እውን ርብቃ ይስሐቅን ስታገባው ሦስት ዓመቷ ነበርን?

እውን ርብቃ ይስሐቅን ስታገባው ሦስት ዓመቷ ነበርን?


ይህ ምልልስ በእኔና በአንድ ሙስሊም አፖሎጂስት መካከል የተደረገ ሲሆን የተጨመረ የተቀነሰ ነገር የለውም። ሙስሊም ወገኖች ሙሐመድ የ 6 ዓመት ህጻን አግብቶ በ9 ዓመቷ አብሯት መተኛቱን ለማጽደቅ የሚያደርጉትን ቀቢጸ ተስፋዊ ጥረት የሚያሳይ ጥሩ አጋጣሚ በመሆኑ ከዋናው ጽሑፍ በማስቀደም ታነቡት ዘንድ አምጥቼዋለሁ። የውይይቱን አውድ ለመግለጽ ያህል፤ ሙስሊሙ ወገን የርብቃን ዕድሜ በተመለከተ በወንድም ክርስቲያን ዳዊት ለተጻፈ ማብራርያ መልስ እየሰጠ ነበር። ይህ ምልልስ በእኔና በእርሱ መካከል የተደረገው ሙስሊሙ ወገን መልስ እንድሰጠው በኩራት ከጋበዘኝ በኋላ ነበር። ውይይቱ በማሕበራዊ ሚድያ ላይ በመደረጉና ሙስሊሙ ወገን ከተጠቀመው ከስርዓት በወጣ አካሄድ ምክንያት አንዳንድ የማይመጥኑ ንግግሮች ሊኖሩ ስለሚችሉ አንባቢው አስቀድሞ እንዲጠነቀቅ ለማሳሰብ እወዳለሁ። እነሆ ውይይቱ፦

ሙስሊም፦ ና የወዳጅህን ሬ-ሳ ሳይሸት ተረከብ፣ ልክ ዮሴፍ የአምላክህን አስክ-ሬን ከጲላጦስ እንደተቀበለው (ምላሱን ያወጣ ኢሞጂ ምስል ተጠቅሟል)።

እኔ፦ ልጁ ሙግትህን ውድቅ ያደረገው በመጽሐፍ ቅዱስ። አንተ የምትሞግተው መጽሐፍ ቅዱስ ውድቅ በሚያደርጋቸው ውጫዊ ምንጮች። አንተም ምንጮችህም ተሳስታችኋል። የተሳሳተ ምንጭ ለተሳሳተ ትርጓሜ ማስረጃ አይሆንም። ምንጮችህ መሳሳታቸውን የሚገልጹ እልፍ ምንጮችን ልጠቅስልህ እችላለሁ። ቁምነገሩ እርሱ አይደለም። አቅሙ ካለህ መጽሐፍ ቅዱስ ውሰጥ የተጻፈውን በትክልል አንብበህ መልስ ስጥ። ያልተጻፈ የሚያነቡ የተሳሳቱ ምንጮች ያንተን ስህተት የማጽደቅ አቅም የላቸውም።

ሙስሊም፦ የመጀመሪያው ሙግቴ መጽሐፍ ቅዱስ መሆኑን ልብ በል። አንድ የሊቅ ቃል ሳያስፈልግ ማንም ቃሉን ብቻ ተከተሉ ርብቃ ከሦስት ዓመት የማትበልጥ ጩጬ መሆኗን ይረዳል። በመቀጠል ማንም በራሱ መረዳት ቃሉን እንዳይተረጉም የገዛ ጥንታዊያን የኦሪት ሊቃውንቶች የተናገሩትን ነው ያመጣሁት። ኦሪት የራሱ ተፋሢሮች (ማብራሪያዎች) አሉት፣ የጠቀስኳቸው ሊቃውንቶች እንዲህ ብለህ የምታጣጥላቸው ተራ ግለሰቦች አይደሉም። ነጻ ፕላትፎም አለ፣ ገብተህ አጣራ። ድባቅ የሚመታህ ሀሳብ ሲመጣ ሁሌም ክህደት ግን አይሰለችህም? ዘመገረም።

