እስልምና የሰላም ሃይማኖት ነውን?

እስልምና የሰላም ሃይማኖት ነውን?

ይህ ጥያቄ በአሁኑ ወቅት በዓለም ዙርያ አነጋጋሪ ከሆኑት ርዕሰ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው፡፡ ክርስትናን ጨምሮ ብዙ የዓለም ሃይማኖቶች ይብዛም ይነስም በአንድ ወቅት የነውጠኝነት (violence) ታሪክ እንደነበራቸው የሚታወቅ ነው፡፡ ነገር ግን አንድ ሃይማኖት መለካት ያለበት በተከታዮቹ ሁኔታ ሳይሆን የእምነቱ መመርያ የሆኑት ቅዱሳት መጻሕፍት በሚያስተምሩት ትምህርት መሆኑ እሙንና ቅቡል ነው፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍቱ ሰላምና ፍቅርን የሚሰብኩ ሆነው ሳሉ የእምነቱ ተከታዮች መመርያውን ባለመታዘዝ ነውጠኞች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ነውጠኝነትን የሚሰብኩ መጻሕፍትን እንደ ሃይማኖት መመርያ የተቀበሉ ነገር ግን ባለማወቅም ይሁን መመርያዎቹን በተለየ መንገድ በመተርጎም ወይም ሆነ ብሎ ባለመታዘዝ በህሊናቸው የሚመሩና ከሌሎች ጋር በሰላም የሚኖሩ ወገኖች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡

የክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ የመጀመርያው ክፍል በሆነው በብሉይ ኪዳን ውስጥ ግልፅ በሆነ አውድ፣ ለአንድ የተወሰነ ዘመን፣ ለአንድ ሕዝብና ውሱን ለሆነ ዓላማ የተሰጡ ጦርነትንና የኃይል እርምጃን የሚያፀድቁ መመርያዎች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ማንም ሰው በዚህ ዘመን እንዲተገብራቸው በሚያነሳሳ ወይም በሚፈቅድ ሁኔታ አልተጻፉም፡፡ የመለኮታዊ መገለጥ መደምደምያ በሆነው አዲስ ኪዳን ውስጥ የተሰጡት መመርያዎች ደግሞ በቀልን፣ ጥላቻን፣ ጦርነትንና ማንኛውንም የኃይል እርምጃ አጥብቀው የሚከለክሉ በመሆናቸው ነውጠኝነት ክርስቲያናዊ እንዳልሆነ ያረጋግጣሉ (ማቴዎስ 5፡44፣ ማርቆስ 11፡25፣ ሉቃስ 6፡27-36፣ ዕብራውያን 12፡14፣ ኤፌሶን 4፡32፣ 1ተሰሎንቄ 5፡15፣ የሐዋርያት ሥራ 7፡60፣ ያዕቆብ 3፡18፣ ሮሜ 12፡18፣ 14፡19፣ 1ጴጥሮስ 3፡9-11፣ 1ቆሮንቶስ 14፡33)፡፡ የእምነታችን ጀማሪና ፈፃሚ የሆነው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባርም ጭምር ሰላምን ሰብኳል፡፡ የክርስቲያኖች እምነት ጀማሪ፣ መሠረት፣ ምሳሌና ሞዴል የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ እንዲሁም የእርሱን ተልዕኮ ይዘው የቀጠሉት ሐዋርያቱ እጅግ ሰላማውያን ነበሩ፡፡

ቤተ ክርስቲያን የሮማ ኢምፓየር ፖለቲካ መጠቀሚያ እስከተደረገችበት እስከ አራተኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የነበሩት ክርስቲያኖች መገደልን እንጂ መግደልን፣ መሰደድን እንጂ ማሳደድን አያውቁም ነበር፡፡ ኮሎሴዩም በተሰኘው የሮም የመጫወቻ እስታዲዮም ውስጥ ጫወታዎችን የሚያሳዩ ጎበዞች ክርስትናን መቀበላቸው የሚታወቅበት አንዱ መንገድ ከአውሬዎች ጋር የመታገል ትዕይንት ቢያሳዩም ከሰዎች ጋር በሚደረግ ደም አፋሳሽ ትግል ላይ አለመሳተፋቸው ነበር፡፡ ከሰዎች ጋር በሚደረግ ትግል ውስጥ ሌላውን ወገን ከመግደል ይልቅ መሣርያዎቻቸውን በመጣል መገደልን ይመርጡ ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ ትምህርትና ምሳሌነት የነበራት መታመን የተሸረሸረው “የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር” የሚለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ችላ በማለት የቄሣሮች መጠቀምያ ከሆነች ወዲህ ነበር፡፡

