የማርቆስ ወንጌል 16፡9-20 ትክክለኛነት

የማርቆስ ወንጌል 169-20 ትክክለኛነት


መግቢያ

በአዲስ ኪዳን የምንባብ ሕየሳ (Textual Criticism) ታሪክ ውስጥ እንደ ማርቆስ ወንጌል 16፡9-20 ያለ ከፍተኛ ክርክር የቀሰቀሰ ክፍል ማግኘት አዳጋች ነው። ይህ በቤተክርስቲያን ታሪክ “ረጅሙ መዝጊያ” (The Longer Ending) ተብሎ የሚታወቀው ክፍል፣ በዘመናችን የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ዘንድ እንደ አንዳች ባዕድ አካል ተቆጥሮ ከዋናው ጽሑፍ እንዲወጣ ወይም በጥያቄ ምልክት ውስጥ እንዲገባ ሲደረግ ቆይቷል። ይህ አካሄድ ከምሁራን መድረክ አልፎ ወደ ቤተክርስቲያን መድረኮች በመሸጋገሩ፣ ብዙ ሰባኪያን ስለ ክፍሉ ትክክለኛነት የተሳሳተ ወይም ግማሽ እውነት ላይ የተመሠረተ መረጃ ለምእመናን ሲያስተላልፉ ይስተዋላሉ። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአንዳንድ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የሚገኙ ሰባኪያን በማርቆስ ወንጌል ላይ የሚያደርጉትን ተከታታይ ስብከት በቁጥር 8 ላይ እንደሚያቆሙና ቀሪዎቹን ጥቅሶች (ቁጥር 9-20) እንደማይሰብኩ በይፋ መግለጻቸው፣ በዘመናዊው የክርስትና ዓለም ውስጥ እየሰረጸ የመጣውን የምንባብ ሕየሳ ከልክ ያለፈ ተጽዕኖ በግልጽ ያሳያል።

በክፍሉ ትክክለኛነት ላይ ጥርጣሬ ያላቸው ወገኖች ለሚያነሱት መከራከሪያ መሠረት የሚያደርጉት በዋናነት ሦስት ነጥቦችን ነው፤ እነርሱም የጽሑፍ ማስረጃዎች (External Evidence)፣ የታሪክ ምስክርነቶች (Patristic Evidence) እና የቋንቋ አጠቃቀም (Internal Evidence) ናቸው። ይሁን እንጂ እነዚህ መከራከሪያዎች በጥልቀት ሲመረመሩ፣ በውስጣቸው ከፍተኛ የሆነ የመረጃ ክፍተት፣ የታሪክ ግድፈትና የተዛባ ድምዳሜ እንደያዙ በግልጽ ይታያል። የጽሑፍ ሕየሳ ሳይንስ ዓላማ ዋናውንና ጥንታዊውን ጽሑፍ መፈለግ እንጂ፣ ለተወሰኑ ጽሑፎች ወገንተኝነትን ማሳየት አይደለም። በዚህ ረገድ የማርቆስ ወንጌል መጨረሻ በቁጥር 8 ላይ ያበቃል የሚለው ድምዳሜ፣ ከቤተክርስቲያን አጠቃላይ ትውፊትና ከአብዛኛው የእጅ ጽሑፎች ምስክርነት ጋር የሚስማማ አይደለም፤ ምክንያቱም 99.8% የሚሆኑት የአዲስ ኪዳን የእጅ ጽሑፎች ውስጥ ይገኛልና (Pickering, 2012, p. 211)። ጀምስ ስናፕ በመጽሐፉ ውስጥ ስቲረር የተሰኘ ምሁር በመጥቀስ እንዳብራራው ከሆነ እነዚህ ጥቅሶች መጀመሪያ ላይ በማርቆስ የተዘጋጁ “የቤተ ክርስቲያን የእምነት አቋም ትምህርት ማጠቃለያ” (Catechetical Summary) ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚያሳዩ በርካታ ማስረጃዎች ይገኛሉ (Snapp, 2014, p. 341)።

በዚህ አጭር ጥናት በክፍሉ ላይ የቀረቡት አሉታዊ መከራከሪያዎች አንድ በአንድ እየተነሱ ምላሽ የሚሰጥባቸው ሲሆን፣ የማርቆስ ወንጌል 16፡9-20 የቅዱሳት መጻሕፍት አካል መሆኑ በምንባብ ሕየሳና በታሪካዊ ማስረጃዎች ይረጋገጣል። ጥናቱ በተለይ በሁለቱ ታዋቂ ኮዲሶች (ቫቲካነስ እና ሲናይቲከስ) ላይ ያለውን የተጋነነ እምነት በመመርመር፣ ከእነርሱ ቀድመው የነበሩትንና በሁለተኛው ክፍለ ዘመን የታዩትን ምስክርነቶች አስፈላጊነት ያጎላል። በተጨማሪም የቋንቋ አጠቃቀምን በተመለከተ የሚቀርቡት መከራከሪያዎች በማርቆስ ወንጌል አጠቃላይ ባሕርይ ውስጥ ሲታዩ ያላቸውን ደካማነት ይገልጣል።