እኔ፦ በለው። እስኪ ርብቃ ስትወለድ ይስሐቅ 37 ዓመቱ ነበር የሚል አንድ ጥቅስ አምጣ። የጠቀስከውን ምዕራፍና ቁጥር ራሱ ለመጻፍ ተሸማቀህ ቁጥር ብቻ ነው ጠቅሰህ የዘለልከው። በል አሁን እዚህ ጥቀስና እንነጋገርበት። እንደዚያ የሚልም ሆነ ያንን የሚጠቁም ነገር በፍጹም አታመጣም። ደግሞ ስንት ነገር የሚዘላብዱ የረበናተ አይሁድ ምንጮች ከመቼ ወዲህ ነው ቅዱሳት መጻሕፍትን ለመተርጎም ብቸኛ መስፈርት የሆኑት? ደግሞ ይስሐቅ ርብቃን ሲያገባት 14 ዓመቷ ነበር የሚሉ ሌሎች የአይሁድ ሚድራሽ መጻሕፍትን ምን ልታደርጋቸው ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ መሞገት ከጀመርክ በመጽሐፍ ቅዱስ ለተሰጠህ ምላሽ በመጽሐፉ ነው መልስ መስጠት ያለብህ። የተሳሳተ ትርጓሜ ወደሚሰጡ መጻሕፍት ከዘለልክ ከመጽሐፍ ቅዱስ ማስረዳት ቸግሮሃል ማለት ነው። የአይሁድን መጻሕፍት መለኪያ ካደረክ ያንተን ሐሳብ የሚደግፉትን ብቻ ሳይሆን የሚቃወሙትንም መቀበል ያስፈልግሃል። አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ አይሆንም። ደግሞ ስህተትህ ሲነገርህ የማትቀበለውን ስታንዳርድ እያመጣህ አትንፈራገጥ። አንባቢ ይታዘበኛል በል።

ሙስሊም፦ ይስሐቅ በ40 ዓመቱ ርብቃን እንዳገባት ሁሉም የሚያውቀው እውነታ ነው። ከእናቱ ሞት ተነስተን በሞሪያ ተራራ ክስተት ወቅት 37 ዓመቱ እንደነበር በቀላሉ ማወቅ እንችላለን። እስኪ በዚህ ወቅት ርብቃ መወለዷን የሚያሳይ አንድ ማስረጃ ከባይብል ስጠኝ። መቼም አታደርገውም!
በተቃራኒው ደግሞ ርብቃ ከዚያ ቡኋለ መወለዷን ዘፍጥረት 22 መጨረሻው አከባቢ ይናገራል፣ ስለ ውልደቷ የነገረን ታሪኩ ከተጠናቀቀ ቡኋለ መሆኑን ልብ ይሏል። በዚህ ቀመር ደግሞ እስከ ጋብቻው ድረስ የርብቃ ዕድሜ በተዓምር ከሦስት ሊያልፍ አይችልም ማለት ነው። በተጨማሪ ወደ ጥንታዊው የአይሁዳውያን ትውፊት በመሄድ የርብቃ ውልደት ከሞሪያ ተራራ ቡኋለ መሆኑን መገንዘብ እንችላለን። እስኪ አንተ ከጥንታዊ ትውፊቶቻቸው ላይ ርብቃ ከዚያ አስቀድመ መወለዷን የሚያሳይ አንድ ፍንጭ ስጠን። ዝምብለህ አታላዝን።

