ምዕራፍ ሦስት የቁርኣን ምንጮች “የሐመረ ተዋሕዶን ቅጥፈት በእስልምና እውነት” በሚል ርዕስ በኡስታዝ ሐሰን ታጁ ለተጻፈ መጽሐፍ የተሰጠ መልስ

ምዕራፍ ሦስት

የቁርኣን ምንጮች

በሙስሊሞች እምነት መሠረት ቁርኣን ከሰማይ የወረደ መገለጥ ነው፡፡ ይህንን በተመለከተ ሐሰን ታጁ እንዲህ ይላሉ፡-

ቁርኣን በመላኢካው ጅብሪል አማካይነት ለነቢዩ ሙሐመድ ከአላህ የተወረደ መለኮታዊ መጽሐፍ መሆኑን ደግሞ ደጋግሞ ያውጃል፡፡ (ገፅ 77)

ለዚህ ማስረጃ ይሆናቸው ዘንድ ሱራ 11፡1፣ 27፡6፣ 17፡105፣ 26፡52 ላይ የሚገኙትን ጥቅሶች ከጠቀሱ በኋላ ተከታዩን ስሞታ ያቀርባሉ፡-

… የክርስቲያን ሚሽነሪዎችና ለእስልምና የመረረ ጥላቻ የቋጠሩ ምእራባዊ አጥኚዎች (ኦሪየንታሊስትስ) ‹‹ወንዝ የማያሻግሩ›› መናኛ ሰበቦችን እየፈጠሩ ቁርኣን መለኮታዊ መሆኑን ላለመቀበል ሲያንገራግሩ ይታያሉ፡፡ … የቁርኣንን መለኮታዊነት መቀበል ማለት የእምነታቸውን ግብአተ መሬት መቀበል ማለት ነው፡፡ … ባጭሩ የክርስትናን ሐሰትነት በይፋ ማወጅ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ መቼም ቢሆን የነቢዩ ሙሐመድን (ሰዐወ) ነብይነት፣ የቁርኣንን መለኮታዊነት አይቀበሉም፡፡ (ገፅ 78)

አንድ መጽሐፍ ከሰማይ የመጣ መገለጥ መሆኑን ስለተናገረ ብቻ አንቀበለውም፡፡ ከንግግር ያለፈ በማስረጃ የተደገፈ ማረጋገጫ ያስፈልገዋል፡፡ አቶ ሐሰንና መሰሎቻቸው የቁርኣንን መለኮታዊነት የሚያሳይ አሳማኝ ማስረጃ ማቅረብ ስለማይችሉ “መጽሐፋችንን ያልተቀበሉት ጥላቻ ስላለባቸው ነው” በማለት ሌላውን ወገን መውቀስና ማማረር ልማዳቸው ነው፡፡

እኛ ክርስቲያኖች ቁርኣንን እንደ ፈጣሪ ቃል የማንቀበልበት አብይ ምክንያት ከፈጣሪ ዘንድ ስለመሆኑ ማስረጃ ስለሌለው ነው፡፡ ቁርኣንን ለመቀበል የሚያበቃ ሰበብ ስለሌለ ላለመቀበል ምንም ሰበብ መስጠት አያስፈልገንም፡፡ ለመቀበል የሚያስችል ምክንያት አለመኖሩ በራሱ በቂ ምክንያት ነው፡፡ ነገር ግን ቁርኣን የፈጣሪ ቃል አለመሆኑንና የሰው እጅ ሥራ መሆኑን የሚያረጋግጡ ብዙ ውጪያዊና ውስጣዊ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ ከውጪያዊ ምክንያቶች መካከል ዋነኞቹ በአሰባሰቡ ዙርያ የነበሩት አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲሆኑ ቀደም ሲል በስፋት ዳሰናቸዋል፡፡ ከውስጣዊ ማስረጃዎች መካከል ደግሞ ምንጮቹ ይጠቀሳሉ፡፡

ቁርኣን ከሰማይ የመጣ መገለጥ መሆኑን ደጋግሞ ቢናገርም ነገር ግን ከሰማይ መጣ የሚያስብል በሙሐመድ ዘመን የማይታወቅ ምንም የተለየ መገለጥ በውስጡ አይገኝም፡፡ የቁርኣን ምንጮችን በተመለከተ የሐመር መጽሔት አዘጋጆች በማስረጃ የተደገፈ ሙግት ያቀረቡ ሲሆን ሐሰን ታጁ በመጽሔቱ ላይ ለተነሱት ነጥቦች የረባ ማስተባበያ መስጠት አልቻሉም፡፡[1] በቁርኣን ላይ ለቀረቡት ሒሶች መልስ ከመስጠት ይልቅ ፍሬ ከርስኪ የሌላቸውን ሐተታዎች በማብዛትና ቀደም ሲል በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያቀረቧቸውን አሰልቺ አሉባልታዎች በመደጋገም ብዙ ገፆችን አባክነዋል (ገፅ 77-124)፡፡

  1. ቁርኣንና መጽሐፍ ቅዱስ

“ቁርኣን ከመጽሐፍ ቅዱስ ኮርጇል” ለሚለው ሙግት መልስ መስጠት የሚጀምሩት “ክርስቲያኖች ብሉይ ኪዳንን በሞላ ከአይሁድ ኮርጀዋል” በሚል “አጸፋዊ” ክስ ነው (ገፅ 82-83)፡፡ ይህንን ገለባ ሙግት ቀደም ሲል መልስ ስለሰጠንበት መድገሙ አስፈላጊ አይደለም፡፡ የኩረጃውን ክስ ለማጠናከር “ብሉይ ኪዳን የክርስትና አካል እንዲሆን የተወሰነው በ397 ዓ.ም. በካርታጎ ጉባኤ ነው” የሚል የተሳሳተ መረጃ አስተላልፈዋል (ገፅ 83)፡፡ የካርታጎ ጉባኤ 27ቱን የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ጨምሮ የብሉይ ኪዳንን መጻሕፍት ዝርዝር ቢጠቅስም ቀደም ሲል የታወቀውን እውነታ ከማረጋገጥ አኳያ እንጂ ውሳኔ ከማስተላለፍ አኳያ አልነበረም፡፡ ብሉይ ኪዳን ቃለ እግዚአብሔር መሆኑን አዲስ ኪዳን በተደጋጋሚ ጠቅሷል፡፡ ከሐዋርያት ዘመን በኋላ በተጻፉት የአበው ጽሑፎች ውስጥም ይህ ሃቅ ተረጋግጧል፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ ብሉይ ኪዳን የክርስትና መጽሐፍ ያልነበረበት ዘመን ስላልነበረ ውሳኔው በካርታጎ ጉባኤ እንደተላለፈ መናገር ስህተት ነው፡፡

በማስከተል ደግሞ የቁርኣን ባሕሪያት ናቸው ያሏቸውን 3 ነጥቦች ከጠቀሱ በኋላ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ያለውን ግንኙነት እንዲህ ያስቀምጣሉ፡-

  • ከብሉይና ከአዲስ ኪዳን ጋር ተመሳሳይ መልእክት ሲይዝ ከመበረዝና ከመከለስ ሾልከው ያመለጡ እውነቶችን እያጸደቀ ነው (ገፅ 85)፡፡
  • ከነርሱ የተለየ ወይም የሚጋጭ መልእክት ሲይዝ እውነቱን ከሐሰት በመለየት ሐሰታቸውን አጋልጦ እውነቱን እያስቀመጠ ነው (ገፅ 86)፡፡
  • ከነርሱ ውስጥ የሌለ ነገር ሲያክል ደግሞ አዲስ እውነትን እየጨመረ ነው (ገፅ 86)፡፡

የጸሐፊው አንድምታ ቁርኣን እውነት ነው ከሚል ያልተረጋገጠ ቅድመ ግንቤ የመነጨ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም፡፡ ነጥቦቹ ተቀባይነት ሊኖራቸው የሚችለው ቁርኣን እውነት መሆኑና መጽሐፍ ቅዱስ መበረዙ በማስረጃ ሲረጋገጥ ብቻ ነው፡፡ ጸሐፊው ይህንን ማድረግ አልቻሉም፡፡

ከክርስትና አቋም በመነሳት ሦስቱን ነጥቦች ቀጥሎ ባሉት መንገዶች መተርጎም ይቻላል፡-

  • ቁርኣን ከብሉይና ከአዲስ ኪዳናት ጋር ተመሳሳይ መልእክቶችን ይዞ መገኘቱ የቁርኣን ደራሲ መረጃዎቹን በትክክል ማስታወሱን ወይም ደግሞ ለዓላማው የሚመቹ ሆኖ ስላገኛቸው አዛብቶ የማቅረብ አስፈላጊነት ስላልታየው መሆኑን ያመለክታል፡፡
  • ከነርሱ የተለየ ወይም የሚጋጭ መልእክት ይዞ መገኘቱ የቁርኣን ደራሲ መረጃዎቹን በትክክል አለማስታወሱን ወይም ደግሞ ለዓላማው ስለማይመቹ ሆነ ብሎ ማዛባቱን ያመለክታል፡፡
  • በእነርሱ ውስጥ የሌለ ነገር አክሎ መጻፉ የግል ፈጠራውን መጨመሩን ወይም ደግሞ ከሌሎች ምንጮች ያገኛቸውን መረጃዎች ማካተቱን ያመለክታል፡፡

ቁርኣን እውነት መሆኑና መጽሐፍ ቅዱስ መበረዙ እስካልተረጋገጠ ድረስ ቁርኣን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ያለውን ግንኙነት ማብራራት የሚቻለው ከላይ በተቀመጡት መንገዶች ብቻ ነው፡፡

  • የመቅዳት ጽንሰ ሐሳብ

አቶ ሐሰን እንዲህ ይላሉ፡-

በተለያየ ዘመን የተጻፉ ሁለት መጽሐፍት ስለ ተመሳሳይ ርእሰ ነገር ማውጋታቸው ብቻ የኋለኛው ከፊተኛው ቀድቷል ሊያሰኝ አይችልም … መቅዳት (plagiarism) የሚኖረው የኋለኛው የፊተኛውን ሐሳብ ቃል በቃል ወይም መልእክቱን እንዳለ ሳያርምና ሳያስተካክል አዳዲስ እውነታዎችን ሳያክል እና ከፊሎቹን ውድቅ ሳያደርግ ሲወስድ ነው፡፡ (ገፅ 86)

ሜርያም ዌብስተር የተሰኘው ታዋቂ መዝገበ ቃላት “መቅዳት” (plagiarism) የሚለውን ፅንሰ ሐሳብ እንዲህ ተርጉሞታል፡-

  • የአንድን ሰው ሐሳብና ቃላት የራስ አስመስሎ ማስተላለፍ፡፡
  • የሌላውን ሥራ ውጤት ለምንጩ ዕውቅና ሳይሰጡ መጠቀም፡፡
  • የሥነ ጽሑፍ ስርቆት መፈፀም፡፡
  • ቀደም ሲል ከነበረ ምንጭ ላይ የወሰዱትን ሐሳብ እንደ አዲስ ማቅረብ፡፡[2]

