“እኔን ያየ አብን አይቷል” – ለሰባልዮሳውያን ምላሽ

“እኔን ያየ አብን አይቷል”

ለሰባልዮሳውያን ምላሽ

በአማን እንዳለ


የሰባልዮስ አስተምህሮ ተቀጽላ የሆነው “የኢየሱስ ብቻ” (Only Jesus) መምህራን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “እኔ አብ ነኝ”  ያለበትን ቦታ እንዲያሳዩን ስንጠይቃቸው ፈጠን በማለት የዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ይገቡና አስራ አራተኛውን ምዕራፍ ቁጥር ዘጠኝ ይጠቅሱልናል።  በእርግጥ እንደዚህ ያለ ጥያቄ የምንጠይቅበት ምክንያት የቃል በቃል ፍለጋ የክርስትና አስተምህሮ መሠረት ስለሆነ ሳይሆን የእነርሱኑ የሙግት አቀራረብ ወደ እነርሱ አዙረን እንጠይቅ በሚል ነው። አስተምህሯችንን የምንመሠርተው ቅዱሳት መጽሐፍት ስልታዊ በሆነ መንገድ ተጠንተው በሚሰጡን አጠቃላይ ድምዳሜ ላይም ጭምር እንጂ የቃል በቃል ንባብ ላይ ብቻ አይደለም። ነገር ግን “የኢየሱስ ብቻ” አቀንቃኞች ቃል በቃል “ሥላሴ”  ወይም “እግዚአብሔር በመለኮት አንድ በአካል ሦስት” የሚል ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ባለመኖሩ የሥላሴ ትምህርት ትክክል አይደለም የሚል መከራከሪያ ስለሚያቀርቡ በተመሳሳይ መመዘኛ አስተምህሯቸውን ሁሉ ቃል በቃል ከመጽሐፍ ቅዱስ እንዲያመጡ መጠየቅ አግባብ ይሆናል። ለምሳሌ “ኢየሱስ አብ ነው” የሚል አንድም የቃል በቃል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ማቅረብ ስለማይችሉ በገዛ መመዘኛቸው መሠረት ኢየሱስ አብ እንደ ሆነ ማመናቸው ስህተት ይሆናል። በተጨማሪም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “መጽሐፍ ቅዱስ” የሚል ቃል ስለማይገኝ ሙሉ ለሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ማመን የለባቸውም ማለት ነው፤ ይህ ካልሆነ ግን ሚዛናቸው አባይና ሚዛን ይሆንባቸዋል።

ለመሆኑ “እኔን ያየ አብን አይቷል” እና “እኔን ብታውቁኝ ኖሮ አባቴንም ባወቃችሁ ነበር” የሚለው ንግግር አንድ ማንነት ስላለው አካል የሚናገር ነውን? በፍጹም! ቁጥር 7 እና 9 ላይ ያለውን ንግግር ስለ አንድ ማንነት አድርገን የምንረዳ ከሆነ የምዕራፉን አውድና አጠቃላዩን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ያላገናዘበ አረዳድ ስለሚሆን ለከፍተኛ ስህተት ይዳርገናል። እስኪ የክፍሉን አውድ ጠብቀን የንግግሩን ፍቺ እንመልከት።

ጌታ ኢየሱስ በዚህ ምዕራፍ ማለትም ዮሐንስ ምዕራፍ 14 ንግግሩን ሲጀምር “ልባችሁ አይጨነቅ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፤ በእኔም ደግሞ እመኑ” በማለት ነው። እንግዲህ “የኢየሱስ ብቻ” አስተምህሮን እየተካን ምንባቡን ከተመለከትን ይህንን የሚናገረው ጌታ ኢየሱስ ራሱ አብም ወልድም በመሆኑ “በእግዚአብሔር እመኑ” ብሎ ሲናገር ይህንን የሚናገረው ኢየሱስ ይህንን እያለ ያለው ስለ ራሱ ነው ማለት ነው። ስለዚህ በነዚህ ወገኖች አረዳድ መሠረት አብና ወልድ የሆነው ኢየሱስ ምን አለ? “በእግዚአብሔር እመኑ” ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ “በእኔም ደግሞ እመኑ” በማለት ተናገረ። ይህንን ሲል በእግዚአብሔር እንድናምን፤ እንደ ገና ደግሞ በአብና በወልድም እንድናምን እየተናገረ ነበር ማለት ነው። ለመሆኑ በአንድ አምላክ ብቻ ማመን የሚገባ ሆኖ ሳለ ጌታ ኢየሱስ “በእግዚአብሔር እመኑ” እንዲሁም ደግሞ “በአብና በወልድ እመኑ” ማለቱ ከራሳቸው አስተምህሮ ጋር አይጣረስምን? ኢየሱስ “በእግዚአብሔር እመኑ” ሲል በውስጡ በሚኖረው መንፈሱ “በእኔም ደግሞ እመኑ” ሲል በሥጋው ማለቱ እንደ ሆነ የሚነግሩን ከሆነ ደግሞ ኢየሱስ ስንት ማንነት አለው? የሚል ጥያቄ እናቀርባለን። “በአብ እመኑ” ካለ በኋላ “በሥጋዬም ደግሞ እመኑ” ያለ በማስመሰል መናገር ትርጉም ይሰጣልን? ሥጋው ከአብ ተነጥሎ “እኔነት” ኖሮት ይታመናልን? እንዲህ ያለ ትርጓሜ ህሊናን ይጎረብጣል። ነገር ግን ይህንን የመሰለ ትርጉም አልባ ውጥንቅጥ ውስጥ ሳንገባ ጥቅሱን በተጻፈበት መንገድ ካነበብን ተናጋሪው ወልድ መሆኑ ግልጽ ስለሆነ ጌታ ኢየሱስ ራሱን ከአብ ለይቶ “በእኔም ደግሞ እመኑ” ብሎ ሲናገር ልባቸው በኅዘን ውስጥ የነበረው ደቀመዛሙርቱ እንዳይጨነቁና በአብና በወልድ እንዲያምኑ እየነገራቸው ነው። ቀጥሎ ጌታ ኢየሱስ “ሄጄ ስፍራ ካዘጋጀሁላችሁ በኋላ…” በማለት ከደቀመዛሙርቱ ጋር የሚኖረው የምድር ቆይታ እያበቃ እንደሆነ ያመለክታቸዋል። ነገር ግን እንደሚሄድ ብቻ ሳይሆን ወደ የት እንደሚሄድና ለምን እንደሚሄድም ጭምር ግልጽ አድርጓል፦ “በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ ይህ ባይሆንማ ኖሮ እነግራችሁ ነበር፤ የምሄደውም ስፍራ ላዘጋጅላችሁ ነው።”

