እስላማዊ አጣብቂኝ
መጽሐፍ ቅዱስ ከተበረዘ ቁርኣን ዋሽቷል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ካልተበረዘ ቁርኣን የፈጣሪ መጽሐፍ አይደለም!
ሙስሊም ወገኖቻችን በመጽሐፍ ቅዱስ ተዓማኒነት ላይ የሚያነሱት ቀዳሚና የተለመደ ተቃውሞ “መጽሐፍ ቅዱስ ተበርዟል” የሚል መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ይህ አመለካከት ከቁርአን አስተምህሮና ከቀደሙት ሙስሊሞች እምነት ጋር የማይስማማ ቢሆንም የዘመናችን አብዛኞቹ ሙስሊሞች “ስለ ነቢዩ መሐመድ የተተነበዩትን ትንቢቶች ለማስወገድና ለማድበስበስ አይሁድና ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስን በርዘውታል” የሚል አቋም አላቸው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚነሱት “ግጭቶች” እና “ሳይንሳዊ ስህተቶችን” የመሳሰሉት መሠረተ ቢስ ውንጀላዎች የዚህኛው ውንጀላ ንዑሳን ክፍሎች ናቸው፡፡ ዓላማቸውም መጽሐፍ ቅዱስ “መበረዙን” ማረጋገጥ ነው፡፡ ሙስሊም ወገኖቻችን ይህንን ተቃውሞ የሚያቀርቡበት ዋናው ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መበረዙ ሁነኛ ማስረጃ ኖሯቸው ሳይሆን “ቁርአን ትክክል ነው” ከሚል አቋም በመነሳት ነው፡፡ ነገር ግን ቁርአንም ሆነ የትኛውም ሃይማኖታዊ መጽሐፍ ትክክል መሆኑን ከመደምደማችንና ሌሎች ሰዎችም እንዲቀበሉት ከመጋበዛችን በፊት ትክክል መሆኑን በማስረጃ ማረጋገጥ ግድ ይለናል፡፡ ይህ እስካልሆነ ድረስ እምነታችንን ጭፍን ከመሆን የሚታደገው ምንም ነገር አይኖርም፡፡
እንደሚታወቀው ቁርአን የመጣው መጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ ከተጠናቀቀ ከስድት መቶ ዓመታት በኋላ ነበር፡፡ መቼም ቢሆን የኋለኛው መገለጥ ትክክለኛነት በፊተኛው መገለጥ ተለክቶ ይታወቃል እንጂ የፊተኛው መገለጥ በኋለኛው አይለካም፡፡ የኋለኛው መገለጥ ከፊተኛው ጋር ተመሳሳይ ከሆነ ምንጭ እንደመጣ ከተናገረ በኋላ ከፊተኛው ጋር ቢጣረስ የተሳሳተው የኋለኛው እንጂ የፊተኛው ሊሆን አይችልም፡፡ ይህ ቀላል አመክንዮ ለአንዳንድ ሰዎች ለምን ሊገባቸው እንደማይችል በእውነቱ ይደንቃል!
