ምዕራፍ ሁለት
የመጽሐፍ ቅዱስ አዘጋገብ ክፍል 2 [ክፍል 1]
-
ከእምነቱ በኋላ መጽሐፉ?
በዚህ ርዕስ ስር አቶ ሐሰን ብዙ የሐሰት መረጃዎችንና እርስ በርሳቸው የተምታቱ ሐሳቦችን ያቀርባሉ፡፡ እንዲህ በማለት ይጀምራሉ፡-
የመለኮታዊ እምነት አመሠራረት እንዲህ ነው፡፡ አምላክ ነቢይ ይልካል፡፡ በእርሱ አማካይነት የሚፈልገውን ይገልጻል፡፡ ሰዎች ሊያምኑት እና ሊፈጽሙት የሚገባውን በመጽሐፉ እና በነቢዩ አንደበት ያብራራል፡፡ አማኞች መጽሐፉን መሠረት አድርገው እምነታቸውን ያንጻሉ፡፡ የክርስትናን ታሪክ ስናጠና የሚያጋጥመን ተቃራኒው ነው፡፡ ከፈረሱ ጋሪው እንደሚባለው፡፡ በመጀመርያ ቤተ ክርስትያን (የእምነቱ ተቋም) ተቋቋመች፡፡ ተከታዮቿ የሚያምኑበትን ነገር ወሰነች፡፡ ይህን ውሳኔዋን መሠረት አድርጋ ስለክርስትና ከተጻፉ ከ300 ያላነሱ መጽሐፍት ውስጥ ከዚህ እምነቷ ጋር የሚጣጣሙ መጽሐፍትን ብቻ መርጣ ለማጽደቅ ሌሎቹን ውድቅ አደረገች፡፡ (ገፅ 44)
ይህ መሠረተ ቢስ አሉባልታ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን አስተማረ፡፡ ከመንፈስ ቅዱስ መውረድ በኋላ አዳዲስ መገለጦችን እንደሚያገኙ ተስፋን ሰጣቸው (ዮሐ. 16፡13)፡፡ ቤተ ክርስቲያንም እንደምትመሠረት አስታወቀ (ማቴ. 16፡18)፡፡ በበዓለ ሃምሳ ዕለት ከመንፈስ ቅዱስ መውረድ ጋር ተያይዞ ቤተ ክርስቲያን ተመሠረተች (ሐዋ. 2)፡፡ ሐዋርያት ወንጌልን ማስተማር ጀመሩ፤ ብዙ ሺህዎችም አመኑ (ሐዋ. 2፡41፣ 4፡4)፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑ እየበዛ ሲመጣ የክርስቶስና የሐዋርያት ትምህርቶች ለሕዝቡ ጥቅም ሲባል በራሳቸው በሐዋርያትና በቅርብ ሰዎቻቸው አማካይነት በጽሑፍ ሰፍረው አዲስ ኪዳንን ፈጠሩ፡፡ የሐሰት አስተማሪዎች አዳዲስ ትምህርቶችን በመፍጠርና የየራሳቸውን ቀኖና በማዘጋጀት ቤተ ክርስቲያንን ማመስ ሲጀምሩ ቤተ ክርስቲያን ኦፊሴላዊ ጉባኤዎችን በመጥራት የእምነት መግለጫዎችን አወጣች፡፡ ቀኖናዋንም አስታወቀች፡፡ እውነቱ ይህ ነው፡፡ ከዚህ የተለየ ታሪክ ማስረጃ የሌለው የፈጠራ ወሬ ነው፡፡
በማስከተል በዚህ ርዕስ ስር ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተዋል፡-
- ክርስቲያኖች ብሉይ ኪዳንን እንዳለ ከአይሁድ ኮርጀዋል (ገፅ 44)፡፡
ይህ የክርስትናን አመሠራረት ካለማወቅ የመነጨ ንግግር ነው፡፡ ክርስትና እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ዘመን በነቢያቱ በኩል የሰጣቸው ተስፋዎች ፍፃሜ በመሆኑ ሥረ መሠረቱ ብሉይ ኪዳን ነው፡፡ ሐዋርያትን ጨምሮ የመጀመርያዎቹ ክርስቲያኖች በሙሉ አይሁዳውያን ነበሩ (ሐዋ. 2፡1-41፣ 4፡4)፡፡ መሲሁ ኢየሱስ ራሱ አይሁዳዊ ነበር (ዮሐ. 4፡22፣ ማቴ 1፡1-17)፡፡ የመጀመርያዎቹ ክርስቲያኖች ከአይሁድ ጋር በቤተ መቅደስና በምኩራቦች ውስጥ እግዚአብሔርን ያመልኩ ነበር (ሐዋ. 3፡1-2)፡፡ ብሉይ ኪዳንን እንደ ቃለ እግዚአብሔር የተቀበልነው እግዚአብሔር የእምነታችን መሠረት ይሆን ዘንድ ለነቢያቱ የሰጠው ሰማያዊ መገለጥ መሆኑን ስላመንን ነው፡፡
አቶ ሐሰን በዚሁ ቦታ ላይ ክርስቲያኖች በቁርኣን ላይ የኩረጃ ክስ ማቅረባቸውን በመግለፅ ያማርራሉ፡፡ ክርስቲያኖች አንዲት ፊደል እንኳ ሳይቀንሱ ከአይሁድ ኮርጀዋል በማለትም ስሞታ ያቀርባሉ፡፡
እኛ ያልተበረዘ ያልተከለሰ ቃለ እግዚአብሔር መሆኑን ስላመንን ብሉይ ኪዳንን ተቀብለናል፡፡ የፈጣሪን መገለጥ ሳይሸራርፉ መቀበል ኩረጃ ነው የሚል ሰው ዕይታው የተወሰደበት ምስኪን መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ዳሩ ግን ቁርኣን የኮረጃቸውን ምንጮች ስንመለከት ሙስሊሞች እንኳ እንደ ፈጣሪ ቃል የማይቀበሏቸውና የፈጠራ ጽሑፎችና አፈታሪኮች መሆናቸው በማስረጃ ሊረጋገጡ የሚችሉ የአይሁድ ተርጉም፣ የክርስቲያን አፖክሪፋ፣ የሳባውያን አፈታሪኮችና የአረብ ጣዖታውያን ልምምዶችን የመሳሰሉ እርባና የሌላቸው ምንጮች ናቸው፡፡ የአቶ ሐሰን ሙግት ፊየል ወዲህ ቁርኣን ወዲያ ዓይነት ነው፡፡ በዚህ ላይ ወደ ኋላ በስፋት እናትታለን፡፡
- ቅዱስ አትናቴዎስ በ367 ዓ.ም. በፋሲካ እለት ቃለ በረከት የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት 27 ብቻ መሆናቸውን ተናግሯል፡፡ በ397 በካርታጎ (ካርቴጅ) የተደረገው ሲኖዶስ 27ቱን መጻሕፍት አፅድቋል (ገፅ 45)፡፡
ይህ መረጃ ትክክል ሲሆን በኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማሕበር በተዘጋጀው የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ገፅ 35 ላይ ተገልጿል፡፡ አያይዘው ተከታዩን ሐሳብ በአንድ ክርስቲያን ከተጻፈ መጽሐፍ ላይ ጠቅሰዋል፡-
“በጣም የቆየው የካኖን ዝርዝር የእስክንድሪያው ጳጳስ የሆነው አትናቴዎስ በ387 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ ላይ ይገኛል፡፡ በደብዳቤው በአሁኑ አዲስ ኪዳን ውስጥ የሚገኙትን 27 መጽሐፍት ዘርዝሯል፡፡ የካርታጎው ጉባኤ በ397 ዓ.ም. በጉዳዩ ላይ ሳይነጋገር የአትናቴዎስን ዝርዝር አፅድቋል፡፡”[1]
አቶ ሐሰን ከላይ ያለውን መረጃ በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ላይ ከተገለፀው የተለየ ሌላ ታሪክ አስመስለው ነው ያቀረቡት፡፡ በዚህ ርዕስ ስር ላሉት መረጃዎች ምንጭ በመሆን ያገለገሏቸው ኡስታዝ አሕመዲን ጀበል ደግሞ በመዝገበ ቃላቱ ላይ ያለውን መረጃና በዶ/ር ፓውል እንዝ የተጻፈውን ከላይ የተቀመጠውን መረጃ በማጋጨት የአትናቴዎስ ደብዳቤ መቼ እንደተጻፈ ክርስቲያኖች እንደማያውቁ በማስመሰል አቅርበዋል፡፡[2] ነገር ግን በዶ/ር ፓውል መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው 387 የሚለው መረጃ ተርጓሚዎቹ የፈፀሙት የትየባ ስህተት ሲሆን ትክክለኛው ዓመት 367 ነው፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ የኖረው ከ296-373 ዓ.ም. በመሆኑ በ387 ደብዳቤ ሊጽፍ አይችልም፡፡[3] አቶ ሐሰን የትየባ ስህተትን ከትክክለኛ መረጃ መለየት ያልቻሉ ሰው ናቸው፡፡ በተጨማሪም ለነዚህ መረጃዎች የሰጡት ትርጉም የረባ ጥናት አለማድረጋቸውን ያመለክታል፡፡
- በኒቅያ ጉባኤ ላይ የመጻሕፍት ምርጫ የተደረገው በውይይት ላይ በመመሥረት ሳይሆን ድራማዊ በሚመስል ሁኔታ ነበር (ገፅ 45)፡፡
በኒቅያ ጉባኤ ላይ የቅዱሳት መጻሕፍት ምርጫ መደረጉንና አሁን ያሉት መጻሕፍት ተመርጠው ሌሎች መወገዳቸውን በመጽሐፉ ውስጥ ደጋግመው አንስተዋል (ገፅ 37፣ 106)፡፡ አልፎ ተርፎም ገፅ 106 ላይ እንዲህ የሚል አስቂኝ ተረት ይነግሩናል፡-
የኒቂያን ጉባኤ በጥንቃቄ ስንመረምር ድራማዊ የሆኑ ነገሮችን እናገኛለን፡፡ 300 የሚደርሱ መጽሐፍ ቅዱሳን ከአዳራሽ ውስጥ ካለ ጠረጴዛ ስር እንዲቀመጡ ተደረጉ፡፡ አምላክ የወደደውን መጽሐፍ ከጠረጴዛው ላይ ያስቀምጥ ዘንድ ጳጳሳት ሌሊቱን ሙሉ ሲጸልዩ እንዲያድሩ ታዘዙ፡፡ ጠዋት የአዳራሹ በር ሲከፈት በንጉሱ የምትደገፈው ጳውሎሳዊት ቤተክርስትያን የምትደግፋቸው መጽሐፍ ቅዱሳን ከጠረጴዛው ላይ ተገኙ፡፡ የዚያን ቀን የአዳራሽ ቁልፍ ከማን እጅ እንደነበር መገመት አያዳግትም፡፡
አቶ ሐሰን ጥሩ የልበወለድ ጸሐፊ መሆናቸውን አስመስከረዋል፡፡ ዳሩ ግን ጥሩ የልበ ወለድ ጸሐፊ መሆን ጥሩ የሃይማኖት መምህር አያደርግም፡፡ የጉባኤውን ዝርዝር ሁኔታ በተመለከተ “ኢየሱስ የኢስላም ነቢይ” በሚል ርዕስ የተጻፈውን መጽሐፍ ያነቡ ዘንድ አንባቢያንን ይጋብዛሉ (ገፅ 106)፡፡ መጽሐፉ ምንም ማስረጃ የሌላቸውን መሰል የፈጠራ ታሪኮች የሚያስነብብ ሐተታ ባልቴት እንጂ የረባ ቁምነገር ያዘለ አይደለም፡፡ በኒቅያ ጉባኤ ላይ የመጻሕፍት ምርጫ መደረጉን የሚያሳይ ምንም ዓይነት ታሪካዊ ማስረጃ የለም! ሙስሊም ወገኖቻችን ስለ ክርስትና ያላቸው መረጃዎች በእንዲህ ዓይነት አሉባልታዎች ላይ የተመሠረቱ መሆናቸው በእጅጉ የሚያሳዝን ነው፡፡ ሐሰን ታጁን የመሳሰሉት ሙስሊም አስተማሪዎች ምሑራዊ ጥናቶችን በማድረግ ሕዝባቸው ትክክለኛ መረጃ ኖሮት ከክርስቲያን ጎረቤቱ ጋር ትርጉም ያለው ውይይት እንዲያደርግ ከማስቻል ይልቅ እንዲህ ዓይነቱን አርቲ ቡርቲ በማስተማር አለመግባባቱን ማክረራቸው ትዝብት ላይ ይጥላቸዋል፡፡ በፈጣሪ ዘንድም ያስጠይቃቸዋል፡፡
- ቤተ ክርስቲያን የእምነት አቋሟን ያገኘችው ከቅዱሳት መጻሕፍት ሳይሆን የእምነት አቋም ይዛ ከውሳኔዋ ጋር የሚሄዱትን መጻሕፍት ብቻ መርጣለች የሚለውን የፈጠራ ታሪክ ለመደገፍ የሰጡት “ማስረጃ” የኒቅያ ጉባኤ በ325 ዓ.ም. ከተደረገ በኋላ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት 27 ብቻ መሆናቸውን የሚገልፀው የቅዱስ አትናቴዎስ የፋሲካ ቃለ በረከት በ367 የተጻፈ መሆኑን እንዲሁም የካርታጎ ጉባኤ በ397 ዓ.ም. ይህንኑ ማፅደቁን ነው (ገፅ 44-45)፡፡ በማስከተል እንደምንመለከተው ለነዚህ መረጃዎች የሰጡት ትርጓሜ ጥራዝ ነጠቅ በሆነ ንባብ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ እንጂ የአዲስ ኪዳን ቀኖና ታሪክ ይህንን አያመለክትም፡፡
የአዲስ ኪዳን ቀኖና አመጣጥ
ኡስታዙ የክርስትና እምነት በኒቅያ ጉባኤ የተወሰነ በማስመሰል የተናገሩት በእጅጉ የተሳሳተ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ያለምንም ኦፊሴላዊ ጉባኤ ቀደም ሲል ተቀብላው የነበረው የሥላሴ ትምህርት አርዮስ በተሰኘ የኑፋቄ አስተማሪ ተግዳሮት ስለገጠመው ነበር ጉባኤ መጥራት ያስፈለገው፡፡ ጉባኤው ቀደም ሲል ቤተ ክርስቲያን የምታምነውን ትምህርት በነገረ መለኮታዊ ቃላት ይበልጥ በማብራራት መግለጫ አወጣ እንጂ አዲስ ነገር አልፈጠረም፡፡ በተጨማሪም የጥንቶቹ ክርስቲያኖች አቋም ከያዙ በኋላ አልነበረም ቅዱሳት መጻሕፍታቸውን ያጸደቁት፡፡ ከኒቅያ ጉባኤ በፊት (325 ዓ.ም. በፊት) የተጻፉ የአዲስ ኪዳንን የተለያዩ ክፍሎች የሚጠቅሱ ስፍር ቁጥር የሌላቸው የአበው ጽሑፎች (Lectionaries) ይገኛሉ፡፡ ክርስቲያን ዐቃቤ እምነት የሆኑት ፕሮፌሰር ኖርማን ጌይዝለር እንደጻፉት ቅድመ ኒቅያ በአበው ጽሑፎች ውስጥ የተጠቀሱትን ከ 36,289 በላይ ጥቅሶችን አንድ ላይ ብንቀጣጥል ከ11 ቁጥሮች (ከግማሽ ገጽ ያነሰ) በስተቀር ሁሉንም የአዲስ ኪዳን ክፍል መልሰን መጻፍ እንችላለን![4] ይህ የሚያሳየው መጻሕፍቱ ቀደም ሲል ተቀባይነት እንደነበራቸውና የኒቅያ ጉባኤም ሆነ ሌሎች የቤተ ክርስቲያን ጉባኤዎች በነዚህ ላይ ተመሥርተው የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ማስታወቃቸውን ነው፡፡ (አርዮስና ሰባልዮስን የመሳሰሉት መናፍቃን እንኳ ክርክራቸውን ያቀረቡት አሁን በእጃችን በሚገኙት የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ላይ በመመሥረት ነበር፡፡)
