“ከአል-ነጃሺ” ታሪክ በስተጀርባ የሚገኝ የአክራሪዎች ሤራ
የእስልምናና የኢትዮጵያ ግንኙነት የእስልምናን ያህል እድሜ ያለው ነው፡፡ የመጀመርያዎቹ ሙስሊም ስደተኞች እምነቱ በተመሠረተ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ነበር ወደ ኢትዮጵያ የመጡት፡፡ “አል-ነጃሺ” የተሰኘ የአክሱም ንጉሥ ጥሩ አቀባበል እንዳደረገላቸውና እንደሰለመ የሚናገሩ ትርክቶች በእስላማዊ ድርሳናት ውስጥ በስፋት ይነበባሉ፡፡ ይህ ንጉሥ በብዙ እስላማዊ ጽሑፎች ውስጥ “አስሓማ ኢብን-አብጃር” ተብሏል፡፡ ስደተኞቹ ወደአገራቸው ከተመለሱ በኋላ መልካም መስተንግዶ እንደጠበቃቸውና ምንም ችግር እንዳልገጠማቸው የመሰከሩ ሲሆን ከዚህም የተነሳ ነቢዩ ሙሐመድ “ሐበሾች እስካልነኳችሁ ድረስ አትንኳቸው” ማለታቸው ይነገራል፡፡ ሆኖም የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች በየዘመናቱ የጂሃድ ሰይፍ ሲመዘዝባቸው ኖረዋል፡፡ አገር-በቀሎቹም ሆኑ የውጪ ጂሃዳውያን ቀን በፈቀደላቸው ቁጥር በኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ላይ ያላቸውን ጥላቻ በተግባር ሳይገልፁ ያለፉበት ዘመን አልነበረም፡፡
ዛሬ በውጪ የሚገኙት ፀረ ኢትዮጵያ አቋም ያላቸው ፅንፈኞችና በአገር ውስጥ የሚገኙት ነጫጭ እሾኾች የኢትዮጵያን ታሪክ በአዲስ መልክ ለመጻፍ እየሞከሩ ይገኛሉ፡፡ በዚህም በመጠቀም ለክፍለ ዘመናት በመቻቻልና በፍቅር አብሮ የኖረውን ሕዝብ እርስ በርሱ ለማባላት ኢትዮጵያ ውስጥ ጂሃድ እንዲነሳ ለማድረግ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ይህም በሁለት መልኩ ይገለፃል፡፡ የመጀመርያው “የአል-ነጃሺን” ጥንታዊ የአረቦች አፈ-ታሪክ እንደ አዲስ ማራገብ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ግራኝ አሕመድን የመሳሰሉ በኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ላይ ወረራና ጥቃቶችን የፈፀሙ ጂሃዳውያንን ማወደስ ነው፡፡
ኢብን ኢስሐቅ የተሰኙት የሙሐመድ ግለ ታሪክ ጸሐፊ “አል-ነጃሺ” እስልምናን በመቀበሉ ምክንያት ሕዝቡ እንዴት እንዳመፀበትና እርሱም ደግሞ እስላማዊውን ታቂያ (ማታለል) በመጠቀም እስልምናውን ሳይለቅ ሕዝቡንም ሳያስቆጣ እንዴት በዘዴ እንዳመለጠ ጽፈዋል፡-
