ሥላሴ

ሥላሴ

እግዚአብሔር የባሕርዩንና የሥልጣኑን ገፅታ በፍጥረታዊው ዓለም ውስጥ ገልጧል፡፡ አስደናቂ የሆነው የፍጥረት ውስብስብነት፣ ሥርዓት፣ ውበት እና ግዝፈት ስለ እግዚአብሔር ግርማ ሞገስ የሚነግረን ነገር አለ፡፡ ነገር ግን በተለይም በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ስለ ራሱ ነግሮናል፡፡ እግዚአብሔር በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ራሱን ከገለጠባቸው ልዩ ሁኔታዎች መካከል አንዱ ሥሉስ አሓዳዊነቱ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሦስቱን የእግዚአብሔር አካላት “ሥላሴ” በማለት ነው የምትጠራው፡፡ ይህ ለመረዳት አስቸጋሪ የሆነ ፅንሰ ሐሳብ መሆኑ ባይካድም እግዚአብሔርን ለመረዳት ወሳኝ ነው፡፡ በሦስቱ የሥላሴ አካላት በኩል እንዴት ራሱን እንደገለጠ በማጥናት እግዚአብሔርን የበለጠ መረዳት እንችላለን፡፡

ዘዳግም 6፡4 “አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው” በማለት ያውጃል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ አንድ እግዚአብሔር ብቻ መኖሩን በግልፅ ይናገራል፡፡ ነገር ግን በባሕርይ አንድ በሆኑና ዘላለማዊ እንዲሁም እኩል በሆኑ ሦስት አካላት ይኖራል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ሦስቱን አካላት አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ በማለት እኩል ያስቀምጣቸዋል (ማቴ. 28፡19፣ 1ጴጥ. 1፡2፣ 1ቆሮ. 12፡4-6፣ 2ቆሮ. 13፡14)፡፡

ሥላሴ ለኛ ታላቅ ምስጢር ነው፡፡ ይህንን በትክክል ሊገልፅ የሚችል ምንም ዓይነት ምሳሌ ስለሌለን እግዚአብሔር አንድ ሆኖ በሦስት አካላት እንዴት እንደሚኖር ሙሉ በሙሉ መረዳት አንችልም፡፡ ውሱን ከሆነው ከኛ ዕይታ ያልተወሰነውን አምላካችንን ሙሉ በሙሉ መረዳት የማይቻል ነው (ኢሳ. 55፡8-9)፡፡ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ስለሚያስተምር መተንተንና ማስተማር እንችላለን፡፡ ኤሌክትሪክ መኖሩን ለማመንና ለመጠቀም የግድ የኤሌክትሪክን አሠራር መረዳት እንደማይጠበቅብን ሁሉ ሥላሴንም ሙሉ በሙሉ መረዳት ባንችልም መኖሩ እርግጥ ነው፡፡

ውኃን እንደ ምሳሌ ውሰዱ፡፡ አንድ ቁስ ነው (H2O)፡፡ ነገር ግን ፈሳሽ፣ ጋስ (እንፋሎት)ና ጠጣር (በረዶ) ሆኖ በሦስት መልክ ይገኛል፡፡ እግዚአብሔርም አንድ ማንነት ያለው አምላክ ሆኖ በሦስት አካላት ተገልጧል፡፡ ነገር ግን ከውኃ በተለየ ሁኔታ የሥላሴ አካላት ሕያው በሆነ መንገድ እርስ በርሳቸው ሕብረት ያደርጋሉ፡፡ ጠቅለል ባለ አነጋገር እግዚአብሔር እንደ ሥላሴነቱ ሦስት ሥራዎችን ይሠራል፡፡ እግዚአብሔር አብ አቃጅ ነው፣ እግዚአብሔር ወልድ የዕቅድ ፈጻሚ ነው፣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ደግሞ ዕቅዱ በአማኞች ሕይወት ውስጥ እንዲሠራ አድራጊ ነው፡፡  በሥላሴ ውስጥ ያለው አንድነት ወልድ ለአብ በመገዛቱና መንፈስ ቅዱስ ለአብና ለወልድ በመገዛቱ ይገለጻል፡፡ እግዚአብሔር አብ ደግሞ መለኮታዊውን ዕቅድ ከግብ ያደርስ ዘንድ ለወልድ ሥልጣንን ሁሉ ሰጥቶታል፡፡

