ቁርኣን በሰው አምሳል ይመጣል

ቁርአን በሰው አምሳል ይመጣል

የሼኽ ኡሥማንና የአንቶኒ ሮጀርስ ሙግት – የዋሸው ማን ነው?


ሰሞኑን የሀገራችን ኡስታዞች ጉዳዩን አጀንዳቸው አድርገውት ስለነበረ መልስ ለመስጠት ብፈልግም ጊዜ ስላላገኘሁ ልጽፍ አልቻልኩም፡፡ ዛሬ ትንሽ ፋታ ስላገኘሁ ይህንን ልል ወደድኩ፡፡

ሼኽ ኡሥማን የተሰኘ ሰው በዚህ ሰሞን በአሜሪካ አደባባዮች በራሪ ወረቀቶችን በማደል እስልምናን እየሰበከ ይገኛል፡፡ ይህ ሰው ክርስቲያን ፕሪንስ ፊትለፊት እንዲሞግተው ጥሪ ያቀረበ ቢሆንም ሲፒ በኢንተርኔት እንጂ በአካል ፊቱን በማሳየት መሞገት ስለማይፈልግ በእርሱ ፈንታ አንቶኒ ሮጀርስ፣ ሳም ሸሙንና ዶ/ር ዴቪድ ውድ ሙግት ሊገጥሙት እርሱ ወዳለበት ድረስ ተጉዘው ነበር፡፡ በሁለቱም ወገኖች የተቀረፁ ቪድዮዎች ዩቲዩብ ላይ ስለሚገኙ ማየት ይቻላል፡፡ አንዳንድ ትዝብቶቼን ላስቀድምና ዋደ ዋናው ነጥብ ልሂድ፡፡

