ታላቁ አምላክና የግራንቪል ሻርፕ ሕግ
የኡስታዙ ቅጥፈት ሲጋለጥ
የሀገራችን ሙስሊም ሰባኪያን የማያውቁትንና ያላጠኑትን የአዲስ ኪዳን የመጀመርያ ቋንቋ እየጠቀሱ ሲዘላብዱ ከማየት በላይ የሚያሳቅቅ ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ የዚህ ተግባር ቀበኞች ከሆኑት መካከል ሰለምቴ ነኝ የሚል አንድ አብዱል ይገኛል፡፡ ይህ ሰው ምንም ዓይነት የግሪክ ቋንቋ ዕውቀት ሳይኖረውና የሚጠቅሳቸውን ምንጮች አጣርቶ ሳይረዳ ሁሉን እንደጨረሰ ሊቅ ሲጽፍና ሲናገር ይታያል፡፡ በዚህ ምላሽ የግራንቪል ሻርፕ የግሪክ ቋንቋ ሕግን በመጥቀስ የፈፀመውን ቅጥፈት የምንመለከት ይሆናል፡፡
የባርያ ንግድ እንዲወገድ በተደረገው ትግል ውስጥ በነበረው ጉልህ ሚና የሚታወቀው ግራንቪል ሻርፕ ከሁለት ክፍለ ዘመናት በፊት የኖረ ሲሆን (1735–1813 ዓ.ም.) የግሪክ ቋንቋ ሊቅ እንዲሁም የብዙ ተሰጥዖዎች ባለቤትም ነበር፡፡ ይህ ሊቅ ቋንቋውን በጥልቀት በማጥናት የተወሰነ መስተኣምር አገባብ በዐረፍተ ነገሮች ትርጉም ላይ የሚፈጥራቸውን ልዩነቶች በመለየት ይታወቃል፡፡ ስድስት ነጥቦችን የያዘው “የግራንቪል ሻርፕ ሕግ” በመባል የሚታወቀው የሰዋሰው አገባብ ጌታችን ኢየሱስ በአዲስ ኪዳን ውስጥ በቀጥታ “አምላክ” (ቴዎስ) ተብሎ የተጠራባቸው ዋና ዋና ጥቅሶች አምላክነቱን ሊያሳዩ በሚችሉ መንገዶች ብቻ የሚተረጎሙ መሆናቸውን በማረጋገጥ ሌሎች ትርጓሜዎችን ውድቅ የሚያደርግ የግሪክ ቋንቋ ሕግ ነው፡፡ ሻርፕ ራሱ በክርስቶስ አምላክነት አጥብቆ የሚያምን ፅኑ ክርስቲያን የነበረ ሲሆን ጥቅሶቹን ከተሳሳቱ ትርጓሜዎች ለመከላከል ርቱዕ ሙግቶችን አቅርቧል፡፡ ይህንን ሐቅ ያልተረዳው ሙስሊሙ ሰባኪ በቂ ጥናት ባለማድረጉና ያነበበውን ባለመረዳቱ ምክንያት እንዴት ራሱን ለስህተት እንደዳረገ አብረን እንቃኛለን፡፡ እንዲህ ሲል ይጀምራል፡-
አብዱል
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኛ በሆነው፡፡
መግቢያ
ጳውሎስ በገማልያ ስር ተቀምጦ ሲማር የነበረ ሰው ነው፣ በብሉይ ኪዳን ሲገለጥ የነበረው የነቢያት አምላክ ታላቁ አምላክ ያህዌህ መሆኑን ጠንቅቆ የተረዳ ሰው ነው፣ መቼም ኢየሱስን ከአንዱ አምላክ እየነጠለ ከተናገረ በኋላ ተመልሶ ያንን ታላቁ አምላክ ኢየሱስ ነው አይልም፣ ምክንያቱም እንደ ጳውሎስ አነጋገር አብ ብቻውን የሆነ አምላክ፣ ኢየሱስ ምሳሌ የሆነለት የማይታይና የማይሞት አምላክ ስለሆነ፦
1ኛ ጢሞቴዎስ 1:17 ብቻውን አምላክ ለሚሆን ለማይጠፋው ለማይታየውም ለዘመናት ንጉሥ ምስጋናና ክብር እስከ ዘላለም ድረስ ይሁን፤ አሜን።
1ኛ ጢሞቴዎስ 6:16 እርሱ ብቻ የማይሞት ነው፤ ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ይኖራል፤ አንድ ሰው እንኳ አላየውም ሊያይም አይቻለውም፤ ለእርሱ ክብርና የዘላለም ኃይል ይሁን፤ አሜን።
ቆላስይስ 1:15 እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው፤
መልስ