የቁርኣን ጸሐፊ እነዚህን ሁሉ ተግባራት ፈፅሟል፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱስና ከሌሎች መጻሕፍት የወሰዳቸውን ሐሳቦችና ቃላት የራሱ አስመስሎ አቅርቧል እንዲሁም ቀደም ሲል የሚታወቁትን ታሪኮችና ትምህርቶች ከሰማይ የተገለጠለት መገለጥ በማስመሰል አስተላልፏል፡፡ ስለዚህ የመቅዳት ወንጀል ፈፅሟል፡፡

በማስከተል እንዲህ ይላሉ፡-

ሁለተኛው መጽሐፍ አጀንዳውን ይበልጥ አብራርቶና አስፋፍቶ፣ ይበልጥ አበጥሮና አጣርቶ ካቀረበ፣ ወይም በመጀመርያው ላይ የታዩ ችግሮችን ካረመ ተግባሩ ቅጅ ሊሆን አይችልም… (ገፅ 86-87)

ቁርኣን የመጽሐፍ ቅዱስን ታሪኮች ቆራርጦ ቅርፅ አልባ ከማድረጉ ውጪ አብራርቶና አስፍቶ ያቀረበበት አንድም ቦታ የለም፡፡ በዘመኑ ከነበሩት አፈታሪኮች የተወሰዱ እንግዳ ሐሳቦችን በመጨመር እውነተኛ የአምላክ መገለጥ አለመሆኑን አረጋግጧል፡፡ ከአፍታ በኋላ እንመለከታቸዋለን፡፡

አንድ ሰው በሆነ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙትን ታሪኮች ወይም ሐሳቦች በመቀነስና በመጨመር የተለየ ቅርፅ አስይዞ ስለጻፈ ብቻ አልቀዳም ልንል አንችልም፡፡ ምክንያቱም፡-

  • ምናልባት ምንጩ እንዳይታወቅበት ሆነ ብሎ የማምታታት ተግባር ፈፅሞ ሊሆን ይችላል፡፡
  • ምንጩን ካነበቡት ሰዎች የሰማውን በመያዝ ሌላ ጊዜ ከትውስታው ሲጽፍ የመጀመርያ ይዘቱን በመርሳት ሊቀንስ ወይም ሊጨምር ይችላል፡፡
  • ከሌላ የተዛባ ምንጭ የሰማውን ወይም ያነበበውን ተመሳሳይ ታሪክ ከዋናው ምንጭ ካገኘው ታሪክ ጋር በመቀየጥ ሊጽፍ ይችላል፡፡
  • ከዋናው ምንጭ ሳይሆን ከተዛባ ሁለተኛ ምንጭ ላይ በመቅዳ ሊጽፍ ይችላል፡፡

ኢንሳይክሎፒድያ ብሪታኒካ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች በቁርኣን ውስጥ የተለየ ቅርፅ ይዘው የመገኘታቸውን ምክንያት ሲያብራራ እንዲህ ይላል፡-

“…የተለያዩ [የቁርኣን] መገለጦችን ይዘቶች የመረመሩት ምዕራባውያን ሊቃውንት የመጽሐፍ ቅዱስ ስብዕናዎችና ክስተቶችን የተመለከቱ አብዛኞቹ ትራኬዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሠፈሩት የተለየ ይዘት እንዳላቸውና ከኋለኞቹ ዘመናት የክርስቲያን ምንጮች እንዲሁም የአይሁድ ምንጮች (ለምሳሌ ሚድራሽ) የተገኙ እንደሚመስሉ አመልክተዋል፡፡ ስለ መጪው ፍርድና ስለ ገነት የተሰጡ ገለጻዎችን የመሳሰሉት ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ደግሞ በዘመኑ ከነበሩት የሦርያ ቤተክርስቲያን አበው የተለመዱ ስብከቶች ጋር ይስማማሉ፡፡ ሆኖም ጥገኝነቱ በጽሑፍ በሠፈሩት ላይ የተመሠረተ ሳይሆን በአፈታሪክ ተፅዕኖ የመጣ ሊሆን ይችላል፡፡[3]

አቶ ሐሰን መጽሐፍ ቅዱስን ለመተቸት ኢንሳይክሎፒድያ ብሪታኒካን ደጋግመው ስለጠቀሱልን ስለ ቁርኣን የጻፈውንም በደስታ እንደሚቀበሉ ተስፋ እናደርጋለን፡፡

ቁርኣን ከመጽሐፍ ቅዱስ እንዳልቀዳ ለማሳየት በመጻሕፍቱ ውስጥ የሚገኙትን የዮሴፍን እንዲሁም የአቤልና የቃየንን ታሪኮች በማነጻጸር አቅርበዋል (ገፅ 87-97)፡፡ የታሪኮቹን ተመሳሳይነትና ልዩነት በሰንጠረዥ በማስቀመጥ ለማሳየት ከሞከሩ በኋላ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ታሪኮች “ስህተት” መሆናቸውንና በአንጻሩ ደግሞ የቁርኣን ትራኬዎች ትክክል መሆናቸውን በመግለፅ ይደመድማሉ (ገፅ 91-93፣ 97)፡፡

አንባቢያን ከእነዚህ ታሪኮች ጋር እንደሚተዋወቁ ተስፋ በማድረግ ከጊዜና ከቦታ አንጻር ሙሉ ታሪኮቹን እዚህ አናሰፍርም፡፡ ነገር ግን ዋና ዋና የምንላቸውን ነጥቦች በመጭመቅ አሳጥረን መልስ እንሰጣለን፡፡

  • የዮሴፍ ታሪክ

በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ዮሴፍ በአባቱ ዘንድ የተወደደ መልከ መልካም ልጅ ነበር፡፡ በወንድሞቹ ላይ እንደሚነግሥ ህልም በማየቱና ከእነርሱ ይልቅ ለአባታቸው ለያዕቆብ የቀረበ በመሆኑ ምክንያት ቅንዓት ስላደረባቸው አንድ ቀን እነርሱን ለመጎብኘት በሄደበት ይዘው ለእስማኤላውያን ነጋዴዎች በሃያ ብር (twenty pieces of silver) ሸጡት፡፡ ነጋዴዎቹም ወደ ግብፅ ይዘውት በመውረድ ጲጥፋራ ለተሰኘ የፈርዖን ባለሟል ሸጡት፡፡ (ዘፍ. 37)

ዮሴፍ በጲጥፋራ ቤት የተወደደ አገልጋይ ሆነ፡፡ ጌታው ጲጥፋራ እጅግ ስለተደሰተ ንብረቱን ሁሉ ለእርሱ በማስረከብ የማስተዳደሩን ኃላፊነት ሰጠው፡፡ ዮሴፍ መልከ መልካም ወጣት ስለነበር የጌታው ሚስት ዓይኗን ጣለችበት፤ አብሯት እንዲተኛም በተደጋጋሚ ትጠይቀው ነበር፡፡ ዮሴፍ ግን ፍቃደኛ አልሆነም፡፡ አንድ ቀን የዕለት ተግባሩን ለመፈፀም ወደ ቤት ሲገባ የጌታው ሚስት አብሯት እንዲተኛ የተለመደውን ጥያቄ ብታቀርብለትም ዮሴፍ እንቢታውን ገለፀ፡፡ እርሷም ልብሱ ላይ ተጠምጥማ በመያዝ ልታስገድደው ሞከረች፡፡ ዮሴፍም ልብሱን ትቶላት ሸሸ፣ ወደ ውጪም ወጣ፡፡ የቤቱን ሠራተኞች በመጥራት ዮሴፍ ሊደፍራት እንደሞከረና ድምጿን ከፍ አድርጋ ጩኸት በማሰማቷ ምክንያት ልብሱን ጥሎ እንደሸሸ ተናገረች፡፡ ለማስረጃነት ልብሱን ይዛ ከቆየች በኋላ ባሏ ሲመጣ ተመሳሳይ ታሪክ ነገረችው፡፡ ጌታው በዚህ ሁኔታ እጅግ ስለተቆጣ ወድያውኑ ዮሴፍን ወደ ወኅኒ አወረደው፡፡ (ዘፍ. 39፡1-20)

የቁርኣን ትረካ መሠረታዊ ሐሳቡ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ተመሳሳይ ቢመስልም በብዙ ነጥቦች ላይ ልዩነቶችን ያሳያል፡፡ በቁርኣን መሠረት፡-

  • ዮሴፍ ወደ ግብፅ የተሸጠው በብር ቁርጥራጭ ሳይሆን “በጥቂት ድርሃሞች” ነበር፡፡ (ሱራ 12፡20)
  • ዮሴፍ ከሴትዮዋ ጋር የመተኛት ሐሳብ አድሮበት ነበር፡፡ ቁርኣን እንዲህ ይላል፡- “በእርሱም በእርግጥ አሰበች፡፡ በእርሷም አሰበ፤ የጌታውን ማስረጃ ባላየ ኖሮ (የተፈጥሮ ፍላጎቱን ባረካ ነበር)፡፡” (ሱራ 12፡24)
  • ቀሚሱን ይዛ ቀደደች እንጂ ተጠምጥማ በመያዝ ጥሎ እንዲሸሽ አላስገደደችውም፡፡ (ሱራ 12፡25)
  • ልክ በሩ ሲከፈት ባሏ በበሩ ላይ ቆሞ አገኙት፡፡ (ሱራ 12፡25)
  • ቀድማ ብትከሰውም አንድ ምስክር «ቀሚሱ ከበስተፊት ተቀድዶ እንደሆነ እውነት ተናገረች፡፡ እርሱም ከውሸታሞቹ ነው፡፡ ቀሚሱም ከበስተኋላ ተቀድዶ እንደሆነ ዋሸች፡፡ እርሱም ከእውነተኞቹ ነው» የሚል “እውነትን ከውሸት” የመለያ ምክር ሰጠ፡፡ በዚህም መሠረት ቀሚሱ ከበስተኋላው ተቀዶ ስለተገኘ ሴትዮዋ መዋሸቷ ተረጋገጠ፡፡ (ሱራ 12፡25-28)
  • ባል ሚስቱን ከመገሰፅ በዘለለ በጉዳዩ ሲቆጣ አይታይም፡፡ (ሱራ 12፡19)
  • የከተማው ሴቶች “የዐዚዝ ሚስት ብላቴናዋን ከነፍሱ ታባብለዋለች፡፡ በእውነቱ ፍቅሩ ልቧን መቷታል” የሚል ወሬ ማናፈስ ስለጀመሩ ሴትዮዋ የከታማውን ሴቶች ምግብ አዘጋጅታ ጠራቻቸው፡፡ ለእያንዳንዳቸው ቢለዋ ከሰጠቻቸው በኋላ ዮሴፍ እንዲታያቸው አደረገች፡፡ እነርሱም በዮሴፍ ውበት ተማርከው ሲያዩት እጆቻቸውን ቆረጡ፡፡ (ሱራ 12፡30-31)
  • ሴትዮዋ ዮሴፍን መውደዷን በሴቶቹ ፊት በመናገር ፍላጎቷን ካልፈፀመ እንደምታሳስረው ዛተች፡፡ በመጨረሻም ዮሴፍ ታሰረ፡፡ (ሱራ 12፡32)

