ለምን የኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን (ኦንሊ ጂሰስ) አባል አልሆንኩም?
ክፍል አንድ
አማኑኤል እንዳለ
“የኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን” በመባል የሚታወቀው ቤተ-እምነት ራሱን የክርስቶስ ሐዋርያት ትምህርት ቅጥያ አድርጎ የሚቆጥር ሲሆን ለመዳን የዚያን ቤተ-እምነት አስተምህሮ ማመንና መቀበል ግዴታ እንደሆነ ይሰብካል። በአገራችን የዚህ ቤተ-እምነት ታሪካዊ አጀማመር አሁን በሕይወት ከሌሉት የቀድሞ የቤተ-እምነቱ ዋና አስተዳዳሪ ቢሾፕ ተክለማርያም ገዛኸኝ የሕይወት ታሪክ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው። ቢሾፑ ቤተ-እምነቱን ከመመስረታቸው ቀደም ብሎ ወደዚህ ትምህርት እንዲገቡ ሰበብ የሆናቸውን ገጠመኝ “ትምህርተ መለኮት” በተሰኘው ክታባቸው በስፋት ገልጸዋል። በግለሰቡ መሠረት ክስተቱ “ልዕለ ተፈጥሯዊ የሆነ መለኮታዊ መገለጥ” ሲሆን ቢሾፕ ተክለማርያም ተቀብዬዋለሁ በሚሉት “መለኮታዊ መገለጥ” ኢየሱስ ራሱ ከአምስት ጊዜ በላይ በአካል በመገለጥ እንደታያቸውና ከነዚያም አጋጣሚዎች በአንዱ እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን የትኛዋ ናት ለሚለው ጥያቄያቸው መልስ በመስጠት ወደ ዩናይትድ ፔንቴኮስታል ቸርች ኢንተርናሽናል (UPCI) እንደመራቸው ይናገራሉ። በእርግጥ ቢሾፕ ተክለማርያም ብዙም ሳይቆዩ ኢየሱስ ዳግም ተገልጦላቸው “ሰማያዊ ሥጋ” የተሰኘ አዲስ አስተምህሮ እንደሰጣቸው በመናገራቸው ሳብያ ከዚያ ቀደም ብሎ የተገለጠላቸው ያው ኢየሱስ አስቀድሞ አባል እንዲሆኑበት ከመራቸው የዩናይትድ ፔንቴኮስታል ቸርች ኢንተርናሽናል (UPCI) ውግዘት ገጥሟቸዋል። ቃለ-ውግዘቱን ራሳቸው ቢሾፕ ተክለማርያም “ቃሉ ይናገር” በተሰኘ ድርሰታቸው እንዲህ አስፍረዋል፦
“ክርስቶስ መለኮታዊ ወይም “ሰማያዊ ሥጋ” ነው የሚለው ትምህርት፤ የአዳም ኃጢአት ሳይበክለው አዳማዊ የተፈጥሮ ሰውነት ያለው የማርያም ልጅ መሆኑን የሚያስተምረውን የእግዚአብሔር ቃል የሚቃረን በመሆኑ ፈጽሞ የተሳሳተ ትምህርት ነው።
“የሰማያዊ ሥጋ ትምህርት” የአብና የወልድ ውሕደት ትምህርትና ለመስዋእት መብቃት የሚችል እውነተኛ አዳማዊ ሰው ማለትም የኛን ቦታ ሊተካ የሚችል “የሥጋ ዘመዳችን የሆነ ቤዛ” የማስፈለጉን ትምህርት ውድቅ ያደርጋል። የ“ሰማያዉ ሥጋ ትምህርት” ከUPCI የእምነት አንቀጽ (ከዓለም አቀፉ የእምነት አንቀጽ እንዲሁም ከሰሜን አሜሪካ የእምነት አንቀጽ) ጋር የሚጋጭ ትምህርት ነው።
