ነጠላ ማንነት ወይስ አሓዱ ሥሉስ?

ነጠላ ማንነት ወይስ አሓዱ ሥሉስ?


የሥላሴ አስተምህሮ መሠረቱ መጽሐፍ ቅዱስ አንድ አምላክ ብቻ መኖሩን ከማስተማሩ በተጨማሪ ይህ አንድ አምላክ የተባለው በሦስት አካላት (ማንነቶች) የሚኖር መሆኑን ማስተማሩ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር አንድነት ሲናገር ባሕርይን እንጂ ማንነትን የተመለከተ አለመሆኑን በብዙ የቅዱሳት መጻሕፍት ማስረጃዎች ማረጋገጥ ይቻላል። ይህንን በተመለከተ በድረ-ገጻችን ላይ በስፋት የጻፍን በመሆኑ እዚህ ቦታ መድገም አያሻንም። ፍላጎቱ ያለው ሰው ተከታዮቹን ገጾች እንዲጎበኝ እንጋብዛለን፦

የቅዱሳት መጻሕፍት ምስክርነት ይህ በሆነበት ሁኔታ አንዳንዶች የተወሰኑ ጥቅሶችን ከአውድ ውጪ በመጥቀስ እግዚአብሔርን በአንድ አካል የተወሰነ ለማስመሰልና የወልድና የመንፈስ ቅዱስን አምላክነት ለመካድ ይሞክራሉ። ከሚጠቅሷቸው ጥቅሶች መካከል ሁለቱ እንደሚከተለው ይነበባሉ፦

“እኔ አምላክ ነኝና፥ ሌላም የለምና የቀድሞውን የጥንቱን ነገር አስቡ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ እንደ እኔም ያለ ማንም የለም” (ኢሳይያስ 46፡9)።

 “ከአንዱም በቀር ማንም አምላክ እንደሌለ እናውቃለን” (1 ቆሮንቶስ 8፡4)

በሥላሴ የማያምኑ ወገኖች በነዚህ ጥቅሶች ውስጥ “እኔ”፣ “ሌላ የለም”፣ “ማንም የለም”፣ ወዘተ. የሚሉት አገላለጾች አንድ ማንነትን ብቻ እንደሚያሳዩ ይሞግታሉ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አንድ ማንነት (person) እንደሆነና አሓዱ ሥሉስ እንዳልሆነ ይነግሩናል። ይህ ከልክ በታች ቀሊል (oversimplified) የሆነ የቅዱሳት መጽሐፍት ዕይታ አጠቃላዩን አስተምህሮ ያገናዘበ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስን በዚህ መንገድ ለመረዳት የሚሞክሩት ወገኖች እግዚአብሔር በብዙ ቁጥር የተገለጸባቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በቸልታ ያልፋሉ ወይም ደግሞ መጽሐፉ በማያውቀው የተለየ መንገድ ለመተርጎም ይሞክራሉ። ሦስቱ መለኮታዊ አካላት አንድ ማንነት እንደሌላቸውና ደግሞም ሦስቱም በመለኮትነት የመጠራታቸውን እውነታ ይክዳሉ። ይህ ሚዛናዊ የሆነ ዕይታ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔርን በነጠላ ብቻ ሳይሆን በብዙ ቁጥርም ጭምር የሚገልጽ ሆኖ ሳለ፤ አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ አንድ ማንነት እንዳልሆኑና ሦስቱም መለኮት መሆናቸው ተገልጾ ሳለ አንድ ነጠላ ማንነት ብቻ ነው ማለት ከመጽሐፉ ጋር የሚስማማ አቋም አይደለም። ሁለቱም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች እስከ ሆኑ ድረስ አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ የመጽሐፍ ቅዱስ አማኝ መሆን አይቻልም። ስለዚህ እነዚህን ጥቅሶች እንዴት ነው መረዳት ያለብን?

