መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት እናንብብ? ጠቃሚ መርሆች
መጽሐፍ ቅዱስ ማዕከላዊ መልዕክቱ ለማንኛውም ሰው ግልፅ ሊሆን በሚችልበት ሁኔታ የተቀመጠ ስለሆነ በሁሉም የዕድሜ ክልሎችና በየትኛውም የትምህርት ደረጃ ላይ ላሉ ሰዎች መናገር የሚችል መጽሐፍ ነው፡፡ 2ጢሞቴዎስ 3፡14-15 ላይ ህጻናት እንኳ የመጽሐፍ ቅዱስን ዋና መልዕክት መረዳት እንደሚችሉ ይናገራል፡፡ ይህ ማለት ግን ሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እኩል በሆነ ሁኔታ ግልፅ ናቸው ወይንም ደግሞ በቀላሉ ለመረዳት የሚያዳግቱ ክፍሎች የሉም ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ማንኛውም ሰው የዘላለምን ሕይወት ማግኘት እንዲችል ማዕከላዊ መልእክቱ ብዙ ጊዜ በመደጋገምና እጅግ ግልጽ በሆነ ሁኔታ ተቀምጧል፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው እንድናነበው እንጂ እንደ ምትሃታዊ መጽሐፍ በመቁጠር ተንተርሰነው እንድንተኛ ወይንም ደግሞ ሊነካካ በማይችልበት ስፍራ በጥንቃቄ እንድናስቀምጠው አይደለም፡፡ የእግዚአብሔር ቃል በሕይወታችን ውስጥ ሊሠራ የሚችለው ሲነበብ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል እንደ አድካሚ ኃይማኖታዊ ሕግጋት ስብስብ ሊታሰብ አይገባም፡፡ የእግዚአብሔር ቃል የሕይወት ቃል ነው፤ ሕያውና የሚሠራም ነው፡፡ ስናነበው እምነትን በውስጣችን ይፈጥራል፣ ነፍሳችንን ያድሳል፤ ይለውጠናልም፡፡ በውስጡ የተቀመጡትን ሕግጋት በራሳችን ኃይልና ጥረት ልንፈፅማቸው እንደምንችል መቁጠር አይኖርብንም፡፡ በእግዚአብሔር ቃል ሐሳብ ለመኖር መጀመርያ ቃሉ በውስጣችን በሚፈጥረው እምነት በክርስቶስ ኢየሱስ አዳኝነት በማመን አዲስ ፍጥረት መሆን ያስፈልገናል፤ ከዚያም ኃይል የሚሰጠውን የክርስቶስን መንፈስ መቀበል ያስፈልገናል፡፡
የእግዚአብሔርን ቃል አንብበን የምንረዳው ሰዎች ባወጡት ቀመር መሠረት ባይሆንም ነገር ግን ሊታወቁ የሚገባቸው መርሆች አሉ፡፡ በማስከተል እነዚህን መርሆች እንዳስሳለን፡፡
የልብ ዝግጅት
አንዳድ ሰዎች በተደጋጋሚ የሚናገሩት የተለመደ ነገር ቢኖር መጽሐፍ ቅዱስን በማንበባቸው ሳብያ ትክክል አለመሆኑን እንደተገነዘቡና በቀደመው ሃይማኖታቸው እንዲፀኑ እንደረዳቸው ነው፡፡ እነዚህ ወገኖቻችን ያልተገነዘቡት አንድ እውነት ቢኖር የእግዚአብሔር ቃል ተልዕኮ ሁለት ገጽታ ያለው መሆኑን ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እውነትን ለሚጠሙ ሰዎች የሕይወት ቃል ሲሆን በእውነት ላይ ለሚያምጹ ሰዎች ደግሞ የፍርድ ቃል ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ሰዎችን ወደ እምነት ያመጣል አለዚያም ደግሞ ልባቸውን በማደንደን ይገፈትራቸዋል፡፡ ሁለቱም ውጤቶች ግን ከሰዎቹ የልብ ዝግጅት አንጻር የሚከወኑ ናቸው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ሕይወት አልባ ንግግር ሳይሆን የሚሠራ ነው፡-
“የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፥ የሚሠራም፥ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፥ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፥ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል” ዕብራውያን 4፡12
