የመጽሐፍ ቅዱስ የንባብ ልዩነቶች መነሻ ምክንያትና ተፅዕኖ (ቁርአንም ይፈተሻል)
በጥንት ዘመን የጽሕፈትና የኮፒ ማሽኖች ስላልነበሩ መጻሕፍት ይገለበጡ የነበሩት በጽሑፍ ባለሙያዎች ነበር፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች በሚገለብጡበት ወቅት ፊደላትን መግደፍ፣ ቃላትን መዝለል፣ ቦታ ማቀያየርና የመሳሰሉትን ስህተቶች ይፈጽማሉ፡፡ የሃይማኖት መጻሕፍትን ጨምሮ የትኛውም ጥንታዊ ጽሑፍ ከንደነዚህ ዓይነት ችግሮች የፀዳ አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም፡፡ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ በጥንታዊ የእጅ ጽሑፎች ስልጣን ከርሱ በፊትም ሆነ በኋላ ከተጻፉት ጥንታዊ መዛግብ ሁሉ የላቀ በመሆኑ የግልበጣ ስህተቶች ተዓማኒነቱን አጠራጣሪ ሊያደርጉ አይችሉም፡፡ በአንዱ ብራና ውስጥ የተዘለለ ወይንም ደግሞ የተገደፈ ክፍል ቢኖር በሌሎች ብራናዎች ውስጥ ተስተካክሎ ይገኛል ወይንም ደግሞ ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በመነሳት ትክክለኛውን አጻጻፍ ማወቅ ይቻላል፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አሉ ከተባሉት የግልበጣ ስህተቶች መካከል አብዛኞቹ እዚህ ግቡ የሚባሉ ካለመሆናቸው የተነሳ ሊተረጎሙ እንኳ የማይችሉ ናቸው፡፡ የከፉ የሚባሉቱ ደግሞ የስምና የቁጥር ስህተቶችን እንዲሁም የቃላትና የአረፍተ ነገሮች መዘለልን የመሳሰሉ ዋናውን መልዕክት ሊነኩ የማይችሉ ነገሮች ናቸው፡፡ ሁለት ምሳሌዎችን እንመልከት፡፡
የሐዋርያት ሥራ 15፡34 ላይ “ሲላስ ግን በዚያ ይኖር ዘንድ ፈቀደ” የሚለው በአንዳንድ የጥንት ቅጂዎች ውስጥ እንደማይገኝ ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም እዚያው የሐዋርያት ሥራ 28፡29 ላይ “ይህንም በተናገረ ጊዜ አይሁድ እርስ በርሳቸው እጅግ እየተከራከሩ ሄዱ” የሚለውም በአንዳንድ የጥንት ቅጆች ውስጥ እንደማይገኝ ተገልጿል፡፡ የጥቅሶቹን ሐሳቦች ከምንባቦቹ አውዶች ማግኘት ስለሚቻል መካተት አለመካተታቸው የምንባቡን ትርጉም አይለውጥም፤ የትኛውንም የክርስትና አስተምህሮ የሚጠቅስ ሐሳብም አላዘሉም፡፡ እነዚህን የሚመስሉት ምንባቦች የተለያዩ የእጅ ጽሑፎችን ጎን ለጎን በማስተያየት ትክክለኛዎቹ ምንባቦቻቸው ሊታወቁ የሚችሉ በመሆናቸው እንደነዚህ ባሉ ጥቃቅን ችግሮች ምክንያት የትኛውም ጥንታዊ ጽሑፍ ተዓማኒነት እንደሚጎለው አይታሰብም፡፡ በዘርፉ እውቀት ያላቸው ምሑራን እነዚህን ችግሮች እንደ አሳሳቢ ችግሮች አይቆጥሯቸውም ነገር ግን ስለጉዳዩ እውቀት የሌላቸው ወገኖች ግራ ሊጋቡ ይችላሉ፡፡
በሊቃውንት እጅ የሚገኙት አብዛኞቹ ብራናዎች በስደት ዘመን የተገለበጡ በመሆናቸው ጸሐፍቱ ሌሊት መብራቶችን በመጠቀም ወይም ዋሻዎች ውስጥ በመደበቅ ነበር ሲገለብጡ የነበሩት፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ብዙ ጸሐፍት በአንድ ክፍል ውስጥ ይሰበሰቡና አንድ አንባቢ ከፊት ሆኖ እያነበበላቸው ይገለብጣሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ስህተቶች የመፈጠራቸው ሁኔታ ይሰፋል፡፡ ነገር ግን ሊቃውንት በዚህ ሁኔታ ችግር እንዳለበት ያረጋገጡት የአዲስ ኪዳን ክፍል ከሁለት በመቶ ያነሰ ነው፡፡ 98.33 ከመቶ የሚሆነው የአዲስ ኪዳን ክፍል ከመሰል ችግሮች የፀዳ ነው፡፡ ከእነዚህ በጣት ከሚቆጠሩት ችግሮች መካከል ዋናውን የእምነት መሠረት የሚነካ አንድም እንኳ የሌለ ሲሆን ወሳኝ የሆኑ ልዩነቶችን በመጽሐፍ ቅዱስ የግርጌ ማስታወሻዎች በማስቀመጥ አንባቢያን እንዲያውቁት ይደረጋል፡፡
