ያሕዌ አምላካችን ሊያድነን መጥቷል!
የሚልክያስ ትንቢትና የሙስሊም ሰባኪያን ስሁት ሙግት
ሰለምቴ ነኝ ባዩ ሙስሊም ሰባኪ እንደተለመደው ከአርዮሳውያንና ዩኒቴርያን ትምህርቶች በቀዳቸው ስሁት ሙግቶች በመጠቀም የክርስቶስን አምላክነት ለማስተባበልና እስላማዊ እምነቱን ለማጽደቅ ጥረት አድርጓል፡፡ ጸሐፊው የጠቀሳቸውን ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ራሳቸው እንዲናገሩ ከመፍቀድ ይልቅ የክርስቶስን አምላክነት ከሚክድ ቅድመ ግንዛቤው በመነሳት በተሳሳተ መንገድ ተርጉሟቸዋል፡፡ የቅዱሳት መጻሕፍትን አጻጻፍና ታሪካዊ ዳራ ባላገናዘበ መንገድም ስህተቶችን ሲፈልግ ይታያል፡፡ በዚህ ጽሑፍ የዚህን ሰው ስሁት ትርጓሜዎች እናስተካክላለን፣ ክርስቶስ ጌታችንም እኛን ለማዳን ከሰማይ የወረደ ያሕዌ መሆኑን በቅዱሳን መጻሐፍት ማስረጃዎች እናረጋግጣለን፡፡ ይህንን ጽሑፍ የሚያነቡ ወገኖች ቅዱሳት መጻሕፍት ስለ ክርስቶስ አምላክነት የሚሰጡትን የማያወላዳ ምስክርነት እንደሚያስተውሉና ይህንን ሰው ከመሳሰሉ ቃለ እግዚአብሔርን ከሚያጣምሙ ሐሳውያን እንደሚጠነቀቁ ተስፋ እናደርጋለን፡፡
ጸሐፊው በመግቢያው ስህተት ያዘለ አንድ የቁርኣን ጥቅስ በመጥቀስ ይጀምራል፡-
አብዱል
መንገድ ጠራጊ
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ፥ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።
5፥17 እነዚያ አላህ እርሱ የመርየም ልጅ አልመሲሕ ነው ያሉ በእርግጥ ካዱ፡፡
መልስ
ይህ የቁርኣን ጥቅስ ክርስቲያናዊውን አስተምሕሮ በተሳሳተ መንገድ የሚያቀርብ በመሆኑ ሁሉን አዋቂ ከሆነው አምላክ ዘንድ ሊሆን አይችልም፡፡ በሌላ ጽሑፍ እንደገለፅነው “አላህ” የሚለው እግዚአብሔርን ለማመልከት የገባ የአረብኛ ቃል ነው ብንል “ክርስቶስ እግዚአብሔር ነው” ማለት እና “እግዚአብሔር ክርስቶስ ነው” ማለት ከፍተኛ የሆነ ልዩነት አላቸው፡፡ በክርስትና አስተምህሮ መሠረት እግዚአብሔር በመለኮቱ ፍጹም አንድ ቢሆንም ነገር ግን በአካል ነጠላ ስላልሆነ ለአብ እና ለመንፈስ ቅዱስ ዕውቅናን በመንፈግ “እግዚአብሔር ክርስቶስ ነው” የሚለው አባባል ከክርስትና ትምሕርት ጋር የሚጣጣም አይደለም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም ምንም ዓይነት ድጋፍ የለውም፡፡ የአብ እና የመንፈስ ቅዱስን ሕልውና በመካድ ኢየሱስ ብቸኛው የእግዚአብሔር አካል እንደሆነ የሚያስተምረው የሰባልዮስ ትምህርት ሙሐመድ ከመወለዱ ከሦስት ክፍለ ዘመናት በፊት በቤተክርስቲያን ተወግዟል፡፡ ሙሐመድ “ነቢይ” ተብሎ በምድረ አረብ ከመነሳቱ በፊት የተጻፉ ኢየሱስ እግዚአብሔር መሆኑን መናገር ትክክል መሆኑን ነገር ግን እግዚአብሔር ኢየሱስ መሆኑን መናገር ስህተት መሆኑን የሚገልፁ ክርስቲያናዊ ጽሑፎች እንዳሉ ኒል ሮቢንሰን የተሰኘ ሙስሊም ጸሐፊ በመጽሐፉ ውስጥ ገልጿል (Neal Robinson, Christ in Islam and Christianity, State University of New York Press, 1991, p. 197) ፡፡ ቁርኣን እውን ከፈጣሪ ዘንድ ከሆነ ክርስቲያናዊ አስተምህሮን እንዲህ በተሳሳተ መንገድ ማቅረብ አልነበረበትም፡፡
አብዱል
የሥላሴ አማንያን ከባይብል ኢየሱስን አምላክ ለማድረግ የማይቆፍሩት ጉድጓድ፣ የማይፈነቅሉት ድንጋይ፣ የማይደረምሱት መሬት የለም። ኢሳይያስ ላይ ያህዌህ መንገድ እንደሚጠረግለት ተነግሮ አዲስ ኪዳን ላይ ግን መጥምቁ ዮሐንስ መንገድ የጠረገው ለኢየሱስ ስለሆነ “ኢየሱስ ያህዌህ ነው” ብለው ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል፦
መልስ
መጽሐፍ ቅዱስ መሲሁ ኢየሱስ አምላክ መሆኑን በበርካታ ስፍራዎች ላይ ይናገራል፡- (ዮሐ. 1፡1፣ 20፡28 ሮሜ 9፡5፣ ቲቶ 2፡13፣ ዕብራውያን 1፡8-10)፤ ስለዚህ ኢየሱስን አምላክ ለማድረግ የምንቆፍረው ጉድጓድ፣ የምንፈለቅለው ድንጋይም ሆነ የምንደረምሰው መሬት የለም፡፡ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን በግልፅ “አምላክ” ብሎት ሳለ አምላክነቱን ለማስተባበል የሞት ሽረት ትግል እያደረጉ የሚገኙት አምላክነቱን የሚክዱ ወገኖች ናቸው፡፡
አብዱል
ኢሳይያስ 40፥3 የአዋጅ ነጋሪ ቃል፦ “የያህዌን መንገድ በምድረ በዳ ጥረጉ፥ ለአምላካችንም ጐዳና በበረሀ አስተካከሉ”።
ማርቆስ 1፥2 “እነሆ መንገድህን የሚጠርግ መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ፥ የጌታን መንገድ አዘጋጁ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ ተብሎ በነቢዩ በኢሳይያስ እንደ ተጻፈ”።
እዚህ ጥቅስ ላይ ብዙ ችግር አለ። አንደኛ “በምድረ በዳ የሚጮህ ሰው ድምፅ” የሚለው ኢሳይያስ ላይ የለም።
መልስ