ሲ.ጂ. ፋንደር የተሰኙ ክርስቲያን ሊቅ ከአንድ መቶ ዓመታት በፊት “ሚዛኑል ሐቅ” (የእውነት ሚዛን) በሚል ርዕስ በጻፉት መጽሐፋቸው ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ እንደተበረዘ ለሚያምኑ ወገኖች የማያዳግም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ጸሐፊው “ይህ ከእኩለ ቀን ፀሐይ ይልቅ ግልፅ ቢሆንም ነገር ግን ክርስቲያኖችና አይሁድ ቅዱሳት መጻሕፍታቸውን በመበረዝ ምን ጥቅም እናገኛለን ብለው ሊያስቡ እንደሚችሉ እንመልከት” በማለት ምላሻቸውን ይጀምራሉ፡፡ ከዚያም እኛ በነጥብ በመከፋፈል ያስቀመጥናቸውን ተከታዮቹን ርቱዕ ሙግቶች ያቀርባሉ፡-
- አይሁድና ክርስቲያኖች ይህንን ነገር ለማድረግ መሞከር በእግዚአብሔር ላይ ኃጢኣት መስራት መሆኑን ያውቃሉ ምክንያቱም ይህ በብሉይ ኪዳንም ሆነ (ዘዳ 4፡2) በአዲስ ኪዳን ውስጥ (ራዕይ 22፡18-19) በግልፅ የተቀመጠ ነውና፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ሃይማኖታቸውን በማጥፋት ራሳቸውን፣ ልጆቻቸውንና የልጅ ልጆቻቸው ለዘለዓለም ከሕይወት መንገድ እንደሚያሳስቱ ያውቃሉ፡፡ ይህንን በሚያውቁበት ሁኔታ እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ሊወስኑ ይችላሉ ብሎ ማሰብ የማይመስል ነው፡፡
- ምስራቃውያን አይሁድና ክርስቲያኖች ከነቢዩ መሐመድና ከተከታዮቻቸው ምድራዊ ጥቅማ ጥቅሞችን ማግኘት ቢፈልጉ ኖሮ ሙስሊሞች እንደሚከሷቸው እንዲያ ያሉትን ክፍሎች ከማስወገድ ይልቅ የመሐመድን ንግር የሚደግፉ ጽሑፎችን አስርገው ያስገቡ ነበር፡፡ መሐመድን ባለመቀበላቸው አዋራጅ የሆነውን የዚሚ ሕይወት በመኖር ራሳቸውንና ዘሮቻቸውን “የተዋረዱ ሆነው ግብርን በእጆቻቸው ለመስጠት” (ሱራ 9፡29) ዳርገዋል፡፡ በዚያ ጊዜም ሆነ ከዚያ በኋላ ብዙ መከራና ስቃዮች ደርሰውባቸዋል፡፡ አይሁድና ክርስቲያኖች መሐመድን እንደ እውነተኛ ነብይ ቢቀበሏቸው ኖሮ እነዚህን ሁሉ መከራና ጭቆናዎች ከመከላከልም ባለፈ ሙስሊሞች ያገኟቸውን ምድራዊ ኃብቶች ሁሉ ይጋሩ ነበር፡፡ አይሁድ ወይም ክርስቲያኖች ከመሐመድ ጋር የተያያዘ ምንም ዓይነት ትንቢት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቢያገኙ ኖሮ በደስታ የርሳቸው ደቀ መዛሙርት በመሆን ምድራዊና ሰማያዊ በረከቶችን ይቀበሉ እንደነበር ግንፅ አይደለምን? ስለዚህ ቅዱሳት መጸሕፍቶቻቸውን ለመበረዝ ብዙ አስገዳጅ ምክንያቶች ነበሯቸው፤ ነገር ግን ከመሐመድ ጋር የተያያዙ ምንባቦችን በመቀነስ ሳይሆን በመጨመር፡፡ እንደዚህ ዓይነት ምንባቦች አለመጨመራቸው ቅዱሳት መጻሕፍቶቻቸውን እንዳልበረዙና መበረዝ እንደማይችሉ ማረጋገጫ ነው፡፡
- እነዚህ ሁለቱ ሃይማኖተኛ ማሕበረሰቦች ቅዱሳት መጻሕፍቶቻቸውን ለመበረዝ ቢያሤሩና ጥረት ቢያደርጉ ኖሮ ሌላኛው ወገን ከመቅፅበት ጉዳዩን ደርሶበት የማጭበርበር ሤራውን ያጋልጥ ነበር፡፡ በመሐመድ ዘመን ከርሱ በፊትና በኋላ እንደነበረው ሁሉ በአይሁድና በክርስቲያኖች መካከል ብዙ አለመግባባት ነበር ስለዚህ ብሉይ ኪዳንን ለማስዋሸት በነርሱ መካከል ሥምምነት መኖሩ የማይቻል ነው፡፡ በተለያዩ ብዙ አገራት ውስጥ ይኖሩ የነበሩት አይሁድ አንዳቸው ሌላቸውን ወደሚቃወሙ ቡድኖች ተከፋፍለው ነበር፡፡ ክርስትናም እንዲሁ እርስ በርሳቸው ወደመይቀባበሉ ብዙ ቡድኖች ተከፋፍሎ ነበር። ከአይሁድ ወይንም ከክርስትና ቡድኖች መካከል አንዳቸው ቅዱሳት መጻሕፍትን ለመበረዝ ጥረት ቢያደርጉ ኖሮ ሌሎቹ ቡድኖች ወንጀሉን ያለምንም ማቅማማት ያጋልጡ ነበር፡፡ ክርስቲያኖችና አይሁድ በጋራ ተስማምተው ቅዱሳት መጻሕፍትን በርዘዋል በማለት ሊያሳስብ በሚችል በቂ እብደት የተለከፈ ሰው ሊኖር አይችልም!
