሉ?
ክደዋል:- 34:34 “በከተማም አስፈራሪን አልላክንም፣ ነዋሪዎችዋ እኛ በዚያ በርሱ በተላካችሁበት ከሐዲዎች ነን ያሉ ቢሆኑ እንጂ።”
And We did not send into a city any warner except that its affluent said,”Indeed we, in that with which you were sent, are disbelievers.”
ያልካዱ አሉ:- ዮናስ የተላከባት ከተማ ህዝቦች አምነዋል – 10:98 “(ከዩኑስ በፊት ካለፉት ከተሞች) ያመነችና እምነትዋ የጠቀማት ከተማ ለምን አልኖረችም ግን የዩኑስ ሕዝቦች ባመኑ ጊዜ በቅርቢቱ ሕይወት የውርደትን ቅጣት ከእነሱ ላይ አነሳንላቸው፡፡ እስከ ጊዜም ድረስ አጣቀምናቸው፡፡”
35:147-148 “ወደ መቶ ሺህ ሰዎችም ዳግመኛ ላክነው ከቶውንም ይጨምራሉ፡፡ አመኑም እስከ ጊዜውም ድረስ አጣቀምናቸው፡፡” ለዚህ ጥያቄ በሙስሊሞች የተሰጠ መልስ
- አላህ ሁሉን አዋቂ ነው ወይንስ አይደለም?
ሁሉን አዋቂ ነው;- ለምሳሌ ቁርኣን 2፡59፤ 2፡96፤ 49፡18፤ ይመልከቱ
ሁሉን አዋቂ አይደለም –
በግምት ይናገራል 53:1 “በኮከብ እምላለሁ በወደቀ (በገባ) ጊዜ። ነቢያችሁ፣ (ሙሀመድ) አልተሳሳተም፤ አልጠመመምም። ከልብ ወለድም አይናገርም። እርሱ (ንግግሩ) የሚወረድ ራዕይ እንጂ ሌላ አይደለም። ኀይሎቹ ብርቱው (መልአክ) አስተማረው። የዕውቀት ባለቤት የሆነው (አስተማረው በተፈጥሮ ቅርጹ ሆኖ በአየር ላይ) ተደላደለም። እርሱ በላይኛው አድማስ ሆኖ። ከዚያም ቀረበ፤ ወረደም። (ከርሱ) የሁለት ደጋኖች ጫፍ ያህል፣ ወይም (ከዚህ) ይበልጥ የቀረበ ሆነም።” “And was at a distance of two bow lengths or nearer.”
ይጠራጠራል 11:12 “በርሱ ላይ የገንዘብ ድልብ ለምን አልተወረደም ወይም ከርሱ ጋር መልአክ ለምን አልመጣም ማለታቸውንም በመፍራት ወደ አንተ ከሚወርደው ከፊሉን ልትተው በርሱም ልብህ ጠባብ ሊኾን ይፈራልሃል፤ አንተ አስፈራሪብቻ ነህ፤ አላህም በነገሩ ሁሉ ተጠባባቂ ነው።”
18:6 “በዚህም ንግግር (በቁርኣን) ባያምኑ፣ በፈለጎቻቸው ላይ በቁጭት ነፍስህን አጥፊ ልትሆን ይፈራልሃል።” “Then perhaps you would kill yourself through grief over them, [O Muhammad], if they do not believe in this message, [and] out of sorrow”
26:3 “አማኞች ባለ መሆናቸው፤ (በቁጭት) ነፍስህን ገዳይ መሆን ይፈራልሃል፤” “Perhaps, [O Muhammad], you would kill yourself with grief that they will not be believers.”
እርግጠኛ ለመሆን ጊዜንና ሁኔታዎችን መጠበቅ ያስፈልገዋል 72:25-28 “የምትስፈራሩበት ነገር ቅርብ፣ ወይም ጌታየ ለርሱ የተወሰነ ጊዜን የሚያደርግለት (ሩቅ)፣ መሆኑን አላውቅም በላቸው። (እርሱ) ሩቁን ሚስጢር ዐዋቂ ነው፣ በሚስጢሩ ላይ አንድንም አያሳውቅም። ከመልክተኛ ለወደደው ቢሆን እንጅ (ለሌላ አይገልጽም)፤ እርሱም ከስተፊቱም ከስተኋላውም ጠባቂዎችን ያደርግለታል። እነሱ ዘንድ ባለው ነገር ዕውቀቱየከበበና ነገሩንም ሁሉ በቁጥር ያጠቃለለ ሲሆን፣ የጌታቸውን መልክቶች ያደረሱ መሆናቸውን ያውቅ ዘንድ (ጠባቂ ያደርጋል)።
“That he may know that they have conveyed the messages of their Lord; and He has encompassed whatever is with them and has enumerated all things in number.”
47:31 “ከናንተም ታጋዮቹንና ታጋሾቹን እስከምናውቅ ወሬዎቻችሁንም እስከምንገልፅ ድረስ በእርግጥ እንሞክራችኋለን።”
3:140 “ቁስል ቢያገኛችሁ ሰዎቹንም መሰሉ ቁስል አግኝቷቸዋል፤ ይኽችንም ቀናት በሰዎች መካከል እናዘዋዉራታለን፤ (እንድትገሠጹና) አላህም እነዚያን ያመኑትን እንዲያዉቅ (እንዲለይ)፣ ከናንተም ሰማዕታትን እንዲይዝ ነዉ፤ አላህም በዳዮችን አይወድም።”
በመጀመርያዎቹ ጥቅሶች ውስጥ አላህ ሁሉን አዋቂ መሆኑ ሲነገረን በሁለተኛዎቹ ውስጥ ግን አላህ ሲጠራጠር በግምት ሲናገር እና ስለ አንዳንድ ጉዳዮችም እርግጠኛ ለመሆን ልክ እንደ ሰው ጊዜንና ሁኔታን መጠበቅ ሲያስፈልገው እናያለን፡፡ ለዚህ ጥያቄ በሙስሊሞች የተሰጠ መልስ
- ከሃዲዎች በፍርድ ቀን ይናገራሉ ወይንስ አይናገሩም?
ይናገራሉ:- 23:105-109 «አንቀጾቼ በእናንተ ላይ የሚነበቡላችሁና በእነርሱ የምታስተባብሉ አልነበራችሁምን» (ይባላሉ)፡፡ ይላሉ «ጌታችን ሆይ! በእኛ ላይ መናጢነታችን አሸነፈችን፡፡ ጠማማዎችም ሕዝቦች ነበርን፡፡ «ጌታችን ሆይ! ከእርሷ አውጣን፡፡ (ወደ ክህደት) ብንመለስም እኛ በደዮች ነን፡፡» (አላህም) «ወራዶች ኾናችሁ በውስጥዋ እርጉ፡፡ አታናግሩኝም» ይላቸዋል፡፡ እነሆ ከባሮቼ «ጌታችን ሆይ! አምነናልና ማረን፡፡ እዘንልንም አንተም ከአዛኞች ሁሉ ይበልጥ አዛኝ ነህ» የሚሉ ክፍሎች ነበሩ፡፡
16:86 “እነዚያም ያጋሩት የሚያጋሩዋቸውን ባዩ ጊዜ፣ ጌታችን ሆይ እነዚህ ከአንተ ሌላእንግ ገዛቸው የነበርነው ተጋሪዎቻችን ናቸው ይላሉ፤ (አማልክቶቹ) እናንተ በእርግጥ ውሸታሞች ናችሁ፣ የማለትንም ቃል ወደነሱ ይጥላሉ።”
20:102-104 “በቀንዱ በሚነፋ ቀን (ሸክማቸው ከፋ)፤ ከሃዲዎችንም በዚያ ቀን (ዓይኖቻቸው) ሰማያዊዎች ሆነው እንሰበስባቸዋለን። ዐሥርን (ቀን) እንጂ አልቆያችሁም በመባባል በመካከላቸው ይንሾካሸካሉ። በሐሳብ ቀጥተኛቸው፣ አንድን ቀን እንጅ አልቆያችሁም በሚል ጊዜ የሚሉትን ነገር እኛ፣ ዐዋቂዎች ነን።”
አይናገሩም:- 17:97 “አላህም ያቀናው ሰው ቅኑ እርሱ ብቻ ነው፤ ያጠመማቸውም ሰዎች ከርሱ ሌላ ለነርሱ ፈጽሞ ረዳት አታገኝላቸውም፤ በትንሣኤ ቀንም ዕውሮች፣ ዲዳዎች፣ ደንቆሮዎችም ሆነው በፊቶቻቸው ላይ (እየተጎተቱ) እንሰበስባቸዋለን፤ መኖሪያቸው ገሀነም ናት፤ (ነዲድዋ) በደከመች ቁጥር፣ መንቀልቀልን እንጨምርባቸዋለን።”
16:84 “ከየሕዝቡም ሁሉ መስካሪን የምንቀሰቅስበትን ቀን (አስታውስ)፤ ከዚያም ለነዚያ ለካዱት (ንግግር) አይፈቀድላቸውም፤ እነሱም በወቀሳ አይታለፉም።”
77:28-36 “ለአስተባባዮች በዚያ ቀን ወዮላቸው። ወደዚያ በርሱ ታስተባብሉ ወደ ነበራችሁት (ቅጣት) አዝግሙ። ባለ ሦስት ቅርንጫፎች፣ ወደ ሆነው ጥላ አዝግሙ፤ (ይባላሉ) አጠላይ ያልኾነ፤ ከእሳቱም ላንቃ የማያድን ወደ ሆነው፣ (አዝግሙ)። እርሷ እንደ ታላላቅ ሕንጻ የሆኑን ቃንቄዎች ትወርውራለች። (ቃንቄውም) ልክ ዳለቻዎች ግመሎችን ይመስላል። ለአስተባባዮች በዚያን ቀን ወዮላቸው። ይህ የማይናገሩበት ቀን ነው። ይቅርታም ይጠይቁ ዘንድ ለነርሱ አይፈቅድላቸውም።”
በመጀመርያዎቹ ጥቅሶች መሠረት ከሃዲዎች በፍርድ ቀን ከሚያጋሯቸው አማልክት ጋር, ከአላህ ጋር እንዲሁም እርስ በዕርሳቸው የሚነጋገሩ ሲሆን ከዝያ ቀጥለው በተቀመጡ ጥቅሶች መሰረት ግን እንደማይናገሩ ተነግሯል፡፡ ታድያ የቱ ነው ትክክል? ለዚህ ጥያቄ በሙስሊሞች የተሰጠ መልስ
- አላህ ፍጥረቱን በቀጥታ ያናግራል ወይስ አያናግርም?
ያናግራል፡- ሱራ 4፡64 “ከዚህም በፊት በአንተ ላይ በእርግጥ የተረክናቸውን መልክተኞች፣ ባንተ ላይም ያልተረክናቸውን መልክተኞች (እንደላክን፣ ላክንህ)። አላህም ሙሳን ማነጋገርን አነጋገረው።”
And [We sent] messengers about whom We have related [their stories] to you before and messengers about whom We have not related to you. And Allah spoke to Moses with [direct] speech.
ይህ የቁርኣን ጥቅስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ሙሴ የተነገረውን የሚያንጸባርቅ ነው፡- “እግዚአብሔርም ሰው ከባልንጀራው ጋር እንደሚነጋገር ፊት ለፊት ከሙሴ ጋር ይነጋገር ነበር። ሙሴም ወደ ሰፈሩ ይመለስ ነበር፤ ነገር ግን ሎሌው ብላቴና የነዌ ልጅ ኢያሱ ከድንኳኑ አይለይም ነበር።” (ዘጸአት 33፡11)
አያናግርም፡- ሱራ 42፡51 “ለሰው አላህ በራእይ፣ ወይም ከግርዶ ወዲያ፣ ወይም መልክተኛን (መልአክን) የሚልክና በፈቃዱ የሚሻውን ነገር የሚያወርድለት ቢሆን እንጅ፣ (በገሃድ) ሊያናግረው ተገቢው አይደለም። እርሱ የበላይ ጥበበኛ ነውና።” ለዚህ ጥያቄ በሙስሊሞች የተሰጠ መልስ
- አላህ የሺርክ ኃጢአትን (በእርሱ ላይ ሌሎች አማልክት ማምለክን) ይቅር ይላል ወይስ አይልም?
ይቅር ይላል፡- ሱራ 4፡153 “የመጽሐፉ፣ ሰዎች በነሱ ላይ ከሰማይ መጽሐፍን እንድታወርድ ይጠይቁሃል ከዚያም የከበደን ሙሳን በእርግጥ ጠይቀዋል፤ አላህንም በግልጽ አሳየን ብለዋል፤ በበደላቸውም መብረቅ ያዘቻቸው። ከዚያም ታምራቶች፣ ከመጡዋቸው በኋላ ወይፈኑን (አምላክ አድርገው) ያዙ፤ ከዚያም ይቅር አልን። ሙሳንም ግልጽ ስልጣንን ሰጠነው።”
ይቅር አይልም፡- ሱራ 4፡48 “አላህ በርሱ ማጋራትን በፍፁም አይምርም፤ ከዚህ ሌላ ያለውንም (ኀጢአት) ለሚሻው ሰው ይምራል። በአላህም የሚያጋራ ሰው ታላቅን ኀጢያት በእርግጥ ቀጠፈ።”
“አላህ በርሱ የማጋራትን (ወንጀል) አይምርም ከዚህም ወዲያ ያለውን፣ ለሚሻ ሰው ይምራል። በአላህም የሚያጋራ ሰው (ከውነት) የራቀን መሳሳት በእርግጥ ተሳሳተ።”
በመጀመርያው ጥቅስ ላይ እንደተገለጸው እስራኤላውያን የእውነተኛውን አምላክ ተዓመራት ያዩና ማንነቱን የሚያውቁ ቢሆኑም የወርቁን ጥጃ አምልከዋል፡፡ ንስሐ ሲገቡ ግን ይቅርታን አገኙ፡፡ የኋለኞቹ ጥቅሶች ግን አላህ እንዲህ ያለውን ኃጢአት በፍጹም ይቅር እንደማይል ይናገራሉ፡፡ ግጭቱ ግልፅ ነው፡፡ ለዚህ ጥያቄ በሙስሊሞች የተሰጠ መልስ
- ሰው ነፃ ፈቃድ አለው ወይስ የለውም?