በቪድዮዎቹ ውስጥ እንደሚታየው ሦስቱ ክርስቲያን ወንድሞች አቀራረባቸው አክብሮት የታየበትና በትዕግስት የተሞላ ነበር፡፡ በአንጻሩ ግን ሼኽ ኡሥማን ወደ እርሱ የመጡትን እንግዶች ቢያንስ እንደ አመጣጣቸው ማስተናገድ ሲኖርበት በንቀትና ትዕግስትን በሚፈታተን እብሪት ነበር ሲያናግራቸው የነበረው፡፡ ገና ከጅምሩ እነዚህ ወንድሞች ቦታው ላይ ሲደርሱ ልክ እንደማያውቃቸው ሆኖ ተዋወቃቸው፡፡ እነርሱም በቀና መንፈስ ተዋወቁት፡፡ የእነርሱን ቪድዮዎች ልቅም አድርጎ ሲከታተል እንደነበረ ግን ወደ ውይይቱ ሲገቡ ግልፅ ሆኗል፡፡ የክርስቲያን-ሙስሊም ውይይቶችን የሚከታተል ሰው እነዚህን ወንድሞች ሊያውቅ የማይችልበት ተዓምር የለም፡፡ ቀጥሎ የተነሳው ሐሳብ ሲፒን የተመለከተ ነበር፡፡ ሼኽ ኡሥማን “ሲፒ ፊቱ እንዳይታይ ከፈለገ የፊት መሸፈኛ ቡርካ ነገር እንደ ሴት አድርጌለት ለምን መጥቶ አይወያይም?” የሚል አስተያየት ሰነዘረ፡፡ ሦስቱ ወንድሞች ግን መልስ አልሰጡትም፤ ዓላማቸው ሲፒን መከላከል አልነበረምና፡፡ ሼኹ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ፊትን ሙሉ በሙሉ መሸፈን የሴተኛ አዳሪ አለባበስ መሆኑን የሚያውቅ አይመስልም (ዘፍጥረት 38፡15)፡፡ ሲጀመር ሼኹ የውይይት ብቃት ካለው የሲፒ ፊት መታየት አለመታየት ምን ያደርግለታል? በአካል ተገናኙም አልተገናኙም ዞሮ ዞሮ በድምፅ ነው የሚነጋገሩት፡፡ በአካል ከተገናኙ የሚወርድ የተለየ ራዕይ ይኖር ይሆን? ሙስሊም ሰባኪያን “በአካል እንገናኝ” የሚሉት ምን እያሰቡ ነው ግን? አብዛኞቹ ያ ነገር ይሆኑ እንዴ? ወይስ የሃይማኖታቸውን ሰላማዊነት ሊያሳዩን? ብቻ ይገርማል፡፡ ከዚያ ውይይቱ ተጀመረ፡፡ ክርስቶስ በሥጋ መገለጡን የተመለከተ ነበር፡፡ ርዕሱን ያነሳው ሼኹ ነበር፡፡ ገና መናገር ሲጀምር የክርስትናን አስተምህሮ በተሳሳተ መንገድ አቀረበ፤ አንቶኒም ወዲያውኑ አረመው፡፡ ሼኹ ስለ ክርስትና አስተምህሮ ምንም ዕውቀት እንደሌለው ግልፅ ነው፡፡ አንቶኒ በጥልቅ ደረጃ ሲናገር የነበረ ሲሆን የሼኹ ጥያቄ ግን የህፃን ይመስል ነበር፡፡ በመሃል ጥያቄ ሲበረታበት ድክመቱን ለመሸፈን “እኔ ተከራካሪ አይደለሁም” የሚል ማስተባበያ ሲሰጥ ይደመጣል፡፡ ሳም በመሃል ገብቶ ጥያቄ ለመጠየቅ ሲሞክር ሼኹ ከአንድ ሰው ጋር ብቻ መነጋገር እንደሚፈልግ ስለገለፀ ሳምና ዴቪድ ዝምታን መርጠው ነበር፡፡ ዴቪድ አልፎ አልፎ ሐሳብ ጣል ከማድረግና ሁለቱን ወገኖች ለማስማማት ከመሞከር የዘለለ ሙግት መግጠም አልፈለገም፡፡ ሳም ከዚያ ወዲህ ጭራሹኑ ሐሳብ ያልሰነዘረ ሲሆን ራቅ ብሎ መቆምን መርጦ ነበር፤ ሼኹ “ለሦስት ገጠሙኝ” ብሎ ወቀሳ እንዳያቀርብ መሆኑን ኋላ ላይ ተናግሯል፡፡ አንዳንድ የሀገራችን ሰባኪያን ግን “ፈርተው ነው” የሚል አስተያየት ሲሰጡ አይቻለሁ፡፡ ቢፈሩማ ኖሮ ሙስሊሞቹ እንደሚያደርጉት ለሦስት ይረባረቡበት ነበር፡፡ አትቀልዱ እንጂ፡፡ እነዚህ ወንድሞች እኮ በዓለም ላይ አሉ የተባሉትን ሙስሊም ሰባኪያንና የኑፋቄ መምህራን ገጥመው ብቃታቸውን ያስመሰከሩ የዓለማችን ምርጥ ተሟጋቾች ናቸው፡፡ አንድ የመንገድ ዳር ሰባኪ ሼኽ ለእነርሱ ምንም ማለት አይደለም፡፡ ለሰላማዊ ውይይት ሲሉ አቀራረባቸውን የተለሳለሰ ስላደረጉ የተሳሳተ ድምዳሜ አትውሰዱ፡፡ ምሑራዊ ሙግት የሚመዘነው ማን ማንን አንጓጠጠ ወይም አሳንሶ ለማሳየት ሞከረ በሚል ሳይሆን በቀረበው ሐሳብ ነው፡፡ የአላዋቂ ሚዛናችሁ ለናንተ እንጂ ማስተዋል ላላቸው ወገኖች አይሠራም፡፡