በዚህ በአንቀጽ 7 ክፍል 2 በ7ኛው አዲስ መስመር ላይ ያለው ከዚህ ቀጥሎ በተገለጠው መሠረት ታርሞ ይነበብ በማለት ቀጥሎም … ከዚህ በተጨማሪ “የክርስቶስ ሥጋ ሰማያዊ እንጂ ከምድራዊ ሥጋና ደም ጋር ዝምድና የለውም” ብሎ ለሚያስተምር ለማንኛውም ሰው የክህነት ፈቃድም ሆነ የሰባኪነት መታወቂያ አንሰጥም” ብለዋል።
ግለሰቡ ቃለ-ውግዘቱን ከላይ በተቀመጠው ሁኔታ ከጠቀሱ በኋላ እርሳቸው ፈላጭ ቆራጭ የሆኑበት ቤተ-እምነት ያለውን አቋም ደግሞ እንዲህ ሲሉ ያስቀምጣሉ፦
“ከላይ የተጠቀሰው የእምነት ውሳኔ የኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተ/ን ፈጽሞ አትቀበለውም።” (ቃሉ ይናገር ገጽ 93 ክፍል 2 ትምህርት 3።
ውድ አንባቢያን፣ የአንድ ግለሰብ እውነተኛነት የሚለካው በትምህርቱ ብቻ ሳይሆን በልምምዱም ጭምር እንደሆነ ሁላችንንም ያስማማናል። ታድያ ለቢሾፕ ተክሌ የተገለጠላቸውና እርስ በራሱ የሚጋጭ ምሪት የሰጣቸው አካል ማነው? ብሎ መጠየቅ አስተዋይነት ነው። የኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን የተሰኘውን የእምነት ተቋም እንደ እውነተኛ የክርስቶስ ቤተክርስቲያን አድርጎ መቀበል የሚሻ ማንኛውም ሰው ይህንን ጉዳይ ልብ ማለት ይኖርበታል። “ሰማያዊ ሥጋ” የሚለው አስተምህሮ በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመረመር ውድቅ ከመሆኑም ባለፈ ታሪካዊ አመጣጡ ራሱ ብዙ ጥያቄዎችን የሚያጭር እንግዳ አስተምህሮ ነው።
ኖና ፍሪማን የተሰኘች በደቡብ አፍሪካ የUPCI የመጀመሪያዋ ሚስዮናዊት በመሆን ከ40 ዓመታት በላይ አገልግላ ያለፈች እንስት የቢሾፕ ተክለማርያምን ሕይወት በሚተርከው መጽሐፏ ላይ ያሰፈረችውን ጽሑፍ በምስል አያይዣለሁ። በዚህ መጽሐፍ በግልጽ እንደሚነበበው ኢየሱስ ቢሾፕ ተከለማርያምን ለኢትዮጵያ ወንጌል እንዲሰብኩ እንደመረጣቸውና ለአገልግሎት የሚያስፈልገውን ሁሉ እራሱ እንደሚያዘጋጅላቸው ቃል ከገባላቸው በኋላ “ትክክለኛዋን ቤተ ክርስቲያኔን እራሴ እገልጥልሃለው እስከዚያው ድረስ የየትየኛውም ሃይማኖታዊ ተቋም አባል እንዳትሆን” በማለት እውነተኛውን ቤተክርስቲያን እንደሚጠቁማቸው ቃል ገብቶላቸው ነበር። የሚገርመው ነገር ቢሾፕ ተክሌ በዚህ ጊዜ የተገለጠላቸውን አካል ማንነት ባለማወቃቸው ምክንያት ከፍተኛ ግራ መጋባት ውስጥ እንደገቡ ተነግሮናል። ፍሪማን እንዲህ ስትል ጽፋለች፦
The call bewildered Tekele. He considered himself too young and lowly for God’s service. Who would listen to him if he tried to preach. Surely satan has sent this manifestation to delude me, he reasoned. For two weeks the vision hovered before him continually.