የለውም፡- ሱራ 10፡100 “ለማንኛዋም ነፍስ በአላህ ፈቃድ ቢሆን እንጂ ልታምን (ችሎታ) የላትም፡፡ (አላህ ለከፊሎቹ እምነትን ይሻል)፡፡ በእነዚያም በማያውቁት ላይ ርክሰትን ያደርጋል፡፡”
ነፃ ፈቃድ አለው፡- ሱራ 81፡27-18 “እርሱ የዓለማት መገሠጫ እንጂ ሌላ አይደለም። ከናንተ ቀጥተኛ መሆንን ለሻ ሰው መገሠጫ ነው።”
It is not except a reminder to the worlds. For whoever wills among you to take a right course.
ሱራ 30፡9 “በምድር ላይ አይኼዱምና የነዚያን ከበፊታቸው የነበሩትን ሰዎች ፍጻሜ እንዴት እንደ ነበረ አይመለከቱምን? በኀይል ከነርሱ ይበልጥ የጠነከሩ ነበሩ፤ ምድርንም አረሱ፤ (እነዚህ) ከአለሟትም የበዛ አለሟት፤ መልክተኞቻቸውም በታምራቶች መጡባቸው፤ (አስተባበሉምና ጠፉ)፤ አላህም የሚበድላቸው አልነበረም፤ ግን ነፍሶቻቸውን ይበድሉ ነበሩ።” ለዚህ ጥያቄ በሙስሊሞች የተሰጠ መልስ
- ክፋትና ደግነት ከማነው?
ክፉም ደጉም ከአላህ፡- ሱራ 4፡78 “የትም ስፍራ ብትኾኑ፣ በጠነከሩ ሕንጻዎች ውስጥ ብትኾኑም እንኳን ሞት ያገኛችኋል፤ ደግም ነገር ብታገኛቸው ይህች ከአላህ ዘንድ ናት፣ ይላሉ፤ መከራም ብታገኛቸው ይህቺ ከአንተ ዘንድ ናት ይላሉ፤ ሁሉም (ደጉም ክፉዉም) ከአላህ ዘንድ ነው በላቸው፤ ለነዚህም ሰዎች፣ ንግግርን ሊረዱ የማይቀርቡት ምን አላቸው?”
ክፉ ከሰው ደግነት ከአላህ፡- ሱራ 4፡79 “ከደግ ነገር የሚያገኝህ ከአላህ (ችሮታ) ነው፤ ከመከራም የሚደርስብህ ከራስህ (ጥፋት የተነሳ) ነው፤ በሰዎችም ሁሉ መልክተኛ ኾነህ ላክንህ መስካሪም በአላህ በቃ።”
What comes to you of good is from Allah, but what comes to you of evil, [O man], is from yourself. And We have sent you, [O Muhammad], to the people as a messenger, and sufficient is Allah as Witness. ለዚህ ጥያቄ በሙስሊሞች የተሰጠ መልስ
- ሙስሊሞች የማያምኑ ሰዎችን እንዲዋጉ ወይስ ይቅር እንዲሉ ነው የታዘዙት?
እንዲዋጉ፡- ሱራ 9፡29 “ከነዚያ መጽሐፍን ከተሰጡት ሰዎች፣ እነዚያን በአላህ በመጨረሻዉ ቀን የማያምኑትን፣ አላህና መልክተኛዉ እርም ያደረጉትንም እርም የማያደርጉትንና እዉነተኛዉንም ሃይማኖት የማይቀበሉትን እነርሱ የተዋረዱ ሆነዉ ግብርን በእጆቻቸው እስከሚሰጡ ድረስ ተዋጉዋቸው።”
ይቅር እንዲሉ፡- ሱራ 45፡14 “ለነዚያ ለአመኑት ሰዎች፣ (ምሕረት አድርጉ)፣ በላቸው፤ ለነዚያ የአላህን ቀኖች ለማይፈሩት ይምራሉና፣ ሕዝቦችን ይሠሩት በነበሩት ነገር ይመነዳ ዘንድ፣ (ምሕረት አድርጉ በላቸው)።” ለዚህ ጥያቄ በሙስሊሞች የተሰጠ መልስ
- የሙሐመድ ኃላፊነት መልእክቱን ማድረስ ብቻ ወይስ ያልተቀበሉትን በኃይል ማስለም?
መልእክቱን ማድረስ ብቻ፡- ሱራ 3፡20 “ቢከራከሩህም :- ፊቴን ለአላህ ሰጠሁ፤ የተከተሉኝም ሰዎች (እንደዚሁ ለአላህ ሰጡ) በላቸዉ፤ ለእነዚያም መጽሐፍን ለተሰጡት ሰዎችና ለመሀይሞቹ፦ሰለችማሁን? በላቸዉ፤ ቢሰልሙም በእርገጥ ተመሩ እምቢ ቢሉም በአንተ ላይ ያለበህ ማድረስ ብቻ ነዉ:: አላህም ባሮቹን ተመልካች ነው::”
ያልተቀበሉትን በኃይል ማስለምም ጭምር፡- ሱራ 8፡38-39 “እውከትም እስከማትገኝ ሃይማኖትም ሁሉ ለአላህ ብቻ እስከሚሆን ድረስ ተጋደሉዋቸው፤ ቢከለከሉም አላህ የሚሠሩትን ሁሉ ተመልካች ነው።” ለዚህ ጥያቄ በሙስሊሞች የተሰጠ መልስ
- የሰውን ነፍስ የሚያወጣው ማን ነው?
መልአከ ሞት (አንድ መልአክ)፡- ሱራ 32፡11 “በእናንተ የተወከለው መልአከ ሞት ይገድላችሗል፤ ከዚያም ወደ ጌታችሁ ትመለሳላችሁ፣ በላቸው።”
ብዙ መላእክት፡- ሱራ 47:27 “መላእክትም ፊቶቻቸውንና ጀርቦቻቸውን የሚመቱ ሲሆኑ በገደሉዋቸው ጊዜ (ሁኔታቸው) እንዴት ይሆናል?” ለዚህ ጥያቄ በሙስሊሞች የተሰጠ መልስ
- ሙስሊሞች ስንት እናቶች ናቸው የሏቸው?
አንዲት እናት ብቻ፡- ሱራ 58:2 “እነዚያ ከናንተ ውስጥ ከሚስቶቻቸው እንደናቶቻቻን ጀርባዎች ይሁኑብን በማለት የሚምሉ እነሱ እናቶቻቸው አይደሉም፤ እናቶቻቸው አሊያ የወለዱዋቸው ብቻ ናቸው። እነርሱም (በዚህ ቃል) ከንግግር የተጠላንና ውሸትን በእርግጥ ይናገራሉ፤ አላህም (ለሚጸጸት) ይቅርባይ መሃሪ ነው።”
ብዙ እናቶች፡- ሱራ 33:6 “ነቢዩ፣ በምእምናን ከነፍሶቻቸው ይበልጥ ተገቢ ነው፤ ሚስቶቹም እናቶቻቸው ናቸው፤ የዝምድና ባለ ቤቶችም ከፊላቸው በከፊሉ (ውርስ) በአላህ መጽሐፍ ውስጥ ከምእምናንና ከስደተኞቹ ይልቅ የተገባቸው ናቸው፤ ግን ወደ ወዳጆቻችሁ (በኑዛዜ) መልካምን ብትሰሩ (ይፈቀዳል)፤ ይህ መጽሐፍ ውስጥ የተመዘገበ ነው።”
የመጀመርያው ጥቅስ ሙስሊሞች አንዲት እናት ብቻ እንዳለቻቸውና ሌሎች ሴቶችን በተምሳሌታዊ መንገድ “እናቶች” ብለው መጥራታቸው ውሸትና በአላህ ዘንድ የተጠላ ንግግር እንደሆነ የሚገልፅ ሲሆን ሁለተኛው ጥቅስ ደግሞ የሙሐመድ ሚስቶች ተምሳሌታዊ በሆነ መንገድ የሙስሊሞች እናቶች እንደሆኑ ይናገራል፡፡ ግጭቱ ግልፅ ነው፡፡ ለዚህ ጥያቄ በሙስሊሞች የተሰጠ መልስ
- መዳን የሚችሉት እነ ማን ናቸው?
ሙስሊሞች ብቻ፡- ሱራ 3:85 “ከኢስላም ሌላ ሃይማኖትን የሚፈልግ ሰዉ፣ ፈጽሞ ከርሱ ተቀባይ የለዉም፤ እርሱም በመጨረሻይቱ ዓለም ከከሳሪዎች ነዉ።”
ሱራ 3:19 “አላህ ዘንድ (የተወደደ) ሃይማኖት ኢስላም ብቻ ነዉ፣ እነዚያም መጽሐፉን የተሰጡት ሰዎች በመካከላቸዉ ላለዉ ምቀኝነት እዉቀቱ ከመጣላቸዉ በኋላ እንጅ አልተለያዩም፤ በአላህም አንቀጾች የሚክድ አላህ ምርመራዉ ፈጣን ነዉ::”
አይሁድ፣ ክርስቲያኖች፣ ሳቢያኖች እንዲሁም በአላህና በመጨረሻው ቀን ያመነ ሁሉ ይድናል፡- ሱራ 5:69 “እነዚያ ያመኑና እነዚያም ይሁዳውያን የኾኑ፣ ሳቢያኖችም ክርስቲያኖችም፣ (ከነርሱ) በአላህና በመጨረሻው ቀን ያመነና መልካምን ሥራ የሠራ ሰው፣ በነርሱ ላይ ፍርሃት የለባቸውም፤ እነርሱም አያዝኑም።”
ሱራ 2:62 “እነዚያ ያመኑ እነዚያም ይሁዳውያን የኾኑ፣ ክርስቲያኖችም፣ ሳቢያኖችም (ከእነርሱ) በአላህና በመጨረሻው ቀን ያመነ መልካምንም ሥራ የሠራ ለነርሱ በጌታቸው ዘንድ ምንዳቸው አላቸው፡፡ በነርሱም ላይ ፍርሃት የለባቸውም፤ እነሱም አያዝኑም፡፡” ለዚህ ጥያቄ በሙስሊሞች የተሰጠ መልስ
- ያላመኑ ቤተሰቦችን መወዳጀት ተፈቅዷል ወይስ አልተፈቀደም?
ተፈቅዷል፡- ሱራ 31:15 “ለአንተ በርሱ ዕውቀት የሌለህን ነገር በኔ እንድታጋራ ቢታገሉህም፣ አትታዘዛቸው፤ በቅርቢቱም ዓለም፣ በመልካም ስራ ተወዳጃቸው፤ ወደኔም የተመለሰን ሰው መንገድ ተከተል፤ ከዚያም መመለሻችሁ ወደኔ ነው፤ ትሰሩት የነበራችሁንም ሁሉ እነግራችኋለሁ፤ (አልነው)።”
አልተፈቀደም፡- ሱራ 9:23 “እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አባቶቻችሁና ወንድሞቻችሁ ክሕደትን ከእምነት አብልጠው ቢወዱ፣ ወዳጆች አድርጋቸሁ አትያዙዋቸው፤ ከናንተም ዉስጥ ወዳጅ የሚያደርጋቸው፣ እነዚያ እርሱ በዳዮች ናቸው፡፡” ለዚህ ጥያቄ በሙስሊሞች የተሰጠ መልስ
- ሙስሊሞች ከክርስቲያኖች ጋር እንዲወዳጁ ተፈቅዷል ወይስ አልተፈቀደም?
ተፈቅዷል፡- ሱራ 5:82 “ይሁዶችንና እነዚያን ያጋሩትን፣ ለነዚያ ለአመኑት በጠላትነት ከሰዎች ሁሉ ይበልጥ የበረቱ ሆነው በእርግጥ ታገኛለህ፤ እነዚያንም እኛ ክርስቲያኖች ነን ያሉትን ለነዚያ ለአመኑት በወዳጅነት በእርግጥ ይበልጥ የቀረቧቸው ሆነው ታገኛለህ፤ ይህ ከነሱ ውስጥ ቀሳውስትና መነኮሳት በመኖራቸውና እነሱም የማይኮሩ በመሆናቸው ነው።”
አልተፈቀደም፡- ሱራ 5:51 “እላንተ ያላመናችሁ ሆይ! ይሁዶችንና ክርስቲያኖችን ረዳቶች አድርጋችሁ አትያዙ፤ ከፊላቸው ለከፊሉ ረዳቶች ናቸው፤ ከናንተም ውስጥ ረዳቶች የሚያደርጋቸው ሰው እርስ ከነርሱ ነው፤ አላህ አመጠኞችን ሕዝቦች አያቀናም።” ለዚህ ጥያቄ በሙስሊሞች የተሰጠ መልስ
- መልእክተኞች ሆነው የተላኩት ሰዎች ብቻ ወይስ ሌሎች ፍጥረታትም ጭምር?
