ልጅ ለምን ወላጆቹን ይመስላል?
ሙሐመድ ሐሰተኛ ነቢይ መሆኑን የሚያረጋግጥ ሳይንሳዊና አመክንዮአዊ ስህተት
አል-ቡኻሪ እንደዘገበው ሙሐመድ መጀመሪያ መዲና ሲገባ እውነተኛ ነቢይ መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ አንድ አይሁዳዊ ሊያየው ሄዶ ነበር። ዓብዱላህ ቢን ሰላማ ተብሎ የሚጠራው ይህ አይሁዳዊ ሙሐመድ እውነተኛ ነቢይ መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ የተወሰኑ ጥያቄዎችን ጠየቀው። ሙሉ ዘገባው እንዲህ ይነበባል፦
አነስ እንደዘገበው፦ ዓብዱላህ ቢን ሰላማ የነቢዩን መዲና መድረስ በሰማ ጊዜ ወደ እርሱ መጥቶ እንዲህ አለው፦ “ከነቢይ በስተቀር ማንም የማያውቃቸውን ሦስት ነገሮች እጠይቅሃለሁ፦ የቂያማ (የሰዓቲቱ) የመጀመሪያዋ ምልክት ምንድን ናት? የጀነት ሰዎች መጀመሪያ የሚመገቡት ምግብ ምንድን ነው? ልጅ ለምን አባቱን ይመስላል? ለምንስ የእናቱን ወንድም (አጎቱን) ይመስላል?” የአላህ መልእክተኛም “አሁን ጅብሪል መልሱን ነገረኝ” አለ። ዓብዱላህም “እርሱ (ጅብሪል) ከመላእክት ሁሉ የአይሁድ ጠላት ነው” አለ።
የአላህ መልእክተኛም እንዲህ አለ፦ “የሰዓቲቱ የመጀመሪያ ምልክት ሰዎችን ከምስራቅ ወደ ምዕራብ የምትሰበስብ እሳት ናት። የጀነት ሰዎች መጀመሪያ የሚመገቡት ምግብ የዓሳ ጉበት ነው። ልጅ ወላጆቹን ስለመምሰሉ ደግሞ፦ አንድ ሰው ከሚስቱ ጋር ግንኙነት ሲያደርግና የእርሱ ፈሳሽ ቀድሞ ከፈሰሰ ልጁ አባቱን ይመስላል፤ የሴቲቱ ፈሳሽ ቀድሞ ከፈሰሰ ደግሞ ልጁ እርሷን ይመስላል።” በዚህ ጊዜ ዓብዱላህ ቢን ሰላማ “አንተ የአላህ መልእክተኛ መሆንህን እመሰክራለሁ” አለ። ዓብዱላህ ቢን ሰላማ በመቀጠልም “የአላህ መልእክተኛ ሆይ! አይሁዶች ውሸታሞች ናቸው፤ እኔ ሰልሜ ወደ እስልምና መግባቴን አንተ እነርሱን (ስለ እኔ) ሳትጠይቃቸው በፊት ካወቁ ስለ እኔ ይዋሻሉ” አለ። አይሁዶች ወደ አላህ መልእክተኛ መጡ፤ ዓብዱላህም ወደ ቤት ውስጥ ገባ። የአላህ መልእክተኛም (አይሁዶችን) “ዓብዱላህ ቢን ሰላማ በእናንተ ዘንድ ምን ዓይነት ሰው ነው?” ብሎ ጠየቀ። እነሱም “እርሱ ከመካከላችን በጣም አዋቂው፤ ምርጣችንና የምርጣችን ልጅ ነው” አሉ። የአላህ መልእክተኛም “እስልምናን ቢቀበል ምን ይመስላችኋል?” አለ። አይሁዶቹም “አላህ ከዚህ ይጠብቀው” አሉ። ከዚያም ዓብዱላህ ቢን ሰላማ ከፊታቸው ወጥቶ “ከአላህ በስተቀር ሊመለክ የሚገባው አምላክ እንደሌለና ሙሐመድም የአላህ መልእክተኛ መሆኑን እመሰክራለሁ” አለ። በዚህ ጊዜ እነርሱ “እርሱ ከመካከላችን በጣም ክፉውና የክፉው ልጅ ነው” በማለት ስለ እርሱ መጥፎ ማውራት ቀጠሉ። (ሰሒህ አል-ቡኻሪ፣ ቅጽ 4፣ መጽሐፍ 55፣ ቁጥር 546)