የትርጉም ጉዳይ እንጂ “በምድረ በዳ የሚጮህ ሰው ድምፅ” የሚለው ኢሳይያስ 40፡3 ላይ ይገኛል፡፡ አንተ ያየኸው የአማርኛውን ትርጉም ብቻ ነው፡፡ የተለያዩ የእንግሊዘኛ ትርጉሞችን ስንመለከት ኢሳይያስ 40፡3ን በዚህ መንገድ ተርጉመውት እናገኛለን፡-
The voice of him that crieth in the wilderness, Prepare ye the way of the LORD, make straight in the desert a highway for our God. (King James Bible)
The voice of one crying in the wilderness: “Prepare the way of the LORD; Make straight in the desert A highway for our God. (New King James Version)
The voice of one who calls out in the wilderness, “Prepare the way of the LORD. Make his roads straight. (New Heart English Bible)
A voice cries out in the desert: “Clear a way for the LORD. Make a straight highway in the wilderness for our God. (GOD’S WORD® Translation)
The voice of him that cries in the wilderness, Prepare you the way of the LORD, make straight in the desert a highway for our God. (King James 2000 Bible)
The voice of him that cries in the wilderness, Prepare you the way of the LORD, make straight in the desert a highway for our God. (American King James Version)
The voice of one crying in the desert: Prepare ye the way of the Lord, make straight in the wilderness the paths of our God. (Douay-Rheims Bible)
The voice of one crying in the wilderness: Prepare ye the way of Jehovah, make straight in the desert a highway for our God! (Darby Bible Translation)
The voice of him that crieth in the wilderness, Prepare ye the way of the LORD, make straight in the desert a highway for our God. (Webster’s Bible Translation)
A voice is crying — in a wilderness — Prepare ye the way of Jehovah, Make straight in a desert a highway to our God. (Young’s Literal Translation)
ከላይ የሚገኙት ትርጉሞች ወንጌላዊው ማርቆስ ኢሳይያስ 40፡3 ላይ የሚገኘውን ጥቅስ ካስቀመጠበት መንገድ ጋር በሚስማማ ሁኔታ የተረጎሙ ሲሆን ሌሎች ደግሞ በአማርኛ ነባር ትርጉም ውስጥ ከምናነበው ጋር በሚስማማ መንገድ ተርጉመውት እናገኛለን፡፡ ይህም ከዋናው ቋንቋ በሁለቱም መንገዶች መተርጎም እንደሚቻል ያሳያል፡፡ ወንጌላዊው ማርቆስ በምንጭነት የተጠቀመው የሰብዓ ሊቃናቱን ትርጉም ሲሆን እነርሱ ዕብራይስጡን የተረጎሙት በዚያ መንገድ ነው፡-
φωνὴ βοῶντος ἐν τῇ ἐρήμῳ ἑτοιμάσατε τὴν ὁδὸν κυρίου εὐθείας ποιεῗτε τὰς τρίβους τοῦ θεοῦ ἡμῶν
ፎኔ ቦኦንቶስ ኤን ቴ ኤሬሞ ኤቶይማሳቴ ቴን ኦዶን ኩርዩ ኤውቴይያስ ሞኢኤይቴ ታስ ትሪቦውስ ቶው ቴው ሄሞን
ይህም ሲተረጎም እንዲህ ነው፡- The voice of one crying in the wilderness, Prepare ye the way of the Lord, make straight the paths of our God. (Brenton Septuagint Translation)
“የጌታን መንገድ አዘጋጁ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ፡፡”
ስለዚህ አጠቃላይ መረጃዎችን ሳያገናዝቡ ለትችት መጣደፍ ለስህተት ይዳርጋል፡፡
አብዱል
ሁለተኛ “እነሆ መንገድህን የሚጠርግ መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ” የሚለው “በነቢዩ በኢሳይያስ እንደ ተጻፈ” ይላል እንጂ ኢሳይያስ አልተጻፈም። የተጻፈው ሚልክያስ ላይ ነው፦
ሚልክያስ 3፥1 “እነሆ መልእክተኛዬን እልካለሁ፥ መንገድንም በፊቴ ያስተካክላል”።
መልስ