ሰዎች ብቻ፡- ሱራ 12:109 “ካንተ በፊትም ከከተሞች ሰዎች ወደነርሱ ራዕይ የምናወርድላቸው የሆኑን ወንዶችን እንጂ አልላክንም፤ በምድር ላይ አይኼዱምና የነዚያን ከነሱ በፊት የነበሩትን ሰዎች መጨረሻ አይመለከቱምን? የመጨረሻይቱም አገር፣ ለነዚያ ለተጠነቀቁት በእርግጥ የተሻለች ናት፤ አታውቁምን?”
ሌሎች ፍጥረታትም ተልከዋል፡- ሱራ 22:75 “አላህ ከመላእክት ውስጥ መልክተኞችን ይመርጣል፤ ከስዎችም፣ (እንደዚሁ) አላህ ስሚ ተመልካች ነው።” ለዚህ ጥያቄ በሙስሊሞች የተሰጠ መልስ
- የሙሐመድ ገነት መግባት እርግጥ ነው ወይስ አይታወቅም?
እርግጥ ነው፡- ሱራ 48፡1-2 “እኛ ላንተ ግልጽ የሆነን መክፈት ከፈትንልህ። አላህ ከኃጥያትህ ያለፈውንና የሚመጣውን ላንተ ሊምር ጸጋውንም ባንተ ላይ ሊሞላ ቀጥተኛውንም መንገድ ሊመራህ፣ (ከፈተልህ)።”
አይታወቅም፡- ሱራ 46:9 “ከመልክተኞች ብጤ የሌለኝ አይደለሁም በኔም በናንተም ምን እንደሚሠራም አላውቅም ወደኔ የሚወረደውን እጅግ ሌላን አልከተልም እኔም ግልጽ አስፈራሪ እንጅ ሌላ አይደለሁም በላቸው፡፡” ለዚህ ጥያቄ በሙስሊሞች የተሰጠ መልስ
- ዮናስ በምድረ በዳ ተጥሏል ወይስ አልተጣለም?
አልተጣለም፡- ሱራ 68:49 “ከጌታው የሆነ ጸጋ ባላገኘው ኖሮ፣ በምድረ በዳ ተወቃሽ ሆኖ በተጣለ ነበር።”
ተጥሏል፡- ሱራ 37፡145 “እርሱ በሽተኛ ሆኖ በቃይ በሌለው (በባሕር) ዳርቻ ላይ ጣልነውም፡፡” ለዚህ ጥያቄ በሙስሊሞች የተሰጠ መልስ
- ህፃናት ጡት እንዲጥሉ አላህ ያዘዘው ከምን ያህል ጊዜ በኋላ ነው?
ከ30 ወራት በኋላ፡- ሱራ 46:15 “ሰውንም በወላጆቹ በጎ መዋልን በጥብቅ አዘዝነው እናቱ በችግር ላይ ሆና አረገዘችው በችግርም ወለደችው፥ እርግዝናውና ከጡት መለያውም ሠላሳ ወር ነው ጥርንካሬውንም ወቅት በደረሰ ጊዜ (ከዚያ አልፎ) አርባ ዓመትንም በደረሰ ጊዜ ጌታዬ ሆይ ያችን በኔ ላይና በወላጆቼ ላይ የለገስካትን ጸጋህን እንዳመሰግን የምትወደውንም መልካም ሥራ እንድሠራ ምራኝ ዘሮቼንም ለኔ አብጅልኝ እኔ ወዳንተ ተመለስኩ እኔም ከሙስሊሞች ነኝ አለ፡፡”
ከሁለት ዓመት (ከ24 ወራት) በኋላ፡- ሱራ 31:14 “ሰውንም በወላጆቹ (በጎ እንዲያደርግ ) በጥብቅ አዘዝነው፤ እናቱ ከድካም በላይ በሆነ ድካም አረገዘችው፤ ጡት መጣያውም በሁለት ዓመት ውስጥ ነው፤ ለኔም ለወላጆችህም አመስግን በማለት (አዘዝነው)፤ መመለሻው ወደኔ ነው።”
ምናልባት 30 ወር የሆነው ከእርግዝና ጋር ስለ ሆነ እንጂ ትክክለኛው 24 ነው ሊባል ይችላል ነገር ግን 24 ላይ 9 ወር ስንጨምር 33 ወር ስለሚሆን ግጭቱ እንዳለ ነው፡፡ ለዚህ ጥያቄ በሙስሊሞች የተሰጠ መልስ
- ለጦርነት ላለመዝመት ሙሐመድን ፈቃዱ የጠየቁት ሁሉ ተወቃሾች ናቸው ወይስ አይደሉም?
ሁሉም ተወቃሾች ናቸው፡- 9፡44-45 “እነዚያ በአላህና በመጨረሻዉ ቀን የሚያምኑት በገንዘቦቻቸዉና በነፍሶቻቸው ከመታገላቸው (ለመቅረት) ፈቃድን አይጠይቁህም፤ አላህም የሚፈሩትን ዐዋቂ ነው። ፈቃድን የሚጠይቁህ እነዚያ በአላህና በመጨረሻዉ ቀን የማያምኑት ልቦቻቸዉም የተጠራጠሩት ብቻ ናቸው፤ እነሱም በጥረጣሬያቸው ዉስጥ ይዋልላሉ።”
የማይወቀሱ አሉ፡- 9፡93 “(የወቀሳ) መንገዱ በነዚያ እነሱ ባለጸጋዎች ሆነዉ ሳሉ ለመቅረት ፈቃድ በሚጠይቁህ ሰዎች ላይ ብቻ ነዉ፣ ከቀሪዎቹ ጋር መኾናቸውን ወደዱ፤ አላህም በልቦቻቸው ላይ አተመባቸው፣ ስለዚህ እነሱ አያውቁም።”
በመጀመርያው ጥቅስ ላይ ከጦርነት ዘመቻ ለመቅረት ፈቃድ የሚጠይቁት “በአላህና በመጨረሻዉ ቀን የማያምኑት ልቦቻቸዉም የተጠራጠሩት ብቻ” እንደሆኑ በመግለፅ ሁሉንም ተወቃሽ የሚያድርግ ሲሆን በኋለኛው ጥቅስ ግን ቃሉን በማጠፍ ባለጸጋዎች ሆነው ሳሉ ለመቅረት ፈቃድ የሚጠይቁት ብቻ ተወቃሾች እንደሆኑ ይናገራል፡፡ ግጭቱ ግልፅ ነው፡፡ ለዚህ ጥያቄ በሙስሊሞች የተሰጠ መልስ
- ሙሴ ሕዝቡን ነፃ ለማውጣት በተላከ ጊዜ ያመኑለት ጥቂት ወገኖቹ ብቻ ወይንስ የግብፅ ደጋሚዎችም ጭምር?
ጥቂት እስራኤላውያን ብቻ፡- 10፡83 “ለሙሳም ከፈርዖንና ከሹማምንቶቻቸው ማሰቃየትን ከመፍራት ጋር ከወገኖቹ የኾኑ ጥቂቶች ትውልዶች እንጂ አላመኑለትም፡፡ ፈርዖንም በምድር ላይ በእርግጥ የኮራ ነበር፡፡ እርሱም በእርግጥ ወሰን ካለፉት ነበር፡፡”
But no one believed Moses, except [some] youths among his people, for fear of Pharaoh and his establishment that they would persecute them. And indeed, Pharaoh was haughty within the land, and indeed, he was of the transgressors.
የግብፅ ደጋሚዎችም ጭምር፡- 7፡120-122 “ድግምተኞችም ሰጋጆች ኾነው ወደቁ። አሉ፦ በዓለማት ጌታ አመንን፤ በሙሳና በሃሩን ጌታ።” (እንዲሁም 20፡56-73፣ 26፡29-51)
የመጀመርያው ጥቅስ በሙሴ ያመኑት ጥቂት የገዛ ወገኖቹ ብቻ እንደሆኑ የሚናገር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የግብፅ ደጋሚዎችም ጭምር እንዳመኑበት ይናገራል፡፡ ግጭቱ ግልፅ ነው፡፡ ለዚህ ጥያቄ በሙስሊሞች የተሰጠ መልስ
- ዒሳ እንደ ማንኛውም ሰው የሆነ ሰው ወይንስ የአላህ ቃልና መንፈስ ብቻ?
እንደ ማንኛውም ሰው የሆነ ሰው፡- 5፡75 “የመርየም ልጅ አልመሲሕ ከበፊቱ መልክተኞች በእርግጥ ያለፉ የሆነ መልክተኛ እንጅ ሌላ አይደለም፤ እናቱም በጣም እውነተኛ ናት፤ (ሁለቱም) ምግብን የሚበሉ ነበሩ፤ አንቀጾችን ለነርሱ (ለከሐዲዎች) እንዴት እንደምናብራራ ተመልከት፤ ከዚያም (ከውነት) እንዴት እንደሚመለሱ ተመልከት።”
የአላህ ቃልና መንፈስ ብቻ፡- 4፡171 “እላንተ የመጽሐፉ ሰዎች ሆይ! በሃይማኖታችሁ ወሰንን አትለፉ፤ በአላህም ላይ እውነትን እንጂ አትናገሩ፤ የመርየም ልጅ አልመሲሕ ዒሳ፣ የአላህ መልክተኛ፣ ወደ መርየም የጣላት (የሁን) ቃሉም ከርሱ የሆነ መንፈስም ብቻ ነው፤ …”
በመጀመርያው ጥቅስ ላይ ዒሳ እንደ ማንኛውም ሰው ሰው መሆኑ የተነገረ ሲሆን በሁለተኛው ጥቅስ ላይ ግን የአላህ ቃልና መንፈስ ብቻ እንደሆነ ተነግሮናል፡፡ የቱ ነው ትክክል? በቅንፍ (የሁን) የሚለው የአማርኛ ተርጓሚዎች የጨመሩት እንጂ በኦሪጅናል አረብኛው ውስጥ አይገኝም፡፡ ለዚህ ጥያቄ በሙስሊሞች የተሰጠ መልስ
- የዒሳ “አፈጣጠር” እንደ አዳም ከአፈር ወይንስ በልደት?
እንደ አዳም፡- 3፡59 “አላህ ዘንድ የዒሳ ምሳሌ፥ እንደ አዳም ብጤ ነዉ፤ ከዐፈር ፈጠረዉ፤ ከዚያም ለርሱ (ሰዉ) ሁን አለዉ፥ ሆነም።”
Indeed, the example of Jesus to Allah is like that of Adam. He created Him from dust; then He said to him, “Be,” and he was.
በልደት፡- 19፡22-23 “ወዲያዉኑም አረገዘችዉ፤ በርሱም (በሆድዋ ይዛዉ) ወደ ሩቅ ስፍራ ገለል አለች። ምጡም ወደ ዘንባባይቱ ግንድ አስጠጋት…”
በመጀመርያው ጥቅስ ውስጥ የዒሳ “አፈጣጠር” ልክ እንደ አዳም እንደሆነ ይናገራል፡፡ አዳም ያለ አባትና ያለ እናት የተፈጠረ ሲሆን ከአፈር ነበር የተፈጠረው፡፡ በሁለተኛው ጥቅስ ውስጥ እንደተገለፀው ግን ዒሳ ከእናት ተረግዞ ተወልዷል፡፡ የሁለቱ አፈጣጠር ተመሳሳይ ባለመሆኑ ግጭቱ ግልፅ ነው፡፡ ለዚህ ጥያቄ በሙስሊሞች የተሰጠ መልስ
- ዒሳ ፈጣሪ ነው ወይስ አይደለም?