የጽሑፍ ማስረጃዎች ፍተሻ፡ ከታላላቅ ኮዲሶች ባሻገር

የማርቆስን ወንጌል መዝጊያ ውድቅ ለማድረግ የሚነሳው ቀዳሚ ምክንያት፣ ክፍሉ በሁለቱ ጥንታዊ የግሪክ መጽሐፍ ቅዱሶች ማለትም በኮዴክስ ቫቲካነስ እና በኮዴክስ ሲናይቲከስ ውስጥ አለመገኘቱ ነው። እነዚህ ሁለት ቅጂዎች በአራተኛው ክፍለ ዘመን (በ300ዎቹ ዓ.ም.) የተጻፉ በመሆናቸው፣ በዘመናዊ የምንባብ ሐያስያን ዘንድ እንደ “ንጹሕ ምንጭ” ተቆጥረው ይወሰዳሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ ጽሑፎች ጥንታዊነት ቢኖራቸውም ከሌሎች ጽሑፎች ተነጥለው ብቻቸውን እውነትን የመወከል አቅም የላቸውም። ወደ 1,650  ከሚሆኑት የግሪክ የማርቆስ ወንጌል ኮፒዎች መካከል ክፍሉን ይዘው የማይገኙት ሦስቱ ብቻ ናቸው (Ibid., 2014, p. 13)።

. የኮዴክስ ቫቲካነስ (B) “የመታሰቢያ ባዶ ቦታ” (Memorial Space)

በኮዴክስ ቫቲካነስ (ከ325 ዓ.ም. ገደማ) ውስጥ የማርቆስ ወንጌል በቁጥር 8 ላይ ቢያበቃም፣ ገልባጩ ከዚያ በኋላ አንድ ሙሉ ባዶ አምድ ትቷል። ይህ ባዶ ቦታ በሌሎች የጥራዙ ክፍሎች ከሚገኙት ባዶ ቦታዎች የተለየና ጸሐፊው ከወንጌሉ የተረፈ ክፍል መኖሩን እንደሚያውቅ የሚያስረዳ ነው (Burgon, 1871, p. 87)። ይህ ክፍተት በጥራዙ ውስጥ ከምናገኛቸው በፎርማት ለውጥ ወይም በጸሐፊ መለወጥ ምክንያት ከተተው ክፍት ቦታዎች የተለየ ነው። የማርቆስን ወንጌል በጻፈው ገልባጭ  የተወው ባዶ ቦታ በትክክል የማርቆስ 16፡9-20 ጥቅሶችን በሌሎች የጥራዙ ክፍሎች በሚታየው መልኩ በመጠነኛ የጽሑፍ መጥበብ (Compression) ለመያዝ የሚያስችል ነው (Snapp., p. 14-15)። ይህ የሚያሳየው ገልባጩ ጥቅሶቹን የሚያውቃቸው ቢሆንም በሚገለብጥበት የመጀመሪያ የእጅ ጽሑፍ (Exemplar) ውስጥ ስላልነበሩ ለወደፊቱ ባለቤት ቦታውን ክፍት ማድረጉን ነው። ይህ “የመታሰቢያ ባዶ ቦታ” (Memorial Space) ተብሎ የሚጠራው ክፍተት የቫቲካነስ ጥራዝ ራሱ ስለ ረጅሙ መዝጊያ መኖር ድምፅ አልባ ምስክርነት እንዲሰጥ ያደርገዋል።

. የኮዴክስ ሲናይቲከስ (א) “የማስተካከያ ገጾች” (Cancel-sheet)

በኮዴክስ ሲናይቲከስ (350 ዓ.ም. ገደማ) ውስጥ በማርቆስ መጨረሻ ላይ ያሉት አራት ገጾች (ከማርቆስ 14፡54 እስከ ሉቃስ 1፡56) በዋናው ገልባጭ ያልተጻፉ መሆናቸው ታውቋል (Peter, 2008, p. 4)። እነዚህ ገጾች በዲዮርቶቴስ (Diorthotes – አራሚ/አርታዒ) የተጻፉ “ምትክ ገጾች” ናቸው። ይህ የሆነውም ዋናው ጸሐፊ በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 1 ላይ ሰፊ የጽሑፍ ክፍል በመዝለሉ (ወይም በመድገሙ) ምክንያት ገጾቹን አስተካክሎ እንደገና መጻፍ ስላስፈለገ ነው። አራሚው እነዚህን አራት ገጾች መልሶ ሲጽፍ፣ በማርቆስ ወንጌል መጨረሻና በሉቃስ ወንጌል መጀመሪያ መካከል ባዶ ዓምድ እንዳይኖር ጥረት አድርጓል። ይህንን ባዶ ቦታ ለመሙላት ሲልም የማርቆስን ወንጌል የመጨረሻ ጥቅሶች ፊደላት ባልተለመደ ሁኔታ በማራራቅና በማስፋት እስከ አሥረኛው ዓምድ ድረስ እንዲዘልቁ አድርጓል። አራሚው የማርቆስን ወንጌል በ9ኛው ዓምድ ላይ መጨረስ ይችል ነበር፤ ነገር ግን ይህ ቢሆን ኖሮ በ9ኛው እና በ10ኛው ዓምድ መካከል ባዶ ቦታ ይተርፍ ነበር። ባዶ ቦታ ቢተው ኖሮ፣ አንባቢዎች “እዚህ ጋር የተተወ ጽሑፍ (ማርቆስ 16፡9-20) አለ” ብለው እንዳያስቡ በመስጋት በሚመስል ሁኔታ ያንን ባዶ ቦታ ለመሙላት ሲል ፊደላቱን አስፍቶ እስከ 10ኛው ዓምድ ድረስ እንዲዘልቁ አድርጓል። በተጨማሪም በማርቆስ 16፡8 ማብቂያ ላይ አራሚው በጣም የተራቀቀና ትልቅ የሆነ የማስጌጫ ንድፍ (Arabesque) ስሏል። ይህ ዓይነቱ ልዩ ጌጥ በሌሎች የመጽሐፉ ክፍሎች ላይ አይታይም። ይህም የሚያሳየው አራሚው ወንጌሉ እዚሁ ጋር (በቁጥር 8 ላይ) እንዲያበቃ ከፍተኛ ፍላጎት እንደነበረው ነው። አንድ ሰው ክፍተቱን ተጠቅሞ ተጨማሪ ጥቅሶችን እንዳይጨምር እንደ “አጥር” ወይም እንደ መዝጊያ ተጠቅሞበታል። ከዚህ በመነሳት ልንደመድም የምንችለው የኮዴክስ ሲናይቲከስ አራሚ የማርቆስ ወንጌል ሌሎች ተጨማሪ ጥቅሶች (ቁጥር 9-20) እንዳሉት ያውቅ እንደነበር፣ ነገር ግን እነዚያን ጥቅሶች ሆን ብሎ እንዳልተቀበላቸውና ወንጌሉ በቁጥር 8 ላይ እንዲያበቃ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ማድረጉን ነው (Snapp, pp. 17-21)።