በአንፃሩ ከክርስቶስ ልደት ስድስት መቶ ዓመታት በኋላ የተሰበከውን የእስልምናን ታሪክ፣ ጀማሪው የሆኑትን የሙሐመድንና የተተኪዎቻቸውን ሕይወት ስንክሳር ስናጠና የክርስቶስና የመጀመርያዎቹ ክርስቲያኖች እምነትና ኑሮ ተቃራኒ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ሁለተኛው ኸሊፋ ኡሥማን ተገደሉ፡፡ ሦስተኛው ኸሊፋ ዑመር ተገደሉ፡፡ የነቢዩ ሙሐመድ የአጎት ልጅና የልጃቸው ባል የነበሩት አራተኛው ኸሊፋ አሊም ተገደሉ፡፡ የአሊ ልጅ ሁሴን የአባታቸውን ሥልጣን ለማስመለስ ሲዋጉ ተገደሉ፡፡ የሙሐመድ ሚስት አይሻ ደጋፊዎቻቸውን በማደራጀት ከሌሎች ሙስሊሞች ጋር ሲዋጉ ነበር፡፡

ነቢዩ ሙሐመድ ለተተኪዎቻቸው ምሳሌ ሊሆን የሚችል ሰላማዊ ሕይወት አልነበራቸውም፡፡ እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ በጦርነት፣ በሽምቅ ውጊያ፣ በዝርፍያና ተቃዋሚዎቻቸውን ከአገር በማባረር ነበር የኖሩት፡፡ ባጠቃላይ ትምህርቶቻቸውና ያሳለፏቸው ታሪኮች በምንም መስፈርት የሰላም ሰው እንደሆኑ እንድንናገር አያስደፍሩንም፡፡ ጥቂቶቹን እንደሚከተለው እናያለን፡፡

የእስልምና ጀማሪ የሆኑት ሙሐመድ እንዲህ ማለታቸው ተነግሯዋል፡-

“በሽብር ድል ነሺ ተደርጌያለሁ፡፡”[1]

በሌላ ዘገባም “በሽብር እታገዛለሁ” ማለታቸው ተዘግቧል፡፡ ይህም ከሌሎች የቀደሙት ነቢያት ሁሉ ልዩ እንደሚያደርጋቸው በኩራት ተናግረዋል፡፡ [2]

ቁርኣንም የእስልምና አምላክ የሆነው አላህ ሽብርን እንደሚነዛ ይናገራል፡-

“በእነዚያ በካዱት ሰዎች ልቦች ውስጥ አላህ በእርሱ አስረጅ ያላወረደበትን ነገር በአላህ በማጋራታቸው ምክንያት ፍርሃትን እንጥላለን፡፡ መኖሪያቸውም እሳት ናት፡፡ የበዳዮችም መኖሪያ ምን ትከፋ!” የዒምራን ቤተሰብ ምዕራፍ 3፡151 (በተጨማሪም ሱራ 8፡12፣ 8፡59-60፣ 33፡25-27፣ 59፡2፣ 59፡4፣ 59፡13)፡፡