ወንጌላት በተጻፉበት ዘመን የአበይት ነቢያትና የደቂቃን ነቢያት ጥቅሶችን በአንድነት ከጠቀሱ በኋላ ከአበይት ነቢያት ወገን የሆነውን ስም ብቻ መጥቀስ የተለመደ ነበር፡፡ ነጣጥሎና አነጣጥሮ መጥቀስ የተጀመረው ከዘመነ ጥቅልል ብራና ወደ ዘመነ ጥራዝ ሽግግር ከተደረገ በኋላ ነበር፡፡ ወንጌላዊው ማቴዎስም ከነቢዩ ኤርምያስና ከነቢዩ ዘካርያስ ከጠቀሰ በኋላ ኤርምያስን ብቻ በስም ሲጠቅስ እናገኛለን (ማቴዎስ 27፡9-10)፡፡ አንዳንድ የኋለኛው ዘመን የእጅ ጽሑፎች ይህንን ሁኔታ ባለመረዳት “በኢሳይያስ” የሚለው የግልበጣ ስህተት መስሏቸው “በነቢያት” በሚል ቃል የመተካት ሙከራ ቢያደርጉም ትክክለኛው ንባብ “በኢሳይያስ” የሚል መሆኑን ሊቃውንት በአንድ ድምፅ ይስማሙበታል፡፡ ስለዚህ አጠቃቀሱ የትኛው ትንቢት በማን እንደተነገረ ካለማወቅ የመነጨ ባለመሆኑና በዘመኑ የነበረውን አጠቃቀስ የተከተለ በመሆኑ በስህተትነት የሚፈረጅ አይደለም፡፡ (Gleason L Archer. Encyclopedia of Bible Difficulties; p. 350)፡፡ ተመሳሳይ ቃላትንና ፅንሰ ሐሳቦችን የያዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን አንድ ላይ በማዋሓድ በዚህ መንገድ መጥቀስ የቆየ የአይሁድ ሊቃውንት ልማድ ሲሆን ገዘራ ሸዋህ በመባል ይታወቃል፡- (Craig S. Keener. A Commentary on the Gospel of Matthew; William B. Eerdmans Publishing Company, 1999, p. 675)፡፡
አብዱል
ሦስተኛ በትንቢቱ ላይ “በፊቴ” እንጂ “በፊትህ” የሚል የለም።
መልስ
ማርቆስ የሚልክያስን ትንቢት የጠቀሰው ቃል በቃል ሳይሆን በራሱ መንገድ (Paraphrasing) ነው፡፡ ይህም በዘፈቀደ ሳይሆን አሁንም ገዘራ ሸዋህ የተሰኘውን የአይሁድ አጠቃቀስ በመጠቀም ነው፡፡ መልእክተኛውን በልጁ ፊት የላከው አብ መሆኑን ግልፅ ለማድረግ በዘጸአት 23፡20 ላይ የሚገኘውን ሚልክያስ 3፡1 ላይ ለሚገኘው እንደ ማብራርያ አስገብቷል፡-
“በመንገድ ይጠብቅህ ዘንድ ወዳዘጋጀሁትም ስፍራ ያገባህ ዘንድ፥ እነሆ፥ እኔ መልአክን በፊትህ እሰድዳለሁ።” (ዘጸ. 23፡20)
“እነሆ፥ መልእክተኛዬን እልካለሁ፥ መንገድንም በፊቴ ያስተካክላል” (ሚልክያስ 3፡1)
ሁለቱ ጥቅሶች ማርቆስ በተጠቀመው የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ተመሳሳይ ናቸው፡-
καὶ ἰδοὺ ἐγὼ ἀποστέλλω τὸν ἄγγελόν μου πρὸ προσώπου σου (ዘጸ. 23፡20)
ካይ ኢዱ ኢጎ አፖስቴሎ ቶን አንጌሎን ሙ ፕሮ ፕሮሶፑ ሱ
ἰδοὺ ἐγὼ ἐξαποστέλλω τὸν ἄγγελόν μου καὶ ἐπιβλέψεται ὁδὸν πρὸ προσώπου μου (ሚልክያስ 3፡1)
ኢዶ ኢጎ ኤግዛፖስቴሎ ቶን አንጌሎን ሙ ካይ ኦፒብሌፕሴታይ ኦዶን ፕሮ ፕሮሶፑ ሙ
በግሪክ ቋንቋ መልአክና መልእክተኛ አንድ ቃል መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ወንጌላዊው ማርቆስ ያደረገው እግዚአብሔር በሕዝቡ ፊት መንገዳቸውን የሚያቀና መልአክ እንደሚልክ በዘጸአት ላይ የተናገረውን በመውሰድ ሚልክያስ ውስጥ እግዚአብሔር መንገዱን የሚጠርግ መልእክተኛን እንደሚልክ የተናገረውን ማብራራት ነው፡፡ ይህም በዘመኑ ተቀባይነት የነበረው የአይሁድ ሊቃውንት የቅዱሳት መጻሕፍት አጠቃቀስ ሲሆን ጌታችን ኢየሱስ ራሱ ሚልኪያስ 3፡1ን ሲጠቅስ በተመሳሳይ መንገድ ጠቅሷል (ሉቃስ 7፡27፣ ማቴዎስ 11፡10)፡፡ የረበናተ አይሁድ ሐተታዎችን ስንመለከት ዘጸአት 23፡20 ላይ የሚገኘውን ቃል ከሚልክያስ 3፡1 ጋር በማቀናጀት ይጠቅሱ እንደነበር እንገነዘባለን፡፡ (William L. Lane. The Gospel according to Mark: The English Text With Introduction, Exposition, and Notes; 2nd edition, 1974, p. 45)፡፡ ስለዚህ አሁንም ችግሩ ከማርቆስ ሳይሆን ከትችት አቅራቢው የዕውቀት እጥረት ነው፡፡
አብዱል
አራተኛ ሙግቱን ጠበብ አርገነው አብ ለወልድ በሁለተኛ መደብ “በፊትህ” ካለ መልእክተኛውን መንገድ የሚጠርገው በሚልክያስ ላይ “በፊቴ” ላለው አብ እና በማርቆስ ላይ “በፊትህ” ለተባለው ለወልድ ነው። ምክንያቱም አብ ለወልድ “መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ” ብሎ መንገድ ጠራጊውን ዮሐንስን ልኳል፦
ዮሐንስ 1፥6 “ከእግዚአብሔር የተላከ ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ”።
ሉቃስ 1፥76 “ደግሞም አንተ ሕፃን ሆይ፥ የልዑል ነቢይ ትባላለህ፥ መንገዱን ልትጠርግ በጌታ ፊት ትሄዳለህና”።
ዮሐንስ የልዑል ነቢይ ከሆነ ልዑል የተባለው አብ እንጂ ኢየሱስ አይደለም፥ ኢየሱስ የልዑል ልጅ እንጂ ልዑል አልተባለም።
መልስ
የሚልክያስን ትንቢት ደግመን እናንብብ፡-
“እነሆ፥ መልእክተኛዬን እልካለሁ፥ መንገድንም በፊቴ ያስተካክላል፤ እናንተም የምትፈልጉት ጌታ በድንገት ወደ መቅደሱ ይመጣል፤ የምትወዱትም የቃል ኪዳን መልእክተኛ፥ እነሆ፥ ይመጣል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፡፡ ነገር ግን እርሱ እንደ አንጥረኛ እሳትና እንደ አጣቢ ሳሙና ነውና የሚመጣበትን ቀን መታገሥ የሚችል ማን ነው? እርሱስ በተገለጠ ጊዜ የሚቆም ማን ነው?”
