የእግዚአብሔር ልጅ ክብር በዕብራውያን ፩
ወንድም ሚናስ
የዕብራውያን መልዕክት ጸሓፊ በመጀመሪያ የመልዕክቱ ምዕራፍ ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ መኾኑን የሚያሳዩ ጠንካራ ማስረጃዎችን ያቀርባል። በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ወልድ ዓለምን መፍጠሩ እና ደግፎ መያዙን፣ ከአብ ጋር የመለኮት ባሕርይ ተካፋይ መኾኑን፣ ከመላእክት ስግደት መቀበሉን፣ እንዲሁም “አምላክ” እና “ጌታ” በሚሉ መለኮታዊ ስሞች መጠራቱን ይገልጻል። በዚህ መጣጥፍም የኢየሱስ ክርስቶስ መለኮታዊነት በሚያመለክቱ እያንዳንዱ አረፍታተ ነገር ላይ ትንታኔ እናቀርባለን። በፀረ ሥላሴአውያን ወገኖች ለሚነሡ ሙግቶችም የዐጸፋ ምላሽ የምንሰጥ ይኾናል።
የዓለማት ፈጣሪ ነው
የዕብራውያን መልእክት ጸሓፊ፣ እግዚአብሔር ልጁን “ዅሉን ወራሽ” እንዳደረገው በመግለጽ የዳዊት ዙፋን ወራሽ መኾኑን ያመለክታል። በዚህ ሳይገደብም፣ አምላክ ዓለማትን በርሱ (በልጁ) መፍጠሩን ይናገራል “ዅሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን” (ዕብ.1፥2)። “ዓለማት” ለሚለው የተተረጐመው የጽርእ ቃል “አዮናስ”(αἰῶνας) የሚል ሲኾን፣ አጽናፈ ዓለምን የሚያመለክት ነው[1]። በዚህም የዕብራውያን ጸሓፊ፣ እንደ ሌሎች የዐዲስ ኪዳን ጸሓፊያን (ዮሐ. 1፥3፤ 1ኛ ቆሮ 8፥6፤ ቈላ. 1፥16) ክርስቶስ የዓለማት ፈጣሪ መኾኑን ይነግረናል። ከጥቂት ቍጥሮች በኋላም፣ ክርስቶስ የፍጥረተ ዓለሙ አስገኝ እንደኾነ በድጋሚ ይናገራል “ደግሞ፦ ጌታ ሆይ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትኽ፥ ሰማዮችም የእጆችኽ ሥራ ናቸው፤ እነርሱም ይጠፋሉ አንተ ግን ጸንተኽ ትኖራለኽ፤ ዅሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ፥ እንደ መጎናጸፊያም ትጠቀልላቸዋለኽ ይለወጡማል፤ አንተ ግን አንተ ነኽ፥ ዓመቶችኽም ከቶ አያልቁም ይላል”(ዕብ.1፥10-12)። ጸሓፊው ይህንን ምንባብ ያጣቀሰው ከመዝሙር 110፥25 ሲኾን፣ በጊዜው ለያህዌ የተነገረ መኾኑን ልብ ይሏል።
ከላይ ከተገለጸው ሐሳብ በተቃራኒ፣ ፀረ ሥላሴአውያን ወልድ የአጽናፈ ዓለም ፈጣሪ መኾኑን አይቀበሉም። ለምሳሌ ኬጋን ቻንድለር የተባሉ ግለሰብ በዕብ1፥2 ላይ “አዮናስ” αἰῶνας የሚለው ቃል “ዘመናት” እንጂ “ዓለማት” የሚል ትርጒም የለውም፤ ይህ ዘመን ደግሞ የሚያመለክተው እግዚአብሔር በመሲሑ አማካኝነት ስላወረሰን “የሚመጣው ዓለም”(ዕብ.2፥5) እንጂ ስለ አጽናፈ ዓለም መፍጠሩ የሚናገር አይደለም ይላሉ[2]።