በነዚህ ቦታዎች ላይ “ፍርሃት” ተብሎ የተተረጎመው በአብዱላህ ዩሱፍ አሊ የእንግሊዘኛ ትርጉም “Terror” ተብሎ ተቀምጧል፡፡

በተከታዩ የቁርኣን ጥቅስ መሠረት ደግሞ አላህ ሙስሊሞች ሙስሊም ያልሆኑትን ሰዎች ለማሸበር እንዲዘጋጁ ይነግራቸዋል፡-

“…ለእነሱም ከማንኛውም ኃይልና ከታጀቡ ፈረሶችም የቻላችሁትን ሁሉ በእርሱ የአላህን ጠላትና ጠላታችሁን ሌሎችንም ከእነርሱ በቀር ያሉትን የማታውቋቸውን አላህ የሚያውቃቸውን (መናፍቃን) የምታሸብሩበት ስትኾኑ አዘጋጁላቸው፡፡” (የጦር ዘረፋዎች ምዕራፍ 8፡60)

በኒ ቁረይዛ የተሰኘ የአይሁድ ጐሣ በሙሐመድ ዘመን በአረብያ ባህረ ሰላጤ ከሚገኙ ጠንካራ የአይሁድ ማህበረሰቦች መካከል አንዱ ነበር፡፡ ሙሐመድም ገብርኤል ተገልጦላቸው ይህንን ማህበረሰብ እንዲያሸብሩ እንደነገራቸው ለተከታዮቻቸው ተናገሩ፡፡ እናም ወንዶቻቸው እንዲገደሉ ያደረጉ ሲሆን ሴቶችና ህፃናትን ለሙስሊሞች ከፋፍለዋል፡፡ በሕይወት የተረፉትን ደግሞ ባርያዎች አድርገዋቸዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች ከመገደላቸው በፊት ሙሐመድ በመዲና የገበያ ስፍራ መካከል ጉድጓድ አስቆፍረው ነበር፡፡ ከዚያም በጥቂቱ 700-800 የሚገመቱ አይሁዳውያንን ወደዚያ ሥፍራ በመውሰድ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ሁሉንም በአንድ ላይ አሳረዷቸው፡፡[3]

የሱኒ ዕውቅ ሐታች የሆኑት ኢብን ከሢር የአይሁድን በጀማ መታረድ እንዲህ በማለት ገልፀዋል፡-

“ከዚያም የአላህ መልእክተኛ ጉድጓዶች እንዲቆፈሩ አዘዙ፤ ተቆፈሩም፡፡ እነርሱም ትከሻቸው ላይ ታስረው እንዲመጡ ከተደረገ በኋላ ታረዱ፡፡ ቁጥራቸውም ከሰባት መቶ እስከ ስምንት መቶ ይገመታል፡፡ ህፃናትና ሴቶችም ተማረኩ፤ ንብረታቸውም ተወረሰ፡፡”[4]

አሳዛኙ ነገር የበኒ ቁረይዛ አይሁድ ሙሐመድ ወረዱልኝ በሚሏቸው “መገለጦች” አይሁድን በማንቋሸሻቸው ምክንያት ከማኩረፋቸው የዘለለ ሙስሊሞችን አጥቅተው የማያውቁ መሆናቸው ነው፡፡ እንዲያውም “የምሽጎች ዘመቻ” (The Battle of Trenches) በተሰኘ የጦርነት ውሎ ወቅት ለሙስሊሞች መሸሸግያን በማዘጋጀት ረድተው ነበር፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፣ ከመካ ነዋሪዎች ጋር ቢያብሩ ኖሮ ሙስሊሞችን ሙሉ በሙሉ የማጥፋት አቅም ነበራቸው፡፡ ነገር ግን ያንን አላደረጉም፡፡ ሙሐመድና ተከታዮቻቸው ግን የእነርሱን ውለታ ወንዶቻቸውን በማረድ፣ ሴቶችና ህፃናቶቻቸውን ባርያ በማድረግና ንብረታቸውን በመዝረፍ ነበር የመለሱት፡፡