በሐዋርያትና በቀደሙት አማኞች ስም የተጻፉ የአፖክሪፋ መጻሕፍት ከሁለተኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ወዲህ መታየት መጀመራቸውንና በተባሉት ሰዎች የተጻፉ አለመሆናቸውን ለዘብተኛም ሆነ አጥባቂ የሥነ መለኮት ሊቃውንት ያለ ልዩነት በአንድ ድምፅ የሚስማሙበት እውነታ ነው፡፡
የቀኖና ምርጫ በአንድ ጀንበር የተከናወነ አልነበረም፡፡ ክርስትና እጅግ ሰፊ በነበረው የሮም ግዛት ውስጥ በመሰራጨቱ ምክንያትና ከበረታው ስደት የተነሳ አንዳንድ መጻሕፍት በሁሉም ስፍራዎች አይታወቁም ነበር፡፡ እነዚህ መጻሕፍት በመላው ክርስቲያን ማሕበረሰብ ዘንድ የተዳረሱት የስደቱ ዘመን ካበቃ በኋላ ሲሆን በጣም ርቀው ይገኙ የነበሩት የተሟላውን ቀኖና ለማግኘት ረጅም ጊዜ ወስዶባቸው ነበር፡፡ እያንዳንዱ የክርስቲያን ማሕበረሰብ መጻሕፍቱን ለመቀበል የየራሱን የማጣራት ሥራ ይሠራ ስለነበር አንዳንድ መጻሕፍት በሁሉም ክርስቲያኖች ዘንድ ወጥ በሆነ ሁኔታ ተቀባይነትን አላገኙም ነበር፡፡ ይህም ደግሞ ሐዋርያዊ ሥልጣን የሌላቸው መጻሕፍት ሾልከው እንዳይገቡ ቤተ ክርስቲያንን ጠብቋታል፡፡
በ170 ዓ.ም. የተጻፈው የሙራቶራውያን ቁርጥራጭ (The Moratorian Fragment) በመባል የሚታወቀው ጥንታዊ ጽሑፍ ደግሞ አራቱ ወንጌላት፣ አሥራ ሦስቱ የጳውሎስ መልዕክታት፣ የይሁዳ መልዕት፣ ሦስቱ የዮሐንስ መልዕክታትና የዮሐንስ ራዕይ በክርስቲያኖች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት እንደነበራቸው ይገልጻል፡፡[5] የቤተ ክርስቲያን ጸሐፌ ታሪክ የነበረው የቂሣርያው ኢዮስቢዮስ (265-340 ዓ.ም.) የቀኖና መጻሕፍትን በሦስት ከፍሎ አቅርቦ ነበር፡፡
- ቀኖናዊነታቸው ከጥርጣሬ በፀዳ ሁኔታ ተቀባይነት ያገኙ 22 መጻሕፍት ሲሆኑ እነዚህም አራቱ ወንጌላት፣ የሐዋርያት ሥራ፣ የጳውሎስ መልዕክታት (ዕብራውያንን ጨምሮ)፣ 1ዮሐንስ፣ 1ጴጥሮስ እና የዮሐንስ ራዕይ ናቸው፡፡
- አምስቱ ከፍተኛ ተቀባይነት የነበራቸው ሲሆን ጥቂቶች ብቻ ይጠራጠሯቸው ነበር፤ እነዚህም ያዕቆብ፣ ይሁዳ፣ 2ጴጥሮስ፣ 2ዮሐንስ እና 3ዮሐንስ ናቸው፡፡
- አምስቱ ላይ ከፍተኛ ጥርጣሬ ነበር፤ እነርሱም የሔርማሱ እረኛ፣ የጳውሎስ ሥራ፣ ራዕየ ጴጥሮስ፣ የበርናባስ መልዕክት[6] እና ዲዳኬ ናቸው (እነዚህ በአዲስ ኪዳን ቀኖና ውስጥ አልተካተቱም)፡፡[7]
በምስራቅ ሃያሰባቱን የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት በቀኖናዊነት ለመጀመርያ ጊዜ የጠቀሰው ቅዱስ አትናቴዎስ ሲሆን (367 ዓ.ም.) በምዕራብ ደግሞ በሂፖ ሬጊዩስ (አልጄርያ) (393 ዓ.ም.) እና በካርታጎ (397 & 419 ዓ.ም.) እነዚሁ መጻሕፍት ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡ የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት የዮሐንስን ራዕይ የተቀበሉት ዘግይተው ሲሆን የሦርያ ቤተ ክርስቲያን 2ጴጥሮስ፣ 2ዮሐንስ፣ 3ዮሐንስ እና ይሁዳን ለመቀበል ከሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ዘግይታለች፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ቤተ ክርስቲያኒቱ ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ርቃ የምትገኝ ስለነበረችና እነዚህ መጻሕፍት ስላልደረሷት ነበር፡፡
ቤተ ክርስቲያን ቀኖናዊ መጻሕፍቷን እንድታስታውቅ ያደረጓት የተለያዩ ሁኔታዎች ነበሩ፡፡ ዋነኛው ምክንያት ግን ኑፋቄያዊ ቡድኖች የየራሳቸውን የመጻሕፍት ስብስብ ማዘጋጀታቸው ነበር፤ (ለምሳሌ ያህል መርቂያን/ ማርሲዮን)፡፡ [8]
ክርስቲያኖች የአዲስ ኪዳንን መጻሕፍት በቀኖናዊነት ለመቀበል የተለያዩ መስፈርቶችን በጥንቃቄ ተጠቅመዋል፡፡ የመጀመርያው መስፈርት “ሐዋርያዊ ሥልጣን” የሚል ነበር፡፡ ይህም አንድ መጽሐፍ ተቀባይነት ማግኘት ያለበት በሐዋርያትና በቅርብ ወዳጆቻቸው የተጻፈ እንደሆነ ነው፡፡ ሉቃስና ማርቆስ ከሐዋርያት ጋር የቀረበ ግንኙነት ስለነበራቸው መጻሕፍታቸው ተቀባይነትን አግኝተዋል፡፡ ሁለተኛው መስፈርት ደግሞ የመጻሕፍቱ ከሌሎች የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ጋር መስማማት ሲሆን ሦስተኛው መስፈርት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለተከታታይ ዘመናት ተቀባይነትን አግኝተው ጥቅም ላይ መዋላቸው ነው፡፡
የቀደሙት ክርስቲያኖች ቀኖናዊ መጻሕፍትን ለመወሰን ጊዜ መውሰዳቸው ሐዋርያዊ ሥልጣን የሌላቸው መጻሕፍት ሾልከው እንዳይገቡ የነበራቸውን ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያሳይ ነው፡፡ እነዚህን መጻሕፍት በአንድ ጥራዝ የመሰብሰቡ ሂደት ጊዜ የወሰደ ቢሆንም ነገር ግን ተቀባይነት ያገኙት በአንድ ጀንበር አዋጅ ሳይሆን ከሐዋርያት ዘመን ተያይዞ በመጣ ሁኔታ ነበር፡፡
ጉባኤዎችም ሆኑ ግለሰቦች ቀኖናን አልፈጠሩም፡፡ ይልቁኑ እውነተኛ ቅዱሳት መጻሕፍት መሆናቸው በዘመናት ተፈትኖ ለተረጋገጡት መጻሕፍት ዕውቅናን ሰጡ እንጂ፡፡[9] ሃቁ ይህ ሆኖ ሳለ ሙስሊም ሰባኪያን የሌሉና ያልተደረጉ የፈጠራ ታሪኮችን በመጻፍ ክርስቲያኖችን ግራ ለማጋባትና የገዛ ሃይማኖታቸውን ህልውና ለማረጋገጥ ሲውተረተሩ ማየት የተለመደ ነው፡፡
-
ሙስሊሞችና መጽሐፍ ቅዱስ
አቶ ሐሰን በዚህ መጽሐፋቸው ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን በተመለከተ እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ ሁለት አቋሞችን አንፀባርቀዋል፡፡ የመጀመርያው አቋም ብሉይም ሆነ አዲስ ኪዳናት በቁርኣን ውስጥ ከተጠቀሱት ተውራትና ኢንጂል ጋር ምንም ዓይነት ዝምድና የሌላቸው የኋለኞቹ ዘመናት ጽሑፎች ናቸው የሚል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የተበረዙ ተውራትና ኢንጂል ናቸው የሚል ነው፡፡ የመጀመርያውን አቋም በተደጋጋሚ እንዲህ አንፀባርቀዋል፡-
- አሁን በክርስትያኖች እጅ የሚገኘው ብሉይ ኪዳን ለሙሣ የወረደው ተውራት ነው ማለት አይደለም፡፡ ሙሣ ከሞቱ ከብዙ ምእተ አመታት በኋላ ማንነታቸው በውል በማይታወቁ ሰዎች ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የቆየውን አፈ ታሪክ መሠረት አድርገው የጻፉት የግለሰቦች ድርሰት እንጅ ለሙሣ የወረደላቸው መልእክት አይደለምና … (ገፅ 47)
[ማሳሰብያ፡- ቁርኣን ሙሣ መጽሐፍን ከአላህ ስለመቀበሉ እንጂ ተውራት የተሰኘ መጽሐፍ ከአላህ ስለመቀበሉ በአንድም ቦታ አልተናገረም፡፡ አቶ ሐሰን አባባላቸውን በማስረጃ እንዲያረጋግጡልን እንፈልጋለን፡፡ ተውራት (በእብራይስጥ ቶራህ ወይም ሕግ) የሚለው ቃል አምስቱን የሙሴ መጻሕፍት ለማመልከትም ሆነ አጠቃላዩን ብሉይ ኪዳን ለማመልከት ጥቅም ላይ ውሏል (ዮሐ. 10፡34፣ 12፡34፣ 15፡25፣ ሮሜ 3፡10-19፣ 1ቆሮ. 14፡21)፡፡ ስለዚህ ቁርኣን ተውራት የሚለውን ቃል ከሙሴ ጋር አለማያያዙ ይህንን ቃል አጠቃላዩን ብሉይ ኪዳንን ለማመልከት መጠቀሙን የሚያሳይ አንድ ማስረጃ ነው፡፡]
- ብሉይ ኪዳን የአምላክ ቃል ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም፡፡ ከአላህ ዘንድ ለሙሣ የተሰጣቸውን ተውራትም አይወክልም … እናም ሙስሊሞች በተውራት እናምናለን ማለት በብሉይ ኪዳን እናምናለን ማለት እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ (ገፅ 48)
- አዲስ ኪዳን ለኢሣ የተወረደላቸውን ኢንጂል አይወክልም፡፡ እርሳቸው ካረጉ በኋላ እስከ 125 ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ ከኢሣ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት በሌላቸው ግለሰቦች የተከተቡ የግል ደብዳቤዎችና ድርሳናት ናቸው፡፡ (ገፅ 48)
[ማሳሰብያ፡- ኢየሱስ ኢንጂል (ወንጌል) እንደወረደለት የሚናገሩት ብቸኛ ምንጮች እስላማዊ መጻሕፍት ናቸው፡፡ ለዒሳ የወረደለት ኢንጂል የተሰኘ ከአራቱ ወንጌላት የተለየ መጽሐፍ መኖሩን ታሪካዊ ማስረጃ በመጥቀስ እንዲያረጋግጡልን አቶ ሐሰን ይጠየቃሉ፡፡]
- እነዚህ የግል ሐሳቦችና ደብዳቤዎች ናቸው ከጊዜ በኋላ ‹ወንጌል› ተሰኝተው ‹ቅዱስ› የተደረጉት፡፡ (ገፅ 51)
- …ስለዚህ ለኢሣ ከወረደው ኢንጂል ጋር ዝምድና የላቸውም፡፡ ቁርኣን በኢንጂል እመኑ ሲል ማርቆስ፣ ማቲዮስ ሉቃስ፣ ዮሐንስ እና ጳውሎስ የተባሉ ግለሰቦች ከእየሱስ ከብዙ አስርት አመታት በኋላ ለግል ጉዳዮቻቸው በጻፏቸው እና በአሁኑ ሰአት ኦሪጅናል ይዘታቸው በጠፋው የግል ደብዳቤዎች እመኑ ማለት እንዳልሆነ ግልፅ ሊሆን ይገባል፡፡ (ገፅ 51)
የአዲስ ኪዳንና የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ከጅምራቸው መለኮታዊ መሆናቸውን ከካዱና ከሙሴም ሆነ ከኢየሱስ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌላቸው በአፅንዖት ከገለፁ በኋላ ይህንን ሐሳባቸውን በማጠፍ እዲህ ብለው ጽፈዋል፡-
- … ቁርኣን ጥንት መለኮታዊ ከነበሩና በኋላ ላይ የሰው እጅ ገብቶባቸው ከተበረዙትና ኦሪጅናል ይዘታቸውን ካጡት መጽሐፍት (አዲስ ኪዳን፣ ብሉይ ኪዳንና ሌሎችም) በተያያዘ ሚናውን መግለፅ ጠቃሚ ነው፡፡ (ገፅ 83)
የጸሐፊው አቋም እርስ በርሱ የተምታታ ነው፡፡ አዲስ ኪዳንና ብሉይ ኪዳን ከሙሴም ሆነ ከኢየሱስ ጋር ግንኙነት ባልነበራቸው ግለሰቦች የተጻፉ ከጅምራቸው መለኮታዊ ያልነበሩ መጻሕፍት እንደሆኑ ከገለፁ በኋላ የለም ተበርዘው ነው እንጂ መጀመርያ መለኮታዊ መጻሕፍት ነበሩ ይሉናል፡፡ የቱ ነው ትክክል? መጀመርያ መለኮታዊ መጻሕፍት ነበሩ ወይስ አልነበሩም?