ፈጣሪ ነው፡- “ከእግዚአብሔር ልዩ ባሕርያት መካከል አንዱ ፈጣሪነቱ ነው፡፡ ይህ መለያው ነው፡፡ ፈጣሪነቱ ከሁሉም ነገር ልዩ የሚያደርገው ሲሆን መታወቂያው ነው፡፡ ይሁን እጂ በቁርኣን ውስጥ ኢየሱስ ይህ የፈጣሪ ልዩ ባሕርይ እንዳለውና በተመሳሳይ መንገድ ሲፈፅም እንመለከታለን፡፡ ይህ እግዚአብሔር አዳምን ከአፈር አበጅቶት የሕይወትን እስትንፋስ እፍ ካለበት ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡
“ጌታህ «ለመላእክት እኔ ሰውን ከጭቃ ፈጣሪ ነኝ ባለ ጊዜ» (አስታውስ)፡፡«ፍጥረቱንም ባስተካከልኩና ከመንፈሴ በነፋሁበት ጊዜ ለእርሱ ሰጋጆች ኾናችሁ ውደቁ» (አልኩ)፡፡” (ሱራ 38፡71-75)
ኢየሱስ ከፈጠረበት መንገድ ጋር ፍፁም ተመሳሳይ ነው፡-
“ወደ እሥራኤልም ልጆች መልክተኛ የደርገዋል፤ (ይላልም) ፡-እኔ ከጌታዬ ዘንድ በታምር መጣኋችሁ። እኔ ለናንተ ከጭቃ አንደ ወፍ ቅርጽ እፈጥራለሁ፤ በርሱም እተነፍስበታለሁ፤ በአላህም ፈቃድ ወፍ ይሆናል። በአላህም ፈቃድ ዕዉር ሆኖ የተወለደን፥ ለምጸኛንም፥ አድናለሁ፤ ሙታንንም አስነሳለሁ። የምትበሉትንና በቤታችሁ የምታደልቡትንም ሁሉ እነግራችኋለሁ፤ የምታምኑ እንደሆናችሁ ለእናንተ በዚህ ዉስጥ በእርግጥ ታምር አለበት።” (ሱራ 3፡49)
ኢየሱስ ወፎችን ከጭቃ የመፍጠሩ ትረካ ከጥንታዊ የክርስቲያን አፈታሪክ የተቀዳ በመሆኑ የኢየሱስን አምላክነት ያሳያል፤ እናም ለኢየሱስ የመፍጠር ችሎታና ሕይወት ሰጪነት ዕውቅናን በመስጠት አምላክነቱን የሚያንጸባርቅ ነው፡፡ ይህ ትረካ አሁን በቁርኣን ውስጥ ይገኛል፡፡ የፈጣሪ እስትንፋስ የኢየሱስ የራሱ እስትንፋስ ሆኖ እናያለን! ይህም ቁርኣን የኢየሱስን የአምላክነት ታሪክ ይዞ ለመገኘቱ ማረጋገጫ ነው፡፡
በቁርኣን ውስጥ ኢየሱስ በፈጣሪ ፈቃድ መሠረት ይህንን እንደፈፀመ ቢናገርም ዳሩ ግን መፍጠር ፈጣሪ ከማንም ጋር የማይጋራው መለያው በመሆኑ ምክንያት ይህ የኢየሱስን አምላክነት ውድቅ አያደርግም፡፡ ፈጣሪ ይህንን ችሎታ ለኢየሱስ ካጋራው ኢየሱስ የፈጣሪን ልዩ ችሎታ ተጋርቷል ማለት ነው፡፡ ፈጣሪ ይህንን ችሎታ ለሌሎች የሚያጋራ ከሆነ ልዩ መሆኑ ይቀራል፡፡ ስለዚህ በጥቅሱ መሠረት ኢየሱስ ፈጣሪ ነው፡፡
አይደለም፡- በሌሎች የቁርኣን ክፍሎች ግን የኢየሱስ ፈጣሪነት ተክዷል፡፡ ይህም ግልፅ ግጭት ነው፡፡ ለዚህ ጥያቄ በሙስሊሞች የተሰጠ መልስ
- ኢብሊስ (ዲያብሎስ) መልአክ ወይንስ ጂን?
መልአክ- 2:34 “ለመላእክትም «ለአደም ስገዱ» ባልን ጊዜ (አስታውስ) ፡፡ ሁሉም ወዲያውኑ ሰገዱ፤ ኢብሊስ (ዲያብሎስ) ብቻ ሲቀር እምቢ አለ፤ ኮራም ከከሓዲዎቹም ኾነ፡፡”
ጂን- 18:50 “ለመላእክትም ለአደም ስገዱ፥ ባልናቸው ጊዜ (የሆነውን አስታውስ)። ወዲያውም ሰገዱ፤ ኢብሊስ ብቻ ሲቀር፤ ከጋኔን (ጎሳ) ነበር፤…”
በመጀመርያው ጥቅስ መሠረት አላህ መላእክት ለአዳም ይሰግዱ ዘንድ ያዘዛቸው ሲሆን ነገር ግን ከነርሱ መካከል ዲያብሎስ ብቻ ትዕዛዙን ሳያከብር ቀርቷል ከዚህ የተነሳም ከገነት ተባሯል፡፡ ዲያብሎስ መልአክ ባይሆን ኖሮ ትዕዛዙ ስላማይመለከተው ባለመስገዱ አይጠየቅም ነበር፡፡ ከዝያ ቀጥሎ በተቀመጠው ጥቅስ መሠረት ግን ዲያብሎስ ከጋኔን ጎሳ ነው፡፡ ከሁለቱ የትኛው ነው ትክክል? ለዚህ ጥያቄ በሙስሊሞች የተሰጠ መልስ
- አላህ ብቸኛ ፈራጅ ወይስ በፍርዱ ተጋሪ አለው?
ብቸኛ ፈራጅ፡- 18፡26 “አላህ የቆዩትን ልክ ዐዋቂ ነው በላቸው፤ የሰማያትና የምድር ምስጢር የሱ ብቻ ነው፤ እርሱ ምን ያይ! ምን ይሰማም! ለነርሱ ከርሱ በቀር ምንም ረዳት የላቸውም፤ በፍርዱም አንድንም አያጋራም።”
6፡114 “እርሱ ያ መጽሐፉን የተብራራ ኾኖ ወደእናንተ ያወረደ ሲኾን «ከአላህ ሌላ ዳኛን እፈልጋለሁን» (በላቸው)፡፡ እነዚያም መጽሐፍን የሰጠናቸው እርሱ ከጌታህ ዘንድ በእውነት የተወረደ መኾኑን ያውቃሉ፡፡ ከተጠራጣሪዎቹም አትኹን፡፡”
በፍርዱ ተጋሪ አለው፡- 33፡36 “አላህና መልክተኛውም ነገርን በፈረዱ ጊዜ፣ ለም እመናንና ለምእምናት ከነገራቸው ለነርሱ ምርጫ ሊኖራቸው አይገባም! የአላህና የመልክተኛውንም ትእዛዝ የጣሰ ሰው ግልጥ የሆነን መሳሳትን በእርግጥ ተሳሳተ።”
በመጀመርያዎቹ ጥቅሶች ውስጥ እንደተመለከተው አላህ በዳኝነቱና በፍርዱ ፍፁም ተጋሪ የሌለው ብቸኛ ዳኛና ፈራጅ ነው፡፡ በሌላኛው ጥቅስ መሠረት ግን አላህ ዳኝነቱንና ፍርዱን ከሙሐመድ ጋር ተጋርቷል፡፡ ከዚህም አልፎ ሙሐመድ እርሱን መታዘዝ ማለት አላህን መታዘዝ መሆኑን በመናገር የአላህን ቦታ ወስዷል፡-
“መልክተኛውን የሚታዘዝ ሰው በእርግጥ አላህን ታዘዘ፤ ከትዕዛዝም የሸሸ ሰው፣ (አያሳስብህ) በነሱ ላይ ጠባቂ አድርገን አልላክንህምና።” (ሱራ 4፡80)
በዚህ ጥቅስ መሠረት ሙሐመድን መታዘዝ አላህን ከመታዘዝ ጋር አንድ መሆኑ ተነግሮናል፡፡ በሌላ ቦታ ደግሞ ቁርኣን ለሙሐመድ ቃል ኪዳን መግባትን ለአላህ ቃልኪዳን ከመግባት ጋር እኩል አድርጎታል፡-
“እነዚያ ቃል ኪዳን የሚጋቡህ ቃል ኪዳን የሚጋቡት አላህን ብቻ ነው። የአላህ እጅ (ኅይሉ) ከእጆቻቸው በላይ ነው፤ ያፈረሰም ሰው የሚያፈርሰው በነፍሱ ላይ ብቻ ነው፤ በርሱ ላይ አላህን ቃል ኪዳን የተጋባባትን የሞላም ሰው ታላቅ ምንዳን በእርግጥ ይሰጠዋል።” (ሱራ 48፡10)
ከዚህ ጥቅስ በላይ የሚገኘው ጥቅስ ደግሞ ሙሐመድና አላህ አምልኮና ውዳሴን እንደሚጋሩ ይናገራል፡-
“በአላህ ልታምኑ በመልክተኛውም (ልታምኑ) ልትረዱትም ልታከብሩትም (አላህን)በጧትና ከቀትር በኋላ ልታወሱትም (ላክነው)።” (ሱራ 48፡9)
በዚህ ጥቅስ ውስጥ በቅንፍ (አላህን) ብለው የጨመሩት ተርጓሚዎች እንጂ የአረብኛው ኦርጅናል ንባብ እንደርሱ አይልም፡፡ በዚህ ቦታ የተጠቀሱት የአምልኮ ተግባራት በሙሉ ለሙሐመድ የተነገሩ ናቸው፡፡ አረብኛው በቀጥታ ሲተረጎም እንዲህ ይላል፡-
“በአላህ ልታምኑ በመልክተኛውም ልታምኑ፤ ልትረዱትም ልታከብሩትም በጧትና ከቀትር በኋላ ልታወሱትም።”
የተለያዩ የእንግሊዘኛ ተርጓሚዎች እንዲህ አስቀምጠውታል፡-
Pickthall: That ye (mankind) may believe in Allah and His messenger, and may honour Him, and may revere Him, and may glorify Him at early dawn and at the close of day.
Yusuf Ali: In order that ye (O men) may believe in Allah and His Messenger, that ye may assist and honour Him, and celebrate His praise morning and evening.
Shakir: That you may believe in Allah and His Messenger and may aid him and revere him; and (that) you may declare His glory, morning and evening.
Arberry: that you may believe in God and His Messenger and succour Him, and reverence Him, and that you may give Him glory at the dawn and in the evening.
በዚህ ጥቅስ ውስጥ ሙስሊሞች እንዲረዱት፣ እንዲያከብሩትና በጧትና በቀትር እንዲያወሱት (በአረብኛ “ቱሰቢሁሁ” ወይንም እንዲያወድሱት) የተነገረው ሙሐመድ እራሱ መሆኑን ከሰዋሰዋዊ አወቃቀሩ መረዳት ይቻላል፡፡ ሙስሊም ሊቃውንት ገሚሶቹ “መርዳትና ማክበር” የተነገረው ለሙሐመድ ሲሆን “ውዳሴው” ግን ለአላህ የተነገረ ነው ይላሉ፡፡ ገሚሶቹ ደግሞ ሁሉም የተነገረው ለሙሐመድ ነው ይላሉ፡፡ በዚህ ላይ ታዋቂው የሱፊ ሊቅ ዶ/ር ጂብሪል ፉአድ ሐዳድ የሰጡትን ሐተታ እዚህ ድረገፅ ላይ ይመልከቱ፡- http://www.masud.co.uk/ISLAM/misc/best.htm ስለዚህ ሙሐመድ በሥልጣን ራሱን ከአላህ ጋር አስተካክሏል፡፡
- ዒሳ ሞቷል ወይንስ አልሞተም?
አልሞተም፡- 4:157 “እኛ የአላህን መልክተኛ የመሬምን ልጅ አልመሲሕ ዒሳን ገደልን በማለታቸው (ረገምናቸው)፤ አልገደሉትም፤ አልሰቀሉትምም ግን ለነሱ (የተገደለው ሰው በዒሳ) ተመሰለ እነዚያም በርሱ ነገር የተለያዩት፣ ከርሱ (መገደል) በመጠራጠር ውስጥ ናቸው፤ ጥርጣሬን ከመከተል በስተቀር በርሱ ነገር ምንም ዕውቀት የላቸውም፤ በእርግጥም አልገደሉትም።”
ብዙ ሙስሊሞች ከዚህ ጥቅስ በመነሳት ዒሳ ሳይሞት ወደ ሰማይ አርጓል ይላሉ፡፡ ይህ ጥቅስ የሚያስከትላቸውን ብዙ ችግሮች ለማየት እዚህ ጋ ጠቅ ያድርጉ፡፡
ሞቷል፡- 3:144 “ሙሐመድም ከበፊቱ መልክተኞች በእርግጥ ያለፉ የሆነ መልክተኛ እንጅ ሌላ አይደለም፤ ታድያ ቢሞት፥ ወይም ቢገደል ወደኋላችሁ ትገለበጣላችሁን? ወደኋላዉ የሚገለበጥም ሰዉ አላህን ምንም አይጐዳም። አላህም አመስጋኞቹን በእርግጥ ይመነዳል።”
የተለያዩ የእንግሊዘኛ ትርጉሞች ይህንን ጥቅስ እንዲህ አስቀምጠዋል፡-
Shakir፡ And Muhammad is no more than an apostle; the apostles have already passed away before him; if then he dies or is killed will you turn back upon your heels?
Sher Ali፡ And Muhammad is but a messenger. Verily all Messengers have passed away before him. If then he dies or is slain, will you turn back on your heels?
Irving፡ Muhammad is only a messenger, Messengers have passed away before him. If he should die or be killed, will you (all) revert to your old ways?
በዚህ ጥቅስ መሠረት ከሙሐመድ በፊት የነበሩት መልእክተኞች በሙሉ ሞተዋል፤ ስለዚህ ዒሳም ሞቷል ማለት ነው፡፡ የሙሐመድ እጣ ፈንታ ከእነርሱ የተለየ እንዳልሆነ የተነገረው በዚያ ምክንያት ነው፡፡ የጥቅሱ ነጥብ ሁሉም ስለሞቱ እርሱም መሞቱ አይቀርም የሚል ነው፡፡ ቀደም ሲል በተጠቀሰው ጥቅስ መሠረት ግን ዒሳ እንዳልሞተ በመግለፅ ከዚህኛው ጥቅስ ጋር የሚጠረስ መልእክት ያስተላልፋል፡፡ ግጭቱ ግልፅ ነው፡፡
- ዒሳ በገሃነም ይቃጠላል ወይስ አይቃጠልም?
አይቃጠልም፡- 4፡158 “…ይልቁኑስ፣ አላህ ወደርሱ አነሳው፤ አላህም አሸናፊ ጥበበኛ ነው።”
3:45 “መላእክት ያሉትን (አስታዉስ) ፡- መርየም ሆይ አላህ ከርሱ በሆነዉ ቃል፣ ስሙ አልመሲሕ ዒሳ የመርየም ልጅ፣ በዚህ ዓለምና በመጨረሻዉም ዓለም የተከበረ፣ ከባለማሎችም በሆነ (ልጅ) ያበስረሻል፡፡”
ከላይ በተጠቀሱት ጥቅሶች መሠረት ዒሳ እውነተኛ የአላህ መልእክተኛ ነው፤ ወደ ሰማይ ተወስዶ በአላህ ዘንድ ይገኛል፤ ስለዚህ በገሃነም አይቃጠልም፡፡
ይቃጠላል፡- 21:98 “እናንተ፣ ከአላህ ሌላ የምትግገዟቸውም (ጣዖታት) የገሃነም ማገዶዎች ናችሁ፤ እናንተ ለርሷ ወራጆች ናችሁ።”
Indeed, you [disbelievers] and what you worship other than Allah are the firewood of Hell. You will be coming to [enter] it.