ኢብኑ ከሲር ከአል-በይሃቂ ተመሳሳይ ዘገባን እንዲህ ሲል ዘግቧል፦
“… እርሱ [ኢብን ሰላማ] ወደ ነቢዩ ዘንድ ሄዶ ‘ለነቢይ ብቻ መልሱ የሚታወቅ ሦስት ነገሮችን እጠይቅሃለሁ። እነሱም… ልጅ አባቱን ወይም እናቱን እንዲመስል የሚያደርገው ምንድን ነው?’ አለው። እርሱም ‘ጅብሪል ቀደም ሲል ነግሮኝ ነበር… የወንዱ ፈሳሽ ከሴቷ ፈሳሽ ከቀደመ ልጁ እርሱን ይመስላል፤ የሴቷ ፈሳሽ ከወንዱ ከቀደመ ደግሞ ልጁ እርሷን ይመስላል’ አለው። ዓብዱላህ ቢን ሰላማም ‘ከአላህ በስተቀር ሌላ አምላክ እንደሌለና አንተም የአላህ መልእክተኛ መሆንህን እመሰክራለሁ፤ የአላህ መልእክተኛ ሆይ አይሁዶች ውሸታም ሕዝቦች ናቸው። ስለ እኔ ሳይጠይቁ እስልምናን መቀበሌን ካወቁ ይዋሹሃል’ አለ።” (ኢብኑ ከሲር፣ የነቢዩ ሙሐመድ ሕይወት (አል-ሲራ አል-ነበዊያ)፣ ቅጽ 2፣ ገጽ 195)
ከላይ ያሉት ዘገባዎች ለሙሐመድ ተዓማኒነትም ሆነ ለኢብን ሰላማ ምስክርነት ከባድ ችግሮችን ያስከትላሉ። እነዚህ ትረካዎች ትልቅ ሳይንሳዊ ስህተትና ከባድ አመክንዮአዊ ግድፈት ይዘዋል።
በመጀመሪያ፣ ኢብን ሰላማ ራሱ አይሁዳዊ ሆኖ ሳለ በአጠቃላይ የአይሁዶች ታማኝነት ላይ ጥርጣሬ ማሳደሩ የሚገርም ነው። እርሱ ራሱ አይሁዳዊ እንደመሆኑ ይህ የገዛ ምስክርነቱን በእጅጉ ያዳክማል። አይሁዶች እንደ ሕዝብ ውሸታሞች ከሆኑ ኢብን ሰላማን ምን ያደርገዋል? እርሱን ከዚህ የጅምላ ፍርድ ነፃ ለማድረግ ምን ምክንያት አለ? አይሁዶች ከሌሎች ሰዎች በበለጠ ውሸታሞች ለመሆናቸው ምንም ማስረጃ የለም። በእርግጥ ቁርኣን ራሱ እንደሚቀበለው በመካከላቸው ውሸታሞች እንዳሉ ሁሉ ታማኝ ሰዎችም አሉ (ሱረቱ ኣሊ-ዒምራን 3፡75፣ 113-114፣ 199)። ኢብን ሰላማ የራሱን ወገኖች ስም እያጠፋ ሙሐመድን ለማስደሰት እየሞከረ ያለ ይመስላል። ምናልባትም በቀጣይ ክልሉን የመቆጣጠር ዕጣ ፈንታ በሙሐመድ እጅ እንደሚሆን ስላሰበ ከአሸናፊዎች ወገን ለመሆን ሲል ወደ ሙሐመድ ጎራ መክዳትን ሊመርጥ ችሏል።
ሁለተኛ፣ ኢብን ሰላማ ለሙሐመድ ላቀረባቸው ሦስት ጥያቄዎች መልስ ከነቢይ በስተቀር ማንም የማያውቃቸው ከሆነ እርሱ ራሱ እንዴት ሊያውቅ ቻለ? ሙሐመድ ትክክለኛ መልስ መስጠቱንስ ነቢይ ያልነበረው ኢብን ሰላማ እንዴት አወቀ? ከዚህ በስተጀርባ ያለውን አመክንዮ ልብ በሉ፦
- ለኢብን ሰላማ ሦስት ጥያቄዎች መልሱን ከነቢይ በስተቀር ማንም አያውቅም።
- ኢብን ሰላማ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልሱን ያውቃል።
- ስለዚህ ኢብን ሰላማ ነቢይ መሆን አለበት!