ጃዕፋር ኢብን ሙሐመድ አባቱን ዋቢ አድርጎ እንደነገረኝ ሐበሾች ተሰብስበው “እምነታችንን ለቀሃል” አሉት፡፡ አመፁበትም፡፡ ስለዚህ መርከቦችን በማዘጋጀት ወደ ጃዕፋርና አብረውት ወዳሉት ሰዎች “እዚህ ላይ ተሳፍራችሁ ተዘጋጁ፤ እኔ ከተሸነፍኩኝ ወዳሰኛችሁ ቦታ ሂዱ፤ እኔ ድል ከቀናኝ ደግሞ ባላችሁበት ሁኑ” አላቸው፡፡ ከዝያም ወረቀት በመውሰድ “ከአላህ በስተቀር አምላክ የለም ሙሐመድም ደግሞ መልእክተኛው ናቸው፤ የማርያም ልጅ ዒሳ ባርያው፣ መልእክተኛው ወደ ማርያምም የጣለው መንፈሱና ቃሉ ነው” ብሎ ጻፈ፡፡ ከለበሰው ካባ ስር በቀኝ ትከሻው በኩል በማስቀመጥ ተሰልፈው ሲጠባበቁት ወደነበሩት ሐበሾች መጣ፡፡ “እናንተ ሰዎች ሆይ እኔ ከመካከላችሁ የተመርጥኩ አይደለሁምን?” አላቸው፡፡ እነርሱም “አዎ ነህ” በማለት መለሱለት፡፡ “ሕይወቴስ በናንተ መካከል እንዴት ነው?” በማለት ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም “በጣም ጥሩ ነው” በማለት መለሱለት፡፡ “ታድያ ችግራችሁ ምንድነው?” በማለት ጠየቃቸው፡፡ “እምነታችንን በመካድ “ኢየሱስ ባርያ ነው” ብለሃል” አሉት፡፡ “ታድያ እናንተ ኢየሱስ ማነው ትላላችሁ?” አላቸው፡፡ እነርሱም “እኛ እርሱ የፈጣሪ ልጅ ነው እንላለን” አሉት፡፡ ንጉሡም እጁን በደረቱ ላይ በማድረግ የማርያም ልጅ ኢየሱስ “ከዚህ በላይ አይደለም” በማለት መሰከረ፡፡ “ከዚህ” ሲል የጻፈውን ለማለት ነው፤ ነገር ግን እነርሱ በተናገረው ነገር በመርካት ተመልሰው ሄዱ፡፡ ይህ ወሬም ነቢዩ ዘንድ ደረሰ፡፡ ንጉሡም ሲሞት ጸለዩለት፣ ኃጢኣቱም ይቅር እንዲባልለት ለመኑለት፡፡[1]
“አል-ነጃሺ” የሚባል ንጉሥ በኢትዮጵያ ታሪክ እንደነበረ የሚናገሩት ብቸኛ ምንጮች እስላማዊ ጽሑፎች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጽ/ቤት “አሕመድ አል-ነጋሺ የሚባል ንጉሥ በኢትዮጵያ አልነበረም” በሚል ርዕስ ባሳተማቸው ሁለት ተከታታይ ቡክሌቶች በዚህ ስም የሚታወቅም ሆነ ወደ እስልምና እምነት የተለወጠ ንጉሥ በኢትዮጵያ ታሪክ አለመኖሩን ማስረጃዎችን በመጥቀስ መልስ ሰጥቷል፡፡ በነዚህ ቡክሌቶች ውስጥ በአክሱም የነገሡት ነገሥታት ከመጀመርያው ጀምሮ በስም ተዘርዝረው የተቀመጡ ሲሆን “ነጃሺ” የሚል ስም ግን አይገኝበትም፡፡ የእስልምና እምነት ተከታዮች ወደ ኢትዮጵያ እንደመጡ የሚነገረው በ615 ዓ.ም. አካባቢ ሲሆን በወቅቱ በሥልጣን ላይ የነበረው ንጉሥ አካለ ውድም (615-623) እንደነበር ተመልክቷል፡፡[2] አንዳንድ የታሪክ ጸሐፍት በወቅቱ የአክሱም ንጉሥ የነበረው አርማሕ እለጸሐም እንደነበረ የሚናገሩ ቢሆንም በዝርዝሩ መሠረት ቀዳማዊ አርማሕ ቅድመ እስልምና በ442-456 ዓ.ም. የነገሠና ዳግማዊ አርማሕ ደግሞ ድህረ እስልምና በ817-822 ዓ.