መንፈስ ቅዱስ ያሕዌ ነው!
የቅዱሳት መጻሕፍት ምስክርነት
ታሪካዊውና መጽሐፍ ቅዱሳዊው ክርስትና እግዚአብሔር በሦስት አካላት የሚኖር አንድ አምላክ መሆኑን ያስተምራል፡፡ ይህ አስተምሕሮ የመጽሐፍ ቅዱስን አጠቃላይ ትምሕርተ እግዚአብሔር ያገናዘበ ሲሆን የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ‹‹ሥላሴ›› በሚል የነገረ መለኮት ቃል ይገልፁታል፡፡ የእግዚአብሔር ሥሉስ አሓዳዊነት ከመጽሐፍ ቅዱስ አንኳር አስተምሕሮዎች መካከል አንዱ ቢሆንም “የይሖዋ ምስክሮችን” ከመሳሰሉት የኑፋቄ ቡድኖችና እስልምናን ከመሳሰሉት የነጠላ አሓዳዊነት አስተምሕሮ አቀንቃኝ ሃይማኖታት ዘንድ የከረረ ተቃውሞ ይነሳበታል፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምሕሮ ያፈነገጡት የኑፋቄ አንጃዎች ብዙ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ማንነት አልባ ኃይል ብቻ እንደሆነ የሚያስተምሩ ሲሆን እስልምና የመንፈስ ቅዱስን ማንነት ከመልአኩ ገብርኤል ጋር ያምታታል፡፡ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ ከሦስቱ የሥላሴ አካላት መካከል አንዱና ያሕዌ እግዚአብሔር መሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍት በግልፅና በማያሻማ መንገድ ይመሰክራሉ፡፡
በዚህ ጽሑፍ መንፈስ ቅዱስ ያሕዌ እግዚአብሔር መሆኑን የሚያረጋግጡ የቅዱሳት መጻሕፍት ምንባባትን እናቀርባለን፡፡ አንባቢያንም እነዚህን የቅዱሳት መጻሕፍት ምስክርነት በአንክሮ በማጤን የመንፈስ ቅዱስን ማንነት በተመለከተ ትክክለኛውንና መጽሐፍ ቅዱሳዊውን አቋም ይወስዱ ዘንድ እናበረታታለን፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያሕዌ እግዚአብሔር መሆኑን ባረጋገጥንበት ጽሑፋችን እንደገለፅነው “ያሕዌ” የሚለው የእግዚአብሔር የተፀውዖ ስም የእብራይስጥ ቃል በመሆኑ ምክንያት በብሉይ ኪዳን እንጂ በግሪክ አዲስ ኪዳን ምንባባት ውስጥ አይገኝም፡፡ በዚህ ጽሑፋችንም በተመሳሳይ መንገድ በአዲስ ኪዳን ስለ መንፈስ ቅዱስ የተጻፉ ምንባባትን በብሉይ ኪዳን ከተጻፉ ምንባባት ጋር በማመሳከር ማስረጃዎችን የምናቀርብ ይሆናል፡፡
- “ኑ፥ እንስገድ ለእርሱም እንገዛ በእርሱ ባደረገን በእግዚአብሔር (ያሕዌ) ፊት እንበርከክ፤ እርሱ አምላካችን ነውና፥ እኛ የማሰማርያው ሕዝብ የእጁም በጎች ነንና። በምድረ በዳ እንደ ተፈታተኑትእንዳስቈጡት ጊዜ፥ ዛሬ ድምፁን ብትሰሙ ልባችሁን አታጽኑ።” (መዝሙር 95፡6-8)
መዝሙረኛው ንጉሥ ዳዊት በዘጸአት 17፡2 ላይ ሊቀ ነበያት ሙሴ የእስራኤልን ሕዝብ “እግዚአብሔርን ስለምን ትፈታተኑታላችሁ?” በማለት ስለ ያሕዌ የተናገረውን ክፍል መለስ ብሎ የቃኘበት መዝሙር ሲኾን፤ ዘማሪው “ያሕዌ” ሲል የጠራው የእስራኤላውያን አምላክ፣ መንፈስ ቅዱስ መኾኑን የዕብራውያኑ ጸሐፊ እንዲህ ያረጋግጥልናል፡-
“ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ እንደሚል። ዛሬ ድምፁን ብትሰሙት፥ አባቶቻችሁ እኔን የፈተኑበትየመረመሩበትም አርባ ዓመትም ሥራዬን ያዩበት በምድረ በዳ በፈተና ቀን በማስመረር እንደ ሆነ፥ ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ።” (ዕብራውያን 3፡7-9)
