ሩሁላህ
የኢየሱስን አምላክነት የሚያረጋግጥ ሌላኛው ስያሜ
ሱረቱ አል-ኒሳእ 4፡171
“እላንተ የመጽሐፉ ሰዎች ሆይ! በሃይማኖታችሁ ወሰንን አትለፉ፤ በአላህም ላይ እውነትን እንጂ አትናገሩ፤ የመርየም ልጅ አልመሲሕ ዒሳ፣ የአላህ መልክተኛ፣ ወደ መርየም የጣላት (የሁን) ቃሉም ከርሱ የሆነ መንፈስም ብቻ ነው፤ በአላህና በመልክተኞቹም እመኑ (አማልክት) ሦስት ናቸው አትበሉም፤ ተከልከሉ ለናንተ የተሻለ ይሆናልና፤ አላህ አንድ አምላክ ብቻ ነው። ለርሱ ልጅ ያለው ከመሆን የጠራ ነው። በሰማያትና በምድር ያለ ሁሉ የርሱ ነው። መመኪያም በአላህ በቃ።”
በቁርአን ውስጥ ኢየሱስ የአላህ ቃል (ከሊማቱላህ) ብቻ ሳይሆን የአላህ መንፈስ (ሩሁላህ) ጭምር ነው የተባለው፡፡ ይህ ስያሜ ከ ከሊማቱላህ በመጠኑ የተለየ ቢሆንም ስያሜው ለኢየሱስ ብቻ የተገባው ሲሆን የቃሉ ምንጭ ራሱ አላህ እንደሆነው ሁሉ የመንፈሱም ምንጭ ራሱ አላህ ነው፡፡ በሱራ 3፡45 ላይ ኢየሱስ ካሊማቲም ሚንሁ (ከእርሱ የኾነ ቃል) ተብሏል፡፡ ልክ እንደዚያው በሱራ 4፡171 ላይ ሩሁን ሚንሁ (ከእርሱ የኾነ መንፈስ) ተብሏል፡፡ በሁለቱም ስያሜዎች ውስጥ ግልጽ ሆኖ እንደሚታየው በዚህ ስም ለሚጠራው አካል ምንጭ የሆነው ራሱ አላህ መሆኑ ነው፡፡ ኢየሱስ የእርሱ ቃል እና የእርሱ መንፈስ ነው፡፡ እንደተለመደው ቁርአን ይህ አጠራር ምን ማለት እንደሆነ የሰጠው የረባ ማብራርያ የለም፡፡ ነገር ግን እኛ ክርስቲያኖች ኢየሱስ ከምድር አፈር የተፈጠረ ሳይሆን ሰው ሆኖ ከመወለዱ በፊት የነበረ ዘላለማዊ መንፈስ መሆኑን የምናምነውን የሚደግፍ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
ለምን ኢየሱስ በዚያ ስም በብቸኝነት እንደተሰየመና ትርጉሙ ምን ማለት እንደሆነ ቁርአን አልገለጸም፤ ከዚህም መረዳት የምንችለው ሙሐመድ የክርስቲያኖችን ትምሕርቶች ሰምቶ ትርጉማቸውን ሳያውቅ የማመሳሰል ሙከራ ማድረጉንና መኮረጁን ነው፡፡ ይህንን ኩረጃውን ደግሞ ኢየሱስ እንደሌሎቹ ነቢያት ነቢይ ብቻ ነው በማለት መልሶ ተቃረነው፡፡
ከላይ በተጠቀሰው አንቀጽ ሙሐመድ ኢየሱስን ለማመልከት “ሎጎስ (ቃል)”ን እና “መንፈስ”ን በመጠቀም ወደ ትምህርተ ሥላሴ ተጠግቷል፡፡ ከዚህም በግልጽ የምንረዳው ሙሐመድ በስሚ ስሚ የተጠቀማቸው የነዚያ መጠርያዎች ትርጉም በክርስትና አስተምህሮ ምንን እንደሚያመለክት አለማወቁን ነው፡፡[1]