ሙሐመድ በጦርነት ወቅት ህፃናትና ሴቶች እንዳይገደሉ እንዳዘዙ የሚናገሩ ሐዲሶች ብዙ ጊዜ ይጠቀሳሉ፡፡ ይህ ግን የሙሐመድ ትምህርት እርስ በእርሱ የሚጣረስና ወጥነት የሌለው መሆኑን ከማረጋገጥ የዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡ ህፃናትና ሴቶች እንዳይገደሉ ይናገራሉ የተባለላቸውን የእስልምና ትውፊቶች ስናጠና ሴቶችና ህፃናት የሚገደሉበት አውድ መኖሩን እንደሚናገሩ ማየት እንችላለን፡፡ አንድ ሐዲስ እንዲህ ይላል፡-

“የአላህ መልእክተኛ ህፃናትን አይገድሉም ነበር። ስለዚህ አል ኸዲር ስለገደለው ህፃን ያወቀውን ነገር የምታውቁ ካልሆናችሁ በስተቀር ወይንም አማኝ በመሆን በሚያድግና አማኝ ባለመሆን በሚያድግ ህፃን መካከል መለየት ካልቻላችሁ አትግደሉ፡፡ ስለዚህ አማኝ የማይሆነውን ትገድላላችሁ፤ አማኝ የሚሆነውን ደግሞ ትተዋላች፡፡”[5]

እንግዲህ በዚህ ሐዲስ መሠረት ሙስሊሞች አማኝ ሳይሆን ሊያድግ እንደሚችል የተረዱትን ህፃን መግደል ይችላሉ ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ሙስሊም ያልሆኑ ህፃናትን ከወላጆቻቸው ነጥሎ በሙስሊሞች መካከል እንዲያድጉ የማድረግ እድል ከሌለ “ካፊሮች” ከሆኑት ወላጆቻቸው ጋር አንድ ላይ መግደል የተፈቀደ ነው፡፡ ለዚህ ነው ሙስሊም ሽብርተኞች በአዋቂዎች ስብስብ መካከል ህፃናት መኖራቸውን እያወቁ አደጋ የሚያደርሱት፡፡

በአንድ ወቅት ደግሞ ሙሐመድ የከሃዲያንን ወይንም ደግሞ መድብለ አማልክትን የሚያመልኩ ሰዎችን ሴቶች እና ሕፃናት መግደል ይቻል እንደሆን ተጠይቀው ነበር፡፡ እርሳቸውም ሲመልሱ “እኔ ልክ እንደ ወላጆቻቸው ነው የምቆጥራቸው” በማለት ነበር፡፡[6] በሌላ አባባል ወላጆች ከሃዲዎች ከሆኑ ልጆቻቸውን መግደል የተፈቀደ ነው ማለት ነው፡፡

ሙሐመድ ሴቶችንም በእንቶ ፈንቶ ምክንያቶች ያስገድሉ እንደነበር በእስላማዊ ምንጮች ውስጥ ተጠቅሶ እናያለን፡-

“ሁለት ልጃገረዶች፣ ፈርተና እና ጓደኛዋ ስለ መልእክተኛው ምፀታዊ የቅኔ መዝሙር ሲዘምሩ ስለነበር እንዲገደሉ አዘዙ፡፡”[7]

ሙሐመድን የሚተች ቅኔ በመናገሯ ምክንያት አስማ ቢንት ማርዋን የተባለች አንዲት ብልህ ሴት እንዲሁ ተገድላለች፡፡ አስማ የተገደለችው ልጇን እያጠባች ሳለች እንደሆነ እስላማዊ ምንጮች ዘግበዋል፡፡[8] ነቢዩ ለአረጋዊያንም የሚያዝን ልብ አልነበራቸውም፡፡ አቡ አፋክ በመባል የሚታወቅ እድሜው 120 እንደነበር የተነገረ በጣም የሸመገለ አይሁዳዊ ሰው ነበር፡፡ ይህ ሰው የሙሐመድን ነቢይነት በጥርጣሬ ከሚመለከቱ ሰዎች መካከል አንዱ ነበር፡፡ በሰይፍ ተወግቶ እንዲገደል ተደረገ፡፡[9]

ተከታዮቹ የቁርኣን ጥቅሶች ሙስሊሞች ጎረቤቶቻቸው የሆኑትን የሌሎች እምነቶች ተከታዮች በመዋጋት እንዲያስጨንቁና ለእስላማዊ ሕግጋት እንዲያስገዙ ያበረታታሉ፡-