የግሪክ ሚኑስኩሎች (አናሳ ፊደላት) እና ሌክሽነሪዎች (የአምልኮ ንባቦች) ምስክርነት

በማርቆስ 16፡9-20 ላይ ጥቃት ሲሰነዘር፣ ክፍሉን የሚደግፉት እጅግ ብዙ ቁጥር ያላቸው (99%) ሌሎች የግሪክ የእጅ ጽሑፎች በቸልታ ይታለፋሉ።

የእጅ ጽሑፍ ምድብ ብዛት / ሁኔታ የማርቆስ 169-20 ሁኔታ
ቀዳሚ ኮዲሶች አራት ዋና ዋና ጽሑፎች በሙሉ ይዘውታል
የግሪክ ሚኑስኩሎች ከ2,800 በላይ 99% የሚሆኑት ይዘውታል
የግሪክ ሌክሽነሪዎች ከ2,000 በላይ ለትንሳኤ በዓል ንባብነት ይጠቀሙታል (Burgon, p. 121)
ኮዴክስ ቫቲካነስ እና ሲናይቲከስ ሁለት ጽሑፎች አያካትቱም (ነገር ግን ቫቲካነስ ባዶ ቦታ ሲኖረው ሲናይቲከስም ጽሑፉን በማረም በጻፈው ሰው ውሳኔ ምክንያት ባይሆን ኖሮ ተመሳሳይ ባዶ ቦታ ይኖረው ነበር።)

እንደ ኮዴክስ አሌክሳንድሪነስ (Codex Alexandrinus) (400–440 ዓ.ም)፣ ኮዴክስ ኤፍራይም ሬስክሪፕተስ (Codex Ephraemi Rescriptus) (425–450 ዓ.ም)፣ ኮዴክስ ቤዛይ (Codex Bezae) (400 ዓ.ም) እና ኮዴክስ ዋሽንግተንያነስ (Codex Washingtonianus) (375-450 ዓ.ም) ያሉ ታላላቅ ቅጂዎች ረጅሙን መዝጊያ ይዘው መገኘታቸው የጽሑፉ ስርጭት በቤተክርስቲያን ውስጥ ምን ያህል ሰፊ እንደነበር ያረጋግጣል። https://www.tbsbibles.org/page/Mark16

የጥንት አባቶች ምስክርነት (Patristic Evidence)

የጥንት አባቶች ምስክርነት ከእጅ ጽሑፎቹ በፊት የነበረውን ሁኔታ ያሳያል (Burgon, p. 25)። ማርቆስ 16፡9-20 በቤተክርስቲያን አባቶች ዘንድ እጅግ ቀደም ብሎ የታወቀና ተቀባይነት የነበረው ክፍል ነው።

የሁለተኛው ክፍለ ዘመን አባቶች

ከአራተኛው ክፍለ ዘመን ኮዲሶች በፊት የነበሩት ምስክሮች ለጽሑፉ ትክክለኛነት የሚሰጡት ክብደት እጅግ የላቀ ነው።

  • ዮስጦንዮስ ሰማዕት (Justin Martyr – 150 ..)፦ በጽሑፎቹ ውስጥ በማርቆስ 16፡20 ላይ የሚገኘውን “ደቀ መዛሙርቱ ወጥተው በሁሉ ሰበኩ” የሚለውን ሐሳብ ጠቅሷል (Justin Martyr, First Apology, Ch. 45)።
  • ታቲያን (Tatian – 170 ..)፦ “ዲያተሳሮን” (Diatessaron) በተሰኘው አራቱን ወንጌላት አሰባጥሮ በጻፈው መጽሐፍ ውስጥ የማርቆስን ረጅሙን መዝጊያ ሙሉ በሙሉ አካቷል (Hogg, 1896, p. 258)።
  • የሊዮኑ ቅዱስ ኢሬኔዎስ (St. Irenaeus of Lyons – 180 ..)፦ “Against Heresies” በተሰኘው ታዋቂ መጽሐፉ ላይ ማርቆስ 16፡19ን በቀጥታ በመጥቀስ “ማርቆስ በወንጌሉ መጨረሻ ላይ እንዲህ ይላል…” በማለት ጽፏል (Irenaeus, Against Heresies, 3.10.6)።
  • ኤፒስቱላ አፖስቶሎረም (Epistula Apostolorum)፦ በ150 ዓ.ም. አካባቢ የተጻፈው ይህ ጽሑፍ፣ የማርቆስ 16፡9-20ን የታሪክ ፍሰት (ከመቃብር መመለስ፣ ለደቀ መዛሙርቱ መናገር፣ አለማመናቸው) በዝርዝር ይከተላል (Snapp, 2014, p. 29)።