ይህ ስያሜ (ሩሁላህ) ምን ትርጉም እንዳለው የሚጠቁሙ ጥቂት ቁርአናዊ ማስረጃዎችን እናገኛለን፡፡ በሌሎች የቁርአን ክፍሎች ውስጥ “ቅዱሱ መንፈስ” (ሩሁል-ቁዱስ ሱራ 2፡85፣2፡253፣ 16፡102) ተጠቅሶ እናገኛለን፡፡ በአረብኛው ቁርአን ቅዱሱ መንፈስ ገብርኤል ስለመሆኑ በግልፅ የተነገረበት ቦታ ባይኖርም በነዚህ ክፍሎች “ቅዱሱ መንፈስ” ተብሎ የተጠራው መልአኩ ገብርኤል እንደሆነ በሙስሊሞች ይታመናል፡፡ የሆነው ሆኖ ሁለት የምንስማማባቸው ነገሮች አሉ፡፡ እነርሱም ቅዱሱ መንፈስ ከሰዎቹ ሁሉ የበላይ መሆኑንና ከሰማይ የሚወርድ ንጹህ (ቅዱስ) መንፈስ መሆኑን ነው፡፡
ኢየሱስ “ከእርሱ የኾነ መንፈስ” (ሩሁን ሚንሁ) ተብሏል፡፡ ይህም መጠርያ በእስልምና ትውፊት “የአላህ መንፈስ” ከሚለው የተቀዳ ነው፡፡ ዳዊት ኸሊፋቱላህ (የአላህ ተወካይ)፤ አብርሃም ኸሊሉላህ (የአላህ ጓደኛ ወይም ወዳጅ) ተብለዋል፡፡ ይህንን ከግንዛቤ ውስጥ ካስገባን ዘንዳ ኢየሱስ ሩሁላህ (የአላህ መንፈስ) መባሉ የግሉ መጠርያ መሆኑን መገንዘብ አያዳግተንም፡፡ በሐዲሳቱ የኢየሱስ ማንነት የተገለጸባቸውን መንገዶች ስናይ “ያ ሩሁላህ” (የአላህ መንፈስ ሆይ) እየተባለ በተደጋጋሙ ሲጠራ እንመለከታለን፡፡ ይህ አጠራር በብዙ ጽሑፎች ውስጥ በመደበኛነት ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን አንድ ጊዜ ደቀ-መዛሙርቱ በዚያ ስም ሲጠሩት ይታያል፡-
“የአላህ መንፈስ ሆይ የማያዝኑና የማይፈሩ የአላህ ወዳጆች እነማን እንደሆኑ እስኪ ንገረን፡፡”[2]
እንግዲህ ለሌሎች ነቢያት የተሰጡ ስያሜዎችን ስንመረምር ሁሉም ስያሜዎች ማንኛውም መልእክተኛ ሊሰየምባቸው የሚችላቸው ናቸው፡፡ በተለይም ለሙሐመድ የተሰጠው ስያሜ “ረሱል አላህ” (የአላህ መልእክተኛ) ለማኛውም ነቢይ የሚሰጥ ስያሜ ነው፡፡ ይህ ስያሜ (ረሱል አላህ) ለየት የሚያደርገው ምንም ነገር የለም፡፡ በሱራ 4፡171 ላይ ኢየሱስም እንደርሱ ተብሏል፡፡ ሆኖም በዚሁ አንቀጽ ላይ ነው ኢየሱስ “ከእርሱ የሆነው መንፈስ” የሚል የተለየና ለማንም ያልተሰጠ ስያሜን አግኝቷል፡፡ ይህም መለኮታዊ ማንነትን አመልካች ነው፡፡ አንድ ክርስቲያን ሊቅ ይህንን በጥሩ ሁኔታ አስቀምጦታል፡-