በዘመነ ብሉይ እስራኤላውያን በምድረ በዳ የተፈታተኑት ያሕዌ እግዚአብሔር በአዲስ ኪዳን መንፈስ ቅዱስ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ይህም መንፈስ ቅዱስ ያሕዌ እግዚአብሔር መሆኑን ያረጋግጥልናል፡፡
- “እነርሱም፦ ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት? አሉት። እርሱም፦ በድንኳኑ ውስጥ ናት አላቸው። እርሱም፦ የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ በእውነት እመለሳለሁ ሚስትህ ሣራም ልጅንታገኛለች አለ። ሣራም በድንኳን ደጃፍ በስተ ኋላው ሳለች ይህንን ሰማች። … በውኑ ለእግዚአብሔር(ያሕዌ) የሚሳነው ነገር አለን? የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ እመለሳለሁ ሣራም ልጅን ታገኛለች።” (ዘፍጥረት 18፡9-14)
በዚህ ክፍል እንተጻፈው ለአብርሃምና ለሣራ ወንድ ልጅን (ይስሐቅን) የሰጣቸው ሁሉን የሚችለው ያሕዌ አምላክ ሲሆን እርሱም መንፈስ ቅዱስ እንደነበር ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በገላቲያ መልዕክቱ እንዲህ ያረጋግጥልናል፡-
“እኛም፥ ወንድሞች ሆይ፥ እንደ ይስሐቅ የተስፋ ቃል ልጆች ነን። ነገር ግን እንደ ሥጋ የተወለደው እንደ መንፈስ የተወለደውን በዚያን ጊዜ እንዳሳደደው ዛሬም እንዲሁ ነው። ነገር ግን መጽሐፍ ምን ይላል? የባሪያይቱ ልጅ ከጨዋይቱ ልጅ ጋር አይወርስምና ባሪያይቱን ከልጅዋ ጋር አውጣት። ስለዚህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ የጨዋይቱ ልጆች ነን እንጂ የባሪያይቱ አይደለንም።” (ገላቲያ 4፡28-29)
በዚህ ክፍል ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ አብርሃም በሥጋ ፈቃዱ ከባርያይቱ ከአጋር የወለደው እስማኤል በመንፈስ ቅዱስ (በያሕዌ) ፈቃድ ከጨዋይቱ ሣራ የተወለደው ልጁ ይስሐቅን እንዳሳደደው ሁሉ በዚህ ዘመንም እንደ መንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ዳግመኛ የተወለድን እኛን እንደ ሥጋ ፈቃድ የተወለዱት ያሳድዱናል እያለ ነው፡፡ በዚህም ለአብርሃምና ለሣራ ይስሐቅን የሰጣቸው ያሕዌ አምላክ፤ ሁሉን የሚችለው መንፈስ ቅዱስ መኾኑን ያስገነዝበናል፡፡
- ” … በእስራኤልም ንጉሥ በዮአስ ልጅ በኢዮርብዓም ዘመን ወደ ብኤሪ ልጅ ወደ ሆሴዕ የመጣ የእግዚአብሔር (የያሕዌ) ቃል ይህ ነው። እግዚአብሔር (ያሕዌ) መጀመሪያ በሆሴዕ በተናገረ ጊዜ …” (ሆሴዕ 1፡1-2)
ያሕዌ እግዚአብሔር ቃሉን በነቢያቱ እንደሚልክና ደግሞም በእነርሱ ሆኖ እንደሚናገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተደጋጋሚ ተገልፆ እንመለከታለን፡፡ ወደ አዲስ ኪዳን ስንመጣ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ነብያትን የሚልከው እግዚአብሔር (አብ) መኾኑንና ነብያቱን እየመራ (እየነዳ) በእነርሱ በኩል የሚናገው ደግሞ መንፈስ ቅዱስ መኾኑን እንዲህ ይመሰክርልናል፡-
“ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ።” (2ጴጥ 1:21)
