የቁርኣን ጸሐፊ ስለ ክርስቲያናዊ ነገረ መለኮት የነበሩት የተሳሳቱ አመለካከቶች

የቁርአን ጸሐፊ ስለ ክርስቲያናዊ ነገረ መለኮት የነበሩት የተሳሳቱ አመለካከቶች

ብዙ ሙስሊም ወገኖች የኢየሱስን አምላክነት ለመቀበል የሚቸገሩት የእግዚአብሔርን ሥሉስ አሐዳዊነት መረዳት ስለሚሳናቸው ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ሥሉስ አሐዳዊነት ለመረዳት የሚቸገሩት ደግሞ በሁለት መሠረታዊ ምክንያቶች ነው፡፡ የመጀመርያው እስልምና ስለ ፈጣሪ አንድነት ያለው አመለካከት ነው፡፡ እስልምና ስለ ፈጣሪ አንድነት ያለው ግንዛቤ ፈጣሪ በአካልም በመለኮትም ሌጣ አንድ (Monadic) እንደሆነ ሲሆን ይህ እምነት “ነጠላ አሃዳዊነት” (Unitarian Monotheism) ይሰኛል፡፡ የእስልምና ነጠላ አሃዳዊነት እምነት በፈጣሪ ማንነት ውስጥ ምንም ዓይነት ብዝሐነት መኖሩንና መኖር መቻሉን የሚክድ በመሆኑ ብዙ ሙስሊሞች እግዚአብሔር በመለኮታዊ ባሕርዩ አንድ ሆኖ በሦስት አካላት የተገለጠ መሆኑን የሚያስተምረውን የክርስትናን ትምህርት እንደ መድብለ አማልክታዊነት እንዲቆጥሩት አድርጓቸዋል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ስለ እግዚአብሔር አንድነት የሚናገሩትን ጥቅሶች የሚተረጉሙት በዚሁ የነጠላ አሃዳዊነት አመለካከት መሠረት ሲሆን የእግዚአብሔርን ሥሉስ አሐዳዊነት ለመረዳት በእጅጉ ይቸገራሉ፡፡ ኢየሱስ አምላክ መሆኑንና ደግሞም የእግዚአብሔር ልጅ መባሉን ሲሰሙ ግራ የሚጋቡት በዚህ ምክንያት ነው፡፡ “ኢየሱስ አምላክ ከሆነ እንዴት የአምላክ ልጅ ሊሆን ይችላል? እንዴት ወደ እግዚአብሔር ሊጸልይ ይችላል? እንዴት በእግዚአብሔር የተላከ ሊሆን ይችላል? ወዘተ.” በማለትም ይጠይቃሉ፡፡

ሁለተኛውና ዋነኛው ምክንያት ደግሞ የቁርአን ጸሐፊ ክርስቲያኖች በሦስት አማልክት የሚያምኑ በማስመሰል መናገሩ ነው፡፡ ቁርአን ሱራ 4፡171 ላይ ለክርስቲያኖች “(አማልክት) ሦስት ናቸው አትበሉ” የሚል መልእክት ያስትላልፋል፡፡ ነገር ግን ክርስቲያኖች በየትኛውም ዘመን “አማልክት ሦስት ናቸው” በማለት አምነው አያውቁም፡፡ ትክክለኛው የክርስትና አስተምህሮ አንድ አምላክ ብቻ እንዳለና ይህ አንዱ አምላክ አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ የተሰኙ ሦስት አካላት እንዳሉት የሚናገር ነው፡፡ የቁርአን ጸሐፊ “አንዱ አምላክ ሦስት አካላት አሉት አትበሉ” ቢል ኖሮ በእርግጥም ክርስትያናዊውን አስተምህሮ የሚመለከት አባባል በሆነ ነበር፡፡ ቁርአን የነቀፈው ይህ አስተምህሮ ለክርስትና ባዕድ በመሆኑ ይህ ትምህርት በክርስትና ውስጥ እንደሚገኝ በማስመሰል የተናገረው ሰው ሀሰተኛ ነው፡፡ የቁርአን ጸሐፊ የሥላሴን አስተምህሮ በትክክል ያቀረበበት አንድም ጥቅስ የለም፡፡ ሦስቱን የሥላሴ አካላት፣ ማለትም አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስን በጋራ አንድም ጊዜ አልጠቀሰም፡፡ ከዚህ በተፃራሪ ተከታዩን ጥቅስ በመጻፍ ሙስሊሞችን ወደ ተሳሳተ ድምዳሜ የመራ መልዕክት አስተላልፏል፡- “አላህም፡- የመርየም ልጅ ዒሳ ሆይ አንተ ለሰዎቹ፡- እኔንና እናቴን ከአላህ ሌላ ሁለት አምላኮች አድርጋችሁ ያዙ ብለሃልን? በሚለው ጊዜ (አስታውስ)፤ ጥራት ይገባህ፤ ለኔ ተገቢዬ ያልሆነን ነገር ማለት ለኔ አይገባኝም፤ ብዬው እንደሆነም እርግጥ አውቀኸዋል፤ በነፍሴ ውስጥ ያለውን ሁሉ ታውቃለህ፤ ግን አንተ ዘንድ ያለውን አላውቅም፤ አንተ ሩቆችን ሁሉ በጣም ዐዋቂ አንተ ብቻ ነህና ይላል” (ሱራ 5፡116)፡፡

