የእግዚአብሔር ልጅ ክብር
የዮሐንስ ወንጌል 5 ሐቲት
በወንድም ሚናስ
የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 5 አውድ ስንመለከት ጌታ ኢየሱስ በቤተ ሳይዳ መጠመቂያ አጠገብ ያለውን ሰው መፈወሱን ከዚያም አይሁድ (በተለይም ፈሪሳውያን) ሰንበትን ሽሯል እንዲሁም ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሏል በማለት እንደ ከሰሱት እናነባለን (ቍ. 18) ። በምላሹም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገሩት ትክክል መሆኑን ለማጽናት የተናገራቸውን ቃላት ስንመለከት አምላክነቱን የሚያረጋግጡ ሆነው እናገኛቸዋለን። በዚህች አጭር መጣጥፍ የተወሰኑትን ቍጥሮች በአትኩሮት በማጤን ስለ ጌታችን ማንነት የሚሰጡንን ድንቅ ምልከታ እንቃኛለን።
ቍጥር 21፦
“ምክንያቱም አብ ሙታንን እንደሚያስነሣ፣ ሕይወትንም እንደሚሰጥ፣ ወልድም ደግሞ ለሚፈቅደው ሁሉ ሕይወትን ይሰጣል።”
ὥσπερ γὰρ ὁ πατὴρ ἐγείρει τοὺς νεκροὺς καὶ ζῳοποιεῖ, οὕτως καὶ ὁ υἱὸς οὓς θέλει ζῳοποιεῖ.
በብሉይ ኪዳን መሠረት “ሙታንን ማስነሳትም” ሆነ “ሕይወትን መስጠት” የያህዌ ፍቃድ ነው፦
“እግዚአብሔር ይገድላል፤ ያድናልም፤ ወደ መቃብር ያወርዳል፤ ያወጣልም።”
— 1ኛ ሳሙኤል 2፥6 (አዲሱ መ.ት)
“የእስራኤልም ንጉሥ ደብዳቤውን ወዲያው እንዳነበበ ልብሱን ቀዶ፣ “ለምጽ እንድ ፈውሰው ይህን ሰው ወደ እኔ መላኩ እኔ ገድዬ ማዳን የምችል አምላክ ሆኜ ነውን? እንግዲህ ጠብ ሲፈልገኝ እዩ!” አለ።”
— 2ኛ ነገሥት 5፥7 (አዲሱ መ.ት)
በብሉይ ኪዳን ብቻ ሳይሆን ጥንታውያን የሆኑት የአይሁድ መዛግብትም ጭምር ሕይወትን ሰጪ የሆነው አምላክ ያህዌ ብቻ መሆኑን ተናግረዋል፤ ለምሳሌ ታልሙድን ብንመለከት እንዲህ ይለናል፦
“ረቢ ዮሐንስ አለ፡- ለማንም የማያጋራው በቅዱሱ እጅ ሦስት መክፈቻዎች ተጠብቀው ይገኛሉ፣ እነርሱም፡ ዝናብን መስጠት፤ ልጅን መስጠት፤ ሙታንን ማስነሳት ናቸው።”[1]
ሆኖም ግን አንዳንድ ወገኖች “ነቢዩ ኤልያስ በ1ኛ ነገሥት 17 ላይ የመበለቲቱን ልጅ አስነስቷል፣ እንዲሁም ሌሎች ነብያት ሙታንን እንደ ቀሰቀሱ ተጽፏል፤ ነገር ግን ኤልያስ ሆነ ሌሎች ነብያት አምላክ እንዳልሆኑ ግልጽ ነው። ታዲያ የክርስቶስም በዚህ ስሌት የማይታይበት አግባብ ምን ይሆን?” ይሉናል። ይሁን እንጂ ይኽ ጥያቄ ጌታችን በዚህ ኃይለ ቃል ላይ ምን እንዳለ ካለማስተዋል የሚመነጭ ነው። ጌታ እንዲህ ነው ያለው “ወልድም ደግሞ ለሚፈቅደው ሁሉ ሕይወትን ይሰጣል [οὕτως καὶ ὁ υἱὸς οὓς θέλει ζῳοποιεῖ]።” ኢየሱስ የወደደውን በፍቃዱ ከሙታን ይቀሰቅሳል። ኤልያስም ሆነ መሰል ነብያት በአምላክ ፍቃድ በመታገዝ ሙታንን ያስነሳሉ። ፕሮፌሰር ዶናልድ ካርሰን የተሰኙ ስመጥር የአዲስ ኪዳን ሊቅ ይህንን አስመልክቶ የተናገሩትን እንመለከት፦
“…በዚህ ክፍል ከኤልያስ በተለየ መልኩ ኢየሱስ መለኮታዊ ኃይል እንዳለው እንረዳለን። ምክንያቱ ደግሞ፤ ነጥቡ በቍ. 22 ላይ ይበልጡኑ ተብራርቷል፣ በቤተ ሳይዳ ከበሽተኞቹ መካከል አንዱን መርጦ እንደፈወሰ (ቁ. 6) እንደዚሁ ሕይወትንም ለወደደው ይሰጣል። ሕይወትን የሚሰጠው ለራሱ ግብና ዓለማ ነውና( ዮሐ 15፥16)።”[2]