የመጀመርያው የመጽሐፍ ቅዱስ መልዕክት በነዚህ ምንባቦች ውስጥ የተጠበቀ በመሆኑ በእውነቱ ከሆነ መሰል ችግሮች ሊያሳስቡን የሚገቡ አይደሉም፡፡ እግዚአብሔር እነዚህ ችግሮች እንዳይከሰቱ የማድረግ ኃይል ቢኖረውም ነገር ግን ቅዱስ ቃሉ በተፈጥሯዊ መንገድ ተጠብቆ እንዲኖር መርጧል፡፡
ብሩስ መዝገር የተሰኙ ዕውቅ የመጽሐፍ ቅዱስ የንባብ ሕየሳ (Textual Criticism) ሊቅ አዲስ ኪዳን 99.5 ከመቶ የተጠበቀ መሆኑን በማረጋገጥ ጽፈዋል፡፡[1] ቁርአንን ጨምሮ በዚህ የጥራት መጠን እንደተጠበቀ የተረጋገጠ ሃይማኖታዊም ሆነ ዓለማዊ መጽሐፍ በሰው ልጆች ታሪክ አይታወቅም!
ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ በትክክል ተጠብቆ መቆየቱን እንጂ እያንዳንዱ በእጅ የተገለበጠ ብራና የፊደል ግድፈትና ጣልቃ ገብ ጽሑፎችን የመሳሰሉ እንከኖች በሌሉበት ሁኔታ ተጠብቆ መቆየቱን ተናግረው አያውቁም፡፡ በያንዳንዱ ብራና ላይ እንዲህ ያሉ እንከኖች ለምን እንደተገኙ የሚጠይቅ ሙስሊም ካለ የቁርአንን 10 ገፆች ያህል በእጁ በመገልበጥ ከስህተት በጸዳ ሁኔታ ገልብጦ እንደሆን ጓደኛውን አስነብቦ እንዲያረጋግጥ እናበረታታዋለን፡፡ እንኳንስ የማተሚያ ማሽን ባልነበረበት ዘመን ይቅርና በዚህ በኛ ዘመን እንኳ አንድን መጽሐፍ እንከን በሌለው ሁኔታ ማሳተም ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ያየ ያውቀዋል፡፡
ዋና ዋና የንባብ ልዩነቶች
በምንዝር የተያዘች ሴት
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት የንባብ ልዩነቶች መካከል በተደጋጋሚ የሚነሳው በአመንዝራነት ተይዛ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይቅር ስላላት ሴት የተጻፈው ነው (ዮሐ. 7፡53-8፡11)፡፡ በነገረ መለኮት ምሑራን ዘንድ “The Pericope de Adultera” የሚል ቴክኒካዊ መጠርያ ያለው ይህ ታሪክ በብዙ ጥንታውያን የመጽሐፍ ቅዱስ የእጅ ጽሑፎች ውስጥ እንደማይገኝ በተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የግርጌ ማስታወሻዎች ላይ ይታያል፡፡ ይህ ማለት ግን የታሪኩን ትክክለኛነት የሚያሳይ ምንም ዓይነት ማስረጃ የለም ማለት አይደለም፡፡
መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ላቲን ቋንቋ የተረጎመው ቅዱስ ጀሮም (415 ዓ.ም.) ይህ ታሪክ በእርሱ ዘመን በነበሩት ብዙ የግሪክና የላቲን የዮሐንስ ወንጌል የእጅ ጽሑፎች ውስጥ እንደሚገኝ ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡ ምሑራን “D” በማለት በሰየሙት በአምስተኛው ክ.ዘ. በተገለበጠ የግሪክ የእጅ ጽሑፍ ውስጥም ይገኛል፡፡[2] ድድስቅሊያና ሥርዓተ ሐዋርያትን በመሳሰሉት (3ኛውና 4ኛው ክ.ዘ.) ጥንታዊያን የአበው ጽሑፎች ውስጥ መገኘቱም ለጥንታዊነቱ ሌላው ማስረጃ ነው፡፡[3]