በአቶ ሐሰን መሠረት የመጽሐፍ ቅዱሱ ትረካ በሁለት ምክንያቶች ትክክል አይደለም፡፡ ከራሳቸው አንደበት እንስማ፡-

  • ዩሱፍ ልብሱን ከሴትየዋ ዘንድ ትቶ እርቃኑን አልወጣም፡፡ ይልቁንም ልብሱን እንደለበሰ ለማምለጥ ሲሞክር ከኋላው ይዛ በመጎተት ቀደደችበት፡፡
  • አባወራው ሲገባ ዩሱፍ በቦታው አልነበረም ስለራሱም አልተከላከለም የሚለው የብሉይ ኪዳን ሐሳብ በቁርኣን ታርሟል፡፡ (ገፅ 91-92)

የመጀመርያውን ነጥብ በማጠናከር እንዲህ ይላሉ፡-

… ክስተቱንም ስንመረምር የቁርኣን ትረካ ትክክል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ቁርኣንም ሆነ ብሉይ ኪዳን ዩሱፍ ንጹህና የመልካም ስነምግባር ባለቤት በመሆኑ ላይ ይስማማሉ፡፡ ይህን እውነታ በልባችን ይዘን የሁለቱን መጽሐፍት ትረካዎች እንመርምር፡፡ ብሉይ ኪዳን ዩሱፍ ልብሱን አውልቆና ከሴትየዋ ዘንድ ትቶ (እርቃኑን) እንደሄደ ይነግረናል፡፡ በአንጻሩ ቁርኣን ልብሱን እንደለበሰ ሊያመልጥ ሲታገል ከኋላው ስባ እንደቀደደችበት ይተርካል፡፡ ከዩሱፍ ንጽህና ጋር የሚጣጣመው ትረካ የቱ ነው? ልብሱን አውልቆ እርቃኑን መሄዱ ወይስ ከኋላው ጎትታ ቀደደችበት የሚለው? የብሉይ ኪዳንን ትረካ ከተቀበልን ዩሱፍ ንጹህ አይደለም፡፡ ሴትዮዋ ፡- ‹‹ለዝሙት ፈልጎኛል›› ማለቷ እውነት ነው፡፡ ምክንያቱም ዩሱፍ ልብሱን ሊያወላልቅ የሚችለው እርሱ ዝሙቱን ከፈለገና እርሷ ደግሞ እንቢ ባይ ከሆነች ብቻ ነው፡፡ (ገፅ 92-93)

ምዘና

አቶ ሐሰን የቁርኣንን ትረካ ከመጽሐፍ ቅዱስ ለማላቅ ካላቸው አጉል ምኞት የተነሳ መጽሐፉ የማይለውን የግል ፈጠራቸውን አክለውበታል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ዮሴፍ ልብሱን አወለቀ አይልም፡፡ እርቃኑንም እንደሄደ አይናገርም፡፡ ነገር ግን ሴትዮዋ ልብሱን ተጠማጥማ ስለያዘች በእጇ ትቶላት እንደሸሸ ብቻ ነው የሚናገረው፡- “ከእኔ ጋር ተኛ ስትል ልብሱን ተጠማጥማ ያዘች፤ እርሱም ልብሱን በእጅዋ ትቶላት ሸሸ ወደ ውጭም ወጣ፡፡” (ዘፍ. 39፡12)

አንድ ሰው ከላይ በለበስነው ኮታችን ወይም መደረቢያችን ላይ ተጠማጥሞ ቢታገለን ከእጁ ለማምለጥ ቀላሉ መንገድ የተጠመጠመበትን ልብስ አውልቆ እጁ ላይ ትቶ መሸሽ ነው፡፡ አቶ ሐሰን ይህ እውነታ ተሰውሮባቸው አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን ግልፅ አጀንዳ ስላላቸው ሐቁን አዛብተው በማቅረብ አንባቢያንን ለማወናበድ ሞክረዋል፡፡ ዳሩ ግን ይህችን ቀላል እውነታ መረዳት የሚሳነው አንባቢ ስለማያገኙ ከማንም በላይ ያታለሉት የገዛ ራሳቸውን ነው፡፡

በዚህ አያበቁም፡፡ እንዲህ ሲሉ የማያዛልቃቸውን ሙግት ይቀጥላሉ፡-

‹‹የለም፣ በሐይል አውልቃበት ነው›› እንዳይባል ዩሱፍ በትኩስ የወጣትነት ወኔና ጉልበት የተሞላ ፈርጣማ ነው፡፡ እንስት ታግላ አሸንፋና ጥላ ልብሱን በቀላሉ አወላለቀችበት፣ በዚህም ሳትወሰን በእጇ ይዛ እንደ መረጃ አስቀረችበት የሚለው ትረካ ይጎረብጣል፡፡ (ገፅ 93)

መጽሐፍ ቅዱስ “ታግላ አሸንፋና ጥላ በኃይል አወለቀችበት” አላለም፡፡ አሁንም ሰውየው የግል ፈጠራቸውን እየጨመሩ ነው፡፡ ደግመን እናንብበው “…ልብሱን ተጠማጥማ ያዘች፤ እርሱም ልብሱን በእጅዋ ትቶላት ሸሸ ወደ ውጭም ወጣ፡፡” ዮሴፍ ታግሎ ማሸነፍ አልተሳነውም፤ ነገር ግን በቀላሉ ለማምለጥ ሲል ነበር የተጠመጠመችበትን ልብስ እጇ ላይ ትቶ የሸሸው፡፡ በዝሙት ከምትፈልገው ሴት ጋር በመታገል ንክኪ ፈጥሮ ፈተና ውስጥ ከመግባት ይልቅ የተጠመጠመችበትን ልብስ ትቶ ማምለጡ የተሻለ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ሴትዮዋ የጌታው ሚስት መሆኗም መታወስ ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ አፍላ ጉልበቱን ተጠቅሞ በመታገል ጉዳት ቢያደርስባት ሊከተለው የሚችለውን ቅጣት ማሰብ አያዳግትም፡፡ በአጠቃላይ የዮሴፍ ውሳኔ ተገቢና በአስተውሎት የተደረገ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡

አቶ ሐሰን አሁንም አልጨረሱም፤ እንዲህ በማለት በድፍረት ይናገራሉ፡-

… በቃል አጠቃቀም ደረጃም ቁርኣን አጀንዳውን የተረከበት መንገድ ጨዋ ሲሆን የብሉይ ኪዳን ትረካ ግን ነውረኛ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ (ገፅ 93)

መጽሐፍ ቅዱስ ትረካውን ያቀረበበት መንገድ እጅግ ውብ፣ ማራኪና ጨዋነት የተሞላ ነው፡፡ አቶ ሐሰን የነውርን ትርጉም ቢያውቁ ኖሮ የአንድን ሃይማኖት ቅዱስ መጽሐፍ እንዲህ ባለ ድፍረትና ንቀት ባልተናገሩ ነበር፡፡ ይህንን በማለታቸው ክቡርና ቅዱስ የሆነውን የእግዚአብሔርን ቃል ሳይሆን የገዛ ራሳቸውን ነው ያዋረዱት፡፡ በዚህ ቦታ ነውረኛ የሆነው የሳቸው ፈጠራና ቅጥፈት ብቻ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ይህንን አረፍተ ነገር ሳነብ እንዲህ የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ትዝ አለኝ፡-

“ሁሉ ለንጹሖች ንጹሕ ነው፤ ለርኵሳንና ለማያምኑ ግን ንጹሕ የሆነ ምንም የለም፥ ነገር ግን አእምሮአቸውም ሕሊናቸውም ረክሶአል፡፡” (ቲቶ 1፡15)

እስኪ አሁን ደግሞ የቁርአኑን ትረካ እንፈትሽ፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱስ ይልቅ አሳማኝ ይሆን?

ታሪካዊ ስህተቶች

በቁርአኑ የዮሴፍ ታሪክ ውስጥ ጎልተው የሚታዩ የቁርኣንን ተዓማኒነት ከስረ መሠረቱ የሚንዱ ታሪካዊ ስህተቶች ይገኛሉ፡፡ የመጀመርያው በዮሴፍ ዘመን ዲርሃም የተሰኘ የመገበያያ ገንዘብ እንደነበረ መጠቀሱ ነው፡፡ እንዲህ ይላል፡

 وَشَرَوْهُ بِثَمَنٍ بَخْسٍ دَرَاهِمَ مَعْدُودَةٍ وَكَانُوا فِيهِ مِنَ الزَّاهِدِينَ

“በርካሽ ዋጋም በሚቆጠሩ ዲርሃሞች ሸጡት፡፡ በእርሱም ከቸልተኞቹ ነበሩ፡፡” (ሱራ 12፡20)

“And they sold him for a reduced price – a few dirhams”

ችግሩ በዮሴፍ ዘመን ዲርሃም የተሰኘ የመገበያያ ገንዘብ አለመኖሩ ብቻ አይደለም፡፡ በዮሴፍ ዘመን ሰዎች በሳንቲም መገበያየት አለመጀመራቸውም ጭምር እንጂ! በታሪክ ምሑራን መሠረት ሰዎች በሳንቲም መገበያየት የጀመሩት በ600 ዓ.ዓ. ገደማ ሲሆን[4] ዮሴፍ ደግሞ የኖረው በ1700 ዓ.ዓ. ገደማ ነው፡፡ ታድያ የመገበያያ ገንዘብ ባልተፈጠረበት ዘመን ዲርሃም የተሰኘ ገንዘብ ከየት መጣ? ችግሩን ይበልጥ ውስብስብ የሚያደርገው ደግሞ ይህ የታሪክ ተፋልሶ (anachronism) ዓለም ከመፈጠሩ በፊት በሰማይ በሚገኝ ሰሌዳ ላይ ተጽፎ እንደነበረ በሙስሊሞች ዘንድ መታመኑ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ዮሴፍ የተሸጠበትን ዋጋ በግልፅ ከማስቀመጡም በላይ በዘመኑ የነበረውን መገበያያ (የብር ቁርጥራጭ pieces of silver) ጠቅሷል፡፡ ቁርኣን ግን በሰባተኛው ክፍለ ዘመን የሚታወቀውን የመገበያያ ሳንቲም ነው የጠቀሰው፡፡

ሁለተኛው የታሪክ ተፋልሶ ዮሴፍ እስርቤት ከገባ በኋላ የተጠቀሰ ነው፡፡ ከዮሴፍ ጋር በእስር ቤት የነበሩት ሁለቱ ሰዎች ሕልማቸውን ከነገሩት በኋላ ዮሴፍ እንዲህ ማለቱ ተነግሯል፡-