ቍጥር 22፦
“አብ በማንም ላይ አይፈርድም፤ ነገር ግን ፍርድን ሁሉ ለወልድ አሳልፎ ሰጥቶታል፤”
οὐδὲ γὰρ ὁ πατὴρ κρίνει οὐδένα, ἀλλὰ τὴν κρίσιν πᾶσαν δέδωκεν τῷ υἱῷ,
እዚህም የክርስቶስ አምላክነት የሚያሳይ ሌላ መረጃ አለን። እንዴት? ካላችሁ፤ ብሉይ ኪዳን ስለ እግዚአብሔር ፈራጅነት የተናገረውን እናንብብ፦
“በዚያ ዘመን፣ በዚያ ጊዜ፣ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ምርኮ ስመልስ፣አሕዛብን ሁሉ እሰበስባለሁ፤ ወደ ኢዮሣፍጥም ሸለቆ አወርዳቸዋለሁ፤ ስለ ርስቴ፣ ስለ ሕዝቤ፣ ስለ እስራኤል፣ በዚያ ልፈርድባቸው እገባለሁ፤ ምድሬን ከፋፍለዋል፤ ሕዝቤንም በሕዝቦች መካከል በታትነዋልና። በሕዝቤ ላይ ዕጣ ተጣጣሉ፤ ወንዶች ልጆችን በዝሙት አዳሪዎች ለወጡ፤ ወይን ጠጅ ለመጠጣትም፣ ሴቶች ልጆችን ሸጡ።” ኢዮኤል 3፥1-3 (አዲሱ መ.ት)
ቍጥር 23፦
“ይኸውም፣ ሁሉ አብን እንደሚያከብሩ ወልድን ያከብሩት ዘንድ ነው፤ ወልድን የማያከብር፣ የላከውን አብንም አያከብርም።”
ἵνα πάντες τιμῶσιν τὸν υἱὸν καθὼς τιμῶσιν τὸν πατέρα. ὁ μὴ τιμῶν τὸν υἱὸν οὐ τιμᾷ τὸν πατέρα τὸν πέμψαντα αὐτόν.
በቍጥር 22 ላይ አብ ለወልድ ፍርድን እንደሰጠው ከተናገረ በኋላ፣ ፍርድን የሰጠበት ምክንያት በቍጥር 23 ላይ ἵνα “ሂና” በምትል ሳብያ ለውጤት አመልካች መስተፃምር ይጀምራል። አብ ለወልድ ፍርድን የሰጠበት ውጤት ደግሞ “ሁሉ አብን እንደሚያከብሩ ወልድን ያከብሩት ዘንድ ነው።”
“እንደ” (καθὼς “ካቶስ”) የሚለውን ቃል እናስተውል። ጌታችን ኢየሱስ አብ በሚመለክበት አግባብ ወልድ እንደሚመለክ እየገለጸ ነው። ልብ በሉ! አንድ ሰው ፍጥረታት ሁሉ ያህዌን እንደሚያከብሩት መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልን ማክበር አለባቸው፤ አሊያም ሁሉም ሰው አምላክን እንደሚያከብር እንደዚያው ሐዋርያው ጴጥሮስን ማክበር አለበት ብሎ ቢናገር ይኼ ዓይነት አገላለጽ ምንም ምክንያት መደርደር ሳያስፈልግ እንዲሁ በደመ ነፍስ ተገቢ እንዳልሆኑ እንገነዘባለን። ሆኖም ኢየሱስ አብን እንደምናከብረው ሁላችንም ወልድን ልናከብረው እንደሚገባን ተናግሯል። ለእግዚአብሔር በብቸኝነት ስለሚሰጠው ክብር ነቢዩ ኢሳይያስ የተናገረውን በአንክሮ እናጢን፦
“እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ስሜም ይህ ነው፤ ክብሬን ለሌላ፣ ምስጋናዬንም ለጣዖት አልሰጥም።”
— ኢሳይያስ 42፥8 (አዲሱ መ.ት)
ክርስቶስ ከአብ ጋር የተካከለ መለኮት ባይሆን ኖሮ እንዲህ ያለ ሥልጣን እንዳለውና በዚህ መጠን ክብር እንደሚገባው ባልተናገረ ነበር!
ማጣቀሻዎች
[1] Talmud, Taanit 2a:12
[2] D.A. Carson, The Pillar New Testament Commentary – The Gospel According to John, pg. 253