እንዲህ ያሉ ጥቅሶችን ስናነብ ጥንቃቄ የሚፈልጉ ጉዳዮች አሉ። የመጀመርያው የቋንቋ ጉዳይ ነው። ለምሳሌ ያህል 1ቆሮንቶስ 8፡4 ላይ “ከአንዱም በቀር ማንም አምላክ እንደሌለ እናውቃለን” ብሎ ሲል በግሪኩም ሆነ በእንግሊዝኛ ትርጉሞች ማንነትን የሚወስን አገላለጽ የለም። “ማንም” የሚለው በአማርኛ ብቻ በተቀመጠበት ሁኔታ ሙግትን በዚያ ላይ መመስረት ትክክል አይደለም። የጥቅሱ ሐሳብ ከአንዱ አምላክ በስተቀር ሌላ እንደሌለ መናገር እንጂ በአንዱ አምላክ ሕላዌ ውስጥ የሚገኙትን ሦስቱን ማንነቶች መካድ አይደለም። “ማንም” በሚለው ላይ ተንጠልጥለን “ሌላ ማንነት” በሚል ብቻ ከተረጎምን ማንነት አልባ የሆኑ በሰዎች የሚመለኩ ጣዖታት ስላሉ ማንነት አልባዎቹ አማልክት እውነተኞች ሊሆኑ ነው። ነገር ግን “ማንም የለም” የሚለው አባባል ማንነት ያላቸውንም ሆነ ማንነት አልባ የሆኑትን ግዑዛን አካላት ሁሉ የሚያጠቃልል ነው በሚል ከተረዳን ከእግዚአብሔር ሕላዌ ውጪ የሚገኙትን አካላት የተመለከተ እንጂ በእግዚአብሔር ሕላዌ ውስጥ ስለሚገኘው ሁኔታ የሚነግረን አይደለም ማለት ነው።

ሌላው ጥንቃቄ የሚፈልግ ጉዳይ አውድ ነው። ኢሳይያስ 46 የአሕዛብ አማልክት ከንቱዎች መሆናቸውን ለመናገር የተጻፈ ክፍል ነው፦

“ቤል ተዋረደ፥ ናባው ተሰባበረ፤ ጣዖቶቻቸው በእንስሳና በከብት ላይ ተጭነዋል፤ ሸክሞቻችሁ ለደካማ እንስሳ ከባድ ጭነት ሆነዋል” (ኢሳ. 46:1)።

ስለዚህ ከጥቅሱ አውድ የምንረዳው የእስራኤል አምላክ ከሌሎች አማልክት ጋር እንደማይቆጠርና ልዩ መሆኑን የሚያሳይ እንጂ በሕላዌው ውስጥ ስለሚገኝ ሁኔታ መናገር አይደለም። በእርግጥ ክርስቲያኖች ሦስት አማልክት ስለማያመልኩ እግዚአብሔር በአንድነት መገለጹ የሥላሴን አስተምህሮ የሚቃወም አይደለም። በዚህ ክፍል ላይ በእኔነት የተናገረው ከሦስቱ አካላት የትኛውም ቢሆን የሦስቱንም ባሕርይ የተመለከተ ነገር እንጂ የተነገረው ሦስቱን አካላት የሚነጣጥል አይደለም። በሥላሴነት የሚኖረው እግዚአብሔር ሲናገር በሦስቱም አካላት አንዱን ባሕርይ የሚገልጽ ነገር ይናገራል። ስለዚህ “ከእኔ በቀር” ብሎ ሲናገር እስራኤላውያን ከሌሎች የአሕዛብ አማልክት እንደ አንዱ እንዳይቆጥሩት በአንዱ ማንነት በኩል የማይከፋፈለውን አምላካዊ ባሕርዩን እየገለጸ እንጂ ነጠላ ማንነትን ለማመልከት አይደለም። እንዲህ ካሉ ጥቅሶች በመነሳት የእስራኤል አምላክ ነጠላ ማንነት እንዳለው የሚከራከሩ ሰዎች በሌሎች ክፍሎች ደግሞ በብዙ ቁጥር የመጠቀሱን እንዲሁም አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ ሦስት ማንነቶች ሆነው ሳሉ በአምላክነት የመታወቃቸውን እውነታ መጋፈጥና ስርዓት በጠበቀ ስነ አፈታት ማብራራት ይጠበቅበታል።