- በአይሁድ፣ በክርስቲያኖችና በሙስሊሞች የተጻፉ ጥንታዊ ታሪኮች ቢኖሩንም በአንዳቸውም ውስጥ በመሐመድ ዘመንም ሆነ ከርሳቸው በኋላ እንዲህ ያለ ነገር ለመሞከሩ ፍንጭ እንኳ የለም፡፡
- ከሁሉም በላይ ይህንን ወንጀል ለመፈጸም አንዱ ቡድን አስቦ ቢሆን ኖሮ አፈፃፀሙ ትልቅ ችግር ይገጥመው ነበር፡፡ ምክንያቱም ከሂጅራ በፊት የክርስትና ሃይማኖት እጅግ ከመስፋፋቱ የተነሳ በትንሹ ኢስያ፣ ሦርያ፣ ግሪክ፣ ግብፅ፣ አቢሲንያ፣ ሰሜን አፍሪካና ጣልያን ይኖሩ የነበሩ አብዛኞቹ ሕዝቦች ክርስቲያኖች ነበሩና፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአረብያ፣ ፋርስ፣ አርመን፣ ጆርጅያ፣ ሕንድ፣ ፈረንሳይ፣ እስጳንያ (እስፔን)፣ ፖርቹጋል፣ እንግሊዝና ጀርመን ይኖሩ የነበሩ ብዙ ሕዝቦች ክርስትናን ተቀብለው ነበር፡፡ በነዚህ ሁሉ አካባቢዎች የተለያዩ ቋንቋዎች ነበሩ ይነገሩ የነበሩት፡፡ በመሐመድ ዘመንም ከነዚህ ቋንቋዎች ወደ ብዙዎቹ መጽሐፍ ቅዱስ ተተርጉሞ ነበር፡፡ ለምሳሌ ያህል ላቲን፣ አርመን፣ ሦርያንኛ፣ ቅጵጥ (ኮፕቲክ)፣ ኢትዮጵያንኛ (ግዕዝ)፣ ጎቲክና ጆርጅያንኛ ይገኙበታል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ ብሉይ ኪዳን በኦሪጅናል እብራይስጥ እንዲሁም አዲስ ኪዳን በኦሪጅናል ግሪክ ነበሩ፡፡ ብሉይ ኪዳን ደግሞ ወደ ግሪክና አብዛኞቹ ክፍሎቹ ወደ አረማይክ ተተርጉሞ ነበር፡፡
- ከመሐመድ በፊት እጅግ ቀድመው ከተጻፉት ጥንታውያን የእጅ ጽሑፎች የተነሳ ወንጀሉ ከብዙ ዘመን በፊት ይደረስበት ነበር፡፡ ከመሐመድ ዘመን በፊት የተጻፉት እጅግ ብዙ ጥንታውያን ቅጂዎችና በሌሎች ደራሲያን ጽሑፎች ውስጥ የተጠቀሱት ጥቅሶች መጽሐፍ ቅዱስ በመሐመድ ዘመንና ከርሱ በኋላ ተበርዟል የሚለውን ክስ ሙሉ በሙሉ ውድቅ ያደርጉታል፡፡
- አይሁድ ብዙ መሲሃዊ ትንቢቶችን በብሉይ ኪዳን ውስጥ አግኝተዋል፡፡ እነዚህ በጌታ ኢየሱስ ሕይወት እንደተፈፀሙና ይህም የመሲህነቱ ማረጋገጫ እንደሆነ ክርስቲያኖች ያምናሉ፡፡ እነዚህ መሲሃዊ ትንቢቶች ለአይሁድ ትልቅ ፍርድ ናቸው፡፡ ነገር ግን አይሁድ እነርሱን ከብሉይ ኪዳን ውስጥ የማስወገድ ሙከራ አላደረጉም፡፡ ከክርስቶስ ጋራ የተያያዙትን ትንቢቶች ከብሉይ ኪዳን ውስጥ የማስወገድ ፍላጎት ቢኖራቸው ኖሮ የሚከተሉትንና ሌሎች ብዙ ጥቅሶችን ከቅዱሳት መጻሕፍ ውስጥ የማስወገድ ጥረት ባደረጉ ነበር፡- ዘዳ. 18፡፡15-8፣ መዝ 