ከምንባቡ እንደምንረዳው ነብያቱን የሚልካቸው “ያሕዌ አብ” ሲሆን በነብያቱ አድሮ የሚናገረው ደግሞ “ያሕዌ መንፈስ ቅዱስ” ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ከርዕሰ ነብያት አንስቶ እስከ ደቂቀ ነብያት ድረስ የሚገኙት ቅዱሳት መጽሐፍት ሁሉ በነብያት አድሮ ይናገር የነበረው ያሕዌ አምላክ፤ መንፈስ ቅዱስ መኾኑን ያረጋግጡልናል፡፡ (በሊቀ ነብያት ሙሴ በኩል ይናገር የነበረው ያሕዌ መንፈስ ቅዱስ እንደኾነ የሚመሰክሩ ምንባባትን ለማሳያነት ያመሳክሩ፡- ዘኁልቁ 12፡2፤ 16፡40፤ 27፡- 23፤ ኢያሱ 20፡2-3፤ 1ነገሥት 8፡53፡፡)
- “የሠራዊትን ጌታ (አዶናይ) ንጉሡን እግዚአብሔርን (ያሕዌን) ስለ አዩ ጠፍቻለሁና ወዮልኝ! አልሁም፦ … እርሱም (አዶናይ) ሂድ ይህን ሕዝብ። መስማትን ትሰማላችሁ አታስተውሉምም ማየትንም ታያላችሁ አትመለከቱምም በላቸው። በዓይናቸው እንዳያዩ፥ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ፥ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፥ ተመልሰው እንዳይፈወሱ፥ የዚህን ሕዝብ ልብ አደንድን፥ ጆሮአቸውንም አደንቍር፥ ዓይናቸውንም ጨፍን አለኝ።” (ኢሳይያስ 6፡5-10)
በዚህ ክፍል ነብዩ ኢሳይያስን የላከው ጌታ እግዚአብሔር (አዶናይ ያሕዌ) ራሱ መንፈስ ቅዱስ መኾኑን ወንጌላዊው ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፉ እንዲህ ይመሰክርልናል፡-
“…እንዲህም አለ፦ መንፈስ ቅዱስ በነቢዩ በኢሳይያስ ለአባቶቻችን። ወደዚህ ሕዝብ ሂድና። መስማትን ትሰማላችሁና አታስተውሉም፥ ማየትንም ታያላችሁና አትመለከቱም፤ በዓይናቸው እንዳያዩ በጆሮአቸው እንዳይሰሙ በልባቸውም እንዳያስተውሉ ተመልሰውም እንዳልፈውሳቸው፥ የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአል ጆሮአቸውም ደንቁሮአል ዓይናቸውንም ጨፍነዋል በላቸው ሲል መልካም ተናገረ። እንግዲህ ይህ የእግዚአብሔር ደኅንነት ለአሕዛብ እንደ ተላከ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን፤ እነርሱ ደግሞ ይሰሙታል።” (የሐዋርያት ሥራ 28፡25-28)
በብሉይ ኪዳን ኢሳይያስ ትንቢትን ይናገር ዘንድ የላከው ጌታ እግዚአብሔር (አዶናይ ያሕዌ) በአዲስ ኪዳን መንፈስ ቅዱስ መሆኑ ተነግናል፡፡ ይህም መንፈስ ቅዱስ ያሕዌ እግዚአብሔር ስለመሆኑ ሌላው ጠንካራ ማስረጃ ነው፡፡
ከላይ የአዲስ ኪዳንንና የብሉይ ኪዳንን ጥቅሶች በማመሳከር ካቀረብናቸው ምንባባት በተጨማሪ ሁለቱን ኪዳናት ማመሳከር ሳያስፈልግ መንፈስ ቅዱስ ያሕዌ እግዚአብሐር መሆኑን የሚያረጋግጡ ጥቅሶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በብዛት ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል ተከታዩን ጥቅስ እንመልከት፡-
“የዳዊትም የመጨረሻ ቃሉ ይህ ነው። ከፍ ከፍ የተደረገው፥ በያዕቆብም አምላክ የተቀባው፥ በእስራኤል ዘንድ መልካም ባለ ቅኔ የሆነ፥ የእሴይ ልጅ የዳዊት ንግግር፤ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ተናገረ፤ ቃሉም በአንደበቴ ላይ ነበረ። የእስራኤል አምላክ ተናገረኝ፤ የእስራኤል ጠባቂ እንዲህ አለ፦ በሰው ላይ በጽድቅ የሚሠለጥን፥ በእግዚአብሔርም ፍርሃት የሚነግሥ፥ እርሱ እንደ ማለዳ ብርሃን እንደ ፀሐይ አወጣጥ፥ በጥዋትም ያለ ደመና እንደሚደምቅ፥ ከዝናብ በኋላ ከምድር እንደሚበቅል ልምላሜ ይሆናል።” (2ሳሙኤል 23፡1-4)