የአዲስ ኪዳንን የቋንቋ አጠቃቀም ስናጠና ልዩ መሆንን የሚያመለክቱ (Exclusive) ቃላት ለሦስቱም የሥሉስ አካላት በተናጠልም ሆነ አንዱን ግጻዌ መለኮት ለማመልከት ጥቅም ላይ ሊውሉ እንደሚችሉ እናስተውላለን፡፡ ሲጀመር የሥላሴ አካላት የአንዱ ብቸኛው መለኮት ሦስት አካላት እንጂ የተነጣጠሉ አማልክት ባለመሆናቸው 1ጢሞቴዎስ 1:17ን በመሳሰሉት ጥቅሶች ውስጥ አብ ብቻውን አምላክ መባሉ ዘላለማዊ ቃሉና መንፈሱን ያገለለ አይደለም፡፡ ይህንን ከዚህ ቀደም ያብራራንባቸውን ተከታዮቹን ሊንኮች በመጠቀም ማየት ይቻላል፡-
http://www.ewnetlehulu.net/am/one-mediator/
http://www.ewnetlehulu.net/am/only-true-god/
1ጢሞቴዎስ 6፡16 አውዱን ባገናዘበ ህታቴ መሠረት ለክርስቶስ የተነገረ መኾኑን ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡ በጥቅሱ አውድ ውስጥ የተዘረዘሩት ባሕርያት እርሱን የሚያመለክቱ መሆናቸውን ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች መረዳት ይቻላል (2ጢሞቴዎስ 1፡8-11፣ ራዕይ 17፡14፣ 19፡11-16፣ 1፡5 ይመልከቱ)፡፡ ሙስሊሞች ለሚያነሷቸው አብዛኞቹ ጥያቄዎች ምንጭ የሆኑትና የኢየሱስን አምላክነት የማይቀበሉት የይሖዋ ምስክሮች እንኳ ሳይቀሩ በጽሑፎቻቸው ውስጥ ይህንን አምነው መቀበላቸውን ገልጸዋል፡፡ (Aid to Bible Understanding, Watch Tower Bible and Tract Society of New York, Inc., 1971, p. 711)
ቆላስይስ 1፡15 ሙሉ አውዱ እንዲህ ይላል፡- “እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው፤ የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው፤ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል፤ እርሱም ከሁሉ በፊት ነው ሁሉም በእርሱ ተጋጥሞአል” (ቆላስይስ 1፡15-17)፡፡ በጥቅሱ መሠረት ጌታችን ኢየሱስ ሁሉን ለክብሩ የፈጠረ ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኩር የሆነ (የፍጥረት የበላይና ገዢ)፤ የፍጥረት ሁሉ ህልውና መሠረት የሆነ ፈጣሪ መሆኑን ይናገራል፡፡ የማይታይ አምላክ ምሳሌ የተባለው መለኮታዊ ባሕርያትን ሁሉ የተጎናፀፈ በሥጋ የተገለጠ ወልደ እግዚአብሔር በመሆኑ ነው፡፡
አብዱል
ነገር ግን ብዙ ክርስቲኣኖች ጳውሎስ በቲቶ 3:13 ላይ ስለ ታላቁ አምላክ የሚናገረውን ለኢየሱስ አምላክነት ከሚጠቅሳቸው ጥቅሶች መካከል ኣንዱ ነው፣ እኔ ደግሞ ቲቶ 3:13 የኢየሱስ ኣምላክነት ሳይሆን የኢየሱስን ኣምላክ ኣንዱን ኣምላክ ማለት አብን የሚያሳይ ነው ብዬ፦ ቲቶ 2:13 የተጻፈበትን ስነጽሁፍ፣ ቋንቋ፣ ሰዋሰው፣ አውድ እና የአረፍተ–ነገር አሰካክ ይዤ እሞግታለው፦
መልስ
በማስከተል እንደምንመለከተው ሙግትህ ምንም መሠረት የለውም፡፡ የጠቀስከውን ጽሑፍ እንኳ በተቃራኒው ተርጉመህ የቋንቋ ዕውቀት እጥረት እንዳለብህ አሳይተሃል፡፡ ይህንን ጽሑፍ ካነበበ በኋላ አንተን እንደ አዋቂ ቆጥሮህ ሙግቶችህን አምኖ የሚቀበል አእምሮ ያለው ሰው ከእንግዲህ አይኖርም፡፡ ቀጣዩ ምላሻችን በሐሰት የገነባኸውን የማሕበራዊ ሚድያ ዕውቅና ከስር መሠረቱ በመናድ ወደ ቦታህ እንደሚመልስህ አትጠራጠር፡፡