እኔ፦ ያልተጨበጠ ነገር የተረጋገጠ ሃቅ አስመስለህ የምታወራው ነገር አስቂኝ ነው። እስኪ ይስሐቅ በሞርያም ክስተት ወቅት 37 ዓመቱ እንደነበር ከመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ አምጣ። ምንም ማስረጃ የለህም። ሳራ እስከ 90 ዓመቷ ድረስ ይስሐቅን አልወለደችም (ዘፍጥረት 17:17)። ሦስቱ እንግዶች ወደ ቤቷ መጥተው በዓመቱ እንደምትወልድ ከነገሯት በኋላ ነው የወለደችው። የሞተችው ደግሞ በ127 ዓመቷ ነው (ዘፍጥረት 23:1)። ስለዚህ እርሷ ስትሞት ይስሐቅ 37 ዓመቱ ነበር። የሞርያም ክስተት ግን መች እንደሆነ አልተገለጸም። ይስሐቅ በዘፍጥረት 22:12 ላይ “ነዓር” (ብላቴና) ተብሎ ስለተጠራ ዕድሜው 37 ሊሆን እንደማይችል እናውቃለን። በነገርህ ላይ ርብቃ አልተወለደችም ብለህ የደመደምከው ራስህ ነህ ስለዚህ ላለመወለዷ ማስረጃ ጥቀስ። አልተወለደችም ብለህ ከደመደምክ በኋላ ማስረጃ ማምጣት ሲቸግርህ የዕዳ ሽግግር ማድረግህ አስቂኝ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ርብቃን በአካልም ሆነ በአእምሮ ብቁ ሴት አድርጎ አቅርቧት ሳለ የምትታቀፍ የሦስት ዓመት ህጻን ናት ያልከን አንተ ነህ። ስለዚህ ማስረጃ ማምጣት ያንተ ኃላፊነት ነው። ማምጣት ሲያቅትህ የቤት ሥራዬን ሥሩልኝ ብሎ መወትወት የሽንፈት ምልክት ነው።

አንተ ልጅ መዋሸት አይሰለችህም እንዴ? የቱ ጋ ነው መጽሐፍ ቅዱስ ርብቃ የተወለደችው ከዚህ ክስተት በኋላ ነው የሚለው? ጥቅሱን በትክክል ጠቅሰህ ጻፍና አሳየኝ። ይህንን ሁሉ ስትጽፍ አንድም ጊዜ ጥቅሱን ጽፈህ አላስነበብከንም። አንተ እንዳልከው የሚል አንድም ጥቅስ የለም። አትቅጠፍ።

ከዚህ ቀደም ባደረግናቸው ውይይቶች ወቅት መመከት ሲቸግርህ መዝረክረክ እንደምትጀምር ታዝቤያለሁ። ማላዘን እንዳንተ የሚናገረውን የማያውቅ ሰው ባሕርይ ነው። ሙያህን አትንገረኝ። Seder Olam Rabbah Chapter 1:1 ላይ ይስሐቅ ርብቃን ሲያገባት 14 ዓመቷ ነበር ይላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸችው ርብቃ ጨቅላ ህጻን አልነበረችም። አዋቂ ሴት የምትሠራውን ሥራ የምትሠራ፣ እየተከናወነ የነበረውን ጉዳይ ትርጉም የምታውቅ በሳል ልጃገረድ ነበርች። መቼስ የሙሐመድን ክፉ ተግባር ለማጽደቅ ቀቢጸ ተስፋ ውስጥ እንደገባህ ባውቅም ይህንን ላለመረዳት በዚህ መጠን የሞተ ህሊና ያለህ ሰው አድርጌ ልስልህ አልፈልግም።

ሙስሊም፦ ዳኒ pls የጠየኩህን ማስረጃ ከቻልክ አቅርብ። ካልቻልክ ለሕሊና እንተወው።

ሙስሊም፦ ዳኒ መረጃ ጠይቄሃለው እኮ

እኔ፦ ወገብህን ጠበቅ አድርገህ ሞግት። አትልመጥመጥ።

——— መጨረሻ ———

እንግዲህ እንደ ታዘባችሁት ሙስሊሙ ወገን ረበናተ አይሁድ እንዲህ አሉ ከማለት የዘለለ ማስረጃ ማቅረብ አልቻለም። መጽሐፍ ቅዱስም እንዲህ ይላል በማለት ምኞቱን ከመናገር በዘለለ ጥቅሱን ጽፎ አላሳየም። እስኪ እነርሱ በሐሰት የሚጠቅሱትን ጥቅስ እናንብበው፦