እግዚአብሔር አብ

እግዚአብሔር አብ የሥላሴ ቀዳሚው አካል ሲሆን በመፍጠርና ለሁሉም ሰው እኩል የሆነውን መልካምነቱን በመለገስ ለአማኞችም ሆነ አማኞች ላልሆኑት ወገኖች አባትነቱን አሳይቷል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው እግዚአብሔር አብ በክፎዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣል፥ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባል፡፡ የእንስሳትና የዱር ፍጥረታት ሁሉ መጋቢ ነው፡፡ ለመንግሥቱ ሰዎችም ሆነ እርሱን ለሚቃወሙት ሳይቀር የሚያስፈልጋቸውን ይሰጣቸዋል (ማቴ. 5፡45፣ 6፡25-33፣ 7፡9-11፣ ሉቃ. 6፡35፣ ዕብ. 12)፡፡

ከዚህም በላይ እግዚአብሔር አብ ከአማኞች ጋር የተለየ ግንኙነት እንዳለው ይፋ አድርጓል፡፡ እግዚአብሔር በጸጋው ወደ ራሱ በመሳብ ልጆቹ አድርጎ ወደ ቤተሰቡ ቀላቅሎናል (ዮሐ. 6፡44፣ 1፡12፣ 1ዮሐ. 3፡1)፡፡ “አባ አባት” ብለን እንጠራው ዘንድ እግዚአብሔር የልጁን መንፈስ ወደ ልባችን ልኳል (ሮሜ. 8፡15-16፣ ገላ. 4፡6-7)፡፡ የሕያው እግዚአብሔር ልጆች ተብሎ መጠራትና ከልጁ ከክርስቶስ ጋር አብሮ ወራሽ መባል ከሚገባን በላይ የሆነ ታላቅ ሚስጥር ነው (ሮሜ 8፡17)፡፡

እግዚአብሔር አብ ልጆቹ አድርጎ ወደ ቤተሰቡ እኛን መቀላቀሉ ጥቅሞችና ኃላፊነቶች አሉት፡፡ ኤፌሶች 1፡3-14 ላይ እንደተጻፈው እግዚአብሔር አብ እንዲያው በነጻ ይቅር ብሎናል፤ መልካም ነገሮችን ሁሉ ደግሞ ይሰጠናል፡፡ ቅዱሳንና ነውር የሌለብን እንድንሆን ለኛ ልዩ ዓላማ አለው፡፡ ዕቅዱንም ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ገልፆልናል፡፡ ፍጹም እንደሆነ አባት ልጆቹ እንደመሆናችን መጠን የመንፈሱን መያዣ በመስጠት ፍቅሩን አረጋግጦልናል፡፡ ዘላለማዊ ደስታና ዋስትና እንዳላቸው ተወዳጅ ልጆች በእምነት በኩል ወደ አብ መግባት ሆኖልናል (ኤፌ. 3፡12)፡፡

እግዚአብሔር አብ ቃሉን መታዘዝንና ዓለምን ከእርሱ ጋር ለማስታረቅ የእርሱ ተወካዮች መሆንን የመሳሰሉ ኃላፊነቶችንም ለልጆቹ ሰጥቷል (ዮሐ. 14፡21፣ 2ቆሮ. 5፡20)፡፡ እንደ ቤተሰቡ አባላት የቤተ ክርስቲያኑ አባል መሆንና በምስጋናና በአምልኮ ለርሱ ምላሽ መስጠት ይኖርብናል (ዕብ. 10፡24-25፣ 1ጴጥ. 2፡9)፡፡

እግዚአብሔር ማን መሆኑን ስናጠና ሳለን የእርሱን ባሕርይና ጠባይ እያወቅን እንሄዳለን፡፡ እግዚአብሔር እንደ ሥላሴነቱ ከአእምሯችን በላይና በእግዚአብሔር አብ በኩል ደግሞ የቅርብ አባታችን መሆኑን ከቅዱሳት መጻሕፍት እንማራለን፡፡ በፍጹም ልባችን ጌታና አባታችን ብለን ልንጠራው እንችላለን!

ማጠቃለያ

እግዚአብሔር በቃሉ ውስጥ ስለ ራሱ የገለጠውን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡

  • እግዚአብሔር በሦስት አካላት የሚኖር አንድ አምላክ (ሥላሴ) ነው፡፡
  • ሥላሴን ሙሉ በሙሉ መረዳት ባይቻልም እንድናምነው መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል፡፡
  • እግዚአብሔር አብ፣ እግዚአብሔር ወልድና እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የየራሳቸው የሥራ ድርሻ አላቸው፡፡
  • እግዚአብሔር አብ የሥላሴ የመጀመርያው አካል ነው፡፡
  • ልጆቹ እንደመሆናችን ልዩ ጥቅሞችና ኃላፊነቶች አሉብን፡፡​