የሴት ውርስ በእስልምና ፍትሃዊ ነውን?
ለሙስሊም ኡስታዝ ቅጥፈት የተሰጠ መልስ
ሰለምቴ ነኝ ባዩ ሙስሊም ሰባኪ እስልምና የሴትን ልጅ ውርስ ከወንድ በእጥፍ ማሳነሱን በተመለከተ ለክርስቲያኖች ጥያቄ መልስ ጽፏል፡፡ ይህ አብዱል የመረጠው አካሄድ ሌሎች ሙስሊም ሰባኪያን እንደሚያደርጉት ቁርአናዊውን ድንጋጌ እንዳለ ወስዶ ምክንያቱን ከማብራራት ይልቅ በቁርአን ውስጥ የሚገኙ ሌሎች የውርስ አጋጣሚዎች ሲደማመሩ የሴቷ ውርስ ከወንድ ይበልጣል የሚል ሙግት ነው፡፡ በዚህ ሒደትም መሠረታዊውን ሒሳብ ባለማወቅ ይሁን አንባቢን ለማጭበርበር በማሰብ ግልፅ ባልሆነ ሁኔታ አስገራሚ ስህተቶችን ፈጽሟል፡፡ በዚህ ምላሻችን ስህተቶቹን እናጋልጣለን፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ላነሳው ጥያቄም ምላሽ እንሰጣለን፡፡
አብዱል
የሴት ውርስ
… አንድ ወንድ ልጅ ከወላጆቹ የሚያገኘው ውርስ የሴትን ልጅ እጥፍ ሲሆን አንዲት ሴት ልጅ ከወላጆቿ የምታገኘው ውርስ የወንድ አንድ ሁለተኛ ½ ነው፦
4፥176 ወንድም እና እህት ወንዶችና ሴቶች ቢኾኑም ለወንዱ የሁለት ሴቶች ድርሻ ብጤ አለው፡፡ አላህ እንዳትሳሳቱ ለእናንተ ያብራራል፡፡ አላህም በነገሩ ሁሉ ዐዋቂ ነው፡፡
4፥11 አላህ በልጆቻችሁ ውርስ በሚከተለው ያዛችኋል፡፡ ለወንዱ የሁለት ሴቶች ድርሻ ብጤ አለው፡፡ ሁለት ወይም ከሁለት በላይም የኾኑ ሴቶች ብቻ ቢኾኑ ለእነርሱ ሟቹ ከተወው ድርሻ ከሦስት ሁለት እጁ አላቸው፡፡ አንዲትም ብትኾን ለእርሷ ግማሹ አላት፡፡
“ግማሽ” ማለት አንድ ሁለተኛ ½ ማለት ነው።
መልስ
ግማሽ ማለት አንድ ሁለተኛ መሆኑን የማያውቅ ማንበብና መጻፍ የሚችል ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን ከአፍታ በኋላ እንደምንመለከተው አንተ አንድ-አራተኛ ከአንድ-ስምንተኛ እንደሚበልጥ እንዲሁም አንድ-ሁለተኛ ከአንድ-አራተኛ እንደሚበልጥ አታውቅም፡፡ ስለዚህ ግማሽ ማለት አንድ ሁለተኛ ማለት መሆኑን ማስረዳትን እንደ ትልቅ ዕውቀት ቆጥረህ ብታብራራው እምብዛም አያስገርምም፡፡
አብዱል
በሸሪዓችን አንዲት ሴት ከምታገኘው ገንዘብ ለቤተሰቧ ማለትም ለባሏ እና ለልጆቿ የመስጠት ግዴታ የላባትም፥ በተቃራኒው አንድ ወንድ ሀብትና ንብረት ለቤተሰቡ ማለትም ለሚስቱ እና ለልጆቹ የሚያስፈልገውን ወጪ በሙሉ የማሟላት ግዴታ አለበት፦
4፥34 ወንዶች በሴቶች ላይ አሳዳሪዎች ናቸው፡፡ አላህ ከፊላቸውን በከፊሉ ላይ በማብለጡ እና ወንዶች ከገንዘቦቻቸው ለሴቶች በመስጠታቸው ነው፡፡
2፥233 እናቶችም ልጆቻቸውን ሙሉ የኾኑን ሁለት ዓመታት ያጥቡ፡፡ ይህም ማጥባትን መሙላት ለሻ ሰው ነው፡፡ ለእርሱም በተወለደለት አባት ላይ ምግባቸው እና ልብሳቸው በችሎታው ልክ አለበት፡፡ ነፍስ ችሎታዋን እንጂ አትገደድም፡፡