አብዱል
ቲቶ 2:13 የታላቁን አምላክ እና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥
τῆς δόξης τοῦ μεγάλου Θεοῦ καὶ Σωτῆρος ἡμῶν Χριστοῦ Ἰησοῦ
the glorious appearing of the great God and our Saviour Jesus Christ; King James Bible
-
- የሰዋስው ሙግት
በጣም ስመ–ጥር የሆነው የግሪክ ሰዋስው ግራንቪል ሻርፕ አንደኛው ላይ የተቀመጠው ህግ ፦ ሁለት የማእረግ ስሞች እና በሚል መስተጻምር ከተለየ፣ ከመጀመሪያው የማእረግ ስም ho(the) የሚል ጠቃሽ አመልካች መስተአምር ከተጠቀመ ፡ ሁለተኛው ላይ ካልተጠቀመ ፣ በመቀጠል አረፍተ–ነገሩ ተመሳሳይ ሙያ ከሆነ አንድን ማንነት የሚያሳይ ነው፣
ነገር ግን ሁለት የማእረግ ስሞች እና በሚል መስተጻምር ከተለየ፣ ከመጀመሪያው የማእረግ ስም ho(the) የሚል ጠቃሽ አመልካች መስተአምር ከተጠቀመ ፡ ሁለተኛው ላይ ካልተጠቀመ ፣ በመቀጠል አረፍተ–ነገሩ የተለያየ ሙያ ከሆነ ሁለትየተለያዩ ማንነቶችን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።
“If two nouns of the same case and the two nouns are connected by the word “and,” and the first noun has the article (“the”) while the second does not, both nouns are referring to the same person
“But If two nouns of the different case and the two nouns are connected by the word “and,” and the first noun has the article (“the”) while the second does not, both nouns are referring to the same person”
ለናሙና ያክል ሁለት ጥቅሶችን እንመልከት፦
መልስ
የምሑሩን ትክክለኛ ሐሳብ ሳትረዳና ሳታስረዳ የምን ወደ “ናሙና” መዝለል ነው? ከላይ በእንግሊዘኛ የጠቀስካቸውን ከየት እንዳመጣኻቸው እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ የመጀመርያው አንቀፅ ከመጀመርያው ሕግ ጋር ተቀራራቢ ቢሆንም እንግሊዘኛው የሰዋሰው ስህተት አለበት፡፡ ሁለተኛው አንቀፅ እንደ መጀመርያው ሁሉ የሰዋሰው ችግር ያለበት ከመሆኑም በላይ በሻርፕ የተነገረ ስለመሆኑ ምንጭ አልጠቀስክም፡፡ በስድስቱ ሕግጋት ውስጥ እንዲህ የሚል ነገር አልተጻፈም፡፡ የሚገርመው ነገር የዐረፍተ ነገሩ መቋጫ “both nouns are referring to the same person” (ሁለቱም ስሞች አንድ ማንነት ያሳያሉ) የሚል ቢሆንም አንተ ግን “ሁለት የተለያዩ ማንነቶችን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል” ብለህ በተቃራኒው ተርጉመሃል፡፡ እንግሊዘኛውን ሳታጣራ ስለ ግሪኩ ማውራትህ አስቂኝ ነው፡፡ እንዳንተ ባልተጣራ ምንጭ፣ በተወናገረ ሰዋሰውና በተቃራኒ ትርጉም ሳይሆን በጠራ አነጋገር ሕጉን ቃል በቃል ከግሪክ መማርያ መጽሐፍ ላይ እጠቅስልሃለሁ፡-