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተናገረው በመጨረሻው ቀን በኛ ላይ የሚፈርደው ቃሉ ነው፡-
“ዓለምን ላድን እንጂ በዓለም ልፈርድ አልመጣሁምና ቃሌን ሰምቶ የማይጠብቀው ቢኖር የምፈርድበት እኔ አይደለሁም። የሚጥለኝ ቃሌንም የማይቀበለው እርሱ የሚፈርድበት አለው፤ እኔ የተናገርሁት ቃል እርሱ በመጨረሻው ቀን ይፈርድበታል።” ዮሐንስ 12፡47-48
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በ2ኛቆሮንቶስ መልዕክቱ ላይ የሚከተለውን ይናገራል፡-
“በሚድኑቱና በሚጠፉቱ ዘንድ ለእግዚአብሔር የክርስቶስ መዓዛ ነንና፤ ለእነዚህ ለሞት የሚሆን የሞት ሽታ ለእነዚያም ለሕይወት የሚሆን የሕይወት ሽታ ነን። ለዚህም ነገር የሚበቃ ማን ነው?” 2ቆሮንቶስ 2፡15-16
ሐዋርያው እያለ ያለው ነገር ቢኖር ወንጌል ዝም ብለን የምንቀበለው ወይንም ደግሞ የምንጥለው ነገር ሳይሆን ብንቀበለው ወይንም ደግሞ ባንቀበለው በሕይወታችን ላይ ተፅዕኖ ማምጣቱ ግድ መሆኑን ነው፡፡ ስለዚህ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል ሲንቁ፣ መዘባበቻ ሲያደርጉና ሲያምጹበት የተሸነፉት እነርሱ እንጂ ቃሉ አይደለም፡፡ በዚህም ሆነ በዚያ የእግዚአብሔር ቃል አሸናፊ ነው፡፡ ለተቀበሉት የዘላለምን ሕይወት ሲሰጥ ባልተቀበሉት ላይ ግን ይፈርዳል፡፡ የወንጌል መልዕክት እውነትን ለማወቅ ለሚፈልጉ ሰዎች የሕይወት ዜና ነው፤ ለዘባቾች ግን የሞት ዜና ነው፡፡ ውድ አንባቢያን እናንተ የእግዚአብሔርን ቃል እውነትን በሚፈልግ ልብ ከሚያነቡት ወገን ናችሁ ወይንስ ከቃሉ ውስጥ “ስህተቶችን” ነቅሰው ለማውጣት ከሚያነቡት ሰዎች ወገን ናችሁ? ቀና በሆነ ልብ ቃሉን በማንበብ የዘላለምን ሕይወት ታገኙ ዘንድ ምኞታችንና ጸሎታችን ነው፡፡
ሥነ ፍታቴ (Hermeneutics)
የሥነ ፍታቴ ጥቅም መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈበት ዘመን ለመጀመርያዎቹ ተቀባዮች የነበረውን ትርጉምና ዛሬም ደግሞ ለኛ ምን ማለት እንደሆነ እንድንረዳ ማገዝ ነው፡፡ በዘመናት መካከል ሰዎች ይህንን ቃል ብዙ ክፉ ሥራዎቻቸውን ለማጽደቅ ጠቅሰውታል፡፡ በዚህ ዘመንም ብዙ ሰዎች በመልካምም ሆነ በእኩይ ፍላጎት በመነሳሳት መጽሐፍ ቅዱስ ያላለውን ነገር ሲያስብሉት እናያለን፡፡ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኙ ብዙ ሰባኪያን ትግላቸው በአንድ ጥቅስ ውስጥ ያለን ልዩ ትርጉም ማግኘት ይመስላል፡፡ የስህተት አስተማሪዎችና ከክርስትና ውጪ ያሉ የአንዳንድ ሃይማኖቶች ተከታዮችም ደግሞ የራሳቸውን አስተምህሮ ለመደገፍ ወይንም ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ስህተት እንዳለበት ለማሳየት በማለም ጥቅሶችን ይጠመዝዛሉ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስን በምናጠናበት ሰዓት ከመሠረታዊ የሥነ ፍታቴ መርሆች ጋራ የሚጣረስ አተረጓጎም የምንጠቀም ከሆነ ወደ ስህተት እንገባለን፡፡ ስለዚህ ማንኛውም መጽሐፍ ቅዱስን ለግል ሕይወቱም ሆነ ሌሎችን ለማስተማር ማጥናት የሚፈልግ ሰው እነዚህን ጠቃሚ መርሆች ማወቅ ይኖርበታል፡፡
ጎርደን ዲ. ፊ. እና ዳግላስ ስቱዋርት የተባሉ ክርስቲያን ጸሐፍት የሥነ ፍታቴን አስፈላጊነት በተመለከተ የሚከተለውን ብለዋል፡-
