ቁርኣን በትክክል ተጠብቋልን?

ቁርኣን በትክክል ተጠብቋልን?

በሙስሊሞች እምነት መሠረት ቁርኣን ፍፁም የሰው እጅ ያልገባበት ከአላህ ዘንድ በቀጥታ የወረደ መገለጥ ነው፡፡ ይህንንም መገለጥ ‹‹ተንዚል›› በማለት ይጠሩታል፡፡ በ23 ዓመታት ውስጥ ለሙሐመድ በጅብሪል አማካይነት የወረዱላቸው የአላህ ቀጥተኛ ንግግሮች ስብስብ እንደሆነም ያምናሉ፡፡ “ኡም አል-ኪታብ” (የመጽሐፉ እናት) በመባል የሚታወቅ ያልተፈጠረ ነገር ግን አላህ በነበረበት ጊዜ ሁሉ ከርሱ ጋር የነበረ ጽሑፍ እንዳለና ቁርኣንም የዚያ ግልባጭ እንደሆነም ይናገራሉ፡፡ (ሱራ 13፡39)

ሙሐመድ በሕይወት በነበሩበት ዘመን ቁርኣን በአንድ ጥራዝ አልተሰበሰበም ነበር፡፡ ቁርኣንን በአንድ ጥራዝ እንዲሰበሰብ ያደረጉት የመጀመርያው ሰው ኸሊፋ አቡበከር ሲዲቅ ሲሆኑ በእርሳቸው ትዕዛዝ በዘይድ ሣቢት የተሰበሰበው ይህ የመጀመርያው ጥራዝ “ስሑፍ” በመባል ይታወቅ ነበር፡፡ ስያሜውም ከኢትዮጵያ እንደተወሰደ ይነገራል፡፡ ይህ የቁርኣን ስብስብ ያለ አናባቢ የተጻፈ ስለነበረ አንድ ወጥ የሆነ አነባበብ አልነበረውም፡፡[1] በአንድ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ በስደት የኖሩት ኻሊፋ ኡሥማን ታርሞ አንድ መልክ ያለው ቁርኣን እንዲዘጋጅ ካደረጉ በኋላ የመጀመርያዎቹን ጽሑፎች አቃጥለዋቸዋል፡፡[2]

ብዙ ሙስሊሞች አሁን በእጃቸው የሚገኘው የአረብኛ ቁርኣን በ1924 ዓ.ም. ይህንን መልክ እንደያዘና ከዚያ ቀደም ከሚገኙት የእጅ ጽሑፎች በብዙ መልኩ የሚለይ መሆኑን አያውቁም፡፡ “ሮያል ካይሮ ኤዲሽን” በመባል የሚታወቀው የአሁኑ ቁርኣን ብዙ ጥንታዊ የቁርኣን የእጅ ጽሑፎችን ያላገናዘበ ነው፡፡ በተለይም የሰነዓ የእጅ ጽሑፎች በመባል የሚታወቁት የቁርኣን ኮፒዎች ከተገኙ ወዲህ ይህ መጽሐፍ ሙስሊሞች ለዘመናት ሲናገሩለት እንደኖሩት ያልተለዋወጠ ሰነድ አለመሆኑ ስለተደረሰበት ብዙ መልስ ያላገኙ ጥያቄዎች ከምሑራን ዘንድ እየተነሱ ይገኛሉ፡፡[3]

በመጀመርያዎቹ ሙስሊሞች ዘመን እንኳ አንድ አይነት ቁርኣን እንዳልነበረና በተለያዩ ሰዎች እጅ የሚገኙት የቁርኣን ጽሑፎች ብዙ ልዩነቶች የሚታዩባቸው እንደነበሩ ከእስላማዊ ምንጮች መረዳት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ያህል ቁርኣንን የማስተማር ብቃቱ በሙሐመድ እንደተመሰከረለት በሐዲሳት ውስጥ የተዘገበው አብዱላህ ኢብን መስዑድ በራሱ የቁርኣን ቅጂ ውስጥ አልፈቲሃ የሚለውን ምዕራፍ አላካተተም ነበር፡፡ የእርሱ ቅጂ ሱራ 113 እና 114 አልነበረውም፣ ሱራ 3፡19፣ 39 ላይ የተለየ ንባብ ይከተላል፡፡[4] የዘይድንም ቁርኣን አይቀበልም ነበር፡፡[5]

