የሴቶች ምስክርነት በእስልምና – እውን የሴት ምስክርነት የወንድ ግማሽ አይደለምን?

የሴቶች ምስክርነት በእስልምና

እውን የሴት ምስክርነት የወንድ ግማሽ አይደለምን?

የሙስሊሞች ቅዱስ መጽሐፍ የሆነው ቁርኣን የሴቶች ምስክርነት የወንዶችን ምስክርነት ግማሽ ያህል ዋጋ እንዳለው ይናገራል፡-

“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! እስከ ተወሰነ ጊዜ ድረስ በዕዳ በተዋዋላችሁ ጊዜ ጻፉት፡፡ ጸሐፊም በመካከላችሁ በትክክል ይጻፍ፡፡ ጸሐፊም አላህ እንደ አሳወቀው መጻፍን እንቢ አይበል፡፡ ይጻፍም፡፡ ያም በርሱ ላይ ዕዳው ያለበት ሰው በቃሉ ያስጽፍ፡፡ አላህንም ጌታውን ይፍራ፡፡ ከእርሱም (ካለበት ዕዳ) ምንንም አያጉድል፡፡ ያም በርሱ ላይ ዕዳው ያለበት ቂል፣ ወይም ደካማ፣ ወይም በቃሉ ማስጻፍን የማይችል ቢኾን ዋቢው በትክክል ያስጽፍለት፡፡ ከወንዶቻችሁም ሁለትን ምስክሮች አስመስክሩ፡፡ ሁለትም ወንዶች ባይኾኑ ከምስክሮች ሲኾኑ ከምትወዱዋቸው የኾኑን አንድ ወንድና አንደኛዋ ስትረሳ አንደኛይቱ ሌላዋን ታስታውሳት ዘንድ ሁለት ሴቶች (ይመስክሩ)፡፡ ምስክሮችም በተጠሩ ጊዜ እንቢ አይበሉ፡፡ (ዕዳው) ትንሽ ወይም ትልቅ ቢኾንም እስከ ጊዜው ድረስ የምትጽፉት ከመኾን አትሰልቹ፡፡ እንዲህ ማድረጋችሁ አላህ ዘንድ በጣም ትክክል ለምስክርነትም አረጋጋጭ ላለመጠራጠራችሁም በጣም ቅርብ ነው፡፡ ግን በመካከላችሁ እጅ በጅ የምትቀባበሏት ንግድ ብትኾን ባትጽፉዋት በናንተ ላይ ኃጢኣት የለባችሁም፡፡ በተሻሻጣችሁም ጊዜ አስመስክሩ፡፡ ጸሐፊም ምስክርም (ባለ ጉዳዩ ጋር) አይጎዳዱ፡፡ (ይህንን) ብትሠሩም እርሱ በእናንተ (የሚጠጋ) አመጽ ነው፡፡ አላህንም ፍሩ፡፡ አላህም ያሳውቃችኋል፡፡ አላህም ነገሩን ሁሉ ዐዋቂ ነው፡፡” ሱረቱ አል በቀራ (የላም ምዕራፍ) 2፡282

ከቁርኣን ረጃጅም አንቀፆች መካከል አንዱ በሆነው በዚህ አንቀፅ ውስጥ በግልፅ እንደተቀመጠው የሁለት ሴቶች ምስክርነት ከአንድ ወንድ ምስክርነት ጋር እኩል ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ እንደ ምክንያት የተቀመጠው የሴቶች የማስታወስ ችሎታ ነው፡፡ የዓለም ሕዝቦች የሴትን ልጅ የከበረ ተፈጥሯዊ ዋጋ በመረዳት ለእኩልነቷ እየታገሉ በሚገኙበት በዚህ የሰለጠነ ዘመን እንዲህ ያለው አስተሳሰብ ተቀባይነት የለውም፡፡ በዚህም ምክንያት እስልምና በዘመናዊው ዓለም ውስጥ ተቀባይነት እንዲኖረው ጥረት እያደረጉ የሚገኙት ሙስሊም ሰባኪያን ይህንን ቁርአናዊ አስተምሕሮ በማድበስበስ እስልምና የሴትን ልጅ እኩልነት የተገነዘበና የተቀበለ ሃይማኖት ለማስመሰል ሲታትሩ ይስተዋላሉ፡፡ ከላይ የሚገኘውን የቁርኣን አንቀፅ በተለየ መንገድ ለመተረጎም ሲሞክሩና በእስልምና የሴቶች ምስክርነት ከወንዶች እኩል መሆኑን “ማስረጃዎችን” በመስጠት ለማሳመን ሲውተረተሩ ማየትም የተለመደ ነው፡፡