ሥነ ፍታቴ አስፈላጊ መሆኑን የሚያሳይ መርህ በመጽሐፍ ቅዱስ ባሕርይ ውስጥ ይገኛል፡፡ ቤተክርስቲያን የመጽሐፍ ቅዱስን ባሕርይ የክርስቶስን ባሕርይ በምትረዳበት ሁኔታ ስትረዳ እንደኖረች ታሪክ ያሳያል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ጊዜ ሰብዓዊም መለኮታዊም ነው፡፡ ፕሮፌሰር ጆርጅ ላድ አንድ ጊዜ እንደተናገሩት፦ “መጽሐፍ ቅዱስ በሰዎች ቃላት በታሪክ ውስጥ የተሰጠ የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡” እንግዲህ ይህ ሁለትዮሽያዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ባሕርይ ነው እንድንተረጉመው የሚያስገድደን፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል በመሆኑ ዘላለማዊ አስፈላጊነት አለው፤ በሁሉም ዕድሜና በሁሉም ባሕሎች ውስጥ ላሉት ለሰው ልጆች በሙሉ ይናገራል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል በመሆኑ ልንሰማውና ልንታዘዘው ይገባናል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ቃሉን በታሪክ ውስጥ በሰው ቋንቋ ለመናገር ስለመረጠ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለ መጽሐፍ ሁሉ ታሪካዊ ውስንነት አለው፡፡ እያንዳንዱ ክፍል መጀመርያ በተጻፈበት ቋንቋ፣ ዘመንና ባሕል የተወሰነ ነው (በአንዳንድ ሁኔታዎች ውስጥ በተጨማሪም በጽሑፍ ከመስፈሩ በፊት በነበረው የአፈታሪክ ትውፊት [የተወሰነ ነው])፡፡ በዘላለማዊ አስፈላጊነቱና በታሪካዊ ውስንነቱ መካከል ያለው “ውጥረት” መተርጎምን አስፈላጊ ያደርገዋል፡፡ (Gordon D. Fee & Douglas Stuart: How to Read the Bible For All Its Worth, Second Edition, Zondervan, Grand Rapids, 1993, Introduction)
ይህ ርዕስ በጣም ሰፊና ጥልቅ ቢሆንም ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስን በግላቸው ለማጥናትና በትክክል ለመረዳት ለሚሹ ወገኖች ጠቃሚ የሆኑ ምክረ ሐሳቦችን ብቻ አጠር አድርገን እናስቀምጣለን፡፡
በሥነ ፍታቴ ውስጥ ሦስቱ መሠረታውያን ነጥቦች፡- ሐቲት፣ መተርጎምና ማዛመድ ናቸው፡፡
ሐቲት (Exegesis)
በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ወቅት የመጀመርያውና በጣም ወሳኙ ነጥብ ሐቲት (exegesis) ነው፡፡ “ኤክሰጂሰስ” የሚለው የእንግሊዘኛ ቃል ከግሪክ የተገኘ ነው፤ ትርጉሙም “ማውጣት” እንደማለት ሲሆን አንድ ቃል ለመጀመርዎቹ ተቀባዮች በራሳቸው ቋንቋና ባሕል ምን ማለት እንደነበር ለማግኘት የሚደረግ ሥርዓትን የጠበቀ ጥናት ነው፡፡ በሐቲት ውስጥ ሁለት መሠረታውያን ነጥቦች አሉ፡፡ የመጀመርያው አውድ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ይዘት ነው፡፡
አውድ
ሁለት ዓይነት አውዶች አሉ፡-
ታሪካዊ አውድ
ይህ መጽሐፉ የተጻፈበትን ጊዜና ባሕል የሚመለከት ሲሆን የጸሐፊውንና የተደራሲያኑን መንፈሳዊ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ኃብታዊ፣ መልክአ ምድራዊ አቀማመጥና ሌሎች ከጽሑፉ ይዘትና ትርጉም ጋር ሊገናኙ የሚችሉ ነጥቦችን ሁሉ ከግምት ውስጥ የማስገባት ሥራ ነው፡፡ የሚከተሉትን ጥያቄዎች በመጠየቅ የአንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ታሪካዊ አውድ ማወቅ እንችላለን፡-
- ጸሐፊው ማነው? (የጸሐፊውን ስም እርግጠኛ በመሆን ማወቅ ቢሳነን እንኳ ከአጻጻፉ በመነሳት ስለ እርሱ መገመት እንችላለን)
- ተደራሲያኑ እነ ማን ናቸው?