ሳሂህ ሙስሊም ውስጥ እንደተዘገበው በሙሐመድ ዘመን ሙስሊሞች 129 አንቀፆች ካሉት ሱራ በረዓት (አል-ተውባ) ጋር እኩል የሆነ ሱራ ይደግሙ ነበር፡፡ ነገር ግን ከአንድ አንቀፅ በስተቀር ሙሉ በሙሉ ተረስቷል፡፡ አንዱም አንቀፅ ቢሆን በሐዲስ ውስጥ ከመጠቀሱ ውጪ በቁርኣን ውስጥ አልተካተተም፡፡[6]

ኢብን አቢ ዳውድ የሚከተለውን አስተላልፈዋል፡ “ብዙ የወረዱ የቁርኣን ጥቅሶች በየማማ ጦርነት ላይ በሞቱት ብዙ ሰዎች ይታወቁ ነበር …. ከጦርነቱ በተረፉት ሰዎች ግን አይታወቁም ነበር እንዲሁም በጽሑፍ አልሰፈሩም ነበር፡፡ ቁርኣን ሲሰበሰብ አቡ በከር፣ ዑመርም ሆነ ኡሥማን አያውቋቸውም ነበር፡፡ ከእነርሱ በኋላ በነበረ አንድም ሰው ጋ ማግኘት አልተቻለም፡፡”[7] ኢብን አቢ ዳውድ ከዚህ በተጨማሪም አንዳንድ የቁርኣን አንቀፆች ሆን ተብለው እንዳይካተቱ መደረጋቸውን ዘግበዋል፡፡[8]

አስ ሱዩጢ፣ ኢትቃን በተሰኘው መጽሐፋቸው ውስጥ የሚከተለውን ማስጠንቀቅያ አስቀምጠዋል፡- “ከእናንተ መካከል ማንም ሰው ሙሉውን ቁርኣን አግኝቼዋለሁ ብሎ መናገር የለበትም፡፡ የቁርኣን አብዛኛው ክፍል የጠፋ ሆኖ ሳለ ሁሉን አውቃለሁ ብሎ መናገር እንዴት ይቻላል? ከዚህ ይልቅ የተረፈውን አግኝቼዋለሁ ብሎ ይናገር፡፡”[9]

የሚከተለው ዘገባ ከአይሻ የተላለፈ ነው፡- “በዲንጋይ ስለመውገር እና ጎልማሳ ወንዶችን አሥር ጊዜ ጡት ስለማጥባት የሚናገሩት የቁርኣን ጥቅሶች ወርደው ነበር፡፡ የተጻፈበትም ወረቀት ከእኔ ጋ በእኔ ትራስ ስር ነበር፡፡ የአላህ መልእክተኛ ባረፉ ጊዜ በእረፍታቸው ተዋክበን ሳለን ፍየል ገብታ በላችው፡፡”[10] በሌላ ዘገባ ደግሞ አይሻ እንዲህ የሚል መረጃ አስተላልፋ ነበር፡- “ጎልማሶችን አሥር ጊዜ ጡት ማጥባት ጋብቻን ያፈርሳል የሚል ሕግ ለአላህ መልእክተኛ (ሶ.ዐ.ወ.) ወርዶላቸው ነበር፡፡ ሕጉም በቁርኣን ውስጥ ነበር፡፡ አምሥት ጊዜ በሚል ሌላ ሕግ ተሻረ፡፡ እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ በቁርኣን ውስጥ ነበር፤ ሙስሊሞችም ይደግሙት ነበር፡፡”[11] እነዚህ ሕግጋት ዛሬ በሙስሊሞች እየተተገበሩ የሚገኙ ቢሆኑም በቁርኣን ውስጥ ግን አይገኙም፡፡

አል ቡኻሪ የሚከተለውን ዘግቧል “አነስ ኢብን ማሊክ እንዳስተላለፈው ‹‹በቢር ማዑና የሞቱትን ሰዎች በተመለከተ እንዲህ የሚል አያት እንቀራ ነበር፡- ‹ለሕዝባችን ጌታችንን እንዳገኘነውና በኛ ደስ መሰኘቱን እኛንም ማስደሰቱን ንገሩልን፡፡› ነገር ግን ይህ አያ ከቁርኣን ውስጥ እንዲወጣ ተደርጓል››፡፡”[12]

