እግዚአብሔር ሰዎችን ይፈትናል ወይስ አይፈትንም?

እግዚአብሔር ሰዎችን ይፈትናል ወይስ አይፈትንም?

በወንድም ሚናስ


ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ እግዚአብሔር ማንንም አይፈትንም ሲለን፣ የዘፍጥረት ጸሓፊ የኾነው ሊቀ ነብያት ሙሴ ደግሞ እግዚአብሔር አብርሃምን እንደፈተነው ይናገራል፤  ታዲያ ይህ ግጭት አይኾንምን? ዐጭሩ መልስ አይኾንም የሚል ነው። ይህንንም በምናቀርበው ምላሽ እናረጋግጣለን። አስቀድመን ግን ኹለቱንም ምንባባት በማቅረብ እንጀምራለን።

“ከነዚህም ነገሮች በኋላ እግዚአብሔር አብርሃምን ፈተነው፥ እንዲህም አለው፦ አብርሃም ሆይ አብርሃምም፦ እነሆ፥ አለሁ አለ።” ዘፍ 22፥1

“ማንም ሲፈተን፦ በእግዚአብሔር እፈተናለሁ አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም።” ያዕ. 1፥13

በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው ክፍል እግዚአብሔር አብርሃምን እንደፈተነው ቢናገርም፣  ያዕቆብ 1፥13 ቃሉን በሚጠቀምበት  መንገድ እንደ ተፈተነ አይናገርም። በዘፍጥረት 22፥1 ላይ፣ “ፈተነው” ተብሎ የተተረጐመው የዕብራይስጥ ቃል נִסָּ֖ה  “ኒሳህ” የሚል ሲኾን፣ ስመ ጥሩ የዕብራይስጥ መዝገበ ቃላት በኾነው በብራውን ድራይቨር ብሪግስ የተሰጠው ትርጓሜ የሚከተለው ነው፦

እንግዲህ በዚህ መዝገበ-ቃላት እንደተብራራው  נִסָּ֖ה (ኒሳህ) የሚለው ግሥ አንድን ጉዳይ ለማረጋገጥ ወይም ለማወቅ የሚደረግ የሙከራ ተግባር ነው። ለዚህም ይህ ሙዳየ ቃላት ለማሳያነት በሚል ዘፍ.22፥1ን  ዐቅርቧል። ከዚህ የምንረዳው አብርሃም በእግዚአብሔር  ላይ ያለውን ጽኑ እምነት ለማወቅ የተደረገ የማረጋገጫ ፈተና መኾኑን ነው። ለዚህም ይመስላል እንደ ኤን.አይ.ቪ፣ ኤን.ኤስ.ቢ፣  ያሉ ደረጃውን የጠበቁ የእንግሊዘኛ ትርጕሞች “Tested” ሲሉ ያስቀመጡት። ኾኖም ግን አንዳንድ ወገኖች ዘፍጥረት 22፡1 ላይ נִסָּ֖ה “ኒሳህ” የሚለውን ግሥ ወክሎ የገባው  የሰባ ሊቃናት ትርጕም πειράζω “ፔይራዞ” የሚል ሲኾን በያዕቆብ 1፥13 ላይ ከሰፈረው ግሥ ጋር ተመሳሳይ መኾኑን ቢናገሩም የዘፍጥረት መጽሐፍ በኵረ ቃሉ ዕብራይስጥ እንጂ ጽርዕ ባለመኾኑ ይህ ምልከታ ወንዝ የማያሻግር ኾኖ ይቀራል ማለት ነው። ደግሞም አንድ ተመሳሳይ ቃል በተለያየ ቦታ መምጣቱ ተመሳሳይ ትርጉም ይኖረዋል ማለት አይደለም። አውዱ ይወስነዋል።

በተጨማሪም በርከት ያሉ የብሉይ ኪዳን ምሁራን የዘፍጥረት 22፥1 ክፍል አስመልክተው ከላይ ባብራራነው አግባብ አስቀምጠዋል። ለምሳሌ ቪክቶር ፒ ሃሚልተን የተባሉ ሊቅ “ፈተነው” የሚለውን ግሥ እንዲህ በማለት ይገልጹታል፦

“ጽሑፉ በግልጽ የሚያመለክተው መለኮታዊ የማረጋገጫ ፈተና እንጂ፣ አጋንንታዊ ፈተና አይደለም”[1]

በአጠቃላይ በዘፍጥረት 22፥1 ላይ የሰፈረው የዕብራይስጥ ግሥ የሚያረጋግጥልን፣ አንድን ጉዳይ ለመረዳት፣ ለማረጋገጥ፣ የሚደረግ  የማረጋገጫ ተግባር እንጂ፣ በያዕቆብ 1፥13 ላይ እንደ ተገለጸው በኀጢአት ለመጣል የሚደረግ የፈተና ዐይነት አይደለም።

ዋቢ መዝገብ
[1] Victor P. Hamilton. The New International Commentary on the Old Testament: The Book of Genesis: Chapters 18-50, p. 101.

መጽሐፍ ቅዱስ