ይህ ታሪክ ብዙ ጥንታዊያን የቤተ ክርስቲያን አበው ምንዝርናን በሚፈፅሙት ወገኖች ላይ ይወስዱ ከነበሩት ጥብቅ እርምጃ በተጻራሪ ይቅርታና ምህረትን የሚያበረታታ በመሆኑ “ምንዝርናን ያበረታታል” በሚል የተሳሳተ ዕይታ ምክንያት በጸሐፍት ዘንድ በጥርጣሬ መታየቱን ጉዳዩን ያጠኑት ምሑራን ይናገራሉ፡፡ ቅዱስ አውጉስጢኖስ (400 ዓ.ም.) ዋና ዋና በሚባሉት የአዲስ ኪዳን የእጅ ጽሑፎች ውስጥ ያለመገኘቱን ሚስጥር ሲያብራራ የሰጠው ምክንያት ተመሳሳይ ሲሆን ለታሪኩ ትክክለኛነት ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡[4] የሚላን ሊቀ ጳጳስ የነበረው ቅዱስ አምብሮስ (374 ዓ.ም.) የታሪኩን ሐቀኝነት የሚጠራጠሩት ወገኖች ትክክል አለመሆናቸውን ተናግሯል፡፡[5]
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙ ጊዜውን ያሳልፍ የነበረው የሃይማኖት መሪዎች “ኃጢአተኞችና አመንዝሮች ናቸው” በማለት ካገለሏቸው ወገኖች ጋር ነበር (ማቴ. 9፡9-13፣ ማር. 2፡15፣ ሉቃ. 5፡32፣ 7፡36-50፣ 15፡2፣ 19፡7)፡፡ ሰው ሁሉ ኃጢአተኛ በመሆኑ ምክንያት ማንም በማንም ላይ የመፍረድ ብቃት እንደሌለው ተናግሯል (ማቴ. 7፡1-5፣ ሉቃ. 6፡37-42)፡፡ በኃጢአተኞች ላይ ለመፍረድ ሳይሆን ኃጢአተኞችን ለማዳን መምጣቱንም አውጇል (ሉቃ. 19፡10)፡፡ ስለዚህ ይህ ታሪክ በአዲስ ኪዳን ላይ የሚጨምረው ወይም የሚቀንሰው የተለየ ትምህርት ስለሌለ የመጽሐፍ ቅዱስ አካል ተደርጎ መወሰድ አለመወሰዱ የእስልምናን የብረዛ ክስ አያረጋግጥም፡፡
የማርቆስ መዝጊያ
ሌላው ለጥያቄ የቀረበ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ማርቆስ 16፡9-20 ላይ የሚገኘው ነው፡፡
የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት ማርቆስ 16፡9-20 ድረስ የሚገኘውን ክፍል ተዓማኒነት በተመለከተ ወጥ አቋም የላቸውም፡፡ ገሚሶቹ በአብዛኞቹ የእጅ ጽሑፎች ውስጥ ስለተካተተ ተዓማኒ እንደሆነ ሲናገሩ የተቀሩት ደግሞ ይህንን ክፍል ላለመቀበል ተከታዮቹን ምክንያቶች ያቀርባሉ፡-
- እነዚህ ቁጥሮች ቀዳሚና ይበልጥ ተዓማኒ በሆኑት የግሪክ የእጅ ጽሑፎች ውስጥ አይገኙም፡፡ በተጨማሪም በቀደመው ላቲን፣ ሢርያክ፣ አርመንያ እና ኢትዮጵያ የእጅ ጽሑፎች ውስጥ አይገኙም፡፡
- ቀለሜንጦስ፣ ኦሪጎን እና ኢዮስቢዮስን የመሳሰሉት ብዙ የጥንት አባቶች እነዚህን ቁጥሮች አያውቋቸውም፡፡ ቅዱስ ጀሮም ከሞላ ጎደል በእርሱ ዘመን በነበሩት በሁሉም የግሪክ የእጅ ጽሑፎች ውስጥ አለመገኘቱን አስታውቋል፡፡
- ይህንን ክፍል የሚያጠቃልሉት ብዙ የእጅ ጽሑፎች አጠራጣሪ መሆኑን ለማሳየት ምልክት ያደርጉበታል፡፡
- በአንዳንድ የእጅ ጽሑፎች ውስጥ ሌላ አጠር ያለ የማርቆስ ወንጌል መዝጊያ ይገኛል፡፡
- አንዳንዶች ደግሞ አጻጻፉና የሰዋሰው ይዘቱ ከተቀረው የማርቆስ ወንጌል ጋር እንደማይመሳሰል ይናገራሉ፡፡
ይህ ክፍል በኦሪጅናል የማርቆስ ወንጌል ውስጥ መገኘት አለመገኘቱ አጠያያቂ እንደሆነ ቢቀጥልም ነገር ግን የያዘው እውነት ከተቀሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ጋር የሚስማማ ነው፡፡ ስለዚህ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቢወጣ ምንም የሚጎድል ትምህርት የለም፡፡ ያዘለው ትምህርት በሌሎች ክፍሎች እንደመገኘቱ መጠን ደግሞ ባለበት ቦታ ቢቆይ በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ላይ የሚጨምረው ነገር የለም፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ የተጠቀሱት በልሳን የመናገር ስጦታ፣ የጥምቀት ሥርዓትና በእባብ መርዝ ያለመጎዳት ተዓምር በሌሎች ክፍሎች ላይ ተጠቅሰዋል (ሐዋ. 2፡1-21፣ 10፡44-48፣ 19፡1-7፣ 28፡3-5)፡፡[6]