ራፊዲ የተሰኙ አክራሪ የሆኑት ሺአዎች አሊ የነቢዩ ትክክለኛ ተተኪ መሆኑን የሚያሳዩትን ጨምሮ ወደ 500 የሚሆኑ ጥቅሶችን ኡስማንና ተባባሪዎቹ ‹ሙሳሂፍ› ከተሰኘው ከመጀመርያው የቁርኣን ስብስብ ውስጥ ሆነ ብለው ማስወገዳቸውን ይናገራሉ፡፡[13]

አብዱላህ ዩሱፍ አሊ የተሰኙት የቁርኣን ተርጓሚ ሱራ 33፡6 ላይ የኡበይ ቢን ካብ ቁርኣን ቅጂ “እንዲሁም እርሱ አባታቸው ነው” የሚል ሐረግ እንዳለው በግርጌ ማስታወሻ ላይ አስቀምጠዋል፡፡ ይህ ሐረግ ግን በዛሬዎቹ ቁርአኖች ውስጥ አይገኝም፡፡[14]

ማጠቃለያ

አል ኪንዲ የተሰኘ ክርስቲያን በ830 ዓ.ም. አል ሐሺም ከተባለ ሙስሊም ለተጻፈለት ደብዳቤ መልስ ሲሰጥ የሙስሊሞች ቅዱስ መጽሐፍ የሆነውን ቁርኣንን በተመለከተ የሚከተለውን ብሎ ነበር፡-

“ታሪኮች ከዚያም ከዚህም ተቆራርጠው በአንድ ቦታ ተዘበራርቀው ተቀምጠዋል፡፡ ይህም ብዙ እጆች በሥራው መሳተፋቸውንና የወደዱትን እየጨመሩና ያልወደዱትን ቆርጠው እያወጡ ግጭቶችን ማስከተላቸውን የሚያመለክት ማስረጃ ነው፡፡ ታድያ እነዚህ ከሰማይ የተላኩ መገለጦች ባህሪያት ናቸውን?”[15]

ይህ ጥያቄ የኛም ጥያቄ ነው፡፡ እውን ቁርኣን በትክክል ተጠብቋልን? ሙስሊም ወገኖቻችን አንድ ፊደል እንኳ እንዳልተጨመረበትና ከላዩ ላይ እንዳልተቀነሰ በተደጋጋሚ መናገራቸው ከነዚህ እውነታዎች አንፃር እንዴት ይታያል?


ማጣቀሻዎች

[1] የአማርኛ ቁርኣን መቅድም፣ ነጃሺ አሳታሚ ድርጅት፣ ገፅ 11

[2] ዝኒ ከማሁ፣ Sahih Al Bukhari 6:61:510

[3] Keith Small, Holy Books Have History, 2010, PP.116-117

[4] Abu Bakr `Abdullah b. abi Da’ud, “Kitab al Masahif”, ed. A. Jeffery, Cairo, 1936/1355, p. 17

[5] Ibn Sa’ad, Kitab al tabaqat al kabir, vol. 2, p. 444

[6] Sahih Muslim 5:2286; Jalal al Din `Abdul Rahman b. abi Bakr al Suyuti, “al Itqan fi `ulum al Qur’an”, Halabi, Cairo, 1935/1354, part 2, p. 25

[7] Ibn abi Da’ud, “Kitab al Masahif”, p. 23

[8] Ibid., p.11

[9] al Suyuti, “al Itqan fi `ulum al Qur’an”, part 2, p. 25

[10] Sunan Ibn Majah, 1944

[11] Sahih Muslim, book 8, no. 3421

[12] Sahih Bukhari, Vol. 5, Book 59, Hadith 416

[13] Ibn abi Da’ud, “Kitab al Masahif”, p. 36

[14] Abdullah Yusuf Ali. “The Holy Quran”, 1975, note 3674

[15] Bennet, C., In Search of Muhammad, 1998, P. 76

 

ቅዱስ ቁርኣን