“When the copulative KAI connects two nouns of the same case, if the article HO or any of its cases precedes the first of the said nouns or participles, and is not repeated before the second noun or participle, the latter always relates to the same person that is expressed or described by the first noun or participle; i.e., it denotes a further description of the first-named person.” (A Manual Of The Greek New Testament, Dana & Mantey, p. 147)
“‹ካይ› የሚለው አያያዥ መስተጻምር ተመሳሳይ ሙያ ያላቸውን ሁለት ስሞች የሚያጣምር ከሆነ፣ ‹ሆ› የሚለው የተወሰነ መስተኣምር ወይንም ማንኛውም ሙያው ከስሞቹ መካከል የመጀመርያውን ቀድሞ ከመጣ እንዲሁም በሁለተኛው ስም ወይንም ቦዝ አናቅጽ ፊት ካልተደገመ የኋለኛው ምን ጊዜም በመጀመርያው ስም ወይንም ቦዝ አንቀጽ የተገለጸውን አካል አመላካች ነው፡፡”
በሕጉ ውስጥ የተገለጸው የቃላት አወቃቀር የሚከተለውን ይመስላል፡- የተወሰነ መስተኣምር (ሆ) + የመጀመርያው ስም + አያያዥ መስተጻምር (ካይ) + ሁለተኛው ስም፡፡ በግራንቪል ሻርፕ ሕግ መሠረት የግሪክ ቃላት በዚህ ሁኔታ ተደርድረው ከመጡ ስሞቹ በሙሉ አንድን አካል የሚያመለክቱ ናቸው፡፡ ቲቶ 2፡13 ላይ የሚገኙት ቃላት ይህንን ድርደራ ተከትለው የተጻፉ ናቸው! ስለዚህ ቲቶ 2፡13 ላይ “የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን” የሚሉት ቃላት ኢየሱስ ክርስቶስን የሚገልጹ ናቸው፡፡ በተጨማሪም 2ጴጥሮስ 1፡1 ተመሳሳይ ሰዋሰዋዊ አወቃቀር ያለው ሲሆን የኢየሱስን አምላክነት በግልጽ የሚናገር ሌላኛው የአዲስ ኪዳን ጥቅስ ነው፡፡
አንዳንድ ወገኖች ይህንን ሕግ በትክክል ባለመረዳት ከሕጉ ጋር የሚጋጩ ምሳሌዎችን ስለሚጠቅሱ ዕውቁ የግሪክ ቋንቋና የንባብ ሕየሳ ሊቅ ዶ/ር ዳንኤል ዋላስ ሕጉ የሚሠራው በምን ሁኔታ እንደሆነ ሲያብራሩ እንዲህ ብለዋል፡-
“In native Greek constructions (i.e., not translation Greek), when a single article modifies two substantives connected by καί (thus, article-substantive-καί-substantive), when both substantives are (1) singular (both grammatically and semantically), (2) personal, (3) and common nouns (not proper names or ordinals), they have the same referent.”