- መቼ ተጻፈ?
- የት ተጻፈ?
- የተጻፈበት ምክንያት ምን ነበር?
- በወቅቱ የነበረው የጸሐፊውና የተደራሲያኑ መንፈሳዊ፣ ማሕበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ኃብታዊ፣ መልክአ ምድራዊ አቀማመጥና ሌሎች ስለ እነርሱ ልናውቃቸው የምንችላቸው የመልዕክቱን ይዘት ሊቃኙ የሚችሉ ሁኔታዎች ምን ይመስሉ ነበር?
ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎች ጥያቄዎችን ብንጠይቅ የመጽሐፉን ታረካዊ አውድ በቀላሉ ማወቅ እንችላለን፡፡ እነዚህን ለመሳሰሉ ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘት ያን ያህል የሚቸግር ባይሆንም ነገር ግን ስለ ጉዳዩ የበለጠ እውቀት ባላቸው ሰዎች የተጻፉ ጥሩ ሐተታዎችንና መዝገበ ቃላትን ብንጠቀም ግንዛቤያችን ይበልጥ ሊሰፋ ይችላል፡፡
የምንባብ አውድ
ይህ ቀላል የሆነ፣ ነገር ግን ብዙ ሰዎች ትኩረት ስለማይሰጡት በመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጎም ላይ ትልልቅ ስህተቶችን እንዲሰሩ ምክንያት የሚሆናቸው ነጥብ ነው፡፡ የሥነ ፍታቴ ምሑራን የዚህን መርህ አስፈላጊነት አፅንዖት ሰጥተው ሲናገሩ “ምንባቡ ንጉሥ ነው” ይላሉ፡፡ አንድን ቃል፣ ሐረግ ወይንም ደግሞ ዓረፍተ ነገር በምንባብ አውድ ውስጥ መረዳት ማለት ዙርያ ገባውን በማንበብ በተጻፈበት በዚያ ክፍል መሠረት የሚሰጠውን ትርጉም መረዳት ማለት ነው፡፡ ዛሬ ብዙ ሰዎች፣ በተለይም ደግሞ ሙስሊም ጸሐፍት ይህንን ቀላል መርህ ባይዘነጉ ኖሮ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ “ስህተቶችና” “ግጭቶች” ብዙ በመጻፍ ባልደከሙ ነበር፡፡ በተደጋጋሚ የሚነሳውን አንድ ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል፤ የምንባብ አውዱን ባንጠብቅ መጽሐፍ ቅዱስን “አምላክ የለም” ልናስብለው እንኳ እንችላለን፡፡ መዝሙር 14፡1 “አምላክ የለም” ይላል፡፡ ነገር ግን ሙሉ ጥቅሱ፡- “ሰነፍ በልቡ አምላክ የለም ይላል። በሥራቸው ረከሱ፥ ጐሰቈሉ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም” የሚል ነው፡፡ ብዙ ጊዜ በተለያዩ መጻሕፍት ታትመው የሚወጡ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ “ግጭቶችና” “ስህተቶች” የሚነገሩ አብዘኞቹ ውንጀላዎች ከዚህ የዘለለ ጥልቀት የሌላቸው ናቸው፡፡
የአንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የምንባብ አውድ ለመረዳት የሚከተሉትን ጥያቄዎች ልናነሳ እንችላለን፡-
- ተናጋሪው ማነው?
- ለማነው የተናገረው?
- ጸሐፊው ለምን ይህንን በዚህ ስፍራ አስገባው?
- ከፊት ምን ተባለ?
- ከኋላ ምን ተባለ?
- ይህ ቃል፣ ሐረግ ወይም አረፍተ ነገር በዚህ ስፍራ ላይ የሚሰጠው ትርጉም ምንድነው?
- ዋናው ጭብጥ ምንድነው?