ወደ ዋናው ሐሳብ ስንመጣ ከውይይቱ በኋላ የብዙዎችን ትኩረት ያገኘው ጉዳይ ቁርአን በሰው አምሳል መምጣቱን በተመለከተ አንቶኒ የጠቀሰው ሐዲስ ነበር፡፡ በቪድየው ውስጥ እንደሚታየው ሼኹና አንቶኒ ሐሳቦችን ሲለዋወጡ የነበሩት ከትውስታ ነበር፡፡ አንቶኒ ሐዲሱን በቃል ጠቅሶ ሲናገር ሼኽ ኡሥማን ምንጩን ጠየቀው፤ አንቶኒም “እንደዚያ የሚል ነገር ሐዲስ ውስጥ የለም እያልክ ነው?” ብሎ ሲጠይቀው ሼኹ “በተዓማኒ ሐዲስ ውስጥ እንደዚያ የሚል ነገር አይቼ አላውቅም” የሚል ምላሽ ሰጠው፡፡ አንቶኒም ቲርሚዚ ሐዲስ ውስጥ እንደሚገኝ ነገረው፡፡ ሼኽ ኡሥማን ሐዲሱ ደኢፍ ነው በሚለው ምላሹ ጸና፡፡ ከዚያ ዴቪድ በሱናን ኢብን ማጃህ ውስጥ የሚገኝ ተመሳሳይ ሐዲስ ከስልኩ በማውጣት አሳየውና ደኢፍ ሳይሆን ሐሰን እንደሚል ነገረው፡፡ የሼኹ ምላሽ “ደሩሰላም” የተባለው አታሚ ድርጅት ሐሰን ቢለውም ሼኽ አል-አልባኒ ደኢፍ ብለውታል ስለዚህ ደኢፍ ነው፤ ደሩሰላም ሐሰን ያለበት ምክንያት ሐዲሱ ሐሰን ስለሆነ ሳይሆን “ቁርአን ይመጣል” የሚል ሐሳብ በሌሎች ሐዲሶች ውስጥ ስለሚገኝ ነው የሚል ነበር፡፡ በዚያ ዙርያ የተወሰነ ያህል ከተወያዩ በኋላ ጉዳዩ ተቋጭቶ በሌሎች ሐሳቦች ላይ መወያየት ቀጠሉ፡፡

ሦስቱ ክርስቲያን ወንድሞች ወደ ቤታቸው እየተጓዙ ሳሉ በመኪናቸው ውስጥ ሆነው ስለ ሁኔታው እየተነጋገሩ በቀረፁት ቪድዮ ደሩሰላም ሐዲሱን ሐሰን የሚል ደረጃ የሰጠው ከአል-አልባኒ ወስዶ እንደሆነ ተናገሩ፤ ሼኹም መዋሸቱን ገለጹ፡፡

በቀጣዮቹ ቀናት ሼኽ ኡሥማን የዋሸው እርሱ እንዳልሆነና ክርስቲያኖቹ እንደሆኑ ለማሳየት በሐዲስ መጻሕፍት ስብስቦች በተሞላ መደርደርያ ፊትለፊተ ተቀምጦ ቪድዮ ቀረፀ፤ በቪድዮውም ውስጥ የኢብን ማጃህ ሐዲስ ደኢፍ መሆኑን አል-አልባኒ የተናገሩበትን ቦታ በኩራት ከመጽሐፍ አውጥቶ አሳየ፡፡ አት-ቲርሚዚ ሐዲስ ውስጥም ቁርአን ደብዛዛ ቀለም ባለው ሰው ተመስሎ ይመጣል የሚል ነገር እንደሌለ በድጋሜ አረጋገጠ፡፡ በሐዲስ ጥናት የማስተርስ ዲግሪ እንዳለው በመመጻደቅ እየተናገረ ክርስያኖቹን ለማሳነስ ሞከረ፡፡ ውሸታሙ ማን ይሆን? እስኪ መረጃዎችን እንመልከት፡፡

በአት-ቲርሚዚ ሐዲስ ቁርአን “ደብዛዛ ቀለም ያለው” ተብሎ ባይገለፅም በዕለተ ትንሣኤ በአላህ ፊት ቀርቦ በትክክል ሲያነበንቡት ለኖሩት ሰዎች እንደሚመሰክርና እንደሚያማልድላቸው ተጽፏል  (At-Tirmidhi, Vol. 5, Book 42, Hadith 2915)፡፡ ሐዲሱ በአት-ትርሚዚ “ሐሰን-ሳሒህ” መሆኑ ተገልጿል፡፡ ዋናው ነጥብ “ቁርአን ማንነት አለው ወይስ የለውም?” የሚለው ጥያቄ በመሆኑ የአንቶኒ ሙግት ምላሽ አላገኘም፡፡