“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! እነዚያን በአቅራቢያችሁ ያሉትን ከሓዲዎች ተዋጉ፡፡ ከእናንተም ብርታትን ያግኙ፡፡ አላህም ከሚጠነቀቁት ጋር መኾኑን ዕወቁ፡፡” (የንስሐ ምዕራፍ 9፡123)

“አንተ ነቢዩ ሆይ! ከሓዲዎችንና መናፍቃንን ታገል፡፡ በእነሱም ላይ ጨክን፡፡ መኖሪያቸውም ገሀነም ናት፡፡ መመለሻይቱም ከፋች፡፡” (የንስሐ ምዕራፍ 9፡73)

“የተከበሩትም ወሮች ባለቁ ጊዜ አጋሪዎቹን በአገኛችሁባቸው ስፍራ ግደሉዋቸው፡፡ ያዙዋቸውም፣ ክበቡዋቸውም፣ ለእነሱም (መጠባበቅ) በየመንገዱ ተቀመጡ፡፡ ቢጸጸቱም፣ ሶላትንም በደንቡ ቢሰግዱ፣ ግዴታ ምጽዋትንም ቢሰጡ መንገዳቸውን ልቀቁላቸው፡፡ አላህ መሓሪ አዛኝ ነውና፡፡” (የንስሐ ምዕራፍ 9፡5)

“ሁከትም እስከማትገኝ ሃይማኖትም ሁሉ ለአላህ ብቻ እስከሚኾን ድረስ ተጋደሏቸው፡፡ ቢከለከሉም አላህ የሚሠሩትን ሁሉ ተመልካች ነው፡፡” (የጦር ዘረፋዎች ምዕራፍ 8፡39)

በእስላማዊ ትውፊቶች ውስጥ የሚከተለው ዘገባ ሰፍሮ እናገኛለን፡

“ኢብን ዑመር እንዳስተላለፈው የአላህ መልእክተኛ እንዲህ ብለዋል፤ ሰዎች ከአላህ በስተቀር ሊመለክ የሚገባው እንደሌለና ሙሐመድም ደግሞ መልእክተኛው መሆኑን እስኪመሰክሩ ድረስ እንዲሁም ሶላትን ደንቡን ጠብቀው እስኪሰግዱ ድረስና ዘካትን እስኪሰጡ ድረስ እንድዋጋቸው (በአላህ) ታዝዣለሁ፡፡ ይህንን የሚያደርጉ ከሆነ በእስልምና ሕግ ከተደነገገው በስተቀር ሕይወታቸውንና ንብረታቸውን ከእኔ ይታደጋሉ፤ ድርሻቸውም በአላህ ይታሰብላቸዋል፡፡”[10]

“ነቢዩ ‹ማንኛውንም እስልምናን ለቆ የሚወጣ ሰው ግደሉት› ብለዋል፡፡”[11]

ቁርኣን ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎች ከፍጥረት ሁሉ ክፉ እንደሆኑ ይናገራል፡-

“እነዚያ ከመጽሐፉ ሰዎች የካዱት፣ አጋሪዎቹም በገሀነም እሳት ውስጥ ናቸው፤ በውስጧ ዘውታሪዎች ሲኾኑ እነዚያ እነርሱ ከፍጥረት ሁሉ ክፉ ናቸው፡፡” (የግልፅ አስረጅ ምዕራፍ 98፡6)

ትክክለኛ ሙስሊሞች ያልሰለሙ ቤተሰቦቻቸውን እንኳ ወዳጅ የማያደርጉ መሆናቸውን ቁርኣን እንዲህ በማለት ይናገራል፡-

“በአላህና በመጨረሻው ቀን የሚያምኑትን ሕዝቦች አላህንና መልክተኛውን የሚከራከሩትን ሰዎች፤ አባቶቻቸው፣ ወይም ልጆቻቸው፣ ወይም ወንድሞቻቸው፣ ወይም ዘመዶቻቸው ቢኾኑም እንኳ የሚወዳጁ ኾነው አታገኛቸውም፡፡ እነዚያ በልቦቻቸው ውስጥ እምነትን ጽፏል፡፡ ከእርሱም በኾነ መንፈስ ደግፏቸዋል፡፡” (የመከራከር ምዕራፍ 58፡22)