ማንኛውንም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በተጻፈበት አውድ ውስጥ ለመረዳት እነዚህንና መሰል ቀላል ጥያቄዎች ማንሳት ጠቃሚ ነው፡፡
ይዘቱን ማተት
ይዘት ከቃላትና ሐረጎች ትርጉም፣ የሰዋሰው አወቃቀርና በጥንታውያን የእጅ ጽሑፎች ውስጥ የተለያዩ አነባበቦች የሚገኙ ከሆነ ትክክለኛውን ከመምረጥ ጋር ይያያዛል፡፡ እነዚህን ነጥቦች ለማወቅ በዘርፉ ላይ ዕውቀት ባላቸው ሰዎች የተጻፉ የተለያዩ ሐተታዎችንና መዝገበ ቃላትን መጠቀም በጣም አስፈላጊ ነው፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እኛ ከለመድናቸው ትርጉሞች የተለየ ትርጉም ያላቸው ቃላትና ሐረጎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እንደምሳሌ ለማንሳት ያህል የጥንት አይሁዳውያን ማንኛውንም የቀን ክፍል እንደ ሙሉ ቀንና ሌሊት ነው የሚቆጥሩት፡፡ ለምሳሌ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ማለት የግድ 72 ሰዓታት ማለት ላይሆን ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የአማርኛ ቃላት እንኳ ሆነው በትክክል የማንረዳቸው ቃላትና ሐረጎች ያጋጥማሉ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈበት ዘመን የነበሩ የተለያዩ መለኪያዎች፣ የቀን አቆጣጠሮችና የመሳሰሉት እኛ ከምናውቃቸው የተለዩ ስለሆኑ ምን ማለት እንደሆኑ ለማወቅ መዝገበ ቃላትን ወይንም ደግሞ ሐተታዎችን መጠቀም ያስፈልገናል፡፡ ሌላው ስለ ይዘት ሲታሰብ ሊታወቅ የሚገባው ነገር ቢኖር አንዳንድ ጊዜ የዓረፍተ ነገሮች ሰዋሰዋዊ አወቃቀር ዓረፍተ ነገሩ የተለያዩ ሁለት ትርጉሞች እንዲኖሩት ሊያደርግ መቻሉ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ሌሎች ትርጉሞችን ማየት ወይንም ደግሞ ሐተታዎችን በመጠቀም በመጀመርያዎቹ ቋንቋዎች ውስጥ ያለውን ትርጉም መፈለግ ጠቃሚ ነው፡፡
መተርጎም
ይህ ርዕስ እጅግ ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ ወደ ውስጥ ጠልቀን በመግባት እያንዳንዱን ነጥብ መተንተን ስለማንችል ጠቅለል ባለ ሁኔታ መሠረታዊውን ሐሳብ ብቻ እናስቀምጣለን፡፡ በመጀመርያው ምዕራፍ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ዓይነት የሥነ ጽሑፍ ዘይቤን ያልተከተለ መሆኑን ገልፀናል፡፡ ለተለያዩ የሥነ ጽሑፍ ዓይነቶች የተለያዩ አተረጓገሞችን አንጠቀማለን፡፡
- የሕግ መጻሕፍት- የብሉይ ኪዳን ሕግጋት በ 3 ይከፈላሉ፡፡ እነርሱም የግብረገብ፣ የሥርዓትና የማሕበረሰብ ሕግጋት ናቸው፡፡ የግብረገብ ሕግጋት የማይለወጠውን የእግዚአብሔርን ባሕርይ የሚገልጹ ስለሆኑ ሊለወጡ ወይንም ደግሞ ሊሻሻሉ የሚችሉ አይደሉም፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሕግጋት በየትኛውም ዘመን ሊጠበቁ ይገባል፡፡ ለምሳሌ አትግደል፣ አትስረቅ፣ አታመንዝር ወዘተ. የሚሉት እነዚህ ሕግጋት የግብረገብ ሕግጋት ስለሆኑ ዓለም አቀፋዊ ናቸው፡፡ የሥርዓት ሕግጋትና የማሕበረሰብ ሕግጋት ግን ለእስራኤላውያን ብቻ የተሰጡ ናቸው፡፡ የሥርዓት ሕግጋት ስለ መቅደሱ የአምልኮ ሥርዓቶች፣ ስለሚበሉና የማይበሉ እንስሳት፣ ስለ መንጻት ሥርአቶች፣ ወዘተ. የሚናገሩ ናቸው፡፡ አይሁዳውያን ያልሆኑ ሕዝቦች