ይህ ካልሆነ ደግሞ ኢብን ሰላማ እውነተኛ ፈተና እያቀረበ ሳይሆን ወገን ለመቀየር ሲል ብቻ ሰበብ እየፈለገ ነበር ማለት ነው። ወይም ሦስተኛው አማራጭ ኢብን ሰላማ በዚህ “ፈተና” ውስጥ ያለውን አመክንዮአዊ ችግር ማየት የማይችል ማስተዋል የጎደለው ሰው ነበረ፤ ስለዚህ በሐሰተኛ ነቢይና በእውነተኛ ነቢይ መካከል መለየት ይችላል ተብሎ ሊታመን የሚችል ሰው አልነበረም ማለት ነው።
ከዚህም በላይ ሙሐመድ ስለ መልክ መመሳሰል የሰጠው መልስ በእጅጉ የተሳሳተ ነው። ጥያቄውንና የሙሐመድን መልስ ልብ በሉ፦
“ልጁ ወላጆቹን ስለመምሰሉ፦ አንድ ሰው ከሚስቱ ጋር ግንኙነት ሲያደርግና የእርሱ ፈሳሽ ቀድሞ ከፈሰሰ ልጁ አባቱን ይመስላል፤ የሴቲቱ ፈሳሽ ቀድሞ ከፈሰሰ ደግሞ ልጁ እርሷን ይመስላል።”
እንደ ሙሐመድ አባባል ጅብሪል እንዳሳወቀው ከሆነ ልጁ አባቱን ወይም እናቱን የሚመስለው ቀድሞ በፈሰሰው ፈሳሽ ላይ ተመስርቶ ነው። ሆኖም የፈሳሽ መፍሰስ ቅደም ተከተል በልጁ መልክ ላይ ምንም ተጽዕኖ እንደ ሌለው ይታወቃል። የሙሐመድ አባባል በርካታ ስህተቶችን ይዟል። በመጀመሪያ፣ የወንዱ ዘር (sperm) እና የሴቷ እንቁላል (ovum) ማን ያሸንፋል በሚል እርስ በርስ አይፎካከሩም። በተቃራኒው ግን መገናኘትና መዋሃድ ይኖርባቸዋል፤ ከዚያም የልጁ አካላዊ መልክ የሚወሰነው በሁለቱም ዘረመል ውህደት (DNA) ነው። ብዙውን ጊዜ ልጆች የሁለቱም ወገን ባሕርያት ይኖሯቸዋል። ሙሐመድ እንዳለው “ይህ ካልሆነ ያ” የሚባል ውድድር ሳይሆን የሁለቱም ንጥረ ነገሮች ውህደት ነው፤ ምንም እንኳ ልጁ አንዱን ወገን በበለጠ ሊመስል ቢችልም።
ሁለተኛ፣ ሙሐመድ በዘመኑ የነበሩት ሰዎች የሚያውቁትን የሚታየውን የወንድና የሴት ፈሳሽ እየጠቀሰ ነበር። ይህ በሙሐመድ አባባል ውስጥ የሚገኝ የከፋ ስህተት ነው፦ በግንኙነት ወቅት የሚወጣው የሴት ፈሳሽ ልጁ ከሚቀበለው የዘረመል መረጃ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፤ ምክንያቱም የሴት ፈሳሽ እንቁላል (ovum) አይዝምና። በሴቶች የስሜት መነሳሳት ወቅት የሚወጡት ፈሳሾች ብቸኛ ዓላማቸው ግንኙነቱን ማለስለስ ሲሆን እነዚህ ፈሳሾች የሚወጡት በብልት (vagina) ውስጥ ነው። በሌላ በኩል እንቁላሉ ሊዳብር የሚችለው ከእንቁላል መለቀቅ (ovulation) በኋላ ለጥቂት ሰዓታት ብቻ ሲሆን፣ የሚቆየውም በማህፀን ቱቦ (fallopian tubes) ውስጥ ነው። የወንዱና የሴቷ ፈሳሾች በብልት ውስጥ ይገናኛሉ ነገር ግን የእንቁላሉ መገኛ ቦታ እዚያ አይደለም። በተለይም የሴቷ ፈሳሽ የልጁ ባሕርያት በሚወሰኑበት (ክሮሞዞሞች በሚዋሃዱበት) ሁኔታ ውስጥ ምንም ሚና የለውም።