በርግጥ “አዮናስ” αἰῶνας የሚለው ቃል “ዘመናት” የሚለው ሊያመለክት የሚችልበት አግባብ ቢኖሩም፣ በዕብ .1፥2 ግን ይህንን ትርጒም ልንጠቀምበት የማንችልበት ቢያንስ ሦስት ምክንያቶች አሉ። አንደኛ፡— ጸሓፊው በዕብ.1፥2 የተጠቀማቸውን ቃላት አጽናፈ ዓለምን የሚያመለክቱ መኾናቸው በሌሎች ቦታዎቹ አሳይቶአል። በዕብ.11፥3 ላይ “ዓለማት በእግዚአብሔር ቃል እንደ ተዘጋጁ” ሲል “ዓለማት” ለማለት የተጠቀመው የጽርእ ቃል “አዮናስ” αἰῶνας የሚለው ተመሳሳይ ቃል ነው። በተጨማሪም “በፈጠረበት” ለሚለው የገባው ቃል “ኤፖዬሴን” ἐποίησεν የሚል ሲኾን በዚሁ ዕብ.12፥27 ፍጥረተ ዓለሙን ለማመልከት ጥቅም ላይ ውሎአል። ነገር ግን በዕብ. 2፥5 “የሚመጣው ዓለም” ለሚለው የተጠቀመው “ኦይኩሜኔ” οἰκουμένη የሚል ሌላ ቃል ሲኾን አማኒያን የሚወርሱትን የወደፊቱን ዘመን የሚገልጽ እንጂ ያለፈውን አጽናፈ ዓለም አያመለክትም። ኹለተኛ፡— ጸሓፊው ከጥቂት ቊጥሮች በኋላ፣ መዝሙረኛው የያህዌን ፈጣሪነት ያመለከተበትን ምንባብ(መዝ 102፥22-25) ለክርስቶስ በመጠቀም የዓለማት ገባሬ (ፈጣሪ) መኾኑን አረጋግጦአል(ዕብ.1፥10-12)። ሦስተኛ፡— ዕብ.1፥2 ላይ ያለው ቃል “ዘመናት” እንጂ “ዓለማት” አይባልም ብለን ብንቀበል እንኳ፣ እነኚህ ዘመናት የአኹኑንና የወደፊቱን ብቻ የሚመለከቱ አይደሉም። ምክንያቱም ዕብ 9፥26 ላይ ክርስቶስ “በዘመናት መጨረሻ” እንደተገለጠ ይናገራል፤ ይኸውም ከክርስቶስ መገለጥ በፊት ብዙ ያለፉ ዘመናት እንደነበሩ አመልካች ነው። ስለዚህ ጸሓፊው “ዘመናትን በፈጠረበት” ብሎ የሚያምን ቢኾን እንኳ፣ ይህ ዘመን የአኹንና የሚመጣውን ብቻ ሳይኾን፣ ያለፉትን ዘመናት ዅሉ የሚጨምር ነው። ስለዚህ ክርስቶስ ያለፈውንም የአኹኑንም የሚመጣውም ዘመናት አስገኚ ፈጣሪ ነው።
አጽናፈ ዓለምን ደግፎ ይዞአል
ጸሓፊያችን፣ ክርስቶስ ዓለማት መፍጠሩን ብቻ ሳይኾን፣ ዓለማትን አጽንቶ፣ ደግፎ የያዘው ርሱ መኾኑን እንዲህ ሲል ይናገራል “በኀያል ቃሉ ዅሉን ደግፎ ይዞአል”(ዕብ.1፥3)። “ደግፎ” ለሚለው የገባው የጽርእ ግስ (“ፌሮን” φέρων) ዓለማትን በቋሚነት አጽንቶ መያዙን የሚያመለክት ነው[3]። የአይሁዳውያን መጻሕፍት ደግሞ ዓለማት የጸኑት በአምላክ ጥበብና ቃል እንደኾኑ ያመለክታሉ[4]። ልክ እንደ ጳውሎስ (ቈላ.1፥17) የዕብራውያን ጸሓፊ ይህንን መለኮታዊ ግብር ለወልድ ይጠቀማል። ቅዱሳት መጻሕፍት ዓለማትን ማጽናት የእግዚአብሔር ተግባር መኾኑን በተደጋጋሚ ከመናገራቸው አንጻርና፣ ጸሓፊው ይህንን ግብር ለክርስቶስ ስለሰጠ፣ የመሲሑ መለኮትነትን ለማመልከት እንደ ተፈለገ መረዳት ይቻላል።
ኤሪክ ቻንግ የተባሉ ፀረ ሥላሴአዊ ለዚህ ሐረግ አማራጭ ትርጓሜ አቅርበዋል። በርሳቸው ዕይታ ዅሉን ነገር ደግፎ መያዙ ቅድመ ህልውናውን ወይም ዓለማት ከመፈጠራቸው በፊት የነበረ ተግባሩን አያሳይም፤ ይልቁንም በእግዚአብሔር ቀኝ በላቀው ስፍራ ከተቀመጠ በኋላ፣ አጽናፈ ዓለምን ያስተዳድር ዘንድ በአምላክ የተሰጠው ሥልጣንን አመልካች ነው ይላሉ። ስለዚህ እንደ ቻንግ አባባል፣ መሲሑ አጽናፈ ዓለምን ደግፎ የመያዙ ሥራው ፍጥረት ከተጀመረበት ጊዜ አንሥቶ ሲያከናውነው የቈየ ተግባር አይደለም። ይልቁንም ይህንን ሥራ መሲሑ ከሙታን ከተነሣ በኋላ፣ የተሰጠውን አስተዳደራዊ ሥልጣን የሚገልጽ ነው[5]። ነገር ግን፣ “በኀያል ቃሉ ዅሉን