እነዚህ ወገኖች ገና ከጅምሩ በጥቅሱ ውስጥ “አንደኛዋ ስትረሳ” ተብሎ የተተረጎመው تَضِلَّ (ተዲላ) የሚለው የአረብኛ ቃል መርሳትን ሳይሆን መሳሳትን የሚያመለክት በመሆኑ ከሴት ልጅ የማስታወስ ችሎታ ጋር እንደማይያያዝ ይናገራሉ፡፡ የእነዚህ ወገኖች ስህተት ቀጥሎ የተቀመጠውንና ለቃሉ አውድ ሰጪ የሆነውን فَتُذَكِّرَ “ፈቱዘኪረ” የሚለውን ቃል ልብ አለማለታቸው ነው፡፡ “ፈቱዘኪረ” “እንድታስታውሳት” የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን በመርሳት ሰበብ የሚፈጠረውን ስህተት ለማረም ማስታወስን የተመለከተ ነው፡፡ ስለዚህ የሴቷ ስህተት ከመርሳት የሚመነጭ በመሆኑ አንቀፁ እየተናገረ ያለው ስለ ሴት ልጅ የማስታወስ ችሎታ ነው፡፡ ኢብን ከሢር የተሰኘው የቁርኣን ሐታች ይህንን አንቀፅ በዚሁ መንገድ አብራርቶታል፡፡[1]

በሁለተኛ ደረጃ እነዚህ ወገኖች ከላይ የተቀመጠው አንቀፅ ገንዘብ ነክ ጉዳዮችን የተመለከተ በመሆኑ በእስልምና የሴቶች ምስክርነት ከወንዶች በእጥፍ የሚያንሰው በገንዘብ ነክ ጉዳዮች ረገድ ብቻ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ሴቶች በገንዘብ ነክ ጉዳዮች ከወንዶች ያነሰ ዕውቀት ስላላቸው በዚህ ሁኔታ ለምስክርነት ተመራጭ አይደሉም ይላሉ፡፡ በመጀመርያ ደረጃ ሁለት ቡድኖች የገንዘብ ብድር ውል ሲፈፅሙ አይቶ መመስከር የፋይናንስ ሊቅ መሆንን አይጠይቅም፡፡ መሠረታዊ የሰው ልጅ የማስታወስ ችሎታ በቂ በመሆኑ ይህንን አይረቤ ምክንያት በመጥቀስ ሴትን ልጅ በሕግ ፊት የእኩልነትን ደረጃ መንፈግ ትክክል አይደለም፡፡ ይህ ሙግት ተቀባይነት የማያገኝበት ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ሙሐመድ ለጥቅሱ የሰጠው ማብራርያ ነው፡፡ በሙሐመድ እምነት መሠረት የሴት ልጅ ምስክርነት ከወንድ በእጥፍ የሚያንስበት ምክንያት የሴት ልጅ የማሰብ ችሎታ ከወንዶች በእጥፍ ያነሰ በመሆኑ ነው፡፡ ሳሂህ አል-ቡኻሪ ውስጥ ሙሐመድ እንዲህ ማለቱ ተነግሯል፡-