«የወህኒ ቤት ጓደኞቼ ሆይ! አንደኛችሁማ ጌታውን (ንጉሡን) ጠጅ ያጠጣል፡፡ ሌላውማ ይሰቀላል፡፡ ከራሱም በራሪ (አሞራ) ትበላለች፡፡ ያ ፍቹን የምትጠይቁት ነገር ተፈጸመ፤» (አላቸው)፡፡ (ሱራ 12፡41)

“…but as for the other, he will be crucified

ስቅለት (Crucifixion በአረብኛ ሰለበ) በዚያን ዘመን በምድረ ግብፅ የወንጀለኛ መቅጫ እንደነበረ የሚያሳይ ምንም ዓይነት ታሪካዊም ሆነ የአርኮዎሎጂ ማስረጃ የለም፡፡ በምሑራን የተደረጉት ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ስቅለት የተጀመረው በ6ው ክፍለ ዘመን ቅድመ ክርስቶስ ሲሆን ዮሴፍ ከኖረበት ዘመን ጋር ቢያንስ የ1000 ዓመታት ልዩነት አለው፡፡[5]

የቁርኣን ጸሐፊ ይህንን የታሪክ ተፋልሶ የፈፀመው የመጽሐፍ ቅዱሱን ትረካ በተዛባ መንገድ በመረዳቱ ምክንያት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡-

“እስከ ሦስት ቀን ድረስ ፈርዖን ራስህን ከፍ ያደርጋል፥ በእንጨትም ላይ ይሰቅልሃል፤ ወፎችም ሥጋህን ይበሉታል።” (ዘፍ. 40፡19)

ይህ ጥቅስ ሰውየው ከተገደለ በኋላ አስክሬኑ ተሰቅሎ ወፎች እንደሚበሉት እንጂ በስቅላት እንደሚገደል አያመለክትም፡፡ የኪንግ ጀምስ የእንግሊዘኛ ትርጉም ይበልጥ ግልፅ ያደርገዋል፡-

“Yet within three days shall Pharaoh lift up thy head from off thee, and shall hang thee on a tree; and the birds shall eat thy flesh from off thee.” (Gen. 40:19) KJV

ሦስተኛው የታሪክ ተፋልሶ ዮሴፍ ከፈታው ሌላ ህልም ጋር የሚገናኝ ነው፡፡ ዮሴፍ የፈርዖንን ህልም ሲፈታ ድርቅ እንደሚሆንና ከድርቁ በኋላ ዝናብ የሚዘንብበትና ሰዎች በዝናቡ የሚያመርቱበት ዘመን እንሚመጣ ይገልፃል፡፡ ቁርኣን እንዲህ ይላል፡-

«ከዚያም ከእነዚያ በኋላ ሰዎቹ በርሱ የሚዘነቡበት በርሱም (ወይንን) የሚጨምቁበት ዓመት ይመጣል፡፡» (ሱራ 12፡49)

Then will come after that a year in which the people will be given rain and in which they will press [olives and grapes].

በዚህ ጥቅስ ውስጥ የሚገኘው ስህተት ለማንኛውም የጂኦግራፊ ተማሪ ግልፅ ነው፡፡ ግብፃውያን በዝናብ ላይ ጥገኛ እንደነበሩ ወይም ዝናብ ተጠቅመው ያመርቱ እንደነበር የሚገልፅ የታሪክም ሆነ የአርኪዎሎጂ ማስረጃ የለም፡፡ የግብፅ ህልውና የተመሠረተው በአባይ ወንዝ ላይ እንጂ በዝናብ ላይ አልነበረም፡፡ እውን ቁርኣን የፈጣሪ ቃል ነውን?

ከዮሴፍ ንፅህና አንፃር

በመጽሐፍ ቅዱስ ትረካ መሠረት ዮሴፍ ሴትዮዋን መመኘቱ አልተገለፀም፡፡ ዮሴፍ እግዚአብሔርን የሚፈራ ቅዱስ ሰው መሆኑ ከመገለፁ አንፃር ከሌላ ሰው ሚስት ጋር የመተኛት ምኞት ይኖረዋል ብሎ ማሰብ ከእርሱ ስብዕና ጋር የሚሄድ አይደለም፡፡ ነገር ግን በቁርኣን ትረካ መሠረት ሴትዮዋ አብራው መተኛት እንደፈለገችው ሁሉ እርሱም አብሯት የመተኛት ፍላጎት አድሮበት ነበር፡፡ ነገር ግን ከዚህ ፍላጎቱ ለመገታት “የጌታውን ማስረጃ” ማየት ነበረበት፡፡ ቁርኣን እንዲህ ይላል፡- “በእርሱም በእርግጥ አሰበች፡፡ በእርሷም አሰበ የጌታውን ማስረጃ ባላየ ኖሮ (የተፈጥሮ ፍላጎቱን ባረካ ነበር)፡፡” (ሱራ 12፡24)

ይህ ትረካ ከዮሴፍ ስብዕና ጋር ይሄዳልን? አቶ ሐሰን የመጽሐፍ ቅዱሱ ትረካ ዮሴፍን ጥፋተኛ እንደሚያደርግና ሴትዮዋን ንፁህ እንደሚያደርግ በመግለፅ “ነውረኛ” እንደሆነ በድፍረት መናገራቸውን እናስታውስ፡፡ ነገር ግን ዮሴፍ የሰው ሚስት መመኘቱን በመናገር ስብዕናውን ያጎደፈው መጽሐፍ ቅዱስ ወይስ ቁርኣን? ፍርዱን ለአንባቢ ትተናል፡፡

ከአመክንዮ አንፃር

በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ጲጥፋራ ሚስቱ የነገረችውን ከሰማና ያሳየችውን ማስረጃ ከተመለከተ በኋላ በቁጣ ተሞልቶ ዮሴፍን ወደ ወኅኒ አውርዶታል፡፡ ማንኛውም ባል የገዛ ሚስቱ አንድ ወንድ ሊደፍራት እንደሞከረ ተናግራ “ጥሎት የሸሸውን” ልብሱን ብታሳየው ተመሳሳይ ምላሽ እንደሚሰጥ እሙን ነው፡፡

ነገር ግን በቁርኣን መሠረት ልክ በሩ ሲከፈት ባሏ “ዐዚዝ” በሩ ላይ ቆሞ ነበር፡፡ (ስሙ አረብኛ መሆኑን ልብ ይሏል!) ቀድማ ከሰሰችው፤ በዚህ ጊዜ አንድ ሰው ጣልቃ ገብቶ እውነትን ከውሸት የመለያ ሐሳብ አቀረብ፡፡ «ቀሚሱ ከበስተፊት ተቀድዶ እንደሆነ እውነት ተናገረች፡፡ እርሱም ከውሸታሞቹ ነው፡፡ ቀሚሱም ከበስተኋላ ተቀድዶ እንደሆነ ዋሸች፡፡ እርሱም ከእውነተኞቹ ነው» አለ፡፡ የዮሴፍ ቀሚስ ከበስተኋላ ተቀዶ ስለተገኘ እርሱ ንፁህ መሆኑና እርሷ መዋሸቷ ተረጋገጠ (ሱራ 12፡25-28)፡፡

ነገር ግን ሰውየው አቀረበው የተባለው ይህ ሐሳብ ምን ያህል አሳማኝ ነው? ቀሚስ ከኋላ ሲጎተት በየትኛውም አቅጣጫ ሊቀደድ ይችላል፡፡ አይችልም እንዴ? ሴትዮዋም ደግሞ ዮሴፍ በገዛ እጁ እንደቀደደ ወይም ሲጀመር ቀሚሱ የተቀደደ እንደነበረ መናገር ትችላለች፡፡ የቀሚስ መቀደድ ባል ከሚስቱ ይልቅ በገንዘብ የገዛውን አገልጋዩን ለማመን የሚያበቃ ማስረጃ ሊሆን አይችልም፡፡

ነገር ግን በቁርኣን መሠረት “ዐዚዝ” የገዛ ሚስቱን ሲወቅስ እናያለን፡- “ቀሚሱንም ከበስተኋላ ተቀድዶ ባየ ጊዜ «እርሱ (የተናገርሺው) ከተንኮላችሁ ነው (ሴቶች) ተንኮላችሁ በእርግጥ ብርቱ ነውና» አላት፡፡” (ሱራ 12፡27)

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ተረጋግቶ እንዲህ ያለ ምላሽ ሊሰጥ የሚችል ባል ምን ዓይነት ነው? ይህ ትረካ በውነቱ አሳማኝ ነውን?

ቁርኣን በዚህ አያበቃም፡፡ ሴትዮዋ ምግብ በማዘጋጀት የከተማውን ሴቶች ሰብስባ ለያንዳንዳቸው ቢለዋ ሰጠቻቸው፡፡ ከዚያም ዮሴፍ በፊታቸው ቆሞ እንዲያዩት አደረገች፡፡ ከውበቱ የተነሳ ፈዝዘው በቢለዋ እጆቻቸውን ቆራረጡ፡፡ ሴትዮዋም ዮሴፍ አብሯት ካልተኛ እንደሚታሰር ሁሉም እየሰሙ ዛተች (ሱራ 12፡31-32)፡፡

ዮሴፍ ምንም ያህል ውብ ቢሆን ሴቶቹ የገዛ እጆቻቸውን በቢለዋ እስኪቆራርጡ ድረስ መፍዘዛቸው አሳማኝ ነውን? ዮሴፍ ፍላጎቷን ካልሞላ እንደምታሳስረው በአደባባይ ዝታለች መባሉስ ምን ያህል አሳማኝ ነው? ያ ሁሉ ምስክር ባለበት የተናገረችውን ባሏ እንዴት ሳይሰማ ቀረ? ዮሴፍ ጥፋተኛ አለመሆኑን ከተማው ሁሉ እያወቀ ባሏ ግን እርሷ ላይ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ እርሱን ማሰሩ የሚመስል ነውን?