ይህ ጥቅስ በዕለተ ቂያማ (በፍርድ ቀን) በአላህና በዒሳ መካከል የሚደረግ ምልልስ እንደሆነ ሙስሊሞች ያምናሉ፡፡ የቁርአን ጸሐፊ መንፈስ ቅዱስ የሥላሴ አካል መሆኑ በክርስቲያኖች መታመኑን የጠቀሰበት ቦታ ባለመኖሩ ብዙሙስሊሞች ከዚህ ጥቅስ በመነሳት ሥላሴ ማለት አላህ፣ ማርያምና ኢየሱስ እንደሆኑ ያስባሉ፡፡ በዚህ ዘመን የሚገኙት አንዳንድ ሙስሊም ምሑራን አሸማቃቂ የሆነውን ይህንን የቁርአን ስሁት መረዳት አለባብሶ ለማለፍ የተለያዩ ትርጉሞችን ለመስጠት ሙከራዎችን ቢያደርጉም ጥንታዊያን ሙስሊም ሊቃውንት ይህ ጥቅስ ስለ ሥላሴ የሚናገር መሆኑን በጽሑፎቻቸው አስፍረዋል፤ በዚህ ዘመን የሚገኙት ብዙ ሙስሊሞችም ተመሳሳይ አመለካከት ያንፀባርቃሉ፡፡

“(Say not: “Three!”) do not elevate `Isa and his mother to be gods with Allah. Allah is far holier than what they attribute to Him. In Surat Al-Ma’idah (chapter 5), Allah said…” https://quranx.com/Tafsir/Kathir/4.171

“…(and say not “Three”) a son, father and wife.” https://quranx.com/Tafsir/Abbas/4.171

ለመጽሐፍ ቅዱስና ለክርስትና ሥነመለኮት መሠረታዊ እውቀት የጎደለው ሰው ካልሆነ በስተቀር ማንኛውም ክርስቲያን ሥላሴ ማለት አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ መሆኑን ያውቃል፡፡ ክርስቲያኖች ኢየሱስና ማርያም ከአላህ ሌላ ሁለት አምላኮች እንደሆኑ አያምኑም፡፡ ነገር ግን አንዱና ብቸኛው አምላክ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ የተሰኙ ሦስት አካላት እንዳሉት ያምናሉ፡፡

የሥላሴን ትምህርት እንደተገነዘቡ የሚናገሩ ቀላል ቁጥር የሌላቸው ሙስሊም ወገኖች ደግሞ አስተምህሮውን ከሰባሊዮስ አመለካከት ጋር ሲያምታቱት ይስተዋላሉ፡፡ ሰባሊዮስ እግዚአብሔር ነጠላ አካል ብቻ እንዳለው ነገር ግን ራሱን እየለዋወጠ እንደገለጠ ያስተማረ በሦስተኛው ክፍለ ዘመን የኖረ ሰው ነበር፡፡2 ሱራ 4፡171 ላይ ከተጻፈው ጋር በሚጣረስ ሁኔታ የቁርአን ጸሐፊ ተከታዩን ሐሳብ ይናገራል፡- “እነዚያ አላህ እርሱ የመርየም ልጅ አልመሲሕ ነው ያሉ በእርግጥ ካዱ፤ አልመሲሕም አለ፦ የእስራኤል ልጆች ሆይ! ጌታዬንና ጌታችሁን አላህን ተገዙ፤ እነሆ! በአላህ የሚያጋራ ሰው አላህ በርሱ ላይ ገነትን በእርግጥ እርም አደረገ፤ መኖሪያውም እሳት ናት፤ ለበዳዮችም ምንም ረዳቶች የሏቸውም፡፡” (5፡72)

