አገልጋይ ሊሆን የመጣው ንጉሥ

አገልጋይ ሊሆን የመጣው ንጉሥ

በወንድም ሚናስ


ብዙ ሙስሊም ወገኖቻችን የክርስቶስን አምላክነት ለመካድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የእግዚአብሔር “አገልጋይ” ተብሎ በተገለጸባቸው  ጥቅሶች ላይ ትኩረት ሲያደርጉ ይስተዋላል። ለዚኽም የሚከተሉት ምንባባት በዋነኝነት ተጠቃሽ ናቸው፦

ሐዋርያት 3፥13፣ 26 “የአብርሃምና የይስሐቅ የያዕቆብም አምላክ፥ የአባቶቻችን አምላክ፥ እናንተ አሳልፋችሁ የሰጣችሁትንና ሊፈታው ቈርጦ ሳለ በጲላጦስ ፊት የካዳችሁትን ብላቴናውን (παῖς) ኢየሱስን አከበረው። […] ለእናንተ አስቀድሞ እግዚአብሔር ብላቴናውን (παῖς) አስነሥቶ፥ እያንዳንዳችሁን ከክፋታችሁ እየመለሰ ይባርካችሁ ዘንድ፥ ሰደደው።”

ሐዋርያት 4፥27፣ 27 “በቀባኸው በቅዱሱ ብላቴናህ (παῖς) በኢየሱስ ላይ ሄሮድስና ጴንጤናዊው ጲላጦስ ከአሕዛብና ከእስራኤል ሕዝብ ጋር፥ እጅህና አሳብህ እንዲሆን አስቀድመው የወሰኑትን ሁሉ ሊፈጽሙ፥ በዚች ከተማ በእውነት ተሰበሰቡ። … አሁንም፥ ጌታ ሆይ፥ ወደ ዛቻቸው ተመልከት፤ ለመፈወስም እጅህን ስትዘረጋ በቅዱስ ብላቴናህም (παῖς) በኢየሱስ ስም ምልክትና ድንቅ ሲደረግ፥ ባሪያዎችህ በፍጹም ግልጥነት ቃልህን እንዲናገሩ ስጣቸው።”

የእንግሊዝኛ ትርጉሞች παῖς የሚለውን ቃል በተመለከተ ተመሳሳይ ትርጉም የላቸውም። ገሚሶቹ “ልጅ” የሚለውን ትርጉም የተጠቀሙ ሲሆን ገሚሶቹ ደግሞ “አገልጋይ” የሚለውን ትርጉም ይመርጣሉ። በዚኽ መጣጥፍ ከ RSV እንዲሁም ሌሎች “አገልጋይ” ከሚሉ ቅጆች  ጋር ብንስማማ እንኳ ከላይ ባየናቸው ጥቅሶች መሠረት የጌታችን መለኮትነት ውድቅ የማይሆንበትን ምክንያት እናሳያለን፤ ኢየሱስ የእግዚአብሔር “አገልጋይ ” መባሉ በሥጋ የተገለጠ አምላክ ስለመሆኑ ማረጋገጫ የሚሰጡ ማስረጃዎችንም እናቀርባለን።

1ኛ. παῖς“ፓይስ” የሚለው  የጽርዕ ቃል “አገልጋይ” የሚል ትርጉም ብቻ የለውም።

RSV የተሰኘውን የእንግሊዝኛ ትርጉምን ጨምሮ አንዳንድ ቅጆች “አገልጋይ” ሲሉ የተረጎሙት παῖς “ፓይስ” የሚለው የጽርዕ ቅጽል ሲሆን፣ ሁል ጊዜ “አገልጋይ” የሚለውን ብቻ አይወክልም። ይኽ ቃል ከልጅነት ጋር በተያያዘ ጥቅም ላይ ከዋለባቸው በርካታ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማሳያዎች መካከል አንዱን እንመልከት፦