ከዚህ ሁሉ የምንረዳው የቁርአኑ ትረካ “ትንሽ ቆሎ ይዘህ ወደ አሻሮ ተጠጋ” ዓይነት መሆኑን ነው፡፡ የቁርኣን ደራሲ የፈጠራ ታኮችን በመጨመር ውብ የሆነውን የዮሴፍን ታሪክ ወደ አፈታሪክነት ለውጦታል፡፡ አቶ ሐሰንና መሰሎቻቸው ቁርኣን ሐቀኛና አሳማኝ በሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ ትረካ ፊት የሚቆምበት ወገብ እንደሌለው ስለተገነዘቡ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያንቋሽሹ ቃላትን በመናገርና ጭቃ በመለጠፍ የገዛ መጽሐፋቸውን ግድፈቶች መሸፈን የሚችሉ ይመስላቸዋል፡፡ ነገር ግን ይህንን ባደረጉ ቁጥር በአንባቢ ፊት ራሳቸውን እንደሚያቃልሉና የገዛ እምነታቸውን እንደሚያዋርዱ የሚገነዘቡበት ማስተዋል የላቸውም፡፡

  • የአቤልና የቃየን ታሪክ

አቶ ሐሰን ቁርኣንን ለማወደስና መጽሐፍ ቅዱስን ለማንኳሰስ በሁለተኛነት ያቀረቡት የአቤልና የቃየንን ታሪክ ነው፡፡ ሁለቱንም ትረካዎች በሰንጠረዥ ካነፃፀሩ በኋላ የቁርኣን ትረካ እውነት መሆኑንና መጽሐፍ ቅዱስ ከቁርኣን የተለየባቸው ነጥቦች ሐሰት መሆናቸውን በመናገር ይደመድማሉ (ገፅ 93-97)፡፡

አቶ ሐሰን የመጽሐፍ ቅዱሱ ትረካ ስህተት መሆኑን ለማሳየት ቃየን አቤልን ከገደለ በኋላ ለእግዚአብሔር ምላሽ የሰጠበትን ሁኔታ እንደ ማስረጃ ጠቅሰዋል (ገፅ 97)፡፡

እግዚአብሔርም ቃየንን አለው፦ ወንድምህ አቤል ወዴት ነው? እርሱም አለ፦ አላውቅም የወንድሜ ጠባቂው እኔ ነኝን? (ዘፍ. 4፡9)

ነገር ግን ይህ የቃየን ምላሽ የእርሱን አመፀኛነትና የእግዚአብሔርን ታጋሽነት የሚገልፅ እንጂ ትረካው ስህተት መሆኑን የሚያሳይ አይደለም፡፡ ቃየን ክፉና አመፀኛ ሰው ስለነበር በዚህ ሁኔታ ለእግዚአብሔር መልስ መስጠቱ ከእርሱ የሚጠበቅ ነው፡፡ እግዚአብሔር ስለ አመፁ ያለ ቅጣት አልተወውም፡፡ በእግዚአብሔር ከተመረጠው ምድር አሳደደው፤ ኮብላይና ተቅበዛባዥም እንዲሆን ፈረደበት፡፡ ነገር ግን ቃየን የፀፀት አዝማሚያን በማሳየቱ ምክንያት እግዚአብሔር እራራለት፡፡ ያገኘው ሁሉ እንዳይገድለው ምልክትን አደረገለት (ዘፍ. 4፡11-15)፡፡

አቶ ሐሰን እንዲህ ይላሉ፡-

በብሉይ ኪዳን ውስጥ ታሪኩ የተወሳው እንዲሁ የእውቀት ሱስን ለመሙላት እንጅ ግልፅ አላማ የለውም፡፡ (ገፅ 96-97)

ይህ ታሪክ ቅንዓት አደገኛ መሆኑን፣ ነፍስ ማጥፋት ለቅጣት እንደሚዳርግ፣ የእግዚአብሔርን ታጋሽነት፣ የንፁህ ልብ አስፈላጊነት፣ ወዘተ. የሚያስተምር ጥልቅ ግንዛቤዎችን የሚሰጥ ታሪክ ነው፡፡ ከዚህ ታሪክ በመነሳት ብዙ ስብከቶች ተሰብከዋል፣ ትምህርቶች ተዘጋጅተዋል፣ መጻሕፍት ተጽፈዋል፡፡ ዳሩ ግን አውቀው ለጠመሙትና የደም አፍሳሽነትን መጥፎነት መማር ለማይፈልጉት ወገኖች ትርጉም ላይሰጥ ይችላል፡፡

  1. ቁርኣንና የአይሁድ አዋልድ መጻሕፍት

በቁርኣን ውስጥ የተጠቀሰው የአቤልና የቃየን ታሪክ የዮናታን ቤን ኡዝያ ተርጉም ከተሰኘ የአይሁድ አዋልድ መጽሐፍ ላይ የተቀዳ ሲሆን የሐመረ ተዋሕዶ አዘጋጆች ከነማስረጃው አስቀምጠዋል፡፡[6] ዳሩ ግን አቶ ሐሰን የሐመር አዘጋጆች ላቀረቡት ማስረጃ መልስ መስጠት ስለተሳናቸው ተከታዩን አንካሳ ምክንያት በመስጠት ርዕሱን አልፈውታል፡-

… የሐመረ ተዋህዶ ጸሐፊዎች ከአይሁድ አዋልድ መጽሐፍት የተቀዱ ናቸው የሏቸውን የቁርኣን መልእክቶች ተቀድተዋል የተባሉት መጽሐፍት ካጠገባችን የማይገኙና የቅጅውን ክስ ለመመርመር የማያመች በመሆኑ እንዳለ ትተናቸዋል… (ገፅ 108)

ጸሐፊው እንዲህ ያለ የመረጃ እጥረት ካለባቸው መጀመርያውኑ መልስ ለመስጠት መነሳታቸው አስገራሚ ነው፡፡ “ከልብ ካለቀሱ…” እንዲሉ ከልብ ፍለጋ ቢያደርጉ ኖሮ በመጻሕፍቱ ውስጥ የሚገኙትን እነዚህን ክፍሎች ቢያንስ በሌሎች ምሑራን በተጻፉት ምንጮች ውስጥ ተጠቅሰው ባገኟቸው ነበር፡፡

መጽሐፍቱ በእጃቸው ስለሌሉ መልስ መስጠት እንደማይችሉ ከገለፁ ቁርኣን ከአይሁድ አዋልድ መጻሕፍት እንዳልቀዳ በልበ ሙሉነት ሊናገሩ እንዴት ይችላሉ? “ሊቀዳ አይችልም” የሚለው ጭፍን እምነት የግል አቋም ለመያዝ ይጠቅም ይሆናል፤ ነገር ግን ሌሎችን ለማሳመን የሚበቃ ሙግት ሊሆን አይችልም፡፡

ማስረጃዎቹን አንድ በአንድ በመመርመር መልስ መስጠት ስላልቻሉ በግምትና በሐሰተኛ መረጃዎች የተሞሉትን ተከታዮቹን “ምላሾች” ሰጥተዋል፡-

በስም የጠቀሷቸውን አዋልድ መጽሐፍት አይሁድ ያልሆኑት ቀርቶ አይሁዶች እንኳ በስፋት የማያገኟቸው፣ በጥቂት የአይሁድ የሐይማኖት አዋቂዎች ብቻ የሚታወቁ እና የጠፉ ናቸው… (ገፅ 111)

አቶ ሐሰን በመሰለኝና በደሳለኝ ከተናገሩት በተጻራሪ መጻሕፍቱ አልጠፉም፤ ዛሬም ድረስ አሉ፡፡ “በስፋት አይገኙም” የሚለው ምላሽ በምንም ዓይነት የቁርኣን ጸሐፊ ከመጻሕፍቱ አለመቅዳቱን አያረጋግጥም፡፡ የቁርኣን ደራሲ እነዚህን ታሪኮች ከየትም ያምጣቸው ከየት በመጻሕፍቱ ውስጥ የሚገኙ በቁርኣን ውስጥ የተጠቀሱ ታሪኮች መኖራቸው እውነት ነው፡፡ ይህንን ሐቅ መካድ አይቻልም፡፡ ለምሳሌ፡-

  • አብረሃም በእሳት ውስጥ ተጥሎ ነበር የሚለውን ጨምሮ ስለ አብርሃም በቁርኣን ውስጥ የተወሱት ታሪኮች በሙሉ ሚድራሽ ራባ በተሰኘ የአይሁድ መጽሐፍ ውስጥ ይገኛሉ፡፡[7] (ሱራ 21፡51-71)
  • ቁርኣን ስለ ንግሥተ ሳባ ያቀረባቸው ትረካዎች ሁለተኛ የመጽሐፈ አስቴር ተርጉም በተሰኘ የአይሁድ መጽሐፍ ውስጥ ይገኛሉ፡፡[8] (ሱራ 27፡17-44)
  • ሃሩትና ማሩት ስለተባሉት ደጋሚ “መላእክት” የተነገረው ሚድራሽ ያልኩት በተሰኘ የአይሁድ መጽሐፍ ውስጥ ይገኛል፡፡[9] (ሱራ 2፡102)
  • የሲና (ጡር) ተራራ በእስራኤላውያን አናት ላይ ስለመንሳፈፉ የተነገረው አቦዳ ሳራህ በተሰኘ የአይሁድ መጽሐፍ ውስጥ ይገኛል፡፡[10] (ሱራ 7፡171)
  • የወርቁ ጥጃ ድምፅ ስለማሰማቱ የተነገረው ፒርኬ ረቢ ኤልኤዘር በተሰኘ የአይሁድ መጽሐፍ ውስጥ ይገኛል፡፡[11] (20፡88)

ታድያ የቁርኣን ጸሐፊ እነዚህን ታሪኮች ከየት አመጣቸው? ከሰማይ ወይንስ ከእነዚህ የተረታ ተረት መጻሕፍት?

አቶ ሐሰን ይቀጥላሉ፡-

[እነዚህ መጻሕፍት] በሂብራይስጥኛ እና በአረማይክ እንጅ በአረብኛ ቋንቋ አልተጻፉም፡፡ ነቢዩ ሂብራይስጥኛና አረማይክ ቀርቶ አረብኛ እንኳ ማንበብም ሆነ መጻፍ አይችሉም፡፡ እርሳቸው ይቅርና መላ የአረብያ ማሕበረሰብ ከጽሑፍና ከንባብ ጋር የማይተዋወቅ መሐይም ነበር… (ገፅ 111)

ነገር ግን በስድስተኛው ነጥብ ላይ እንዲህ በማለት የገዛ ሙግታቸውን ያፈርሳሉ፡-

ከአይሁድ ውጭ ያለው የመዲና ማሕበረሰብ እስልምናን መቀበሉና በፍቅር ማስተናገዱ ይታወቃል፡፡ ይህ ማሕበረሰብ ከአይሁዶች ጋር ለረዥም ዘመናት ግንኙነት የነበረውና የአይሁድ የሐይማኖት ትውፊቶችንና ተሪኮችን ጠንቅቆ የሚያውቅ ማሕበረሰብ ነበር፡፡ ነቢዩ የአይሁድ የጥንት ታሪኮችን ‹‹ተገለጹልኝ›› በማለት ቢያቀርቧቸው ኖሮ መዲናውያን በቀላሉ ይለዩአቸው ነበር፡፡ ነቢዩንም ሐሳዊነት ይረዱ ነበር… (ገፅ 113)