መጽሐፍ ቅዱስ መሲሁ ኢየሱስ አምላክ መሆኑን በበርካታ ስፍራዎች ላይ ይናገራል፡፡ (ዮሐንስ 1፡1፣ 20፡28 ሮሜ 9፡5፣ ቲቶ 2፡13፣ ዕብራውያን 1፡8-10)፡፡ ከላይ በተቀመጠው የቁርአን ጥቅስ ውስጥ ክርስቲያኖች “አላህ የመርየም ልጅ አልመሲህ ነው” እንደሚሉ ተነግሯል፡፡ “አላህ” የሚለው እግዚአብሔርን ለማመልከት የገባ የአረብኛ ቃል ነው ብንል “ክርስቶስ እግዚአብሔር ነው” ማለት እና “እግዚአብሔር ክርስቶስ ነው” ማለት ከፍተኛ የሆነ ልዩነት አላቸው፡፡ በክርስትና አስተምህሮ መሠረት እግዚአብሔር በመለኮቱ ፍጹም አንድ ቢሆንም ነገር ግን በአካል ነጠላ ስላልሆነ ለአብ እና ለመንፈስ ቅዱስ እውቅናን በመንፈግ “እግዚአብሔር ክርስቶስ ነው” የሚለው አባባል ከክርስትና ትምህርት ጋር የሚጣጣም አይደለም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም ምንም አይነት ድጋፍ የለውም፡፡ የአብ እና የመንፈስ ቅዱስን ህልውና በመካድ ኢየሱስ ብቸኛው የእግዚአብሔር አካል እንደሆነ የሚያስተምረው ትምህርት ነቢዩ መሐመድ ከመወለዳቸው ከሦስት ክፍለ ዘመናት በፊት በቤተ ክርስቲያን ተወግዟል፡፡ መሐመድ “ነቢይ” ተብለው በምድረ አረብ ከመነሳታቸው በፊት የተጻፉ ኢየሱስ እግዚአብሔር መሆኑን መናገር ትክክል መሆኑን ነገር ግን እግዚአብሔር ኢየሱስ መሆኑን መናገር ስህተት መሆኑን የሚገልፁ ክርስቲያናዊ ጽሑፎች አሉ፡፡

የቁርአን ጸሐፊ ስለ ሥላሴ አስተምህሮ ያለው የተሳሳተ አመለካከት በዚህ ብቻ የሚያበቃ አይደለም፡፡ እስኪ ተከታዩን ጥቅስ ልብ ብላችሁ ተመልከቱ፡- “እነዚያ አላህ የሦስት ሦስተኛ ነው ያሉ በእርግጥ ካዱ፤ ከአምላክም አንድ አምላክ እንጅ ሌላ የለም፤ ከሚሉትም ነገር ባይከለከሉ፣ ከነሱ እነዚያን የካዱትን አሳማሚ ቅጣት በእርግጥ ይነካቸዋል” (5፡73)፡፡ በክርስትና አስተምህሮ መሠረት እግዚአብሔር የሦስት ሦስተኛ ሳይሆን በሦስት አካላት የሚኖር አንድ አምላክ ነው፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በስፋት እንደምንመለከተው ለዚህ አስተምህሮ ከበቂ በላይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃዎች አሉ፡፡ በየትኛውም ዘመን ክርስትያኖች እግዚአብሔር የሦስት ሦስተኛ እንደሆነ አምነው አያውቁም፡፡ ምናልባት ከላይ በተጠቀሰው የቁርአን ቃል ውስጥ አላህ የተባለው እግዚአብሔር አብን ለማመልከት ከሆነ፤ በሥላሴ ውስጥ እግዚአብሔር አብ መጀመርያ እንጂ ሦስተኛ አይደለም፡፡ ክርስቲያኖች የሥላሴን አካላት ሲጠሩ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ በማለት አብን ያስቀድማሉ (ማቴ 28፡19)፡፡ የቁርአን ጸሐፊ ስለ ክርስትና አስተምህሮ ምንም ዕውቀት የሌለው ሰው መሆኑ ግልፅ ነው፡፡