ይህንን ጥቅስ የሚጠቅሱት ወገኖች የክርስቶስን አምላክነት ለመቃወም በመሆኑ እውን ይህ ጥቅስ ክርስቶስን ያገለለ ነው ወይንስ ስለ ክርስቶስ አምላክነት የሚናገር? የሚለውን በሌሎች ጥቅሶ መመልከት ይቻላል። ከሁለት ምዕራፎች በኋላ እግዚአብሔር በነቢዩ በኢሳይያስ በኩል እንዲህ ሲል ይናገራል፦

“ያዕቆብ ሆይ፥ የጠራሁህም እስራኤል ሆይ፥ ስማኝ፤ እኔ ነኝ፤ እኔ ፊተኛው ነኝ እኔም ኋለኛው ነኝ” (ኢሳይያስ 48:12)።

በአዲስ ኪዳን ውስጥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ቦታ የተገለጸውን ዓይነት አነጋገር በመጠቀም በተደጋጋሚ ተናግሯል። ለምሳሌ ያህል በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ የተነገሩትን “እኔ ነኝ” የሚሉ ክፍሎችን በተለይም ደግሞ ቅድመ አብረሃም የነበረ መሆኑን ለመግለጽ የተጠቀመውን (በግሪክ “ኢጎ ኤይሚ”) መጥቀስ እንችላለን (ዮሐ. 8:58)። ይህ አባባል የኢየሱስን አምላክነት የሚገልጽ መሆኑን ሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት በአንድ ድምጽ የሚስማሙበት ጉዳይ ነው። በሌላ ስፍራም ጌታችን ኢየሱስ እንዲህ ማለቱን ዮሐንስ ይነግረናል፦

“ባየሁትም ጊዜ እንደ ሞተ ሰው ሆኜ ከእግሩ በታች ወደቅሁ። ቀኝ እጁንም ጫነብኝ እንዲህም አለኝ፦ አትፍራ፤ ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ፥ ሞቼም ነበርሁ እነሆም፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ፥ የሞትና የሲኦልም መክፈቻ አለኝ” (ራዕይ 1:17-18)።

“እነሆ፥ በቶሎ እመጣለሁ፥ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ። አልፋና ዖሜጋ፥ ፊተኛውና ኋለኛው፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ” (ራዕይ 22:12-13)።

ከዚህ በተጨማሪ ኢሳይያስ 48 ምዕራፉን በጥንቃቄ ያነበብን እንደሆን ሦስቱንም የሥላሴ አካላት የሚጠቅስ ሆኖ ማግኘታችን የተናጋሪውን ማንነት በግልፅ ያሳየናል፦

“ያዕቆብ ሆይ፥ የጠራሁህም እስራኤል ሆይ፥ ስማኝ፤ እኔ ነኝ፤ እኔ ፊተኛው ነኝ እኔም ኋለኛው ነኝ። እጄም ምድርን መሥርታለች ቀኜም ሰማያትን ዘርግታለች፤ በጠራኋቸው ጊዜ በአንድነት ይቆማሉ። እናንተ ሁሉ፥ በአንድነት ተሰብስባችሁ ስሙ፤ ከእነርሱ ይህን የተናገረ ማን ነው? እግዚአብሔር የወደደው ፈቃዱን በባቢሎን ላይ ያደርጋል፥ ክንዱም በከለዳውያን ላይ ይሆናል። እኔ ራሴ ተናግሬአለሁ፤ እኔ ጠርቼዋለሁ፤ አምጥቼዋለሁ፥ መንገዱም ትከናወንለታለች። ወደ እኔ ቅረቡ ይህንም ስሙ፤ እኔ ከጥንት ጀምሬ በስውር አልተናገርሁም፤ ከሆነበት ዘመን ጀምሮ እኔ በዚያ ነበርሁ፥ አሁንም ጌታ እግዚአብሔርና መንፈሱ ልከውኛል” (ኢሳይያስ 48:12-16)።