በዚህ መሠረት ሙስሊም ያልሆኑትን ቤተሰቦቹን መጥላት ያልቻለ ሰው የእስልምናን መንፈስ አልተቀበለም፡፡

ክርስቲያኖችንና አይሁድን ስለ መጥላት እስላማዊ ትውፊት እንዲህ ይላል፡-

“ነቢዩ (የአላህ ሰላምና በረከት በእሳቸው ላይ ይሁንና) እንዲህ ብለዋል ‹አይሁድን ወይንም ክርስቲያኖችን ቀድማችሁ ሰላም አትበሉ፡፡ በመንገድ ላይ ቢመጡባችሁ ወደ ጠባቡ የመንገድ ጠርዝ ግፏቸው፡፡›”[12]

እንዲሁም በቁርኣን ውስጥ የእርግማንን ቃላት በክርስቲያኖችና በአይሁድ ላይ ሲናገሩ እንመለከታለን፡-

“አይሁድ ዑዘይር የአላህ ልጅ ነው አለች፡፡ ክርስቲያኖችም አልመሲሕ የአላህ ልጅ ነው አሉ፡፡ ይህ በአፎቻቸው (የሚናገሩት) ቃላቸው ነው፡፡ የእነዚያን ከነሱ በፊት የካዱትን ሰዎች ቃል ያመሳስላሉ፡፡ አላህ ያጥፋቸው፡፡ (ከእውነት) እንዴት ይመለሳሉ!” (የንስሐ ምዕራፍ 9፡30)

ሙሐመድ ሕይወታቸው ከማለፉ በፊት የተናገሩት የመጨረሻው ንግግራቸው አይሁድንና ክርስቲያኖችን መርገም እንደነበር እስላማዊ ትውፊቶች ይናገራሉ፡:

“አይሻና አብዱላህ እንደዘገቡት ፡ የአላህ ምልእክተኛ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁንና) የመጨረሻ እስትንፋሳቸውን ሊተነፍሱ በነበሩበት ጊዜ ፊታቸውን በአንሶላው ሸፈኑ፤ ትንሽ ከተረጋጉ በኋላ ፊታቸውን ገለጡና በዚያ ሁኔታ እያሉ እንዲህ አሉ ‹የሐዋርያቶቻቸውን መቃብሮች እንደ ፀሎት ቦታ በመጠቀማቸው በአይሁድና በክርስቲያኖች ላይ እርግማን ይሁን፡፡› (ተከታዮቻቸውንም) (አይሁድና ክርስቲያኖች) የሚያደርጉትን ነገር እንዳያደርጉ አስጠንቅቀዋል፡፡”[13]

ተከታዩ ጥቅስ ሙሐመድና ትምህርታቸውን የተቀበሉ ሰዎች ሙስሊም ባልሆኑ ሰዎች ላይ ጨካኞች እንደሚሆኑ ይናገራል፡-

“የአላህ መልክተኛ ሙሐመድ እነዚያም ከእርሱ ጋር ያሉት (ወዳጆቹ) በከሓዲዎቹ ላይ ብርቱዎች በመካከላቸው አዛኞች ናቸው፡፡” (አገር የመክፈት ምዕራፍ 48፡29)

ይህ ጥቅስ በአረብኛ ሲነበብ ሙሐመድና ተከታዮቻቸው “በካፊሮች” ላይ ምህረት የለሽ ጨካኞች (Ruthless) እና እርስ በእርሳቸው ደግሞ የሚተዛዘኑ መሆናቸውን የሚናገር ነው፡፡ በሚከተለው ጥቅስ ውስጥ ደግሞ “በካፊሮች” ላይ መጨከን የአላህ ትእዛዝ መሆኑን እናያለን፡-