ሦስተኛ፣ የሴቷ ፈሳሽ ከጄኔቲክ መረጃ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው በመገንዘብ አንዳንድ ሙስሊሞች “የሴቷ ፈሳሽ” የተባለው የእንቁላል መለቀቅ (ovulation) ነው ለማለት ይሞክራሉ። ሆኖም ያም ቢሆን አይሠራም። የሙሐመድ አባባል እያንዳንዱ ግንኙነት ልጅን የሚፈጥር አስመስሎ የሚያቀርብ ቢሆንም እያወራ ያለው በግንኙነት ወቅት ስለሚፈሰው ፈሳሽ መሆኑ ግልጽ ነው። ሆኖም እንቁላል ብዙውን ጊዜ በግንኙነት ወቅት አይለቀቅም። በእንቁላልና በዘር ፍሬ ዝግተኛ ፍጥነት ምክንያት የእንቁላል መዳበር ብዙውን ጊዜ የሚከሰተው እንቁላል ከመለቀቁ ከጥቂት ቀናት በፊት በተደረገ ግንኙነት በሚገኝ የወንድ ዘር ነው። ሙሐመድ ስለ ሂደቱ የተናገረበት መንገድ ከሕክምና እውነታ ጋር በጭራሽ አይስማማም።
አንዳንድ ሙስሊሞች ይህ ሐዲሥ ስለ መልክ መመሳሰል ሳይሆን ስለ ጾታ መወሰን (ወንድ ወይም ሴት መሆኑን) እያወራ ነው ብለው ለመረዳት ይፈልጋሉ። ምንም እንኳ በሐዲሡ ውስጥ ያለው የጥያቄ አወቃቀር (በተለይ በሰሒህ አል-ቡኻሪ ያለው) እንዲህ ዓይነት ትርጓሜን ባይፈቅድም ይህ ሙከራ ግን ሌላ አስገራሚ ስህተት ያስከትላል። ምክንያቱም በሕክምናው ዓለም (ለምሳሌ በዶክተር ላንድረም ሸትልስ ጥናት መሠረት) የወንድ ዘር ፈሳሽ ከእንቁላል መለቀቅ (ovulation) በኋላ ጥቂት ቆይቶ ከተከሰተ ወንድ ልጅ የመፈጠር ዕድሉ ከሴት ይልቅ በጣም ከፍተኛ ነው። ይህም የሙሐመድ አባባል ቀጥተኛ ተቃራኒ ነው። ለዚህም ምክንያቱ X-ክሮሞዞም ያላቸው የወንድ ዘሮች (ሴት ልጅን የሚፈጥሩ) ዝግተኛ ቢሆኑም ረጅም ዕድሜ ይኖራሉ። Y-ክሮሞዞም ያላቸው (ወንድ ልጅን የሚፈጥሩ) ደግሞ ፈጣን ቢሆኑም ዕድሜያቸው አጭር ነው። ስለዚህ እንቁላሉ በማህፀን ቱቦ ውስጥ ዝግጁ ሆኖ ከቆየ (የሴቷ ፈሳሽ ቀድሞ ከፈሰሰ)፤ ፈጣኑ Y-ክሮሞዞም ያለው ዘር ቀድሞ የመድረስና እንቁላሉን የማዳበር ዕድሉ ከፍተኛ ነው። ይህም ወንድ ልጅ የመወለድ ዕድልን ይጨምራል። ሙሐመድ ግን “የሴቷ ፈሳሽ ቀድሞ ከፈሰሰ ልጁ እሷን (ሴት) ይመስላል” በማለት የተናገረው ከላይ ከተጠቀሰው ሳይንሳዊ እውነታ ጋር ይጋጫል። ይህ የሚያሳየው ሙሐመድ ስለ ጾታ አወሳሰንም ሆነ ስለ ዘረመል (genetics) የነበረው ግንዛቤ የተሳሳተ መሆኑን ነው።