በዚህ ጥቅስ መሠረት ደግሞ ሰዎች ከአላህ ሌላ የሚያመልኳቸው አማልክት ከአምላኪዎቻቸው ጋር በገሃነም ይቃጠላሉ፡፡ በዚህ ጥቅስ ውስጥ በቅንፍ (ጣዖታት) የሚለው በተርጓሚዎቹ የተጨመረ ሲሆን ዒሳ በዚህ ውስጥ የመካተቱን ጥያቄ ለማስወገድ ሲሉ ያደረጉት ነው፡፡ በአረብኛው ቁርኣን ውስጥ ግን አይገኝም፡፡ በአረብኛው ቁርኣን ሰዎች የሚያመልኳቸው ማናቸውም ነገሮች ከነአምላኪዎቻቸው ወደ ገሃነም እንደሚጣሉ ነው የተነገረው፡፡
በሌላ ቦታ ላይ ቁርኣን ክርስቲያኖች ዒሳን እንደሚያመልኩት ይናገራል፡-
5:72 “እነዚያ አላህ እርሱ የመርየም ልጅ አልመሲሕ ነው ያሉ በእርግጥ ካዱ፤ አልመሲሕም አለ፦ የእስራኤል ልጆች ሆይ! ጌታዬንና ጌታችሁን አላህን ተገዙ፤ እነሆ! በአላህ የሚያጋራ ሰው አላህ በርሱ ላይ ገነትን በእርግጥ እርም አደረገ፤ መኖሪያውም እሳት ናት፤ ለበዳዮችም ምንም ረዳቶች የሏቸውም።”
ሰዎች የሚያምልኳቸው ነገሮች ከአምላኪዎቻቸው ጋር በገሃነም የሚቃጠሉ ከሆነ፤ ከእነዚህ ተመላኪዎች መካከል አንዱ ዒሳ ከሆነ፤ ዒሳም በገሃነም ሊቃጠል ነው፡፡ ይህ ደግሞ ዒሳ በአላህ ዘንድ የተመረጠ ነቢይ መሆኑን ከሚናገረው የቁርኣን አንቀጽ ጋር ይጋጫል፡፡
- ቁርኣን የማን ቃል ነው?
የአላህ ቃል፡- 17፡106 “ቁርኣንንም በሰዎች ላይ በዝግታ ላይ ኾነህ ታነበው ዘንድ ከፋፈልነው፡፡ ቀስ በቀስ ማውረድንም አወረድነው፡፡”
የክቡር መልእክተኛ ቃል፡- 81፡19-21 “እርሱ (ቁርኣን) የክቡር መልክተኛ ቃል ነው፡፡ የኀይል ባለቤት በዙፋኑ ባለቤት ዘንድ ባለሟል የሆነ፤ በዚያ ስፍራ ት እዛዙ ተሰሚ ታማኝ የሆነ (መልክተኛ ቃል) ነው።”
የቁርኣን ምንጭ አላህ ከሆነ “የመልእክተኛ ቃል” ስለምን ተባለ? ምንጩ አላህ ከሆነ የመልእክተኛ ቃል እንዴት ሊባል ይችላል?
- ያለ ወሲባዊ ግንኙነት ልጅ መውለድ ይቻላል ወይስ አይቻልም?
ይቻላል፡- 19፡19-21 “እኔ ንጹሕን ልጅ ለአንቺ ልሰጥሽ፣ የጌታሽ መልክተኛ ነኝ አላት። (በጋብቻ) ሰዉ ያልነካኝ ኾኜ፣ አመንዝራም ሳልኾን ለኔ እንዴት ልጅ ይኖረኛል! አለች። አላት (ነገሩ) እንደዚህሽ ነው ፤ ጌታሽ ፦ እርሱ በእኔ ላይ ገር ነው፤ ለሰዎችም ታምር፣ ከኛም ችሮታ ልናደርገው (ይህንን ሠራን) የተፈረደም ነገር ነዉ አለ፤ (ነፋባትም)።”
አይቻልም፡- 6:101 “(እርሱ) ሰማያትንና ምድርን ያለ ብጤ ፈጣሪ ነው፡፡ ለእርሱ ሚስት የሌለችው ሲኾን እንዴት ለእርሱ ልጅ ይኖረዋል? ነገርንም ሁሉ ፈጠረ፡፡ እርሱም ነገሩን ሁሉ ዐዋቂ ነው፡፡”
ማርያም ወንድ ሳታውቅ ልጅ መውለድ የቻለች ቢሆንም በዚያ ሁኔታ ልጅ እንዲኖራት ማድረግ የቻለው አላህ ግን ያለ ሚስት ልጅ ሊኖረው እንደማይችል ተነግሮናል፡፡ በእርግጥ የቁርኣን ጸሐፊ ይህንን ያለው ክርስትና ስለ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅነት የሚያስተምረውን ትምሕርት ሰዋዊ በሆነ የተዋልዶ መንገድ በመረዳቱ ነው፡፡ ራሱ የፈጠረውን ስሁት መረዳት ለማስተባበል ጥረት ሲያደርግ ሳለ ግን ከሌላ የቁርኣን ክፍል ጋር የሚጋጭ ሐሳብ መፍጠሩንና የአላህን ሁሉን ቻይነት ውድቅ ማድረጉን አላስተዋለም፡፡
44. የመጀመርያው ሙስሊም ማነው?
ቁርኣን ለዚህ ጥያቄ የሰጣቸው ምላሾች እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ ናቸው፡፡ ሙሐመድ የመጀመርያው ሙስሊም እንደሆነ ይናገራል (39፡12፣ 6፡163፣ 6፡14)፣ ነገር ግን አብረሃምና ኢስማኤል (2፡128፣ 3፡36)፣ የፈርዖን ድግምተኞች (7፡126) እንዲሁም ሐዋርያት (5፡111) ሙስሊሞች ነበሩ ይላል፡፡ በተጨማሪም እስልምና የነቢያት ሁሉ ሃይማኖት መሆኑን ይናገራል፡፡
አንዳንድ ሙስሊሞች ይህንን ግጭት “ሲያስታርቁ” ሙሐመድ በወቅቱ ከነበሩት ሕዝቦች አንፃር የመጀመርያው ሙስሊም ነበር ይላሉ፡፡
በሙሐመድ ዘመን አላህን ሲያመልኩ የነበሩ የአብረሃምን መንገድ የተከተሉ “ሐኒፎች” እንደነበሩ በእስላማዊ ምንጮች ውስጥ ከመጠቀሱ አንጻር ይህ መልስ የሚያስኬድ አይደለም፡፡ እነዚህ “የአብረሃም እምነት ተከታዮች” ዋረቃ ኢብን ናውፋል፣ ኡቤይዱላህ ኢብን ጃሽ፣ ኡሥማን ኢብን አል-ሑዋሪሥ እና ዘይድ ኢብን ዐምር መሆናቸውን ኢብን ኢስሐቅ ዘግቧል፡፡ እነዚህ ሰዎች የአብረሃምን ሃይማኖት በማወቅ ከሙሐመድ የቀደሙ በእርሱ ዘመን የነበሩ ሰዎች ናቸው፡፡ በቁርኣን ውስጥ አብረሃም ራሱ ሐኒፋ መሆኑ ተነግሯል፡-
“ኢብራሂም ይሁዳዊም ክርስቲያንም አልነበረም፡፡ ግን ወደ ቀጥተኛው ሃይማኖት የተዘነበለ [በአረብኛ ሐኒፈን] ሙስሊም ነበረ፡፡ ከአጋሪዎችም አልነበረም፡፡” (3፡67)
“«እኔ ጌታዬ ወደ ቀጥተኛው መንገድ ትክክለኛን ሃይማኖት ወደ እውነት አዘንባይ ሲኾን [በአረብኛ ሐኒፈን] የአብርሃምን መንገድ መራኝ፡፡ እርሱም ከአጋሪዎቹ አልነበረም» በል፡፡” (6፡161)
እስልምና የሰው ልጆች የተፈጥሮ ሃይማኖት መሆኑን ይናገራል (ሱራ 30፡30፣ 2፡138)፡፡ ስለዚህ ሙስሊሞች ማንኛውም ህፃን ሲወለድ ሙስሊም ሆኖ እንሚወለድና ኋላ ላይ ራሱን ሲያውቅ በወላጆቹ ምክንያት የተፈጥሮ ሃይማኖቱን እንደሚለቅ ይናገራሉ፡፡ ስለዚህ በሙሐመድ ዘመን የነበሩት ህፃናት ቢያንስ ለተወሰነ ጊዜ ከእርሱ ቀድመው ሙስሊሞች ሆነው ነበር ማለት ነው፡፡
ሙሴ በዘመኑ የምእመናን መጀመርያ መሆኑን የሚገልፀውን ተከታዩን ጥቅስ በመጥቀስ እርሱም በወቅቱ የሙስሊሞች መጀመርያ መሆኑን ለማስረዳት የሚሞክሩ ሙስሊሞች አሉ፡-
“…ሙሳም ጮሆ ወደቀ፡፡ በአንሰራራም ጊዜ «ጥራት ይገባህ፡፡ ወዳንተ ተመለስኩ፡፡ እኔም (በወቅቱ) የምእምናን መጀመሪያ ነኝ» አለ፡፡” (ሱራ 7፡143)
(በወቅቱ) የሚለው በተርጓሚዎች የተጨመረ እንጂ በአረብኛው ውስጥ አይገኝም፡፡ ይህንን ማብራርያ በመጨመር ጥቅሱ የሚፈጥረውን ችግር ለማስወገድ ሞክረዋል፡፡ ነገር ግን ይህ ማብራርያ የሙሴ እናትና ሌሎች አማኞች በዘመኑ እንደነበሩ ከሚገልፁት የቁርኣን ጥቅሶች ጋር ይጋጫል፡-
“ወደ ሙሳም እናት «አጥቢው፣ በርሱም ላይ በፈራሽ ጊዜ በባሕሩ ውስጥ ጣይው አትፈሪም፣ አትዘኝም፣ እኛ ወዳንቺ መላሾቹና ከመልክተኞቹም አድራጊዎቹ ነንና» ማለትን አመለከትን፡፡” (ሱራ 28፡7)
በቁርኣን መሠረት የሙሴ እናት የአላህን መልእክት መስማት የቻለች አማኝ ሴት ነበረች፡፡ በተጨማሪም በሙሴ ዘመን ከፈርዖን ባለሟሎች መካከል አማኝ የነበረ ሰው መኖሩን ቁርኣን ይናገራል (ሱራ 40፡28-46)፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ለሙሴ በተገለጠለት በዚያው ጊዜ ወንድሙ አሮን የእግዚአብሔርን ድምፅ በመስማት ሊቀበለው ወደ መንገድ እንደወጣ ይናገራል (ዘጸአት 4፡14-28)፡፡ እነዚህ ማስረጃዎች ሙሴ በወቅቱ የመጀመርያው አማኝ እንዳልሆነ ያረጋግጡልናል፡፡ በሙሴ ዘመን የነበሩት የግብፅ አስማተኞች “የመጀመርያዎቹ ሙስሊሞች” መሆናቸውን የሚገልፀው የቁርኣን ጥቅስ ደግሞ ከላይ ያሉትን በሙሉ ያፈርሳል(ሱራ 7፡126)፡፡ ስለዚህ ጉዳዩ አንዳንድ ሙስሊሞች አቅልለው ለማሳየት የሞከሩትን ያህል ቀላል አይደለም፡፡
- ፍጥረት በስድስት ወይንስ በስምንት ቀናት ተፈጠረ?