ም. የነገሠ በመሆኑ ትክክል ሊሆን አይችልም፡፡ በግዕዝ ነጋሢ በአማርኛ ደግሞ ነጋሽ የሚለው ስያሜ ግብር አስከፋዮች ለሆኑት ሹማምንት የሚሰጥ እንጂ ለነገሥታት የሚሰጥ ስም አልነበረም፡፡ በተለይ ባህር ነጋሺ የሚለው ስያሜ የሐማሴን የባሕር በር ኀላፊ መጠርያ የነበረ ነው፡፡ ስያሜው እንዲያውም ማዕርግ እንጂ መጠርያ ስም አይደለም፡፡[3] በተጨማሪም በሰባተኛው ክፍለ ዘመን የነበሩት የአክሱም ሳንቲሞች የመስቀል ምልክት የነበራቸውና ምንም የእስልምና ምልክት የሌላቸው ናቸው፡፡ የመጀመርያዎቹ ሙስሊሞች ወደ ኢትዮጵያ መሰደዳቸው እሙን ቢሆንም ንጉሡ ሰልሟል የሚለው በእስልምና መዛግብት ውስጥ የሰፈረው ትርክት በኢትዮጵያም ሆነ በሌላ በማንኛውም የታሪክ ድርሳን ያልተመዘገበ የአርኪዎሎጂ ማስረጃም ሆነ የጽሑፍ ማስረጃ የሌለው የፈጠራ ታሪክ ነው፡፡
ነቢዩ ሙሐመድ “ሐበሾች እስካልነኳችሁ ድረስ አትንኳቸው” በማለት እንደተናገሩት የሚነገረው አባባል “ከአል-ነጃሺ” የመስለም ታሪክ ጋር ተያይዞ በተደጋጋሚ ይጠቀሳል፡፡ በርግጥ ይህ አባባል በትክክል በሙሐመድ በመነገሩ ዙርያ በሙስሊም ሊቃውንት ዘንድ ጥርጣሬ አለ፡፡[4] አባባሉ ትክክል ቢሆን እንኳ በሁለት ምክንያቶች ኢትዮጵያ ከጦርነት ነፃ ልትሆን እንደማትችል ሙሐመድ ጦይብ የተሰኙ አረባዊ ጸሐፊ ይናገራሉ፡፡ የመጀመርያው የእስላም ሕግ ተፈጻሚ አለመሆኑ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ይኩኖ አምላክ “ቃል ኪዳን በማፍረስ ሙስሊሞችን መዋጋቱ” ነው፡፡[5] ስለዚህ ሙስሊሞች “አል-ነጃሺ” እንደሰለመ ማመናቸው ኢትዮጵያ ከጂሃድ ነፃ እንድትሆን ያደርጋታል የሚለው አስተሳሰብ ዋስትና የለውም፡፡
በአሁኑ ወቅት በተለይም በአክራሪ ሙስሊሞች ዘንድ እየጎላ የመጣው አመለካከት ኢትዮጵያ “በአል-ነጃሺ” መስለም ምክንያት “የእስላም ሕጋዊ ግዛት” የመሆኗ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ አመለካከት በብዙ ሙስሊም ጸሐፊያን ጽሑፎች ውስጥ በስፋት ተንፀባርቆ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ ያህል አሊ አል-ሼኽ አሕመድ በክር የተሰኙ የሳዑዲ አረቢያ ጸሐፊ “መዓሊም አል-ሒጅራተይን ኢለ አርድ አል-ሐበሽ” (ወደ ሐበሻ ምድር የተደረጉት የሁለቱ ሒጅራዎች ባህርያት) በሚል ርዕስ በጻፉት መጽሐፍ ውስጥ አል-ነጃሺ እስልምናን በመቀበሉ ምክንያት ኢትዮጵያ የእስላም ግዛት አካል መሆኗን፣ እስልምና በአል-ነጃሺ መስለም ያስመዘገበው ድል በትክክል አለመጠበቁን፣ ጨቋኝ የሆነው የክርስትና እምነት ሙስሊሞችን በኢትዮጵያ ውስጥ ማዋረዱን፣ ኢትዮጵያ ሙስሊም አገር መሆኗን፣ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች አረቦች መሆናቸውን፣ አሕመድ ግራኝ የፈፀመው ጂሃድ የኢስላምን ጠላቶች ለመጋፈጥ ጥሩ ሞዴል መሆኑን፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረገው ጂሃድ በሙስሊም አገራት መታገዝ እንደሚገባው፣ ወዘተ. በስፋት ጽፈዋል፡፡[6]