እነዚህን ሕግጋት የመጠበቅ ግዴታ የለባቸውም፡፡ የማሕበረሰብ ሕግጋት ደግሞ የጋብቻ ሥርዓቶች፣ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግጋት፣ የካሳ አከፋፈል፣ የንብረት ክፍፍል፣ ወዘተ. ናቸው፡፡ እነዚህ ሕግጋት ሊሠሩ የሚችሉት መለኮታዊ አስተዳደር (Theocracy) ባለበት ቦታ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ የሕግ መጻሕፍትን ስናጠና እነዚህን ሦስቱን በመለየትና የትኞቹ ለእስራኤላውያን ብቻ እንደተሰጡና የትኞቹ ደግሞ ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዳላቸው በመረዳት መሆን አለበት፡፡
ሌላው እዚህ ጋር ሊታወስ የሚገባው ነጥብ ቢኖር አብዛኞቹ የመቅደሱ የአምልኮ ሥርዓቶች ክርስቶስ ኢየሱስን የሚያሳዩ መሆናቸው ነው፡፡ ስለዚህ የትኞቹ በክርስቶስ ሕይወት እንደተፈጸሙ መመልከት ያስፈልገናል፡፡ ይህንን በሚገባ ለመረዳት የዕባራውያንን መጽሐፍ ማንበብ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡
- ትረካዎች – መጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ታሪኮች የተሞላ መጽሐፍ ነው፡፡ አንድ ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተጻፈ ብቻ እንደ እግዚአብሔር ሐሳብ የተፈጸመ ትክክለኛ ድርጊት ነው ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን የተጻፈው እያንዳንዱ ታሪክ ለትምህርታችን ተጽፏል፡፡ የብሉይ ኪዳን ታሪኮች እግዚአብሔር በፍጥረቱ ውስጥ እንዴት እንደሠራና ሰዎች ደግሞ ለእርሱ የሰጡትን ምላሽ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ እነዚህን ታሪኮች ባሉበት ሁኔታ ከመረዳት ይልቅ ስውር ትርጉሞችን በመፈለግ ልንተነትናቸው አይገባም፡፡ በአጠቃላይ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ትረካዎችን ስናጠና የሚከተሉትን ነጥቦች ማስታወስ ያሻናል፡-
- ትረካዎች እውነተኛ ታሪኮችን የሚናገሩ ናቸው ነገር ግን የእያንዳንዱን ክንውን ዝርዝር ሁኔታ የመናገር ዓላማ ላይኖራቸው ይችላል፡፡
- ትረካዎች መጽሐፍ ቅዱስ በሌሎች ስፍራዎች ላይ የሚያስተምራቸውን እውነታዎች የሚያብራሩ ናቸው፡፡
- ትረካዎች ብዙ ጊዜ የሚዘግቡት የተፈፀመውን እንጂ ሊፈፀም የሚገባውን ላይሆን ይችላል፡፡
- ትረካዎች ልንከተላቸው የሚገቡ በጎ ምሳሌዎችን ወይንም ደግሞ ልንርቃቸው የሚገቡት መጥፎ ምሳሌዎችን ሊይዙ ይችላሉ፡፡
- የሁሉም ትረካዎች ዋና ባለታሪክ እግዚአብሔር መሆኑ ሊታወቅ የሚገባው መርህ ነው፡፡
- መዝሙራት– በቅኔ ውስጥ የሚመደቡ ሲሆኑ በተለያዩ ዘመናት የእግዚአብሔር ሰዎች የዘመሯቸውን መዝሙራትና የጸለዩዋቸውን ጸሎቶች ያጠቃልላሉ፡፡ እነዚህም በመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ የተሰበሰቡ ሲሆኑ አብዛኞቹ በዳዊት የተጻፉ ናቸው፡፡ ብዙ ጊዜ መዝሙራት ትዕምርታዊ ንግግሮችን ስለሚጠቀሙ እያንዳንዱን ነገር በቀጥታ መተርጎም ትክክል አይደለም፡፡ ለምሳሌ ለእግዚአብሔር የተሰጡ ሰዋዊ ባሕርያትን በቀጥታ በመውሰድ እግዚአብሔርን በዚያ ሁኔታ መሳል ስህተት ነው፡፡ እነዚህ መዝሙራት ከሰው ወደ እግዚአብሔር የቀረቡ ምስጋናዎችና ጸሎቶች እንደመሆናቸው መጠን ዘማርያኑ የግል ስሜቶቻቸውን፣ ቁጣቸውን ወይንም ደግሞ ኀዘናቸውን የሚገልጹባቸውን ክፍሎች በመውሰድ ተግባራዊ ልናደርጋቸው እንደሚገቡ ነገሮች መቁጠርም እንደዚሁ ስህተት ነው፡፡ ሌላው ዘማርያኑ ስለ ተፈጥሮ፣ ስለ ዓለም፣ ባጠቃላይ ስለ አፅናፈ ዓለም ባላቸው መረዳት መጠን መናገራቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ሳይንሳዊ ስህተቶች እንደሆኑ ማሰብ ተገቢ አይደለም፡፡