በስድስት ቀን፡- 7:54 “ጌታችሁ ያ ሰማያትንና ምድርን በስድስት ቀኖች ውስጥ የፈጠረ አላህ ነው…”
በስምንት ቀን፡- 41:9-12 “በላቸው፦ እናንተ በዚያ ምድርን በሁለት ቀኖች ውስጥ በፈጠረው አምላክ በእርግጥ ትክዳላችሁን? ለርሱም ባላንጣዎችን ታደርጋላችሁን? ያ (ይህንን የሠራው) የዓለማት ጌታ ነው። በርሷም ከበላይዋ የረጉ ጋራዎችን አደረገ፤ በርሷም በረከትን አደረገ፤ በውስጧም ምግቦችዋን (ካለፉት ሁለት ቀኖች ጋር) በአራት ቀናት ውስጥ፣ ለጠያቂዎች ትክክል ሲሆኑ ወሰነ። ከዚያም ወደ ሰማይ እርሷ ጭስ ሆና ሳለች አሰበ፤ ለርሷም ለምድርም ወዳችሁም ሆነ ወይም ጠልታችሁ፣ ኑ፤ አላቸው። ታዛዦች ሆነን መጣን አሉ። በሁለት ቀኖችም ውስጥ ሰባት ሰማያት አደርጋቸው፤ በሰማያቱም ሁሉ ነገሯን አዘጋጀ፤ ቅርቢቱንም ሰማይ በመብራቶች አጌጥን፤ (ከሰይጣናት) መጠበቅንም ጠበቅናት፤ ይህ የአሸናፊው፣ የዐዋቂው (ጌታ) ውሳኔ ነው።”
በዚህ ጥቅስ መሠረት ምድር በሁለት ቀናት ተፈጠረች፣ በላዩዋ ላይ የሚገኙት በአራት ቀናት ውስጥ ተፈጠሩ፣ ሰማይ ደግሞ ሰባት ሰማያት ሆነው ተፈጠሩ፡፡ ስለዚህ 2+4+2=8 ይሆናል፡፡ የአማርኛ ቁርኣን ተርጓሚዎች አራቱን ቀን ሁለት ለማድረግና አጠቃላይ ቁጥሩን ስድስት አድርጎ ከሌሎች የቁርኣን ክፍሎች ጋር ለማስማማት በቅንፍ (ካለፉት ሁለት ቀኖች ጋር) የሚል አክለዋል፡፡ ነገር ግን ይህ ጭማሬ በአረብኛው ቁርኣን ውስጥ የለም፡፡ ከሙሐመድ የተላለፈ ሐዲስ ፍጥረት የተፈጠረባቸውን ሰባት ቀናት በመዘርዘር ይህንን ማብራርያ ውድቅ ያደርጋል፡-
አሁ ሁረይራ እንደዘገበው የአላህ መልእክተኛ (ሰላም በሳቸው ላይ ይሁንና) እጄን ይዘውኝ እንዲህ አሉኝ፡- ከፍ ያለውና የተከበረው አላህ ቅዳሜ ሸክላን ፈጠረ፣ እሑድ ተራሮችን ፈጠረ፣ ዛፎችን ሰኞ ፈጠረ፣ የጉልበት ሥራ የሚፈልጉ ነገሮችን ማክሰኞ ፈጠረ፣ ብርሃንን ረቡዕ ፈጠረ፣ እንስሳትን ሐሙስ ፈጠረ፣ አዳምን አርብ ከአስር በኋላ ፈጠረ፤ እርሱም በመጨረሻው ቀን በመጨረሻው ሰዓት የተፈጠረ ፍጥረት ነው፡፡ (ሳሂህ ሙስሊም ሐዲስ ቁጥር 6707)
በዚህ ሐዲስ ውስጥ ፍጥረት የተፈጠረባቸው ቢያንስ 7 ቀናት ተጠቅሰዋል፡፡ ይህ ሐዲስ ፍጥረት በሰባት ቀን ብቻ እንደተፈጠረ አይናገርም ነገር ግን ቢያንስ ሰባት ቀናትን ጠቅሷል፤ በዚህ ዝርዝር ውስጥ ያልተካተቱ ፍጥረታት ስላሉ ከዚያ በላይ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ይህ ደግሞ ሱራ 41፡9-12 ላይ የተጠቀሱት 8 ቀናት ስለመሆናቸው ጥሩ ማስረጃ ነው፡፡ እናም ግጭቱ ግልፅ ነው፡፡
- ፈጣን ወይንስ ዘገምተኛ የመፍጠር ሒደት?
ዘገምተኛ፡- 7፡54 “ጌታችሁ ያ ሰማያትንና ምድርን በስድስት ቀኖች ውስጥ የፈጠረ አላህ ነው፤ ከዚያም (ስልጣኑ) በዐርሹ ላይ ተደላደለ፤ (አላህ) ሌሊትን በቀን ፈጥኖ የሚፈልገው ሲሆን ይሸፍናል፤ ፀሃይንና ጨረቃንም፣ ከዋክብትንም በትእዛዙ የተገሩ ሲሆኑ (ፈጠራቸው)፤ ንቁ፤ መፍጠርና ማዘዝ የርሱ ብቻ ነው፤ የዓለማት ጌታ አላህ (ክብሩ) ላቀ።”
ሙስሊም ምሑራን (ለምሳሌ ያህል ዶ/ር ዛኪር ናይክ፣ ዶ/ር ሻቢር አሊ) ቁርኣንን ከዘመናዊ ሳይንስ ጋር ለማስማማት ካላቸው ጉጉት የተነሳ በዚህ ቦታ “ስድስት ቀኖች” የተባለው ስድስት የ24 ሰዓት ቀናት ማለት እንዳልሆነና ስድስት ረጃጅም ስፍረ ዘመናት (epochs) እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ ስለዚህ በዚህ ፍቺ መሠረት አላህ ሰማይና ምድርን ለመፍጠር በቢሊየን የሚቆጠሩ ዓመታት ፈጅቶበታል ማለት ነው፡፡
ፈጣን፡- 2፡117 “ሰማያትንና ምድርን ያለብጤ ፈጣሪ ነው፤ ነገርንም (ማስገኘት) በሻ ጊዜ ለርሱ የሚለው፡- «ኹን ነው፤» ወዲያውም ይኾናል፡፡”
በዚህ ጥቅስ መሠረት ደግሞ የሰማይና የምድር ፈጣሪ የሆነው አላህ አንድ ነገር መፍጠር ሲፈልግ “ኹን” እንደሚለውና ወዲያም እንደሚኾን ተነግሮናል፡፡ ስለዚህ ሙስሊም ምሑራን ቁርኣንን ከሳይንስ ጋር ለማስማማት ስድስቱን ቀናት (በአረብኛ “የውም”) ረጃጅም ስፍረ ዘመናት ናቸው ማለታቸው ትክክል ከሆነ አላህ መፍጠር ሲፈልግ “ኹን” በሚለው ቃል ብቻ ካለመኖር ወደ መኖር ማምጣት መቻሉን የሚናገረው የቁርኣን ጥቅስ ስህተት ሊሆን ነው፤ ስለዚህ የቱ ነው ትክክል?
- ከሰማይና ከምድር ቀድሞ የተፈጠረው የቱ ነው?
ምድር፡- 2:29 “እርሱ ያ በምድር ያለውን ሁሉ ለእናንተ የፈጠረ ነው፡፡ ከዚያም ወደ ሰማይ አሰበ፤ ሰባት ሰማያትም አደረጋቸው፡፡ እርሱም በነገሩ ሁሉ ዐዋቂ ነው፡፡”
ሰማይ፡- 79፡27-30
- አላህ መላእክትን የሚያወርደው በቅጣት ብቻ ወይስ በራዕይ?
በቅጣት እንጂ በሌላ አያወርድም፡- ሱራ 15:7-8 “«ከእውነተኞቹ እንደ ኾንክ በመላእክት (መስካሪ) ለምን አትመጣንም» (አሉ)፡፡መላእክትን በእውነት (በቅጣት) እንጂ አናወርድም፡፡ ያን ጊዜም የሚቆዩ አይደሉም፡፡”
በራዕይ ያወርዳቸዋል፡- ሱራ 6:2
- አላህ ሰማይና ምድርን ወደ አንድ ጠራቸው ወይስ ለያያቸው?
ወደ አንድ ጠራቸው፡- 41:11 “ከዚያም ወደ ሰማይ እርሷ ጭስ ሆና ሳለች አሰበ፤ ለርሷም ለምድርም ወዳችሁም ሆነ ወይም ጠልታችሁ፣ ኑ፤ አላቸው። ታዛዦች ሆነን መጣን አሉ።”
ለያያቸው፡- 21:30 “እነዚያም የካዱት ሰማያትና ምድር የተጣበቁ የነበሩና የለያየናቸው መሆናችንን አያውቁምን? ሕያው የኾነንም ነገር ሁሉ ከውሃ ፈጠርን አያምኑምን?”
- ጂኒዎች ከምንድነው የተፈጠሩት?
ከእሳት፡- 15:27 “ጃንንም (ከሰው) በፊት ከእሳት ነበልባል ፈጠርነው፡፡” (በተጨማሪም 55:15፣ 7:12፣ 38:76)
ከውኀ፡- 21፡30 “…ሕያው የኾነንም ነገር ሁሉ ከውሃ ፈጠርን አያምኑምን?”
የመጀመርያው ጥቅስ ጂኒዎች ከእሳት እንደተፈጠሩ የሚናገር ሲሆን ሁለተኛው ጥቅስ ደግሞ ሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ ከውኀ እንደተፈጠሩ ይናገራል፡፡ በእስልምና መሠረት ጂኒዎች የሚንቀሳቀሱ፣ የሚመገቡና የሚያስቡ ሕያዋን ፍጥረታት እንጂ እንደ ድንጋይ ግዑዛን አይደሉም፡፡ “ሁሉ” የሚል ከሆነ ደግሞ ጂኒዎችን ስለሚያጠቃልል ግጭቱ ግልፅ ነው፡፡
- በፍርድ ቀን ከሃዲያን ከአላህ የሚደብቁት ነገር አለ ወይስ የለም?
አለ፡- 6:22-23 “ሁላቸውንም የምንሰበስብበትንና ከዚያም ለእነዚያ (ጣዖታትን) ለአጋሩት እነዚያ (ለአላህ) ተጋሪዎች ናቸው ብላችሁ ታስቧቸው የነበራችሁት ተጋሪዎቻችሁ የት ናቸው የምንልበትን ቀን (አስታውስ)፡፡ከዚያም መልሳቸው «በጌታችን በአላህ ይኹንብን አጋሪዎች አልነበርንም» ማለት እንጅ ሌላ አትኾንም፡፡”
የለም፡- 4:42 “በዚያ ቀን እነዚያ የካዱትና መልዕክተኛውን ያልታዘዙት በነሱ ምድር ብትደፋባቸው ይመኛሉ፤ ከአላህም ወሬን አይደብቁም።”
መጀመርያ በተጠቀሰው ጥቅስ ውስጥ ከሃዲያን በምድር በነበሩ ጊዜ ከአላህ ጋር ሌሎች ነገሮችን ሲያጋሩ የነበሩ ቢሆንም በፍርድ ቀን አላህ ሲጠይቃቸው አጋሪ መሆናቸውን ለማስተባበል ይሞክራሉ፡፡ ነገር ግን በሁለተኛው ጥቅስ ላይ ከሃዲያን ከአላህ የሚደብቁት ምንም ነገር እንደሌለ ይናገራል፡፡
- መናፍቃን ዕውሮች ናቸው ወይስ አይደሉም?
ዕውሮች ናቸው፡- 2፡17-18 (በንፍቅና) ምሳሌያቸው እንደዚያ እሳትን እንዳነደደ ሰው በዙሪያው ያለውን ሁሉ ባበራች ጊዜም አላህ ብርሃናቸውን እንደወሰደባቸው በጨለማዎችም ውስጥ የማያዩ ኾነው እንደተዋቸው (ሰዎች) ብጤ ነው፡፡ (እነሱ) ደንቆሮዎች፣ ዲዳዎች፣ ዕውሮች ናቸው፤ ስለዚህ እነርሱ አይመለሱም፡፡”
በመጠኑ ያያሉ፡- 2፡20 “ወይም (ምሳሌያቸው) ከሰማይ እንደ ወረደ ዝናም (ባለቤቶች) ነው፤ በርሱ (በደመናው) ውስጥ ጨለማዎች፣ ነጎድጓድም፣ ብልጭታም ያሉበት ሲኾን ከመብረቆቹ ሞትን ለመፍራት ጣቶቻቸውን በጆሮቻቸው ውስጥ እንደሚያደርጉ ብጤ ነው፡፡ አላህም ከሓዲዎችን ከባቢ ነው፡፡ ብልጭታው ዓይኖቻቸውን ሊነጥቅ ይቀርባል፡፡ ለነርሱ ባበራላቸው ቁጥር በርሱ ውስጥ ይኼዳሉ፡፡ በነሱም ላይ ባጨለመ ጊዜ ይቆማሉ፡፡ አላህም በሻ ኖሮ መስሚያቸውንና ማያዎቻቸውን በወሰደ ነበር፤ አላህ በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነውና፡፡”
በመጀመርያው ጥቅስ ውስጥ እንደምንመለከተው መናፍቃን በፍፁም የማያዩ ዕውራን እንደሆኑ ሲሆን ምሳሌያቸውም እሳት አንድደው ነገር ግን እንዳያዩ አላህ ብርሃናቸውን ሰዎች ዓይነት ነው፡፡ ነገር ግን በሁለተኛው ጥቅስ ውስጥ መናፍቃን መናፍቃን እውር እናዳልሆኑና ምሳሌያቸውም ዝናብ በዘነበ ጊዜ የመብረቅ ብልጭታ ሲታይ እንደሚጓዙ ሲጨልም ደግሞ እንደሚቆሙ ዓይነት ሰዎች እንደሆኑ ተነግሮናል፡፡ “…አላህም በሻ ኖሮ መስሚያቸውንና ማያዎቻቸውን በወሰደ ነበር” የሚለው ዓረፍተ ነገር እነዚህ ሰዎች ዕውራን እንዳልሆኑና እንደሚያዩ ያረጋግጥልናል፡፡ ስለዚህ መናፍቃን ዕውራን ናቸው የሚያዩ?
እነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ሌላ ግጭትም እናስተውላለን፡፡ ይኸውም የመጀመርያው ጥቅስ መናፍቃን ደንቆሮዎችና ዕውሮች እንደሆኑ ስለዚህም እንደማይመለሱ በአፅንዖት ሲገልፅ ሁለተኛው ጥቅስ ደግሞ “አላህም በሻ ኖሮ መስሚያቸውንና ማያዎቻቸውን በወሰደ ነበር” በማለት እነዚህ ሰዎች እንደሚሰሙና እንደሚያዩ በተዘዋዋሪ በመግለፅ የመጀመርያ ሐሳቡን ያፈርሳል፡፡ ታድያ የቱ ነው ትክክል?