ለሌሎች ነቢየት የተሰጡ ስያሜዎች ለምሳሌ “የአላህ ወዳጅ፣ የአላህ ነቢይ፣ ለአላህ የተመረጠ” የሚሉ ስሞች እንደ እኛው ደካማ ለሆኑ ለሌሎች ሰዎች መዋል የሚችሉ አጠራሮች ናቸው፡፡ ነገር ግን “የአላህ መንፈስ” የሚለው የሙስሊሞች አጠራር ግልጽ በሆነ ሁኔታ ኢየሱስ እጅግ ከፍ ያለና የከበረ ማንነት ያለው መሆኑን ያሳያል፤ ከሌሎች ነቢያት የላቀ መሆኑንም ከጥርጣሬ በጸዳ ሁኔታ ያረጋግጣል፡፡ እንዲህ ዓይነት አካል የእግዚአብሔር ልጅ ተብሎ ቢጠራ ስህተት አይሆንም፡፡ ሙስሊም ወገኖቻችን ራሳቸው “የእግዚአብሔር ልጅ” ከሚለው የማይተናነስ ስም ሰጥተውት ሲያበቁ ሁለተኛውን መጠርያ ለምን እንደሚቃወሙ አናውቅም፡፡[3]
ጸሐፊው ስያሜው የተለየ እንደሆነ ከሚያምኑ ሙስሊም ሊቃውንት መካከል ኢማም ራዚንና በይዳዊን ይጠቅሳል፡-
“ዕውቅ ሙስሊም ጸሐፊያን “የአላህ መንፈስ” የሚለው መጠርያ ለሌላ ነቢይ በማይውልበት ሁኔታ ልዩ የሆነ መልእክት ያዘለ መሆኑን በግልጽ ይቀበላሉ፡፡”[4]
በሱራ 4፡171 ላይ ለኢየሱስ የተሰጠው ሩሁን ሚንሁ የሚለው ስያሜ በተመሳሳይ አወቃቀር በሱራ 58፡22 ላይ አላህ አማኞችን “ከእርሱ በኾነ መንፈስ” እንዳበረታቸው በተነገረበት አውድ ጥቅም ላይ ውሎ መገኘቱ ትኩረትን የሚስብ ነው፡፡ ዩሱፍ አሊ የተባለ ሙስሊም ተርጓሚ ከላይ ስለተጠቀሰው ክፍል እንዲህ በማለት ጽፏል፡-
እዚህ ጋር መልካም እና ጻድቃን የሆኑ ሰዎችን ሁሉ አምላክ በመንፈሱ አማካኝነት እንደሚያበረታቸው እንገነዘባለን፡፡ እዚህ ጥቅስ ውስጥ ጠንካራው ሐረግ “ከእርሱ የሆነ መንፈስ” የሚለው ነው፡፡ ማንም ሰው ልቡን በእምነትና በንጽሕና ለአምላክ ሲያቀርብ አምላክ ይቀበለዋል፡፡ በአማኙም ልብ እምነቱን ቅርጽ ያስይዝለታል፤ የአምላክን ማንነትና ባሕርይ ከምንገልጽባቸው ሰውኛ ቋንቋ ውጪ አጥጋቢ በሆነ በምንም መንገድ ልንገልጸው በማንችለው በመለኮታዊ መንፈስ ያጠነክረዋል፡፡[5]
ይህ ትርጓሜ ሩሁን ሚንሁ በማንነቱ ያልተፈጠረና ዘላለማዊ የሕያው እግዚአብሔር የራሱ መንፈስ መሆኑን በውስጠ አዋቂነት የሚገልፅ ትልቅ አንድምታ ያለው ትርጓሜ ነው፡፡ ዩሱፍ አሊ ይህ “መለኮታዊ መንፈስ” ልክ እንደ ራሱ እንደ አምላክ ልንረዳው የማንችለው ነገር ነው ይለናል፡፡ በማያሻማ መልኩም ጽፏል፡፡ እንደሱ እምነት የአምላክ መንፈስ ከመለኮቱ ዓለም እንጂ ከፍጡራኑ መደዳ አይደለም፡፡ በዚህ አተረጓጎም ክርስቲያኖች ስለ መንፈስ ቅዱስ ከሚያምኑት ጋር ይመሳሰላል፡፡