በስህተት የተተረጎሙ የአበው ንግግሮች

የእስክንድርያው ቀለሜንጦስ (Clement of Alexandria) እና ኦሪጎን (Origen) እነዚህን ጥቅሶች እንደማያውቁ ተደርጎ የሚቀርበው መረጃ መሠረት የሌለው ነው። ቀለሜንጦስ በማርቆስ ወንጌል ውስጥ ምዕራፍ 10ን ብቻ በብዛት የተጠቀመ ሲሆን፣ የመጀመሪያዎቹን ሰባት ምዕራፎችም በጽሑፎቹ ውስጥ አልጠቀሰም (Burgon, p. 33)። የአንድን ጥቅስ አለመጠቀስ (Argument from Silence) ጥቅሱ የለም ለማለት እንደ ማስረጃ መጠቀም በታሪክ ምርመራ ረገድ ተቀባይነት የሌለው አካሄድ ነው።

አውሳብዮስና ጀሮም፦ ምንም እንኳን ጥቅሶቹ “በአንዳንድ ትክክለኛ ቅጂዎች ውስጥ አይገኙም” ቢሉም፣ ሁለቱም ጥቅሶቹን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አካትተዋል። አውሳብዮስ (Eusebius) ይህንን ያለው ለማሪነም በሰጠው ምላሽ (Ad Marinum) ላይ ሲሆን፣ ዋናው ዓላማው በወንጌላት መካከል ያለውን የትንሣኤ ታሪክ ልዩነት “ለማስታረቅ” (Harmonization) ሲል ነበር (Eusebius, Ad Marinum, Question 1)። አውሳብዮስ ራሱ የመረጠውና የመከረው ሁለተኛውን አማራጭ ማለትም ጥቅሶቹን ተቀብሎ በአተነባበብ (Punctuation) ልዩነቱን ማስታረቅን ነው (Burgon, pp. 44-50)። ቅዱስ ጀሮም (Jerome) እነዚህን ጥቅሶች በላቲን ቩልጌት (Latin Vulgate) ውስጥ አካቷል። ጀሮም የአውሳብዮስን ቃል የጠቀሰው ጽሑፎቹን ሲተረጉም እንጂ፣ በራሱ ስም የሰጠው ምስክርነት አይደለም (Jerome, Ad Hedibiam, Question 3)። ጥቅሶቹም እውነተኛ መሆናቸውን ያምን እንደ ነበር አመላክቷል (Burgon, pp. 56-57)።

የቋንቋ የቃላት አጠቃቀም ሙግት (Linguistic Argument)

አንዳንድ ወገኖች በዚህ ክፍል ውስጥ ብቻ የሚገኙ በሌሎች የማርቆስ ወንጌል ክፍሎች የማናገኛቸው በርካታ ቃላት በመኖራቸው ምክንያት ክፍሉ የወንጌሉ አካል ሊሆን እንደማይችል ይናገራሉ። ነገር ግን ይህ የሙግት አካሄድ ወጥነት ይጎድለዋል። አንድ ጸሐፊ በአንድ አጭር ክፍል ውስጥ አዳዲስ ቃላትን መጠቀሙ የጽሑፉን ትክክለኛነት ጥያቄ ላይ አይጥለውም። ለምሳሌ በማርቆስ 15፡40-16፡4 ባሉት 12 ቁጥሮች ውስጥ በማርቆስ ወንጌል በሌላ ስፍራ የማይገኙ 20 አዳዲስ ቃላት ይገኛሉ (Lunn, 2014, p. 114)።

የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የቁጥሮች ብዛት አዳዲስ ቃላት (Hapax Legomena)
ማርቆስ 15፡40 – 16፡4 12 ቁጥሮች 20 ቃላት
ማርቆስ 16፡9-20 12 ቁጥሮች 14 ቃላት

ይህ ንጽጽር እንደሚያሳየው፣ የማርቆስ 16፡9-20 የቃላት አጠቃቀም ከወንጌሉ አጠቃላይ የቋንቋ ባሕርይ ጋር የሚስማማ እንጂ እንግዳ አለመሆኑን ነው (Robinson, 2001, p. 32)። በዚህ አጋጣሚ ከሪም አል-ሃኒፊ የተሰኘ ምሑር The end of an argument on the ending of Mark በሚል ርዕስ በዚህ ክፍል የቃል አጠቃቀም ላይ የሠራውን ጥናት መጥቀሱ አስፈላጊ ነው። አል-ሃኒፊ በማርቆስ 1፡1-16፡8 ውስጥ ማርቆስ አንድ ጊዜ ብቻ የሚጠቀምባቸው 696 ቃላት እንዳሉ ለይቷል። በቃላት አጠቃቀም ረገድ ይህ ክፍል ከተቀረው የማርቆስ ወንጌል ክፍል ምንም የተለየ ባሕርይ የለውም። መመዘኛው ይህ ከሆነ በርካታ የወንጌሉ ክፍሎች ተመሳሳይ ባሕርይ ስለሚያሳዩ እነርሱንም በማርቆስ እንዳልተጻፉ በመደምደም ልንጥላቸው ነው።