በአዲስ ኪዳን ውስጥ ከሚገኙት ሰፋፊ ምንባቦች መካከል በዚህ ሁኔታ በምሑራን ዘንድ ክርክር ያስነሱት ክፍሎች ከላይ የተጠቀሱት ሁለቱ ብቻ ሲሆኑ መሠረታዊውን የአዲስ ኪዳን መልእክት የሚለውጡና የእስልምናን የብረዛ ክስ የሚያረጋግጡ አይደሉም፡፡ እነዚህ ክፍሎች የዲስ ኪዳን ክፍል ተደርገው መቆጠር አለመቆጠራቸው በአዲስ ኪዳን ትምህርት ላይ የሚጨምረውም ሆነ የሚቀንሰው ምንም ነገር የለም፡፡
የቁርአን የንባብልዩነቶች
ክርስቲያን ምሑራን የአዲስ ኪዳንን የእጅ ጽሑፎች ታሪክ በተመለከተ ያሳዩትን ግልጸኝነትና ሐቀኝነት ሙስሊም ጸሐፊያን በመጠምዘዝ የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ሲነዙ ማየት በእጅጉ የሚያሳዝን ነው፡፡ ከሙስሊም ምሑራን በተጻራሪ ክርስቲያን ምሑራን ከሕዝባቸው የሚሰውሩት ምንም ነገር የለም፡፡ በአዲስ ኪዳን ውስጥ የሚገኙትን የንባብ ልዩነቶች ያለምንም መሸፋፈን ያሳውቃሉ፡፡ ጥንታውያን የእጅ ጽሑፎችንም ሙዚየሞች ውስጥ ከማስቀመጥ ባለፈ ገፅ በገፅ ፎቶግራፍ አንስተው በመጽሐፍና በበይነ መረብ በማሳተም ለመላው ዓለም ያሳያሉ፡፡ በእያንዳንዱ የእጅ ጽሑፍ ውስጥ የሚገኘውን የፊደል ግድፈትና ጭረት ሳይቀር ጥልቅ የሆኑ ማነጻጸርያዎችን (Critical Editions) በማዘጋጀት በየጊዜው ያሳትማሉ፡፡
በእስልምና ግን እንዲህ ያለ ነገር አይታወቅም፡፡ ቁርአን ሙስሊሞች ከሚሉት በተጻራሪ በትክክል ያልተጠበቀና ብዙ መለዋወጦችን ያስተናገደ መጽሐፍ መሆኑን የሚያሳዩ ብዙ ማስረጃዎች ቢኖሩም ክርስቲያን ምሑራን መጽሐፍ ቅዱስን በተመለከተ በሚያዘጋጁት ሁኔታ የቁርአንን የንባብ ታሪክ የሚያሳይና የብራና ጽሑፎቹን የሚገመግም ምንም ዓይነት ጥልቅ ማነጻጸርያ (Critical Edition) አይገኝም፡፡
ሙስሊም ምሑራን በቁርአን ጥንታዊያን የእጅ ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙትን ግድፈቶች ዕውቅና ሰጥተው ለሕዝባቸው ይፋ በማድረግ ሃይማኖታቸውን በእውነት ላይ ከመመሥረት ይልቅ ቁርአን በእጅ ሲገለበጥ በኖረባቸው ክፍለዘመናት የተጻፉት የብራና ጽሑፎች ሁሉ ፍጹም እንከን የለሽ በሆነ ሁኔታ የተገለበጡ በማስመሰል ይናገራሉ፡፡ “ከነቢዩ ዘመን ጀምሮ አንዲት ጭረት አልተጨመረበትም ከላዩ ላይም አልተቀነሰም” በማለት ይወሸክታሉ፡፡ አከራካሪ የሆኑ የቁርአን የንባብ ልዩነቶች የሌሉ በማስመሰልም ሕዝባቸውን ያታልላሉ፡፡ እውነቱ ግን እንደርሱ አይደለም፡፡ በማስከተል በቁርአን ውስጥ የንባብ ልዩነቶችና የግልበጣ ስህተቶች መኖራቸውን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን እናቀርባለን፡፡ ሙስሊም ወገኖቻችንም ከስሜታዊነት በጸዳ ሁኔታ ማስረጃዎቹን እንዲያጤኑ እንጠይቃቸዋለን፡፡
በትውፊት የተዘገቡ የንባብ ልዩነቶች
ቀዳሚያን ሙስሊሞች በቁርአን ውስጥ የነበሩ ለቁጥር የሚያታክቱ የንባብ ልዩነቶችን ዘግበው አልፈዋል፡፡ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል፡-
- የማሊክ ሙዋጣዕ በተሰኘ የሐዲስ ስብስብ ውስጥ ተከታዩ ተዘግቧል፡-