“ሴቶች ሆይ ምፅዋት ስጡ የገሃነም አብዛኞቹ ነዋሪዎች ሴቶች መሆናቸውን አይቻለሁና፡፡ ‹የአላህ መልእክተኛ ሆይ ለምንድነው?› ብለው ጠየቁት፡፡ ‹ብዙ ጊዜ ትሳደባላችሁ፤ ለባሎቻችሁም ምስጋና ትነፍጋላችሁ፡፡ በዕውቀትና በሃይማኖት ከእናንተ በከፋ ሁኔታ ጎደሎ የሆነ አላየሁም›… ሴቶቹም እንዲህ ብለው ጠየቁ፡- ‹የአላህ መልእክተኛ ሆይ በዕውቀትና በሃይማኖት ጎደሎዎች የሆንነው እንዴት ነው?› እርሱም ‹የሁለት ሴቶች ምስክርነት ከአንድ ወንድ ምስክርነት ጋር እኩል አይደለምን?› በማለት ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም በአዎንታ መለሱ፡፡ ‹ይህ በዕውቀት ጎደሎዎች መሆናችሁን ያሳያል፡፡ ሴት በወር አበባ ጊዜዋ መጸለይም ሆነ መፆም አለመቻሏ እውነት አይደለምን?› ብሎ ጠየቃቸው፡፡ ሴቶቹም በአዎንታ መለሱ፡፡ ‹ይህ በሃይማኖት ጎደሎ መሆናችሁን ያሳያል› በማለት መለሱላቸው፡፡”[2]

በሙሐመድ መረዳት መሠረት የሴት ልጅ ምስክርነት ከወንድ በእጥፍ ያነሰው የአስተሳሰብ ጉድለት ስላለባት ነው፡፡ ይህ ሐዲስ በአጠቃላይ ጉዳዮች የሴት ምስክርነት ከወንድ በእጥፍ ያነሰ መሆኑንም ያስረዳል፡፡ ስለዚህ የቁርአኑ አንቀፅ በገንዘብ ነክ ጉዳዮች ብቻ የተወሰነ መሆኑንና የሴትን ልጅ የማስታወስ ችሎታ እንደማይመለከት የሚነግሩን ሙስሊም ሰባኪያን ከሙሐመድ የላቀ ቁርኣንን የመተንተን ሥልጣንና ዕውቀት ኖሯቸው እንደሆን ይንገሩን፡፡ የሙስሊም ሰባኪያን ሙግቶች ሁሉ የእምቧይ ካብ ሆነው ጫወታው እዚህ ጋ ያከተመ ቢሆንም ሌሎች የሙግት ነጥቦቻቸው እስከ ምን እንደሚያስኬዷቸው እንመልከት፡፡

እነዚህ ወገኖች የሚያነሱት ሦስተኛው ነጥብ ቁርኣን የአንዲት ሴት ምስክር ከአንድ ወንድ ምስክርነት ጋር እኩል መሆኑን የገለጸበት ቦታ አለ የሚል ነው፡፡ ለዚህም ተከታዩን ጥቅስ ይጠቅሳሉ፡-

“እነዚያም ሚስቶቻቸውን (በዝሙት) የሚሰድቡ ለእነሱም ከነፍሶቻቸው በስተቀር ምስክሮች የሌሏቸው የኾኑ የአንዳቸው ምስክርነት እርሱ ከውነተኞች ለመኾኑ በአላህ ስም አራት ጊዜ ምሎ መመስከር ነው፡፡” (ሱራ 24፡6)

ይህ ጥቅስ ባል ሚስቱን በምንዝርና በመጠርጠር ቢከሳትና ለጉዳዩ ምስክር ባይኖር እርሷም እርሱም እውነት መናገራቸውን አራት ጊዜ በመማል መመስከር እንደሚችሉ ይናገራል፡፡ ይህ ትዕዛዝ የሴቷ የማሰብ ችሎታ ከወንዱ እኩል መሆኑን በመቀበል ላይ የተመሠረተ ሳይሆን የአስገዳጅ ሁኔታ ትዕዛዝ ነው፡፡ ምስክር ከሌለ የተገኘውን ምስክር እንደ በቂ በመቁጠር አስገዳጁን ሁኔታ ከመዳኘት ውጪ አማራጭ የለም፡፡ ስለዚህ ከዚህ ጥቅስ በመነሳት ቁርኣን የሴትና የወንድ ምስክርነት እኩል እንደሆነ እንደሚያስተምር መናገር አይቻልም፡፡