ሌሎች መዝጊያዎችና ትርጉሞች

  • አጭሩ መዝጊያ (Shorter Ending)፦ ይህ መዝጊያ በግብፅ (እስክንድርያ) የተጻፈ ሊሆን ይችላል፣ በጣት የሚቆጠሩ የግሪክ የእጅ ጽሑፎችና የግብፅ (ሳሂዲክና ቦሃይሪክ) ትርጉሞች ይዘውታል (Snapp, 2014, p. 276)። በነባር የአማርኛ ትርጉም ማርቆስ 16፡8 ላይ የተካተተ ሲሆን እንዲህ ይነበባል፦ “እነርሱም ያዘዛቸውን ሁሉ ለጴጥሮስና ከእርሱ ጋር ላሉት በአጭሩ ተናገሩ። ከዚህም በኋላ ኢየሱስ ራሱ ለዘላለም ድኅነት የሆነውን የማይለወጠውን ቅዱስ ወንጌል ከፀሐይ መውጫ እስከ መጥለቂያው ድረስ በእጃቸው ላከው።” ይህ አጭሩ መዝጊያ የተሰኘው ሲሆን በዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ መሠረት የመልእክት ችግር ባይኖርበትም በቂ የጽሑፍ ድጋፍ ስለሌለው ከንባብ ውጪ ማድረጉ ተገቢ ነው። የአዲሱ መደበኛ ትርጉም አዘጋጆች ይህንን ክፍል አለማካተታቸው ትክክለኛ ውሳኔ ነው።
  • ፍሪር ሎጊዮን (Freer Logion)፦ በኮዴክስ ዋሽንግተንያነስ (W) ውስጥ በቁጥር 14 እና 15 መካከል የሚገኝ ተጨማሪ ጽሑፍ አለ። ይህ በአንድ ጥራዝ ውስጥ ብቻ የሚገኝ በመሆኑ በቂ የእጅ ጽሑፍ ድጋፍ የለውም፤ ስለዚህ ትክክለኛነቱን የሚቀበል ምሑር የለም።
  • የላቲን እና የሲሪያክ ትርጉሞች፦ 99.9 በመቶ የሚሆኑት የላቲን ቅጂዎች ረጅሙን መዝጊያ ይዘው ይገኛሉ። የሲሪያክ (Syriac) ትርጉሞችን ስንመለከትም 99 በመቶ ጥቅሶቹን ይዘዋል። https://bcs.edu/wp-content/uploads/2025/01/Snapp-ECJ_final.pdf
  • የግዕዝ መጽሐፍ ቅዱስ የኢትዮጵያ ምስክርነት፦ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቀኖና ውስጥ፣ የማርቆስ ወንጌል 16፡9-20 ከመጀመሪያው ጀምሮ የነበረና ያለ ክፍል ነው። ብሩስ መዝገር (Bruce Metzger) ቀደም ሲል በጻፈው መጽሐፉ ውስጥ “የኢትዮጵያ (ግዕዝ) ትርጉም ጥቅሶቹን አይይዝም” ማለቱ ስህተት መሆኑን በማመን በኋላ ላይ በርካታ የኢትዮጵያ የእጅ ጽሑፎችን መርምሮ ጥቅሶቹን የያዙ መሆናቸውን አረጋግጧል (Snapp, 2014, p. 235-37)። ጥንታዊነቱ የተረጋገጠው የአባ ገሪማ ወንጌል (430-540 ዓ.ም) ይህንን ክፍል ይዟል (Ibid., 235)።

የትምህርተ መለኮት (ዶክትሪን) ጥያቄዎች

በማርቆስ 16፡9-20 ውስጥ የሚገኙት “አስቸጋሪ ትምህርቶች” (እባብ መያዝ፣ መርዝ መጠጣት) ጥቅሶቹን ውድቅ ለማድረግ እንደ ምክንያት ይቀርባሉ። ይሁን እንጂ አንድ ጥቅስ ለኛ ትርጓሜ ስላልተመቸን ብቻ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ልናወጣው አንችልም። እነዚህ ትምህርቶች ከቀሪው መጽሐፍ ቅዱስ ጋር አይጋጩም፤ ለምሳሌ ሐዋርያው ጳውሎስ በማልታ ደሴት ላይ ያጋጠመው ተአምር (ሐዋርያት ሥራ 28) ለዚህ ጥቅስ ግልጽ ማሳያ ነው። በቤተክርስቲያን ታሪክም ተመሳሳይ ክስተቶች ታይተዋል። ለምሳሌ ያህል ከሐዋርያው ዮሐንስ ጋር የሚተዋወቀው ሐዋርያዊ አባት ፓፕያስ (60-130 ዓ.ም) ከወንጌላዊው ፊሊጶስ ሴት ልጅ በመስማት ባስተላለፈው ትውፊት መሠረት ለሐዋርያነት ታጭቶ የነበረው ዮስጦስ የተሰኘው በርሲያስ (ሐዋ. 1፡23) አደገኛ መርዝ እንዲጠጣ በተደረገ ጊዜ መርዙ ሳይጎዳው በተዓምር መትረፉን ዘግቧል። ፓፕያስ የማርቆስን ወንጌል ጠቅሶ ባይናገርም ስለዚህ ተዓምራዊ ክስትተ የዘገበው ተፈጻሚ የሆነው የክርስቶስ ተስፋ በማርቆስ ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ ለክፍሉ እውነተኛነት ተጨማሪ ምስክርነት ነው (Burgon, p. 39)። ይህንን ክፍል ያለ አግባብ የተጠቀሙ ወገኖች በዘመናት ሁሉ መኖራቸው ክፍሉ የወንጌሉ አካል ላለመሆኑ ማስረጃ ሊሆን አይችልም። እንዲህ ያለ መመዘኛ ትክክል ቢሆን ኖሮ በሐሰተኛ መምህራንና ብስለት በጎደላቸው አማኞች ያለ አግባብ ጥቅም ላይ የዋሉ የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍሎችን ሁሉ በጣልን ነበር።