“በዋናው የግሪክ አወቃቀር (ትርጉም ባልሆነ ግሪክ) “ካይ” በሚል መስተጻምር የተያያዙ ሁለት ስሞች አንድ መስተኣምር ከፊታቸው ከገባ እና ሁለቱም ባሕርይ ገላጮች (1) በሰዋሰውም ሆነ በቃል ደረጃ ነጠላ ከሆኑ (2) ማንነታዊ ከሆኑ (ህልውና ያላቸውን አካላት አመልካች ከሆኑ) እና (3) የወል ስሞች ከሆኑ (የተጸውዖ ስሞች ወይንም ቅደም ተከተላዊ ካልሆኑ) አንድን አካል ያመለክታሉ፡፡ https://bible.net/article/sharp-redivivus-reexamination-granville-sharp-rule
ጥቅሱ የክርስቶስን አምላክነት አያሳይም የሚሉ ሰዎች τοῦ μεγάλου Θεοῦ καὶ Σωτῆρος ἡμῶν “ቶው ሜጋሎው ቴው ካይ ሶቴሮስ ሄሞን” (የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን) በሚለው ውስጥ “ታላቁ አምላክ” የተባለው አብ ሲሆን መድኃኒታችን ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ይላሉ፡፡ ነገር ግን τοῦ μεγάλου Θεοῦ (የታላቁን የአምላካችንን) በሚለው ውስጥ τοῦ (the) የሚለው መስተኣምር Θεοῦ (አምላካችን) ከሚለው ቀድሞ የመጣ በመሆኑ እንዲሁም καὶ (እና) ከሚለው መስተጻምር በኋላ Σωτῆρος (መድኃኒታችን) በሚለው ስም ፊት ለፊት መስተኣምር ባለመኖሩ በግራንቪል ሻርፕ ሕግ መሠረት በዚህ ክፍል “ታላቁ አምላካችንና መድኃኒታችን” የሚሉት አጠራሮች በሙሉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚያመለክቱ ናቸው፡፡ “አምላክ እና መድኃኒት” የሚሉት ቃላት ነጠላ ቁጥርን የሚያመለክቱ፣ ህልውና ያላቸውን አካላት ለማመልከት የገቡ፣ የወል ስሞች እንዲሁም ተመሳሳይ ሙያ በመሆናቸው የሕጉን መስፈርቶች በትክክል ያሟላሉ፡፡
አብዱል
ናሙና 1
ማቴ 21:12 ኢየሱስም ወደ መቅደስ ገባና በመቅደስ የሚሸጡትን እና የሚገዙትን ሁሉ አወጣ፥” those selling and buying”
ሻጪ እና ገዢ የተባሉት ሁለት የማእረግ ስሞች እና በሚል መስተጻምር ተለይተዋል፣ ከመጀመሪያው የማእረግ ስም ሻጪ ከሚለው those የሚል ጠቃሽ አመልካች መስተአምር ይጠቀማል ፡ ሁለተኛው የማእረግ ስም ገዢ ከሚለው ላይ ግን አይጠቀምም ፣ ይህም ሰዋስው ሻጪ እና ገዢ የሚያሳየው ሁለት የተለያየ ማንነቶች እንደሆነ ሁሉ ታላቁ አምላክ አብና መድኃኒታችን የተባለው ኢየሱስ ሁለት የተለያየ ማንነቶች መሆናቸውን በቀላሉ መረዳት ይቻላል።
መልስ
ሙግትህን ስትጀምር ግራንቪል ሻርፕን ጠቅሰህ ሕጉ አቋምህን የሚደግፍ በማስመሰል ነበር፡፡ አሁን ደግሞ የሻርፕን ሕግ የማይቀበሉ ወገኖች የሚጠቀሙትን ሙግት ተጠቅመህ እየተሟገትክ ነው፡፡ ምን ቢነካህ ነው እንዲህ የተምታታብህ? ለማንኛውም በዶ/ር ዳንኤል ዋላስ ማብራርያ መሠረት ሕጉ የሚሠራው ባሕርይ ገላጭ ስሞች በሰዋሰውም ሆነ በቃል ደረጃ ነጠላ ከሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ “የሚሸጡ” “የሚገዙ” ተብለው የተተረጎሙት ቃላት በግሪክ πωλοῦντας (ፖሎውንታስ) እና ἀγοράζοντας (አጎራዞንታስ) የሚሉ ሲሆን ግሥ ከመሆናቸውም በተጨማሪ ብዙ ቁጥርን የሚያመለክቱ እንጂ ነጠላ ቁጥርን የሚያመለክቱ ባለመሆናቸው ሕጉ ተግባራዊ ሊሆን አይችልም፡፡