ዮሐንስ 4፥43-53 “ኢየሱስም ውሃውን የወይን ጠጅ ወዳደ ረገበት፣ በገሊላ ወደምትገኘው ወደ ቃና ከተማ ዳግመኛ መጣ፤ በቅፍርናሆምም ልጁ (ὁ υἱὸς ሆ ሁዮስ)  የታመመበት አንድ የቤተ መንግሥት ሹም ነበረ፤ ይህም ሰው ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ መምጣቱን በሰማ ጊዜ፣ ወደ እርሱ ሄደና በሞት አፋፍ ላይ የነበረውን ልጁን (αὐτοῦ τὸν υἱόν አውቱ ቶን ሁዮን) መጥቶ እንዲፈውስለት ለመነው። ኢየሱስም፣ “መቼውንም እናንተ ምልክቶችንና ድንቅ ነገሮችን ካላያችሁ አታምኑም” አለው። ሹሙም፣ “ጌታዬ፤ ልጄ (τὸ παιδίον μου ቶ ፓይዲዮን ሞው)  ከመሞቱ በፊት እባክህ ድረስልኝ” አለው። ኢየሱስም፣ “ልጅህ (ὁ υἱός σου ሆ ሁዮስ ሶው) በሕይወት ይኖራልና ሂድ” አለው። ሰውየውም ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አምኖ ሄደ፤  በመንገድ ላይ እንዳለም፣ አገልጋዮቹ አግኝተውት ልጁ (ὁ παῖς αὐτοῦ ሆ ፓይስ አውቶው) በሕይወት መኖሩን ነገሩት። እርሱም ልጁ በስንት ሰዓት እንደ ተሻለው ሲጠይቃቸው፣ “ትኵሳቱ የለቀቀው ትናንት በሰባት ሰዓት ላይ ነው” አሉት። አባትዮውም ሰዓቱ ኢየሱስ፣ “ልጅህ (Ὁ υἱός σου ሆ ሁዮስ ሶው)  በሕይወት ይኖራል” ያለበት ሰዓት መሆኑን ተገነዘበ፤ እርሱና ቤተ ሰቡም ሁሉ አመኑ።”

ልብ ይበሉ፤ ከላይ ባነበብነው ትረካ ውስጥ የባለስልጣኑ ሥጋዊ ልጅ υἱός “ሁዮስ” እና παῖς “ፓይስ” የሚሉት የጽርዕ ቅጽሎች፣ በተለዋዋጭነት ወክለውት ሲጠራበት እናነባለን፤ ስለዚህም “ፓይስ”  የሚለው የጽርዕ ቃል አገልጋይ የሚል ትርጉም ብቻ አለው የሚለው የሙስሊም ወገኖቻችን ሙግት ከጅምሩም ውድቅ ነው። ቃሉ ለአባቱ የመታዘዝ ደረጃና ሚና ያለውን ልጅ የሚገልፅ ጥምር ትርጉም ያለው በመሆኑ “ብላቴና” የሚለው የአማርኛ ቃል ይበልጥ ይቀርበዋል።

2ኛ. መሲሑ አገልጋይ ቢባል እንኳን ከመለኮታዊ ክብሩ አያጎድለውም። ለምሳሌ፣ ነቢዩ ኢሳይያስ አገልጋዩ መሲሕ፣ ነፍሱን ስለ ኃጢአት መሥዋዕት አድርጎ ካቀረበ በኋላ ከፍ ከፍ እንደሚል እና እንደሚከብር ተናግሯል፦

“እነሆ፤ ባሪያዬ የሚያከናውነው በማስተዋል ነው፤ ገናና ይሆናል፤ ከፍ ከፍ ይላል፤ እጅግ ይከብራልም (ὑψωθήσεται καὶ δοξασθήσεται ሁፕሶቴሴታይ ካይ ዶክሳስቴሴታይ)።”
  — ኢሳይያስ 52፥13 (LXX)

ከላይ ያለው ምንባብ በእጅጉ የሚያስደንቀው ነቢዩ የአገልጋዩን ክብር ለመግለጽ የተጠቀመበት አገላለጽ፣ ያህዌ በፍጥረታት ኹሉ ላይ ከፍ ያለ ቦታውን በገለጸበት አግባብ መሆኑን ስናስተውል ነው፦