- ከሚከተሉት ውስጥ ሙሐመድ የትኛውን ነው?
አስፈራሪ ብቻ፡- 11፡12 “አንተ አስፈራሪ ብቻ ነህ” (እንዲሁም 38፡65)
አብሳሪና አስፈራሪ ብቻ፡- 34፡28 “አንተንም ለሰዎች ሁሉ በመላ፣ አብሳሪና አስፈራሪ አድርገን ቢሆን እንጂ አልላክንህም፤ ግን አብዛኞቹ ሰዎች አያውቁም።” (እንዲሁም 11፡2፣ 35፡24)
መስካሪ አብሳሪና አስፈራሪ፡- 33፡45 “አንተ ነቢዩ ሆይ! እኛ መስካሪ አብሳሪና አስፈራሪም አድርገን ላክንህ።” (እንዲሁም 48፡8፣ 6፡48)
ግልፅ አስጠንቃቂ ብቻ፡- 22፡49 “እላንተ ስዎች ሆይ እኔ ለናንተ ግልጽ አስጠንቃቂ ብቻ ነኝ፣ በላቸው።”
27፡92 “…የተሳሳተም ሰው እኔ አስጠንቃቂዎች ነኝ እንጂ ሌላ አይደለሁም በለው።”
34፡46 “…እርሱ ለናንተ ከብርቱ ቅጣት በስተፊት አስጠንቃቂ ነው እንጂ ሌላ አይደለም፣ በላቸው።”
ከአላህ ጋር በሽርክና የሚፈርድ ፈራጅ፡- 33፡36 “አላህና መልክተኛውም ነገርን በፈረዱ ጊዜ…”
ነቢይ፡- 3፡50 “አንተ ነቢዩ ሆይ…” (እንዲሁም 33፡50፣ 33፡38)
ከላይ የተጠቀሱት ጥቅሶች ሙሐመድ በምን ዓይነት ሁኔታ እንደተላከ የሚገልፁ ሲሆኑ እርስ በርሳቸው የማይጣጣሙ ናቸው፡፡ የመጀመርጠያው ጥቅስ አስፈራሪ ብቻ እንደሆነ ይነግረናል፡፡ “ብቻ” የምትል ልዩ መሆንን አመልካች ቃል ስላለች ከተባለው ነገር ውጪ ሌላ ሊሆን አይችልም ማለት ነው፡፡ ከዚያ በማስከተል ግን አንድ ተግባር በማከል “አብሳሪና አስፈራሪ ብቻ ነው” ይለናል፡፡ ስለዚህ ከላይ “አስፈራሪ ብቻ” ያለውን አፍርሶታል ማለት ነው፡፡ ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ ሌላ አንድ ተግባር በማከል “መስካሪ፣ አብሳሪና አስፈራሪ” እንደሆነ ይነግረናል፡፡ ይህንን ሁሉ በማፍረስ ደግሞ “ግልፅ አስጠንቃቂ ብቻ ነው” ይለናል፡፡ በማስከተል ደግሞ ከአላህ ጋር በሽርክና የሚፈርድ ፈራጅና ነቢይ እንደሆነ ይነግረናል፡፡ አስፈራሪ ብቻ ከሆነ መስካሪ፣ አብሳሪ፣ አስጠንቃቂ፣ ፈራጅና ነቢይ አይደለም ማለት ነው? አብሳሪና አስፈራሪ ብቻ ከሆነ መስካሪ፣ አስጠንቃቂ፣ ፈራጅና ነቢይ አይለም ማለት ነው? ግልፅ አስጠንቃቂ ብቻ ከሆነ የተቀሩትን ሁሉ አይደለም ማለት ነው? የግጭት ትርምሱ ግልፅ ነው፡፡
- የገነት ስፋት ምን ያህል ነው?
የምድርና ከአንድ በላይ ሰማያት ያህል፡- 3:133 “ከጌታችሁ ወደ ኾነችም ምሕረትና ስፋትዋ (عَرضُهَا) እንደ ሰማያትና ምድር ወደ ሆነች ገነት፥ አላህን ለሚፈሩ የተዘጋጀች ስትሆን ተቻኮሉ።”
የምድርና የአንድ ሰማይ ያህል፡- 57:21 “ከጌታችሁ ወደ ሆነች ምሕረት ወርዷ (عَرضُهَا) እንደሰማይና ምድር ወርድ ወደ ሆነችም ገነት ተሽቀዳደሙ…”
የአማርኛ ተርጓሚዎች ግጭቱን ለማስወገድ አንዱ ቦታ ላይ “ስፋትዋ” ሌላ ቦታ ላይ ደግሞ “ወርዷ” በማለት ቢተረጉሙም አረብኛው ግን عَرضُهَا “ዐርዱሐ” የሚል አንድ ዓይነት ቃል ተጠቅሟል፤ ስለዚህ ሁለቱም ጥቅሶች ስለ ገነት ስፋት የሚናገሩ ናቸው፡፡ ታድያ የገነት ስፋት የምድርና የብዙ ሰማያት ወይንስ የምድርና የአንድ ሰማይ ያህል? የቱ ነው ትክክል?
- መላእክት በአላህ ትዕዛዝ ላይ ያምፃሉ ወይንስ አያምፁም??
አያምፁም፡- 16፡49-50 “ለአላህም በሰማያት ያለው ከተንቀሳቃሻም በምድር ያለው ሁሉ መላክትም ይሰግዳሉ፤ እነርሱም አይኮሩም። ጌታቸውን ከበላያቸው ሲሆን ይፈሩታል፤ የታዘዙትንም ሁሉ ይሠራሉ።”
ያምፃሉ፡- 2፡102 “ሰይጣናትም በሱለይማን (ሰሎሞን) ዘመነ መንግስት የሚያነቡትን (ድግምት) ተከተሉ፡፡ ሱለይማንም አልካደም፤ (ድግምተኛ አልነበረም)፤ ግን ሰይጣናት ሰዎችን ድግምትን የሚያስተምሩ ሲኾኑ ካዱ፡፡ ያንንም በባቢል በሁለቱ መላእክት በሃሩትና ማሩት ላይ የተወረደውን ነገር (ያስተምሩዋቸዋል)፡፡ «እኛ መፈተኛ ነንና አትካድ» እስከሚሉም ድረስ አንድንም አያስተምሩም፡፡ ከእነሱም በሰውየውና በሚስቱ መካከል በርሱ የሚለዩበትን ነገር ይማራሉ፡፡ እነርሱም በአላህ ፈቃድ ካልኾነ በርሱ አንድንም ጎጂዎች አይደሉም፡፡ የሚጎዳቸውንና የማይጠቅማቸውንም ይማራሉ፡፡ የገዛውም ሰው ለርሱ በመጨረሻይቱ አገር ምንም እድል የሌለው መኾኑን በእርግጥ ዐወቁ፡፡ ነፍሶቻቸውንም በርሱ የሸጡበት ዋጋ ከፋ! የሚያውቁ በኾኑ ኖሮ (ባልሠሩት ነበር)፡፡”
በመጀመርያው ጥቅስ ውስጥ መላእክት ለአላህ ፍፁም ታዛዦች እንደሆኑ የተነገረ ሲሆን በሙስሊሞች እምነት መሠረት ኃጢአትን የሚሠሩበት ነፃ ፈቃድ የላቸውም፡፡ በሁለተኛው ጥቅስ ውስጥ ግን ሰዎችን ድግምትንና አመፅን ያስተማሩ ሁለት መላእክት እንደነበሩ ተነግሮናል፡፡ በእስላማዊ ምንጮች መሠረት ሃሩትና ማሩት ወደ ምድር በመምጣት በኃጢአት የወደቁ ሁለት መላእክት ናቸው፡፡ (Mahmoud M. Ayoub, The Qur’an and its Interpreters, pp. 130-131)
በሌላ ነጥብ ደግሞ ቀደም ሲል እንዳየነው ዲያብሎስ መልአክ የነበረ ሲሆን ለአላህ እንዳልታዘዘ ቁርኣን ይነግረናል፡፡ በሌላ ቦታ ላይ ጂን እንደሆነ በመናገሩ ሌላ ግጭት እንጂ መልአክ መሆኑ አለመነገሩን አያረጋግጥም፡፡
- የዘካርያስና የመልአኩ ንግግር – ሁለት ዘገባዎች፣ ብዙ ግጭቶች
መልአክ ወደ ዘካርያስ በመምጣት ስለ ያሕያ (ዮሐንስ) ልደት እንዳበሰረ በተነገረባቸው ሁለት የቁርኣን ዘገባዎች መካከል ብዙ ግጭቶች ይገኛሉ፡፡ ካነበብናቸው በኋላ ግጭቶቹን እንዘረዝራለን፡-
ዘገባ አንድ፡- 3፡38-41 “እዚያ ዘንድ ዘከርያ ጌታዉን ለመነ- ጌታዬ ሆይ ከአንተ ዘንድ መልካም ዘርን ለኔ ስጠኝ፤ አንተ ጸሎትን ሰሚ ነህና አለ። እርሱም በጸሎት ማድረሻዉ ክፍል ቆሞ ሲጸልይ መላእክት ጠራችዉ። አላህ በየሕያ ከአላህ በሆነ ቃል የሚያረጋግጥ ጌታም ድንግልም፣ ከደጋጐቹ ነቢይም ሲሆን ያበስርሃል፤ በማለት፥ (መላእክት ጠራችዉ) – ጌታዬ ሆይ! እኔ እርጅና በእርግጥ የደረሰብኝ ስትሆን ባልተቤቴም መካን ስትሆን፥ ለኔ እንዴት ልጅ ይኖረኛል? አለ (መልአኩም) እንደዚሁ አላህ የሚሻዉን ነገር ይሠራል አለዉ፤ ፡- ጌታዬ ሆይ! ለኔ ምልክትን አድርግልኝ አለ፤ ምልክትሕ ሦስት ቀን በጥቅሻ ቢሆን እንጅ ሰዎችን አለማናገርህ ነዉ፤ ጌታህንም በብዙ አዉሳ፤ በማታና በጧትም አወድሰዉ፥ አለዉ።”
ዘገባ ሁለት፡- 19፡2-11 “(ይህ) ጌታህ ባሪያውን ዘከሪያን በችሮታዉ ያወሳበት ነው። ጌታውን የምስጢር ጥሪ በተጣራ ጊዜ (አስታውስ)፦ አለ ጌታዬ ሆይ እኔ አጥንቴ ደከመ ፤ ራሴም በሺበት ተንቀለቀለ፤ አንተንም በመለመኔ ጌታዬ ሆይ! (ምንግዜም) ዕደለ ቢስ አልኾንኩም። እኔም ከበኃላዬ ዘመዶቼን በእርግጥ ፈራሁ፤ ሚስቴም መካን ነበረች፣ ስለዚህ ከአንተ ዘንድ ለኔ ልጅን ስጠኝ፤ ሃይማኖትህን ይበድላሉ ብዬ የሚወርሰኝ ከያዕቆብ ቤተሰቦችም የሚወርስ የኾነን፣ (ልጅ)፤ ጌታዬ ሆይ! ተወዳጅም አድርገው። ዘከሪያ ሆይ! እኛ በወንድ ልጅ፣ ስሙ የሕያ በኾነ፣ ከዚህ በፊት ሞክሼን ባላደረግንለት እናበስርሃለን፤ (አለው)። ፦ ጌታዬ ሆይ! ሚስቴ መካን የነበረች ስትኾን፣ እኔም ከእርጅና ድርቀትን በእርግጥ የደረስኩ ስኾን፣ እንዴት ልጅ ይኖርኛል! አለ። (ጅብሪል) አለ (ነገሩ) እንደዚሁ ነው ጌታህ ከአሁን በፊት ምንም ያልነበርከውን የፈጠርኩህ ስኾን፣ እርሱ በኔ ላይ ቀላል ነው፤ አለ። ጌታዬ ሆይ! (እንግዲያስ) ለኔ ምልክትን አድርግልኝ አለ፤ ምልክትህ ጤናማ ሆነህ ሳለህ ሦስት ሌሊትን (ከነቀናቸዉ) ሰዎችን ለማነጋገር አለመቻልህ ነዉ፤ አለው። ከምኲራቡም በሕዝቦቹ ላይ ወጣ፤ በጧትና በማታ (ጌታችሁን) አወድሱ በማለትም፣ ወደነሱ ጠቀሰ።”
በዚህ ትረካ ውስጥ ብዙ ግጭቶች ይገኛሉ፡፡ ለአብነት ያህል፡-
- የመልአኩና የዘካርያስ ንግግር ትክክለኛው የቱ ነው? መልአኩ ለዘካርያስ “አላህ በየሕያ ከአላህ በሆነ ቃል የሚያረጋግጥ ጌታም ድንግልም፣ ከደጋጐቹ ነቢይም ሲሆን ያበስርሃል” አለው ወይንስ “ዘከሪያ ሆይ! እኛ በወንድ ልጅ፣ ስሙ የሕያ በኾነ፣ ከዚህ በፊት ሞክሼን ባላደረግንለት እናበስርሃለን” አለው? መልአኩ የተናገረው በሦስተኛ ነጠላ መደብ “አላህ … ያበስርሃል” በማለት ተናገረ ወይንስ በአንደኛ ብዙ መደብ “እኛ … እናበስርሃለን” አለው?