አብ ባለበት በዚያ ስፍራ ሊያዘጋጅላቸው ይሄዳል፤ ስለዚህ ኢየሱስ ወደ የት ነው የሚሄደው? ለሚለው ጥያቄ ምላሹ ወደ አባቱ የሚል ነው። አሁንም መለስ ብለን “የኢየሱስ ብቻ” አስተማሪዎችን ትምህርት በዚህ ምንባብ እንቃኝ። ኢየሱስ እራሱ አብም ወልድም ከሆነ ኢየሱስ በዚህ ቦታ ወደ አብ እሄዳለሁ ሲል ምን ማለቱ ነው? ጌታ ኢየሱስ ግልጽ እንዳደረገው ወደ አባቱ ይሄዳል። ነገር ግን አባቱ እርሱ ራሱ ነው ከተባለ ወደ ራሱ ሄደ ማለት ስለሚሆን ትርጉም አልባ ንግግር ሊሆን ነው። “እኔ ወደ ምሄድበትም ስፍራ የሚያደርሰውን መንገድ ታውቃላችሁ” በማለት ጌታችን ሲናገር ፊልጶስ መልሶ “ወዴት እንደምትሄድ አናውቅም ታዲያ መንገዱን እንዴት ማወቅ እንችላለን?” ብሎ ሲጠይቅ እንመለከታለን። ከዚህ በኋላ የምናገኘው የጌታ ኢየሱስና ከደቀመዛሙርቱ አንዱ የነበረው የፊልጶስን ጥያቄና መልስ ነው። መጀመሪያ የጠየቀው ጥያቄ “ወዴት እንደምትሄድ አናውቅምና መንገዱን እንዴት ማወቅ እንችላለን?” የሚል ሲሆን ጌታ ኢየሱስ መንገዱ እርሱ ራሱ እንደሆነ በእርሱ በኩል ወይም በዚህ መንገድ በኩል ወደ አብ እንደምንመጣ ይናገራል። ከላይ ጌታችን የተናገረውን ልብ ብለን እንደገና ማየት አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም ይህ ንግግር የአንድ ጊዜ ንግግር ስለሆነ በአንድ አውድ ውስጥ ሆነን መረዳት ይገባናል። ኢየሱስ ወደ አብ ይሄዳል በዚያም ስፍራ ያዘጋጃል፤ ስለዚህ እርሱ ወዳዘጋጀው ስፍራ የምንሄደው በማንበኩል ነው ከተባለ ምላሹ በኢየሱስ በኩል ነው የሚል ነው። ይህንን ጥያቄ ነው ፊልጶስም የጠየቀው፤ ኢየሱስም በተለየ መንገድ ይህንኑ ነው መልሶ እያስተማረ የሚገኘው። “እኔን ብታውቁኝ ኖሮ አባቴንም ባወቃችሁ ነበር” በማለቱ ከላይ ከቁጥር አንድ ጀምሮ “በእኔም እመኑ” የሚለው እርሱን ማወቅ አብን ማወቅ እንደሆነ በመናገር እርሱ ማለትም የእግዚአብሔር ልጅ አብን ሙሉ ለሙሉ የሚገልጥ መሆኑን አጽንዖት በመስጠት ያስተምራል። ስለዚህ ቀጥሎ “ታውቁታላችሁና አይታችሁትማል” የሚለው እርሱ ራሱ አብ ስለሆነ ሳይሆን ስለ አብ መታወቅ የሚገባው ነገር ሁሉ በእርሱ በመካከላቸው በመኖር እንደታወቀ መናገሩ ነው። ጌታችን በዚህ ስፍራ በፍጹም እኔ ራሱ አብ ነኝ እያለ አይደለም። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ማየት” እና “ማወቅ” የሚሉ አነጋገሮችን ከዕወቀት ጋር አገናኝቶ መናገሩ በዚህ ክፍል ለአንባቢ ግልጽ ነው።