የምንባብ ሕየሳ የቤተክርስቲያን ቀኖና

አዲስ ኪዳን ከየትኛውም ጥንታዊ ጽሑፍ በላቀ ሁኔታ በእጅ ጽሑፎች የተደገፈ መሆኑ ከታመነ፣ ታዲያ 99 በመቶ የሚሆኑት የእጅ ጽሑፎች የሚደግፉት የማርቆስ ረጅሙ መዝጊያ ለምን ውድቅ ይደረጋል? የማርቆስ ወንጌል በቁጥር 8 ላይ “ፈርተው ነበርና ለማንም ምንም አልተናገሩም” በሚል ቃል ቢጠናቀቅ ኖሮ፣ ወንጌሉ ፍጹም ያልተሟላና ተስፋ አስቆራጭ በሆነ ሁኔታ ተዘጋ ማለት ይሆን ነበር። ቁጥር 9-20 ይህንን ክፍተት የሚሞሉና ማርቆስ የጀመረውን ታሪክ ወደ ትክክለኛ ማጠቃለያ የሚያመጡ ናቸው። ይህ ክፍል ምናልባት በማርቆስ እጅ እንዳልተጻፈ መናገር የተወሰነ ያህል ሊያስኬድ ይችል ይሆናል፤ ነገር ግን ከመጀመሪያው ጀምሮ በቤተክርስቲያን የሚታወቅ ክፍል እንደ መሆኑ ሐዋርያዊ ሥልጣን እንደ ሌለው ባዕድ ቅጥያ ቆጥሮ መጣል ፈጽሞ የሚያስኬድ አይደለም። በእጃችን ከሚገኙ እጅግ የበዙ ማስረጃዎች አኳያ እንዲያ ያለ ድምዳሜ የድርድር ሜዳ ሊሆን የማይችል ከክርክሩ ክበብ ውጪ ሊደረግ የሚገባው የተሳሳተ ሐሳብ ነው።

ክፍሉ የዋናው ጽሑፍ አካል እንዳልነበረ የሚያምኑ ሊቃውንት ሙሉ በሙሉ ይጥሉታልን?

የዚህ ጥያቄ ምላሹ አሉታዊ ነው። ለምሳሌ እ.ኤ.አ. በ1844 የጻፈው አልፎርድ (Alford)፣ የክፍሉን ትክክለኛነት (originality) በግልጽ ውድቅ ቢያደርግም፣ እንዲህ ሲል ግን አምኗል፦ “ስለዚህ የእኔ መደምደሚያ፤ ክፍሉ በጥንት ዘመን ወንጌሉን ለማጠናቀቅ የተቀመጠ እውነተኛ ቅንጣቢ ታሪክ (authentic fragment) መሆኑ ነው፤ በማን እንደተጻፈ በእርግጠኝነት ባይታወቅም ነገር ግን በጣም ክብደት ባለው ድጋፍ ወደ እኛ የመጣ፣ እንዲሁም እንድንቀበለውና እንድናከብረው ከፍተኛ መብት ያለው ነው” (1:438)። ሰር ፍሬደሪክ ኬንዮን (Sir Frederic Kenyon) ጥቅሶቹ አሪስቲዮን የተባለ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር እንደ ጻፈው ከተናገሩ በኋላ እንዲህ ይላሉ፦ “ምንም እንኳ የማርቆስ ወንጌል የመጀመሪያ አካል ባይሆንም፣ ክፍሉን እንደ እውነተኛና ትክክለኛ ትረካ ልንቀበለው እንችላለን” (Kenyon, 1951, p. 174)። በቅርብ ጊዜ ደግሞ እንደ ከርት እና ባርባራ አላንድ (Kurt and Barbara Aland) ያሉ ዝነኛ የምንባብ ሕየሳ ምሁራን፣ አወዛጋቢ የሆኑትን አሥራ ሁለቱን ጥቅሶች የመጀመሪያነት ውድቅ ቢያደርጉም፣ ረጅሙ መደምደሚያ “እንደ ቀኖናዊ (canonical) ይታወቅ እንደነበር” እንዲሁም “ከሁለተኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ጀምሮ የነበረ ሊሆን ይችላል” በማለት አምነዋል (Aland and Aland, 1987, p. 69, 227)። በፕሪንስተን ቲኦሎጂካል ሴሚናሪ የአዲስ ኪዳን ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ ፕሮፌሰር የነበሩት የአዲስ ኪዳን ንባብ ሕየሳ ምሁር ብሩስ መዝገር፣ “የረጅሙ መደምደሚያ ጥንታዊነት ግልጽ ነው፤ በወንጌሉ የጽሑፍ ወግ ውስጥም አስፈላጊ ነው” በማለት ገልጸዋል (Metzger, 1994, p. 105)። መዝገር ይህ ክፍል የዋናው የማርቆስ ወንጌል ክፍል እንዳልነበረ በመግለጽ የሚታወቁ ሲሆኑ ብዙ ወገኖች ለዚህ ክፍል አጠራጣሪነት በዋናነት የሚጠቅሷቸው ምሑር ናቸው። በአዲስ ኪዳን ጥናት እጅግ የሚታወቁት ኤፍ ኤፍ ብሩስ ደግሞ ይህ ክፍል በጥንቷ ቤተክርስቲያን እንደሚታወቅና ሐዋርያዊ ሥልጣን እንዳለው የሚያሳዩ በርካታ ማስረጃዎችን ከጠቀሱ በኋላ በማጠቃለያቸው “ምንም እንኳን አሁን ከተያያዙበት የወንጌል ክፍል እንደ አንድ ዋና አካል ልንቆጥራቸው ባንችልም፣ ማንኛውም ክርስቲያን እንደ ቅዱስ መጽሐፍ ሊያነባቸው ምንም ዓይነት ማመንታት ሊኖረው አይገባም” ብለዋል (F.F. Bruce, 1945, p. 181)። እነዚህን ምንጮች የጠቀስነው ክፍሉን የሚጠራጠሩ ምሑራን እንኳ እንደ ቀላል ነገር ታይቶ ሊጣል የሚገባው አድርገው እንደማያስቡ ለማስገንዘብ ያህል ነው።