ደግፎ ይዞአል” የሚለውን ሐረግ ወልድ አጽናፈ ዓለም ከተጀመረበት ጊዜ አንሥቶ እስከ አኹን ያለ ተግባሩ አመልካች ለመኾኑ ኹለት ምክንያቶችን አቀርባለኹ። በመጀመሪያ፡— ምሁራን በዕብራውያን 1፥2-4 ላይ የተጠቀሱት ሰባቱ ነጥቦች “ቀለበታዊ መዋቅር” የተከተሉ እንደኾኑ ይናገራሉ። ይህ መዋቅር የወልድን ከፍ ከፍ ማለት በማወጅ ጀምሮ፣ ቅድመ ህልውናውንና ዓለማትን በመፍጠር እንዲሁም በማጽናት ረገድ ስላለው ሚና ይገልጻል፤ አስከትሎም ኀጢአትን ስለ ማንጻት ሥራው በጥልቀት ካብራራ በኋላ፣ በስተመጨረሻም እንደገና ወደ ከፍ ከፍ ማለቱ (ክብሩ) ይመለሳል። አከራካሪው ሐረግ የሚገኘው ደግሞ ጸሓፊው ወልድ ዓለምን ስለ መፍጠሩ በገለጸበት እና ኀጢአትን ስለ ማንጻቱ በጻፈበት ክፍል መኻከል ነው። ይህ አቀማመጥ የሚያሳየው ወልድ አጽናፈ ዓለምን ደግፎ የመያዝ ሥራው የተከናወነው ኀጢአትን ከማንጻቱና ከፍ ከፍ ከማለቱ በፊት እንደ ነበረ ነው።

ኹለተኛ፡— ከላይ እንደተጠቀሰው፣ በዚህ ክፍል ውስጥ መሲሑ የተገለጠበት አገላለጽ፣ የአምላክን ጥበብ ወይም ቃል ፍጥረተ ዓለሙን በመፍጠር ኺደት የነበራቸውን ሚና በሚናገሩ የተለያዩ የአይሁድ ድርሳናት ውስጥ ከተጠቀሱ ቃላት ጋር ይመሳሰላል። እነዚህ ጥንታዊ ድርሳናት የአምላክ ጥበብ እና ቃል ከመጀመሪያውኑ ከአምላክ ጋር እንደ ነበሩ፣ ዓለማትን በመፍጠር ኺደትም የአምላክ ወኪል ኾነው እንደሚሠሩ፣ ዅሉን ነገር ደግፈው እና አጽንተው እንደሚያዙ ይገልጻሉ[6]። የዕብራውያን የመጀመሪያ ተደራሲያን ደግሞ ይህንን የአይሁዳውያን ምልከታ በእጅጉ እንደሚያውቁ ይገመታል። የዕብራውያን ጸሓፊ ዐሳብ፣ ልክ እንደ አምላክ ጥበብ እና ቃል ዅሉ፣ ወልድም ከቍሳዊው ፍጥረት በፊት የነበረ፣ ፍጥረታትን ያመጣ እና ደግፎ የያዘ ነው። ከዚህ አንጻርም የወልድ አጽናፈ ዓለምን የመደገፍ ግብር፣ ከትንሣኤው በኋላ ዓለምን ለመግዛት የተሰጠውን ሥልጣንን ብቻ አመልካች ነው የሚለው የቻንግ ትርጓሜ፣ የዕብራውያን ጸሓፊ ሐረጉን የተጠቀመበት ዐውዳዊ ሐሳብ በአግባቡ አያብራራም። በመኾኑም “በሥልጣኑ ቃል ዅሉን ይደግፋል” የሚለው አረፍተ ነገር ፣ መሲሑ ፍጥረታት ህልውናቸውን ካገኙበት ጊዜ ጀምሮ እያከናወነ ያለውን መለኮታዊ ተግባሩን የሚያመለክት ነው።
ከአባቱ ጋር በመለኮት ተካክሎ ይኖራል
የዕብራውያን መልእክት ጸሓፊ የወልድን መለኮታዊ ተግባራት ከመግለጽ ባለፈ፣ የወልድን መለኮታዊ ማንነት ጭምር ይነግረናል። እንደ ጸሓፊው ገለጻ “ርሱ የክብሩ ነጸብራቅና የባሕርዩ ትክክለኛ ምሳሌ” (ዕብ.1፥3) ነው። “ትክክለኛ ምሳሌ” ለሚለው የገባው የጽርእ ቃል “ኻራክቴር” (χαρακτὴρ) የሚል ሲኾን ተመሳሳይ አንድ ዐይነት የኾነን ቅጂ ለመግለጽ ጥቅም ላይ የሚውል ቃል ነው[7]። ወልድን “የባሕርዩ ትክክለኛ ምሳሌ(ኻራክቴር) ” ብሎ መግለጹ፣ ወልድ አባቱ ተደርጐ ከተገለጠው ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም አምሳል መኾኑን ያመለክታል ። ጸሓፊው በእግዚአብሔር እና በወልድ መኻከል ያለውን የአባትና የልጅ ቊርኝት እየገለጸ መኾኑን ለማሳየት “ኻራክቴር” (χαρακτὴρ) የሚለው ቃል በሚከተለው ምንባብ በምን አግባብ እንደገባ ልብ ይሏል:—