በዚህ ጥቅስ ውስጥ “እኔ ከጥንት ጀምሬ በስውር አልተናገርሁም፤ ከሆነበት ዘመን ጀምሮ እኔ በዚያ ነበርሁ፥ አሁንም ጌታ እግዚአብሔርና መንፈሱ ልከውኛል” የሚሉት ቃላት በነቢዩ በራሱ የተነገሩ መሆናቸውን የሚሞግቱ ወገኖች ቢኖሩም አውዱ የነቢዩ ቃል እንዳልሆነ በግልጽ ያሳየናል። ክፍሉ ስለ ባቢሎናውያን መጥፋት የሚናገር ሲሆን አጥፊው ደግሞ የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንደሆነ የሚታወቅ ነው። ይህ ትንቢት የተፈጸመው ነቢዩ ኢሳይያስ ከሞተ ከብዙ ዘመናት በኋላ በመሆኑ ነቢዩ ከጥንት ጀምሮ እስከ ትንቢቱ ፍጻሜ ዘመን ድረስ በዚያ ሊሆን አይችልም። ቀደም ሲል “እኔ ራሴ ተናግሬአለሁ፤ እኔ ጠርቼዋለሁ፤ አምጥቼዋለሁ፥ መንገዱም ትከናወንለታለች” የሚለው አባባል ቀጥሎ ከመጣው ጋር አንድ ላይ ተያይዞ ያለ በመሆኑ ተናጋሪው አንድ ማንነት ነው። ይህ አገላለጽ ደግሞ እዚሁ በኢሳይያስ ትንቢት ውስጥ በሌላ ስፍራ በእግዚአብሔር የተነገረ መሆኑን መመልከት ተናጋሪው መለኮታዊ አካል መሆኑን ያረጋግጥልናል፦

በስውር ወይም በጨለማ ምድር ስፍራ አልተናገርሁም፤ ለያዕቆብ ዘር፦ በከንቱ ፈልጉኝ አላልሁም እኔ እግዚአብሔር ጽድቅን እናገራለሁ ቅንንም አወራለሁ። እናንተ ከአሕዛብ ወገን ሆናችሁ ያመለጣችሁ፥ ተሰብስባችሁ በአንድነትም ቅረቡ፤ የተቀረጸውን የምስላቸውን እንጨት የሚሸከሙና ያድን ዘንድ ወደማይችል አምላክ የሚጸልዩ እውቀት የላቸውም” (ኢሳይያስ 45:19-20)።

በዚህ ክፍል ውስጥ ተናጋሪው ነቢዩ እንደሆነ አድርገው የሚረዱ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን ነቢዩ የክርስቶስ ተምሳሌት (Type) እንደሆነ የሚናገሩ ሲሆን ሌሎች ደግሞ በአብና በመንፈስ ቅዱስ የተላከው ራሱ ወልድ በነቢዩ አንደበት እየተናገረ እንደሆነ ይናገራሉ። ማስረጃዎቹን እዚህ እና እዚህ ማግኘት ትችላላችሁ። በዚህ ጥቅስ ውስጥ ተናጋሪው ወልድ መሆኑ የእስክንድርያው ኦሪጎን፣ አውጉስጢኖስና ጀሮሜን የመሳሰሉት አበው አስተምረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ነቢዩ ኢሳይያስ እግዚአብሔርን በነጠላ ቁጥር ብቻ ሳይሆን በብዙ ቁጥር በመግለጽም ይታወቃል። ለምሳሌ ያህል ተከታዮቹን ጥቅሶች በእብራይስጥ ይመልከቱ፦

ፈጣሪሽ ባልሽ ነው (በእብራይስጥ “ቦዓለይከ ኦሳይከ” – ሁለቱም ቃላት ብዙ ቁጥር ናቸው)፥ ስሙም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው፤ የእስራኤልም ቅዱስ ታዲጊሽ ነው፥ እርሱም የምድር ሁሉ አምላክ (ኤሎሄይ ካል ሃ ኤሬጽ – ብዙ ቁጥር) ይባላል” (ኢሳይያስ 54:5)።