- በመጀመርያው ጥቅስ ውስጥ ተናጋሪው መልአኩ ሲሆን “አላህ … ያበስርሃል” በማለት በሦስተኛ ነጠላ መደብ ይናገራል፡፡ በሁለተኛው ውስጥ ግን “እኛ … እናበስርሃለን” የሚለው ንግግር የአላህ ሲሆን ያለ መልአክ ጣልቃ ገብነት አላህና ዘካርያስ እየተነጋገሩ ነው፡፡ ስለዚህ መልአክ ተልኳል ወይንስ አልተላከም? በሁለቱም አጋጣሚዎች መልአክ ከተላከ በሁለተኛው ውስጥ ንግግሩ በመልአክና በዘካርያስ መካከል ከመሆን ይልቅ በዘካርያስና በአላህ መካከል ስለምን ሆነ?
- ዘካርያስ ምን ብሎ መለሰ? “ጌታዬ ሆይ! እኔ እርጅና በእርግጥ የደረሰብኝ ስትሆን ባልተቤቴም መካን ስትሆን፥ ለኔ እንዴት ልጅ ይኖረኛል?” በማለት ወይንስ “ጌታዬ ሆይ! ሚስቴ መካን የነበረች ስትኾን፣ እኔም ከእርጅና ድርቀትን በእርግጥ የደረስኩ ስኾን፣ እንዴት ልጅ ይኖርኛል!” በማለት? የቱ ነው ትክክለኛው ንግግር?
- የመልአኩ መልስ ምን የሚል ነበር? “እንደዚሁ አላህ የሚሻዉን ነገር ይሠራል” የሚል ወይንስ “(ነገሩ) እንደዚሁ ነው ጌታህ ከአሁን በፊት ምንም ያልነበርከውን የፈጠርኩህ ስኾን፣ እርሱ በኔ ላይ ቀላል ነው” የሚል?
- ዘካርያስ ምልክትን በጠየቀ ጊዜ የተሰጠው ምላሽ ምን የሚል ነበር? “ምልክትሕ ሦስት ቀን በጥቅሻ ቢሆን እንጅ ሰዎችን አለማናገርህ ነዉ” የሚል ወይንስ “ምልክትህ ጤናማ ሆነህ ሳለህ ሦስት ሌሊትን (ከነቀናቸዉ) ሰዎችን ለማነጋገር አለመቻልህ ነዉ” የሚል? በመጀመርያው ላይ “ቀን” እንደተባለና በሁለተኛው ላይ “ሌሊት” እንደተባለ ልብ በሉ፡፡ በሁለተኛው ላይ በቅንፍ (ከነቀናቸው) የሚለውን የጨመሩት ተርጓሚዎች እንጂ በአረብኛው ውስጥ አይገኝም፡፡
የቱ ነው ትክክል?
- እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲገቡ ምን ተባሉ?
እስራኤላውያን ከግብፅ በመውጣት ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲገቡ አላህ የተናገራቸውን በተመለከተ ሁለት እርስ በርሳቸው የሚጋጩ ዘገባዎች በቁርኣን ውስጥ ይገኛሉ፡፡ እናንብባቸው፡-
ዘገባ አንድ፡- 2፡58-59 “«ይህችንም ከተማ ግቡ፡፡ ከርሷም በሻችሁት ስፍራ ሰፊን (ምግብ) ተመገቡ፡፡ በሩንም ያጎነበሳችሁ ኾናችሁ ግቡ፤ (ጥያቄያችን የኃጢአታችን መርገፍ ነው) በሉም፡፡ ኃጢአቶቻችሁን ለናንተ እንምራለንና፡፡ በጎ ሠሪዎችንም (ምንዳን) እንጨምርላቸዋለን» ባልን ጊዜ (አስታውሱ)፡፡ እነዚያም የበደሉት ሰዎች ከዚያ ለነሱ ከተባሉት ሌላ ቃልን ለወጡ፡፡ በነዚያም በበደሉት ላይ ያመጹ በመሆናቸው ምክንያት መቅሠፍትን አወረድንባቸው፡፡”
ዘገባ ሁለት፡- 7፡161-162 “ለነርሱም በተባሉ ጊዜ (አስታውስ) በዚች ከተማ ተቀመጡ፤ ከርሷም በሻችሁት ስፍራ ብሉ፤ (የምንፈልገው) የኃጢአታችንን መርገፍ ነው በሉም፤ የከተማይቱንም በር አጎንብሳችሁ ግቡ፤ ኃጢአቶቻችሁን ለእናንተ እንምራለንና፤ በጎ ለሰሩት በእርግጥ እንጨምራለን። ከነሱም ውስጥ እነዚያ (ራሳቸውን) የበደሉት ሰዎች፣ ከዚያ ለነርሱ ከተባለው ሌላ የኾነን ቃል ለወጡ፤ በነርሱም ላይ የበድሉ በነበሩት በደል መዐትን ከሰማይ ላክንባቸው።”
ይህ ዘገባ ብዙ ግጭቶችን በውስጥ ሸክፏል፡-
- እስራኤላውያን በትክክል ምንድነው የተባሉት? “ይህችንም ከተማ ግቡ” ወይንስ “በዚች ከተማ ተቀመጡ”?
- “ከርሷም በሻችሁት ስፍራ ሰፊን (ምግብ) ተመገቡ” ወይንስ “ከርሷም በሻችሁት ስፍራ ብሉ”?
- “በሩንም ያጎነበሳችሁ ኾናችሁ ግቡ” ወይንስ “የከተማይቱንም በር አጎንብሳችሁ ግቡ”?
- “በጎ ሠሪዎችንም (ምንዳን) እንጨምርላቸዋለን” ወይንስ በጎ ለሰሩት በእርግጥ እንጨምራለን?
የቱን እንቀበል?
- አላህ ሙሴን ምን አለው?
ዘገባ አንድ፡- 27:9-12 “ሙሳ ሆይ! እነሆ እኔ አሸናፊው ጥበበኛው አላህ ነኝ። በትርህንም ጣል (ተባለ ጣለም)፤ እርሷ እንደ ትንሽ እባብ በፍጥነት ስትስለከለክ ባያትም ጊዜ ፊቱን ዞሮ ሸሸ፤ አልተመለሰምም፤ ሙሳ ሆይ! አትፍራ፤ እኔ መልክተኞቹ እኔ ዘንድ አይፈሩምና፡፡ ግን የበደለ ሰው ከዚያም ከመጥፎ ሥራው በኋላ መልካምን የለወጠ እኔ መሐሪ አዛኝ ነኝ፡፡”
ዘገባ ሁለት፡- 28:31-32 “በመጣትም ጊዜ ከሸለቆው ቀኝ ዳርቻ ከዛፊቱ በኩል በተባረከችው ስፍራ ውስጥ «ሙሳ ሆይ! እኔ የዓለማት ጌታ አላህ እኔ ነኝ» በማለት ተጠራ በትርህንም ጣል» (ተባለ)፡፡ እንደ ትንሽ እባብ ስትስለከለክ ባያትም ጊዜ ወደ ኋላ ዞሮ ሸሸ፤ አልተመለሰምም፡፡ «ሙሳ ሆይ! ተመለስ አትፍራም፤ አንተ ከጥብቆቹ ነህና» (ተባለም)፡፡”
- አላህ በትክክል ምን አለው? “ሙሳ ሆይ! እነሆ እኔ አሸናፊው ጥበበኛው አላህ ነኝ” ወይንስ “ሙሳ ሆይ! እኔ የዓለማት ጌታ አላህ እኔ ነኝ”?
- “ሙሳ ሆይ! አትፍራ፤ እኔ መልክተኞቹ እኔ ዘንድ አይፈሩምና” ወይንስ “ሙሳ ሆይ! ተመለስ አትፍራም፤ አንተ ከጥብቆቹ ነህና”?
- በሎጥ ዘመን የነበሩት ህዝቦች ለሎጥ የመለሱለት መልስ የትኛውን ነው?
27:55-56 “«እናንተ ከሴቶች አልፋችሁ ወንዶችን ለመከጀል ትመጣላችሁን በእውነቱ እናንተ የምትሳሳቱ ሕዝቦች ናቸሁ፡፡» የሕዝቦቹም መልስ የሉጥን ቤተሰቦች «ከከተማችሁ አውጡ፡፡እነርሱ የሚጥራሩ ሰዎች ናቸውና» ማለት እንጅ ሌላ አልነበረም፡፡”
29:29 “እናንተ በእርግጥ ወንዶችን ትመጣላችሁን? መንገድን ትቆርጣላችሁን? በሸንጓችሁም የሚነወርን ነገር ትሠራላችሁን?(አላቸው)፤ የሕዝቦቹም መልስ ከውነተኞቹ እንደ ኾንክ የአላህን ቅጣት አምጣብን ማለት እንጂ ሌላ አልነበረም።”
26:165-167 “«ከዓለማት ሰዎች ወንዶችን ትመጣላችሁን? «ከሚስቶቻችሁም ጌታችሁ ለናንተ የፈጠረላችሁን ትተዋላችሁን በእውነቱ እናንተ ወሰን አላፊዎች ሕዝቦች ናችሁ፡፡» (እነርሱም) አሉ «ሉጥ ሆይ! ባትከለከል በእርግጥ (ከአገር) ከሚወጡት ትኾናለህ፡፡»”
የነዚህ ሦስቱ ጥቅሶች አውድ ተመሳሳይነት ያለው ሲሆን ተመለሱ የተባሉት መልሶች ግን በጣም የተራራቁና እርስ በርሳቸው የማይስማሙ ናቸው፡፡ የመጀመርያው ጥቅስ ሰዎቹ የተናገሩት እንዲህ ብቻ ነው ሲል ሁለተኛው ጥቅስ ደግሞ ከመጀመርያው መልስ የተለየ ነገር እንደ ተናገሩና ከዝያ ውጪ ሌላ ምንም ነገር እንዳልተናገሩ ይነግረናል፡፡ ሦስተኛውንም ጥቅስ ስንመለከት ከሁለቱ የተለየ ንግግር ያቀርብልናል፡፡ ታድያ የቱን እንቀበል?
- የሙሴን እጅ መንጣት በተመለከተ አላህ ምን አለው?
ዘገባ አንድ፡- 20፡22 “እጅህንም ወደ ብብትህ አግባ፣ ሌላ ታምር ስትሆን ያለ ነውር ነጭ ሆና ትወጣለችና።”
ዘገባ ሁለት፡- 27፡12 “እጅህንም በአንገትጌህ ውስጥ አግባ፤ ያለነውር (ያለ ለምጽ) ነጭ ሆና ትወጣለችና…”
ግጭቱ ግልፅ በመሆኑ ማብራርያ ማከል አስፈላጊ አይደለም፡፡
——————
ሙስሊም ሊቃውንት የቁርኣን ግጭቶችን ለማስወገድ ሁለት ተግባራትን ፈፅመዋል፡፡ የመጀመርያው ናሲክ ወልመንሱክ (ሻሪና ተሸሪ) የሚል አስተምሕሮን ማዳበር ነው፡፡ ይህ አስተምሕሮ በሙሐመድ ዘመን መሠረት የተጣለለት ሲሆን ሁለት እርስ በርሳቸው የሚጋጩ ጥቅሶች በቁርኣን ውስጥ ቢኖሩ በጊዜ ቅደም ተከተል የኋለኛው የፊተኛውን ይሽረዋል የሚል ነው፡፡ ነገር ግን ይህ አካሄድ ከሞላ ጎደል በትዕዛዛት መካከል የሚገኙ ግጭቶችን ለማስታረቅ እንጂ ሌሎች ግጭቶችን ለማስታረቅ አያገለግልም፡፡
ቀደምት ሙስሊም ሊቃውንት የቁርኣን ግጭቶችን ለማስወገድ የተጠቀሙት ሌላው አስደንጋጭ ዘዴ ከሌሎች የቁርኣን ክፍሎች ጋር የሚጋጩ የቁርኣን አናቅፅን ማስወገድ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ሱራ 33፡6 ላይ “ነቢዩ፣ በምእምናን ከነፍሶቻቸው ይበልጥ ተገቢ ነው፤ ሚስቶቹም እናቶቻቸው ናቸው” በሚለው ውስጥ የኡበይ ቢን ካዕብ ቁርኣን “እንዲሁም እርሱ አባታቸው ነው” በማለት ሙሐመድ የሙስሊሞች አባት መሆኑን ይገልፃል (Abdullah Yusuf Ali, The Holy Qur’an, p. 1104, footnote 3674)፡፡ ነገር ግን ይህ ንባብ እዚያው ሱራ 33፡40 ላይ “ሙሐመድ ከወንዶቻችሁ የአንድንም ሰው አባት አይደለም…” የሚል ንባብ ስለሚገኝ የኡበይ ቢን ካዕብ ንባብ ትክክለኛ እንደሆነ ቢታመንም ከኡሥማን ቁርኣን ውስጥ እንዲወገድ ተደርጓል፡፡ ቀደምት ሙስሊሞች ይህንን ንባብ በማስወገድ ግጭቱ እንዳይኖር ባያደርጉ ኖሮ የዘመናችን ሙስሊሞች ይህንን ዐይን ያወጣ ግጭት ለማስታረቅ የሚያዩትን ፍዳ ማሰብ አያዳግትም፡፡ በኡሥማንና በአል-ሐጃጅ ዘመናት ቁርኣንን የማረምና ቀደምት ቅጂዎችን የማቃጠል ተግባር በመፈፀሙ ምክንያት ስንት ግጭቶችን የሚያስከትሉ ጥቅሶች ከቁርኣን ውስጥ እንዲወገዱ እንደተደረጉ የሚያውቀው ፈጣሪ ብቻ ነው፡፡
ይቀጥላል…
ቅዱስ ቁርኣን