“ወላጆች ለልጆቻቸው ያላቸውን ጥልቅ ፍቅርና ስሜት እንዴት ልገልጽ እችላለኹ ?! ትንሽ ልጅ ላይ በአእምሮውም ኾነ በቅርጹ ከእኛ ጋር አንድ ዐይነት የኾነ አምሳል(χαρακτὴρ) እናተምበታለን” (4ኛ መቃብያን 15፥4)።
ይህ ኾኖ ሳለ፣ የክርስቶስ መለኮትነትን የማይቀበሉ ግለሰቦች የዕብራውያን ጸሓፊ ወልድ ከአብ ጋር አንድ ዐይነት ባሕርይ እንዳለው መግለጹን ለማስተባበል ሞክረዋል። ቻንግ ይህንን አገላለጽ ኢየሱስ ኀጢአት የሌለበት ፍጹም ሰው መኾኑን ለማረጋገጥ ብቻ የቀረበ ነው ብለው ይከራከራሉ። እንደ ርሳቸው አባባል ኢየሱስ ልክ እንደ ማንኛውም ሰው በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ ቢኾንም፣ ከሌሎች ፍጥረታት በተለየ መልኩ ኀጢአትን አልሠራም፤ በዚህም ምክንያት የእግዚአብሔርን ባሕርይ ፍጹም በኾነ ኹኔታ ያንጸባርቃል ይላሉ[8]። በርግጥም ክርስቶስ በምድራዊ ሕይወቱ እግዚአብሔርን ፍጹም በኾነ ኹኔታ የወከለ ኀጢአት የሌለበት ሰው ነበር (ዕብ. 4፥15፤ 1 ጴጥ. 2፥22፤ 2 ቆሮ. 5፥21 ይመለከቷል)። ይኹን እንጂ ከላይ ለማሳየት እንደተሞከረው፣ በዕብ. 1፥3 ላይ የሚገኙት እነዚህ መግለጫዎች ቀጥተኛ ዐውድ የሚያመለክተው የወልድን ቅድመ ህልውና ወይም ዓለም ከመፈጠሩ በፊት የነበረውን ሥራ በሚተርከው ምንባባዊ ዐውድ ነው። ስለዚህ ምንም እንኳን ጸሓፊው ወደፊት ስለ ወልድ ምድራዊ ሕይወት የሚያብራራ ቢኾንም (ዕብ. 2:9-18)፣ ኢየሱስ በምድር ላይ ሳለ ኀጢአት አልባ ሕይወት መኖሩን በዚህ ክፍል ውስጥ አልተጠቀሰም።
ከመላእክት ስግደትን ተቀብሎአል
ክርስቶስ የኀጢአት ስርየትን ካስገኘ በኋላ፣ በክብር ሊነግሥ ወደ እግዚአብሔር ዙፋን ከፍ ማለቱ ተጽፎአል (ዕብ. 1፥3-4፤ 8፥1፤ 12፥2)። በእግዚአብሔር ዙፋን ከፍ ከፍ ማለቱን ከመላእክት የላቀ ለመኾኑ አንዱ ማሳያ ነው(ዕብ.1፥4)። ዓለምን የፈጠረው ወልድ፣ ሰብኣዊ ሥጋን በመልበሱና መከራን በተቀበለ ጊዜ “ከመላእክት በጥቂት አንሶ ነበር” (ዕብ. 2፥9)። ነገር ግን ሥጋ የለበሰው ወልድ ከሙታን ተነሥቶ ወደ እግዚአብሔር ዙፋን ሲያርግ ከመላእክት በክብርና በማዕረግ የላቀ መኾኑን ተረጋግጦአል። የወልድን ከፍ ከፍ ማለት (መክበር) መነሻ በማድረግም፣ እግዚአብሔር መላእክት ለወልድ እንዲሰግዱ ሲያዝዝ ይነበባል “ደግሞም በኵሩን ወደ ዓለም ሲያገባ፦ የእግዚአብሔር መላእክት ዅሉ ለርሱ ይስገዱ ”(ዕብ.1፥6) ። ይህ ጥቅስ የተወሰደው ከዘዳግም 32፥43 ሲኾን፣በምንባቡ ላይ መላእክት የሰገዱለት ያህዌ (እግዚአብሔር) ራሱ ነበር። ስለኾነም፣ በዕብ. 1፥6 ላይ መላእክት በእግዚአብሔር ትእዛዝ መሠረት ለአምላክ ብቻ የሚገባውን አምልኮ ለወልድ እንዳቀረቡ ይነግረናል።
