ከእስልምና የወጣ ሰው ይገደል?
በሸሪኣ ሕግ መሠረት አንድ ሰው እስልምናን ከለቀቀ ወደ እምነቱ እንዲመለስ የተወሰኑ ቀናት ዕድል ይሰጠዋል (በአንዳንዱ የ3 በሌሎች የ10 ቀናት፣ ወዘተ.)፡፡ በነዚህ ቀናት ውስጥ ካልተመለሰ ይገደላል፡፡ ነገር ግን በአገራችንም ሆነ በዓለም ዙርያ እንደምንታዘበው አንዳንድ ሙስሊም የነበሩ ሰዎች ወደ ሌላ ሃይማኖት ከሄዱ በኋላ ብዙ ቆይተው እንደገና ሲመለሱ የበለጠ ታዋቂነትን አትርፈው ለእስልምና ሲሠሩ ይታያሉ፡፡ ይህ ሁኔታ ግን ትልቅ ጥያቄ እንድናነሳ ያስገድደናል፡፡ አንድ ሰው ከእስልምና ከወጣና የሸሪኣ ሕግ በሚያስቀምጠው መሠረት በጥቂት ቀናት ውስጥ ከመገደል ተርፎ ወደ እስልምና በመመለስ ይበልጥ ጠቃሚ ሰው መሆን ከቻለ በአጭር ቀናት ውስጥ ግደሉት የሚለው ሕግ ኢ-ምክንያታዊና እርባና ቢስ የመሆኑ ማሳያ አይሆንምን? ሕጉ ፍፁምና ትክክል ከሆነ እስልመናን ከድተው በሕጉ መሠረት በአጭር ጊዜ ያልተገደሉ ሰዎች ወደ እስልምና ሲመለሱ ሙስሊሞች ጮቤ የሚረግጡትና ለግለሰቦቹ ይበልጥ ታዋቂነትን የሚሰጡት ለምንድነው? ይህንን ማድረጋቸውስ የአላህ ሕግ ፋይዳ የሌለው መሆኑን ማረጋገጥ አይሆንምን?
ለምሳሌ ያህል ሲ ኤል ኤድዋርድስ (አቡ ያዚድ) የተባለ ጥቁር አሜሪካዊ ደካማ ክርስቲያን የነበረ ሲሆን እስልምናን ተቀብሎ ሙስሊም ሴት አግብቶ ብዙ ከቆየ በኋላ እንደገና ወደ ክርስትና ተመልሶ ነበር፡፡ ከዚያም ኤ ቢ ኤን በተባለ የቴሌቪዥን ጣብያ ውስጥ ተቀጥሮ እስልምናን የተመለከቱ ፕሮግራሞችን ይመራ ነበር፡፡ ይህ ሰው ከጣቢያው ከተሰናበተ በኋላ የተወሰኑ ዓመታትን በመቆየት እንደገና ወደ እስልምና መመለሱን አስታውቋል፡፡ ከዚህ የተነሳም በዚህ ሰሞን በሙስሊሞች እየተጨበጨበለት ይገኛል፡፡ በተመሳሳይ ኢብን አኑዋር የተባለ ሙስሊም አፖሎጂስት ወደ አራት ጊዜ ያህል ከእስልምና በመውጣት እንደገና ተመልሶ አሁን እስልምናን እየሰበከ ይገኛል፡፡ ሌላ ፖል ቢላል ዊልያምስ የተባለ እንግሊዛዊ ሙስሊም ሰባኪ ብዙ ጊዜ ከእስልምና መውጣቱን ያስታወቀ ሲሆን እንደገና ተመልሶ አሁን እስልምናን እየሰበከ ይገኛል፡፡ በተለይም ይህ ሰው ግበረ ሰዶማዊ መሆኑን በግልፅ የሚናገር ሲሆን ክርስትናን ስለሚያብጠለጥል ብቻ በሙስሊሞች ሲወደስ ይታያል፡፡ ከእስልምና የሚወጡ ሰዎች ወደ እስልምና ተመልሰው ይበልጥ አክራሪና እስልምናን የሚጠቅሙ ሰዎች መሆን ከቻሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ግደሏቸው የሚለው ሕግ ፍፁም ነው ሊባል የሚችለው እንዴት ሆኖ ነው? ሙስሊም ወገኖችስ የአምላካቸው ሕግ ፍፁም እንደሆነ ካመኑ ስለምን ይህንን ያደርጋሉ? ይህ እስልምና ምድራዊ ፖለቲካ መሆኑን አያረጋግጥምን?