See, I will send my messenger, who will prepare the way before my face. Then suddenly the Lord you are seeking will come to HIS temple; the messenger of the covenant, whom you desire, will come,’ says Yahweh of hosts.”
በጥቅሱ ውስጥ እንደተባለው ያሕዌ እግዚአብሔር መንገድን በፊቱ የሚያስተካክል መልእክተኛ ይልካል፡፡ በማርቆስ ፍቺ መሠረት ያሕዌ እግዚአብሔር በልጁ ፊት መንገድን የሚያስተካክል መልእክተኛ ልኳል፡፡ ሚልክያስ ያሕዌ እግዚአብሔር እንደሚመጣ የተናገረውን ማርቆስ ልጁ ይመጣል በሚል መረዳቱ በያሕዌ እግዚአብሔርና በልጁ መካከል የባሕርይ ልዩነት አለመኖሩን ያመለክታል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ራሱ እንደተናገረው፡- “አንተ ፊልጶስ፥ ይህን ያህል ዘመን ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቶአል፤ እንዴትስ አንተ፦ አብን አሳየን ትላለህ?” (ዮሐንስ 14፡9)፡፡ በያሕዌ እግዚአብሔር መምጣትና በልጁ መምጣት መካከል ልዩነት የለም ምክንያቱም ልጁ ራሱ የመለኮታዊ ባሕርዩ ተካፋይ ያሕዌ ነውና፡፡
በማስከተል ትንቢቱ በአካል የሚገለጠው ማን እንደሆነ ይናገራል፤ እርሱም የመቅደሱ ባለቤት የሆነው እስራኤላውያን የሚፈልጉት ጌታ ነው፡፡ ለመሆኑ እስራኤላውያን የመቅደሱ ባለቤትና ጌታችን የሚሉት ከያሕዌ ውጪ ማን ነው? ይህ የሚያመለክተው ከያሕዌ እግዚአብሔር ዘንድ የተላከው ልጁ በመለኮት ከእርሱ ጋር አንድ መሆኑን ነው፡፡
መጥምቁ ዮሐንስ የልዑል እግዚአብሔር ነቢይ መባሉና ይህ ማዕርግ የአብ መሆኑ ኢየሱስ ደግሞ ልጁ መሆኑ እውነት ነው፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ ማንም ባልተባለበት መንገድ “የልዑል እግዚአብሔር ልጅ” መባሉን ከቅዱሳት መጻሕፍት ማስተዋል ያስፈልገናል (ማርቆስ 12፡1-8፣ ዮሐንስ 1፡18፣ 1ዮሐንስ 4፡9)፡፡ ይህም ልጁ የአባቱ መለኮታዊ ባሕርይ አካልና የአምላካዊ ሥልጣን ባለቤት በመሆኑ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ አብ ሁሉ በሰማይና በምድር ቅዱሳን መላእክትን ጨምሮ በፍጥረት ሁሉ ላይ ሉኣዊ ሥልጣን ያለው መለኮት ነው፡-
“እርሱም መላእክትና ሥልጣናት ኃይላትም ከተገዙለት በኋላ ወደ ሰማይ ሄዶ በእግዚአብሔር ቀኝ አለ።” (1ጴጥሮስ 3፡22)
“እነዚህ በጉን ይወጋሉ፤ በጉም የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ስለ ሆነ እነርሱን ድል ይነሣል፥ ከእርሱም ጋር ያሉ የተጠሩና የተመረጡ የታመኑም ደግሞ ድል ይነሣሉ።” (ራዕይ 17፡14)
“በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና፤ ለአለቅነትና ለሥልጣንም ሁሉ ራስ በሆነ በእርሱ ሆናችሁ ተሞልታችኋል።” (ቆላስይስ 2፡9-10)
“ይህም ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፥ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል፡፡” (ቲቶ 2፡12-13)
ስለዚህ ኢየሱስ በመለኮቱ ከአብ ጋር አንድ በመሆኑ ልዑል ነው፡፡
አብዱል
ሲቀጥል ሉቃስ 1፥76 ላይ “ጌታ” የተባለው “አብ” ነው፥ ዐውደ-ንባቡ ላይ “በጌታ ፊት ሊያቆሙት ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት” ይላል፦
ሉቃስ 1፥32 እርሱ ታላቅ ይሆናል “የልዑል ልጅም” ይባላል።
ሉቃስ 2፥22 በጌታ ፊት ሊያቆሙት…ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት”።
ስለዚህ “መንገዱን ልትጠርግ በጌታ ፊት ትሄዳለህና” ሲል “ጌታ” የተባለው አብ ነው፥ ምክንያቱም ወልድን “በጌታ ፊት ሊያቆሙት ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት” ስለሚል። ዮሐንስ የአብ ማለትም ያያህዌን መንገድ እና የወልድ ማለትም የመሢሑን መንገድ ጠራጊ ነው።
መልስ