አብዱል
ናሙና 2
ኤፌሶን 2:20 በሐዋርያት እና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፥
ሐዋርያት እና ነቢያት የተባሉት ሁለት የማእረግ ስሞች እና በሚል መስተጻምር ተለይተዋል፣ ከመጀመሪያው የማእረግ ስም ሐዋርያት ከሚለው the የሚል ጠቃሽ አመልካች መስተአምር ይጠቀማል ፡ ሁለተኛው የማእረግ ስም ነቢያት ከሚለው ላይ ግን አይጠቀምም ፣ ይህም ሰዋስው ሐዋርያት እና ነቢያት የሚያሳየው ሁለት የተለያየ ማንነቶች እንደሆነ ሁሉ ታላቁ አምላክ አብና መድኃኒታችን የተባለው ኢየሱስ ሁለት የተለያየ ማንነቶች መሆናቸውን በቀላሉ መረዳት ይቻላል።
መልስ
ሕጉ የሚሠራው ባሕርይ ገላጭ ስሞች በሰዋሰውም ሆነ በቃል ደረጃ ነጠላ ከሆኑ ነው የሚለውን ማብራርያ ደግመህ አስታውስ፡፡ በዚህ ቦታ ሐዋርያትና ነቢያት የሚሉት ቃላት ብዙ ቁጥር በመሆናቸው ሕጉ ተግባራዊ አይደሆንም፡፡
አብዱል
ሙግቱን ሰፋ ስናደርገው ደግሞ ከቲቶ መልእክት አንጻር ስንመለከተው አምላክ ኣብ መድኃኒታችን ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ይላል፦
ቲቶ 1:4 ከአምላክ Θεὸς አብ ከመድኃኒታችንም ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ምሕረት ሰላምም ይሁን። “from God Father and the Lord Jesus Christ our Saviour”
መልስ
ጥቅሱ “ከእግዚአብሔር አብ ከመድኃኒታችንም ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ምሕረት ሰላምም ይሁን” ይላል፡፡ “አብ አምላክ ስለተባለ ኢየሱስ አምላክ አይደለም እንዲሁም ኢየሱስ መድኃኒት ስለተባለ አብ መድኃኒት አይደለም” የሚል እሳቤ አመክንዮአዊ መሠረት የለውም፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እግዚአብሔር አብን “መድኃኒታችን” በማለት የገለጸባቸው ጥቅሶች በዚሁ በቲቶ መልእክትና በጢሞቴዎስ መልእክት ውስጥ ይገኛሉ፡-
“መድኃኒታችን እግዚአብሔር ተስፋችንም ኢየሱስ ክርስቶስ…” (1ጢሞ. 1፡1)
“በዘመኑም ጊዜ፥ መድኃኒታችን እግዚአብሔር…” (ቲቶ 1፡3)
“…ስለ መድኃኒታችን ስለ እግዚአብሔር የሚሆነውን ትምህርት…” (ቲቶ 2፡9)
“…የመድኃኒታችን የእግዚአብሔር ቸርነትና…” (ቲቶ 3፡4)