ፕሮፌሰር ሓጋይ ኢርሊች የተሰኙ በኢትዮጵያ እስልምና ላይ ጥልቅ ጥናቶችን ያደረጉ ምሑር “የሰለመ አል-ነጃሺ” ማለትም “የሰለመ የኢትዮጵያ ንጉሥ” የሚለው ትርክት በመካከለኛው ምስራቅ በሚገኙት ፀረ ኢትዮጵያ አቋም ባላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ዘንድ “ኢትዮጵያ የእስላም ምድር ናት” በሚል እንደሚተረጎም ይገልፃሉ፡፡ ፕሮፌሰሩ ካደረጉት ጥናት በመነሳት እንደገለፁት ሙስሊሙ “አል-ነጃሺ” በጦር አዛዦቹና በካህናቱ ተከድቶ ለብቻው እንዲገለል ከተደረገ በኋላ እንደሞተ መነገሩ እስልምና ለመጀመሪያ ጊዜ የተሸነፈባት ምድር ተደርጋ እንድትቆጠርና የኢትዮጵያ የክርስትና ታሪክም “ሕገወጥ” ተደርጎ እንዲቀርብ ምክንያት ሆኗል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ እስልምና በአፍሪቃ ውስጥ ያለውን መስፋፋት የገታችና ሙስሊም ዜጎቿን የምትጨቁን አገር ተደርጋ ተቆጥራለች፡፡ በአክራሪ ሙስሊሞች አመለካከት መሠረት ኢትዮጵያ ሙስሊም መሪ እንደገና በማስቀመጥ ልትቤዥ ይገባታል፡፡ “የሰለመ አል-ነጃሺ” የሚለው መፈክር በመካከለኛው ምስራቅ ለሚገኙት ሙስሊሞች የኢትዮጵያን ክርስቲያናዊ ሥርኣት ለማጣጣልና የአፍሪቃ ቀንድ ሙስሊሞች ፖለቲካዊ ስልጣኗን እንዲቆናጠጡ ለማደፋፈር መጠቀሚያ ሆኗቸዋል፡፡ ይህ “የሰለመ አል-ነጃሺ” ታሪክ ጂሃዳውያን ኢትዮጵያ ላይ እንዲዘምቱ ምክንያት በመሆን በተደጋጋሚ አገሪቱን ለአደጋ አጋልጧታል፡፡ በአፄ ዮሐንስ ዘመን የሱዳን መሐዲዎች ለንጉሡ በጻፉት ደብዳቤ ውስጥ የአል-ነጃሺን ዱካ ተከትለው እስልምናን እንዲቀበሉ የሚያሳስብና እምቢ ካሉ ደግሞ ጥፋት እንደሚጠብቃቸው የሚገልፅ መልእክት መስፈሩን ፕሮፌሰር ሓጋይ ለዚህ እንደ ምሳሌ ይጠቅሳሉ፡፡ በምሑሩ ጥናት መሠረት ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ በገባችባቸው ጊዜያት ሁሉ አገሪቱን ለመደገፍም ሆነ ከጠላቶቿ ወገን ለመሰለፍ እንደ ዋና ጉዳይ ተነስቷል፡፡ በኢጣሊያ ወረራ ወቅትም የሆነው ይህ ነበር፡፡[7]
