መጽሐፍ ቅዱስ ተዓማኒ ቃለ እግዚአብሔር ነውን? መግቢያ

መግቢያ

“ከአንድ ክፍለ ዘመን በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ ከምድረ ገፅ ይጠፋል፡፡” ቮልቴር የተሰኘ ስመ ጥር የፈረንሳይ ፈላስፋ የዛሬ 250 ዓመታት ገደማ የተናገረው ነበር፡፡ ቮልቴር ይህንን የተናገረው የሰው ልጅ በዕውቀት እየመጠቀ በሄደ ቁጥር የመጽሐፍ ቅዱስ ተፈላጊነት ያሽቆለቁላል ከሚል የተሳሳተ ግምት በመነሳት ነበር፡፡ ቮልቴር አልፏል ነገር ግን ከእርሱ ግምት በተፃራሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ተፈላጊነትና ስርጭት ከመቸውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ እየጨመረ ሄደ እንጂ ሲቀንስ አልታየም፡፡ ከእርሱ ህልፈት በኋላ ማተምያና መኖርያ ቤቶቹን የጄኔቫ መጽሐፍ ቅዱስ ማሕበር በመግዛት የመጽሐፍ ቅዱስ መጋዘን ማድረጉ ብዙዎችን ያስደመመ ክስተት ሆኗል፡፡ በዚህ አላበቃም፡፡ ታህሳስ 24/ 1933 ዓ.ም. ዝነኛውን የኮዴክስ ሲናይቲከስ የመጽሐፍ ቅዱስ የእጅ ጽሑፍ የእንግሊዝ መንግሥት ከራሽያ መንግሥት  በግማሽ ሚሊዮን ዶላር የገዛ ሲሆን በዚያኑ ዕለት በፓሪስ በሚገኝ የመጽሐፍት መሸጫ መደብር ውስጥ የቮልቴር መጽሐፍ የመጀመርያው እትም በአስራ አንድ ሳንቲሞች ብቻ ተሽጧል፡፡

ዲዮክሌሽያን የተባለ የሮም ንጉሥ ክርስቲያኖችን ክፉኛ ካሳደዱ የሮም ነገሥታት መካከል በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡ ይህ ክፉ ንጉሥ መጽሐፍ ቅዱስን ከምድረ ገፅ ለማጥፋት ቆርጦ በመነሳት እጅግ ብዙ ኮፒዎችን አቃጥሎ ነበር፡፡ ክርስትና የጠፋ እስኪመስል ድረስ ብዙ ክርስቲያኖችንም ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ገድሎ ነበር፡፡ በመጨረሻም “ለድሉ” መታሰብያ በተቃጠሉ መጽሐፍ ቅዱሶች ላይ ሐውልት በማቆም “ክርስቲያን የሚባል ስም ሙሉ በሙሉ ጠፍቷል” የሚል ጽሑፍ አስጻፈበት፡፡ ይህ ከሆነ ከሃያ ዓመታት በኋላ ቆስጠንጢኖስ የተሰኘ ክርስቲያኖችን የሚወድ ንጉሥ በሮም ነገሠ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስንም ይዞ ለሚመጣ ሰው ከፍተኛ ሽልማት እንዳዘጋጀ አወጀ፡፡ በሃያ አራት ሰዓታት ውስጥ ከሃምሳ ያላነሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ኮፒዎች ከየተደበቁበት በመውጣት ንጉሡ ዘንድ ደረሱ፡፡ ክርስቲያኖችም በተሰደዱበትና በግፍ በተጨፈጨፉበት ምድር መንግሥታዊ ጥበቃ እየተደረገላቸው በነፃነት ይህንን የሕይወት መጽሐፍ ማባዛትና ማሰራጨት ቻሉ፡፡

በሰው ልጆች ታሪክ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ የተሰደደና ብዙ  ሂሶችን ያስተናገደ መጽሐፍ የለም ብንል ማጋነን አይሆንም፡፡ ተቃዋሚዎች ይህንን መጽሐፍ ዋጋ ለማሳጣት  ያልፈነቀሉት ድንጋይ ያልቧጠጡት ተራራ የለም፡፡ ተኣማኒነቱን ለመሸርሸር ለቁጥር የሚያታክቱ መጽሐፍት ተጽፈዋል፡፡ ባጠቃላይ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥፋት የቃሉን አገልጋዮች ከማሳደድና ጽሑፎቹን ሰብስቦ ከማቃጠል ጀምሮ ምሑራዊ የጥናት መንገዶችን ተጠቅሞ ሂስ እስከ መሰንዘር ድረስ ያሉት ሁሉም ዓይነት መንገዶች ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡ ዛሬ ግን በቀዳሚያን የእጅ ጽሑፎች ብዛትና ወደ ብዙ ቋንቋዎች በመተርጎም እንዲሁም በህትመትና በስርጭት ከዚህ ታላቅ መጽሐፍ ጋር ሊወዳደር የሚችል ኃይማኖታዊም ሆነ ዓለማዊ መጽሐፍ የለም፡፡ የቅርብ ጊዜ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከ 25,000 በላይ የአዲስ ኪዳን ጥንታውያን የእጅ ጽሐፎች በተለያዩ ቤተ መዘክሮች ውስጥ የሚገኙ ሲሆን ወደ ገፅ ብንቀይራቸው ወደ 1.3 ሚሊዮን ገፆች ይኖሩናል! ይህንን ቁጥር 643 የእጅ ጽሑፎች ብቻ ካሉት በእጅ ጽሑፎች ብዛት ከመጽሐፍ ቅዱስ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው ኢልያድ ከተሰኘው የሆሜር ሥራ ጋር ብናነፃፅር ምን ያህል የገዘፈ እንደሆነ ምስሉ ይከሰትልናል፡፡