እነዚህ ወገኖች የሚያቀርቡት አራተኛው ሙግት አይሻ የዘገበቻቸው 2250 የሚሆኑ ሐዲሳት ተቀባይነት ማግኘታቸው የሴት ልጅ ምስክርነት ከወንድ እኩል ተቀባይነት እንዳለው ያመለክታል የሚል ነው፡፡ ይህ ሙግት በሦስት ምክንያቶች ውድቅ ነው፡፡ የመጀመርያው የአይሻ ምስክርነት ተቀባይነትን እንዲያገኝ ሙሐመድ በልዩ ሁኔታ ማዘዙ ነው፡፡ እንዲያውም መገለጥ የሚወርድለት በአይሻ ልብስ ውስጥ ሲሆን እንደሆነ እስከመናገር ደርሷል፡፡[3] ይህም ሙሐመድ ለእርሱ ለቀረቡት ሴቶች አድልዎ ማድረጉን እንጂ በእስልምና ሴት ልጅ ከወንድ ጋር እኩል መታየቷን አያመለክትም፡፡ ሙሐመድ ለእርሱ ቅርበት ለነበራቸው ሴቶች ሲያደላ የመጀመርያው አይደለም፡፡ ልጁ ፋጢማ ላይ ድርብ ጋብቻ እንዳይፈፅም ለአሊ ፅኑ ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ እንመለከታለን፡፡[4] ይህ እስከ አራት ማግባትን የሚፈቅደውን ቁርአናዊ ትዕዛዝ ከመጣስም ባለፈ የሙሐመድን አድሎአዊ አመለካከት በግልፅ የሚያሳይ ነው፡፡ በመሆኑም አይሻ ብዙ ሐዲሳትን መዘገቧ የሙሐመድ ሚስት በመሆኗ ምክንያት አድሎ እንደተደረገላት የሚያሳይ እንጂ ሙስሊም ሴቶችን የሚወክልና በእስልምና ሴቶች ከወንዶች የተስተካከለ ደረጃ እንዳላቸው የሚያሳይ አይደለም፡፡

ይህ ሙግት ውድቅ የሚሆንበት ሁለተኛው ምክንያት በሴቶች የተዘገቡት ሐዲሳት መጠን በወንዶች ከተዘገቡት ጋር ሲስተያይ ኢምንት መሆኑ ነው፡፡ አይሻን ብቻ ነጥለን ባንመለከትና በሴቶች የተዘገቡትን በወንዶች ከተዘገቡት ጋር ብናነፃፅር የምናገኘው ቁጥር የወንዶችን ፍፁማዊ የበላይነት የሚያሳይ በመሆኑ ሙግቱን ውድቅ ያደርገዋል፡፡

ሦስተኛው ምክንያት ደግሞ የአይሻ ትውስታ ከፍተኛ መሆኑና ይህን ያህል የሚበዙ ታሪኮችን ማስተላለፍ መቿሏ ሴት ልጅ ዕድሉን ብታገኝ ምን ያህል ታላላቅ ሥራዎችን መሥራት እንደምትችል በማረጋገጥ የሴትን ልጅ አእምሯዊ ብቃት ዝቅ አድርጎ የሚመለከተውን እስላማዊ አስተሳሰብ ፉርሽ ማድረጉ ነው፡፡ በሙሐመድ አድሎ ዕድሉን በማግኘቷ ምክንያት ብዙ ተግባራትን መፈፀም የቻለችው አይሻ ሴቶች የማሰብ አቅማቸው ከወንዶች እንደማያንስ ጥሩ ምሳሌ ናት፡፡ ስለዚህ ይህ ሙግት በቁርኣንም ሆነ በሌሎች እስላማዊ መጻሕፍት ውስጥ የሰፈሩት የሴትን ልጅ ችሎታና ሚና ዝቅ አድርገው የሚያሳዩት ሐሳቦች ሁሉ ስህተት መሆናቸውን ከማሳየት በዘለለ እስልምና ሴት ልጅ ያላትን የላቀ ዋጋ መቀበሉን የሚያሳይ ሙግት ሊሆን አይችልም፡፡