ቀጥሎ ባለው ጥቅስ ውስጥ የሚገኘውን የብዙ ቁጥር አገላለጽ ሁሉም ትርጉሞች በትክክል አስቀምጠዋል፦

“የጌታንም ድምፅ፦ ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል? (ኡሚ ዬሌከ ላኑ) ሲል ሰማሁ። እኔም፦ እነሆኝ፥ እኔን ላከኝ አልሁ” (ኢሳይያስ 6:8)።

በአዲስ ኪዳን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ንግግር ለኢሳይያስ የተናገረው መንፈስ ቅዱስ መሆኑን ይነግረናል፡-

“እርስ በርሳቸውም ባልተስማሙ ጊዜ፥ ጳውሎስ አንዲት ቃል ከተናገረ በኋላ ሄዱ፤ እንዲህም አለ፦ መንፈስ ቅዱስ በነቢዩ በኢሳይያስ ለአባቶቻችን፦ ወደዚህ ሕዝብ ሂድና፦ መስማትን ትሰማላችሁና አታስተውሉም፥ ማየትንም ታያላችሁና አትመለከቱም…” (የሐዋርያት ሥራ28፡25-26)

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እየጠቀሰ የነበረው ኢሳይያስ 6 ላይ የሚገኘውን ቃል ነው፡-

“የጌታንም ድምፅ፦ ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል? ሲል ሰማሁ። እኔም፦ እነሆኝ፥ እኔን ላከኝ አልሁ። እርሱም፦ ሂድ፥ ይህን ሕዝብ፦ መስማትን ትሰማላችሁ አታስተውሉምም ማየትንም ታያላችሁ አትመለከቱምም በላቸው።” (ኢሳይያስ 6፡8-9)

ኢሳይያስ የሰማው የመንፈስ ቅዱስን ድምፅ ነበር፡፡ በብሉይ ኪዳን ለኢሳይያስ የተናገረው አዶናይ በአዲስ ኪዳን መንፈስ ቅዱስ መሆኑ መነገሩ የመንፈስ ቅዱስን መለኮትነት በማረጋገጥ የሥላሴን አስተምህሮ የሚደግፍ ጠንካራ ማስረጃ መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ መንፈስ ቅዱስ በዚህ ቦታ አብና ወልድን በመወከል በእኛነት እንደተናገረ ግልጽ ነው። ነቢዩ ኢሳይያስ በዚህ ምዕራፍ ላይ በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ያየው ኢየሱስ ክርስቶስን መሆኑን ወንጌላዊው ዮሐንስ ይነግረናል (ዮሐንስ 17:37-41)። (ጌታ ቢፈቅድና ብንኖር በዚህ ላይ ሰፋ ያለ ማብራርያ ወደፊት የምናቀርብ ይሆናል)።

በሌላ ቦታ እንዲሁ ነቢዩ ኢሳይያስ የአሓዱ ሥሉስን አካላት ይጠቅሳል፡፟-

“እርሱም፦ በእውነት ሕዝቤ፥ ሐሰትን የማያደርጉ ልጆች፥ ናቸው አለ፤ መድኃኒትም ሆነላቸው። በጭንቃቸው ሁሉ እርሱ ተጨነቀ፥ የፊቱም መልአክ አዳናቸው፤ በፍቅሩና በርኅራኄውም ተቤዣቸው፥ በቀደመውም ዘመን ሁሉ አንሥቶ ተሸከማቸው። እነርሱ ግን ዐመፁ ቅዱስ መንፈሱንም አስመረሩ፤ ስለዚህ ተመልሶ ጠላት ሆናቸው፥ እርሱም ተዋጋቸው” (ኢሳይያስ 63:8-10)።