“ይህም ከሆነ በኋላ ለአብርሃም እንዲህ ተብሎ ተነገረ። እነሆ፥ ሚልካ ደግሞ ለወንድምህ ለናኮር ልጆችን ወለደች፤ እነርሱም በኵሩ ዑፅ፥ ወንድሙ ቡዝ፥ የአራም አባት ቀሙኤል፥ ኮዛት፥ ሐዞ፥ ፊልዳሥ፥ የድላፍ፥ ባቱኤል ናቸው። ባቱኤልም ርብቃን ወለደ፤ እነዚህን ስምንቱን ሚልካ ለአብርሃም ወንድም ለናኮር ወለደች። ሬሕማ የሚሉአት ቁባቱ ደግሞ ጥባህን፥ ገአምን፥ ተሐሸን፥ ሞክሳን ወለደች።” (ዘፍጥረት 22፡20-24)

አብርሃም ይህ ወሬ የደረሰው ይስሐቅን ከመሰዋት ከተመለሰ በኋላ ነበር። በትክክል ማንበብ የሚችል ሰው ሁሉ እንደሚረዳው ክፍሉ እነዚህ የተጠቀሱት ሰዎች መወለዳቸውን አብርሃም መስማቱን እንጂ መች እንደተወለዱ አይናገርም። አብርሃም ከዘመዶቹ ተለይቶ ከሀገሩ ከወጣ ብዙ ዘመናት አልፈዋል። በዚያን ዘመን ጉዞ የሚደረገው በእግርና በእንስሳት ጀርባ እንጂ እንደዚህ ዘመን ፈጣን መጓጓዣዎችና መልዕክት መለዋወጫዎች አልነበሩም፤ ስለዚህ ከሀገሩ ይህንን ያህል ርቆ የሄደ ሰው ምናልባትም በብዙ ዓመታት አንዴ መልዕክት ይደርሰው ይሆናል። በአብርሃምም ታሪክ የሆነው ይህ ነው።

እነዚህ ሙስሊም ወገኖች ከነዚህ ሁሉ ከተዘረዘሩት አሥራ ሦስት የተወለዱ ሰዎች መካከል ርብቃን ብቻ በመነጠል ወሬው ለአብርሃም በደረሰበት በዚያ ጊዜ እንደተወለች መናገራቸው የማስተዋል አቅማቸው ምን ያህል እንደ ሆነ የሚያሳይ አስቂኝ አረዳድ ነው። መቼስ ለአብርሃም ወሬው ሲደርሰው ከተወለዱበት ዓመት ጋር በዝርዝር እንደ ተነገረው የሚገልጽ ነገር በቦታው ላይ የለም። ታድያ እነዚህ ልጆችና የልጅ ልጆች ሁሉ በአንድ ዘመን ተወለዱ ሊሉን ነው ወይስ ርብቃ የተወለደችበትን ጊዜ ነጥሎ የሚገልጽ ቃል በጥቅሱ ውስጥ አንብበው ነው? ጉድ እኮ ነው!