“ጥሪው ተክሌን ግራ አጋባው። ለእግዚአብሔር አገልግሎት ያልበቃ ወጣትና ታናሽ አድርጎ ራሱን ይቆጥር ነበር። ለመስበክ ቢሞክር ማን ያዳምጠዋል? በእውነት እኔን ለማሳሳት ይህንን መገለጥ የላከው ሰይጣን ነው በማለት አሰበ። ለሁለት ሳምንታትም ራዕዩ ያለማቋረጥ በፊቱ ያንዣብብ ነበር።” (Nona Freeman. Unseen Hands: The Story of Revival in Ethiopia, 1987, Word Aflame Pr, pp. 29-30)
በዚህ ታሪክ ውስጥ እንደሚነበበው ቢሾፕ ተክለማርያም ያዩትን ራዕይ ሰይጣን እንዳሳያቸው በማሰብ ግራ ተጋብተው ለሁለት ሳምንታት ከቆዩ በኋላ በመጨረሻም አንድ ኩርባን የተባለ ሚስዮናዊ አግኝቷቸው ታሪካቸውን አውግተውት እንዲጸልይላቸውና ጌታ የሚያሳየውን እንዲነግራቸው ተክሌ ተማጽነውት ተለያዩ። በበነጋው ቢሾፕ ተክሌ ወንድም ኩርባንን ሲያገኙት ወንድም ኩርባን ሮጦ አቀፋቸው። የሚገርመው ነገር ለቢሾፕ ተክሌ የተገለጠላቸው ማን እንደሆነ ወንድም ኩርባን እርግጠኛ ሆኖ ይነግራቸዋል። ይህንንም ኖና ፍሪማን በመጽሐፏ ከትበዋላች። ወንድም ኩባርን ቢሾፕ ተክለማርያም ኢየሱስ የተናገራቸውን እንዲቀበሉ ያበረታታበት ትንቢታዊ ንግግር በመጽሐፉ ውስጥ ቃል በቃል እንዲህ ይነበባል፦
Listen to what the Lord has said ‘I am Alpha and Omega, unchanging Jesus, Lord and God. I have called my servant to minister the gospel. He will bring the shining light of truth to this people. Tell him not to doubt, but to go to mekele and dedicated to himself to the ministry. I will be his shield and lead him in the way I want him to go and I will provide for his needs.’ He also told me to give you tewnety birr for your transport to mekele.
“ጌታ ያለውን ስማ። «አልፋና ዖሜጋ፥ የማይለዋወጥ ኢየሱስ ጌታና አምላክ ነኝ። ወንጌልን እንዲያገለግል አገልጋዬን ጠርቻቸዋለሁ። እርሱ [ተክሌ] ለዚህ ሕዝብ አንጸባራቂ የእውነት ብርሃን ያመጣል። ወደ መቀሌ እንዲሄድና ራሱን ለአገልግሎቱ እንዲሰጥ እንጂ እንዳይጠራጠር ንገረው። ጋሻ እሆነዋለሁ፤ እንዲሄድም በፈለግሁት መንገድ እመራዋለሁ፤ የሚያስፈልገውንም ሁሉ አሟላለታለሁ»። ወደ መቀሌ ለሚወስደው ትራንስፖርት ሃያ ብር እንድሰጥህም ነግሮኛል።”
አሁን በእርግጥም የተገለጠላቸው ኢየሱስ መሆኑን ተክሌ ልበ ሙሉ ሆነዋል። ከዚህ በኋላ በእርግጠኛነት መንፈስ ትምህርቱን በመቀበል የሕይወታቸውን ትልቁን እርምጃ መውሰድ ቻሉ። ታዲያ ወደዚህ አገልግሎት የገቡበት ዋናው መነሻ ይህ መገለጥ ነው ከተባለ ቢሾፕ ተክሌን እንደ እውነተኛ አገልጋይ የተቀበሉ ሰዎች ሁሉ በአንክሮ ሊያጤኗቸው የሚገቡ ተጣርሶዎችን እንመልከት።
- ለቢሾፕ ተክለማርያም የተገለጠላቸው ኢየሱስ ነውን?