እነዚህ ወገኖች እንደ መጨረሻ የሙግት ሐሳብ የሚያነሱት በእስልምና ሴቶች የረመዳን ፆም መግባቱንና መውጣቱን የምታበስረዋ ጨረቃ መታየቷን ቢመሰክሩ ምስክርነታቸው ተቀባይነት አለው የሚል ነው፡፡ የአንዲት ሴት ምስክርነት ከእስልምና መሠረቶች በአንዱ ላይ ተቀባይነት አግኝቶ የዓለም ህዝብ ፆሙን እንደሚጀምርና እንደሚፈፅምም በመናገር ሁኔታውን አግዝፈው ለማሳየት ይሞክራሉ፡፡

የነዚህ ወገኖች ትልቁ ስህተት በዚህ ጉዳይ ላይ ሙስሊም ሊቃውንት ከስምምነት የደረሱ በማስመሰል መናገራቸው ነው፡፡ ሴት ልጅ የጨረቃን መውጣት መመስከር እንደምትችል የሚቀበሉት የሀነፊና ሐንበሊ ቤተ እምነቶች ሊቃውንት በደመናማ ቀን ምስክርነቷ ተቀባይነት እንዳለውና በሌላ ቀን ግን ተቀባይነት እንደማይኖረው ይናገራሉ፡፡  የሻፊ ቤተ እምነት ሊቃውንት በደመናማ ቀን መመስከር መቻሏን እንደ አንድ አመለካከት ዕውቅና በመስጠት ነገር ግን ትክክለኛው አመለካከት መመስከር አትችልም የሚለው እንደሆነ ያስተምራሉ፡፡  የሀነፊ ቤተ እምነት ሊቃውንት እንዲያውም በደመናማ ቀን የሁለት ወንዶች ወይንም የአንድ ወንድና የሁለት ሴቶች ምስክርነት ብቻ ተቀባይነት ያለው መሆኑን፤ በጠራ ሰማይ ግን ብዙ ሰዎች ምስክርነታቸውን መስጠታቸው ግዴታ መሆኑን ያስተምራሉ፡፡

የማሊኪ ቤተ እምነት ሊቃውንት ግን በዚህ ረገድ የሴት ልጅ ምስክርነት ተቀባይነት ሊኖረው እንደማይችል የሚያስተምሩ ሲሆን በሻፊዎች አስተምሕሮ መሠረት ትክክለኛው አመለካከት እርሱ ነው፡፡

ፆም ፍቺ መድረሱን ወይንም የሸዋል ወር መግባቱን የምታበስረዋን ጨረቃ አይቶ በመመስከር ረገድ ግን የሴት ምስክርነት በምንም ዓይነት መንገድ ተቀባይነት እንደሌለውና ወንዶች ብቻ መመስከር እንደሚችሉ ሁሉም የእስልምና ቤተ እምነቶች ሊቃውንት ይስማማሉ፡፡ በዚህ ላይ ያለውን አጠቃላይ እስላማዊ ድንጋጌ ከታች በተቀመጠው ኢፊሴላዊ የእስልምና የፋትዋ ድረገፅ ላይ ማየት ይቻላል፡፡[5]

ፆምን ለመጀመር የአንዲት ሴት ምስክርነት ተቀባይነት እንዳለው የሚያምኑ ጥቂት ሊቃውንት ጨረቃ መታየቷን መመስከር መረጃ መስጠት እንጂ ሃይማኖታዊ ትዕዛዝን ማስተላለፍ ባለመሆኑ የሴቷን ምስክርነት መስማት ችግር የለውም ከሚል አመለካከት በመነሳት እንጂ የሴትን ልጅ እኩልነት ከመቀበል አይደለም፡፡[6]