ሌላው እነዚህ ወገኖች የረበናተ አይሁድን ምንጮች በመጠቀም የርብቃን ዕድሜ ሦስት ለማድረግ ሲሞክሩ ይታያል። እዚህ ጋር ግን ሁለት ዋና ዋና ችግሮች ይገጥሟቸዋል። የመጀመርያው የአይሁድ መጻሕፍት እርስ በርሳቸው የማይስማሙ መሆናቸው ሲሆን ሌላው ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ርብቃን ከገለጸበት አገላለጽ ጋር በግልጽ መጋጨታቸው ነው።

በመጀመርያ ደረጃ እነዚህ የአይሁድ ምንጮች በስህተቶች የተሙሉና መጽሐፍ ቅዱስን ለማብራራት የማይበቁ ሲሆን በመካከለኛው ዘመን የተጻፉ እርስ በርሳቸው የሚጋጩ ምንጮች ናቸው። Jewish Encyclopedia ስለ ጉዳዩ እንዲህ ይላል፦

The Rabbis disagree as to the age of Rebekah at the time of her marriage to Isaac. The statement of the Seder ‘Olam Rabbah (i.) and Gen. R. (lvii. 1) that Abraham was informed of Rebekah’s birth when he ascended Mount Moriah for the ‘Aḳedah, is interpreted by some as meaning that Rebekah was born at that time, and that consequently she was only three years old at the time of her marriage. Other rabbis, however, conclude from calculations that she was fourteen years old, and that therefore she was born eleven years before the ‘Aḳedah, both numbers being found in different manuscripts of the Seder ‘Olam Rabbah (comp. Tos. to Yeb. 61b). The “Sefer ha-Yashar” (section “Ḥayye Sarah,” p. 38a, Leghorn, 1870) gives Rebekah’s age at her marriage as ten years. https://jewishencyclopedia.com/articles/12610-rebekah

ትርጉም፦

ረበናት ርብቃ ከይስሐቅ ጋር በተጋባችበት ጊዜ ዕድሜዋ ስንት እንደነበረ አይስማሙም። ሴደር ኦላም ራባህ (i.) እና ጀነሲስ ራባህ አብርሃም ወደ ሞሪያ ተራራ ለአኬዳህ (መስዋዕት) በወጣ ጊዜ ስለ ርብቃ መወለድ ስለተነገረው በዚህም ምክንያት በጋብቻዋ ጊዜ ገና የሦስት ዓመት ልጅ እንደ ነበረች ይናገራሉ። ሌሎች ረበናት ግን ስሌት በመሥራት የአሥራ አራት ዓመት ልጅ እንደነበረችና ከዚህም በመነሳት የተወለደችው ከአኬዳህ አሥራ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ እንደሆነ ይናገራሉ። ሁለቱም ቁጥሮች በሴደር ኦላም ራባህ በተለያዩ የእጅ ጽሑፎች ውስጥ ይገኛሉ። “ሴፈር ሀ-ያሻር” የርብቃን ዕድሜ በጋብቻዋ ወቅት አሥር ዓመት ያህል ያደርገዋል።

ከዚህ ምሑራዊ ምንጭ እንደምንረዳው ረበናተ አይሁድ በርብቃ ዕድሜ አይስማሙም። ከታች በተቀመጠው ምስል ላይ እንደሚታየው ሙስሊሞች በተደጋጋሚ የሚጠቅሱት ሴደር ኦላም ራባህ የተሰኘው መጽሐፍ ራሱ በሌላኛው የእጅ ጽሑፉ የርብቃ ዕድሜ 14 መሆኑን ይገልጻል።

ስለዚህ የአይሁድን ምንጮች መጥቀስ ለሙስሊሞች ፋይዳ ያለው ሙግት አይደለም። ተዓማኒ አለመሆናቸው እንዲህ በግልጽ የሚታዩ እርስ በርሳቸው የማይስማሙ ምንጮችን መጥቀስ ለትዝብት ይዳርጋቸዋል።

ሌላው መጽሐፍ ቅዱስ ርብቃን ለአቅመ ሔዋን የደረሰች በአእምሮም ሆነ በአካል ብቁ የሆነች ልጃገረድ አድርጎ እንጂ የወላጆቿ ድጋፍ የሚያሻት ጨቅላ አድርጎ አይስላትም። እስኪ ይህንን እናንብብ፦