ያህያ ከማሊክ፣ ከዘይድ ኢብን አስለም፣ ከአል-ቃቃ ኢብን ሐኪም የተላለፈውን እንደነገረኝ የአማኞች እናት የሆነችው የአይሻ ጸሐፊ እንዲህ ብሎ ነበር፡- “አይሻ ቁርአንን እንድጽፍላት አዘዘችኝ፡፡ ‹‹በሶላቶች (በተለይ) በመካከለኛይቱም ሶላት ላይ ተጠባበቁ፡፡ ታዛዦች ኾናችሁም ለአላህ ቁሙ›› የሚለው አንቀጽ ጋር ስትደርስ አሳውቀኝ፡፡ እኔም አንቀጹ ጋር ስደርስ አሳወኳት፡፡ ከዚያም እንዲህ ብዬ እንድጽፍ ነገረችኝ ‹‹በሶላቶች በመካከለኛይቱ ሶላት እንዲሁም በአስር ሶላት ላይ ተጠባበቁ፡፡ ታዛዦች ኾናችሁም ለአላህ ቁሙ፡፡›› አይሻ ይህንን ከአላህ መልእክተኛ መስማቷን ተናግራለች፡፡”[7]
ይህ አንቀጽ በዛሬው ቁርአን ውስጥ ሱራ 2፡238 ላይ የሚገኝ ሲሆን እንዲህ ይነበባል፡- “በሶላቶች (በተለይ) በመካከለኛይቱም ሶላት ላይ ተጠባበቁ፡፡ ታዛዦች ኾናችሁም ለአላህ ቁሙ፡፡” በአይሻ ቁርአን ውስጥ የነበረው “እንዲሁም በአስር ሶላት” የሚለው ሐረግ ተቀንሷል ማለት ነው፡፡ የዘመናችን ሙስሊም ምሑራን ሐቀኞች ቢሆኑ ኖሮ በቁርአን የግርጌ ማስታወሻዎች ላይ “የአይሻ ቅጂ ‹‹እንዲሁም በአስር ሶላት›› የሚል ሐረግ ይጨምራል” የሚል መረጃ ለአንባቢያን መስጠት ነበረባቸው፡፡
- ሳሂህ ሙስሊም ውስጥ ተከታዩ ተዘግቧል፡- “አቡ ሀርብ ቢን አቡ አል-አስዋድ አባታቸውን ዋቢ በማድረግ እንደዘገቡት አቡ ሙሳ አል-ሸዐሪ የበስራ ቁርአን አነብናቢዎችን አስጠሯቸው፡፡ ቁጥራቸው ወደ ሦስት መቶ የሚሆኑቱ መጡ፡፡ ቁርአንን አነበነቡት፤ እርሳቸውም እንዲህ አሏቸው ‹‹እናንተ አነብናቢዎች እንደመሆናችሁ ከበስራ ነዋሪዎች ሁሉ ምርጦች ናችሁ፡፡ ማነብነባችሁን ቀጥሉ፡፡ (ነገር ግን) ለረጅም ጊዜ ማነብነባችሁ ከናንተ በፊት የነበሩትን ሰዎች ልቦች እንዳደነደነ ልቦቻችሁን እንዳያደነድን ተጠንቀቁ፡፡ በርዝመትና በጥንካሬ ከሱራ በረዓት ጋር የሚነፃፀር ሱራ እናነበንብ ነበር፡፡ ነገር ግን ከተከታዩ ውጪ የተቀረውን ረስቼዋለሁ፡- ‹‹የአደም ልጅ በኃብት የተሞሉ ሁለት ሸለቆዎች ቢኖሩት ሦስተኛውን ይመኛል፡፡ ከአፈር ውጪ የአደምን ልጅ ሆድ የሚሞላ ምንም ነገር የለም፡፡›› ከሱረት ሙሰቢሃት መካከል ከአንዱ ጋር የሚመሳሰል ሌላ ሱራም እናነበንብ ነበር ነገር ግን ከተከታዩ ውጪ የተቀረውን ረስቼዋለሁ፡- ‹‹እናንተ ያመናችሁ ሆይ የማትፈፅሙትን ነገር ስለምን ትናገራላችሁ? እርሱም በናንተ ላይ ምስክር እንዲሆንባችሁ በአንገቶቻችሁ ላይ ተጽፏል፤ በዕለተ ትንሣኤም ከእርሱ ትጠየቃላችሁ፡፡››” [8]
በኛ ዘመን የሚገኙት ሙስሊም ሊቃውንት በያንዳንዱ የቁርአን መቅድም ላይ በዘመናችን የሚገኘው ቁርአን ያልተሟላ መሆኑንና ረጃጅም ምዕራፎች ከውስጡ መጉደላቸውን ማሳወቅ ነበረባቸው፡፡
- ሳሂህ አል-ቡኻሪ ውስጥ እንደተዘገበው አብደላህ ኢብን መስዑድ የተሰኘው የመሐመድ ወዳጅ ሱራ 92፡3 ላይ የሚገኘውን “ወንድንና ሴትን በፈጠረውም (አምላክ እምላለሁ)” የሚለውን አንቀጽ ሲያነብ “በወንድና በሴት እምላለሁ” በማለት ነበር፡፡ አቡ ደርዳ የተሰኘ ሌላ የመሐመድ ወዳጅ ይህንኑ ንባብ ከነቢዩ መስማቱን በመሐላ በማረጋገጥ የኡሥማንን ንባብ እንደማይቀበል ተናግሯል፡፡[9]
የዘመናችን ሙስሊም ምሑራን ሐቀኞች ቢሆኑ ኖሮ በቁርአን የግርጌ ማስታወሻዎች ላይ የአብደላህ ኢብን መስዑድ ቅጂ “ወንድንና ሴትን በፈጠረውም (አምላክ እምላለሁ)” በሚለው ቦታ “በወንድና በሴት እምላለሁ” እንደሚል ማሳወቅ ነበረባቸው፡፡
በሕትመት ላይ የሚገኙት ልዩነቶች