“የአል-ነጃሺ” ጉዳይ የታሪክ ሃቀኝነት ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ የፅንፈኛ ሙስሊሞች ፍላጎት አንዳንድ የዋኀን እንደሚያስቡት የነቢዩን ወዳጆች በመልካም ሁኔታ ያስተናገደውን የአገራችንን ንጉሥ እንደ ሙስሊም በመቁጠር “አክብሮት መስጠት” አይደለም፡፡ ይህ ታሪክ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ሙስሊም የነበረውን ንጉሥ አሰቃይተው ገድለዋል በማለት ይከሳል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች በሙስሊም ባልጀሮቻቸው ዘንድ የተጠሉ እንዲሆኑ ለማድረግ እኩይ ዓላማ ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል፡፡ እስከ ቅርብ ዘመን ድረስ “ኢትዮጵያ የመጀመርያዎቹን ሙስሊም ስደተኞች ተቀብላ ያስተናገደች አገር ናት”፤ “ሐበሾችን ካልነኳችሁ አትንኳቸው”፤ “ኢትዮጵያ ለእስልምና ክብር የሰጠ ደግ ንጉሥ የነበራት አገር ናት”፤ ወዘተ. የሚሉት አባባሎች ጎልተው ይነገሩ የነበረ ሲሆን አሁን ግን “ኢትዮጵያ ሙስሊም ንጉሷን አሰቃይታ የገደለች አገር ናት”፤ “ለእስልምና መስፋፋት እንቅፋት የሆነች አገር ናት”፤ “የእስላም ግዛት አካል ናት”፤ “ሙስሊም ዜጎቿን የምትጨቁን አገር ናት”፤ ወዘተ. የሚሉ ድምፆች አይለው እየተሰሙ ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ “የሰለመ አል-ነጃሺ” የሚለው የፈጠራ ታሪክ ለአገር ደህንነትና ለኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ህልውና አደጋ የሚፈጥር ሤራ ከበስተጀርባው የሚገኝ በመሆኑ እንዲሁም ለዘመናችን ጂሃዳውያን የፕሮፓጋንዳ መሣርያ በመሆን እያገለገለ ስለሚገኝ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ወገኖች አንድ ሊሉት ይገባል፡፡ በፈጠራ ታሪክ አገር ስለምን ለአደጋ ትጋለጥ?
————————————–
[1] Guillaume. The Life of Muhammad; pp. 154-155
[2] በአንዳንድ ጸሐፍት የንጉሡ ስም አድርአዝ ነው መባሉ የዚህ ታሪክ ብቸኛ ምንጮች የሆኑትን እስላማዊ ጽሑፎች ውድቅ ያደርጋል፡፡ በዝርዝሩ መሰረት አድርአዝ ከ595-615 ነበር የነገሠው፡፡ ስደተኞቹ ወደ አክሱም መጡ በተባለበት ዘመን (615) ከሞተ ደግሞ ከሙሐመድ ጋር የረጅም ጊዜ ግንኙነት እንደነበረውና የገፀ በረከት ልውውጥ እንዳደረገ በእስላማዊ ምንጮች ውስጥ መነገሩ ስህተት ነው ማለት ነው፡፡
[3] የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጽ/ቤት፣ 2000 ዓ.ም.፣ አሕመድ አል–ነጋሺ የሚባል ንጉሥ በኢትዮጵያ አልነበረም፤ ክፍል 1 እና ክፍል 2፡፡
[4] ሙሐመድ ጦይብ፡፡ ኢትዮጵያ እና ኢስላም፤ 1999፣ ገፅ 104፤ በኢድሪስ ሙሐመድ የተተረጎመ
[5] ዝኒ ከማሁ
[6] Haggai Erlich. Saudi Arabia & Ethiopia; 2007, pp. 194-200
[7] Ibid., p. 3