እንግዲህ የዩሱፍ አሊንም ሆነ የሌሎችን የሱራ 58፡22ን ትርጓሜ ከተረዳንና ያንኑ አተረጓጎም በሱራ 4፡171 ላይ ለኢየሱስ በተሰጠው ስያሜ ላይ ተግባራዊ ካደረግን ኢየሱስ “መለኮታዊ መንፈስ” እና የአምላክን ማንነትና ባሕርይ ከምንገልጽባቸው ሰውኛ ቋንቋ ውጪ አጥጋቢ በሆነ በምንም መንገድ ልንገልጸው የማንችለው መለኮት ነው ወደሚለው ድምዳሜ እንደርሳለን፡፡ ስለዚህ እርሱ በማንነቱ አምላክ ነው ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ዩሱፍ አሊ ሩሁን ሚንሁ የአምላክን ባሕርይና ማንነት የሚጋራ መለኮታዊ መንፈስ መሆኑን በመመስከሩና ይህ አጠራር በሱራ 4፡171 ላይ ለኢየሱስ በመዋሉ ነው፡፡ ልክ እንደ “አል-መሲሕ” እና “ካሊማቱላህ” ይህም ስያሜ ለኛ ለክርስቲያኖች ትልቅ አንድምታ ያለው ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ የመሆኑ ጠቋሚ ስያሜ ነው፡፡ ይህም ዘይቤአዊ አጠራር ሳይሆን እርሱ በማንነቱ ከዘላለም ጀምሮ ሕያው ስለሆነ ነው፡፡ ዩሱፍ አሊ ይህንን ላለመቀበል የነበረው ብቸኛ አማራጭ በሱራ 58፡22 ላይ የጻፈውን በሱራ 4፡171 ላይ ከተጻፈው ጋር በሚጋጭ መንገድ መተርጎም ነው፡፡ (ስለ ሱራ 4፡171 ሲጽፍ የኢየሱስን መለኮትነት፣ ልጅነትና ከአባቱ ጋር ያለውን አንድነት ይክዳል፡፡) ይህም ትርጓሜውን ወጥነት የሌለውና ግብታዊ በማድረግ ለእውነት ታማኝነት እንደሌለው ግልፅ ያደርጋል፡፡
ልክ እንደሁለቱ ስያሜዎች ሁሉ ይህም ስም ለኢየሱስ በብቸኝነት የተሰጠው ስም ነው፡፡ ይህ ለምን እንደሆነና ትርጉሙ ምን እንደሆነ ቁርአን እንደተለመደው የረባ ማብራርያ አይሰጠንም፡፡ የሆነው ሆኖ ከዚህኛውም ስያሜ የምንረዳው ኢየሱስ እንደሌሎቹ ነቢይ ብቻ ሳይሆን ከነቢያት ከፍ ያለና ልዩ ቦታ ያለው መሆኑን ነው፡፡
ሦስቱ የኢየሱስ ቁርአናዊ ስሞች (አል-መሲሕ፣ ካሊማቱላህ እና ሩሁላህ) ከእስልምና ይልቅ ከክርስትና እምነት ጋር የሚስማሙ ናቸው፡፡ ለኛ ለክርስቲያኖችም ወንጌልን ለመመስከር ጥሩ የጅማሬ ነጥቦች ይሆኑናል፡፡
የመነሻ ሐሳብ The Uniqueness and Titles of Jesus in Islam
[1] Frieling, Christianity and Islam, p. 71
[2] Robson, Christ in Islam, p. 86
[3] Goldsack, Christ in Islam, p. 21
[4] Goldsack, Christ in Islam, p. 21
[5] Yusuf Ali, The Holy Qur’an, p. 1518
ከሊመቱላህ – የኢየሱስን አምላክነት የሚያረጋግጥ ስያሜ
መሲሁ ኢየሱስ