ማጠቃለያ

ከማጠቃለላችን በፊት በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የቀረቡትን መረጃዎች ጥቂት እውነታዎችን በማከል መለስ ብለን እንመልከት። ይህ ክፍል የመጽሐፍ ቅዱስ አካል እንዳልሆነ የሚያስቡ ወገኖች ተከታዮቹን እውነታዎች ከግንዛቤ ውስጥ ሊያስገቡ ይገባል፦ ከሁለተኛው እስከ አራተኛው ክፍለ ዘመን ባለው ጊዜ ውስጥ ይህንን ክፍል የያዙ ወይም የሚጠቅሱ እንደ ኤፒስቱላ አፖስቶሎረም (120–140 ዓ.ም.)፣ ሰማዕቱ ዮስጢኖስ (160 ዓ.ም.)፣ የታቲያን ዲያቴሳሮን (160–175 ዓ.ም.)፣ ሄሬኔዎስ (180 ዓ.ም.)፣ ሂጶሊጦስ (235 ዓ.ም)፣ የቲባሪሱ ቪንሰንቲየስ (256 ዓ.ም)፣ ዴ ሪባፕቲስማቴ (258 ዓ.ም)፣ እንዲሁም በ305 ዓ.ም አማንያንን ለመተቸት ማርቆስ 16:18ን የተጠቀመው አረማዊው ጸሐፊ ሂሮክለስ ይገኙበታል። በተጨማሪም ሶርያዊው አፍራሃት (337 ዓ.ም)፣ የጲላጦስ ሥራዎች የተሰኘ የአፖክሪፋ መጽሐፍ (Acts of Pilate – 4ኛው ክፍለ ዘመን)፣ ላቲናዊው ተርጓሚ ፎርቱናቲያኑስ (350 ዓ.ም)፣ ኤጲፋንዮስ (375 ዓ.ም)፣ አምብሮስ (385 ዓ.ም)፣ ሥርዓተ ሐዋርያት (Apostolic Constitutions – 380 ዓ.ም)፣ ፓላዲየስ (በ300ዎቹ መገባደጃ) እና ቅዱስ አውግስጢኖስ (430 ዓ.ም) ይጠቀሳሉ። አውግስጢኖስ የጠቀሳቸው የግሪክ ቅጂዎችና ከ3ኛው እስከ 5ኛው ክፍለ ዘመን የነበሩ የጥንት ላቲን ምዕራፍ ማጠቃለያዎችም የዚሁ ድጋፍ አካል ናቸው። በአምስተኛው ክፍለ ዘመን፣ የማርቆስ ወንጌል 16:9-20 ትክክለኛነት በነዚህ አካላት ተረጋግጧል፦ ማካሪየስ ማግነስ (410 ዓ.ም)፣ ፔላጊየስ፣ ፊሎስቶርጊየስ (425 ዓ.ም)፣ ማርየስ መርኬተር (430 ዓ.ም)፣ ማርከስ ኤሬሚታ (435 ዓ.ም)፣ አርመናዊው ተርጓሚ የጎልቡ እዝኒክ (440 ዓ.ም)፣ የኤክሳይቴኑ ፕሮስፐር (450 ዓ.ም)፣ የእስክንድርያው ቄርሎስ በጠቀሰው መሠረት ንስጥሮስ (440 ዓ.ም)፣ ጴጥሮስ ክሪሶሎገስ (440 ዓ.ም)፣ ታላቁ ሊዮ እና ቅዱስ ፓትሪክ (በ450 ዓ.ም ገደማ)። ከዚህም ባለፈ፣ ጥቅሶቹ በነዚህ ታዋቂ ትርጉሞች ውስጥ ይገኛሉ፦

  • የሶርያው ፔሺታ (Peshitta)
  • በኩሬቶኒያ ሶርያዊ ቅጂ (ምንም እንኳ ያልተሟላ ቢሆንም ቁጥር 16:17-20ን ይዟል)
  • በቩልጌት (Vulgate)፤ ቅዱስ ጄሮም ይህን ትርጉም በ383 ዓ.ም ሲያዘጋጅ ጥንታዊ የግሪክ ቅጂዎችን ማመሳከሩን ገልጿል።
  • በ4ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ በተዘጋጀው የጎቲክ ትርጉም (Gothic version) ውስጥም ይገኛል። ይህ ትርጉም በ6ኛው ክፍለ ዘመን በነበረው ኮዴክስ አርጀንቲየስ (Codex Argenteus) ላይ ተጠብቆ የቆየ ሲሆን፣ ፍራንዝ ሃፍነር እ.ኤ.አ በ1970 በጀርመን ስፓየር ከተማ የመጨረሻዋን ገጽ በማግኘቱ ምክንያት ከቁጥር 12-20 ያሉት ክፍሎች መካተታቸው ተረጋግጧል።
  • ብዙ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ትርጉሞችም ይህንን ክፍል ይዘው ይገኛሉ።

