ሼኽ ዘከርያህ – ኢትዮጵያዊው የወንጌል አርበኛ

ሼኽ ዘከርያህ – ኢትዮጵያዊው የወንጌል አርበኛ


ሼኽ ዘከርያህ (1845-1920 ዓ.ም) ካዩዋቸው ተከታታይ ራዕዮች የተነሳ ወደ ክርስትና የገቡ የቀድሞ ሙስሊም ነበሩ። ሼኽ ዘከርያህ በ1845 በበጌምድር ክፍለ ሀገር ናጋላ አካባቢ እንደተወለዱ የሕይወት ታሪካቸው ያስረዳል። ወላጆቻቸው የአማራ ሙስሊሞች ሲሆኑ በመጠነኛ ንግድ ይተዳደሩ ነበር። ሼኽ ዘከርያህ በወሎ ክፍለ ሀገር ገና በለጋ እድሜያቸው የቁርኣንን ትምህርት ተምረዋል። ነገር ግን ሁለት ራዕዮችን ካዩ በኋላ ቁርኣንን ብቻ በመጠቀም ከክርስትና አስተምህሮ ጋር ተቀራራቢ የሆነ አስተምህሮ በመስጊዶች ውስጥ ማስተማር ጀመሩ። ከሙስሊሙ ማሕበረሰብ ራሳቸውን ሳይነጥሉ እስልምናን ለማሻሻልና ለማደስ በቁርኣን ውስጥ የሚገኙ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጣረሱ ስህተቶችን እየተቃወሙ ስለ ክርስቶስ ማንነትና ታላቅነት የሚናገሩ ጥቅሶችን እያብራሩ ያስተምሩ ነበር። በወቅቱ ሼኽ ዘከርያህ ክርስቲያን ለመሆን መንገድ ቢጀምሩም ገና አልደረሱም ነበር። የሼኹ አስተምህሮ ብዙ ተከታዮችን በማፍራት ወደ ትልቅ ንቅናቄ በማደጉ ምክንያት የአካባቢው ሙስሊም ማሕበረሰብ ለስብከታቸው በቁጣ ምላሽ መስጠት ጀመሩ። በዚህም ምክንያት ጉዳያቸው ከአካባቢው ባለ ሥልጣናት አልፎ የሀገሪቱ ዋና መሪዎች ዘንድ የደረሰ ሲሆን በነጻነት እንዲያስተምሩ ፈቃድ አግኝተው መንግሥታዊ ጥበቃም ይደረግላቸው ጀመር። እንደ ሕይወት ታሪካቸው ከሆነ ከወሎ ወደ በጌምድር አካባቢ ከተዛወሩ በኋላ ትኩረታቸው ከእስልምና ተሐድሶ ወደ ክርስትና እምነት ተቀይሮ ነበር። በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ተጠምቀውም ስማቸው “ነዋየ ክርስቶስ” ተብሎ ተቀይሮ ነበር፤ “አለቃ” የሚል ማዕርግም ተሰጥቷቸው ነበር። የአለቃ ነዋየ ክርስቶስ ልምድና አቀራረብ በተለያዩ ደረጃዎች ውስጥ እንዳለፈ መገንዘብ ይቻላል። ሲጀምሩ ሙስሊም ሆነው እስልምናን በመጠራጠርና ወደ ክርስትና በማድላት ሲሆን ቁርኣንን በመጠቀም እስልምናን በመቃወም ክርስቶስ ከሙሐመድ እንደሚበልጥና መለኮታዊ ባህሪያት እንዳሉት በመሞገት ነበር። ስለ እግዚአብሔርና ስለ መዳን መንገድ መጽሐፍ ቅዱሳዊው ትምህርት ሙሉ በሙሉ የተገለጠላቸው አይመስልም። ቁርኣንን በተለየ መንገድ እንዲመለከቱ ሰበብ የሆናቸው ከእግዚአብሔር ዘንድ የተገለጠላቸው ራዕይ ነበር። ወደ ክርስትና በመግባት ቁርኣንን በክርስትና ብርሃን ማየት የጀመሩት ከዚያ በኋላ ነበር። ኋላም እስልምናን ለማሻሻል ከመሞከር ይልቅ ሙስሊሞችን ወደ ክርስትና መለወጥና ማጥመቅ አስፈላጊ መሆኑን ተገነዘቡ። በአስመራ የሚገኘው የስዊድን ሚሲዮን የመጻሕፍት ማከፋፈያ ለእርሳቸውና ለደቀ መዛሙርቶቻቸው አጋዥ የሆኑ የክርስቲያን መጻሕፍትንና በራሪ ጽሑፎችን በአረብኛና በአማርኛ በማቅረብ ይደግፋቸው ነበር። አለቃ ነዋየ ክርስቶስ በትግርኛና አማርኛ ተናጋሪዎች ዘንድ የነበራቸው ተወዳጅነት በፍጥነት እያደገ በመምጣቱ ምክንያት በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሙስሊሞችን ወደ ክርስትና ማምጣት ችለው ነበር። በሕይወት በነበሩበት ዘመን ሰባ አምስት ታዋቂ ሙስሊም ሼኾችና ባለሥልጣናት ከተከታዮቻቸ መካከል ነበሩ። አለቃ ነዋየ ክርስቶስ አስደናቂ የትንቢት ስጦታም እንደነበራቸው ይነገራል። ለበለጠ ንባብ Donald Crummey, “Shaikh Zäkaryas: an Ethiopian Prophet”, Journal of Ethiopian Studies, 10, no. 1 (January 1992), 55-66; J. Iwarsson, “A Moslem Mass Movement toward Christianity in Abyssinia,” Moslem World, 14 (1924), 286-289.2015).
አለቃ ነዋየ ክርስቶስ ከአፍሪካ ታላላቅ የወንጌል አርበኞች መካከል እንደ አንዱ ተቆጥረው በብዙ የውጪ ሀገራት መጻሕፍትና ምሑራዊ ጆርናሎች ስማቸው ይወሳል።