የቁርአን ጸሐፊ ስለ ክርስትና አስተምህሮ ምንም ፍንጭ ያልነበረው ሰው መሆኑ የተጋለጠበት ሌላው አጋጣሚ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ለማስተባበል በሞከረበት ወቅት ነው፡፡ ሱራ 23፡91 እንዲህ ይነበባል፡- “አላህ ምንም ልጅን አልያዘም (አልወለደም)፡፡ ከእርሱም ጋር አንድም አምላክ የለም…” እንዲሁም ሱራ 9፡30 ላይ ጸሐፊው ስለ ክርስቲያኖች በእርግማን የታጀበ ንግግር ይናገራል፡- “አይሁድ ዑዘይር የአላህ ልጅ ነዉ፣ አለች፤ ክርስቲያኖችም አልመሲሕ የአላህ ልጅ ነዉ አሉ፤ ይህ በአፎቻቸዉ (የሚናገሩት) ቃላቸው ነው፤ የነዚያን ከነሱ በፊት የካዱትን ሰዎች ቃል ያመሳስላሉ፤ አላህ ያጥፋቸዉ (ከእዉነት) እንዴት ይመለሳሉ!” የቁርአን ጸሐፊ አላህ ልጅ አለመውለዱን ሲናገር ሚስት አግብቶ ልጅ መውለድን ታሳቢ በማድረግ መሆኑን ሱራ 6፡101 ላይ “ለርሱ ሚስት የሌለችው ሲሆን እንዴት ልጅ ይኖረዋል?” በማለት ከተናገረው መረዳት ይቻላል፡፡ በተጨማሪም ሱራ 72፡3 ላይ “…ሚስትንም ልጅንም አልያዘም” ይላል፡፡ ብዙ ሙስሊሞች “ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው” የሚለውን ንግግር ሲሰሙ ወደ አዕምሯቸው የሚመጣው ሚስት አግብቶ ልጅ መውለድ የሚለው የተሳሳተ ግንዛቤ በመሆኑ ይህ ንግግር አይዋጥላቸውም፡፡ ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው የሚለው አባባል በእርሱና በእግዚአብሔር አብ መካከል ያለውን ዘላለማዊ ሕብረት ለማመልከት የሚያገለግል መንፈሳዊ አገላለጽ እንጂ ሚስት አግብቶ ልጅ መውለድን የሚያመለክት አይደለም፡፡ ክርስቲያኖች እንዲህ ያለውን ንግግር በእጅጉ ይቃወማሉ፤ ለመስማትም ይጸየፋሉ፡፡

ማጠቃለያ

የቁርአን ጸሐፊ ክርስቲያናዊ አስተምህሮዎችን በትክክል ማቅረብ አለመቻሉ መገለጡ ሁሉን አዋቂ ከሆነው አምላክ ዘንድ እንዳልመጣለትና ውሱን ከሆነው አእምሮው ያመነጫቸው ስለመሆኑ ጥሩ ማስረጃ ነው፡፡ እውነተኛው አምላክ አእማሬ ኩሉ በመሆኑ እንዲህ ያሉ ስህተቶችን ሊሠራ አይችልም፡፡ ሙስሊም ወገኖቻችን በእንዲህ ያሉ ስህተቶች የተሞላውን ቁርአንን ከመከተል ይልቅ እውነተኛ ወደሆነው ቃለ እግዚአብሔር ወደ መጽሐፍ ቅዱስተመልሳችሁ የዘለዓለምን ሕይወት ታገኙ ዘንድ ጥሪ እናደርግላችኋለን፡፡ የልብ ዓይኖቻችሁ ተከፍተው የእውነትንብርሃን ታዩ ዘንድ የዘወትር ጸሎታችን ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ይርዳችሁ!

እግዚአብሔር ማነዉ?