“አንተ ነቢዩ ሆይ! ከሓዲዎችንና መናፍቃንን ታገል፡፡ በእነሱም ላይ ጨክን፡፡ መኖሪያቸውም ገሀነም ናት፡፡ መመለሻይቱም ከፋች፡፡” (የንስሐ ምዕራፍ 9፡73)

በአንድ ወቅት የተወሰኑ ሰዎች ወደ ሙሐመድ በመምጣት እስልምናን ተቀበሉ፡፡ ሙሐመድም በደህና አስተናገዷቸው፡፡ የመዲና የአየር ሁኔታ ስላልተስማማቸው ወደ ግመል መንጋ በመሄድ ወተታቸውንና ሽንታቸውን ለመድኃኒትነት እንዲጠጡ አዘዟቸው፡፡ ሰዎቹ ከተሻላቸው በኋላ የሙሐመድን እረኛ በመግደል ግመሎቹን ወስደው ሄዱ፡፡ ሙሐመድም ጠባቂዎቹን በመላክ ተከታትለው ይዘዋቸው እንዲመጡ አደረጉ፡፡ ከዝያም “ዓይን ስለ ዓይን ጥርስ ስለ ጥርስ” በሚለው ትእዛዝ መሠረት ሳይሆን ለመስማት በሚዘገንን ሁኔታ ቀጧቸው፡፡ ቡኻሪ የተሰኙት የትውፊት ዘጋቢ እንዲህ በማለት ጽፈዋል፡-

“(ነቢዩ) እጆቻቸውና እግሮቻቸው እንዲቆረጡ አዘዙ፤ ተቆረጡም፡፡ ዓይኖቻቸውም በጋለ ብረት ተጠብሶ እንዲጠፋ ተደረገ፡፡ ከዝያም እስኪሞቱ ድረስ በአል ሀራ (ፀሐያማ የሆነ የመዲና ደረቅ ቦታ) ላይ ተጣሉ፡፡ ውኃ በጠየቁ ጊዜ ምንም ውኃ አልተሰጣቸውም ነበር፡፡”[14]

በሚከተለው ሐዲስ መሠረት ነቢዩ ሙሐመድ ለገንዘብ ብለው ሰዎችን ያሰቃዩ እንደነበር እናያለን፡፡ በሐዲሱ ውስጥ የተጠቀሰው ሰው በኸይበር የሚገኙ አይሁድ መሪ የነበረ ወጣትና አዲስ ሙሽራ ነበር፡፡ ሙሐመድ ካስገደሉት በኋላ መልከመልካም የ17 ዓመት ወጣት የነበረችውን ሰፊያ የተሰኘች ሚስቱን ለራሳቸው ወስደዋል፡፡ ሐዲሱ እንዲህ ይነበባል፡-

“ነቢዩ ኪናና የተባለውን ሰው በተመለከ ለዙባይር እንዲህ የሚል ትእዛዝ ሰጡ ‹በውስጡ የደበቀውን ሁሉ እስኪያወጣ ድረስ አሰቃየው፡፡› ስለዚህ ዙባይር ኪናና ለሞት እስኪቃረብ ድረስ ደረቱ ላይ እሳት አስቀመጠበት፡፡ ከዚያም ነቢዩ ለመስለማህ አሳልፈው ሰጡት፡፡ እርሱም አረደው፡፡”[15]

ሙሐመድ ሰዎች በእሳት እንዳይቃጠሉ እንደከለከሉ የሚናገሩ ሐዲሶች አሉ ነገር ግን ደግሞ ሰዎች በእሳት እንዲቃጠሉ ያዘዙባቸው ቦታዎችም አሉ፡፡[16]

ሌላው እጅግ አሰቃቂና ለመስማት የሚዘገንን የነቢዩ ሙሐመድና የተከታዮቻቸው የጭካኔ ታሪክ አል-ጦበሪ እና ኢብን ኢስሐቅ በጻፏቸው የሙሐመድ ታሪኮች ውስጥ ይገኛል፡-