ሙስሊም ወገኖች በዚህ ዘመን በዓለም ላይ አንድ ዓይነት የአረብኛ ቁርአን ብቻ እንደሚገኝና ምንም ዓይነት ልዩነት እንደማያሳይ ሲናገሩ መስማት የተለመደ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ፍጹም የተሳሳተና ከተጨባጩ እውነታ ጋር የሚጣረስ ነው፡፡ በዚህ ዘመን በዓለም ላይ እጅግ ብዙ የንባብ ልዩነቶች ያሏቸው ቁርአኖች ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ልዩነቶች እንዴት እንደተፈጠሩ ለማወቅ ቁርአን በምን ሁኔታ እየተላለፈ ለዚህ ዘመን እንደበቃ መረዳት አስፈላጊ ነው፡፡
በመሐመድና በተከታዮቻቸው ዘመን የነበረው የአረብኛ ቋንቋ ተነባቢ ፊደላት እንጂ አናባቢ ስላልነበረው በጽሑፍ የሰፈረው ቁርአን በብዙ መንገዶች መነበብ የሚችልና ቋሚ ንባብ ያልነበረው ግራ አጋቢ ጽሑፍ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ሙስሊሙ ማሕበረሰብ ግራ ስለተጋባ በተነባቢ ፊደላት ላይ ተቀፅለው ትክክለኛ ድምፃቸውን የሚያመለክቱ እንዲሁም እርስ በርሳቸው የሚመሳሰሉ ተነባቢ ፊደላትን ለይተው የሚያሳዩ ቋሚና ወጥ መልክ ያላቸው ምልክቶች (Diacritical Marks) እንዲፈጠሩ ተደረገ፡፡ ሙስሊም ገዢዎች ከላይ በተጠቀሰው ችግር ምክንያት የተፈጠሩትን የንባብ ልዩነቶች ለማፈን ቢሞክሩም እነዚህን ንባቦች ለማጥፋት አልቻሉም ነበር፡፡ ከዚህ የተነሳ በአራተኛው የእስልምና ክፍለ ዘመን ቀደም ሲል ተፈጥረው የነበሩትን ሰባት ቁርአኖች ኦፊሴላዊ ለማድረግና ልዩነቶቹን ለማቻቻል ጥረት ተደረገ፡፡ ሰባቱ የንባብ መንገዶች (ቂርአት) ከሰባት ታዋቂ አነብናቢዎች (ቁረ) የተላለፉ ሲሆኑ ትክክለኛነታቸውን ለማረጋገጥ ሁለት ሁለት አስተላላፊዎች (ሩዋህ) ተመረጡ፡፡ ከእነዚህ አስተላላፊዎች የተገኙት ቁርአኖች ደግሞ መጠነኛ ልዩነቶችን በሚያሳዩ ሁለት ሁለት ቅጂዎች (ሪዋያተን) እየተላለፉ ለዚህ ዘመን በቅተዋል፡፡[10] “ከሰባቱ” በተጨማሪ “ሦስቱ” በመባል የሚታወቁ ሌሎች ቁርአኖች ስለተገኙ የቂርአት ቁጥር ወደ አሥር ከፍ ብሏል፡፡
በመላው ዓለም በብዛት ተሰራጭቶ የሚገኘው ቁርአን የንጉሥ ፈሐድ ዕትም በመባል የሚታወቀው የሐፍስ ንባብ ሲሆን ተፎካካሪ ተደርጎ የሚወሰደው የዋርሽ ንባብ ደግሞ አልጄርያ፣ ሞሮኮ፣ ቱኒዝያ፣ ሱዳንና ምዕራብ አፍሪካን በመሳሰሉት አካባቢዎች ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል፡፡ በሁለቱ መካከል ከሚገኙት ልዩነቶች መካከል ጥቂቶቹን እንደሚከተለው እናያለን፡፡
رواية ورش عن نافع – دار المعرفة –دمشق የዋርሽ ንባብ – ደር አል ማሪፋህ ደማስቆ | رواية حفص عن عاصم – مجمع الملك فهد- المدينة የሐፍስ ንባብ – የንጉሥ ፈሐድ ጥራዝ መዲና | አንቀፅ |
يُغْفَرْ ይምራልና | نَّغْفِرْ እንምራለንና | 2:58 |
لَوْ تَرَى الذِينَ ظَلَمُواْ እነዚያን የበደሉትን ሰዎች ባያችሁ ጊዜ | لَوْ يَرَى الَّذِينَ ظَلَمُواْ እነዚያም የበደሉት ሰዎች … ባዩ ጊዜ | 2:165 |
ድኾችን ማብላት አለባቸው | ድኻን ማብላት አለባቸው | 2፡183 |
فَنُوَفِّيهِمُ ምንዳዎቻቸውን እንሞላላቸዋለን | فَيُوَفِّيهِمْ ምንዳዎቻቸውን ይሞላላቸዋል | 3:57 |
تَبْغُونَ ትፈልጋላችሁን | يَبْغُونَ ይፈልጋሉን | 3:83 |
تُرْجَعُونَ የምትመለሱ ስትኾኑ | يُرْجَعُونَ የሚመለሱ ሲኾኑ | 3:83 |