“ሲመሽም ሴቶች ውኃ ሊቀዱ በሚወጡበት ጊዜ ከከተማይቱ ውጪ በውኃው ጕድጓድ አጠገብ ግመሎቹን አስበረከከ። እንዲህም አለ። የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ እለምንሃለሁ፤ መንገዴን ዛሬ በፊቴ አቅናልኝ፥ ለጌታዬም ለአብርሃም ምሕረትን አድርግ። እነሆ፥ በዚህ የውኃ ምንጭ አጠገብ እኔ ቆሜአለሁ፥ የዚህችም ከተማ ሴቶች ልጆች ውኃውን ሊቀዱ ይመጣሉ፤ ውኃ እጠጣ ዘንድ እንስራሽን አዘንብዪ የምላት እርስዋም። አንተ ጠጣ፥ ግመሎችህን ደግሞ አጠጣለሁ የምትለኝ ቆንጆ፥ እርስዋ ለባሪያህ ለይስሐቅ ያዘጋጀሃት ትሁን፤ በዚህም ለጌታዬ ምሕረትን እንዳደረግህ አውቃለሁ። ይህን መናገሩንም ሳይፈጽም እነሆ፥ ሚልካ የወለደችው የባቱኤል ልጅ ርብቃ እንስራዋን በጫንቃዋ ተሸክማ ወጣች፤ ሚልካም የአብርሃም ወንድም የናኮር ሚስት ናት። ብላቴናይቱም መልክዋ እጅግ ያማረ፥ ወንድ የማያውቃት ድንግልም ነበረች፤ ወደ ምንጭም ወረደች እንስራዋንም ሞላች፥ ተመልሳም ወጣች። ሎሌውም ሊገናኛት ሮጠና። ከእንስራሽ ጥቂት ውኃ ታጠጪኝ ዘንድ እለምንሻለሁ አላት። እርስዋም። ጌታዬ ሆይ፥ ጠጣ አለችው፤ ፈጥናም እንስራዋን በእጅዋ አውርዳ አጠጣችው። እርሱንም ካጠጣች በኋላ። ለግመሎችህ ደግሞ ሁሉም እስኪረኩ ድረስ ውኃ እቀዳለሁ አለች። ፈጥናም ውኃውን ከእንስራዋ በማጠጫው ውስጥ ገለበጠችው፥ ደግሞም ልትቀዳ ወደ ጕድጓዱ ሮጠች፥ ለግመሎቹም ሁሉ ውኃ ቀዳች። ሰውዮውም ትክ ብሎ ይመለከታት ነበር፤ እግዚአብሔር መንገዱን አቅንቶለት እንደ ሆነ ወይም እንዳልሆነ ለማወቅም ዝም አለ። ግመሎቹም ከጠጡ በኋላ እንዲህ ሆነ፤ ሰውዮው ግማሽ ሰቅል የሚመዘን የወርቅ ቀለበት፥ ለእጆችዋም አሥር ሰቅል የሚመዘን ጥንድ የወርቅ አምባር አወጣ፤ እንዲህም አላት። አንቺ የማን ልጅ ነሽ? እስኪ ንገሪኝ፤ በአባትሽ ቤት የምናድርበት ስፍራ ይገኛልን? አለችውም። እኔ ሚልካ ለናኮር የወለደችው የባቱኤል ልጅ ነኝ። በእኛ ዘንድ ገለባና ገፈራ የሚበቃ ያህል አለ፥ ለማደሪያም ደግሞ ስፍራ አለን። ሰውዮውም አጎነበሰ፥ ለእግዚአብሔርም ሰገደ። እንዲህም አለ። ቸርነቱንና እውነቱን ከጌታዬ ያላራቀ የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን፤ እኔ በመንገድ ሳለሁ እግዚአብሔር ወደ ጌታዬ ወንድሞች ቤት መራኝ። ብላቴናይቱም ሮጠች፥ ለእናትዋም ቤት ይህን ነገር ሁሉ ተናገረች።” (ዘፍጥረት 24፡11-28)