የመጀመርያውን አቋም ይደግፍልኛል ያሏቸውን “ማስረጃዎች” እንደተለመደው ከለዘብተኛ የሥነ መለኮት ምሑራንና ከኢንሳይክሎፒድያ ላይ በመቀነጫጨብ ይጀምራሉ (ገፅ 47)፡፡ ምንጮቹን በታማኝት መተርጎማቸውን ወይም በትክክል መጥቀሳቸውን ለማወቅ የሚያስችል የተሟላ ማጣቀሻ ስላልሰጡ ምሑራን ተናግረውታል በማለት የጠቀሷቸውን አባባሎች ለማመን የሚያስችል ምንም ምክንያት የለም፡፡ ከዚያም ከዚህም በመለቃቀም በየቦታው ለሚጥፏቸው “የምሑራን” ንግግሮች ቦታ እንድንሰጥ ከፈለጉ ምንጮቹን በትክክል እንዲጠቅሱ እንጠይቃቸዋለን፡፡
-
የሉቃስ ተዓማኒነት
የመጽሐፍ ቅዱስን ጸሐፊያንና የተጻፈበትን ዘመን በተመለከተ ቀደም ሲል መልስ የሰጠንባቸውን ነጥቦች ከደገሙ በኋላ የሉቃስ ወንጌል መግቢያ ላይ የተጻፈውን ቃል በመጥቀስ ወንጌሉን ይተቻሉ፡፡
“የከበርህ ቴዎፍሎስ ሆይ፥ ከመጀመሪያው በዓይን ያዩትና የቃሉ አገልጋዮች የሆኑት እንዳስተላለፉልን፥ በኛ ዘንድ ስለ ተፈጸመው ነገር ብዙዎች ታሪክን በየተራው ለማዘጋጀት ስለ ሞከሩ፥ እኔ ደግሞ ስለ ተማርኸው ቃል እርግጡን እንድታውቅ በጥንቃቄ ሁሉን ከመጀመሪያው ተከትዬ በየተራው ልጽፍልህ መልካም ሆኖ ታየኝ፡፡” (ሉቃስ 1፡1-4)
ከወንጌላዊው አባባል በመነሳት ተከታዮቹን ሒሶች ሰንረዋል፡-
- በርሱ ዘመን በርካታ ሰዎች የየራሳቸውን ወንጌል ይጽፉ ነበር፡፡ በክርስትና የመጀመርያ ክፍለ ዘመን ወንጌሎች እንደ አሸን የፈሉበት ሁኔታ ነበር፡፡
- ሉቃስ ጽሑፉን የጻፈው ‹የጌታ ቃል› ብሎ ሳይሆን ለባልንጀራው የግል ደብዳቤ ነው፡፡
- የጻፈው ‹መልካም ሆኖ ታየኝ› በሚል የግል ተነሳሽነት ሲሆን ሁሉንም ነገር ከመጀመርያው ጀምሮ በመከታተል በግል ጥረቱ እንጅ በመንፈስ ተሞልቶ አይደለም፡፡
- ሉቃስ ደብዳቤው ከዘመናት በኋላ ወንጌል ይሆናል ብሎ ፈጽሞ አላሰበም፡፡ ለጓደኛው እርግጡን ያውቅ ዘንድ ሲል ነው የጻፈለት፡፡ (ገፅ 48-49)
የመጀመርያው ነጥብ መልስ እንኳ የሚያሻው አይደለም፡፡ የወንጌላት በጽሑፍ መስፈር ክፉ ነገር ይመስል አቶ ሐሰን “እንደ አሸን” እንደፈሉ መናገራቸው አስገራሚ ነው፡፡ የክርስቶስ ታሪክና ትምህርቶች ላልሰሙት ይደርሱ ዘንድ በምስክሮች በጽሑፍ መስፈራቸው ምኑ ላይ ነው ክፋቱ? በእርግጥ ጽሑፎቹ የክርስቶስን ታሪክ ለማስተማር በወቅቱ ማገልገላቸውን መናገር ይቻላል፡፡ ነገር ግን የክርስቶስን ታሪኮች ለመጻፍ የተደረጉ ሙከራዎች መሆናቸውን እንጂ እንደ አራቱ ወንጌላት በሐዋርያት እጅና ዕውቅና የተጻፉ ስለመሆናቸው ማረጋገጫ መስጠት አይቻልም፡፡ ሉቃስ እነዚህን ጽሑፎች “ወንጌላት” ብሎ አልጠራቸውም፡፡ ነገር ግን አሁን በእጃችን ከሚገኙት ወንጌላት የተለየ መረጃ ሊሰጡን እደማይችሉ እርግጠኞች ሆነን መናገር እንችላለን፡፡ ሉቃስ የጠቀሳቸው ጽሑፎች ይዘት እርሱ ከጻፈው የተለየ ቢሆን ኖሮ ባልጠቀሳቸው ነበር፡፡
ከሁለተኛው ነጥብ በኋላ ያሉት ሙግቶች ጸሐፊው ስለ ቅዱሳት መጻሕፍት መገለጥ ያላቸው ግንዛቤ እስላማዊ በመሆኑ ይህንኑ አመለካከታቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለመጫን መሞከራቸውን የሚያሳዩ ናቸው፡፡
ሙስሊሞች ቁርኣን “የተገለጠበትን” ሁኔታ ተንዚል ወይም ናዚል በማለት ይጠሩታል፡፡ ተንዚል ማለት “ከላይ የወረደ መገለጥ” ማለት ነው፡፡ ከጥንት ጀምሮ የነበረው ክርስቲያናዊ አመለካከት መጽሐፍ ቅዱስ ከላይ የወረደ መገለጥ ነው የሚል ሳይሆን የእግዚአብሔር ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ በመነዳት (በመመራት) የጻፉት ቃል ነው የሚል ነው፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ የነበራቸውን እውቀት፣ ባህልና ቋንቋ እንዲጠቀሙ መንፈስ ቅዱስ ፈቅዷል፡፡ ግልጠተ መለኮት ማለት ጸሐፊያኑ በጥንቃቄ የተሞሉ ምርመራዎችን በማድረግ አይጽፉም ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ ስለሚመራቸው ስህተቶችን አይፈጽሙም ማለት ነው፡፡
የጸሐፊው መነፅር እስላማዊ በመሆኑ በጎ ገፅታውን ማየት ተሳናቸው እንጂ የሉቃስ መግቢያ በወንጌሉ ላይ እንድንተማመን የሚያስችሉንን ተከታዮቹን መልዕክቶች የሚያስተላልፍ ነው፡-
- ሉቃስ ምሑራዊ የመግቢያ አጻጻፍ መጠቀሙ ወንጌሉ በታሪክ ምሑራን ዘንድ ከፍተኛ ግምት እንዲሰጠው አድርጓል፡፡
- መረጃዎቹን ያገኘው የዓይን ምስክሮችና የቃሉ አገልጋዮች ከነበሩት ከሐዋርያት ነው፡፡
- ሁሉንም ከመጀመርያው በጥንቃቄ መርምሯል፡፡
- አመክንዮአዊ ቅደም ተከተሉን በጠበቀ ሁኔታ ጽፏል፡፡
- ይህንን ያደረገው ደግሞ የቴዎፍሎስ እምነት በማስረጃ የተረጋገጠ እንዲሆን ነው፡፡
ተከታዮቹ ነጥቦች የሉቃስ ወንጌል ኢየሱስን በተመለከተ አስተማማኝ ምንጭ መሆኑን ያሳያሉ፡-
-
ወንጌሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከብሉይ ኪዳን እኩል ደረጃ ተሰጥቶታል
የመጀመርያዎቹ ክርስቲያኖች የሉቃስን ወንጌል እንደ ቃለ እግዚአብሔር በመቀበል መስክረውለታል፡፡ ለምሳሌ ያህል ሐዋርያው ጳውሎስ ሙሴ የጻፈውንና ሉቃስ የጻፈውን አንድ ላይ አጣምሮ በመጥቀስ ሁለቱም መጻሕፍት እኩል ቅዱሳት መጻሕፍት መሆናቸውን አረጋግጧል፡፡
“መጽሐፍ፦ የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር፥ ደግሞ፦ ለሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋል ይላልና፡፡” 1ጢሞቴዎስ 5፡18፡፡
“የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር” የሚለው ዘዳግም 25፡4 ላይ የሚገኝ ሲሆን “ለሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋል” የሚለው ደግሞ ሉቃስ 10፡7 ላይ ይገኛል፡፡ ይህ የሚያሳየን የሐዋርያት ዘመን ከማለፉ በፊት የሉቃስ ወንጌል ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት እኩል ተቀባይነት ማግኘቱን ነው፡፡ ሐዋርያው እንደ ዘዳግም ሁሉ የሉቃስ ወንጌልን በስም ሳይጠቅስ ‹መጽሐፍ› (Scripture) ብሎ መጥራቱ በወቅቱ የሉቃስ ወንጌል በክርስቲያኑ ማሕበረሰብ ዘንድ በሚገባ የሚታወቅ እንደነበረ ከማሳየቱም በላይ የቅዱሳት መጻሕፍት አካል ተደርጎ መቆጠሩን ያሳያል፡፡ ስለዚህ የሉቃስ ወንጌል መለኮታዊ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ እራሱ አረጋግጧል ማለት ነው፡፡[10]
-
ወንጌሉ የጌታ ሐዋርያት በሕይወት በነበሩበት ዘመን የተጻፈ በመሆኑ ተዓማኒ ነው
የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት መቼ እንደተጻፉ ለማወቅ የተለያዩ ውጭያዊና ውስጣዊ መረጃዎችን ይጠቀማሉ፡፡ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የሉቃስ ወንጌል ሁለተኛ ክፍል መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ዝርዝር ታሪካዊ ክስተቶችን በማካተቱ ምክንያት መቼ እንደተጻፈ ለማወቅ የሚያስችሉ በቂ መረጃዎችን ይሰጣል፡፡ በአጠቃላይ ለዘብተኛ እንዲሁም አጥባቂ ከሆኑት ሊቃውንት መካከል የሚበዙቱ የሐዋርያት ሥራ ከ63 ዓ.ም. በፊት የተጻፈ መሆኑን ይስማማሉ፡፡ ኮሊን ሐመር የተሰኙ የሮም ታሪክ ሊቅ የሐዋርያት ሥራ በ61 እና 62 ዓ.ም መካከል የተጻፈ መሆኑን የሚያሳዩ 17 ምክንያቶችን ዘርዝረዋል፡፡[11] ወንጌሉ ደግሞ ቀደም ሲል የተጻፈ በመሆኑ (ሉቃስ 1፡1 እና የሐዋርያት ሥራ 1፡1 ያነፃፅሩ) ቢያንስ ከ61 ዓ.ም. በፊት እንደተጻፈ መናገር ይቻላል፡፡ ወንጌሉ ሐዋርያትና የመስቀሉ ትውልድ በሕይወት በነበሩበት ዘመን ስለተጻፈ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ማንነትና ሥራ ለማወቅ አስተማማኝ ምንጭ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡
-
የሉቃስ ተዓማኒነት በዓለማውያን የታሪክ ሊቃውንት ሳይቀር የተመሰከረለት ነው
ሰር ዊልያም ራምሰይ የተባሉ እንግሊዛዊ የታሪክ ምሑር የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ተዓማኒነት እንደሌላቸው የሚያምኑ ሰው ነበሩ፡፡ በተለይም ደግሞ የሉቃስ ጽሑፍ የሆነው የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የሁለተኛው ክፍለ ዘመን ሥራ እንደሆነ አጥብቀው ያምኑ ነበር፡፡ እኚህ ምሑር በትንሹ ኢስያ (Asia Minor) ውስጥ የተለያዩ የሥነ ቁፋሮ ግኝቶችን ሲመረምሩ ሳሉ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው የሚገኙ ብዙ ነገሮች እውነት መሆናቸውን የሚያረጋግጡ የትየለሌ ማስረጃዎችን አገኙ፡፡ ከዚህ የተነሳ ሉቃስ መጽሐፉን የጻፈው በመጀመርያው ምዕተ ዓመት (ሐዋርያት በነበሩበት ዘመን) መሆኑን ብቻ ሳይሆን ሉቃስ ከታላላቅ የታሪክ ጸሐፊያን መካከል መመደብ እንደሚገባውም ተናግረዋል፡፡[12]
ሌላው አቶ ሐሰን ያነሱት ነጥብ ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ዘመን ሉቃስ ደቀ መዝሙር ያለመሆኑን ጉዳይ ነው (ገፅ 49)፡፡
አንድ ሰው ቅዱሳት መጻሕፍትን ለመጻፍ የግድ ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ዘመን የእርሱ ተከታይ መሆን እንዳለበት የሚገልፅ ነገር በመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ በቀደሙት ክርስቲያናዊ ጽሑፎች ውስጥ አልተጠቀሰም፤ ምናልባት አቶ ሐሰን ዛሬ አዲስ መስፈርት ካላወጡልን በስተቀር፡፡ የሉቃስ ጽሑፍ የኢየሱስ ሐዋርያት በሆኑት በማቴዎስና በዮሐንስ ከተጻፉት ወንጌላት ጋር ስለሚስማማ ሐዋርያ አለመሆኑ የኢየሱስን ታሪክና ትምህርቶች በትክክል ከመመዝገብ እንዳልከለከለው ማረጋገጥ ይቻላል፡፡
-
የማቴዎስ ወንጌል ተዓማኒነት
አቶ ሐሰን በማቴዎስ ወንጌል ተዓማኒነት ላይ ተከታዮቹን ሒሶች ሰንዝረዋል፡-
ማቲዮስ ወንጌሉን የጀመረው ስለ እየሱስ ትውልድ በመተረክ ሲሆን ‹ከአምላክ በእይ ተገለፀልኝ› የሚል መልእክት አላሠፈረም…
የጸሐፊው ማንነት አይታወቅም፡-
‹ወንጌሉን የጻፈው ማቲዮስ ነው ያሉት የቀደሙ የቤተክርስትያን አባቶች ናቸው እንጅ የጸሐፊው ስም አልተጻፈበትም፡፡ መች እንደተጻፈ ደግሞ አልታወቀም፡፡› (የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፣ የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር፣ ገፅ 41) (ገፅ 49)
አቶ ሐሰን ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ላይ በቀጥታ የጠቀሱ በማስመሰል በትዕምርተ ጥቅስ ያስቀመጡት በመጽሐፉ ውስጥ በዚህ መልኩ አይገኝም፡፡ ለንፅፅር እነሆ፡-
“እንደ ጥንት ቤ.ክ. ትውፊት የመጀመርያውን ወንጌል የጻፈው ማቴዎስ ነው፡፡ ዛሬ አንዳንድ ሊቃውንት ይህን ሐሳብ ባይቀበሉትም የወንጌሉ አጻጻፍ በጥንቃቄ ከሚጽፍና ከሚሠራ ወደ ወንጌላዊነት ከተለወጠ ቀራጭ አሠራር ጋር ይስማማል፡፡ የማቴዎስ ወንጌል የተጻፈባቸው ዘመናት በብዙ ሊቃውንት የተለያዩ እንደሆኑ ቢጠቀስም አንዳንዶች ማቴዎስ ወንጌሉን የጻፈው ከ50 ዓ.ም. በፊት እንደሆነ ሲያመለክቱ ሌሎች ግን ጸሐፊው የማርቆስን ወንጌል ተመልክቶ ኢየሩሳሌም ከወደቀችበት ከ70 ዓ.ም. በኋላ እንዳዘጋጀው ይናገራሉ፡፡”[13]
ሜሪል ሲ. ቴኒ ደግሞ እንዲህ ይላሉ፡-
“በወንጌሉ ውስጥ ማቴዎስ ጸሐፊው እንደሆነ አልተናገረም፡፡ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊዎች ማቴዎስ እንደጻፈው ግን አረጋግጠዋል፡፡ … የመጀመርያውን ወንጌል መነሻ በተመለከተ ከእነኚህ ጥንታዊ ገለፃዎች ብዙ ማጠቃለያ አሳቦች ማግኘት ይቻላል፡፡ አንደኛ የማቴዎስ ጸሐፊነት የሚያከራክር አይደለም፤…”[14]
ማቴዎስ ከአሥራ ሁለቱ የጌታ ሐዋርያት መካከል አንዱ በመሆኑ የክርስቶስን ሕይወትና ትምህርት በታማኝነት በጽሑፍ ለማስፈር ብቁ ነው (ማቴ. 9፡9፣ 10፡3፣ ማር. 3፡18፣ ሉቃ. 6፡15፣ ሐዋ. 1፡13)፡፡ ስለዚህ የጸሐፊው ማንነት አይታወቅም የሚለው የኡስታዙ አባባል ከእውነት የራቀ ነው፡፡
-
የማርቆስ ወንጌል ተዓማኒነት
በማርቆስ ወንጌል ተዓማኒነት ላይ ተከታዮቹን ሒሶች ሰንዝረዋል፡-
ማርቆስ ወንጌሉን ‹ተገለጸልኝ› በማለት አልጀመረም፡፡ ባይሆን ለመጀመርያ ጊዜ የግል ጽሑፉን ወንጌል ብሎ ሲጠራው እናነባለን፡፡ ማርቆስ የእየሱስ ተማሪ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ የጸሐፊው ማንነትም አይታወቅም፡-
‹ከሌሎች ጋር ሲነጻጸር ስለዚህኛው ወንጌል ጸሐፊ ብዙ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ መጽሐፉ በየትኛውም ስፍራ ስሙን አይጠቅስም› (ሜሪል ሲ. ቴኒ፣ የአዲስ ኪዳን ቅኝት፣ ገፅ 236)
ቴኒ የተናገሩት ከሌሎች ጋር በተነጻጻሪነት ስለ ማርቆስ ብዙም እንደማይታወቅ እንጂ አቶ ሐሰን እንደተናገሩት ማንነቱ እንደማይታወቅ አይደለም፡፡ በንጽጽር መናገርና በሌጣ መናገር የተለያዩ ናቸው፡፡ ቴኒ በማስከተል እንደጻፉት ማርቆስን የተመለከተ በ115 ዓ.ም. የተነገረ ከፓፒያስ የተገኘ መረጃ ኢዮስቢዮስ (375 ዓ.ም.) በጻፈው ጽሑፍ ውስጥ ተጠብቋል፡፡ ይህ መረጃ በቀዳሚነት የተላለፈው ከሐዋርያው ዮሐንስ ሲሆን፤ ማርቆስ የጴጥሮስ አስተርጓሚ የነበረ መሆኑን፤ መረጃዎቹን ሳይጨምርና ሳይቀንስ ያለ አንዳች ስህተት በታላቅ ጥንቃቄ መጻፉን መስክሯል፡፡[15] የጸሐፊውን ማንነት በተመለከተ አበው ስለሰጡት መረጃ ተዓማኒነት ቴኒ እንዲህ ይላሉ፡
“የእነኚህ ታሪኮች አስተማማኝነት አጠያያቂ ሊሆን አይችልም፡፡ የሁለተኛው ወንጌል ጸሐፊ ማርቆስ መሆኑን ሁሉም ተስማምተዋል፤ ወንጌሉንም ከጴጥሮስ ስብከት ጋር ያያይዙታል፡፡”[16]
መጽሐፍ ቅዱስ ማርቆስን በተመለከተ ተከታዮቹን መረጃዎች ይሰጠናል፡-
- የማርቆስ ሌላኛው ስም ዮሐንስ ነው (ሐዋ. 12፡25)፡፡
- የሐዋርያት ወዳጅ የሆነችው የኢየሩሳሌሟ ማርያም ልጅ ነው (ሐዋ. 12፡12)፡፡
- ክርስቲያኖች በቤታቸው ለጸሎት ይሰበሰቡ ነበር (ሐዋ. 12፡12)፡፡
- የበርናባስ የወንድሙ ልጅ ነው (ሐዋ. ቆላ. 4፡10-11)፡፡
- ጳውሎስና ወዳጁ በርናባስ ለስብከተ ወንጌል በወጡበት ወቅት ረዳት በመሆን ከአንፆኪያ ወደ ትንሹ ኢስያ አብሯቸው ተጉዞ ነበር (ሐዋ. 13፡5፣ 15፡37-38)፡፡
- ነገር ግን ሥራውን ሳይፈፅም በመመለሱ ምክንያት ጳውሎስ ተቀይሞት ነበር (ሐዋ. 15፡37-38)፡፡
- ከጳውሎስ ከተለየ በኋላ በርናባስ ከአንፆኪያ ወደ ቆጵሮስ ይዞት ሄዶ ነበር (ሐዋ. ሐዋ. 15፡39)፡፡
- ኋላ ላይ ስለተስማሙ በአገልግሎት እንዲረዳው ጳውሎስ ወደ ሮም ጠርቶታል (2ጢሞ. 4፡11፣ ፊል. 1፡24)፡፡
- የሐዋርያው ጴጥሮስ መንፈሳዊ ልጅ ነበር (1ጴጥ. 5፡13)፡፡
ታድያ ይህ ሁሉ መረጃ ባለበት ማንነቱ አይታወቅም እንዴት ይባላል?