ሡነን አቢ ዳውድ መጽሐፍ 12, ሐዲስ 99
ሙዓዊያህ አል-ቁሸይሪይ እንደተረከው፦ “ወደ አላህ መልእክተኛ” መጣሁና ስለሚስቶቻችም ምን ይሉናል? ብዬ ጠየኳቸው። እርሳቸውም፦ “የምትበሉትን አብሏቸው! የምትለብሱትን አልብሷቸው!” አሉ”
ቡሉጉል መራም መጽሐፍ 8, ሐዲስ 206
ጃቢር ኢብኑ ዐብደሏህ”ረ.ዐ.” እንደተረከው፦ “ነቢዩ” በረጅሙ በሐዲሱል ሐጅ ስለ ሴት አንስተው እንዲህ አሉ፦ “እነርሱ(ሴቶች) በእናንተ ላይ መብት አላቸው፥ እናንተም ምግባቸውን እና አልባሳታቸው በደግነት አድርጉላቸው”።
መልስ
እንደ ሌሎች ማሕበረሰቦች ሁሉ ሙስሊሞችም ወንዶች ለቤተሰቦቻቸው አስፈላጊውን ነገር የማቅረብ ግዴታ እንዳለባቸው ስለሚያምኑ ከላይ የተጠቀሱት ዓይነት ትዕዛዛት እስላማዊ መጻሕፍት ውስጥ መኖራቸው የተለየ ነገር አይደለም፡፡ ትልቁ ጥያቄ ከመሠረታዊ ፍጆታ በዘለለ እስልምና ለሴቶች የሰጠው መብት ምን ያህል ነው? የሚል ነው፡፡
አብዱል
ለምሳሌ የወላጆች ውርስ 150 ሺህ ቢኖር 50 ሺህ ለሴቷ፥ 100 ሺህ ለወንዱ ነው። ወንዱ ከውርሱ 80 ሺህ ለቤተሰቡ ቢያውል 20 ይቀረዋል፥ ሴቷ ምንም ወጪ ስለማታወጣ 50 ሺህ ተቀማጭ ስላላት በ 30 ሺ ትበልጠዋለች።
መልስ
ሴቷስ ቤተሰብ አይኖራትም እንዴ? በጋብቻ ውስጥ ያለች ሴት ለቤተሰቧ ምንም ወጪ አታወጣም ማለት ነው? የሙስሊም ቤተሰብ የኑሮ ሁኔታ ወንዱ ብቻ ወጪ እያወጣ ሴቷ በግሏ ገንዘብ የምታጠራቅምበት ከሆነ የጤናማ ቤተሰብ አኗኗር አይደለም፡፡ ጤናማ ቤተሰብ ወንዱም ሆነ ሴቷ በሚያገኙት ገቢ ልክ እየተደጋገፉ የሚኖሩበት እንጂ ወንዱ ብቻ ወጪ እያወጣ ሴቷ ገንዘብ የምታጠራቅምበት የኑሮ ዘይቤ አይደለም፡፡ ከላይ ያቀረብከው ሴናርዮ እንኳንስ ሴት ልጅ እንደ ባሏ ንብረት በምትቆጠርበት የሙስሊሙ ዓለም ይቅርና በነፃ ማሕበረሰብ መካከል እንኳ የሚተገበር አይደለም፡፡ ሙስሊም ሴት ገንዘቧ ይቅርና እርሷ ራሷ የባሏ ንብረት ናት፡፡
አብዱል
ነገር ግን የሴት ውርስ የሚሆነው ሁልጊዜ አንድ አይነት አይደለም፥ ለምሳሌ ወላጆች ሟች ልጅ ካላቸው እና ሟቹ ልጃቸው ልጆች ካሉት እናትና አባቱ እኩል እኩል አንድ ስድስተኛ ይወርሳሉ፦
4፥11 “ለአባት እና ለእናቱም ለእርሱ ልጅ እንዳለው ከሁለቱ ለእያንዳንዱ ከስድስት አንድ አላቸው”፡፡
ሟቹ ልጅ ከሌለው አባት አንድ ስድስተኛ ሲያገኝ፥ እናት ከአባት በላይ ሲሶ ማለትም አንድ ሦስተኛ ትወርሳለች፦
4፥11 “ለእርሱም ልጅ ባይኖረውና ወላጆቹ ቢወርሱት ለእናቱ ሲሶው አላት”፡፡
እዚህ ጋርም ከባል ሚስት የበለጠ ውርስ አላት።
መልስ
ሐሰት! እስላማዊ የሸሪኣ ሕግ እንደሚለው አንድ ሰው ልጅ ባይኖረውና ወላጆቹ ቢወርሱት እናት ሲሦ (አንድ ሦስተኛ) የምትወስድ ሲሆን አባት ግን ቀሪውን ይወስዳል፡፡ ይህ ማለት አባት ሁለት ሦስተኛውን ማለትም ከእናት ሁለት እጥፍ ያህል ይወስዳል ማለት ነው፡፡ ምንጭ