“እግዚአብሔር በአርያም ተቀምጦአልና ከፍ  አለ (ὑψηλῷ ሁፕሴሎ)፤ ጽዮንን በጽድቅና በፍትሕ ይሞላታል። … እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “አሁን እነሣለሁ፤ አሁን ከፍ ከፍ እላለሁ (δοξασθήσομαι ዶክሳስቴሶማይ)፤ አሁን እከብራለሁ (ὑψωθήσομαι ሁፕሶቴሶማይ)።”

“ንጉሥ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን ከፍ ባለ (ὑψηλοῦ ሁፕሴሎው)  ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁት፤ ክብሩም (τῆς δόξης αὐτοῦ ቴስ ዶክሴስ አውቶው) መቅደሱን ሞልቶት ነበር።”
  — ኢሳይያስ 6፥1

የአገልጋዩ መሲሕ ልዕለ ኃያልነትና ከፍታ፣ ይበልጡኑ ልዩ የሚያደርገው ደግሞ ነብየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ፣ ያህዌ ብቻ ከፍ ከፍ እንደሚልና ሌሎች ፍጥረታት ሁሉ በፊቱ የተዋረዱ መሆናቸውን በግልፅ በማወጁም ጭምር ነው፦

“የሰው እብሪት ይዋረዳል፤ የሰውም ኵራት ይወድቃል፤ በዚያን ቀን ጌታ ብቻ (μόνος) ከፍ ከፍ ይላል (ὑψωθήσεται)፤”
  — ኢሳይያስ 2፥17 (አዲሱ መ.ት)

ታዲያ ሐዋርያው ​​ቅዱስ ጴጥሮስ መሲሑ ኢየሱስን  ሉዓላዊ ጌታ ሆኖ በእግዚአብሔር ቀኝ በሰማያዊው ዙፋን ላይ ተቀምጦ ከፍ ከፍ  ማለቱን ለሰዎች በሚያውጅበት ወቅት፣ ኢሳይያስ የተናገራቸውን ተመሳሳይ ቃላት ይጠቀማል፦

ሐዋርያት 2፥32-33 “ይህን ኢየሱስ፣ እግዚአብሔር ከሞት አስነሣው፤ እኛም ሁላችን ለዚህ ነገር ምስክሮች ነን። ስለዚህ በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ (ὑψωθείς) ካለ በኋላ፣ የመንፈስ ቅዱስን ተስፋ ከአብ ተቀብሎ አሁን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው።”

መሲሑ የሕይወት መገኛ፣  ቅዱስና ጻድቅ ሆኖ ሳለ አይሁድ ቢገድሉትም፣ እግዚአብሔር ግን እንዳከበረውም ተናግሯል፦

ሐዋርያት 3፥14-15 “የአባቶቻችን አምላክ፣ የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ ብላቴናውን ኢየሱስን አከበረው (ἐδόξασεν) ፤ እናንተ ግን እንዲሞት አሳልፋችሁ ሰጣችሁት፤ ጲላጦስ ሊፈታው ቢፈልግም እናንተ በእርሱ ፊት ካዳችሁት፤ ቅዱሱንና ጻድቁን ክዳችሁ ነፍሰ ገዳዩ እንዲፈታላችሁ ለመናችሁ፤ የሕይወት መገኛ የሆነውን ገደላችሁት፤ እግዚአብሔር ግን ከሙታን አስነሣው፤ እኛም ለዚህ ምስክሮች ነን።”

ይህ የሚያሳየው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  ለቅዱስ ጴጥሮስ የአብ አገልጋይ ብቻ ሳይሆን ከሙታን ተለይቶ የተነሳ ጌታ አምላክም  መሆኑን ነው። ሰው ሆኖ በሥጋ ስለተገለጠ በምድር አገልጋይ ሆኖ ቢመላለስም ለአምላክ ብቻ ተገቢ በሆነ ክብር የከበረ መለኮት ነው!

መሲሁ ኢየሱስ