ለተጨማሪ መረጃ ይህንን ርዕሰ ጉዳይ በጥልቀት ያጠኑትን የጀምስ ስናፕን ጽሑፍ ያንብቡ፦ https://textandcanon.org/a-case-for-the-longer-ending-of-mark/

ስለ ማርቆስ 16:9-20 የሚገልጹና የአባቶችን ማስረጃዎች ሳይጠቅሱ የብራና ማስረጃዎችን በደፈናው የሚያስቀምጡ የመጽሐፍ ቅዱስ የግርጌ ማስታወሻዎችን ስናነብ የሚከተሉትን ተጨማሪ ነጥቦች ልብ ማለት ያስፈልጋል፦ “አንዳንድ ቀደምት የብራና ቅጂዎች ከቁጥር 9-20 ያሉትን አይጨምሩም” ከሚለው ቀላል ዓረፍተ ነገር በስተጀርባ ያለው እውነታ ሰፊ ነው። በጀምስ ስናፕ አገላለጽ መሠረት ቀደምት የግሪክ የብራና ቅጂዎችን (MSS) በተመለከተ፣ “አንዳንዶች” የሚለው ቃል የሚወክለው ሁለቱን ብቻ ነው። “ቀደምት” የሚለው ቃል ደግሞ፣ የቤተክርስቲያን አባቶች የነዚህን ቁጥሮች ይዘት በግልጽ መጠቀም ከጀመሩበት ጊዜ ከ100 ዓመታት በላይ ዘግይቶ የመጣን ዘመን ያመለክታል። “አይጨምሩም” ሲባልም፣ ቁጥሮቹን ባያካትቱም እንኳ ገልባጮቹ ስለ ቁጥር 9-20 መኖር ግንዛቤ እንደነበራቸው በሚያሳይ መልኩ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል (Snapp, 2014, p. 24)። በታሪክ አጋጣሚ በተፈጠረው “የጽሑፍ መቆረጥ” ሁለቱ ታላላቅ ኮዲሶች ውስጥ ባናገኘውም የአብዛኛው የቤተክርስቲያን ክፍል ግን ዋናውንና ሙሉውን ጽሑፍ ከጥንት ጀምሮ ጠብቆ አቆይቷል። የማርቆስ ረጅሙ መዝጊያ በቤተክርስቲያን ውስጥ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የኖረ፣ በጥንታውያን አበው የተመሰከረለትና በአብዛኛው የእጅ ጽሑፎች የተጠበቀ የእግዚአብሔር ቃል ነው። ታዋቂው ምሁር ኤፍ ኤፍ ብሩስ እንዳለው፣ እነዚህ ጥቅሶች በማንኛውም ክርስቲያን ዘንድ እንደ ቅዱስ ቃሉ ተቆጥረው ሊነበቡ ይገባል (Bruce, 1988, p. 258)። የማርቆስ ወንጌል መጨረሻ በድልና በተልዕኮ የተሞላ እንጂ በፍርሃትና በዝምታ የተዘጋ አይደለም።


ዋቢ ምንጮች 

Burgon, John William. The Last Twelve Verses of the Gospel according to St. Mark Vindicated against Recent Critical Objectors and Established. London: James Parker and Co., 1871.

F.F. Bruce, “The End of the Second Gospel,” The Evangelical Quarterly 17 (1945): 169-81.

Hanifi, Karim, “The end of an argument on the ending of Mark”, (2019).

Hogg, Hope W., trans. Tatian’s Diatessaron. Edinburgh: T&T Clark, 1896.

Irenaeus of Lyons. Against Heresies. In The Ante-Nicene Fathers, vol. 1. Edited by Alexander Roberts and James Donaldson. Buffalo, NY: Christian Literature Publishing Co., 1885.

Jerome. Ad Hedibiam (Epistle 120). In Nicene and Post-Nicene Fathers, Second Series, vol. 6. Edited by Philip Schaff and Henry Wace. Buffalo, NY: Christian Literature Publishing Co., 1893.

Justin Martyr. First Apology. In The Ante-Nicene Fathers, vol. 1. Edited by Alexander Roberts and James Donaldson. Buffalo, NY: Christian Literature Publishing Co., 1885.

Lunn, Nicholas P. The Original Ending of Mark: A New Case for the Authenticity of Mark 16:9–20. Eugene, OR: Pickwick Publications, 2014.

Metzger, Bruce M. A Textual Commentary on the Greek New Testament. 2nd ed. Stuttgart: Deutsche Bibelgesellschaft, 1994.

Head, Peter M. “The Gospel of Mark in Codex Sinaiticus: Textual and Reception-Historical Considerations.” TC: A Journal of Biblical Textual Criticism 13 (2008): 1-38.

Pickering, Wilbur N. The Identity of the New Testament Text IV. 4th ed. Dallas: Wilbur N. Pickering, 2012.

Robinson, Maurice A. “The Case for the Longer Ending of Mark.” TC: A Journal of Biblical Textual Criticism 6 (2001).

Snapp, James. Authentic: The Case for Mark 16:9–20. n.p.: self-published, 2014.

Snapp, James. The Early Patristic Reception of Mark 16:9–20. https://bcs.edu/wp-content/uploads/2025/01/Snapp-ECJ_final.pdf

Trinitarian Bible Society. “Mark 16.” Accessed March 3, 2026. https://www.tbsbibles.org/page/Mark16.


መጽሐፍ ቅዱስ