ለመሆኑ የትኛዋ የሦስት ዓመት ህጻን ናት እንስራ አዝላ ውኅ ለመቅዳት የምትሄደው? እሺ እርሱስ ይሁን እንበል፤ የትኛዋ የሦስት ዓመት ህፃን ናት ከጉድጓድ ውኅ ቀድታ ግመሎችን የምታጠጣው? መረጃዎች እንደሚያሳዩት አንድ ግመል በአንድ ጊዜ ወደ 200 ሊትር ወይም 53 ጋሎን ያህል ይጠጣል። በዚህ ቦታ ስንት ግመሎች እንደሆኑ ባይጠቀስም ከአንድ በላይ ናቸው። አንዲት ለአቅመ ሔዋን የደረሰች ሴት ብቻዋን ግመሎችን ማጠጣት መቿላ ራሱ አስገራሚ በሆነበት ሁኔታ ከወላጆቿ እቅፍ ያልወጣች የሦስት ዓመት ህፃን ይህንን አድርጋለች ማለት በእውነቱ ከሆነ እብደት ነው። ርብቃ የአብርሃምን ሎሌ ያናገረችበት መንገድ የአእምሮ ብስለቷ ምን ያህል ከፍ ያለ እንደ ሆነ የሚያሳይ ሌላው ጉዳይ ነው። ለጋብቻውም ፈቃዷ በቤተሰቦችዋ ተጠይቆ እንደ ፈቀደች እናነባለን (ቁ. 57-58)። ርብቃ ይስሐቅን ባየችው ጊዜ የሰጠችው ምላሽ ደግሞ ከሦስት ዓመት ህፃን በጭራሽ የሚጠበቅ አይደለም፦

“ይስሐቅም በመሸ ጊዜ በልቡ እያሰላሰለ ወደ ሜዳ ወጥቶ ነበር፤ ዓይኖቹንም አቀና፥ እነሆም ግመሎች ሲመጡ አየ። ርብቃም ዓይኖችዋን አቀናች፥ ይስሐቅንም አየች፥ ከግመልም ወረደች። ሎሌውንም። ሊገናኘን በሜዳ የሚመጣ ይህ ሰው ማን ነው? አለችው። ሎሌውም። እርሱ ጌታዬ ነው አላት፤ እርስዋም መሸፈኛ ወስዳ ተከናነበች። ሎሌውም ያደረገውን ነገር ሁሉ ለይስሐቅ ነገረው። ይስሐቅም ወደ እናቱ ወደ ሣራ ድንኳን አገባት፥ ርብቃንም ወሰዳት፥ ሚስትም ሆነችው፥ ወደዳትም፤ ይስሐቅም ከእናቱ ሞት ተጽናና።” (ቁ. 63-67)

የማሰብ አቅሙ ከሦስት ዓመት ህፃን የተሻለ ሰው የሦስት ዓመት ህፃን እንዲህ ያለ ብስለት እንደ ነበራት ሊያስብ ይችላል ብለን አናምንም። ይህንን ሙግት የሚያቀርቡትን ሙስሊም ወገኖቻችንን የማሰብ አቅም በዚህ ልክ አሳንሰን መመልከት አንሻም። ሙግቱን ከልባቸው አምነውበት ሳይሆን ነቢያቸው ህፃኗን አይሻን በማግባት የፈጸመው ነውር ስላሳፈራቸው ነው። ጉዳዩ ከኅሊናቸው ጋር እየተጋጨ ስለተቸገሩ ሙስሊሙንም ሕብረተሰብ ከዚህ እምነታቸውን ሊያናጋ ከሚችል የኅሊና ክስ ነፃ ለማድረግ ስለሚፈልጉ ብቻ ነው እንዲህ ያለ መናኛ ሙግት የሚያቀርቡት። እግዚአብሔር አምላክ ልቦና እንዲሰጣቸው የዘወትር ጸሎታችን ነው።


 

ተመሳሳይ ጽሑፎች፦

ሴቶች በእስልምና