በኢብን ማጃህ ውስጥ የሚገኘውን ሐዲስ በተመለከተ ሼኹ ግልፅ ቅጥፈት ቀጥፏል፡፡ አል-አልባኒ ሐዲሱን ደኢፍ ብቻ ብሎ አልተወውም፤ ነገር ግን ሐሰንም ሊሆን እንደሚችል አስተያየቱን አስቀምጧል፡፡የሚገርመው ነገር ሼኹ የመጽሐፉን ምስል ቪድዮው ላይ ሲያሳይ “ደኢፍ” የሚለውን ብቻ አሳይቶ “ሐሰን ተብሎ ሊመደብ ይችላል” የሚለውን ክፍል ቆርጦ አስቀርቶታተል፡፡ ይህንን ቅጥፈቱን ሲፒ መጽሐፉን በማሳየት አጋልጦታል፡፡ ሼኹ ክፍሉን የቆረጠው “አል-አልባኒ ሐዲሱን ሐሰን አላሉትም” የሚለውን ቅጥፈቱን ስለሚያጋልጥበት ነው፡፡ እንዲህ ያለ ማጭበርበር ከምሑር አይጠበቅም፤ ከሙስሊም ሰባኪያን ካልሆ በስተቀር፡፡ ሌላው አል-አልባኒ “አል-ሲልሲላት አልሳሂህ” በሚለው መጽሐፉ ያንኑ ሐዲስ ጠቅሰው “ሳሂህ” ደረጃ እንዳለው ተናረዋል፡-

2829 – ( الصحيحة )

يجيء القرآن يوم القيامة كالرجل الشاحب يقول لصاحبه : هل تعرفني ؟ أنا الذي كنت أسهر ليلك واظميء هواجرك وإن كل تاجر من وراء تجارته وأنا لك اليوم من وراء كل تاجر فيعطى الملك بيمينه والخلد بشماله ويوضع على رأسه تاج الوقار ويكسى والداه حلتين لا تقوم لهم الدنيا وما فيها فيقولان : يا رب أنى لنا هذا ؟ فيقال : بتعليم ولدكما القرآن . وإن صاحب القرآن يقال له يوم القيامة : اقرا وارق في الدرجات ورتل كما كنت ترتل في الدنيا فإن منزلك عند آخر آية معك

ከላይ እንደሚነበበው ሐዲሱ  الصحيحة አ-ሷሂህ ተብሏል፡፡ የመጀመርያው መስመር ትርጉም እንደሚከተለው ነው፡- “በፍርድ ቀን ቁርአን ደብዛዛ ቀለም ባለው ሰው መልክ በመምጣት ለባለቤቱ “ታውቀኛለህ ወይ?” ይለዋል…”፡፡ የአል-አልባኒን መጽሐፍ በዚህ ገጽ ማግኘት ይቻላል http://islamport.com/w/alb/Web/3111/2829.htm

አል-አልባኒ “አህከም አል-ጀናዒዝ” በሚል መጽሐፋቸው ይህንኑ ሐዲስ “ሳሂህ” ደረጃ እንደሰጡት ከዚህ የፋትዋ ገጽ ላይ ያገኘሁት መረጃ ያሳያል፡፡ https://islamqa.info/en/answers/93151/good-deeds-appear-in-the-form-of-a-man-in-the-grave

በተመሳሳይ በኢብን ማጃህ ውስጥ የሚገኘውን( ሼኽ ኡስማን ደዒፍ ነው ብሎ የተከራከረውን ሐዲስ ማለት ነው) አል-ቡሰይሪ እና አል-አልባኒ “ሐሰን” የሚል ደረጃ እንደሰጡት እዚሁ ገጽ ላይ ተነግሯል፡፡ ስለዚህ ማን ነው የዋሸው? ሼኹ አጭበርባሪ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ የሀገራችን ኡስታዞች በባዶ ሜዳ አቧራ አታንሱ፡፡ አንድ ሰው ከልክ ባለፈ በራስ መተማመን ተወጣጥሮ ተናገረ ማለት እውነተኛ ነው ማለት አይደለም፡፡ ጭብጨባና ጫጫታ ከማብዛታችሁ በፊት መረጃ አጣሩ፡፡ መቼስ እናንተን መምከር ጥቁር ድንጋይ ላይ ውኃ ማፍሰስ ነው፡፡

እግዚአብሔር ከፈቀደ ቁርአን በሰው አምሳል ይመጣል የሚለው ሐሳብ በክርስቲያን-ሙስሊም ውይይት ውስጥ ስላለው አንድምታ ወደፊት እንመለስበታለን፡፡

ቁርኣን