ስለዚህ ባንተ ሙግት መሠረት ከቲቶ መልእክት አንጻር “አምላክ” አብ፣ “መድኃኒታችን” ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሆነ ሐዋርያው “መድኃኒታችን እግዚአብሔር” ብሎ የተናገረባቸው ቦታዎች ላይ “እግዚአብሔር” የተባለው አብ ነው ወይንስ ኢየሱስ? አብ ነው የምትል ከሆነ አምላክ የሚለውን ቃል በአብ መድኃኒታችን የሚለውን ደግሞ በኢየሱስ የወሰንከው ከምን ተነስተህ ነው? አንተ ከተናገርከው በተጻራሪ ሐዋርያው “መድኃኒታችን” እንዲሁም “አምላካችን” የሚሉትን ቃላት ለአብም ለኢየሱስም ተጠቅሟል፡፡ ሙግትህ በተዛባ መረጃ አንባቢን የማወናበድ ተግባር ነው፡፡
አብዱል
-
- የስነ–ጽሑፍ ሙግት
የባይብልን ዙርያ ስንመለከት ደግሞ ታላቁ አምላክ የተባለው የኢየሱስ ኣባትና ኣምላክ ነው ፦
ዘዳ.10:16፤17፤ እንግዲህ አምላካችሁ እግዚአብሔር የአማልክት አምላክ የጌቶችም ጌታ፥ ታላቅ አምላክ …ነውና።
ነህ.8:6፤ ዕዝራም ታላቁን አምላክ እግዚአብሔርን ባረከ፤
መዝ.95:3 እግዚአብሔር ታላቅ አምላክ ነውና፥
መዝ.77:13 እንደ አምላካችን ያለ ታላቅ አምላክ ማን ነው?
እስራኤላውያን ታላቁ አምላክ የሚሉት አምላካቸውን ነው፣ እስራኤላውያን አምላካቸው የሚሉት ደግሞ የኢየሱስ አባት ነው፦
ዮሐ.8:54 ኢየሱስም መለሰ ዓለም። እኔ ራሴን ባከብር ክብሬ ከንቱ ነው፤ የሚያከብረኝ እናንተ አምላካችን የምትሉት አባቴ ነው፡፡
መልስ
እግዚአብሔር በአንድ አካል የተወሰነ እንዳልሆነ የተገነዘቡ ብዙ አይሁድ ሊቃውንት በኢየሱስ ዘመን መኖራቸው ይታወቃል፤ ሆኖም አብዛኞቹ አይሁድ አንዱን አካል ብቻ የሚያውቁ ቢሆኑም “ታላቁ አምላክ” በአንድ አካል የተወሰነ እንዳልሆነ በአዲስ ኪዳን ግልፅ ሆኗል፡፡ ከላይ የጠቀስካቸውን የሚመስሉ ብዙ የብሉይ ኪዳን ጥቅሶች በአዲስ ኪዳን ውስጥ ክርስቶስን ለማመልከት መጠቀሳቸውን ልብ ላለ ሰው ሙግትህ ምን ያህል ደካማ እንደሆነ ይገባዋል፡፡ ማስረጃዎቹ በዚህ ሊንክ ውስጥ ተሰባስበዋል፡- http://www.ewnetlehulu.net/am/who-is-jesus/jesus-is-yahweh/
አብዱል
መቼም በሥላሴአውያን ዘንድ አብና ኢየሱስ ሁለት የተለያዩ ማንነቶች እንደሆኑ እሙንና ቅቡል ነው፣ ታዲያ ዳዊት አንተ ብሎ በነጠላ ተውላጠ–ስም የሚጠራው አንድ ማንነት ማንን ነው አብን ወይስ ኢየሱስን? ስንል መልሱ አብን የሚል ነው፣ ምክንያቱም ብቻህን በሚል ገላጭ”Adjective” ተቆልፏልና፦
መዝ.86:10 አቤቱ፥ ድንቅ የምታደርግ አንተ ታላቅ ነህና፥ አንተም ብቻህን ታላቅ አምላክ ነህና።
መልስ
ዳዊት የእግዚአብሔር ነቢይ በመሆኑ የእግዚአብሔርን ሥላሴነት መገንዘቡ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ዳዊት ስለ አብ ብቻ ሳይሆን ስለ ወልድና ስለ መንፈስ ቅዱስ አምላክነትም ጽፏል፡-
“አሕዛብ በአንድነት በተሰበሰቡ ጊዜ መንግሥታትም ለእግዚአብሔር (ያሕዌ) ይገዙ ዘንድ … አቤቱ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፥ ሰማያትም የእጅህ ሥራ ናቸው። እነርሱ ይጠፋሉ፥ አንተ ግን ትኖራለህ፤ ሁላቸው እንደ ልብስ ያረጃሉ፥ እንደ መጐናጸፊያም ትለውጣቸዋለህ፥ ይለወጡማል፤ አንተ ግን ያው አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም።” (መዝ 102፡22-25)