የዚህ ሙግት ሌላው ችግር በእስላማዊ ሐዲሳት ውስጥ ከሚገኙት ከ 25 በላይ ዘገባዎች መካከል ሴት ልጅ የረመዳንን ጨረቃ ዐይታ መመስከር እንደምትችል የሚጠቁም አንድም ዘገባ አለመኖሩ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የሴትን ልጅ ምስክርነት የሚቀበሉት ሊቃውንት ከሙሐመድ የተገኘ ማስረጃ የላቸውም፡፡

እንግዲህ በዝርዝር እንደተመለከትነው በእስልምና የሴት ልጅ ምስክርነት ከወንድ ልጅ ምስክርነት ጋር እኩል መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ የለም፡፡ ከሙሐመድና ከብዙ ሙስሊም ሊቃውንት የተገኙት ማስረጃዎች በሙሉ የሴት ልጅ ምስክርነት ከወንድ በእጥፍ ያነሰ መሆኑን የሚያመለክቱ ናቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ሙሐመድ የሴቶች አእምሯዊ ብቃት ከወንዶች ያነሰ መሆኑን ማመኑ ነው፡፡ ለዚህ ነው ሙስሊም ሊቃውንት የሁለት ሴቶች አእምሯዊ ብቃትና የትውስታ አቅም የአንድ ወንድ ያህል እንደሆነ ያለ ምንም ማቅማማት የሚናገሩት፡፡[7]

ወንዶች በሴቶች ላይ ተፈጥሯዊ ብልጫ እንዳላቸው ቁርኣን እንዲህ ሲል ይናገራል፡-

“ወንዶች በሴቶች ላይ ቋሚዎች (አሳዳሪዎች) ናቸው፤ አላህ ከፊላቸውን በከፊሉ ላይ በማብለጡና (ወንዶች) ከገንዘቦቻቸው (ለሴቶች) በመስጠታቸው ነው። መልካሞቹም ሴቶች (ለባሎቻቸው) ታዛዦች አላህ ባስጠበቀው ነገር ሩቅን ጠባቂዎች ናቸው። እነዚያንም ማመጣቸውን የምትፈሩትን ገሥጹዋቸው፤ በመኝታዎችም ተለዩዋቸው፣ (ሳካ ሳታደርሱ) ምቱዋቸውም። ቢታዘዙዋችሁም (ለመጨቆን) በነርሱ ላይ መንገድን አትፈልጉ። አላህ የበላይ ታላቅ ነውና።” (ሱራ 4፡34)

የእስልምና አስተምሕሮ ይህ ነው፡፡ የሴቶች ሰብኣዊ ዋጋ ከወንዶች ያነሰ ነው፡፡ ስለዚህም ባሎች ሚስቶቻቸውን እስከ መምታት ድረስ በእነርሱ ላይ የበላይነት አላቸው፡፡ ለምስክርነት ከወንድ እኩል መቆም አለመቻላቸው ተፈጥሯቸውን በማሳነስ ከሚመለከተው እስላማዊ አስተምሕሮ የመነጨ ነው፡፡ ዘመናንኛ ሙስሊም ሰባኪያን ይህንን እውነታ አድበስብሰው እስልምናን ለሰዎች ኀሊና ምቹ ለማድረግ ጥረት ቢያደርጉም እስላማዊ መጻሕፍት በተገለጡ ቁጥር ከዚህ መራራ ሃቅ ጋር ለመጋፈጥ ይገደዳሉ፡፡

 


[1] Tafseer Ibn Katheer, part 1, p. 724

[2] Sahih Al-Bukhari vol.1 no.301 p.181. See also Sahih Muslim vol.2 book 4 no.1982,1983 p.432

[3] Sahih al-BukhariHadith Number 2393

[4] Sahih al-Bukhari, Volume 4, Book 53, Number 342; Aisha Bewley, The Sahih Collection of al-Bukhari, Chapter 66. Book of the Virtues of the Companions; source

[5] https://islamqa.info/en/98154

[6] Hidayah v.1 p. 215

[7] I’laam al-Muwaqqa’een, part 1, p. 75

————————–

ሴቶች በእስልምና