ይህ ምንባብ የክርስቶስን መለኮትነት አያሳይም የሚሉ አንዳንድ ምሁራን፣ ይህንን ለማስተባበል የሚያቀርቡት ማስተባበያ አለ። ይኸውም በጥንት የአይሁድ ድርሳናት ከኾኑት መኻከል በኾነው “ሕይወተ አዳም ወሔዋን”[9] መላእክት ለአዳም በሰማያት እንደ ሰገዱ ተገልጾአል ይህ ከክብር እንጂ አዳምን ከማምለክ ጋር እንደማይያያዝ ዅሉ፣ ለወልድም መላእክት መስገዳቸው ክርስቶስን ማምመለካቸው ወይም መለኮት መኾኑን አያመለክትም ይላሉ[10]። እንግዲህ በተባለው ድርሳን ላይ ሰይጣን ከእግዚአብሔር “ፊት” (facies) እንደተባረረ ተጽፎአል፤ ይህ ደግሞ ሰይጣን በሰማያዊ ስፍራ እንደነበረ በግልጽ ያሳያል። በአንጻሩ ግን፣ መላእክት ለአዳም በሰገዱለት ጊዜ አዳም የነበረው በእግዚአብሔር “ዕይታ” (conspectus) እንደ ነበር ተገልጾአል። በድርሳኑ ውስጥ “ፊት”(facies) እና “ዕይታ”(conspectus) የሚሉት ቃላት፣ በሌላ ቦታዎች ላይ ጥቅም ላይ የዋሉበትን መንገድ ስንመለከት፣ መላእክት ለአዳም የሰገዱለት በምድር ላይ እያለ መኾኑን እንረዳለን። ምንም እንኳን አዳም ወደፊት በዓለም መጨረሻ ላይ ሰማያዊ ዙፋን እንደሚያገኝ የተጻፈ ቢኾንም፣ ይህ ዙፋን ግን ቀደም ሲል የሰይጣን የነበረው ዙፋን ነው። ይህ ሰማያዊ ዙፋን ሰይጣን ባመፀ ጊዜ ዙፋኑን ከሰማይ ከዋክብት በላይ ከፍ አድርጐ እንደ እግዚአብሔር ለመኾን ሽቶ ነበር፤ ይኸውም የርሱ ዙፋን በታችኛው የሰማይ ክፍል ላይ የነበረ መኾኑን አስረጅ ነው። የዕብራውያን ጸሓፊ ግን መላእክት ለወልድ የሰገዱለት በሰማያዊ ስፍራ ከእግዚአብሔር ጐን በዙፋን ላይ ተቀምጦ ሳለ ነው[11]። ስለዚህ መላእክት ለአዳም በምድር መስገዳቸው፣ ክርስቶስ ከመላእክት ለቀረበለት ስግደት ተፃራሪ ሙግት ሊኾን አይችልም ብዬ ዐስባለኹ።
አምላክ ተብሎአል
በማስከተል ጸሓፊው በመልእክቱ ከምዕራፍ አንድ እስከ ኹለት ባለው ክፍል ውስጥ፣ ወልድ ከመላእክት ዅሉ እጅግ የላቀ መኾኑን የሚያሳይ ሰፊ ማብራሪያ ያቀርባል። በዚህ መኻከልም፣ መዝሙር 45፥6 በመጥቀስ ወልድን በቀጥታ “አምላክ” ብሎ ሲጠራው እናነባለን “ ስለ ልጁ ግን፦ “አምላክ ሆይ፥ ዙፋንኽ እስከ ዘላለም ድረስ ይኖራል፤ የመንግሥትኽ በትር የቅንነት በትር ነው”(ዕብ.1፥8)። በዚህ ምንባብ አምላክነቱ በእግዚአብሔር አብ መነገሩ ይበልጥ የሚያስደንቅ ነው።
በዕብራውያን 1፥8 ላይ ወልድ “አምላክ” ተብሎ መገለጹን በተመለከተ፣ ፀረ ሥላሴአውያን የሚያቀርቡት ሙግት፣ የዕብራውያን ጸሓፊ ያጣቀሰው የመዝሙር ምንባብ፣ በመጀመሪያው ዐውዱ (አቀማመጡ) ለእስራኤል ንጉሥ የተነገረ መኾኑን በማመልከት ነው። ኾኖም ግን መዝሙር 45 የንጉሡ ማንነት ፈጽሞ አለመጠቀሱን ያስተውሏል። በዚህም የዕብራውያን ጸሓፊ በመላው መልእክቱ እንደ ጠቀሳቸው ሌሎች የመዝሙራት ክፍሎች ኹሉ፣ መዝሙር 45 መሲሐዊ ፍቺን (ትንቢትን) ያዘለ ነው። የዕብራውያን ጸሓፊ ለዘመኑ ቅርብ እንደነበሩት እንደ ሌሎች የጥንት ክርስቲያን አማኒያን [12] ዅሉ ይህንን የመዝሙር ክፍል መሠረት በማድረግ ኢየሱስ አምላክ መኾኑን ይነግረናል።