የተሟጋቹ አመክንዮ አብ ጌታ ስለተባለ ወልድ ጌታ ሊሆን አይችልም በሚል ስሁት ቅድመ ግንዛቤ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ አዲስ ኪዳን አብና ወልድን ለይቶ ለማሳየት አብን “እግዚአብሔር/አምላክ” (ቴዎስ) ወልድን ደግሞ “ጌታ” (ኩርዮስ) በማለት ነው የሚጠራው፡፡ ሁለቱም መለኮታዊ መጠርያዎች ሲሆኑ ቃላቱን በመደበኛነት ለአብና ለወልድ ተጠቅሟል፤ ነገር ግን መቶ በመቶ በተገደበ ሁኔታ አይደለም፡፡ ወልድ በአዲስ ኪዳን ውስጥ “ቴዎስ” የተባለባቸው የተወሰኑ ቦታዎች እንዳሉ ሁሉ አብም “ኩሪዮስ” የተባለባቸው የተወሰኑ ቦታዎች አሉ፡፡ አብ “ኩሪዮስ” ከተባለባቸው የአዲስ ኪዳን ጥቅሶች መካከል አንዱ ከላይ የተጠቀሰው ሉቃስ 2፡22 ነው፡፡ ነገር ግን በቅርበት ከሚገኘው አውድና ከታሪኩ ፍሰት እንደምንረዳው ሉቃስ 1፡76 ላይ ጌታ የተባለው ኢየሱስ እንጂ አብ አይደለም፡፡ ይህንንም ከተከታዩ ጥቅስ እንረዳለን፡-
“ማርያምም በዚያ ወራት ተነሥታ ወደ ተራራማው አገር ወደ ይሁዳ ከተማ ፈጥና ወጣች፥ ወደ ዘካርያስም ቤት ገብታ ኤልሳቤጥን ተሳለመቻት። ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ ፅንሱ በማኅፀንዋ ውስጥ ዘለለ፤ በኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ ሞላባት፥ በታላቅ ድምፅም ጮኻ እንዲህ አለች፦ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፥ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው። የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል? እነሆ፥ የሰላምታሽ ድምጽ በጆሮዬ በመጣ ጊዜ ፅንሱ በማኅፀኔ በደስታ ዘሎአልና። ከጌታ፤ የተነገረላት ቃል ይፈጸማልና ያመነች ብፅዕት ናት።” (ሉቃስ 1፡39-45)
የመጥምቁ ዮሐንስ እናት ኤልሳቤጥ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልታ ኢየሱስን “ጌታዬ” ስትለው እንመለከታለን፡፡ በወቅቱ በማህፀኗ ውስጥ የነበረው ዮሐንስም በማርያም ማህፀን ውስጥ ለነበረው ለጌታው ክብርን ሰጥቷል፡፡ አባቱ ዘካርያስ የዮሐንስን አገልግሎት በተመለከተ እንዲህ ብሏል፡-
“ደግሞም አንተ ሕፃን ሆይ፥ የልዑል ነቢይ ትባላለህ፥ መንገዱን ልትጠርግ በጌታ ፊት ትሄዳለህና…” (ሉቃስ 1፡76)
መጥምቁ ዮሐንስ መንገድ እየጠረገ በማን ፊት ነው የሄደው? ምንም ጥምዘዛና ወዲያ ወዲህ መዝለል ሳያስፈልገን መልሱ “በኢየሱስ ፊት” የሚል ነው፡-
“ሕዝቡም ሲጠብቁ ሳሉ ሁሉም በልባቸው ስለ ዮሐንስ፦ ይህ ክርስቶስ ይሆንን? ብለው ሲያስቡ ነበር፥ ዮሐንስ መልሶ፦ እኔስ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ነገር ግን የጫማውን ጠፍር መፍታት ከማይገባኝ ከእኔ የሚበረታ ይመጣል፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል፤ መንሹም በእጁ ነው፥ አውድማውንም ፈጽሞ ያጠራል፥ ስንዴውንም በጎተራው ይከታል፥ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል አላቸው።” (ሉቃስ 3፡15-17)
ዮሐንስ ስለ ክርስቶስ ማንነት እየተናገረ፣ ሕዝቡን ወደ ንስሐ እየጠራ እንዴት መንገዱን እንዳዘጋጀለት ልብ እንበል፡፡ ስለ ክርስቶስ የተናገራቸው ነገሮችም ለአምላክ ብቻ የሚነገሩ ናቸው፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ማጥመቅ የእግዚአብሔር ሥልጣን ነው (ኢዩኤል 2፡28-32)፡፡ ጻድቃንን ወደ መንግሥቱ ማስገባትና ኃጢአንን በማይጠፋ እሳት ማቃጠል ለፍጡር የሚቻል አይደለም፡፡ ነገር ግን ዮሐንስ ይህንን ሁሉ ስለ ክርስቶስ አለ፡፡ ወንጌላዊው ዮሐንስ የመጥምቁ ዮሐንስን መንገድ ጠራጊነት እንዲህ በማብራራት ያቀርብልናል፡-
“እርሱም፦ ነቢዩ ኢሳይያስ እንዳለ፦ የጌታን መንገድ አቅኑ ብሎ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ እኔ ነኝ አለ። የተላኩትም ከፈሪሳውያን ነበሩና፦ እንኪያስ አንተ ክርስቶስ ወይም ኤልያስ ወይም ነቢዩ ካይደለህ፥ ስለ ምን ታጠምቃለህ? ብለው ጠየቁት። ዮሐንስ መልሶ፦ እኔ በውኃ አጠምቃለሁ፤ ዳሩ ግን እናንተ የማታውቁት በመካከላችሁ ቆሞአል፤ እኔ የጫማውን ጠፍር ልፈታ የማይገባኝ፥ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ ይልቅ የሚከብር ይህ ነው አላቸው። ይህ ነገር ዮሐንስ ያጠምቅበት በነበረው በዮርዳኖስ ማዶ በቢታንያ በቤተ ራባ ሆነ። በነገው ዮሐንስ ኢየሱስን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ፦ እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ። አንድ ሰው ከእኔ በኋላ ይመጣል፥ ከእኔም በፊት ነበርና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል ብዬ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነው። እኔም አላውቀውም ነበር፥ ዳሩ ግን ለእስራኤል ይገለጥ ዘንድ ስለዚህ በውኃ እያጠመቅሁ እኔ መጣሁ። ዮሐንስም እንዲህ ብሎ መሰከረ፦ መንፈስ ከሰማይ እንደ ርግብ ሆኖ ሲወርድ አየሁ፤ በእርሱ ላይም ኖረ። እኔም አላውቀውም ነበር፥ ዳሩ ግን በውኃ አጠምቅ ዘንድ የላከኝ እርሱ፦ መንፈስ ሲወርድበትና ሲኖርበት የምታየው፥ በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው አለኝ። እኔም አይቻለሁ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ መስክሬአለሁ።” (ዮሐንስ 1፡23-34)
ከላይ እንዳነበብነው ዮሐንስ አስቀድሞ የመጣው መሲሁ ለእስራኤል ይገለጥ ዘንድ መንገድ ለማመቻቸት ነበር፡፡ ይህም በነቢያት አስቀድሞ እንደተነገረው ነው፡፡ ከታላቅነቱ የተነሳ “ክርስቶስ ይሆንን?” ተብሎ የተጠረጠረው መጥምቁ ዮሐንስ በኢየሱስ ፊት እጅጉን ራሱን ሲያዋርድና ኢየሱስ ከእርሱ በፊት የነበረ መሆኑን፣ በመንፈስ ቅዱስ እንደሚያጠምቅ እንዲሁም የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ሲመሰክር ይታያል፡፡ ኢየሱስ ሰው ብቻ ቢሆን ኖሮ ዮሐንስን የሚያህል የእግዚአብሔር ነቢይ እንዴት እንዲህ በፊቱ ራሱን ያዋርዳል? በስድስት ወር የሚበልጠው ሆኖ ሳለስ እንዴት ከእርሱ በፊት እንደነበረ ሊናገር ይችላል? በመንፈስ ቅዱስ ማጥመቅ የእግዚአብሔር ሥልጣን ሆኖ ሳለ እንዴት በመንፈስ ቅዱስ እንደሚያጠምቅ ይናገራል? ልጅነቱ እንደ ማንኛውም አማኝ የፀጋ ከሆነስ እንዴት ለይቶ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ይመሰክራል? የማይሆን ነው! ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ በነቢያት እንደተተነበየው በሥጋ የተገለጠ አምላክ ነው፡፡
አብዱል
አራት ቆጠራችሁ? አምስተኛ ደግሞ ብሉይ ላይ የተጠቀሰ ጥቅስ አዲስ ላይ ፍጻሜ ካገኘ ብሉይ ላይ ያለ ጥቅስ የአዲስ ኪዳኑ ማንነት ነው ተብሎ በአራት ነጥብ አይደመደምም። አንዳንድ ናሙና እስቲ እንይ፦
2 ሳሙኤል 7፥14 “እኔም አባት እሆነዋለሁ፥ እርሱም ልጅ ይሆነኛል፤ ክፉ ነገርም ቢያደርግ፥ ሰው በሚቀጣበት በትርና በሰው ልጆች መቀጫ እገሥጸዋለሁ”።
ዕብራውያን 1፥5 “ደግሞም፦ እኔ አባት እሆነዋለሁ እርሱም ልጅ ይሆነኛል” ያለው ከቶ ለማን ነው?።
“እኔ አባት እሆነዋለሁ እርሱም ልጅ ይሆነኛል” የሳሙኤል ዐውደ-ንባብ የሚናገረው ለንጉሥ ሰለሞን ነው፥ የዕብራውያን ጸሐፊ ለኢየሱስ ነው ይለናል። እና ኢየሱስ ብሉይ ላይ የነበረው ሰለሞን ነውን? እንደ እናንተ እምነት ኢየሱስ ያህዌህ ከሆነ ያህዌህ አምላክ እንዴት ፍጡሩን ሰለሞን ይሆናል? መልሱ፦ “ድርብ አጠቃቀም ነው” የሚል ነው፥ እንግዲያውስ ብሉይ ላይ የያህዌህ መንገድ ተብሎ አዲስ ላይ የጌታ መንገድ መባሉ “ድርብ አጠቃቀም ነው” በሚል ስሌትና ቀመር መረዳት ይቻላል።
ናሙናውን እንቀጥል፦
ሆሴዕ 11፥1-2 “እስራኤል ሕፃን በነበረ ጊዜ ወደድሁት፥ ልጄንም ከግብፅ ጠራሁት። አብዝቼ ብጠራቸው አጥብቀው ከፊቴ ራቁ፤ ለበኣሊምም ይሠዉ ነበር፥ ለተቀረጹ ምስሎችም ያጥኑ ነበር”።
ማቴዎስ 2፥14-15 “እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን በሌሊት ያዘና ከጌታ ዘንድ በነቢይ፦ “ልጄን ከግብፅ ጠራሁት” የተባለው እንዲፈጸም ወደ ግብፅ ሄደ፥ ሄሮድስም እስኪሞት ድረስ በዚያ ኖረ”።
“ልጄንም ከግብፅ ጠራሁት” የሆሴዕ ዐውደ-ንባብ የሚናገረው ለእስራኤል ሕዝብ ነው፥ የማቴዎስ ጸሐፊ ለኢየሱስ ነው ይለናል። ታዲያ ኢየሱስ ሲጠራ አጥብቆ ከአምላክ ፊት የራቀ ነውን? ለበኣሊምም ይሠዋ ነበርን? ለተቀረጹ ምስሎችም ያጥን ነበርን? ቅሉ ግን “ድርብ አጠቃቀም ነው” የሚል ነው፥ እንግዲያውስ ብሉይ ላይ የያህዌህ መንገድ ተብሎ አዲስ ላይ የጌታ መንገድ መባሉ “ድርብ አጠቃቀም ነው” በሚል ልክና መልክ መረዳት ይቻላል።
መልስ
በትንቢቶች ፍፃሜ ውስጥ ተምሳሌታዊነት (Typology) የሚባል ነገር አለ፡፡ ይህም ማለት በብሉይ ኪዳን ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ስብዕናዎችና ክስተቶች ከክርስቶስና ከሕይወቱ ጋር የሚመሳሰል ገፅታ አላቸው የሚል ነው፡፡ ከላይ የሚገኙት ጥቅሶች በዚያ መንገድ ጥቅም ላይ የዋሉ ናቸው፡፡ ነገር ግን ስለ መንገድ ጠራጊውና ስለ ያሕዌ መምጣት የተነገረው ተምሳሌታዊ ሳይሆን ቀጥታ ነው፡፡ ሙስሊሙ ተሟጋች ስለ ትንቢት ዓይነትና አፈጻጸም የዕውቀት እጥረት እንዳለበት ግልፅ ነው፡፡
