ኢየሱስ ያሕዌ ነው!
ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ
“የመጠበቂያ ግንብ” (Watchtower) የተሰኘው የሐሳውያን ማሕበር “ኢየሱስ ያሕዌ አይደለም” የሚል አቋም አለው፡፡ ይህ አቋሙም ከቅዱሳት መጻሕፍት የተወሰደ ስለመሆኑና የሰዎች ፈጠራ ስላለመሆኑ በአፅንዖት ይናገራል፡፡ በዘመናችን የሚገኙት ብዙ ሙስሊም ሰባኪያን ከዚህ ማሕበር የተቀዱ የሙግት ሐሳቦችን ተጠቅመው ክርስቲያኖችን ሲገዳደሩ ማየት የተለመደ ነው፡፡ ነገር ግን ቅዱሳት መጻሕፍትን በጥልቀት የመረመርን እንደሆን ኢየሱስ ያሕዌ እግዚአብሔር መሆኑ በማያጠራጥርና በማያሻማ ሁኔታ ተጽፎ እንመለከታለን፡፡ በዚህ ጽሑፍ ኢየሱስ ያሕዌ መኾኑን የሚመሰክሩ የቅዱሳት መጻሕፍት ምንባባትን እናቀርባለን፡፡ አንባቢያንም የቅዱሳት መጻሕፍቱን ምስክርነት በማገናዘብ የኢየሱስን ማንነት በተመለከተ ትክክለኛውን አቋም ይወስዱ ዘንድ እናበረታታለን፡፡
እንደሚታወቀው “ያሕዌ” የሚለው ቃል የዕብራይስጥ ቃል እንደመሆኑ በግሪክ አዲስ ኪዳን ውስጥ ተጠቅሶ አናገኘውም፡፡ ስለዚህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ያሕዌ” ተብሎ መጠራቱን ለማረጋገጥ ቃሉ የተጠቀሰባቸውን የብሉይ ኪዳን ምንባባት ከአዲስ ኪዳን ቅዱሳት መጻሕፍት ጋር ማመሳከር ያስፈልገናል፡፡ በዚህ አግባብ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያሕዌ መሆኑን የሚያረጋግጡ የብሉይና የአዲስ ኪዳን ምንባባትን መሳ ለመሳ እናቀርባለን፡-
- “አሕዛብ በአንድነት በተሰበሰቡ ጊዜ መንግሥታትም ለእግዚአብሔር (ያሕዌ) ይገዙ ዘንድ … አቤቱ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፥ ሰማያትም የእጅህ ሥራ ናቸው። እነርሱ ይጠፋሉ፥ አንተ ግን ትኖራለህ፤ ሁላቸው እንደ ልብስ ያረጃሉ፥ እንደ መጐናጸፊያም ትለውጣቸዋለህ፥ ይለወጡማል፤ አንተ ግን ያው አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም።” (መዝ 102፡22-25)
መዝሙረኛው ይህንን ቅኔ እየተቀኘ ያለው ለያሕዌ ነው፡፡ በእብራይስጡ ንባብ ውስጥም “ያሕዌ” የሚለው ስም በተደጋጋሚ ተጠቅሶ የምናገኝ ሲሆን እርሱ “ያሕዌ” በማለት የሚቀኝለት አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደነበር የዕብራውያን ጻሐፊ እንዲህ ያረጋግጥልናል፡-
“ደግሞ፦ጌታ ሆይ [ኢየሱስ]፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፥ ሰማዮችም የእጆችህ ሥራ ናቸው፤ እነርሱም ይጠፋሉ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ፤ ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ፥ እንደ መጎናጸፊያም ትጠቀልላቸዋለህ ይለወጡማል፤ አንተ ግን አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም ይላል።” (ዕብ 1፡10-12)፡፡
- “ይናገሩ ይቅረቡም በአንድነትም ይማከሩ፤ ከጥንቱ ይህን ያሳየ ከቀድሞስ የተናገረ ማን ነው? ያሳየሁም የተናገርሁም እኔ እግዚአብሔር (ያሕዌ) አይደለሁምን? ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ የለም፤ እኔ ጻድቅ አምላክና መድኃኒት ነኝ፥ ከእኔም በቀር ማንም የለም። እናንተ የምድር ዳርቻ ሁሉ፥ እኔ አምላክ ነኝና፥ ከእኔም በቀር ሌላ የለምና ወደ እኔ ዘወር በሉ ትድኑማላችሁ። ቃሌ ከአፌ በጽድቅ ወጥታለች፥ አትመለስም፦ ጕልበት ሁሉ ለእኔ ይንበረከካል፥ ምላስም ሁሉ በእኔ ይምላል ብዬ በራሴ ምያለሁ።” (ኢሳ 45፡21-23)
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በፊልጵስዩስ መልእክቱ ይህንኑ ቃል ለኢየሱስ ክርስቶስ በመጠቀም ያሕዌ መኾኑን ያጸናልናል፡-
“ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።” (ፊል 2፡10-11)
- “እንግዲህ አምላካችሁ እግዚአብሔር (ያሕዌ) የአማልክት አምላክ የጌቶችም ጌታ፥ ታላቅ አምላክ ኃያልም የሚያስፈራም፥ በፍርድ የማያደላ፥ መማለጃም የማይቀበል ነውና እናንተ የልባችሁን ሸለፈት ግረዙ፥ ክእንግዲህ ወዲህም አንገተ ደንዳና አትሁኑ።” (ዘዳ 10፡16-17)
ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ በራዕይ መጽሐፉ ይህኑን ቃል ለክርስቶስ በማዋል ጌታችን ኢየሱስ ያሕዌ መኾኑን አረጋግጦልናል፡-
“እነዚህ በጉን ይወጋሉ፤ በጉም የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ስለ ሆነ እነርሱን ድል ይነሣል፥ ከእርሱም ጋር ያሉ የተጠሩና የተመረጡ የታመኑም ደግሞ ድል ይነሣሉ።” (ራዕይ 17፡14)
- “የእስራኤል ንጉሥ እግዚአብሔር፥ የሚቤዥም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር (ያሕዌ) እንዲህ ይላል፦ እኔ ፊተኛ ነኝ እኔም ኋለኛ ነኝ፥ ከእኔ ሌላም አምላክ የለም። እንደ እኔ ያለ ማን ነው? ይነሣና ይጥራ ይናገርም፤ ከጥንት የፈጠርሁትን ሕዝብ ያዘጋጅልኝ፥ የሚመጣውም ነገር ሳይደርስ ይንገሩኝ።” (ኢሳ 44፡6)
ነብዩ ኢሳያስ በትንቢት መጽሐፉ የጻፈው ያሕዌ ስለኾነው ኢየሱስ ክርስቶስ መኾኑን ዮሐንስ በራዕይ መጽሐፉ እንዲህ ያረጋግጥልናል፡-
“እነሆ፥ በቶሎ እመጣለሁ፥ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ። አልፋና ዖሜጋ፥ ፊተኛውና ኋለኛው፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ፡፡” (ራዕይ 22፡- 12 -13)
- “ከእግዚአብሔር (ያሕዌ) ዘንድ ምሕረት፥ በእርሱም ዘንድ ብዙ ማዳን ነውና እስራኤል በእግዚአብሔር ይታመን። እርሱም እስራኤልን ከኃጢአቱ ሁሉ ያድነዋል።” (መዝ 130፡7-8)
መዝሙረኛው የተቀኘለት ሕዝቡን ከኃጢአታቸው የሚያድናቸው ያሕዌ ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑ በማቴዎስ ወንጌል ውስጥ እንዲህ ተጽፏል፡-
“እርሱ ግን ይህን ሲያስብ፥ እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ታየው፥ እንዲህም አለ፦ የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ፥ ከእርስዋ የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ። ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ።” (ማቴ. 20-21)
- “በዳዊትም ቤት ላይ፥ በኢየሩሳሌምም በሚኖሩት ላይ፥ የሞገስንና የልመናን መንፈስ አፈስሳለሁ ወደ እርሱም ወደ ወጉት ይመለከታሉ ሰውም ለአንድያ ልጁ እንደሚያለቅስ ያለቅሱለታል፥ ሰውም ለበኵር ልጁ እንደሚያዝን በመራራ ኀዘን ያዝኑለታል።” (ዘካ 12፡10)
ለግልፅነት ያህል ይህንን ጥቅስ በአዲሱ መደበኛ ትርጉም እናንብበው፡- “በዳዊት ቤትና በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ላይ የርኅራኄና የልመና መንፈስ አፈሳለሁ፤ ወደ ወጉኝ ወደ እኔም ይመለከታሉ፤ እነርሱም ለአንድያ ልጅ እንደሚለቀስ ያለቅሱለታል፤ ለበኵር ልጅ ምርር ተብሎ እንደሚለቀስም አምርረው ያለቅሱለታል።”
አዲሱ መደበኛ ትርጉምና ብዙ የእንግሊዘኛ ትርጉሞች የተወጋው ያሕዌ እግዚአብሔር ራሱ መሆኑን በሚገልፅ ሁኔታ ተርጉመውታል፡፡ በ1954 ዕትም “ወደ ወጉት ወደ እርሱ” ተብሎ የተተረጎመው መጠነኛ የትርጉም ስህተት እንዳለበት ልብ ሊባል ይገባል፡፡
በገዛ ወገኖቹ የተወጋው ያሕዌ ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን የራዕይ መጽሐፍ እንዲህ ያረጋግጥልናል፡-