አቶ ሐሰን የወንጌል ጸሐፊያን “ተገለጠልኝ” በማለት አለመጀመራቸውን ደጋግመው መጥቀሳቸው የረባ የሙግት ግብአት ሊሆን አይችልም፡፡ አንድ ሰው “ተገለጠልኝ” ብሎ ጽሑፍ መጀመሩ መገለጥ መቀበሉን እንደማያመለክት ሁሉ እንደርሱ ብሎ አለመጀመሩም አለመቀበሉን አያመለክትም፡፡
-
የዮሐንስ ተዓማኒነት
በዮሐንስ ወንጌል ተዓማኒነት ላይ ተከታዮቹን ሒሶች ሰንዝረዋል፡-
ዩሐንስ ወንጌሉን የጻፈው ለተለየ ዓላማ መሆኑን በግልፅ ያስቀምጣል፡፡ እርሱም እየሱስ የአምላክ ልጅ መሆኑን ለማሳመን ነው፡፡ በዩሐንስና በሌሎች ጸሐፊዎች ድርሳናት መካከል የእሳትና የጭድ አይነት ልዩነት ስለመኖሩ ምእራባው የሐይማኖት ሊቃውነት የሰጡትን ምስክርነት ከዚህ ቀደም ማስፈራችን ይታወሳል… (ገፅ 49-50)
አቶ ሐሰን “ማስረጃ” በማለት የጠቀሷቸው ሐሳቦች ሁሉ መሠረተቢስ አሉባልታዎች መሆናቸውን ቀደም ሲል ስላረጋገጥን አንደግምም፡፡ አቶ ሐሰን “እከሌ እንዲህ አለ፣ እንትን የሚል መጽሐፍ እንዲህ ይላል” ከሚል ያልተጨበጠ ሰበካ በዘለለ ዮሐንስና ሌሎች ወንጌላት “እሳትና ጭድ” መሆናቸውን የሚያሳይ ማስረጃ ሊሰጡ አልቻሉም፡፡ በማስከተል እንዲህ የሚል አስገራሚ ነገር ጽፈዋል፡-
ዮሐንስ የእየሱስ ተማሪ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ ማንነቱም በውል አይታወቅም፡፡ (ገፅ 50)
ጉድ! ዮሐንስ ለኢየሱስ እጅግ የቀረበ ሐዋርያ እንደነበረ የማያውቅ ለክርስትና መልስ ለመስጠት መጽሐፍ የጻፈ የመጀመርያው ሰው አቶ ሐሰን ሳይሆኑ አይቀሩም፡፡ ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት መካከል ከጴጥሮስ ቀጥሎ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተደጋጋሚ የተጠቀሰው የጌታ ሐዋርያ ዮሐንስ ነው፡፡
- ዮሐንስ የአባቱ ስም ዘብዴዎስ ነው፡፡ ዓሣ ሲያጠምዱ ሳሉ እርሱንና ወንድሙ ያዕቆብን ኢየሱስ እንዲከተሉት ጠራቸው (ማቴ. 4፡21፣ ማር. 1፡19)፡፡
- ቦአኔርጌስ (የነጎድጓድ ልጆች) በሚል ቅፅል ይጠራቸው ነበር (ማር. 3፡17)፡፡
- በደብረ ታቦር ተራራ ላይ የኢየሱስን መለኮታዊ ክብር አይቷል (ማቴ. 17፡1፣ ማር. 9፡2፣ ሉቃ. 9፡28)፡፡
- ኢየሱስ ይወደው የነበረ ሐዋርያ እንደሆነ ተገልጿ (ዮሐ. 19፡26-27)፡፡
- በጌቴ ሰማኒ ከኢየሱስ ጋር ነበር (ማር. 14፡33)፡፡
- በኢየሱስ መስቀል አጠገብ ነበር (ዮሐ. 19፡26-27)፡፡
- ከጴጥሮስ ጋር ወንጌልን ይሰብክ ነበር (ሐዋ. 3፡1-4፡13፣ 8፡14)፡፡
እኔ ባደረኩት ቆጠራ መሠረት የሐዋርያው ዮሐንስ ስም በአዲስ ኪዳን ውስጥ ወደ 30 ጊዜ ተጠቅሷል፡፡ ቁርኣን ሙሐመድን ከሚያውቃቸው በላይ መጽሐፍ ቅዱስ ሐዋርያው ዮሐንስን ያውቀዋል፡፡ የሙሐመድ ስም በቁርኣን ውስጥ የተጠቀሰው 4 ጊዜ ብቻ ነው፡፡
-
የጳውሎስ ተዓማኒነት
በማስከተል ደግሞ ያልተገራ ሒሳቸውን የሰነዘሩት በሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ላይ ነው፡፡ እንዲህ ይላሉ፡-
ጳውሎስ በሕይወቱ ለአንድ ጊዜ እንኳ ከእየሱስ ጋር አልተገናኘም፡፡ ክርስትያኖችን በጠላትነት ሲያሳድድ ከቆየ በኋላ በድንገት ‹እየሱስ ተገለጠልኝ› አለና የክርስትና ሰባኪ መሆኑን አወጀ፡፡ መጀመርያ ላይ የእየሱስ ተማሪዎች ተጠራጥረውት ነበር፡፡ ባርናባስ በተባለ ደግ ሰው ማግባባት ነው የተቀበሉት…
የጳውሎስን ደብዳቤዎች በቅርበት ስናጠና የግል ጉዳዮቹን የጻፈባቸው ሆኖ እናገኛቸዋለን፡፡ በሰላምታ ይጀምራሉ፡፡ እገሌን እገሌን ሰላም በልልኝ፣ ሳምልኝ፣ በሚል ሰላምታ ይጠናቀቃሉ… (ገፅ 50-51)
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በዓለም ታሪክ ከተነሱት ታላላቅ ሰዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ የታዋቂው አይሁዳዊ ረቢ የገማልያል ተማሪ የነበረ ሲሆን በአይሁድ ሕግ ዕውቀት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ የተመሰከረለት ምሑር ነበር (ሐዋ. 22፡3)፡፡ የክርስትና ተቃዋሚና አሳዳጅ የነበረው ጳውሎስ በቅፅበት ተቀይሮ የኢየሱስ ተከታይ መሆኑ ክርስትና እውነት መሆኑን ከሚያሳዩ ማስረጃዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ የምድራዊ ጥቅማ ጥቅሞች ችግር ያልነበረበት ጳውሎስን የመሰለ አይሁዳዊ ምሑር ክርስቲያኖችን ለማሳደድ በቁጣ ተመልቶ ሲሄድ ሳለ አቋሙን ቀይሮ አማኝ በመሆን ምድራዊ ጥቅማ ጥቅሞችን ሁሉ ትቶ ስለ ክርስቶስ ሲል የድኽነት፣ የመከራና የስደትን ሕይወት መምረጡ፣ በመጨረሻም በሰማዕትነት ይህችን ምድር መሰናበቱ ያለ አንዳች ምክንያት አይደለም፡፡
የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ መልእክቶች በአንደኛው ክፍለ ዘመን ከብሉይ ኪዳን ጽሑፎች እኩል ተቀባይነት አግኝተው ነበር፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል፡-
“የጌታችንም ትዕግሥት መዳናችሁ እንደ ሆነ ቍጠሩ። እንዲህም የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስ ደግሞ እንደ ተሰጠው ጥበብ መጠን ጻፈላችሁ፥ በመልእክቱም ሁሉ ደግሞ እንደ ነገረ ስለዚህ ነገር ተናገረ፡፡ በእነዚያ ዘንድ ለማስተዋል የሚያስቸግር ነገር አለ፥ ያልተማሩትና የማይጸኑትም ሰዎች ሌሎችን መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ እነዚህን ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ” (2ጴጥ. 3፡15-16)፡፡
“As also in all his epistles, speaking in them of these things; in which are some things hard to be understood, which they that are unlearned and unstable wrest, as they do also the other scriptures, unto their own destruction.” (KJV)
ቅዱስ ጴጥሮስ ሐዋርያው ጳውሎስ እግዚአብሔር በሰጠው ጥበብ መጠን እንደጻፈ ከመናገሩም በላይ ጽሑፎቹን “መጻሕፍት” (Scriptures) በማለት በመጥራት ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት እኩል አስቀምጧቸዋል፡፡
ሙስሊም ወገኖች በሐዋርያው ጳውሎስ ላይ የከረሩ ትችቶችን መሰንዘራቸው ካለማወቅና ከአጉል ጥላቻ የመነጨ እንጂ በተጨባጭ ማስረጃ ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ እውነተኛ የክርስቶስ ተከታይ መሆኑን ጥንታውያን ሙስሊሞች መመስከራቸውን አቶ ሐሰን ቢሰሙ ምን ይሉ ይሆን? መቼስ ለገዛ መጻሕፍታቸው እንግዳ ስለሆኑ እኛው እናሳያቸው እንጂ!
ኢብን ኢስሐቅ የተሰኘው ቀዳሚውን የሙሐመድ ግለ ታሪክ የከተበ ሙስሊም እንዲህ ሲል ጽፏል፡-
“ዒሳ የመርየም ልጅ የላካቸው ደቀ መዛሙርትና ከእነርሱ በኋላ የመጡት በአገሪቱ ውስጥ የነበሩት እነዚህ ነበሩ፡- ደቀ መዝሙሩ ጴጥሮስና ከእርሱ ጋር ደግሞ ጳውሎስ ወደ ሮም ተላኩ፡፡ (ጳውሎስ ከተከታዮቹ መካከል ሲሆን ደቀ መዝሙር አልነበረም፡፡) እንድርያስና ማቴዎስ ወደ በላዔ-ሰብዕ ምድር፤ ቶማስ በምስራቅ ወደሚገኘው ወደ ባቤል ምድር፤ ፊልጶስ ወደ ካርቴጅና ወደ አፍሪካ፤ ዮሐንስ የዋሻዎቹ ወጣቶች ምድር ወደሆነው ወደ ኤፌሶን…”[17]
የኢብን ኢስሐቅ ጽሑፍ ሳሂህ አል-ቡኻሪና ሳሂህ ሙስሊምን ከመሳሰሉት ሐዲሳት እንኳ የሚቀድም የሙሐመድ ግለ ታሪክ ነው፡፡ በቅንፍ የተቀመጠው ሐዋርያው ጳውሎስ ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ደቀ መዝሙር እንዳልነበረ በትክክል የሚገልፅ በመሆኑ ስህተት የለበትም፡፡
የእስልምና ጀማሪ የሆኑት ሙሐመድ ሐዋርያው ጳውሎስ የጻፈውን ከጠቀሱ በኋላ የአላህ ቃል መሆኑን መመስከራቸውን ቢሰሙስ አቶ ሐሰን ምን ይውጣቸው ይሆን?
“ነገር ግን፦ ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው ተብሎ እንደተጻፈ፥ እንዲህ እንናገራለን” (1ቆሮንቶስ 2፡9)፡፡
ከላይ የተጠቀሰው ሐዋርያው ጳውሎስ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የተጠቀሱትን የእግዚአብሔርን ተስፋዎች በራሱ አባባል ጨምቆ ያስቀመጠበት ዓረፍተነገር ሲሆን ከእርሱ በሚቀድም በየትኛውም ምንጭ ውስጥ በዚህ መልኩ ተጽፎ አይገኝም፡፡ ሙሐመድ እንዲህ ጠቅሰውታል፡-
“አቡ ሁረይራ እንዳስተላለፈው ነቢዩ እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹አላህ እንዲህ አለ ‹እኔ ለታማኝ ባርያዎቼ ዓይን ያላየችውን፣ ጆሮ ያልሰማውን የሰው ልብ ሊያስበው የማይችለውን (አስደናቂ ነገሮች)› አዘጋጅቻለሁ፡፡››”[18]
አቶ ሐሰን ከነቢያቸው በላይ አዋቂ ከሆኑ ይንገሩን፡፡
ሌላው ያነሱት ነጥብ በጳውሎስ መልዕክታት ውስጥ ስለሚገኙት የሰላምታ መልዕክቶች ጉዳይ ነው፡፡ የክርስትና ግልጠተ መለኮት ግንዛቤ የቅዱሳት መጻሕፍት ጸሐፊያን የግል ሕይወታቸውን የሚመለከቱ ጉዳዮችን እንዳይጽፉ አይገድብም፡፡ እነዚህ ሰላምታዎች በመንፈስ ቅዱስ ምሪት የተጻፉ ስለሆኑ የቅዱሳት መጻሕፍት አካል ናቸው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መካተታቸው አራት ጥቅሞች አሉት፡-
- የጸሐፊያኑን ነባራዊ ሁኔታ እንድናውቅና ስሜታቸውን እንድንገነዘብ ይረዱናል፡፡
- የጽሑፎቹን አውድ በማሳየት የተሟላ ምስል ይሰጡናል፡፡
- ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር ስለ ወንጌል ዋጋ የከፈሉትን የመጀመርያዎቹን ክርስቲያኖች ስሞች መጥቀስ ለመታሰብያቸው ይሆናል፡፡
- ሐዋርያው ጳውሎስ ከጠቀሳቸው ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ በዓለማውያን ምንጮች ውስጥ የሚታወቁ በመሆናቸው የጽሑፎቹን መቼት በውጫዊ ማስረጃዎች እንድናረጋግጥ በመርዳት በሐቀኝነታቸው ላይ ያለንን መተማመን ይጨምሩልናል፡፡
-
ሕልውና የሌላቸው መጻሕፍት?
የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ከላይ ባየነው ሁኔታ ለማጣጣልና በቁርኣን ውስጥ የተጠቀሱት ተውራትና እንጅል እንዳልሆኑ ለማረጋገጥ ጥረት ካደረጉ በኋላ “ታድያ ሕልውና በሌላቸው መጻሕፍት እንድናምን ቁርኣን ለምን ያዘናል?” የሚል ጥያቄ ያቀርባሉ (ገፅ 51)፡፡ ሦስት ምክንያቶችንም በመስጠት ጥያቄውን ለመመለስ ይሞክራሉ፡፡ እኛ ደግሞ “ሲጀመር የተውራትና የኢንጂል ሕልውና እንደጠፋ መች አረጋገጡና?” ብለን እንጠይቃቸዋለን፡፡ ተከታዮቹን ቁርአናዊ ምስክርነቶች ካገናዘብን በኋላ ቁርኣን የጠቀሳቸው ተውራትና ኢንጂል ቢያንስ በሙሐመድ ዘመን ሕልውና ያልነበራቸው መጻሕፍት መሆናቸውን መደምደም ይቻል እንደሆን አንባቢ ፍርዱን እንዲሰጥ እናቀርባቸዋለን፡-
-
መጽሐፉ በሙሐመድ ዘመን በአይሁድና በክርስቲያኖች እጅ ነበር፡-
“የእስራኤል ልጆች ሆይ! ያችን በናንተ ላይ የለገስኳትን ጸጋዬን አስታውሱ፡፡ በቃል ኪዳኔም ሙሉ፤ በቃል ኪዳናችሁ እሞላለሁና፤ እኔንም ብቻ ፍሩ፡፡ ከናንተ ጋር ያለውን (መጽሐፍ) የሚያረጋግጥ ሆኖ ባወረድኩትም (ቁርኣን) እመኑ፡፡ በርሱም የመጀመሪያ ከሓዲ አትሁኑ፡፡ በአንቀጾቼም ጥቂትን ዋጋ አትለውጡ፡፡ እኔንም ብቻ ተጠንቀቁ፡፡” (ሱራ 2፡40-41)
“ከነሱም ጋር ያለውን (መጽሐፍ) አረጋጋጭ የኾነ መጽሐፍ ከአላህ ዘንድ በመጣላቸው ጊዜ (ከመምጣቱ) በፊት በነዚያ በካዱት ላይ ይረዱበት የነበሩ ሲኾኑ ያወቁት ነገር በመጣላቸው ጊዜ በርሱ ካዱ፡፡ የአላህም ርግማን በከሓዲዎች ላይ ይኹን፡፡” (ሱራ 2፡89)
“አላህም ባወረደው (ሁሉ) ለእነርሱ «እመኑ» በተባሉ ጊዜ «በኛ ላይ በተወረደው (መጽሐፍ ብቻ) እናምናለን» ይላሉ፡፡ ከርሱ ኋላ ባለው (ቁርኣን) እርሱ ከነሱ ጋር ላለው (መጽሐፍ) አረጋጋጭ እውተኛ ሲኾን ይክዳሉ፡፡ «አማኞች ከኾናችሁ ከአሁን በፊት የአላህን ነቢያት ለምን ገደላችሁ?» በላቸው፡፡” (ሱራ 2፡91)
“እነርሱ ጋርም ላለው (መጽሐፍ) አረጋጋጭ የኾነ መልክተኛ ከአላህ ዘንድ በመጣላቸው ጊዜ ከነዚያ መጽሐፍን ከተሰጡት ከፊሉ እነርሱ እንደማያውቁ ኾነው የአላህን መጽሐፍ ከጀርባዎቻቸው ኋላ ጣሉ፡፡” (የላም ምዕራፍ 2፡101) በተጨማሪም 3:81; 4:47; 5:43; 16:43-44; 21:7 ይመልከቱ፡፡
-
ሙሐመድና አድማጮቻቸው መጽሐፉን የሚያነቡትን እንዲጠይቁ አላህ አዟቸዋል
“ወደ አንተም ካወረድነው በመጠራጠር ውስጥ ብትሆን እነዚያን ከአንተ በፊት መጽሐፉን የሚያነቡትን ጠይቅ፡፡ እውነቱ ከጌታህ ዘንድ በእርግጥ መጥቶልሃል፡፡ ከተጠራጣሪዎቹም አትሁን፡፡” (ሱራ 10፡94)
“ከአንተም በፊት ወደእነሱ የምናወርድላቸው የኾነን ሰዎችን እንጂ ሌላን አላክንም፡፡ የማታውቁም ብትኾኑ የመጽሐፉን ባለቤቶች ጠይቁ፡፡” (ሱራ 21፡7)
-
አይሁድና ክርስቲያኖች መጽሐፉን የማንበብ ዕድል ነበራቸው፡-
“ከኋላቸውም፡- መጽሐፉን የወረሱ መጥፎ ምትኮች ተተኩ፡፡ የዚህን የቅርቡን ጠፊ ጥቅም ይይዛሉ፡፡ ብጤውም ጥቅም ቢመጣላቸው የሚይዙት ሲኾኑ « (በሠራነው)፡- ለኛ ምሕረት ይደረግልናል» ይላሉ፡፡ በአላህ ላይ ከእውነት በቀር እንዳይናገሩ በእነርሱ ላይ የመጽሐፉ ቃል ኪዳን አልተያዘባቸውምን? በእርሱ ውስጥ ያለውንም አላነበቡምን? የመጨረሻይቱም አገር ለእነዚያ ጌታቸውን ለሚፈሩት በላጭ ናት፡፡ አታውቁምን?” (ሱራ 7፡169)
“እናንተ መጽሐፉን የምታነቡ ሆናችሁ ሰዎችን በበጎ ሥራ ታዛላችሁን? ነፍሶቻችሁንም ትረሳላችሁን? (የሥራችሁን መጥፎነት) አታውቁምን?” (2፡44) “Do you order righteousness of the people and forget yourselves while you recite the Scripture? Then will you not reason?”