አብዱል
ስድስተኛ “የያህዌህን መንገድ ማለት የያህዌህ ሕግ፣ ሥርዓት፣ ትእዛዝ፣ መርሕ እና ቃል ነው፦
መዝሙር 18፥21 “የያህዌህን መንገድ ጠብቄአለሁ፥ በአምላኬም አላመፅሁም”።
መዝሙር 18፥30 “የአምላኬ መንገድ ፍጹም ነው፥ የያህዌህን ቃል የነጠረ ነው፥ በእርሱ ለሚታመኑት ሁሉ ጋሻ ነው”።
ምሳሌ 10፥29 የያህዌህ መንገድ ያለ ነውር ለሚሄድ አምባ ነው፥ ጥፋት ግን ክፋትን ለሚያደርጉ።
ኤርምያስ 5፥4 እኔም፦ የያህዌህን መንገድና የአምላካቸውን ሕግ አላወቁምና እነዚህ በእውነት ድሆችና ሰነፎች ናቸው”።
መልስ
መጽሐፍ ቅዱስ “የእግዚአብሔር መንገድ” ሲል የእግዚአብሔርን ሕግ ብቻ ለማለት አይደለም፡፡ “የእግዚአብሔር መንገድ” የሚለው በተለያየ ሁኔታ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ ለምሳሌ ያህል የእግዚአብሔር አሠራርና ወደ ሰዎች ሕይወት የሚመጣበት ሁኔታ “መንገድ” ተብሏል፡-
“እግዚአብሔር በወጀብና በዐውሎ ነፋስ ውስጥ መንገድ አለው፥ ደመናም የእግሩ ትቢያ ነው” (ናሆም 1፡3)፡፡
“የእግዚአብሔር ባለ ጠግነትና ጥበብ እውቀቱም እንዴት ጥልቅ ነው፤ ፍርዱ እንዴት የማይመረመር ነው፥ ለመንገዱም ፍለጋ የለውም።” (ሮሜ 11፡33)
መፍጠሩና ፍጥረተ ዓለሙን ማስተናበሩ “መንገድ” ተብሏል፡-
“በመንፈሱ ሰማያት ውበትን አገኙ፥ እጁም በራሪይቱን እባብ ወጋች። እነሆ፥ ይህ የመንገዱ ዳርቻ ብቻ ነው፤ ይህም የሰማነው ነገር ምንኛ ጥቂት ነው! የኃይሉንስ ነጐድጓድ ያስተውል ዘንድ ማን ይችላል?” (ኢዮብ 26፡13-14)
“እግዚአብሔር የመንገዱ መጀመሪያ አደረገኝ፥ በቀድሞ ሥራው መጀመሪያ።” (ምሳሌ 8፡22)
ስለዚህ “የእግዚአብሔር መንገድ” ሲባል በሕጉ ብቻ መወሰን ትክክል አይደለም፡፡ የእግዚአብሔር መንገድ “ሕግ፣ ሥርዓት፣ ትእዛዝ፣ መርሕ እና ቃል” ብቻ ነው ከተባለ ዮሐንስ “የያሕዌ መንገድ ጠራጊ” ስለተባለ “ሕጉን፣ ሥርዓቱን፣ ትዕዛዙን፣ መርሑንና ቃሉን” ይጠርጋል ማለት ነውን? ትርጉም አይሰጥም፡፡ ይልቅስ ዮሐንስ ሰዎችን ስለ መሲሁ ማንነት በማስተማር፣ መምጫው መድረሱን በማወጅ፣ ሰዎች ንስሐ ገብተው እንዲመለሱ የንስሐ ጥምቀት በማጥመቅና መሲሁ ሲገለጥ እርሱ መሆኑን በመመስከር መንገዱን ጠርጎለታል፡፡ የዮሐንስን ስብከት የተቀበሉ ወገኖች መሲሁን ለመቀበል ዝግጁዎች ነበሩ፡፡ ዮሐንስ መንገድ ጠራጊ ነው ሲባል ትክክለኛው መረዳት ይህ ነው፡፡
አብዱል
የኢየሱስ ትምህርት እና ሕግ የያህዌህ ሕግ ነው፥ የራሱ ሳይሆን የላከኝ አብ የሰጠው ትእዛዝ ነው፦
ዮሐንስ 12፥49 እኔ ከራሴ አልተናገርሁምና፥ ነገር ግን የላከኝ አብ እርሱ የምለውን የምናገረውንም ትእዛዝ ሰጠኝ”።
ዮሐንስ 14፥24 የማይወደኝ ቃሌን አይጠብቅም፤ “የምትሰሙትም ቃል የላከኝ የአብ ነው እንጂ የእኔ አይደለም”።
ዮሐንስ 17፥8 “የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸዋለሁና እነርሱም ተቀበሉት”።
የአብን ቃል ወደ እራሱ በማስጠጋት “ቃሌ” ማለቱ በራሱ የአብ እና የወልድ መንገድ አንድ መሆኑን ያሳያል። ዮሐንስ አዋጅ ነጋሪ የሆነ እና የጠረገው የያህዌህን እና የመሢሑን መንገድ ነው። ስለዚህ ኢሳይያስ 40፥3 ኢየሱስ ያህዌህ መሆኑን በፍጹም አያሳይም።
መልስ
በጣም የተሳሳተ ድምዳሜ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአባቱን ትዕዛዝና ተልዕኮ ነው ከሰማይ ይዞ የመጣው፡፡ ስለዚህ ልጅ ለአባት እንደሚታዘዝና እንደሚላክ የአብን መልእክትና ትዕዛዝ ይዞ ፈቃዱን ለመፈጸም ከሰማይመጥቷል፡፡ ሰው ሆኖ በምድር ላይ በመኖርም ልክ ነቢይ የአምላኩን ቃል እንደሚያደርስና ትዕዛዙን እንደሚፈፅም ለመለኮታዊ ክብሩ ሳይሳሳ በምድር ላይ እንደ ሰው ተመላልሷል፡፡ ስለዚህ ከላይ የሚገኙትን ንግግሮች መናገሩ አያስገርምም፡፡ ይህ ማለት ግን በመለኮታዊ ባሕርዩ ከአብ ያነሰ ነው ማለት አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡-
“በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ያ አስተሳሰብ በእናንተ ዘንድ ይሁን፡፡ እርሱ በባሕርዩ አምላከ ኾኖ ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን ሊለቀው እንደማይገባ አድርጎ አልቆጠረውም፡፡ ነገር ግን የባርያን መልክ ይዞ በሰውም አምሳል ተገኝቶ ራሱን ባዶ አደረገ፡፡ ሰው ኾኖ ተገልጦ ራሱን ዝቅ አደረገ፡፡ እስከ ሞት ያውም በመስቀል ላይ እስከመሞት ታዛዥ ሆነ፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር እጅግ ከፍ ከፍ አደረገው ከስምም ሁሉ በላይ የሆነውን ስም ሰጠው፡፡ ይኸውም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ጉልበት ሁሉ ለኢየሱስ ስም ይንበረከክ ዘንድ ምላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው፡፡” (ፊልጵስዩስ 2፡5-11 – አ.መ.ት.)፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ኢየሱስ የአብ ዘላለማዊ ቃል (ሎጎስ) በመሆኑ በመለኮታዊ ባሕርዩ ከአብ ጋር የተካከለ፣ የሕይወት ምንጭ፣ የፍጥረት ሁሉ ጌታና ፈጣሪ ነው፡-
“በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ እኔም አውቃቸዋለሁ ይከተሉኝማል፤ እኔም የዘለዓለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፥ ለዘለዓለምም አይጠፉም፥ ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም፡፡ የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል፥ ከአባቴም እጅ ሊነጥቃቸው ማንም አይችልም፡፡ እኔና አብ አንድ ነን፡፡ አይሁድ ሊወግሩት ደግመው ድንጋይ አነሡ፡፡” (ዮሐ. 10፡27-31)፡፡
“በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም።” (ዮሐንስ 1፡1-3)
“ከመላእክት ይልቅ እጅግ የሚበልጥ ስምን በወረሰ መጠን እንዲሁ ከእነርሱ አብዝቶ ይበልጣል፡፡ ከመላእክትስ፡፡ አንተ ልጄ ነህ፥ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ፥ ደግሞም፦ እኔ አባት እሆነዋለሁ እርሱም ልጅ ይሆነኛል ያለው ከቶ ለማን ነው? ደግሞም በኵርን ወደ ዓለም ሲያገባ፡፡ የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉም ለእርሱ ይስገዱ ይላል፡፡ ስለ መላእክትም፡፡ መላእክቱን መናፍስት አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል የሚያደርግ ይላል፤ ስለ ልጁ ግን፡፡ አምላክ ሆይ፥ ዙፋንህ እስከ ዘለዓለም ድረስ ይኖራል፤ የመንግሥትህ በትር የቅንነት በትር ነው፡፡ ጽድቅን ወደድህ ዓመፅንም ጠላህ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክህ ከጓደኞችህ ይልቅ በደስታ ዘይት ቀባህ ይላል፡፡ ደግሞ ጌታ ሆይ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፥ ሰማዮችም የእጆችህ ሥራ ናቸው፤ እነርሱም ይጠፋሉ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ፤ ኹሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ፥ እንደ መጎናጸፊያም ትጠቀልላቸዋለህ ይለወጡማል፤ አንተ ግን አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም ይላል፡፡ ነገር ግን ከመላእክት ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ ከቶ ለማን ብሎአል? ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገዝ የሚላኩ የሚያገለግሉም መናፍስት አይደሉምን?” (ዕብ. 1፡4-14)፡፡
ከላይ በሚገኙት ጥቅሶች መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስ በመለኮቱ ከአብ ጋር የተካከለ የሁሉ ፈጣሪ ነው፡፡ የዕብራውያን መልእክት በዚያው ጎን ለጎን በሰብዓዊ ባሕርዩ ከአብ ጋር ያለውን ግንኙነት እንደሚጠቅስ ማስተዋል ያስፈልጋል፡- “ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክህ…” የሚለው ኢየሱስ በሰብዓዊ ባሕርዩ ከአብ ጋር ያለውን ግንኙነት የተመለከተ ነው፡፡ እንደ ቃል (ሎጎስ) ግን ከአብ ወጥቶ ወደ ዓለም የመጣ የአብ ባሕርይ ተካፋይ በመሆኑ በመለኮቱ ከአብ ጋር አንድ ነው፤ ስለዚህ ያሕዌ ነው፡፡
ቅዱሳን ነቢያት ያሕዌ በአካል ተገልጦ ከሕዝቡ ጋር እንደሚኖር የተናገሩት ትንቢት ተፈፅሟል፡፡ ይህ እውነት የበራላቸው ወገኖች በፊቱ ተንበርክከው ጌታዬና አምላኬ ብለው ሰግደውለታል፡- “ቶማስም ጌታዬ አምላኬም ብሎ መለሰለት፡፡ ኢየሱስም፦ ስለ አየኸኝ አምነሃል፤ ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው አለው፡፡” (ዮሐ. 20፡28-29)፡፡
እኛም እንሰግድለታለን፣ የሚገባውን ክብርም እንሰጠዋለን፡፡ ክብርና ምስጋና አምልኮና ውዳሴ ለስሙ ይሁን!