“እነሆ፥ ከደመና ጋር ይመጣል፤ ዓይንም ሁሉ የወጉትም ያዩታል፥ የምድርም ወገኖች ሁሉ ስለ እርሱዋይ ዋይ ይላሉ። አዎን፥ አሜን።” ራእይ 1፡- 7፡፡
- “እንዲህም ይሆናል፤ የእግዚአብሔር (ያሕዌ) ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል እግዚአብሔርም እንደ ተናገረ፥ በጽዮን ተራራና በኢየሩሳሌም መድኃኒት ይገኛል። ደግሞም እግዚአብሔር የጠራቸው፥ የምስራች የሚሰበክላቸው ይገኛሉ።” (ኢዩ 2፡32)
ስሙን ስንጠራ የሚያድነን ያሕዌ ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለመሆኑ በሮሜ መጽሐፍ እንዲህ ተጽፏል፡-
“የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና” (ሮሜ 10፡13)
- “እግዚአብሔር (ያሕዌ) እረኛዬ ነው፥ የሚያሳጣኝም የለም። በለመለመ መስክ ያሳድረኛል በዕረፍት ውኃ ዘንድ ይመራኛል።” (መዝ 23፡1-2)
መዝሙረኛው ያሕዌ ሲል የተቀኘለት እረኛችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡-
“በዙፋኑ መካከል ያለው በጉ (ኢየሱስ) እረኛቸው ይሆናልና፥ ወደ ሕይወትም ውኃ ምንጭ ይመራቸዋልና፤ እግዚአብሔርም እንባዎችን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል።” (ራእይ 7፡17)
- “እነሆ፥ ጌታ እግዚአብሔር (ያሕዌ) እንደ ኃያል ይመጣል ክንዱም ስለ እርሱ ይገዛል እነሆ፥ ዋጋው ከእርሱ ጋር ደመወዙም በፊቱ ነው።” (ኢሳ 40፡10)
በተመሳሳይ መልኩ፤ በዚህ ክፍል “ያሕዌ” የተባለው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መኾኑን ቅዱስ ዮሐንስ መስክሯል፡-
“እነሆ፥ በቶሎ እመጣለሁ፥ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ። አልፋና ዖሜጋ፥ ፊተኛውና ኋለኛው፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ። ወደ ሕይወት ዛፍ ለመድረስ ሥልጣን እንዲኖራቸው በደጆችዋም ወደ ከተማይቱም እንዲገቡ ልብሳቸውን የሚያጥቡ ብፁዓን ናቸው። ውሻዎችና አስማተኞች ሴሰኛዎችም ነፍሰ ገዳዮችም ጣዖትንም የሚያመልኩት ውሸትንም የሚወዱና የሚያደርጉ ሁሉ በውጭ አሉ። እኔ ኢየሱስ በአብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ይህን እንዲመሰክርላችሁ መልአኬን ላክሁ። እኔ የዳዊት ሥርና ዘር ነኝ፥ የሚያበራም የንጋት ኮከብ ነኝ።” (ራዕይ 22፡12-16)
- “የእስራኤል ንጉሥ እግዚአብሔር (ያሕዌ)፥ የሚቤዥም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር (ያሕዌ) እንዲህ ይላል፦ እኔ ፊተኛ ነኝ እኔም ኋለኛ ነኝ፥ ከእኔ ሌላም አምላክ የለም።” (ኢሳ 44፡6)
በዚህ ክፍል “ፊተኛውና ኋለኛው” በማለት የሚናገረው ያሕዌ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፦
“… እንዲህም አለኝ፦ አትፍራ፤ ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ፥ ሞቼም (ኢየሱስ) ነበርሁ እነሆም፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ፥ የሞትና የሲኦልም መክፈቻ አለኝ።” (ራእይ 1፡17-18)
- “ንጉሡ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁት፥ የልብሱም ዘርፍ መቅደሱን ሞልቶት ነበር። ሱራፌልም ከእርሱ በላይ ቆመው ነበር፥ ለእያንዳንዱም ስድስት ክንፍ ነበረው በሁለት ክንፍ ፊቱን ይሸፍን ነበር፥ በሁለቱም ክንፍ እግሮቹን ይሸፍን ነበር፥ በሁለቱም ክንፍ ይበር ነበር። አንዱም ለአንዱ። ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር (ያሕዌ) ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች እያለ ይጮኽ ነበር።” (ኢሳ 6፡1-3)