نُدْخِلْهُ እናገባዋለን | يُدْخِلْهُ ያገባዋል | 4:14 |
نُفَصِّلُ እናብራራለን | يُفَصِّلُ ያብራራል | 10:5 |
يُوحى የሚያወርድላቸው | نُّوحِى የምናወርድላቸው | 12:109 |
تُوقِدُونَ የምታነዱበትም | يُوقِدُونَ የሚያነዱበትም | 13:17 |
مَا تَنَزِّلُ አታወርድም | مَا نُنَزِّلُ አናወርድም | 15:8 |
تّقُولُونَ እንደሚሉት | يَقُولُونَ እንደምትሉት | 17:42 |
قُل በል | قَالَ አለ | 21:4 |
ከላይ የተጠቀሱት ልዩነቶች በሁለቱ ቁርአኖች መካከል ከሚገኙ 1354 ከሚሆኑት ልዩነቶች መካከል ለናሙናነት የተወሰዱ ናቸው፡፡[11] እነዚህ ልዩነቶች የምንባቡን አጠቃላይ ትርጉም የሚለውጡ ባይሆኑም በዓለም ላይ የሚገኙት ቁርአኖች ፍፁም አንድ እንደሆኑ ሲነገር የምንሰማውን እስላማዊ ተአብዮ ከንቱ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ እነዚህ ልዩነቶች በንባብ ወቅት የሚፈጠሩ ልዩነቶች ሳይሆኑ በጽሑፍ የሰፈሩ ንባቦች በመሆናቸው ልዩነቶቹ በአነባብ ስልት ወይም በአረብኛ ዘዬ ምክንያት ብቻ የተፈጠሩ ናቸው የሚለው የሙስሊም አቃቤ እምነታውያን ማስተባበያ የሚያስኬድ አይደለም፡፡
የሙስሊም ምሑራን ኑዛዜ
በቁርአን ውስጥ የሚገኙትን የንባብ ልዩነቶችና ስህተቶች ዕውቅና ሰጥቶ ለሕዝብ የማሳወቅ ድፍረትና ዝግጅት በሙስሊም ምሑራን ዘንድ ባይታይም ዝምታውን በመስበር ይህንን ለማድረግ የሞከሩ ጥቂቶች አልጠፉም፡፡ ለምሳሌ ያህል አብዱላህ ዩሱፍ አሊ የተሰኘው ዕውቅ የቁርአን ተርጓሚ ሱራ 33፡6 የንባብ ልዩነት እንደሚያሳይ ጠቅሷል፡፡ የኡሥማን ቅጂ እንደሆነ የሚታመነው በኛ ዘመን የሚገኘው ቁርአን እንዲህ ይነበባል፡-
“ነቢዩ በምእምናን ከነፍሶቻቸው ይበልጥ ተገቢ ነው፡፡ ሚስቶቹም እናቶቻቸው ናቸው፡፡”
ዩሱፍ አሊ የኡበይ ቢን ካዕብ ቅጂ “እንዲሁም እርሱ አባታቸው ነው” የሚል ሐረግ እንደሚጨምር በግርጌ ማስታወሻው ላይ ገልጿል፡፡[12]
ረሺድ ኸሊፋ የተሰኘ ሌላ የቁርአን ተርጓሚ ሱራ 9፡128-129 ላይ የሚገኙት ሁለት አንቀፆች ነቢዩ መሐመድ ከሞቱ ከዓመታት በኋላ በኡሥማን ዘመን በቁርአን ላይ የተጨመሩ መሆናቸውን በመግለፅ ከራሱ ቅጂ ውስጥ አስወግዷቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በአክራሪ ሙስሊሞች ተገድሏል፡፡[13]
ቁርአን ሲለዋወጥ የኖረ መጽሐፍ መሆኑን በተናገሩ ሙስሊም ባልሆኑ ምሑራን ላይም ዛቻና ማስፈራራት እየደረሰ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ ያህል ገርድ ሩዲጀር ፑዊን የተሰኘ ጀርመናዊ የአረብኛ ቋንቋ ሊቅ “የሰነዓ የእጅ ጽሑፎች” ተብለው በሚታወቁት የቁርአን ጽሑፎች ላይ ጥናትና ምርምር እንዲያደርግ በየመን መንግሥት ጥሪ ተደርጎለት ነበር፡፡ ነገር ግን ቁርአን የተለዋወጠ መጽሐፍ መሆኑን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን ማግኘት ሲጀምር የየመን መንግሥት ሥራውን አስቁሞታል፡፡ ጽሑፎቹንም ድጋሜ እንዳያገኛቸው እገዳ ጥሎበታል፡፡ ዶ/ር ፑዊን ጽሑፎቹን ቀደም ሲል በፎቶ ፊልም ወስዷቸው ስለነበር ወደ አገሩ በመመለስ ጥናቱን ቀጥሏል፡፡ የጥናቱን ውጤት በመጽሐፍ አንደሚያሳትም ማሳወቁ በሙስሊሞች ዘንድ ቁጣና ተቃውሞን ሊያስነሳ እንደሚችል ከፍተኛ ስጋት መኖሩን ዘጋርዲያን ዘግቧል፡፡[14]