22፡14-18፣ ኢሳ 7፡14፣ ኢሳ 9፡6-7፣ ኢሳ 11፡1-10፣ ኢሳ 52፡13-መጨረሻ እና 53፣ ዳን 6፡13-14፣ ሚክ 5፡2፣ ዘካ 2፡10፡፡ እነዚህ ሁሉ ጥቅሶች በግልፅ ስለ እርሱ የሚናገሩ ናቸው (ከሉቃስ 24፡25-27 ጋር ያነፃፅሩ)፡፡ ሌላው አይሁድ መጽሐፍ ቅዱስን የመበረዝ ፍላጎት ቢኖራቸው ኖሮ የሚያስወግዷቸው ጥቅሶች ቢኖሩ ስላለፈው ኃጢኣታቸውና ስለሚደርስባቸው ፍርድ የሚናገሩትን ነው፡፡ ዛሬ እንኳ እነዚህ በእብራይስጥ ብሉይ ኪዳን ሁሉም ቅጂዎች ውስጥ ይገኛሉ፡፡ እግዚአብሔር የቶራን ሕግ እንዲጠብቁ (ኢያሱ 1፡7) እና ከርሱ ላይ እንዳይቀንሱ እንዲሁም በርሱ ላይ እንዳይ ጨምሩ (ዘዳ 4፡2፣ 12፡32) አዟቸዋል፡፡ አንድም ቃል ወይንም ፊደል እንኳ እንዳይጠፋ ለመጠንቀቅ ቁጥራቸውን በመጻፍ ብሉይ ኪዳንን በሙሉ እስካሁን ድረስ ጠብቀው በማቆየት ስኬትን አስመዝግበዋል፡፡ ክርስቲያኖችና አይሁድ የሚጠቀሙበት ብሉይ ኪዳን በኦሪጅናል እብራይስጥ አንድ ነው፡፡ እንዲያውም በአንድ ማተምያ የሚታተም ነው፡፡
- ምናልባት አይሁድ ከክርስቶስ ዘመን በፊት ብሉይ ኪዳንን በርዘውት ይሆናል የሚል ጥርጣሬ በአንባብያን ልብ ውስጥ የሚኖር ከሆነ ይህ አለመደረጉ ግልፅና መታወቅ ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ቁርአን ራሱ በትክክል እንዳስቀመጠው ክርስቶስ እነርሱ በዚያን ዘመን የነበሯቸውንና አሁንም ድረስ በእጃቸው የሚገኙትን ቅዱሳት መጻሕፍት አረጋግጧል፡፡
- ክርስቶስም ሆነ የርሱ ደቀ መዛሙርት ትክክለኛዎቹን የአይሁድ ኃጢአቶች ቢቃወሙም ነገር ግን በአንድም የአዲስ ኪዳን ክፍል ውስጥ ቅዱሳት መጻሕፍትን በመበረዝ አልወነጀሏቸውም፡፡ በአንጻሩ ግን በሁሉም ቦታዎች ላይ አዲስ ኪዳን የብሉይ ኪዳንን ትክክለኛነት በማረጋገጥ ሰዎች ያጠኑት ዘንድ በጥብቅ ያሳስባል፡፡ ይህ በሚከተሉት ጥቅሶች ውስጥ በግልፅ ተቀምጧል፡- ማቴ 5፡17-18፣ 22፡31-32፣ ማር 6፡6-10፣ ሉቃ 11፡29-32፣ 24፡25-27፣ ዮሃ 5፡39፣ 45-47፣ ጢሞ 3፡16 ወዘተ.። ስለዚህ በክርስቶስ ዘመን ብሉይ ኪዳን ግልጠተ መለኮት የሆኑ፣ እውነተኛና ያልተበረዙ መጻሕፍትን እንደያዘ ታምኗል ማለት ነው፡፡ በእርግጠኝነት አይሁድ አበላሽተውት ቢሆን ኖሮ ለንደዚህ አይነቱ ትልቅ ክፋት ክርስቶስ ራሱ በግልፅ በገሰፃቸው ነበር፡፡ ያለ ጥርጥር ደግሞ የተበረዙትን እነዚህን ክፍሎች ነቅሶ በማውጣት ለተከታዮቹ ጥቅም ሲል ባስተካከላቸው ነበር፡፡ ይህ ነጥብ በባቢሎን ምርኮ ዘመን በናቡ ከደነፆር ኢየሩሳሌም በወደቀች ጊዜ ቅዱሳት መጻሕፍት እንዳልወደሙ ወይንም ደግሞ እንዳልተበረዙ ለማሳየትም ይረዳል፡፡ ባይሆን ኖሮ ክርስቶስ ራሱ ያንን በነገረን ነበር፡፡