አብዱል
ባል እና ሚስት ልጆች ከወለዱ ሚስት ባሏ ሲሞት አንድ ስምንተኛ የምትወርስ ሲሆን፥ ባል ደግሞ ሚስቱ ስትሞት አንድ አራተኛ ይወርሳል። ባል እና ሚስት ልጆች ካልወለዱ ሚስት ባሏ ሲሞት አንድ አራተኛ የምትወርስ ሲሆን፥ ባል ደግሞ ሚስቱ ስትሞት ግማሽ አንድ ሁለተኛ ይወርሳል፦
4፥12 “ለእናንተም ሚስቶቻችሁ ከተዉት ንብረት ለእነርሱ ልጅ ባይኖራቸው ግማሹ አላችሁ፡፡ ለእነርሱም ልጅ ቢኖራቸው ከተዉት ሀብት ከአራት አንድ አላችሁ፡፡ ይህም በእርሷ ከሚናዘዙባት ኑዛዜ ወይም ከዕዳ በኋላ ነው፡፡ ለእናንተም ልጅ ባይኖራችሁ ከተዋችሁት ንብረት ለእነርሱ ለሚስቶች ከአራት አንድ አላቸው፡፡ ለእናንተም ልጅ ቢኖራችሁ ከተዋችሁት ንብረት ለእነርሱ ከስምንት አንድ አላቸው። ይህም በርሷ ከምትናዘዙባት ኑዛዜ ወይም ከዕዳ በኋላ ነው”፡፡
እዚህ ጋርም ከባል ሚስት የበለጠ ውርስ አላት።
መልስ
ኧረ የሒሳብ ያለህ! ምን ጉድ ነው? በአንድ ሁኔታ የባል ውርስ አንድ አራተኛ ሆኖ የሚስት ውርስ አንድ ስምንተኛ ቢሆንና በሌላ ሁኔታ ደግሞ የባል ውርስ አንድ ሁለተኛ ሆኖ የሚስት ውርስ አንድ አራተኛ ቢሆን እንዴት ሆኖ ነው ሚስት ከባል የበለጠ ውርስ የሚኖራት? እንዲህ ያለ ስህተት ከሁለተኛ ክፍል ተማሪ እንኳ የሚጠበቅ አይደለም!
አብዱል
ሟች ወላጅም ልጅም የሌለው ከሆነ ወንድሙ ወይም እኅቱ ቢኖሩ ከሁለቱ ለያንዳንዳቸው ከስድስት አንድ አላቸው፦
4፥12 ወላጅም ልጅም የሌለው በጎን ወራሾች የሚወርስ ወንድ ወይም ሴት ቢገኝ ለእርሱም ለሟቹ ወንድም ወይም እኅት ቢኖር ከሁለቱ ለያንዳንዳቸው ከስድስት አንድ አላቸው፡፡
እዚህ ጋርም የሟች ወንድም እና እህት እኩል እኩል ናቸው። እንግዲህ የውርስ ሕግ ቂያሥ ሲደረግ ሴት ከወላጆቿ የወንድን ግማሽ ½ ብታገኝም፥ ልጅ ካለው ልጇ አንድ ስድስተኛ ⅙ ከባሏ እኩል፣ ልጅ ከሌለው ልጇ አንድ ሦስተኛ ⅓ ባሏን በመብለጥ፣ ባል ቢሞትባት ልጅ ካላቸው አንድ ስምንተኛ ⅛ በመብለጥ፣ ባል ቢሞትባት ልጅ ከሌላቸው አንድ አራተኛ ¼ በመብለጥ፣ ከሟች ወንድሟ ወይም እህቷ የምታገኘው ከወንድሟ ጋር እኩል = በመሆን ከወንድ ይልቅ ብዙ ውርስ የምታገኘው እርሷ ናት። ከወላጆቿ ከላይዮሽ የምታገኘውን ብቻ አስቦ ከቧሏ እና ከወንድምና እህቷ ከጎንዮሽ የምታገኘው እና ከልጇ ከታችዮሽ የምታገኘውን ውርስ ዘንግቶ ተጨቆናለች ማለት ፍትሓዊነት አይደለም።
መልስ