መዝሙረኛው ይህንን ቅኔ እየተቀኘ ያለው ለያሕዌ ነው፡፡ በእብራይስጡ ንባብ ውስጥም “ያሕዌ” የሚለው ስም በተደጋጋሚ ተጠቅሶ የምናገኝ ሲሆን እርሱ “ያሕዌ” በማለት የሚቀኝለት አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደነበር የዕብራውያን ጻሐፊ እንዲህ ያረጋግጥልናል፡-
“ደግሞ፦ጌታ ሆይ [ኢየሱስ]፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፥ ሰማዮችም የእጆችህ ሥራ ናቸው፤ እነርሱም ይጠፋሉ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ፤ ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ፥ እንደ መጎናጸፊያም ትጠቀልላቸዋለህ ይለወጡማል፤ አንተ ግን አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም ይላል።” (ዕብ 1፡10-12)፡፡
መንፈስ ቅዱስንም በተመለከተ እንዲህ ብሏል፡-
“የዳዊትም የመጨረሻ ቃሉ ይህ ነው። ከፍ ከፍ የተደረገው፥ በያዕቆብም አምላክ የተቀባው፥ በእስራኤል ዘንድ መልካም ባለ ቅኔ የሆነ፥ የእሴይ ልጅ የዳዊት ንግግር፤ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ተናገረ፤ ቃሉም በአንደበቴ ላይ ነበረ። የእስራኤል አምላክ ተናገረኝ፤ የእስራኤል ጠባቂ እንዲህ አለ፦ በሰው ላይ በጽድቅ የሚሠለጥን፥ በእግዚአብሔርም ፍርሃት የሚነግሥ፥ እርሱ እንደ ማለዳ ብርሃን እንደ ፀሐይ አወጣጥ፥ በጥዋትም ያለ ደመና እንደሚደምቅ፥ ከዝናብ በኋላ ከምድር እንደሚበቅል ልምላሜ ይሆናል።” (2ሳሙኤል 23፡1-4)
በዚህ ክፍል ንጉሥ ዳዊት የእግዚአብሔርን መንፈስና እግዚአብሔርን በማተካካትና በአንድ ግብር እንዲሁም በአንድ መለኮታዊ ባሕርይ ሲገልፅ እንመለከታለን፡፡ በሌላ ቦታም እንዲሁ የመንፈስ ቅዱስን በሁሉም ቦታ መገኘት በመጥቀስ መለኮት መሆኑን ሲመሰክር እናያለን (መዝሙር 139፡7-10)፡፡ ስለ ፈጣሪነቱም ተናግሯል (መዝሙር 33፡6፣ መዝሙር 104፡29-30)፡፡
ውድ ሙስሊም ወገኖቻችን! ኡስታዞቻችሁ በማያውቁት እየገቡ እንዲህ እያወናበዷችሁ ነውና እነርሱን የትክክለኛ መረጃ ምንጮች አድርጋችሁ በጭፍን ከመከተል ይልቅ የግል ጥናቶችን በማድረግ እውነት የት ጋ እንዳለች ትመረምሩ ዘንድ እንመክራችኋለን፡፡ እንዲህ ያሉ አሳቾች ዛሬ ለሚያገኙት ኃብትና ዝና እንጂ ለሕይወታችሁ ግድ የላቸውም፡፡ ስለዚህ እነርሱ የሚጽፉትንና የሚናገሩትን ብቻ አምኖ መቀበል አያዛልቃችሁምና ነቅታችሁ መንገዳችሁን መርምሩ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ማስተዋልን ይስጣችሁ፡፡ አሜን፡፡