ከላይ ባለው መረጃ መሠረት ቢሾፑ የተገለጠላቸው አልፋና ኦሜጋ ጌታ አምላክ እንደሆነ በግልጽ ተነግሯቸው እሳቸውም ተቀብለዋል። ነገር ግን የተገለጠላቸው አካል “የእኔ እውነተኛ ቤተክርስቲያን ናት” በማለት ምሪት ወደ ሰጣቸው ድርጅት ከተቀላቀሉ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ በፈጠሩት “የሰማያዊ ሥጋ” ትምህርት ምክንያት እነዚያው መገለጦቻቸን በማረጋገጥ የተቀበሏቸው ወገኖች በሙሉ ትምህርቱን ተቃውመው የቢሾፑን የአገልግሎት ማዕርግ በመግፈፍ አውግዘዋቸዋል። አስገራሚው ነገር ለቢሾፑ ይህንን ትምህርት የገለጠላቸው ይኸው ቀደም ሲል ወደ እነዚህ ሰዎች የመራቸው አካል መሆኑ ነው። ቢሾፕ ተክለማርያምም ሆኑ የኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን የተሰኘው የእምነት ተቋም ሰማያዊ ሥጋን ማመን ለመዳን የግድ እንደሆነና ይህንንም የማያምንና የማይቀበል የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው በማለት ይፈርጃሉ (ቃሉ ይናገር፣ ትምህርት 21፣ ገጽ 49፤ ትምህርት 2፣ ገጽ 16፣ በኤሌክትሮኒክስ የተዘጋጀ)። ታዲያ ጥያቄው ቢሾፕ ተከልማርያምን ወደ ክርስቶስ ተቃዋሚዎች የላካቸው እራሱ ኢየሱስ ነውን? የሚል ነው።
ለቢሾፑ የተገለጠው ኢየሱስ አይደለም የምንል ከሆነ ታዲያ ማን ሊሆን ይችላል? ብለን እንጠይቃለን።
- በሰይጣን ተታልለው ይሆንን?
ለቢሾፕ ተክሌ ተገልጦ የነበረው ኢየሱስ አይደለም ብለን ካሰብን ምናልባት ያኔ ከተገለጠላቸው በኋላ እንደፈሩት ሰይጣን ራሱ አደናግሯቸው ሊሆን ይችላል። እውነታው እንደዚያ ከሆነ ታድያ በሰይጣን ምሪት ወይም መገለጥ የተመሠረተን ቤተ-እምነት እንቀበልን? ከዚህ ጋር የሚስማማ ሰው ሊኖር ይችላል ብዬ አላስብም።
- ቃዥተው ይሆንን?
ለቢሾፑ የተገለጠው አካል ኢየሱስ ካልሆነ ወይም በሰይጣን ተታልለው ካልሆነ ሊሆን የሚችለው ሌላው አማራጭ የገዛ አእምሯቸው በፈጠረው የቁም ቅዠት (Hallucination) ምክንያት ተታልለው ሊሆን ይችላል የሚል ነው። ከዚህ በመነሳት ምናልባት ቢሾፕ ተክሌ በቅንነት የገዛ ምናባቸውን በማመን የኖሩ ሰው ናቸው ሊባል ይችላል ነገር ግን ቅን ሐሳዊ መሆናቸው ትምህርታቸውንና ቤተ-እምነታቸውን ሐራጥቃ ከመሆን አይታደግም።
- ዋሽተው ይሆንን?