- አንዳንድ ሙስሊም ጸሐፊያን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ግጭቶች እንደሚገኙና ይህም ደግሞ መጽሐፉ ለመበረዙ ማረጋገጫ እንደሆነ ለማሳየት ጥረት አድርገዋል፡፡ ሁለት ወይንም ሦስት ጸሐፊንያን ስለ አንድ ክስተት ራሳቸውን የቻሉ ትረካዎችን በሚጽፉበት ወቅት በአንዱና በሌለኛው ትራኬ መካከል የተወሰነ ልዩነት መታየቱ አስተዋይ የሆኑ ሰዎች ሁሉ የሚስማሙበት እውነታ ነው፡፡ ካልሆነ ግን የሆነ ሤራ መሠራቱ እርግጥ ይሆናል፡፡ ስለጉዳዩ ጠቅላላ መረጃ ለሌለው ሰው እነዚህ ዘገባዎች ምናልባት ከግጭቶች ሊቆጠሩ ይችላሉ ነገር ግን ጉዳዩን በጥልቀት ላጠኑ ሰዎች እንደርሱ አይሆንም፡፡ የንደነዚህ ዓይነቶቹ ልዩነቶች መኖር የቅዱሳት መጻሕፍትን ጽሑፎች ማንም ሰው ላለመበረዙ ትልቅ ማረጋገጫዎች ናቸው፡፡ ባይሆን ኖሮ እነዚህ ልዩነቶች በተወገዱ ነበር። (ለበለጠ መረጃ C.G. Pfander, The Mizanu’l Haqq نازﯾــﻣ قــﺣﻟا (Balance Of Truth) pp. 101-125 ያንብቡ)
በእርግጥ ቁርአን ቶራህ፣ ዘቡርና እንጂል (የሙሴ ሕግ፣ መዝሙረ ዳዊትና ወንጌል) ከእግዚአብሔር የተሰጡ ቅዱሳት መጻሕፍት መሆናቸውንና ሰዎችም ደግሞ ሊቀበሏቸውና ሊታዘዟቸው እንደሚገባቸው ይናገራል፡፡ ለምሳሌ ያህል የሚከተሉትን ጥቅሶች ማየት ይቻላል፡ (ሱራ 5፡44-48, 29:46, 10:37, 46:12, 6:91, 35:31, 2:40-42, 2:89, 3:3, 21:7, 2:285, 3፡93, 4፡47, 5፡68-69, 5፡6, 5፡15 ወዘተ.)፡፡ መሐመድ በእሳቸው ዘመን የነበሩትን ሰዎች ወንጌልን እንዲታዘዙና በእርሱም መሠረት እንዲፈርዱ ሲመክሩ በቁርአን ውስጥ እናነባለን፡-
“የኢንጅልም ባለቤቶች በውስጡ አላህ ባወረደው ሕግ ይፍረዱ፡፡ አላህም ባወረደው የማይፈርድ ሰው እነዚያ አመጸኞች እነርሱ ናቸው” (ሱራ 5፡47)።
በዚያን ዘመን ወንጌል የተበረዘ ቢሆን ኖሮ ስለምን ይህንን ይናገሩ ነበር? ከእሳቸው ዘመን በኋላ ነው የተበረዘው እንዳይባል ደግሞ ከእሳቸው ዘመን በመቶዎች በሚቆጠሩ ዓመታት የሚቀድሙትን አሁን በእጃችን ከሚገኙት ጽሑፎች ጋር በይዘት ፍፁም ተመሳሳይ የሆኑትን ጥንታውያን የአዲስ ኪዳን የእጅ ጽሑፎች ምን ልንላቸው ነው?