ሙስሊም ወገኖቻችን ሆይ፤ በሃይማኖት መሪዎቻችሁ የተነገራችሁን ነባር አስተምህሮ የሚገዳደሩ ድምፆችን በዚህ ሁኔታ ለማፈን የምትሞክሩ ከሆነ ቁርአን መሰል ተግዳሮቶችን መቋቋም እንደሚችል ከልባችሁ አታምኑም ማለት ነው፡፡ ካልተጠናና ካልተመረመረ ታድያ ያለምንም እንከን ተጠብቆ ለዚህ ዘመን እንደበቃ ስትናገሩ ምን ማስረጃ ይዛችሁ ነው? ጥንታውያን ቁርአኖች እንደሆኑ የሚነገርላቸው በቱርክ ቶፖካፒ ቤተ መዘክርና በኡዝቤኪስታን ታሽኪን ቤተ መዘክር የሚገኙት ቁርአኖች ታትመው ለሕዝብ ይፋ አልሆኑም፡፡ እነዚህ ቁርአኖች ልክ እንደ ኮዴክስ ሲናይቲከስና ኮዴክስ ቫቲካነስ ታትመው ለሕዝብ ይፋ የማይሆኑት ለምንድነው? ሙስሊም መሪዎች ከሕዝባቸው ሰውረው በሚስጥር መያዝ የፈለጉት በመጻሕፍቱ ውስጥ የሚገኝ ችግር ምን ይሆን?
ማጣቀሻዎች
[1] “Most other ancient books are not so well authenticated. New Testament scholar Bruce Metzger estimated that the Mahabharata of Hinduism is copied with only about 90 percent accuracy and Homer’s Illiad with about 95 percent. By comparison, he estimated the New Testament is about 99.5 percent accurate.” (Geisler. Baker Encyclopedia of Christian Apologetics, p. 532)
[2] Edward F. Hills. The King James Version Defended; 4th edition (Des Moines: Christian Research Press, 1984), pp. 151-152
[3] Ibid., p. 52
[4] Ibid., p. 50
[5] Ibid.
[6] Norman L. Geisler & Thomas Howe. When Critics Ask: A Popular Hand Book on Bible Difficulties, Victor Books, p. 321-322 (pdf)
[7] Malik’s Muwatta, Book 8, Number 8.8.26; Book 8, Number 8.8.27
[8] Sahih Muslim 5:2286; Jalal al Din `Abdul Rahman b. abi Bakr al Suyuti. Al Itqan fi `ulum al Qur’an; Halabi, Cairo, 1935/1354, part 2, p. 25
[9] Sahih Al-Bukhari, Volume 5, Book 57, Number 105; Volume 6, Book 60, Number 468; Volume 5, Book 57, Number 85
[10] Cyril Glassé, The Concise Encyclopedia of Islam, p. 324
[11] ለበለጠ መረጃ፡- www.answering-islam.net/Green/seven.htm
በተከታዩ ድረ-ገፅ ላይ በሁለቱ ቁርአኖች መካከል የሚገኙ ብዙ ልዩነቶች ተዘርዝረዋል፡- www.answering-islam.net/Quran/Text/warsh_hafs.html
[12] Abdullah Yususf Ali, The Holy Qur’an, p. 1104, foot note. 3674
[13] http://masjidtusco.net/quran/appendices/appendix24.html
[14] https://www.theguardian.com/education/2000/aug/08/highereducation.theguardian