የመዲና ሕዝብ የእብራይስጥና የአረማይክ ቋንቋዎችን የማያውቅ፣ ማንበብና መጻፍ የማይችል ሆኖ ሳለ የአይሁድን ሃይማኖት ትውፊቶችና ታሪኮች “ጠንቅቆ” ማወቅ ከቻለ ነቢዩ ሙሐመድ እነዚህን ቋንቋዎች አለመቻላቸውና መጻፍና ማንበብ አለመቻላቸው የአይሁድን ሃይማኖት ትውፊቶችና ታሪኮች “ጠንቅቀው” እንዳያውቁ እንዴት ሊከለክላቸው ይችላል? ነቢዩ ሙሐመድ እንደ መዲና ሕዝቦች ሁሉ በትክክል የሚሰማ ጆሮ ስለነበራቸው ታሪኮቹን ማወቅ የማይችሉበት ምንም ምክንያት አልነበረም፡፡ በእርግጥ ሙሐመድ ማንበብና መጻፍ አይችሉም ነበር የሚለው የቁርኣንን ተዓምራዊነት ለማጉላት በኋለኞቹ ሙስሊሞች የተፈጠረ ታሪክ እንጂ ማንበብና መጻፍ ይችሉ እንደነበር በብዙ እስላማዊ ትውፊቶች ውስጥ ተዘግቧል፡፡[12]

አይሁድ እነዚህን ትውፊቶችና ታሪኮች እንደ መለኮታዊ መገለጥ ይቆጥሯቸው ስለነበር መዲናውያንም እንደዚያው መስሏቸው ሊሆን ይችላል፡፡ በተጨማሪም የመዲና አረቦች እስልምናን የተቀበሉት በፖለቲካዊ ጥቅማ ጥቅሞች ምክንያት እንጂ በቁርኣን መገለጦች ተማርከው እንዳልነበር እስላማዊ ድርሳናትን በጥንቃቄ ያነበበ ሰው ሁሉ በቀላሉ የሚገነዘበው እውነታ ነው፡፡

በሙሐመድ ዘመን የመዲና ከተማ ከሞላ ጎደል የአይሁድ ከተማ ነበረች፡፡ ነገር ግን አውስና ኸዝራጅ የተሰኙ እሳትና ጭድ የሆኑ የአረብ ጎሣዎችም ይኖሩባት ነበር፡፡ እነዚህ ጎሣዎች በአይሁድ የበላይነትና ስኬት ይቀኑ ነበር፡፡ ሙሐመድ ሁለቱን ጎሣዎች የበላይ እንደሚያደርጉና አይሁድን እንደሚያዋርዱ ቃል በመግባት አስማምተዋቸው “የአቃባ ቃል ኪዳን” በመባል የሚታወቀውን ስምምነት ከተወካዮቻቸው ጋር ተፈራረሙ፡፡ አውስ እና ኸዝራጅ በመዲና ውስጥ የነበረውን የአይሁድ የበላይነትና ቁረይሾች በርቀት ሆነው የሚያሳድሩትን ተፅዕኖ የመስበር ብርቱ መሻት ነበራቸው፡፡ ይህንን ለማሳካት “መለኮታዊ” መጽሐፍ የሚያመጣ ነቢይና ቁረይሾችን መበቀል የሚችል ጠንካራ መሪ ያስፈልጋቸው ነበር፡፡ ለዚህ ደግሞ ከሙሐመድ የተሻለ ሰው አልነበረም፡፡[13] የመዲና ሰዎች ሙሐመድን የተቀበሏቸው በፖለቲካዊ ስሌት በመሆኑ መገለጦቻቸውን ለመመርመር ያን ያህል ላይጨነቁ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ከላይ የተጠቀሰው የአቶ ሐሰን ሙግት አያስኬድም፡፡

እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፡-

በመዲና የነበሩ አረብ አይሁዶች አቀናበሩት እንዳይባል እነርሱም እነዚህን መጻሕፍት አያውቋቸውም፡፡ ነቢዩም ከነርሱ ጋር የመገናኘት እድል ያገኙት በነቢይነት ከተላኩ ከ13 ዓመታት በኋላ ነው፡፡ (ገፅ 112)

አቶ ሐሰን አይሁድ መጻሕፍቱን እንደማያውቁ በምን አወቁ? ይህንን አባባላቸውን የሚደግፍ ምን ማስረጃ አላቸው? ታሪኮቹ አይሁድ በነበሩበት ቦታ ሁሉ ስለነበሩ ሙሐመድ እነዚህን ታሪኮች ለማወቅ በመዲና ከነበሩት አይሁድ ጋር መገናኘት አያስፈልጋቸውም፡፡ ሆኖም ግን የመጨረሻዎቹን 10 ዓመታት በመዲና ስላሳለፉ ከአይሁድ በሰሟቸው ታሪኮች “መገለጦቻቸውን” ለማጠናከር ሰፊ ዕድል ነበራቸው፡፡

ሙግታቸውን ይቀጥላሉ፡-

የመዲና አይሁዶች የእስልምና ቀንደኛ ጠላቶች ነበሩ … ከአይሁዶች መካከል አንዳቸውም ‹‹ሙሐመድ ታሪኮቹን የቀዳው ከኛ የአዋልድ መጽሐፍት ነው›› አላለም… (ገፅ 112)

አቶ ሐሰን ታሪክ በአሸናፊዎች እንደሚጻፍ ዘንግተዋል፡፡ በመዲና ስለነበሩት አይሁድ መረጃዎችን የሚሰጡት እስላማዊ ምንጮች ናቸው፡፡ እነዚህ ምንጮች ደግሞ ገለልተኛ አይደሉም፡፡ በምንም መስፈርት ሐቀኛ ሊባሉም አይችሉም፡፡ ዓላማቸው በተቻለ መጠን አይሁድን ክፉና የእውነት ጠላት አድርጎ ማቅረብ ነው፡፡ ሆኖም ሙሐመድ መገለጦቻቸውን ያቃለሉትን አይሁድ፣ ነፍሰ ገዳዮችን እየላኩ ያስገድሉ እንደነበር እነዚሁ እስላማዊ ምንጮች ይናዘዛሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል አቡ አፋክ የተሰኘ ዕድሜው 120 የነበረ አይሁዳዊ አዛውንት የሙሐመድን መገለጥ በማቃለሉ ምክንያት ሰሊም ቢን ዑመይር በተሰኘ ነፍሰገዳይ ተገድሏል፡፡[14] አስማ ቢንት ማርዋን የተሰኘች ጥበበኛ ሴት በተመሳሳይ ምክንያት ዑመይር ቢን ዓዲ አል-ኸትሚ በተሰኘ ከሙሐመድ የተላከ ነፍሰ ገዳይ ተገድላለች፡፡[15] ካዕብ ቢን አል-አሽራፍ የተሰኘ አስተዋይ አይሁዳዊም ሙሐመድ ቢን መስለማ በተሰኘ የነቢዩ ተከታይ እንዲገደል ተደርጓል፡፡[16] እነዚህ ወገኖች የቁርኣንን ኩረጃ ያጋልጣሉ በሚል ስጋት ተገድለው እንደሆነስ?

አቶ ሐሰን እንዲህ ይላሉ፡-

በመዲና ውስጥ የአይሁድ ሐይማኖት ሊቃውንት የነቢዩ ሙሐመድን ትክክለኛነት ያውቁ ነበር … (ገፅ 112)

“አይሁድ የሙሐመድን ትክክለኛነት ያውቁ ነበር” የሚለው የሙስሊም ጸሐፊያን ምኞት መሠረት አልባ ነው፡፡ ካወቁ ታድያ ለምን አልተቀበሏቸውም? አቶ ሐሰን ይህንን ምኞት ያረጋግጥልኛል ያሉትን አንድ ታሪክ ጠቅሰዋል፡፡ ተራኪዋ ሳፊያ የተሰኘችው የሙሐመድ ሚስት ስትሆን ልጅ ሳለች ሁለት የአይሁድ ሊቃውንት ወደ መዲና በመሄድ ሙሐመድን ካገኟቸው በኋላ “የሚጠብቁት ነቢይ” እርሱ መሆኑን ማረጋገጣቸውንና ነገር ግን ከሁለቱ አንዱ ያለ ምክንያት እንደሚጠላው መግለፁን የሚናገር ነው (ገፅ 112-113)፡፡

ተራኪዋ ሳፊያ ማናት? ሳፊያ አይሁዳዊት ስትሆን ሙሐመድ በኸይበር አይሁድ ላይ ወረራ በፈፀሙበት ዕለት ለገንዘብ ብለው አዲስ ሙሽራ የነበረውን ባሏን፣ አጎቷንና አባቷን የገደሉባት ሴት ናት፡፡ አል-ቡኻሪ የሳፊያን ባል አሟሟት እንዲህ ይተርካል፡-

“ነቢዩ ኪናና የተባለውን ሰው በተመለከ ለዙባይር እንዲህ የሚል ትእዛዝ ሰጡ ‹የደበቀውን ሁሉ እስኪያወጣ ድረስ አሰቃየው፡፡› ስለዚህ ዙባይር ኪናና ለሞት እስኪቃረብ ድረስ ደረቱ ላይ እሳት አስቀመጠበት፡፡ ከዚያም ነቢዩ ለመስለማህ አሳልፈው ሰጡት፡፡ እርሱም አረደው፡፡”[17]

ነቢዩ ሙሐመድ ባሏን በእንዲህ ዓይነት አሳቃቂ ሁኔታ እንዲገደል ካደረጉ በኋላ በወቅቱ የ17 ዓመት ልጅ የነበረችውን ሳፊያን በዚያው ምሽት ወሰዷት፤ ሚስታቸውም አደረጓት፡፡ ይህቺ ምስኪን ሴት ነፍሷን ለማትረፍ ስትል የፈጠረችውን ታሪክ ነው እንግዲህ አቶ ሐሰን ለሙሐመድ ነቢይነት ማረጋገጫ አድርገው ያቀረቡልን፡፡ ይደንቃል!

በማስከተል ደግሞ እንዲህ ይላሉ፡-

ከአይሁድ የሐይማኖት ሊቃውንት መካከል ከፊሎቹ እስልምናን ተቀብለዋል፡፡ አብደላህ ቢን ሰላማህ የተባለው ሊቅ ተጠቃሽ ነው፡፡ ሙሐመድ ራእይ ተገለጸልኝ ያሉት የነርሱን አዋልድ መጽሐፍ ታሪኮች ገጣጥመው መሆኑን ቢያውቁ ኖሮ ከማመን ይልቅ ሐሳዊ መሆናቸውን በማጋለጥ ያዋርዷቸው ነበር፡፡ (ገፅ 113)

አብደላህ ቢን ሰላማህን የመሳሰሉ ለጥቅም ሲሉ እስልምናን የተቀበሉ በጣት የሚቆጠሩ አይሁዳውያን መኖራቸው ባይካድም ነገር ግን አቶ ሐሰን የመዲና አይሁድ ሊቃውንት እስልምናን በገፍ የተቀበሉ በማስመሰል መናገራቸው ትክክል አይደለም፡፡ በአንድ ወቅት ሙሐመድ በመዲና ወደሚገኝ የአይሁድ ምኩራብ በመግባት 12 አይሁድ እንኳ ነቢይነታቸውን ቢቀበሉ አላህ የአይሁድን ማሕበረሰብ ከቁጣው እንደሚያድን ተስፋ በመቁረጥ ስሜት ተናግረው ነበር፡፡[18] ታድያ አቶ ሐሰን ከአይሁድ ሃይማኖት ሊቃውንት መካከል ከፊሎቹ እስልምናን እንደተቀበሉ የተናገሩት በምን ማስረጃ ነው?