ዕብ. 1፥8 ኢየሱስ አምላክ መኾኑን ያሳያል የሚለውን አተረጓጐም ለመቃወም የሚሰነዘረው ሌላም ሙግት፣ ቍጥር 9 ላይ ሌላ አካል (አብ) የርሱ አምላክ ተድርጐ መገለጹን ዐቢይ በማድረግ ነው[13]። ነገር ግን በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ እንደሚታየው ዅሉ፣ በዕብራውያን መልእክትም ውስጥ ኢየሱስ አምላክ መኾኑን የሚያረጋግጡት ክፍሎች እና አብ የኢየሱስ አምላክ መኾኑን የሚገልጹት ሐረጐች ምንም ዐይነት የሐሳብ ግጭት ሳይታይባቸው ጐን ለጐን ተቀምጠዋል (ዮሐ. 20፥17, 28፤ ዕብ. 1፥8, 9)። ኢየሱስ በሥጋ በመገለጡ (በትሥጉቱ) ምክንያት ሰው ኾኖአል፤ የፍጥረት ዓለም አካልም ለብሶአል(ዮሐ. 1:14፤ ፊልጵ. 2:6–7)፤ ስለዚህም ሰው በመኾኑ በዚህ ሰብኣዊ ማንነቱ አብን አምላኩ አድርጐ ማክበሩ የሚያስገርም አይደለም። በተመሳሳይ ጊዜ ግን ከመጀመሪያ በነበረው፣ ባልተፈጠረው መለኮታዊ ባሕርዩ ምክንያት ግን አምላክነቱ የጸና ነው።
ዘላለማዊ ነው
ከላይ እንደተጠቀሰው፣ በዕብራውያን 1:10-12 ላይ ጸሓፊው ወልድ ዓለምን በመፍጠር ረገድ የነበረውን ሚና ለማብራራት መዝ. 102፥25-27 ይጠቅሳል “ጌታ ሆይ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትኽ፥ ሰማያትም የእጆችኽ ሥራ ናቸው” (ዕብ. 1፥10፤ ከመዝ. 102፥25 ያነጻጽሩ)። በመቀጠልም ጸሓፊው ሰማይና ምድር ጊዜያዊ መኾናቸውን፣ እንደሚጠፉና እንደ ልብስም እንደሚጠቀለሉ፣ ወልድ ግን ለዘላለም ሕያው ኾኖ እንደሚኖር ይናገራል(ዕብ. 1፥11-12)። በተጨማሪም፣ ጸሓፊው ቀደም ሲል ወልድን “አምላክ” ብሎ ከጠራው በኋላ (ዕብ. 1:8)፣ አኹን ደግሞ ያህዌ ለሚለው ቃል ዐቻ በኾነው “ጌታ (“ኩሪዮስ” κύριος ) በሚል ቃል ይጠራዋል።
በመዝሙር 102፥25 ላይ ያለው ቃል በዕብራውያን 1፥10 ላይ ለወልድ መዋሉ፣ ክርስቶስ ዓለምን አልፈጠረም የሚለውን የመናፍቃንን አመለካከት የሚቃረን ነው። ፀረ ሥላሴአውያን በመዝሙር 102፥25 ያህዌ ዓለምን ስለ መፍጠሩ የሚናገር መኾኑን የሚቀበሉ ቢኾንም፣ የዕብራውያን ጸሓፊ ግን ይህንን ጥቅስ ለኢየሱስ የሰጠው የአጽናፈ ዓለም አስገኝ እንደነበረ ለማሳየት ሳይኾን፣ የዐዲሱ ዘመን ወይም ዓለም መሥራችና ገዥ አድርጐ ለመግለጽ ነው ብለው ይከራከራሉ። በዚህ ምክንያትም ይህንን ጥቅስ ከዕብራውያን 1፥2 አረዳዳቸው ጋር በማቈራኘት፣ ክፍሉ ኢየሱስን የቍሳዊው ዓለም ከዋኝ አድርጐ ሳይኾን፣ ለሚመጣው መሲሐዊ ዘመንና ዓለም፣ መሐንዲስ (ዋና ከዋኝ) እንደ ኾነ የሚያሳይ ነው ይላሉ[14]።
ኾኖም ግን፣ የዕብራውያን 1፥10 ምንባብ ዐውድ እዚህ ላይ እየተናገረ ያለው ወልድ ስለሚያመጣው ስለሚመጣው ዓለም(ዘመን) ነው የሚለውን ሐሳብ ሙሉ በሙሉ ውድቅ ያደርገዋል። ምክንያቱም ቀጥሎ ያሉትን ቍጥሮች ስንመለከት፣ እየተገለጸ ያለው ዓለም እንደሚጠፋና ፍጻሜም እንደሚኖረው በግልጽ ይናገራሉ(ዕብ.1፥11-12) ። ይህ ደግሞ “የማይጠፋ፣ የማይበላሽ፣ የማይለወጥ” (1ኛ ጴጥ.1፥4) ተብሎ ከተገለጸው ዘላለማዊቷ ዐዲሲቷ ዓለም ጋር ፈጽሞ ሊገናኝ እንደማይችል ግልጽ ነው። የዕብራውያን