“አብን አሳየንና ይበቃናል” የሚለው የፊልጶስ ንግግርና “ይህን ያህል ጊዜ ከአንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን?” የሚለው የኢየሱስ ንግግር “ማየት” የሚለው ቃል በክፍሉ ውስጥ “ማወቅ” ከሚለው ጋር በተለዋዋጭ እያገለገለ እንደሆነ ግልጽ ያደርግልናል። ኢየሱስ ይህንን ተናግሮ “እኔን ያየ አብን አይቷል” አለ እንጂ “እኔ አብ ነኝ” አላለም። በዚህ ቦታ ላይ ያለው በመጀመሪያ መደብ ነጠላ ቁጥር እራሱን “እኔ” የሚለውን ማንነት በደንብ ከላይ አይተናል። ይህ በተጨማሪ የፊሊጶስና የኢየሱስ ቃለ-ምልልስ ኢየሱስ አብ ነው ከሚለው ጋር ልዩነቱን ግልጽ ያደርግልናል። ነገር ግን ከዚህ በተጻራሪ ኢየሱስ “እኔን ያየ አብን አይቷል” ብሎ መናገሩ ኢየሱስ ውስጥ አብ በመኖሩና ኢየሱስ ሲናገርም ሆነ በአካል/በሥጋ ሲታይ አብ ታይቷል የምንል ከሆነ ጌታ ኢየሱስ በዚሁ በዮሐንስ ወንጌል ከራሱ ጋር የሚጣረስ ንግግር አድርጓል ማለት ነው፤ እነሆ ማስረጃ፦

ዮሐ 5:37 “የላከኝ አብ ራሱ ስለ እኔ መስክሯል፤ እናንተም ከቶ ድምፁን አልሰማችሁም፤ መልኩንም አላያችሁም፤”

የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 14 ላይ ተመሥርተን ጌታ ኢየሱስ ሲናገር አብ ተናግሯል የምንል ከሆነ እንዲሁም ጌታ ኢየሱስን ሰዎች ሲያዩት አብን በሥጋ አይተዋል የሚል አረዳድ የሚኖረን ከሆነ ጌታ ኢየሱስ ታዲያ በዚህ ስፍራ አብን አላያችሁትም ድምጹንም አልሰማችሁትም እንዴት ይላል? ይህን የሚናገረው እራሱ አብ ከሆነና በመካከላቸው ተገልጦ ያለው አብ ከሆነ “አላያችሁትም አልሰማችሁትም” የሚለው የጌታ ንግግር ትርጉሙ ምንድነው?

መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ስፍራ ያነሳውን ሐሳብ በሌላ ስፍራ አያፈርስም፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ቃል ነውና። ስለዚህ የፊሊጶስና የኢየሱስ ንግግር ኢየሱስ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነና በእርሱ መታመን እንዳለብን በተጨማሪም እግዚአብሔር አብን በሙላት የተረከልን ወይም ፈቃዱን በሙላት እንድናውቅ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከ መሆኑን የሚናገር እንጂ ኢየሱስ ራሱ የኢየሱስ አባት የሆነው እግዚአብሔር አብ ነው ማለት አይደለም። የእግዚአብሔርን ልጅ መታዘዝ አባቱን መታዘዝ፤ የወልድን ፈቃድ ማወቅ የአብን ፈቃድ ማወቅ ስለሆነ ነው ጌታ ኢየሱስ “እኔን ያየ አብን አይቷል” በማለት የተናገረው እንጂ ኢየሱስ እኔ አብ ነኝ ማለቱ አይደለም። እርሱ በባሕርዩ ከአብ ጋር የተካከለና በሙላት አባቱን የሚገልጥ በመሆኑ እርሱን ያየ ሰው አብን ማየት አያስፈልገውም፤ እርሱ የአባቱን ባሕርይ በትክክል የሚገልጥ ልጁ ነውና፦

“እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ በተለያየ ጊዜና በልዩ ልዩ መንገድ በነቢያት በኩል ለአባቶቻችን ተናግሮ፣ በዚህ መጨረሻ ዘመን ግን ሁሉን ወራሽ ባደረገውና ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ ለእኛ ተናገረን። እርሱ የእግዚአብሔር ክብር ነጸብራቅና የባሕርዩ ትክክለኛ ምሳሌ ሆኖ፣ በኀያል ቃሉ ሁሉን ደግፎ ይዟል። የኀጢአት መንጻት ካስገኘ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ።” (ዕብራውያን 1፡1-3)


መልስ ለሰባልዮሳውያን