ሙሐመድ ወደ መዲና በገቡበት ወቅት አይሁድን ወደ እስልምና ለመሳብ ያልተሳኩ ጥረቶችን አድርገው ነበር፡፡ ለምሳሌ እንደ አይሁድ ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም አቅጣጫ በመዞር ይሰግዱ ነበር (ሱራ 2:142-145)፡፡ የአሹራ (የፋሲካ) ፆምንም ይፆሙ ነበር፡፡[19] አይሁድ በአላህ የተመረጡ ሕዝቦች መሆናቸውንም ተናግረዋል (2፡47)፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ ጥረት አይሁድ እንዲቀበሏቸው አላደረገም፡፡ በዚህም ስለተከፉ ወደ ኢየሩሳሌም አቅጣጫ የነበረውን ስግደት ወደ መካ እንዲዞር አደረጉ (ሱራ 2:142-145)፡፡ የአሹራንም ፆም በሮመዳን እንዲተካ አደረጉ፡፡[20] የሙገሳ መገለጦቻቸው በቁጣና በጥላቻ ተተኩ (ሱራ 4፡46፣ 5:51፣ 5:82)፡፡ በኒ ቀይኑቃዕ እና በኒ ነዲር የተሰኙ የአይሁድ ጎሣዎችን ከመዲና ከተማ አባረዋል፡፡ በኒ ቁረይዛ በተሰኙት ላይ ጭፍጨፋ ፈፅመዋል፡፡ የኸይበር አይሁዶችን ባርያ አድርገዋል፡፡[21] በመጨረሻም ኸሊፋ ዑመር አይሁዶችና ክርስቲያኖች ከአረብያ ተጠራርገው እንዲወጡ አስገድደዋል፡፡[22]

ነቢዩ ሙሐመድና ተከታዮቻቸው አይሁድን እንደ ሥጋት በመቁጠር ማሳደዳቸው ያለምክንያት አልነበረም፡፡ እነርሱም ደግሞ አዲሱን ሃይማኖት ከመቀበል ይልቅ ባርነት፣ ስደትና ሞትን መምረጣቸው ያለምክንያት አልነበረም፡፡ ሙሐመድ እውነተኛ ነቢይ እንዳልሆኑ የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች ነበሯቸው፡፡ እነዚህ ድምፆች ለክፍለ ዘመናት ቢታፈኑም አሁን ግን ዘመን መጥቷል፡፡ የእስልምና የሃይማኖት ሊቃውንት ቁርኣን ከአይሁድ አዋልድ መጻሕፍት የኮረጃቸውን አፈታሪኮች በተመለከተ መልስ ለመስጠት እየተገደዱ ነው፡፡ መልስ እንዳሌላቸው ደግሞ እያየን ነው፡፡

  1. ቁርኣንና ኖስቲሳውያን

ኖስቲሲዝም (Gnosticism) በሁለተኛውና በሦስተኛው ክፍለ ዘመን ተከታዮችን አፍርቶ የነበረ የኑፋቄ ቡድን ሲሆን አጀማመሩንና የተጀመረበትን ዘመን በተመለከተ በሊቃውንት መካከል ስምምነት የለም፡፡ አንዳንዶቹ ከአይሁድ ኑፋቄያዊ ቡድኖች የተገኘ እንደሆነ ሲናገሩ ሌሎች ደግሞ ክርስቲያናዊ አውድ ይሰጡታል፡፡ ሙሉ በሙሉ አረማዊ ስረ መሠረት እንዳለው የሚናገሩ ሊቃውንትም አሉ፡፡[23] ኖስቲክ (Gnostic) የሚለውን ቃል ለመጀመርያ ጊዜ የተጠቀመው ሄንሪ ሞር የተሰኘ በ17ው ክ.ዘ. የኖረ ሰው ሲሆን “ዕውቀት” የሚል ትርጉም ካለው ኖሲስ (Gnosis) ከሚለው የግሪክ ቃል የተዋቀረ ነው፡፡[24] ኖስቲሲዝም በተሰኘው እምነት ስር የሚመደቡ ብዙ ቡድኖች የሚገኙ ሲሆን ከክርስትና የሚለዩዋቸው ዋና ዋና ትምህርቶቻቸው የሚከተሉት ናቸው፡-

  • የብሉይ ኪዳን አምላክ ከአዲስ ኪዳን አምላክ የተለየ ነው፡፡ የብሉይ ኪዳን አምላክ ክፉና ውሱን ሲሆን የአዲስ ኪዳን አምላክ ሁሉን ቻይ ነው፡፡
  • ፍጥረት የተፈጠረው በሶፍያ (ጥበብ) ውድቀት ምክንያት ነው፡፡
  • ቁስ የተባለ ሁሉ ክፉ ነው፡፡
  • ኢየሱስ በስጋ አልመጣም፣ በመስቀል ላይ አልሞተም፣ ትክክለኛው ኢየሱስ መንፈስ ነው፡፡
  • የመንፈስ ትንሣኤ እንጂ የሥጋ ትንሣኤ የለም፡፡[25]

ስለ ኖስቲሳውያን ከጥንት ቤተ ክርስቲያን አበው ጽሑፎች ብዙ መረጃዎችን የምናገኝ ሲሆን በ1945 ዓ.ም. ነጅ ሐማዲ በተባለ ቦታ የኖስቲሳውያን እምነቶች የተንጸባረቁባቸው ብዙ መጻሕፍት በመገኘታቸው ምክንያት ስለ እነርሱ ያለን መረጃ ከፍ ብሏል፡፡ ከነዚህ መጻሕፍት መካከል “የቶማስ ወንጌል” የተሰኘው መጽሐፍ ይገኝበታል፡፡[26] በቁርኣን ውስጥ የሚገኘው ኢየሱስ በህፃንነቱ ከጭቃ ወፍ ሠርቶ ስለማብረሩ የሚናገረው ታሪክ ከዚህ ወንጌል ላይ የተወሰደ ነው፡፡[27] የሐመር አዘጋጆች ይህንን ነጥብ በጥሩ ሁኔታ ያስቀመጡ ቢሆንም አቶ ሐሰን መልስ ሳይሰጡ አልፈዋል፡፡[28] ከዚህ ይልቅ ጉዳዩን ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ለማዞር እንዲህ በማለት ጽፈዋል፡-

ግኖስቲኮች በእየሱስ ሞትና ስቅለት ከጳውሎሳውያን ክርስትያኖች ጋር ይለያዩ እንጅ አምላክ በሰው አምሳል በመገለጹ ላይ ይስማማሉ፡፡ ከዚህም አልፎ ለእየሱስ ትምህርት ፍፁም እንግዳ የሆነውና በ4ኛው ክፍለ ዘመን መጀመርያ የተፈበረከው የሥላሴ ጽንሰ ሐሳብ መነሻዎች ሳይሆኑ እንዳልቀሩ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ እንዲያውም ለሥላሴ ትምህርት እንደ ዋነኛ መሠረት ተደርጎ የሚቆጠረው የዩሐንስ ወንጌል ግኖስቲካዊ ሳይሆን እንደማይቀር ምሁራን ከድምዳሜ ላይ ደርሰዋል፡፡ (ገፅ 103)

[ግኖስቲክ ሳይሆን ኖስቲክ ተብሎ ነው የሚነበበው፡፡]

አቶ ሐሰን ክርስቲያኖችን ሲጠቅሱ በተደጋጋሚ “ጳውሎሳውያን” የሚለውን ቃል ይጠቀማሉ፡፡ ሙስሊም ወገኖቻችን “መሐመዳውያን” ብለን ብንጠራቸው ደስተኞች ይሆናሉን? በፍጹም አይሆኑም፡፡ ማንም እምነቱ እንዲከበርለት የሚሻ ሰው የሌላውን እምነት ማክበር ይኖርበታል፡፡ ስለ እምነታችን መሠረቶች ማስረጃ አቅርቦ መሟገትና በቅፅል ስሞች እርስ በርሳችን በመጠራራት መጎነታተል የተለያዩ ናቸው፡፡ አቶ ሐሰን በመከባበር ላይ የተመሠረቱ ምሑራዊ ውይይቶችን የማድረግ ዝግጅት ከሌላቸው ይህንን ርዕስ ለሌሎች ሙስሊሞች በመተው ወደ መጻሕፍት ትርጉም “ሙያቸው” ቢመለሱ መልካም ይመስለናል፡፡

በተደጋጋሚ እንዳየነው ኡስታዙ ማስረጃ አልባ የግል ፈጠራዎቻቸውን ከኪሳቸው እየመዘዙ በያንዳንዱ ገፅ ላይ መደርደራቸውን ቀጥለዋል፡፡ የሥላሴ ፅንሰ ሐሳብ ከኖስቲሳውያን የተቀዳ ስለመሆኑ ምንም ዓይነት ማስረጃ ማቅረብ አይችሉም፤ ምክንያቱም ኖስቲሳውያን በእግዚአብሔር ሥላሴነት ማመናቸውን የሚያሳይ ምንም ዓይነት ማስረጃ የለምና! “ሥላሴ” የሚለውን ቃል ለመጀመርያ ጊዜ የተጠቀመው ቅዱስ ጠርጡሊያኖስ ኖስቲሳውያንን የሚቃወሙ ብዙ ጽሑፎችን ጽፏል፡፡[29]

የዮሐንስ ወንጌልን በተመለከተ የተናገሩት ደግሞ በእጅጉ አስገራሚ ነው፡፡ “ለሥላሴ ትምህርት እንደ ዋነኛ መሠረት ተደርጎ የሚቆጠረው የዩሐንስ ወንጌል ግኖስቲካዊ ሳይሆን እንደማይቀር ምሁራን ከድምዳሜ ላይ ደርሰዋል” ማለት ምን የሚሉት አማርኛ ነው? “ሳይሆን አይቀርም” ማለት ጥርጣሬ እንጂ ድምዳሜ አይደለም፡፡ ስለዚህ “ሳይሆን እንደማይቀር… ከድምዳሜ ደርሰዋል” የሚል አማርኛ ትርጉም አይሰጥም፡፡ ለዚህ ጥርጣሬ ዋቢ አድርገው ያቀረቡት ቻርለስ ፒተር የተሰኘ “ክርስቲያን የታሪክ ተመራማሪ” ነው (ገፅ 103)፡፡ አቶ ሐሰን ማንነቱ በውል የማይታወቅ ፈረንጅ ስም እየጠቀሱ “ክርስቲያን ተመራማሪ” የሚል ማዕርግ የማጎናጸፍ ሱስ የተጠናወታቸው ይመስላል፡፡ እንኳንስ ማንነቱ ያልተረጋገጠ “ተመራማሪ” ተብዬ ጠቅሰው ይቅርና የተመሰከረለትን ሊቅ እንኳ ቢጠቅሱ የሊቁን ሐሳብ ማስረጃ ጠቅሰው እስካላረጋገጡ ድረስ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም፡፡ ይህ በስነ አመክንዮ ሕግ “Fallacy of Appeal to Authority” ይሰኛል፡፡ “እከሌ የተባለው ታዋቂ ሰው እንዲህ ስላለ እውነት መሆን አለበት” ብሎ ያለ ተጨባጭ ማስረጃ ከድምዳሜ መድረስ እንደ ማለት ነው፡፡ ምሑራዊ ውይይት ማለት ምን ማለት እንደሆነ የሚያውቁ ሰዎች እንዲህ ላለው ባዶ ሙግት ቦታ አይሰጡም፡፡

የዮሐንስ ወንጌል የክርስቶስን በሥጋ መምጣት፣ ሞትና ትንሣኤውን በማወጅ የኖስቲሳውያንን እምነት ያፈርሳል፡፡ ቁርኣን ግን ሞትና ትንሣኤውን በመካድ ከኖስቲሳውያን ጋር ይስማማል (ሱራ 4፡57)፡፡ ታድያ የቱ ነው ከኖስቲሲዝም የተቀዳው?