ለማንኛውም ግን ከ100 ሚሊዮን በላይ የወንድ ዘሮች በአንድ ጊዜ ስለሚለቀቁ በዚህ መንገድ ፆታን ለመወሰን ከፍተኛ ዕድል ይኖራል እንላለን እንጂ መቶ በመቶ እርግጠኛ መሆን አይቻልም። ሙሐመድ ግን እንደዚህ ሲሆን እንዲህ ይሆናል እንደዚያ ከሆነ ደግሞ እንደዚያ ይሆናል የሚል የሙሉ እርግጠኛነት ንግግር ነው የተናገረው። ይህ ደግሞ በእጅጉ የተሳሳተ ነው።
ለማጠቃለል፣ በማንኛውም መንገድ ቢታይ ይህ አባባል ሳይንሳዊ ስህተት ነው፤ ይህንን መገለጥ ለሙሐመድ የሰጠው ጅብሪል ነው ከተባለ አላህ የሳይንሳዊ ስህተት ምንጭ ነው ማለት ነው። ይህም የሚከተሉትን አማራጮች ይሰጠናል። ወይ ኢብን ሰላማ የራሱን ጥያቄ አመክንዮአዊ ግድፈት ቢያውቅም ሐቀኛ አልነበረም፤ ስለዚህ ፈተና ተብዬው ወገን ለመቀየር ብቻ የቀረበ ሰበብ ነበር። ወይም ኢብን ሰላማ ይህ እውነተኛ ፈተና ነው ብሎ ካመነ፤ መልሱን ነቢይ ብቻ ስለሚያውቀውና እርሱ ነቢይ ስላልሆነ ሙሐመድ ትክክል መሆኑን ለመወሰን የሚበቃ ሰው አልነበረም።
ሆኖም የሙሐመድ ምላሾች በሁለት መንገድ በፈተናው እንደወደቀ ያሳያሉ። በመጀመሪያ፣ የተሳሳተ ሳይንሳዊ መልስ ሰጥቷል። ሁለተኛ፣ እንደ እውነተኛ ነቢይ በፈተናው ውስጥ ያለውን ስህተት ማጋለጥ ነበረበት፤ ማለትም ነቢይ ሳይሆኑ መልሱ ትክክል መሆኑን ማንም ሊያውቅ ስለማይችል ፈተናው ከንቱ መሆኑን መጠቆም ነበረበት። ነገር ግን ነገሩ ከዚህ ይብሳል። በእነዚህ ዘገባዎች መሠረት ሙሐመድ ይህን ዓይን ያወጣ የሐሰት መረጃ ያገኘው ልክ የቁርኣን አንቀጾችን በሚያገኝበት መንገድ ከጅብሪል ነው! መረጃው ስህተት ስለሆነ ወይ አላህና ጅብሪል ስለ ጄኔቲክስ ምንም የሚያውቁት ነገር የለም፤ ወይም ሙሐመድ ከጅብሪል ምንም ዓይነት መረጃ ሳይደርሰው ዝም ብሎ ዋሽቷል። ይህም ሙሐመድ ከተመሳሳይ ምንጭ አገኘሁ በሚላቸው ሌሎች “መገለጦች” ላይ ያለውን እምነት ሁሉ ያጠፋል።
ይህ ሁሉ የሚጠቁመው ሙሐመድ በዘመኑ የነበረውን የተሳሳተ ሳይንሳዊ ግንዛቤና ተረቶች ዝም ብሎ ይደግም እንደነበር ነው። ሙሐመድ በዘመኑ ሰዎች ያምኑባቸው የነበሩትን ኢ-ሳይንሳዊ ጉዳዮች ከአላህ እንደመጣ መገለጥ አድርጎ ለማቅረብ ሞክሯል። በዚህም አላህን የእነዚህ ተረቶችና ሳይንሳዊ ስህተቶች ደራሲ አድርጎታል። ዛሬ ስለ ጄኔቲክስ እውነቱን በምናውቅበት ደረጃ ላይ በመሆናችን የሙሐመድ የተሳሳተ መልስ ሐሰተኛ ነቢይ መሆኑን ያለምንም ጥርጥር ያረጋግጣል።
ምንጭ ከመጠነኛ ማሻሻያ ጋር፦ Islamic Genetics: How a Jew’s testing of Muhammad proves that he was not a true prophet