ጸሓፊ እንደሚለው፣ ወልድ በመጀመሪያ ሰማያትንና ምድርን የፈጠረ ነው፤ እንዲሁም ፍጥረታት ቢለዋወጡና ውሎ ዐድረው ፍጻሜያቸውን ቢገኙ እንኳ፣ ርሱ ግን ለዘላለም ሳይለወጥ የሚኖር ነው። በርግጥም ጸሓፊው በኋላ ላይ እንዲህ ሲል ዐውጆአል “ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ዘላለምም ያው ነው” (ዕብ. 13:8)። ወልድ ዘላለማዊና የማይለወጥ ነው። እነዚህ ደግሞ ፍጹም የእግዚአብሔር ብቻ የኾኑ ባሕርያት ናቸው (ለምሳሌ፦ ሚል. 3፥6፤ መዝ. 102፥25-27)።
ማጠቃለያ
የዕብራውያን መልእክት ጸሓፊ በመልእክቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ ላይ ለመሲሑ አምላክነት (መለኮትነት) አሳማኝና ጠንካራ ማስረጃዎችን ያቀርባል። ክርስቶስን የዓለማት ፈጣሪና አጽንቶ የያዘ መኾኑን በመግለጽ፣ ከአብ ጋር ያንንኑ ተመሳሳይ መለኮታዊ ሥራ እንደሚሠራ፣ ርሱ “የክብሩ ትክክለኛ ነጸብራቅና የባሕርዩ ምሳሌ” መኾኑን በመጥቀስም፣ ወልድ ከአብ ጋር ያንንኑ ተመሳሳይ መለኮታዊ ማንነት ባሕርይ እንደሚጋራ በአጽንዖት አመልክቶአል። መላእክት ዅሉ ለርሱ እንደ ሚሰግዱለትም በመናገር ፣ ልክ እንደ አብ የመላእክትን አምልኮ እንደሚቀበል ይነግረናል። “አምላክ” እና “ጌታ/ያህዌ” ብሎ በመጥራትም፣ የመለኮታዊ ስሞች ተጋሪ መኾኑን ጽፎልናል። ፀረ ሥላሴአውያን የኾኑ መምህራን የእነዚህ ጥቅሶች ትርጒምና ክብደት ለመለወጥ ወይም ለማሳነስ የሚያደርጉት ጥረት ከዐውዱም ኾነ ከአመክንዮ አንጻር የሚያስኼድ አይደለም። በዕብራውያን ጸሓፊ መረዳት መሠረት፣ ወልድ ከአባቱ ጋር እኵል የኾነ፣ አምላካዊ ባሕርይ እና ሥልጣንን የተጐናጸፈ መለኮት ነው። ስሙ ቡሩክ ይኹን። አሜን።
ማስታወሻ
አንዳንዶች “በኵሩን ወደ ዓለም ሲያስገባ” የሚለውን በመያዝ መላእክት ለክርስቶስ የሰገዱት በምድር ነው የሚል ክርክር ሊያቀርቡ ይችላሉ ይህ ሙግት ግን በሚከተሉት ምክንያቶች አሳማኝ አይደለም። 1ኛ) የዕብራውያን ምዕራፍ 1 አጠቃላይ ሐሳብ የተመሠረተው በ በዕብ.1፥3 ላይ የተጠቀሰው ልጁ በክብር በአብ ቀኝ (በሰማይ) መቀመጡ ላይ ሲኾን፣ የብሉይ ኪዳን ጥቅሶችም የተዘረዘሩበት ምክንያትም ልጁ ከመላእክት በላይ መኾኑን ለማረጋገጥ ነው። በምዕራፉ ውስጥ ዙፋን፣ በትር፣ መንግሥት፣ እንዲሁም እንደ መዝሙር 2፣ 45 እና 110 ያሉ ንጉሣዊ መዝሙሮች በተደጋጋሚ በመጠቀም የመሲሑ ንጉሣዊ ሥልጣን እየተገለጸ ነው። በዕብ 1፥6 ያለው “በኵር” ( “ፕሮቶቶኮስ” πρωτότοκος) የሚለው ቃል ከመዝሙር 89 የተወሰደ ንጉሣዊ ማዕረግ ሲኾን፣ ዳዊት በኵር ተብሎ የተጠራው የመጀመሪያ ልጅ ስለነበር ሳይኾን እግዚአብሔር ከምድር ነገሥታት ዅሉ በላይ ስላከበረውና ዘላለማዊ ዙፋን ስለሰጠው ነው፤ ስለዚህም ይህ ማዕረግ በፍጹም ኹኔታ በመሲሑ ተፈጽሟል። በዚህ ምክንያት ዕብ.1፥6 ሥጋ ከመልበሱ ወይም በዳግም ምጽአቱ ስለሚፈጸም ኩነት የሚያመለክት ነው የሚለውን ክርክር ያፈርሳል። 