  1. ቁርኣንና መስመ ወንጌላት

ቁርኣን ከቶማስ ወንጌል ብቻ ሳይሆን የኖስቲሲዝም ንክኪ ካላቸው ከሐዋርያት ዘመን በኋላ ከተጻፉ ሌሎች መስመ ወንጌላት (Pseudo Gospels) ላይ የተቀዱ በርካታ ታሪኮችን በውስጡ አጭቋል፡፡ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል፡-

  • ሱራ 3፡44 ላይ ቁርኣን እንዲህ ይላል፡- “ይኸ ወደ አንተ የምናወርደው የኾነ ከሩቅ ወሬዎች ነው፡፡ መርየምንም ማን እንደሚያሳድግ ብርኦቻቸውን (ለዕጣ) በጣሉ ጊዜ እነሱ ዘንድ አልነበርክም፡፡ በሚከራከሩም ጊዜ እነሱ ዘንድ አልነበርክም፡፡”

ማርያምን ለማሳደግ እጣ ስለመጣሉ የያዕቆብ ወንጌል ወይም የማርያም ልደት የተሰኘው መጽሐፍ አስቀድሞ ተርኳል፡፡ እንዲህ ይላል፡-

ዕጣዎቹን ወስዶ ከቤተ መቅደሱ በመውጣት በሰጣቸው ጊዜ ምንም ምልክት አልነበረባቸውም … ዮሴፍ በእርግብ የተመሰለ መለኮታዊ ምልክት አገኘ፡፡ ካህኑም ለዮሴፍ እንዲህ አለው፡- “ዮሴፍ ሆይ የጌታን ድንግል ወስደህ እንድትንከባከባት መልካሙ ዕጣ ላንተ ወድቋል፡፡”[30]

ቁርኣን በዚህ የተረት መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘውን ታሪክ በመውሰድ መለኮታዊ መገለጥ አስመስሎ አቅርቧል፡፡

  • በተጨማሪም ሱራ 3፡37 ላይ የጌታ እናት ማርያም በቤተ መቅደስ ስለማደጓና መላእክት ይመግቧት እንደነበር የሚናገረው ታሪክ ከዚሁ የያዕቆብ ወንጌል ወይም የማርያም ልደት በመባል ከሚታወቀው የአፖክሪፋ መጽሐፍ የተወሰደ ነው፡፡[31]
  • ሱራ 19፡23-26 እንዲህ ይላል፡- “ምጡም ወደ ዘንባባይቱ ግንድ አስጠጋት፡፡ «ዋ ምኞቴ! ምነው ከዚህ በፊት በሞትኩ፡፡ ተረስቼም የቀረሁ በሆንኩ» አለች፡፡ ከበታቿም እንዲህ ሲል ጠራት «አትዘኝ፡፡ ጌታሽ ከበታችሽ ትንሽን ወንዝ በእርግጥ አድርጓል፡፡ «የዘምባባይቱንም ግንድ ወዳንቺ ወዝውዣት ባንቺ ላይ የበሰለን የተምር እሸት ታረግፍልሻለችና፡፡ «ብይም፣ ጠጭም፣ ተደሰችም፡፡ እኔ ለአልረሕማን ዝምታን ተስያለሁ፤ ዛሬም ሰውን በፍጹም አላነጋግርም» በይ፡፡”

መስመ-ማቴዎስ (Pseudo-Matthew) በተሰኘ የአፖክሪፋ መጽሐፍ ውስጥ ይህ ታሪክ እንዲህ ቀርቧል፡-

“በእናቱ ጭን ላይ በደስታ ተቀምጦ የነበረው ህፃኑ ኢየሱስ ዘንባባዋን እንዲህ አላት፡ “አንቺ ዛፍ ሆይ ቅርንጫፎችሽን ዝቅ አድርጊና እናቴን በፍሬዎችሽ አጥግቢ፡፡” ወድያውኑ በድምፁ ትዕዛዝ ዘንባባዋ ብፅዕት ወደሆነችው ወደ ማርያም እግሮች ዝቅ አለች፡፡ ሁላቸውም ፍሬዎቿን በመልቀም ጠገቡ፡፡ “ከስሮችሽ ውሃን አፍልቂ … ውሃውም ይፍሰስ” [ብሎ አዘዛት] … የውሃውንም ምንጭ ባዩ ጊዜ በጣም ደስ አላቸው፣ ጥማቸውንም አረኩ፡፡”[32]

ሁለቱ ታሪኮች መጠነኛ ልዩነት ቢኖራቸውም እጅግ የተቀራረቡ ናቸው፡፡ የቁርኣን ጸሐፊ በታሪኩ ላይ ለውጥ ማድረጉ በትክክል አለማስታወሱን ወይንም ደግሞ ከተዛባ ምንጭ መቅዳቱን ያመለክታል፡፡

  • ሱራ 19፡29-30 ላይ ቁርኣን እንዲህ ይላል፡- “ወደርሱም ጠቀሰች፡፡ «በአንቀልባ ያለን ሕጻን እንዴት እናናግራለን!» አሉ፡፡ (ሕፃኑም) አለ «እኔ የአላህ ባሪያ ነኝ፡፡ መጽሐፍን ሰጥቶኛል ነቢይም አድርጎኛል፡፡» «በየትም ስፍራ ብሆን ብሩክ አድርጎኛል፡፡ በሕይወትም እስካለሁ ሶላትን በመስገድ ዘካንም በመስጠት አዞኛል፡፡»”

ይህ ታሪክ የህፃንነቱ ታሪክ በተሰኘ የአረብኛ መጽሐፍ ውስጥ እንዲህ ሰፍሯል፡-

“በክርስቶስ ዘመን በነበረው በሊቀ ካህኑ በዮሴፍ መጽሐፍ ውስጥ (አንዳንዶች ቀያፋ ነው ይሉታል) ኢየሱስ በአንቀልባ ውስጥ ሆኖ እንደተናገረና ለእናቱ ለማርያም እንዲህ እንዳላት ተጽፏል፡- “እኔ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ፣ መልአኩ ገብርኤል በነገረሽ መልካም ዜና መሠረት የወለድሽኝ ቃል ነኝ፤ አባቴም ዓለም ይድን ዘንድ ልኮኛል፡፡”[33]

የቁርኣን ጸሐፊ ይህን በምድረ አረብ የታወቀ ታሪክ አስልሞ አቅርቦታል፡፡

በጊዜና በቦታ ባንገደብ ኖሮ ብዙ መሰል ታሪኮችን መጥቀስ በቻልን ነበር፡፡ ነገር ግን የቁርኣን ምንጭ መለኮታዊ አለመሆኑን ለማረጋገጥ ይህ በቂ ይመስለናል፡፡


ማጣቀሻዎች

[1] ሐመር ልዩ ዕትም፣ 2000፣ ገፅ 29-35

[2] Merriam-Webster Dictionary, Online Edition: https://www.merriam-webster.com/dictionary/plagiarism

[3] Encyclopædia Britannica, page 6. Entry “Islam”

[4] The Origin of Electrum Coinage by Robert W. Wallace, a professor at Northwestern University, in American Journal of Archaeology, July 1987

[5] Britannica: Encyclopedia of World Religions; p. 270

[6] ሐመር ልዩ ዕትም፣ 2000፣ ገፅ 30

[7] Rev. W. ST Clair Tisdall. The Sources of Islam; Translated and Abridge by Sir William Muir: pp. 21-24

[8] Ibid., pp. 25-30

[9] Ibid., pp. 31-36

[10] Ibid., p. 37

[11] Ibid., p. 38

[12] Sunan Abu Dawud, Book 19, Number 2993; Sahih Bukhari 5.553; Sahih Bukhari 7.88; Sahih Bukhari 1.65; Sahih Bukhari 1.114; Sahih Bukhari 4.288; Sahih Bukhari 5.716; Sahih Bukhari 5.717; Sahih Bukhari 9.468; Sahih Bukhari 4.393, also Ibn Sa’d’s biography, Vol. II, p. 302.

[13] ሳም ሶሎሞንና ኢ.አል መቅዲሲ፡፡ አልሒጅራ፤  እስላማዊ የስደት አስተምህሮ፤ ገፅ 47

[14] Alfred Guillaume. The Life of Muhamma A Translation of Ibn Ishaq’s Sirat Rasul Allah; 1955, p. 675

[15] Ibn Hisham. Al-Sira al-Nabawiyya;  p. 306 http://www.quranicstudies.com/downfile24

[16] Sahih al-Bukhari, vol. 5 Hadith Number 369.

[17] Al-Tabari; Vol. 8, p. 122

[18] Musnad Ahmad Ibn Hanbal, Hadith Number 23464

[19] Sahih al-Bukhari, Vol. 3, Book 31, Number 222

[20] Sahih al-Bukhari, Vol. 3, Book 31, Number 116

[21] Guillaume. The Life of Muhammad; pp. 363, 437, 461, 510

[22] Sahih al-Bukhari, Vol. 3, Book 39, Number 531

[23] Geisler. Encyclopedia; p. 504

[24] Britannica, Encyclopedia of World Religions; p. 380

[25] Geisler. Encyclopedia; p. 504

[26] Britannica, Encyclopedia of World Religions; p. 380

[27] The New Testament Apocrypha, vol. 1, rev. ed. by W. Schneemelcher, trans. R. McL. Wilson, Westminster / John Knox, 1991, p. 444

[28] ሐመር፣ ልዩ ዕትም፣ 2000፣ ገፅ 34

[29] Geisler. Encyclopedia; p. 504

[30] Ibid., pp. 429-430

[31] Ibid., 429

[32] Ibid., p. 463

[33] Rev. W. ST Clair Tisdall. The Sources of Islam; p. 58

ለሐሰን ታጁ ምላሽ ዋናው ማውጫ