“እነርሱ መጽሐፉን የሚያነቡ ሲኾኑ አይሁዶች፡- ክርስቲያኖች በምንም ላይ አይደሉም አሉ፡፡ ክርስቲያኖችም፡- አይሁዶች በምንም ላይ አይደሉም አሉ፡፡ እንደዚሁ እነዚያ የማያውቁት (አጋሪዎች) የንግግራቸውን ብጤ አሉ፡፡ አላህም በዚያ በርሱ ይለያዩበት በነበሩት ነገር በትንሣኤ ቀን በመካከላቸው ይፈርዳል፡፡” (2፡113)
“እነዚያ መጽሐፉን የሰጠናቸው ተገቢ ንባቡን ያነቡታል፡፡ እነዚያ በርሱ ያምናሉ፤ በርሱም የሚክዱ እነዚያ እነርሱ ከሳሪዎቹ ናቸው፡፡” (ሱራ 2፡121)
“ተውራት ከመወረድዋ በፊት እስራኤል በራሱ ላይ እርም ካደረገው ነገር በስተቀር ምግብ ሁሉ ለእስራኤል ልጆች የተፈቀደ ነበር፡፡ እውነተኞችም እንደኾናችሁ ተውራትን አምጡ አንብቡዋትም በላቸው፡፡” (ሱራ 3፡93)
“(የመጽሐፉ ሰዎች ሁሉ) እኩል አይደሉም፡፡ ከመጽሐፉ ሰዎች ቀጥ ያሉ በሌሊት ሰዓቶች እነርሱ የሚሰግዱ ኾነው የአላህን አንቀጾች የሚያነቡ ሕዝቦች አሉ፡፡” (ሱራ 3፡113)
-
አይሁድና ክርስቲያኖች የተሰጣቸውን መጽሐፍ መታዘዝ ይኖርባቸዋል፡-
“እነርሱም ተውራትንና ኢንጂልን ከጌታቸውም ወደእነሱ የተወረደውን መጽሐፍ ባቋቋሙ (በሠሩበት) ኖሮ ከበላያቸውና ከእግሮቻቸው ሥር በተመገቡ ነበር፡፡ ከእነሱ ውስጥ ትክክለኞች ሕዝቦች አልሉ፡፡ ከእነሱም ብዙዎቹ የሚሠሩት ነገር ከፋ!” (ሱራ 5፡66)
“«እናንተ የመጽሐፉ ባለቤቶች ሆይ! ተውራትንና ኢንጂልን ከጌታችሁም ወደእናንተ የተወረደውን እስከምታቆሙ (እስከምትሠሩባቸው) ድረስ በምንም ላይ አይደላችሁም» በላቸው፡፡ ከጌታህም ወደ አንተ የተወረደው ቁርኣን ከእነሱ ብዙዎቹን ትዕቢትንና ክህደትን በእርግጥ ይጨምርባቸዋል፡፡ በከሓዲያን ሕዝቦችም ላይ አትዘን፡፡” (ሱራ 5፡68)
-
በመካከላቸው ያለውን ሙግት መፍታት ያለባቸው በቁርኣን ሳይሆን በመጽሐፋቸው ነው፡-
“እነርሱም ዘንድ ተውራት እያለች በውስጧ የአላህ ፍርድ ያለባት ስትኾን እንዴት ያስፈርዱሃል! ከዚያም ከዚህ በኋላ እንዴት ይሸሻሉ! እነዚያም በፍጹም ምእምናን አይደሉም፡፡ እኛ ተውራትን በውስጥዋ መምሪያና ብርሃን ያለባት ስትኾን አወረድን፡፡ እነዚያ ትዕዛዝን የተቀበሉት ነቢያት በእነዚያ አይሁዳውያን በኾኑት ላይ በርሷ ይፈርዳሉ፡፡ ሊቃውንቱና ዐዋቂዎቹም ከአላህ መጽሐፍ እንዲጠብቁ በተደረጉትና በርሱም ላይ መስካሪዎች በኾኑት (ይፈርዳሉ)፡፡ ሰዎችንም አትፍሩ፡፡ ፍሩኝም፡፡ በአንቀጾቼም አነስተኛን ዋጋ አትለውጡ፡፡ አላህም ባወረደው ነገር ያልፈረደ ሰው እነዚያ ከሓዲዎቹ እነርሱ ናቸው፡፡” (ሱራ 5፡43-44)
“የኢንጂልም ባለቤቶች በውስጡ አላህ ባወረደው ሕግ ይፍረዱ፡፡ አላህም ባወረደው የማይፈርድ ሰው እነዚያ አመጸኞች እነርሱ ናቸው፡፡” (ሱራ 5፡47)
-
አይሁድና ክርስቲያኖች ተውራትንና ኢንጂልን ከታዘዙ ይባረካሉ፡-
“እነርሱም ተውራትንና ኢንጂልን ከጌታቸውም ወደእነሱ የተወረደውን መጽሐፍ ባቋቋሙ (በሠሩበት) ኖሮ ከበላያቸውና ከእግሮቻቸው ሥር በተመገቡ ነበር፡፡ ከእነሱ ውስጥ ትክክለኞች ሕዝቦች አልሉ፡፡ ከእነሱም ብዙዎቹ የሚሠሩት ነገር ከፋ!” (ሱራ 5፡65)
-
ሙስሊሞች በቀደሙት መገለጦች ማመን ይጠበቅባቸዋል፡-
“ለእነዚያም ወደ አንተ በተወረደውና ከአንተ በፊትም በተወረደው የሚያምኑ በመጨረሻይቱም (ዓለም) እነርሱ የሚያረጋግጡ ለኾኑት (መሪ ነው)፡፡” (ሱራ 2፡4)
“«በአላህና ወደኛ በተወረደው (ቁርኣን) ወደ ኢብራሂምም ወደ ኢስማዒልና ወደ ኢስሐቅም ወደ ያዕቁብና ወደ ነገዶቹም በተወረደው በዚያም ሙሳና ዒሳ በተሰጡት በዚያም ነቢያት ሁሉ ከጌታቸው በተሰጡት ከነርሱ በአንድም መካከል የማንለይ ስንኾን አመንን፤ እኛም ለርሱ (ለአላህ) ታዛዦች ነን» በሉ፡፡” (ሱራ 2፡136)
“መልክተኛው ከጌታው ወደ ርሱ በተወረደው አመነ፡፡ ምእምኖቹም (እንደዚሁ)፡፡ ሁሉም በአላህ፣ በመላዕክቱም፣ በመጻሕፍቱም፣ በመልክተኞቹም ከመልክተኞቹ «በአንድም መካከል አንለይም» (የሚሉ ሲኾኑ) አመኑ፡፡ «ሰማን፤ ታዘዝንም፡፡ ጌታችን ሆይ! ምሕረትህን (እንሻለን)፡፡ መመለሻም ወዳንተ ብቻ ነው» አሉም፡፡” (ሱራ 2፡285)
“«በአላህ አመንን፡፡ በእኛ ላይ በተወረደውም (በቁርኣን)፣ በኢብራሂምና በኢስማዒልም፣ በኢስሓቅም፣ በያዕቆብም፣ በነገዶችም ላይ በተወረደው፤ ለሙሳና ለዒሳም ለነቢያትም ሁሉ ከጌታቸው በተሰጠው (አመንን)፡፡ ከእነርሱ መካከል አንድንም አንለይም፡፡ እኛ ለእርሱ ታዛዦች ነን» በል፡፡” (ሱራ 3፡84)፣ በተጨማሪም 3፡119; 4:136; 5:59; 28:49; 29:46
ከላይ እንዳየነው በቁርኣን መሠረት መጽሐፉ በሙሐመድ ዘመን በአይሁድና በክርስቲያኖች እጅ ነበረ፤ ሙሐመድና አድማጮቻቸው የመጽሐፉን አንባቢዎች እንዲጠይቁ አላህ አዟቸዋል፤ አይሁድና ክርስቲያኖች መጽሐፉን የማንበብ ዕድል ነበራቸው፤ አይሁድና ክርስቲያኖች የተሰጣቸውን መጽሐፍ መታዘዝ እንደሚኖርባቸው ተነግሯል፤ በመካከላቸው ያለውን ሙግት እንኳ ለመፍታት የገዛ መጽሐፋቸው በቂ ስለሆነ ቁርኣን አያስፈልጋቸውም፤ መጽሐፋቸውን ከታዘዙ እንደሚባረኩ ተነግሯል፤ ሙስሊሞች በቀደሙት መገለጦች ማመን እንደሚጠበቅባቸው ተነግሯል፡፡ ስለዚህ ቢያንስ በሙሐመድ ዘመን ተውራትና ኢንጂል በአይሁድና በክርስቲያኖች እጅ መኖራቸው የሚያከራክር አይደለም፡፡ ሙስሊሞች ሕልውና በሌላቸው ተውራትና ኢንጂል እንዲያምኑ ቁርኣን አላዘዛቸውም፡፡ እናዝናለን ኡስታዝ ሐሰን፣ እርስዎ ከተናገሩት በተጻራሪ በቁርኣን መሠረት መጽሐፍቱ በሙሐመድ ዘመን ነበሩ!