በዚህ ቦታ አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ ተጠቅሰዋል። በክፍሉ ውስጥ በባለቤትነት የተጠቀሰው ልጁንና መንፈሱን የሚልከው እግዚአብሔር አብ ሲሆን “የፊቱ መልአክ” ተብሎ የተገለጸው በዘመነ ብሉይ በአምሳለ መልአክ እየተገለጠ ሕዝቡን ሲያድን የነበረው ወልድ ነው። (“መላክ” የሚለው የእብራይስጥ ቃል መላእክት ብለን የምናውቃቸውን መንፈሳውያን ፍጥረታት ለማመልከት ብቻ የሚገባ ቃል አለመሆኑንና ሰዎችን ጨምሮ ማንኛውንም መልእክተኛ ሆኖ የሚላክን አካል ለማመልከት ጥቅም ላይ እንደሚውል ልብ ይሏል)። በተጨማሪም በዚህ ክፍል መንፈስ ቅዱስ እንደ ግዑዝ አካል ሳይሆን ህልውና እንዳለው ማንነት መገለጹን እንመለከታለን፤ ማሰብ ለማይችል አካል ፈቃድ፣ ዕውቀትና ስሜት አይነገርምና። “የፊቱ መልአክ” ተብሎ የተገለጸው ወልድ መሆኑን ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት ይናገራሉ፤ በቂ ማብራርያም ይሰጣሉ። ለምሳሌ ያህል እዚህ እዚህ እና እዚህ በመጫን የሊቃውንትን ማብራርያ ይመልከቱ። በብሉይ ኪዳን ውስጥ ለየት ባለ ሁኔታ “የያሕዌ መልአክ” ተብሎ የተጠራና ለያሕዌ ብቻ ተገቢ የሆነ ክብር እየተሰጠው ደግሞም “ያሕዌ” ተብሎ በመጠራት መለኮታዊ አካል መሆኑ የተነገረለት መልእክተኛ አለ። እስራኤላውያንን በምድረ በዳ የመራቸውና ያዳናቸው ይኸው መልአክ ሲሆን በስም፣ በባሕርይና በኃይሉ ችሎት ከያሕዌ የተለየ አይደለም። በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የተሰጠውን ሰፊ ትንታኔና ማስረጃ እዚህ ጋር በመጫን በገጻችን ላይ ያንብቡ።

ስናጠቃልል መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔርን በእኔነት ብቻ ሳይሆን በብዝሃ ቁጥርም ጭምር ይጠቅሳል፤ የሦስቱን አካላት የማንነት ልዩነት በግልጽ አስቀምጦ በመለኮትነት ይገልጻቸዋል። ስለዚህ እግዚአብሔር በእኔነት በተገለጸባቸው ክፍሎች ላይ የአካል ነጠላነትን ለማመልከት ሳይሆን ከሌሎች አማልክት የተለየ መሆኑንና የባሕርይ አንድነቱን ለማሳየት መሆኑን መረዳት እንችላለን። ይህ የባሕርይ አንድነቱና ልዩ መሆኑ ከሦስቱ አካላት በአንዱ ቢነገር ሌሎቹን አካላት ለማግለል የታለመ ሳይሆን የሦስቱም የሆነው አንዱ ባሕርይ ከሦስቱ በአንዱ መገለጹን የሚያረጋግጥ ነው። እግዚአብሔር ነጠላ አካል ብቻ እንደሆነ ማመን የሚፈልጉ ወገኖች በነጠላ የተነገረባቸውን ክፍሎች ብቻ መርጦ መጥቀስ ሳይሆን በብዙ ቁጥር የተገለጸባቸውን እንዲሁም ወልድና መንፈስ ቅዱስ በየራሳቸው ቅዋሜ ማንነት ያላቸውና ደግሞም በመለኮትነት የተገለጹ የመሆናቸውን እውነታ የመጋፈጥና በቂ ማብራርያ የመስጠት ኃላፊነት ይሸከማሉ። አምላካችን እግዚአብሔር በባሕርዩ አንድ በማንነት ግን ሦስት ነው፤ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ።


እግዚአብሔር ማነዉ?