- የጥበብ መጻሕፍት- መጽሐፈ ኢዮብ፣ መጽሐፈ ምሳሌ፣ መጽሐፈ መክብብና መኃልየ መኃልይ ሲሆኑ በቅኔ መጻሕፍት ውስጥ ይመደባሉ፡፡ እነዚህን መጻሕፍት ሙሉ በሙሉ ካላነበብን ብዙ ጊዜ በተሳሳተ መንገድ ልንተረጉማቸው እንችላለን፡፡ ለምሳሌ መጽሐፈ መክብብን ከምዕራፍ 11፡9 በፊት የሚገኘውን ብቻ በማንበብ ብንተው ትክክለኛ ነጥቡን ሳናገኝ እንቀራለን፡፡ እነዚህ መጻሕፍት በአብዛኛው ምሳሌያዊ ንግግሮችን፣ ምፀቶችን፣ ቅኔያዊ አገላለፆችን ወዘተ. ይጠቀማሉ፡፡ እነዚህን የንግግር ዓይነቶች መረዳትና መተርጎም ያለብን እንደየባሕርያቸው ነው፡፡ ሌላው የቅኔ መጻሕፍትን ስንተረጉም ልንረዳው የሚገባን ነገር ቢኖር የየዕለት ተግባራዊ የሕይወት መመርያን ከማስተላለፍ በዘለለ ጠንካራ የሥነ መለኮት አስተምህሮዎችን በቀጥታ የማስተላለፍ ሁኔታቸው አነስተኛ መሆኑን ነው፡፡ እንደ ተጨማሪ ድጋፍ ከመጠቀም ያለፈ መሠረታዊ አስተምህሮዎችን በቅኔ መጻሕፍት ውስጥ በሚገኙ ጥቅሶች ላይ ብቻ ሙሉ በሙሉ መመሥረት አይገባንም የሚል አጠቃላይ ግንዛቤ በመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን ዘንድ አለ፡፡
- ትንቢቶች- የትንቢት መጻሕፍት ስለወደፊቱ ሁኔታዎች የሚናገሩ ናቸው፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትን በምንተረጉበት ሰዓት ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ ልናደርግባቸው ከሚገቡ ክፍሎች መካከል ትንቢቶች የመጀመርያዎቹ ናቸው፡፡ የሚከተሉት ጥያቄዎች የትንቢት መጽሐፍትን ለመረዳት ያግዛሉ፡-
- የቋንቋ አጠቃቀሙ ምን ዓይነት ነው? (ትዕምርታዊ፣ ቅኔያዊ፣ ራዕያዊ፣ አቡቀለምሲሳዊ፥ ወዘተ.)
- የምንባብ አውዱ ምንድነው?
- የትንቢቱና የተናጋሪው ታሪካዊ ዳራ ምንድነው?
- የተሰጠው ተስፋ አኳኋናዊ (conditional) ነው ወይንስ ኢ-አኳኋናዊ (unconditional)?
- የተነገረው ትንቢት የተፈፀመ፣ እየተፈፀመ ያለ ወይንስ ወደፊት የሚፈፀም?
- ምሳሌዎች- ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርቶቹን ብዙ ጊዜ በምሳሌዎች ያስተምር ነበር፡፡ እነዚህ ምሳሌዎች ትምህርቶቹን ይበልጥ ያብራራሉ ወይንም ደግሞ ከሰዎች አዕምሮ እንዳይጠፉ ያደርጋሉ፡፡ እነዚህን ምሳሌዎች በምናነብበት ሰዓት ከእነርሱ በፊት ወይንም በኋላ የተነገሩትን ነገሮች ልብ ብሎ ማንበብ አስፈላጊ ነው፡፡ የምሳሌ እያንዳንዱ ነጥብ ትርጉም ባለው መልኩ ከፍቺው ጋር ላይገናኝ ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግም ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ያህል ስለ ወይን እርሻ ገበሬዎች በተሰጠው ምሳሌ ውስጥ ከተዘረዘሩ የወይኑ ጌታ ባህርያት መካከል ከእግዚአብሔር ባሕርት ጋር የማይገጥሙ አሉ (ማቴዎስ 21፡33-43)፡፡ ምሳሌዎች ደግሞ በክፍሉ ላይ ከተጠቀሰው ፍቺ ውጪ ሌላ የተደበቀ ትርጉም ይኖራቸዋል ብሎ ማሰብ ስህተት ነው፤ ስለዚህ በወቅቱ ምሳሌው የተነገረበትን ትክክለኛ ነጥብ ካገኘን ዘንዳ ሌላ አላስፈላጊ ሐተታ ውስጥ መግባት አያሻንም፡፡