ጊነስ ወርልድ ርኮርድስ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን በድረ ገፁ ላይ አስፍሯል፡ “ትክክለኛውን ቁጥር ለማግኘት አዳጋች ቢሆንም ነገር ግን በሽያጭ ደረጃና በስርጭት መጽሐፍ ቅዱስ የዓለም ቁጥር አንድ መጽሐፍ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ማሕበር የተደረገ ዳሰሳዊ ጥናት እንደሚያመለክተው በ 1815 እና በ 1975 ዓ.ም. መካከል 2.5 ቢሊዮን የሚሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ኮፒዎች የታተሙ ሲሆን የቅርብ ጊዜ ግምቶች ቁጥሩን ከ 5 ቢሊዮን በላይ ያደርጉታል…. መላው መጽሐፍ ቅዱስ ወደ 349 ቋንቋዎች የተተረጎመ ሲሆን 2,123 የሚሆኑ ቋንቋዎች ደግሞ ቢያንስ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ አላቸው፡፡”[1]

መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች እንደሚሉት የእግዚአብሔር ቃል ነውን? ይህንንስ የሚደግፉ ማስረጃዎች አሉን? መጽሐፉ እንደተበረዘ፣ በተቃርኖዎች፣ በታሪካዊ ስህተቶችና በሳይንሳዊ ስህተቶች እንደተሞላ ለሚናገሩ ተቃውሞዎችስ ክርስቲያኖች የሚሰጡት ምላሽ ምንድነው? መልእክቱን በትክክል ለመረዳት የተሻለው የንባብ መንገድ የቱ ነው? ለሚሉትና ለሌሎች ብዙ ጥያቄዎች በማስረጃ የተደገፉ ዝርዝር መልሶችን በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ታገኛላችሁ፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ ክርስቲያኖች የቆሙበት መሠረት ምን ያህል ተኣማኒና የፀና እንደሆነ እንዲያውቁ ማስቻል ሲሆን ለሚጠየቋቸው  ጥያቄዎችም ተገቢውን ምላሽ መስጠት እንዲችሉ ይረዳቸዋል፡፡ ክርስቲያን ያልሆኑ  ወገኖች ደግሞ ያሉትን ማስረጃዎች በማጤን መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር  ቃል መሆኑን ወደማወቅ እንዲመጡ እንደሚያግዝና የሚሰነዘሩ የተለመዱ ክሶችም መሠረተ ቢስ መሆናቸውን እንዲያውቁ ዐቃቤ እምነታዊ ሚና እንደሚጫወት ይታመናል፡፡ በእቅብተ እምነት የአገልግሎት መስክ ላይ ለተሰማሩ ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶችም  ደግሞ ለበለጠ ጥናት አቅጣጫ ጠቋሚ ጠቃሚ የመረጃ ምንጭ እንደሚሆን ተስፋ አለ፡፡ መጽሐፉን ለሁሉም ዓይነት አንባቢያን ተስማሚ ለማድረግ ቀለል ካለውና መሠረታዊ ከሆነው ጀምሮ ጠጠር እስካለው ድረስ ያሉትን መረጃዎችና ፅንሰ ሐሳቦች አካተናል፡፡

ውድ አንባቢያን፡ “መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ነውን?” ለሚለው ጥያቄ ያላችሁ ምላሽ ምን ይሆን? ለዚህ ጥያቄ የምትሰጡት ምላሽ  የዘላለም  መኖርያችሁን የሚወስን የመጀመርያው ነጥብ መሆኑን አትጠራጠሩ፡፡ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ያምናሉ፡፡ ይህ እምነት ደግሞ ጭፍን እምነት እንዳልሆነና በፀና መሠረት ላይ የቆመ እምነት መሆኑን ይህንን ጽሑፍ ወደ ውስጥ ዘልቃችሁ ባነበባችሁ ቁጥር ልታረጋግጡ የምትችሉት እውነታ ነው፡፡ እውነትን ለመቀበል በተዘጋጀ ልብና ከችኮላ በፀዳ እንዲሁም ሚዛናዊ ፍርድ ለመስጠት በተዘጋጀ በጎ ህሊና ታነቡት ዘንድ ተጋብዛችኋል፡፡ ጥያቄ ወይንም አስተያየት ካላችሁ በተጠቀሰው አድራሻ ብትልኩልን በደስታ እንቀበላለን፡፡ መልካም ንባብ፡፡

[1] http://www.guinnessworldrecords.com/world-records/best-selling-book-of-non-fiction/

መጽሐፍ ቅዱስ ተዓማኒ ቃለ እግዚአብሔር ነውን? ዋናው ማውጫ