2ኛ.) በዕብ.1፥6 ያለው “ዓለም” (“ኦይኩሜኔ” οἰκουμένη ) የሚለው ቃል የምድርን ዓለም ሳይኾን ሰማያዊውን ዓለም የሚያመለክት ነው፤ ምክንያቱም ዕብራውያን 2፥5 “የሚመጣውን ዓለም” ሲናገር፣ በዕብ11፥16 የሰማያዊው አገር፣ በ12፥22 ደግሞ ሰማያዊቷን ኢየሩሳሌም፣ በ13፥14 ደግሞ የሚመጣችው ከተማ በማለት ያንኑ ሰማያዊ እውነታ ይገልጻል። ስለዚህ ከከበረ በኋላ ወደዚህ ሰማያዊ ዓለም በገባ ጊዜ እግዚአብሔር መላእክቱ እንዲሰግዱለት ዐዘዘ የሚለው ፍቺ ትክክለኛ ሐሳቡን የጠበቀ ነው።
የኅዳግ መዘክር
[1] መጽሐፈ ጥበብ 13፥9፣ 14፥6፣ 18:4 Walter Bauer, A Greek-English Lexicon of the New Testament and Other Early Christian Literature, rev. and ed. Frederick W. Danker, 4th ed. (Chicago: University of Chicago Press, 2021), 28-29.
[2] Chandler, The God of Jesus, 300
[3] “ፌሮን” φέρων ገቢር፣ የአኹን ጊዜ ግሳዊ ቅጽል ሲኾን ሰዋስዋዊ አገባቡ ጅማሬን ሳያሳይ ካለፈ ጊዜ ጀምሮ እስከ አኹን ያለ ድርጊትን ያመለክታል።
[4] ሲራክ 43፥26፣ መጽሐፈ ጥበብ 7፥24፣ 8፥1፣ Philo, On Dreams 1.241; Migration of Abraham 6; De plantation 8-9
[5] Eric H.H. Chang, The Only Perfect Man: The Glory of God in The Face of Jesus Christ, 2nd ed. (np: Christian Disciples Church, 2016), 204-205
[6] Amy L. B. Peeler, You Are My Son: The Family of God in the Epistle to the Hebrews (New York, NY: T&T Clark, 2014), 21-22-23.
[7] Scott D. Mackie, “Confession of the Son of God in the Exordium of Hebrews,” JSNT 30 (2008), 442.
[8] Chang, 204
[9] በእንግሊዘኛው The live of Adam and Eve
[10] Moffitt, Atonement, 136–37; Fletcher-Louis, “Worship,” 114.
[11] በዚህ ርእሰ ጒዳይ ሰፊ ማብራሪያ ከፈለጉ የሚከተለውን መጽሐፍ ይመለከቷል፡— Ray M. Lozano, The Proskynesis of Jesus in the New Testament: A Study on the Significance of Jesus as an Object of “Proskuneo” in the New Testament Writings.
[12] ለምሳሌ ዮስጢኖስ ሰማዕት Dialogue with Trypho 38.3; 63.5
[13] Chang, 210
[14] Anthony Buzzard, Jesus Was Not a Trinitarian: A Call to Return to the Creed of Jesus (Morrow, GA: Restoration Fellowship, 2007), 423.