- መልዕክቶች- መልዕክቶች እንደስማቸው ከሰዎች ወደ ሌሎች የተላኩ ደብዳቤዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ደብዳቤዎች ተራ ደብዳቤዎች ሳይሆኑ ቅዱሳን ሐዋርያት በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው የጻፏቸው ናቸው፡፡ የእነዚህን መልዕክቶች አጻጻፍ በምናይበት ጊዜ በአብዛኛው ተመሳሳይ የሆነ ቅርፅ እንዳላቸው እናስተውላለን፡፡ እነዚህም፡-
- ጸሐፊው
- የተቀባዩ ስም
- ሰላምታ
- ጸሎት፣ መልካም ምኞት ወይንም ምስጋና
- የመልዕክቱ ዋና አካል
- የመጨረሻ የስንብት ሰላምታ ናቸው፡፡
መልዕክቶችን በምነተረጉምበት ሰዓት ታሪካዊና ምንባባዊ አውዳቸውን ተከትለን የማጥናት መርህ እንደተጠበቀ ሆኖ በተጨማሪም መልዕክቶች እንደመሆናቸው ሳናቆራርጥ የንባብ ሂደቱን መጨረስ ይገባናል፡፡
ማዛመድ
ዕብራውያን 4፡2 ላይ የእግዚአብሔር ቃል ሲናገር “ዳሩ ግን የሰሙት ቃል ከሰሚዎቹ ጋር በእምነት ስላልተዋሐደ አልጠቀማቸውም” ይላል፡፡ ያጠናነው ቃል ከሕይወታችን ጋር ካልተዛመደ ከላይ የተጠቀሱትን ሁለቱን መንገዶች ተጠቅመን መጽሐፍ ቅዱስን ብንመረምር ለአዕምሯችን ዕውቀትን ከማግኘት ያለፈ ለመንፈሳችን የሚሆን በረከት ልናገኝ አንችልም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ከብዙ ዘመናት በፊት ለነበሩ ሰዎች የተሰጠ ቃል ነው፤ ነገርግን በሐቲትና በመተርጎም በእኛና በእነርሱ መካከል የሚገኙትን የማንነት፣ የቋንቋ፣ የባሕል፣ የታሪክ፣ የቦታ፣ የአጻጻፍ፣ የዘመን፣ ወዘተ. ልዩነቶችን አስወግደን በየትኛውም ዘመንና በሁሉም ቦታ ሊሠራ የሚችል ለሁሉም ሕዝቦች ጠቃሚ የሆነን መልዕክት እናገኛለን፡፡ ማዘመድ ማለት በአጭር ቋንቋ ያጠናነው ቃል አሁን ስላለንበት ሁኔታ ወይንም ደግሞ ስለ ሕይወታችን ምን እንደሚልና ቃሉን ተግባራዊ ማድርግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ በማወቅ በቃሉ መሠረት መኖር ማለት ነው፡፡ ዕለት ዕለት ይህንን ማድረግ ከቻልን የእግዚአብሔርን ኃይልና አብሮነት በሕይወታችን ውስጥ እንለማመዳለን፡፡
ይህንን ጽሑፍ ስንደመድም አፅንዖት ሰጥተን ልንናገረው የምንፈልገው የመጨረሻው ነጥብ ቢኖር መጽሐፍ ቅዱስን ስናጠና የመንፈስ ቅዱስን ድርሻ ልንዘነጋ እንደማይገባን ነው፡፡ እርሱ ከማንኛውም መዝገበ ቃላት፣ ሐተታ ወይንም ደግሞ አስተማሪ ይልቅ ሊያስተምረን የሚችል ሕልውናው እውን የሆነ መምህር ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ እንደሚመራን ነግሮናል (ዮሐንስ 16፡13)፡፡ ጴጥሮስና ሌሎቹ ሐዋርያት ቅዱሳት መጻሕፍትን ያልተማሩ ሰዎች ቢሆኑም እንኳ መንፈስ ቅዱስ እራሱ ስላስተማራቸው ስለ ቅዱሳት መጻሕፍት የነበራቸው ጥልቅ ዕውቀት በወቅቱ የነበሩትን የአይሁድ መምህራን ሳይቀር አስገርሞ ነበር (የሐዋርያት ሥራ 3፡13)፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳችንን ስናነብ እኔና እናንተንም መንፈስ ቅዱስ እንዲያስተምረን በጸሎት ልንጠይቀው ይገባል፡፡
“አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል።” (ዮሐንስ 14፡26)