ኢሳይያስ ረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ተቀምጦ ያየው ያሕዌ እግዚአብሔር ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደነበር ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ አረጋግጦልናል፡-
“ኢሳይያስ ደግሞ። በዓይኖቻቸው እንዳያዩ፥ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፥ እንዳይመለሱም፥ እኔም እንዳልፈውሳቸው፥ ዓይኖቻቸውን አሳወረ ልባቸውንም አደነደነ ብሎአልና ስለዚህ ማመን አቃታቸው። ክብሩን ስለ አየ ኢሳይያስ ይህን አለ፥ ስለ እርሱም ተናገረ።” (ዮሐ 12፡39-41)
- አንቺ ከባቢሎን ሴት ልጅ ጋር የምትኖሪ ጽዮን ሆይ፥ ኰብልዪ። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ ከክብሩ በኋላ ወደ በዘበዙአችሁ አሕዛብ ልኮኛል፤ የሚነካችሁ የዓይኑን ብሌን የሚነካ ነውና። እነሆ፥ እጄን በላያቸው አወዛውዛለሁ፥ ተገዝተው ለነበሩት ብዝበዛ ይሆናሉ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም እንደ ላከኝ ታውቃላችሁ። የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እነሆ፥ መጥቼ በመካከልሽ እኖራለሁና ዘምሪ ደስም ይበልሽ፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡ በዚያም ቀን ብዙ አሕዛብ ወደ እግዚአብሔር ይጠጋሉ፥ ሕዝብም ይሆኑኛል፤ በመካከልሽም እኖራለሁ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ወደ አንቺ እንደ ላከኝ ታውቂአለሽ።” (ዘካ 2፡8-10)
ይህንን ጥቅስ ልብ ብለን ያነበብን እንደሆን “ያሕዌ” ተብለው የተጠሩ ሁለት አካላትን እናስተውላለን፡፡ ያሕዌ ተብሎ የተጠራው አንዱ አካል ላኪ ሲሆን በሕዝቡ መካከል እንዲኖር የተላከውም ሁለተኛው አካል ያሕዌ ተብሎ ተጠርቷል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ ከያሕዌ ዘንድ የተላከው “ያሕዌ” ክርስቶስ መኾኑን ይመሰክርልናል፡-
“ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም (ኢየሱስ) ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን።” (ዮሐ 1፡14)
- “ያዕቆብ ሆይ፥ የጠራሁህም እስራኤል ሆይ፥ ስማኝ እኔ (ያሕዌ) ነኝ እኔ ፊተኛው ነኝ እኔም ኋለኛው ነኝ።” (ኢሳ 48፡12)
በተከታዩ የአዲስ ኪዳን ጥቅስ መሠረት ያኔ በብሉይ እኔ “ፊተኛው ነኝ እኔም ኋለኛው ነኝ” ይለን የነበረው አምላክ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፦
“በሰምርኔስም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ። ሞቶ የነበረው (ኢየሱስ) ሕያውም የሆነው ፊተኛውና መጨረሻው እንዲህ ይላል።” ራእይ 2፡- 8፡፡
- “አላወቅህምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፥ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው አይደክምም፥ አይታክትም፥ ማስተዋሉም አይመረመርም።” ኢሳ 40፡- 28፡፡
በክፍሉ እንደተጻፈው ምድርንና ዳርቻዋን የፈጠረው ያሕዌ ጌታ ኢየሱስ ነው፡-
“ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም፡፡” (ዮሐ 1፡3)
- “የአዋጅ ነጋሪ ቃል። የእግዚአብሔርን (ያሕዌ) መንገድ በምድረ በዳ ጥረጉ፥ ለአምላካችንም ጐዳና በበረሀ አስተካከሉ።” (ኢሳ 40፡3)
ኢሳይያስ በትንቢቱ የያሕዌን መንገድ ጥረጉ ሲል የጻፈው ስለ ኢየሱስ መኾኑን ወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ በሚገባ ዘግቦልናል፡-