ከላይ የተጠቀሱትን የመሳሰሉ መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን የሚናገሩ የቁርአን ጥቅሶችና በሌሎች እስላማዊ ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙ ሐሳቦች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ከሚጣረሱት የቁርአን አስተምህሮዎች አኳያ ሲታዩ በዘመናችን የሚገኙት ሙስሊም ወገኖች በቀላሉ የማይፈቱት አጣብቂኝ ውስጥ እንዲገቡ አድርገዋቸዋል፡፡ የአላህ ቃል እንደማይለወጥና ማንም ደግሞ ሊለውጠው እንደማይችል የሚናገሩት የሚከተሉት የቅዱስ ቁርአን ጥቅሶች ሲታከሉበት ደግሞ አጣብቂኙ ይከፋል፡፡
- “የአላህን ንግግሮች ለዋጭ የለም” 6፡34
- “ለቃላቱ ለዋጭ የለም” 6፡115
- “የአላህ ቃል መለወጥ የላትም” 10፡64
- “ለቃላቱ ለዋጭ የላቸውም” 18፡27
- “ለአላህ ድንጋጌ ፈጽሞ መለወጥን አታገኝም” 33፡62
በዚህ ዘመን የሚገኙት ሙስሊም ወገኖች እምነታቸውን ከዚህ የከፋ አጣብቂኝ ለመታደግ ሲሉ እነዚህን ጥቅሶች ከመሐመድና ከመጀመርያዎቹ ሙስሊሞች በተለየ መንገድ ለመተርጎም ተገድደዋል፡፡ ይህ ግን የመሐመድንና የመጀመርያዎቹን ሙስሊሞች ሥልጣን አለመቀበል በመሆኑ የሚያስኬድ አይሆንም፡፡
ከሐዲሳትና ከቀዳሚያን ተፍሲሮች እንደምንረዳው የጥንት ሙስሊሞች አላህ ያወረዳቸው ቅዱሳት መጻሕፍት ፈጽሞ እንደማይለወጡና ማንም ሊለውጣቸው እንደማይችል አጥብቀው ያምኑ ነበር፡፡ ለምሳሌ የሚከተለውን የኢብን ከሢር ተፍሲር ተመልከቱ፡-
“… አል ቡኻሪ እንደዘገበው ኢብን አባስ እንዲህ ብሏል የዚህ አያ ትርጉም የሚከተለው ነው፡– … ከአላህ ፍጥረታት መካከል ማንም የአላህን ቃላት ከመጻሕፍቱ ውስጥ ማስወገድ አይችልም፡፡ ግልፅ ትርጉማቸውን ያጣምማሉ ማለት ነው፡፡ ወሃብ ኢብን ሙነቢህ እንዲህ አለ “ተውራ እና እንጂል ልክ አላህ በገለጣቸው ሁኔታ ተጠብቀው ይገኛሉ፡፡ ከውስጣቸው አንድም ፊደልአልተወገደም፡፡ ነገር ግን ሰዎች ራሳቸው በጻፏቸው መጻሕፍት ላይ ተሞርኩዘው በመጨመር እና ውሸት በሆነ አተረጓጎም ሌሎችን ያሳስታሉ፡፡” … “የአላህ መጻሕፍት ግን እስከ አሁን ተጠብቀው ይገኛሉ፤ ሊለወጡም አይችሉም፡፡” (Tafsir Ibn Kathir – Abridged, Volume 2, Parts 3, 4 & 5, Surat