“የ80 ዓመት ዕድሜ ባለጠጋ የሆነች ትክክለኛ ስሟ ፋጢማ ቢንት ሩቢያዐ የተሰኘ ኡም ቂርፋ የምትባል ሴት ነበረች፡፡ ሙሐመድን የሚተች ግጥም በማዘጋጀትም ትደግም ነበር፡፡ 13 ወንዶች ልጆች የነበሯት ሲሆን ሁሉም ጎልማሶችና የአይሁድ ጎሣ መሪዎች ነበሩ፡፡ በዘይድ የሚመራ አጥቂ ቡድን በረመዳን ወቅት በኡም ላይ ዘመተ፡፡ በዚያን ጊዜ ኡም አሳቃቂ አሟሟት ሞተች፡፡ ዘይድ እግሮቿን በገመድ አድርጎ በሁለት ግመሎች መካከል አሰራት፡፡ በተቃራኒ አቅጣጫዎችም እንዲሄዱ አደረገ፤ እርሷም ለሁለት ተሰነጠቀች፡፡ በጣም ያረጀች ሴት ነበረች፡፡ ከዝያም የኡምን ልጅና አብዳላን ወደ ነቢዩ አመጧቸው፡፡ የኡም ልጅ፣ የማረካት የሰላማህ ንብረት ሆና ነበር፡፡ ሙሐመድም ሰላማህን ስለ እርሷ ጠየቁት፡፡ ሰላማህም እርሷን ሰጣቸው፡፡”[17]

ዋና ዋና የሚባሉት እስላማዊ ምንጮች ስለ ነቢዩ ሙሐመድና ስለ ተከታዮቻቸው ከላይ የተባሉትን እውነታዎች የሚገልጡ ከሆነ በሙሐመድ የተሰበከውና የተኖረው ትክክለኛው እስልምና የሰላም ሃይማኖት መሆኑን ለመናገር የሚያስደፍር መሠረት የለንም፡፡

[1] Sahih Al-Bukhari; Volume 4, book 52, Number 220

[2] Sahih Muslim; Book 004, Number 1062, 1063, 1066, 1067

[3] Sunan Abu Dawud; 14:2665; 38:4390; Sahih Al Bukhari 4:52:280

[4] Tafsir Ibn Kathir – The Campaign against Banu Qurayzah www.tafsir.com

[5] Sahih Muslim 4457

[6] Sahih Muslim; 4322; Sahih Al Bukhari 52:256

[7] Guillaume. The Life of Muhammad; p. 819

[8] Guillaume. The Life of Muhammad; pp. 675-676; Ibn Sa’d. Kitab al-tabaqat al-kabir pp. 30-31; Ibn Sa’d al-Baghdadi. The Book of the Major Classes Vol. 2, pp. 32

[9] Kitab al-Maghazi; translated by Faizer R., Ismail A., & Tayob, A. K. (2011); Guillaume. The Life of Muhammad; pp.86-87

[10] Sahih Al-Bukhari; Vol. 1 Book 2, Number 24

[11] Sahih al-Bukhari, 52:260; 83:37; 84:57; 89:271; 84:58; Abu Dawud, 4346

[12] Sahih Muslim, 2167; Sahih al-Bukhari Book 25, Number 5389 በተጨማሪም ኢማም አን-ነወዊ፡፡ ሪያዱ ሷሊሒን፤ ከሐዲስ ቁጥር 811-1896፣ ቅፅ 2፤ ትርጉም በሐሰን ታጁ፣ ገፅ 42 ይመልከቱ

[13] Sahih Muslim; 1082; Sahih Al-Bukhari; 2:23:472

[14] Sahih Al-Bukhari; 7:71:623; 5:59:505; 1:4:234; 4:52:261; Sahih Muslim; 16:4131; 16:4130; 16:4132; 16:4134; Abu Dawud; 38:4356; 36:4357

[15] Al-Tabari; Vol. 8, p. 122

[16] Sahih Al-Bukhari; 11:626; Guillaume. The Life of Muhammad; p. 316

[17] Al-Tabari; Vol. 8, p.96; Guillaume. The Life of Muhammad; pp. 664-665

 

እስልምናና ሽብርተኝነት