“እነሆ፥ መንገድህን የሚጠርግ መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ የጌታን (የኢየሱስን) መንገድ አዘጋጁ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ ተብሎ በነቢዩ በኢሳይያስ እንደ ተጻፈ” (የማርቆስ ወንጌል 1፡2-3)
- “እኔ እግዚአብሔር (ያሕዌ) ለሰው ሁሉ እንደ መንገዱ፥ እንደ ሥራው ፍሬ እሰጥ ዘንድ ልብን እመረምራለሁ ኵላሊትንም እፈትናለሁ፡፡” (ኤርምያስ 17፡10)፡፡
በራዕይ መጽሐፍ ውስጥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ በማለት ተናግሯል፡-
“አብያተ ክርስቲያናትም ሁሉ ኵላሊትንና ልብን የምመረምር እኔ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ” (ራእይ 2፡23)
ከላይ ከቀረቡት ጥቅሶች በተጨማሪ ሊመጣ ያለው መሲህ ያሕዌ መሆኑን ቅዱሳን ነቢያት በብዙ መንገዶች ተናግረዋል፡፡ ለምሳሌ ያሕል ነቢዩ ኤርሚያስ እስራኤልን ለማዳን የሚመጣው አዳኝ “ያሕዌ ጽድቄኑ” (እግዚአብሔር ጽድቃችን) በሚል ስም እንደሚታወቅ እንዲህ ተናግሯል፡-
“እነሆ፥ ለዳዊት ጻድቅ ቍጥቋጥ የማስነሣበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር፥ እርሱም እንደ ንጉሥ ይነግሣል፥ ይከናወንለታልም፥ በምድርም ፍርድንና ጽድቅን ያደርጋል። በዘመኑም ይሁዳ ይድናል እስራኤልም ተዘልሎ ይቀመጣል፥ የሚጠራበትም ስም፦ እግዚአብሔር ጽድቃችን ተብሎ ነው።” (ኤር 23፡5-6)
ነቢዩ ሚክያስ በትንቢቱ ሊመጣ ያለው መሲህ ዘላለማዊ መሆኑን እንዲህ ይናገራል፡-
“አንቺም ቤተ ልሔም ኤፍራታ ሆይ፥ አንቺ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ፤ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ፥ በእስራኤልም ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልኛል።” (ሚክ 5፡2)
ነቢዩ ኢሳይያስም ስለ ኢየሱስ ዘላለማዊነት ተመሳሳይ ነገር ተናግሯል፤ አማላክነቱንም እንዲህ ያውጃል፡-
“ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።” (ኢሳ 9፡6)
ነቢዩ ዳንኤልም ስለ ኢየሱስ አምላክነት እንዲህ ሲል መስክሯል፡-
“በሌሊት ራዕይ አየሁ እነሆም፥ የሰው ልጅ የሚመስል ከሰማይ ደመናት ጋር መጣ በዘመናት ወደ ሸመገለውም ደረሰ ወደ ፊቱም አቀረቡት፡፡ ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር መንግሥትም ተሰጠው ግዛቱም የማያልፍ የዘለዓለም ግዛት ነው፥ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው፡፡” (ዳን 7፡13-14)
በዚህ ጥቅስ መሠረት ይህ የሰው ልጅ የተባለው አካል ህዝቦችን ሁሉ የሚገዛ፤ የማያልፍ የዘለዓለም ግዛት ያለውና የማይጠፋ መንግሥት ያለው ነው፡፡ ከአምላክ በስተቀር ህዝቦች ሁሉ ሊገዙት የሚገባ፣ ዘለዓለማዊ ግዛትና መንግሥት ሊኖረው የሚችል ማነው? በዚህ ጥቅስ ውስጥ መገዛትን ለማመልከት ጥቅም ላይ የዋለው “ፕላኽ” የሚለው የአረማይክ ቃል ለፈጣሪ ብቻ የሚሆን አምልኮን የሚያመለክት መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ ኢየሱስ “የሰው ልጅ” የሚለውን ማዕርግ በተደጋጋሚ በመጠቀም ሥጋን ለብሶ የመጣ አምላክ መሆኑን ግልፅ አድርጓል (ማርቆስ 13፡23-27፣ 14፡60-64)፡፡
ስለዚህ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያሕዌ እግዚአብሔር ነው፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት ይህንን ያረጋግጣሉ!
ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ መሆኑን ተናግሯልን?
መሲሁ ኢየሱስ