በዚህ ክፍል ንጉሥ ዳዊት የእግዚአብሔርን መንፈስና እግዚአብሔርን በማተካካትና በአንድ ግብር እንዲሁም በአንድ መለኮታዊ ባሕርይ ሲገልፅ እንመለከታለን፡፡
ከአዲስ ኪዳን አንድ እንጨምር፡-
“ጴጥሮስም፦ ሐናንያ ሆይ፥ መንፈስ ቅዱስን ታታልልና ከመሬቱ ሽያጭ ታስቀር ዘንድ ሰይጣን በልብህ ስለ ምን ሞላ? ሳትሸጠው የአንተ አልነበረምን? ከሸጥኸውስ በኋላ በሥልጣንህ አልነበረምን? ይህን ነገር ስለ ምን በልብህ አሰብህ? እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን አልዋሸህም አለው።” (የሐዋርያት ሥራ 5፡3-4)
በዚህ ቦታ ላይ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ መንፈስ ቅዱስን መዋሸት እግዚአብሔርን መዋሸት መሆኑን መግለፁ መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር መሆኑን ማመኑን ያሳያል፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መንፈስ ቅዱስ መለኮታዊ ባሕርያት ሁሉ እንዳሉት ተገልጿል፡፡ ለአብነት ያህል፡-
- ፈጣሪ ነው – ኢዮብ 33፡4፣ መዝሙር 33፡6፣ መዝሙር 104፡29-30፣ ኢዮብ 33፡4
- ምሉዕ በኲለሄ (በሁሉም ቦታ የሚገኝ) ነው – መዝሙር 139፡7-10፣ 1ቆሮንቶስ 2፡10-11
- አዕማሬ ኲሉ (ሁሉን አዋቂ) ነው – ኢሳይያስ 40፡13፣ ዮሐንስ 14፡16፣ 1ቆሮንቶስ 2፡10-11
- ከኃሊ ኩሉ (ሁሉን ቻይ) ነው – ሚክያ 2፡7፣ መዝሙር 104፡30፣ ማቴዎስ 12፡28፣ ሮሜ 15፡18-19
- ዘላለማዊ ነው – ኢሳይያስ 48፡16፣ ኢሳይያስ 61፡1፣ ዮሐንስ 14፡16፣ ዕብራውያን 9፡14
መንፈስ ቅዱስ ማንነት ያለው (እኔ ማለት የሚችል) አካል መሆኑንና አንዳንዶች እንደሚሉት ኃይል ብቻ አለመሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ፡፡ ለአብነት ያህል፡-
- ይናገራል:- 2 ሳሙኤል 23:2፣ የሐዋርያት ሥራ 8:29፣ የዮሐንስ ራዕይ 2፡7
- ይመራል:- ሮሜ 8 14፣ ዮሐንስ 16:13
- ይጠራል፣ ተልእኮዎችንም ይሰጣል፡- ሐዋርያት ሥራ 13፡2፣ 20:28
- ያዛል፡- የሐዋርያት ሥራ 8፡29
- በአማኞች ውስጥ ይኖራል፡- ዮሐንስ 14 17፣ 1 ቆሮንቶስ 6:19
- ያስተምራል፡- ዮሐንስ 14 26; 1 ዮሐንስ 2:27
- ይልካል፡- የሐዋርያት ሥራ 13:4
- ኃይልን ይሰጣል፡- የሐዋርያት ሥራ 1:8፣ 2ጴጥሮስ 1:21
- ይመሰክራል፡- ዮሐንስ 15፡26፣ 27፣ 16: 13,14
- ሊመረር ይችላል፡- ኢሳይያስ 63:10
- ያዝናል፡- ኤፌሶን 4፡30
- ሰዎች ሊዋሹት ይችላሉ፡- የሐዋርያት ሥራ 5 3
- ሰዎች ሊሰድቡት ይችላሉ፡- ማቴዎስ 12፡31
- ይከበራል፡- መዝሙር 51፡11
- ስጦታን ይሰጣል፡- 1ቆሮንቶስ 12፡27-28
- ያፅናናል፡- ዮሐንስ 16፡7
- ይወቅሳል፡- ዮሐንስ 16፡8-11
ማንነት አልባ ኃይል ከላይ የተጠቀሱትን ነገሮች ማድረግ አይችልም፡፡
እግዚአብሔር ማነዉ?