ከስድስቱ የሐዲስ ስብስቦች መካከል አንዱ የሆነው ሱናን አቡ ዳውድ እንዲህ በማለት ይህንን ሐቅ ያጠናክራል፡-
“… ለአላህ መልእክተኛ (ሰላም በእሳቸው ላይ ይሁንና) ወንበር አመጡላቸው፤ ተቀመጡበትም፡፡ ከዚያም ተውራትን አምጡልኝ አሉ፤ አመጡላቸውም፡፡ ከዚያ ከወንበሩ ላይ ተነስተው ተውራትን አስቀመጡና እንዲህ አሉ፡- በአንተ እና አንተን በገለጠው አምላክ አምናለሁ፡፡”[19] ኢብን ከሢር የተሰኘው ስመ ጥር የቁርኣን ተንታኝ ደግሞ አላህ ስላዘዛቸው ሙሐመድ ይህንን ማድረጋቸውን ይናገራል፡፡[20]
ስለዚህ ሙስሊሞች በሙሐመድ ዘመን ተውራትና ኢንጂል በአይሁድና በክርስቲያኖች እጅ መኖሩን መካድ አያዋጣቸውም፡፡ ሙስሊሞች ይህንን ሐቅ ከተቀበሉ ቁርኣንን ከስህተቱ ለማዳን ሁለት “መልስ” ብቻ ነው የሚኖራቸው፡-
የመጀመርያው “መልስ” ቁርኣን የጠቀሰው የተበረዙትን መጻሕፍት ነው የሚል ነው፡፡ ነገር ግን ቁርኣን የመጻሕፍቱን መኖር ብቻ ሳይሆን አይሁድና ክርስቲያኖች እንዲታዘዟቸውና በነርሱ መሠረት እንዲፈርዱ ከማዘዝም አልፎ የመጣላቸውን መገለጥ ለማረጋገጥ ሙሐመድ የነዚህን መጻሕፍት ምስክርነት እንዲጠይቁ ያዛቸዋል፡፡ ሱናን አቡ ዳውድ ውስጥ በተጻፈው መሠረት ደግሞ ሙሐመድ በዘመኑ በነበረው ተውራት ማመናቸውን በአደባባይ ተናግረዋል፡፡ አይሁድና ክርስቲያኖች የተበረዙትን መጻሕፍት እንዲታዘዙና በርሱ መሠረት እንዲፈርዱ ቁርኣን ስለምን ያዛቸዋል? ሙሐመድስ ለነቢይነታቸው ማረጋገጫ ከተበረዙት መጻሕፍት እንዲጠይቁ እንዴት ሊያዛቸው ይችላል? ተውራት ተበርዞ ከነበረ ሙሐመድ እንዴት በእርሱ ማመናቸውን በአደባባይ ሊመሰክሩ ቻሉ? ስለዚህ ይህ “መልስ” አያስኬድም፡፡
ሁለተኛው “መልስ” ደግሞ ተውራትና ኢንጂል የተበረዙት ከሙሐመድ ዘመን በኋላ ነው የሚል ነው፡፡ ይህ እጅግ ደካማ “መልስ” ነው፡፡ በሙሐመድ ዘመን በአይሁድና በክርስቲያኖች ዘንድ የሚታወቁት ተውራትና ኢንጂል ዛሬ በእጃችን ከሚገኘው መጽሐፍ ቅዱስ የተለየ ይዘት እንዳልነበራቸው በዘመኑ ከነበሩት የእጅ ጽሑፎች መረዳት ይቻላል፡፡ የቁምራን ጥቅልሎች፣ የቸስተር ቢቲ ጽሑፎች፣ ኮዴክስ ቫቲካነስ፣ ኮዴክስ ሲናይቲከስና ሌሎች ስፍር ቁጥር የሌላቸው ጥንታውያን የመጽሐፍ ቅዱስ የእጅ ጽሑፎች ይህንኑ የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡ በሰባተኛው ክፍለ ዘመን የነበረው መጽሐፍ ቅዱስ አሁን በእጃችን ከሚገኘው የተለየ መሆኑን የሚያመለክት ቅንጣት ታክል ማስረጀ የለም፡፡ በብዙ ሺህ ኮፒዎች ተጽፎ፣ በብዙ ቋንቋዎች ተተርጉሞና በመላው ዓለም ተበትኖ ይገኝ የነበረ መጽሐፍ ሊበረዝ መቻሉን እንኳ ማሰብ እብደት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ሙግት እንደ መጀመርያው ሁሉ የሚስኬድ አይደለም፡፡
ከሁሉም በላይ ደግሞ የአላህ ቃል እንደማይለወጥ የሚናገሩት የቁርኣን ጥቅሶች “መጽሐፍ ቅዱስ ተለውጧል” የሚለውን መሠረተ ቢስ የሙስሊሞች ሙግት መቀመቅ ይከቱታል፡፡ ቁርኣን በተከታዮቹ አናቅፅ ላይ የአላህ ቃል ሊለወጥ እንደማይችል ይናገራል፡-
- “የአላህን ንግግሮች ለዋጭ የለም” 6፡34
- “ለቃላቱ ለዋጭ የለም” 6፡115
- “የአላህ ቃል መለወጥ የላትም” 10፡64
- “ለቃላቱ ለዋጭ የላቸውም” 18፡27
- “ለአላህ ድንጋጌ ፈጽሞ መለወጥን አታገኝም” 33፡62
ከሐዲሳትና ከቀዳሚያን ተፍሲሮች እንደምንረዳው የጥንት ሙስሊሞች አላህ ያወረዳቸው ቅዱሳት መጻሕፍት ፈጽሞ እንደማይለወጡና ማንም ሊለውጣቸው እንደማይችል አጥብቀው ያምኑ ነበር፡፡ ለምሳሌ የሚከተለውን የኢብን ከሢር ተፍሲር ተመልከቱ፡-
“… አል ቡኻሪ እንደዘገበው ኢብን አባስ እንዲህ ብሏል፤ ‹የዚህ አያ ትርጉም የሚከተለው ነው፡- … ከአላህ ፍጥረታት መካከል ማንም የአላህን ቃላት ከመጻሕፍቱ ውስጥ ማስወገድ አይችልም፡፡ ግልፅ ትርጉማቸውን ያጣምማሉ ማለት ነው፡፡› ወሃብ ኢብን ሙነቢህ እንዲህ አለ “ተውራት እና ኢንጂል ልክ አላህ በገለጣቸው ሁኔታ ተጠብቀው ይገኛሉ፡፡ ከውስጣቸው አንድም ፊደል አልተወገደም፡፡ ነገር ግን ሰዎች ራሳቸው በጻፏቸው መጻሕፍት ላይ ተሞርኩዘው በመጨመርና ውሸት በሆነ አተረጓጎም ሌሎችን ያሳስታሉ፡፡” … “የአላህ መጻሕፍት ግን እስከ አሁን ተጠብቀው ይገኛሉ፤ ሊለወጡም አይችሉም፡፡”[21]
እዚሁ ተፍሲፍ የግርጌ ማስታወሻ ላይ እንዲህ የሚል እናገኛለን፡-
“ቃሉን ያጣምማሉ ማለት ትርጉሙን ይለውጣሉ ወይም ያጣምማሉ ማለት ነው፡፡ ከየትኞቹም የአላህ መጻሕፍት ውስጥ አንድ ቃል እንኳ መለወጥ የሚችል የለም፡፡ ይህ ማለት በተሳሳተ መንገድ ይተረጉማሉ ማለት ነው፡፡”
ቁርኣን ተውራትና ኢንጂል መለወጣቸውን በአንድም ቦታ የማይናገር ሲሆን ራሱ ቁርኣን መለዋወጡን ግን በተደጋጋሚ ይናገራል፡-
“ከአንቀጽ ብንለውጥ ወይም እርሷን ብናስረሳህ ከርሷ የሚበልጥን ወይም ብጤዋን እናመጣለን፤ አላህ በነገሩ ሁሉ ላይ ከሃሊ (ቻይ) መኾኑን አታውቅምን?” (ሱራ 2፡106)
“በአንቀጽም ስፍራ አንቀጽን በለወጥን ጊዜ አላህም የሚያወርደውን ነገር አዋቂ ነው፡፡ «አንተ ቀጣፊ እንጂ ሌላ አይደለህም» ይላሉ፡፡ በእውነቱ አብዛኞቻቸው አያውቁም፡፡” (16፡101)
ሙስሊም ሰባኪያን መጽሐፍ ቅዱስ ተበርዟል የሚለውን ሙግት ለማቅረብ የተገደዱበት ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ ከቁርኣን ጋር የማይጣጣም መልእክት በመያዙ እንጂ የረባ ማስረጃ ኖሯቸው አይደለም፡፡ ይህንን ሙግት ለመጀመርያ ጊዜ ያቀረበው ኢብን ሐዝም (994-1064 ዓ.ም.) የተሰኘ የእስፔን ሙስሊም ነበር፡፡ ይህ ሰው እዚህ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ የተገደደው መጽሐፍ ቅዱስን ካነበበ በኋላ ከቁርኣን ጋር የሚጣረስ መሆኑን በመገንዘቡ ምክንያት ነበር፡፡
የሙስሊም ሰባኪያን የብረዛ ክስ ቁርኣን ትክክል ነው ከሚል ድምዳሜ የመነጨ እንጂ በማስረጃ ላይ ተደግፎ ወደ ድምዳሜ ያመራ አይደለም፡፡ ቁርኣን የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኝነት ከመሰከረ በኋላ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጣረሱ ትምህርቶችን ማስተማሩ ደራሲው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይዘት የነበረው ዕውቀት በጣም አናሳ መሆኑን ያመለክታል፡፡
-
መጽሐፍ ቅዱስን በሐዲስ ሚዛን?
ሐሰን ታጁ የመጽሐፍ ቅዱስን ተዓማኒነት በማጣጣል ከቁርኣን ጋር ማወዳደር እንደማይቻል ከገለፁ በኋላ “ትንሽ ዝቅ እንበልና ሐዲሶች በተሰበሰቡበት ሚዛን እንመዝነው” በማለት ርዕሱን ይጀምራሉ (ገፅ 53)፡፡ ስለ ሐዲስ አሰባሰብና ደረጃ አሰጣጥ ለማብራራት 6 ገፆችን ከፈጁ በኋላ ምሑራን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ተናግረዋል ያሏቸውንና ቀደም ሲል መልስ የሰጠንባቸውን የተቆራረጡ ጥቅሶች በመድገም አንባቢያንን ያሰለቻሉ (ገፅ 59-61)፡፡ በመጽሐፋቸው ውስጥ ያሉትን ድግግሞሾች ማንበብ አልማዙን የጨረሰ ቴፕ የማድመጥ ያህል አሰልቺ ቢሆንም ምናልባት አዲስ ሐሳብ ጣል ያደርጉ እንደሆን ብዬ በጥንቃቄ አንብቤያቸዋለሁ፡፡ ነገር ግን ምንም አዲስ ነገር ስለሌላቸው እናልፋቸዋለን፡፡
በታሪክ ተመራማሪዎች ዘንድ ቦታ የሌላቸውን ሙሐመድ ካለፉ ከክፍለ ዘመናት በኋላ የተጻፉትን ሐዲሳት ተዓማኒ ለማስመሰል በብዙ ሙገሣ የተሞሉ አረፍተ ነገሮችን የጻፉ ሲሆን እንዲህ በማለት ይደመድማሉ፡-
“እናም የመጽሐፍ ቅዱስ አዘጋገብ ከቁርኣን ቀርቶ ከሐዲስ፣ ከሶሂህ ሐዲስ ቀርቶ ከደካማው ጋር እንኳ ሊወዳደር የሚችል አይደለም፡፡ የፍጹም ሐሰትነት (መውዱእ) ደረጃን ተራምዶ ሊያልፍ የሚችል አንድም አንቀፅ በውስጡ አላካተተም፡፡” (ገፅ 62)
ይህ በወኔ የተወጠረ አባባላቸው ምን ያህል ትክክል ነው? እውን ሐዲሳት ከመጽሐፍ ቅዱስ በላይ ተዓማኒ ናቸውን? አንባቢያን አይተው መፍረድ ይችሉ ዘንድ በአዲስ ኪዳን ውስጥ የሚገኙትን የማቴዎስ፣ የማርቆስ፣ የሉቃስ፣ የዮሐንስ፣ የጳውሎስና የጴጥሮስን ጽሑፎች ከአል-ቡኻሪ፣ ሙስሊም፣ አቡ ዳውድ፣ አት-ትርሚዚ፣ አን-ነሳዒና ኢብን ማጃህ ሐዲሳት ጋር እናነፃፅራለን፡፡ (
የሐዲስ ጸሐፊ | የጻፈበት ዘመን | የጊዜ ልዩነት | የዓይን ምስክር | ከዓይን ምስክሮች ጋር የነበረው ቅርርብ | በታሪካዊ ዘገባ መስፈርት ያለው ተቀባይነት |
አል-ቡኻሪ | 256 ዓ.ስ. | 246 | አይደለም | አይተዋወቅም | ውድቅ |
ሙስሊም | 261 ዓ.ስ. | 251 | አይደለም | አይተዋወቅም | ውድቅ |
አቡዳውድ | 275 ዓ.ስ. | 265 | አይደለም | አይተዋወቅም | ውድቅ |
አት-ትርሚዚ | 279 ዓ.ስ. | 269 | አይደለም | አይተዋወቅም | ውደቅ |
አን-ነሳዒ | 303 ዓ.ስ. | 293 | አይደለም | አይተዋወቅም | ውድቅ |
ኢብን ማጃህ | 273 ዓ.ስ. | 263 | አይደለም | አይተዋወቅም | ውድቅ |
ዓ.ስ. – ዓመተ ስደት (ሒጅራ) ያመለክታል
ከሰንጠረዡ እንደምንረዳው በጸሐፊያኑና በሙሐመድ መካከል ያለው የጊዜ ልዩነት በአማካይ 264 ዓመት ሲሆን የጊዜ ክፍተቱ አፈታሪኮችን ለመፍጠር ከበቂ በላይ ነው፡፡ ሁሉም ጸሐፊያን የዘገቡትን ጉዳይ በዓይናቸው አላዩም፡፡ ከዓይን ምስክሮችም አልሰሙም፡፡ ከዓይን ምስክሮች ሊሰሙ ይቅርና ከዓይን ምስክሮች የሰሙትን ግለሰቦች እንኳ የማግኘት ዕድል አልነበራቸውም፡፡ የጻፏቸው ታሪኮች ሁሉ የስሚ ስሚ በመሆናቸው በመጨረሻው አስተላላፊ ምስክርነት ላይ መቶ በመቶ ከመደገፍ ውጪ ሌላ ምርጫ የላቸውም፡፡ ከሙስሊሞች በስተቀር የዒስናድ (የአስተላላፊዎች ሰንሰለት) የሚለውን የታሪካዊ ዘገባ አስተላለፍ የሚቀበል የታሪክ ምሑር በዓለም ላይ ስለሌለ የሐዲሳት አዘጋገብ በራሱ የተዓማኒ ዘገባዎችን መስፈርት አያሟላም፡፡ በሐዲሳት አስተማማኝነት ላይ ሙስሊሞች እንኳ ስምምነት የላቸውም፡፡ ለምሳሌ ያህል የሺኣ ሙስሊሞች በነዚህ የሐዲስ ስብስቦች ላይ ከፍተኛ ጥርጣሬ አላቸው፡፡
የአዲስ ኪዳን ጸሐፊያንን ደግሞ እንመልከት፡-
ጸሐፊ | የተጻፈበት ዘመን | የጊዜ ልዩነት | የዓይን ምስክር | ከዓይን ምስክሮች ጋር የነበረው ቅርርብ | በታሪካዊ ዘገባ መስፈርት ያላቸው ተቀባይነት |