የመጨረሻው አማራጭ ቢሾፑ ሆነ ብለው ያልተከሰተ ታሪክ ፈጥረው ተናግረው ሊሆን ይችላል የሚል ነው። ከላይ የተጠቀሱት ሁሉ ሊያስኬዱ አይችሉም ከተባለ ቀሪ የሆነው አማራጭ ይህ ነው። ቢሾፑ ይህንን ታሪክ ሆነ ብለው ፈጥረው ካወሩ ለሃይማኖታዊ አገልግሎት የማይበቁ ሊታመኑ የማይችሉ ሰው ይሆናሉ። በዓለም ታሪክ ሁሉ እንዲህ ያሉ ሰዎች ስላሉ ይህንን እንደ አማራጭ መያዝ ይቻላል።
ይህንን ጽሑፍ ስናጠቃልል ቢሾፕ ተክሌ የተገለጠላቸው አካል ኢየሱስ እንዳልሆነ በአዲሱ ትምህርታቸው ምክንያት ከቀደመው ቤተ-እምነታቸው ባፈነገጡና በተወገዙ ጊዜ ይፋ ሆኗል። አስቀድሞ ወደ ቤተ-እምነቱ የመራቸውና እውነተኛ ቤተክርስቲያን እንደሆነ የነገራቸው ያው ኢየሱስ ኋላ ላይ ከቤተ-እምነቱ ጋር የማይስማማ እምነት በመፍጠር ቤተ-እምነቱ የሚከተለውን ዓይነት እምነት መከተል ለዘላለም ጥፋት የሚዳርግ የሰይጣን ትምህርት እንደሆነ እንዲሰብኩ ሊነግራቸው አይችልም፤ ቃሉ እንደሚለው ክርስቶስ ራሱን አይጣረስምና!
“እግዚአብሔር ግን የታመነ ነው፥ ለእናንተም የሚነገረው ቃላችን አዎንና አይደለም አይሆንም። በእኛ ማለት በእኔና በስልዋኖስ በጢሞቴዎስም በመካከላችሁ የተሰበከ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ አዎንና አይደለም አልነበረም፥ ነገር ግን በእርሱ አዎን ሆኖአል።” (2ኛ ቆሮ 1፡8-9)
ስለዚህ ለቢሾፕ ተክሌ ክርስቶስ ካልተገለጠላቸው እውነት ሊሆን የሚችለው ከተቀሩት አማራጮች አንዱ ነው። ይህ ደግሞ እሳቸውም ሆኑ በእሳቸው የተመሠረተው ቤተ-እምነት ሐሳውያን መሆናቸውን በመግለጥ ትምህርታቸው ከአጋንንት መሆኑን ያረጋግጣል። ቢሾፕ ተክሌንም ሆነ የመጣላቸውን መገለጥ ለመቀበል ምንም ዓይነት ተዓማኒነት ያለው ማስረጃ የለም። እኒህ ሰው ትምህርታቸው በእርስ በርስ ግጭት የተሞላ የማያሳምንና ደካማ በመሆኑ ሳብያ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነ ስሙር ሙግት ከማቅረብ ይልቅ መገለጥን ተገን በማድረግ የዋኅንን ሲያወናብዱ የኖሩ ሐሳዊ መምህር ናቸው። ይህንን የምለው ግለሰቡን እንደ ግለሰብ ለመንቀፍ ሳይሆን የሰውየው የፈጠራ መገለጦች በግላጭ የሚታዩና ትምህርቶቻቸውም ከቃለ እግዚአብሔር ጋር በቀጥታ የሚጋጩ ስለሆኑ ነው። በኢትዮጵያ የሐዋርያት ቤተክርስቲያን በመባል የሚታወቀው የእምነት ተቋም የሐሳውያን ማሕበር መሆኑን እንዲህ ከመስራቹ የግል ልምምድ በመነሳት ሙግቴን አቅርቤያለሁ። በተከታታይ በማቀርባቸው ጽሑፎች ይህንን ድርጅት እንደ ትክክለኛ ቤተክርስቲያን የማልቀበልባቸውን አያሌ ምክንያቶቼን ይዤ እመጣለሁ። እስከዚያው ቸር ይቆየን።
ተጨማሪ ጽሑፎች