Al-Baqarah, Verse 253, to Surat An-Nisa, verse 147, abridged by a group of scholars under the supervision of Shaykh Safiur-Rahman Al-Mubarakpuri [Darussalam Publishers & Distributors, Riyadh, Houston, New York, Lahore; First Edition: March 2000], p. 196
እዚሁ ተፍሲፍ የግርጌ ማስታወሻ ላይ እንዲህ የሚል እናገኛለን፡- “ቃሉን ያጣምማሉ ማለት ትርጉሙን ይለውጣሉ ወይም ያጣምማሉ ማለት ነው፡፡ ከየትኛው የአላህ መጻሕፍት ውስጥ አንድ ቃል እንኳ መለወጥ የሚችል የለም፡፡ ይህ ማለት በተሳሳተ መንገድ ይተረጉማሉ ማለት ነው፡፡”
ሱናን አቡዳውድ ላይ ደግሞ እንዲህ የሚል ሐዲስ እናነባለን፡-
“… ለአላህ መልእክተኛ (ሰላም በእሳቸው ላይ ይሁንና) ወንበር አመጡላቸው፤ ተቀመጡበትም፡፡ ከዚያም ተውራት አምጡልኝ አሉ፤ አመጡላቸውም፡፡ ከዚያ ከወንበሩ ላይ ተነስተው ተውራትን አስቀመጡና እንዲህ አሉ፡– በአንተ እና አንተን በገለጠው አምላክ አምናለሁ፡፡” Sunan Abu Dawud, Book 38 (Kitab al Hudud, i.e. Prescribed Punishments), Number 4434
ኢብን ከሢር ደግሞ አላህ ስላዘዛቸው መሐመድ ይህንን ማድረጋቸውን ይናገራል፡፡ (Tafsir Ibn Kathir (Abridged) Volume 3, Parts 6, 7 & 8)
ስለዚህ ማንን እንስማ? ዘመንኛ ተርጓሚዎችን ወይንስ መሐመድና የጥንት ሙስሊሞችን? የቅርብ ዓመታት መጻሕፍትን ወይንስ ሐዲሳትና ጥንታውያን ሊቃውንትን?
መጽሐፍ ቅዱስ የአላህ ቃል ከሆነና የአላህን ቃል ደግሞ መለወጥ የሚችል ከሌለ መጽሐፍ ቅዱስ አልተለወጠም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሙስሊሞች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በሚጣረሱ የቁርአን አስተምህሮዎችና ከላይ በተጠቀሱት ጥቅሶች መካከል መምረጥ ግድ ይላቸዋል፤ ሁለቱም በአንድ ጊዜ እውነት ሊሆኑ አይችሉምና። መጽሐፍ ቅዱስ ከተበረዘ ከላይ የተጠቀሱት ጥቅሶች ውሸት ይሆናሉ፣ ካልተበረዘ ደግሞ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጋጩት የቁርኣን ጥቅሶች ውሸት ይሆናሉ። ቁርአን እውነት መሆኑን ማመን ውሸት መሆኑን ማመን ነው!