ማቴዎስ | 50-70 ዓ.ም. | 20-40 | ነው | የዓይን ምስክር | እጅግ ከፍተኛ |
ማርቆስ | 55-70 ዓ.ም.. | 25-40 | በከፊል | የቅርብ ወዳጅ | ከፍተኛ |
ሉቃስ | 61-62 ዓ.ም. | 28-29 | አይደለም | የቅርብ ወዳጅ | ከፍተኛ |
ዮሐንስ | 80-90 ዓ.ም. | 47-57 | ነው | የዓይን ምስክር | እጅግ ከፍተኛ |
ጳውሎስ | 55-56 ዓ.ም. | 22-23 | ነው | የዓይን ምስክርና የቅርብ ወዳጅ | እጅግ ከፍተኛ |
ጴጥሮስ | 62-64 ዓ.ም.. | 32-34 | ነው | የዓይን ምስክር | እጅግ ከፍተኛ |
ብዙ አንባቢያን የሐዲስ መጻሕፍትን አግኝተው የማንበብ ዕድል ስለሌላቸው ሐሰን ታጁ መጽሐፍ ቅዱስን ከምን ዓይነት መጻሕፍት ጋር እያነጻጸሩ እንዳሉ ላያውቁ ይችላሉ፡፡ የሐዲስ መጻሕፍት ለመንፈሳዊም ሆነ ለሥጋዊ ሕይወት የማይጠቅሙ እንቶ ፈንቶ ጉዳዮችን የሚያወሩ በተረት መሳይ አፈታሪኮች የተሞሉ መጻሕፍት በመሆናቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ለንጽጽር ሊቀርቡ የሚገባቸው አይደሉም፡፡ አንባቢያን አይተው ይፈርዱ ዘንድ ሙስሊሞች ከቁርኣን ቀጥሎ በጣም ተዓማኒ አድርገው ከሚቆጥሩት ሳሂህ አል-ቡኻሪ ከተሰኘው የሐዲስ ስብስብ ጥቂቶቹን እናስነብባለን፡-
- አቡ ሁራይራ እንደዘገበው የአላህ መልእክተኛ እንዲህ ብለዋል፡- “ጫማዎቻችሁን ስታጠልቁ የቀኝ ጫማዎቻችሁን አስቀድሙ፡፡ ስታወልቁ የግራችሁን አስቀድሙ፡፡” ሳሂህ አል-ቡኻሪ ቅፅ 7፣ መጽሐፍ 72፣ ቁጥር 747
- አቡ ሁራይራ እንዳስተላለፈው ነቢዩ እንዲህ ብለዋል፡- “በምትጠጡበት ዋንጫ ውስጥ ዝንብ ብትወድቅ ወደ ውስጥ ድፈቋት ምክንያቱም በአንዱ ክንፏ ላይ በሽታን የተሸከመች ስትሆን በሌላኛው ላይ ደግሞ ፈውስን ትሸከማለችና፡፡” ሳሂህ አል-ቡኻሪ ቅፅ 4፣ መጽሐፍ 54፣ ቁጥር 537
- ኢብን አባስ እንዳስተላለፈው ነቢዩ እንዲህ ብለዋል፡- “ስትበሉ እጃችሁን ሳትልሱ ወይም ሌላ ሰው ሳታስልሱ እንዳትጠርጉት፡፡” ሳሂህ አል-ቡኻሪ ቅፅ 7፣ መጽሐፍ 65፣ ቁጥር 366
- ሡማማ ቢን አብደላ እንዳስተላለፈው፡- አነስ ሲጠጣ ከመጠጣቱ በፊት ሁለቴ ወይም ሦስቴ በመጠጫው ውስጥ ይተነፍስ ነበር፡፡ ነቢዩ ከመጠጣታቸው በፊት ሦስቴ ትንፋሽ እደሚወስዱ ተናግሯል፡፡ ሳሂህ አል-ቡኻሪ ቅፅ 7፣ መጽሐፍ 69፣ ቁጥር 535
- አቡ ሁራይራ እንዳስተላለፈው ነቢዩ እንዲህ ብለዋል፡- “በኢማም ፊት ራሱን ቀና የሚያደርግ ሰው አላህ ጭንቅላቱን ወደ አህያ ጭንቅላት መልኩንም ወደ አህያ መልክ መለወጥ እንደሚችል አውቆ አይፈራምን?” ሳሂህ አል-ቡኻሪ ቅፅ 1፣ መጽሐፍ 11፣ ቁጥር 660
- ኡመር እንዳስተላለፈው የአላህ መልእክተኛ እንዲህ ብለዋል፡- “ጠዋት ፀሐይ ብቅ ስትል ሙሉ በሙሉ እስክትታይ ድረስ ማንም መጸለይ የለበትም፡፡ እንዲሁም ስትጠልቅ ሙሉ በሙሉ እስክትጠልቅ ድረስ ማንም መጸለይ የለበትም ምክንያቱም ፀሐይ የምትወጣው በሁለቱ የሰይጣን ቀንዶች መካከል ነውና፡፡” ሳሂህ አል-ቡኻሪ ቅፅ 4፣ መጽሐፍ 54፣ ቁጥር 494
- ናዚ እንደዘገበው አብዱላህ ኢብን ኡመር የሚከተለውን ዘግቧል፡- “ነቢዩ እንዲህ አሉ፡- ‹‹ትኩሳት የሚመጣው ከሲዖል ነው፡፡ ስለዚህ በውሃ አብርዱት፡፡››” ሳሂህ አል-ቡኻሪ ቅፅ 7፣ መጽሐፍ 71፣ ቁጥር 619
- አብዱላህ እንደዘገበው ስለ አንድ ሰው በነቢዩ ፊት ተወራ፡፡ ሰውየው ለሰላት እንዳልተነሳና እስኪነጋ ድረስ እንደተኛ ተነገረ፡፡ ነቢዩም ‹‹ሰይጣን በጆሮው ውስጥ ሽንቱን ሸንቷል›› አሉ፡፡ ሳሂህ አል-ቡኻሪ ቅፅ 2፣ መጽሐፍ 21፣ ቁጥር 245
- አቡ ሁራይራ እንዳስተላለፈው ነቢዩ እንዲህ ብለዋል፡- “ማዛጋት ከሰይጣን ነው፡፡ አንድ ሰው ሲያዛጋው በተቻለ መጠን ለመቆጣጠር ይሞክር፡፡ ሰውየው ሲያዛጋ ‹‹ሃ…›› ሲል ሰይጣን ይስቅበታልና፡፡” ሳሂህ አል-ቡኻሪ ቅፅ 4፣ መጽሐፍ 54፣ ቁጥር 509
- አነስ እንዳስተላለፈው ነቢዩ እንዲህ ብለዋል፡- “የናንተ መሪ ዘቢብ (የደረቀ ወይን) የመሰለ የራስ ቅል ያለው ኢትዮጵያዊ ቢሆን እንኳ ታዘዙት፡፡” ሳሂህ አል-ቡኻሪ ቅፅ 1 መጽሐፍ 11 ቁጥር 662
- አቡ ሁራይራ እንዳስተላለፈው ነቢዩ እንዲህ ብለዋል፡- “ማንም ሰው ከእንቅልፉ ተነስቶ ሲታጠብ ውሃ በአፍንጫው ውስጥ በመጨመር ሦስት ጊዜ መንፋት ይኖርበታል፤ ምክንያቱም ሰይጣን ሌሊቱን ሙሉ በላይኛው አፍንጫው ውስጥ አድሯልና፡፡” ሳሂህ አል-ቡኻሪ ቅፅ 4፣ መጽሐፍ 54፣ ቁጥር 516
- አቡ ሁራይራ እንዳስተላለፈው የአላህ መልእክተኛ እንዲህ ብለዋል፡- “ሐዳስ የሚፈፅም ሰው ድጋሜ እስኪታጠብ ድረስ ጸሎቱ አይሰማለትም፡፡” ከሀደረማውት የመጣ አንድ ሰው ሐዳስ ምንድነው? በማለት አቡ ሁራይራን ጠየቀው፡፡ አቡ ሁራይራም ሲመልስ “በመቀመጫችን በኩል አፈትልኮ የሚወጣ አየር ነው” አለ፡፡ ሳሂህ አል-ቡኻሪ ቅፅ 1፣ መጽሐፍ 4፣ ቁጥር 137
- አቡ ሁራይራ እንዳስተላለፈው የአላህ መልእክተኛ እንዲህ ብለዋል፡- “የእስራኤል ሕዝቦች ገላቸውን ሲታጠቡ ራቁታቸውን እርስ በርሳቸው እየተያዩ ነበር፡፡ ነቢዩ ሙሳ ግን ብቻውን ነበር የሚታጠበው፡፡ እርስ በርሳቸውም፡- ‹‹ወላሂ! ሙሳ ከኛ ጋር የማይታጠበው በሰውነቱ ላይ እንከን ስላለበት ነው›› ተባባሉ፡፡ ስለዚህ አንድ ቀን ሙሳ ገላውን ሊታጠብ ልብሱን አወላልቆ በድንጋይ ላይ አስቀመጠ፤ ከዚያም ድንጋዩ ልብሱን ይዞ መሮጥ ጀመረ፡፡ ሙሳም ‹‹አንተ ድንጋይ ልብሴን! አንተ ድንጋይ ልብሴን!›› እያለ በሩጫ ተከተለው፡፡ በዚህ ጊዜም የእስራኤል ሕዝቦች አይተውት ‹‹ወላሂ! ሙሳ በሰውነቱ ላይ ምንም እንከን የለውም›› አሉ፡፡ ሙሳም ልብሱን መልሶ በመውሰድ ድንጋዩን መምታት ጀመረ፡፡” አቡ ሁራይራ እንዲህ አለ፡- “ወላሂ! ከዚያ ከባድ ድብደባ የተነሳ በድንጋዩ ላይ ስድስት ወይም ሰባት ምልክቶች ይታያሉ፡፡” ሳሂህ አል-ቡኻሪ ቅፅ 1፣ መጽሐፍ 5፣ ቁጥር 277
- አምር ቢን ማኢሙን እንዲህ አለ፡- “ከእስልምና ዘመን በፊት በነበረው ያለማወቅ ዘመን አንዲት ሴት ጦጣ በብዙ ጦጣዎች ተከባ አየኋት፡፡ ዝሙት በመፈፀሟ ምክንያት በድንጋይ ሲወግሯት ነበር፡፡ እኔም አብሬያቸው ወገርኳት፡፡” ሳሂህ አል-ቡኻሪ ቅፅ 5፣ መጽሐፍ 58፣ ቁጥር 188
- አይሻ እንዲህ አለች፡- “ከነቢዩ ልብስ ላይ የወንድ ዘር ፈሳሽ ሳጥብ ነበር፡፡ እርሳቸውም ውሃው ሳይደርቅላቸው ወደ ሰላት ይሄዱ ነበር፡፡” ሳሂህ አል-ቡኻሪ ቅፅ 1፣ መጽሐፍ 4፣ ቁጥር 229
ሐሰን ታጁ እንዲህ ካሉ መንፈሳዊም ሆነ ፍልስፍናዊ እሴት ከሌላቸው የአፈታሪክ መጻሕፍት ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ለማነጻጸር በመሞከራቸው ሊያፍሩ ይገባል፡፡
ማጣቀሻዎች
[1] ፓውል እንዝ፣ ታሪካዊ ሥነ–መለኮት አመጣጡና ትንተናው፤ በምኒሊክ አስፋውና ሰለሞን ጥላሁን ወደ አማርኛ የተመለሰ፣ 1991፣ ገፅ 13፡፡
[2] አሕመዲን ጀበል፡፡ ክርስቶስ ማነው? 303 ወሳኝ ጥያዌዎች፣ 2001፣ ገፅ 116 የግርጌ ማስታወሻ
[3] Geisler. Encyclopedia; p. 102
[4] Norman Geisler. Encyclopedia of Christian Apologetics, p. 532
[5] Norman Geisler and Shawn Nelson. Evidence of an Early New Testament Canon; 2015, pp. 50-51.
[6] የመካከለኛው ዘመን ፈጠራ ከሆነው የበርናባስ ወንጌል ጋር መምታታት የለበትም
[7] Bruce Metzger: The New Testament Its background and Content, Abingdon Press, 1982, p. 275
[8] Ibid. 276
[9] Ibid.
[10] አዲሱ መደበኛ ትርጉም 1ጢሞቴዎስ 5፡18 የግርጌ ማጥኛ ገፅ 1844 ይመልከቱ፡፡
[11] Norman Geisler. Encyclopedia of Christian Apologetics, p. 5-6
[12] Sir William Ramsay. Saint Paul: the Traveller and the Roman Citizen, New York, G. P. Putnam’s Sons, 1896. [Dr. Ramsey stated: “Luke is a historian of the first rank; not merely are his statements of fact trustworthy … this author should be placed along with the very greatest of historians.”]
Ramsey further said: “Luke is unsurpassed in respects of its trustworthiness.” (Josh McDowell. The Best of Josh Mcdowell: A Ready Defense, pp. 108-109)
[13] የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፣ የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር፣ ገፅ 53
[14] ቴኒ፣ የአዲስ ኪዳን ቅኝት፣ ገፅ 217-218
[15] ዝኒ ከማሁ፣ ገፅ 239
[16] ዝኒ ከማሁ
[17] Alfred Guillaume. The Life of Muhammad: a Translation of Ibn Ishaq’s Sirat Rasul Allah, p. 653
[18] Sahih Al-Bukhari, Vol. 9, Book 93, Number 589
[19] Sunan Abu Dawud, Book 38 (Kitab al Hudud, i.e. Prescribed Punishments), Number 4434
[20] (Tafsir Ibn Kathir (Abridged) Volume 3, Parts 6, 7 & 8)
[21] (Tafsir Ibn Kathir – Abridged, Volume 2, Parts 3, 4 & 5, Surat Al-Baqarah, Verse 253, to Surat An-Nisa, verse 147, abridged by a group of scholars under the supervision of Shaykh Safiur-Rahman Al-Mubarakpuri [Darussalam Publishers & Distributors, Riyadh, Houston, New York, First Edition: March 2000], p. 196