ከላይ የጻፍከው የሁለተኛ ክፍል ሒሳብ ካለማወቅ የተፈጠረ ስህተት አለበለዚያም አንባቢን ከመናቅ የመነጨ ማጭበርበር ነው፡፡ በእስልምና የውርስ ሕግ መሠረት ሴት ከወላጆቿ የምታገኘው ውርስ የወንድ ግማሽ ነው፡፡ ባልና ሚስት ሟች ልጅ ካላቸውና ሟቹ ልጃቸው ልጆች ካሉት እናትና አባት እኩል እኩል አንድ ስድስተኛ ይወርሳሉ፡፡ ልጃቸው ልጅ ከሌለው የእርሷ ውርስ አንድ ሦስተኛ ሆኖ ባል ቀሪውን ማለትም ሁለት ሦስተኛውን ይወርሳል፡፡ ይህ በቁርአን በውስጠ አዋቂነት የተገለጸ በሸሪኣ ሕግ የተብራራ ሲሆን ከሴቷ እጥፍ ያህል ነው፡፡ ባል ቢሞትባት ልጅ ካላቸው ሴቷ አንድ ስምንተኛ የምታገኝ ሲሆን እርሷ ብትሞት ባሏ የርሷን እጥፍ ያህል፣ ማለትም አንድ አራተኛ ያገኛል፡፡ ባል ቢሞትባትና ልጅ ከሌላቸው አንድ አራተኛ የምታገኝ ሲሆን እርሷ ብትሞት ባሏ እጥፍ ያህል፣ ማለትም አንድ ሁለተኛ ያገኛል፡፡ ወራሽ ከሌለው እህትና ወንድም ውርስ እኩል አንድ ስድስተኛ ያገኛሉ፡፡ ከላይ በሚገኙት የቁርአን ጥቅሶች ሴት ልጅ ከወንድ እኩል ውርስ የምታገኘው ልጅ ያለው ልጇ ከሞተና ወራሽ የሌላቸው እህቶቿና ወንድሞቿ ከሞቱ ነው፡፡ በሌሎች ሁኔታዎች ግን የምታገኘው ውርስ ከወንዱ በእጥፍ ያነሰ ነው፡፡ የቁርአን ጥቅሶች ይህንን እንደሚያስረዱ ማንም አንብቦ መገንዘብ የሚችለው ጉዳይ ነው፡፡ ማንበብና መጻፍ እየቻለ ይህንን መገንዘብ የማይችል የምድራችን ብቸኛው ሰው አንተ ሳትሆን አትቀርም!
አብዱል
ሚሽነሪዎች፦ “በቁርኣን ሴት በውርስ የተጨቆነች ናት” የሚሉት በየትኛው ቀመርና ሴት ቀምረውትና አስልተዉት ነው? በየትኛው መስፈትና ሚዛን ለክተውትና መዝነውት ነው?
መልስ
ቀመሩን ከላይ አሳይተናል፡፡ እስልምናን እንወክላለን በማለት ብዙ ተከታይ የሚያንጋጉት ሙስሊም ሰባኪያን የዕውቀት ልካቸው ይህ ከሆነ በእጅጉ አስገራሚ ነው፡፡ አንድ አራተኛ ከአንድ ስምንተኛ፣ አንድ ሁለተኛ ከአንድ አራተኛ እንደሚበልጥ የማያውቅ ሰው በየትኛው ጭንቅላቱ ነው “ሚሽነሪዎችን” መተቸት የሚችለው? ይልቅስ ሚሽን ትምህርት ቤት ገብቶ የሁለተኛ ክፍል ሒሳብ መማር ነው ያለበት፡፡
አብዱል
ይልቁኑስ በባይብል ሴት ልጅ የምትወርሰው ወላጅ ወንድ ልጅ ከሌለው ነው፦
ዘኍልቍ 27፥8 ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ሰው ቢሞት ወንድ ልጅም ባይኖረው፥ ርስቱ ለሴት ልጁ ይለፍ!
ለምሳሌ ሰለጰዓድ ሴቶች ልጆች እንጂ ወንዶች ልጆች አልነበሩትም፥ ስለዚህ የሰለጰዓድ ሴቶች ልጆች ውርስ አልፎላቸዋል፦
ዘኍልቍ 26፥33 የኦፌርም ልጅ ሰለጰዓድ ሴቶች ልጆች እንጂ ወንዶች ልጆች አልነበሩትም።
ዘኍልቍ 27፥7 የሰለጰዓድ ልጆች እውነት ተናግረዋል፤ በአባታቸው ወንድሞች መካከል የርስት ድርሻ ስጣቸው፤ የአባታቸውን ርስት ለእነርሱ አሳልፈህ ስጥ።
አንድ ሰው ወንድም ሴትም ልጅ ከሌለውስ? ለወንድሞቹ ያወርሳል፥ ለእህት ማውረስ የሚባል ሕግ የለም፦
ዘኍልቍ 27፥9 ሴት ልጅም ባትኖረው ርስቱን ለወንድሞቹ ስጡ!
ወንድሞች ከሌሉትስ? ለእህቶቹ ያወርሳል? እረ በፍጹም ለአጎቶቹ ያወርሳል፥ ለአክስት ማውረስ የሚባል ሕግ የለም፦
ዘኍልቍ 27፥10 ወንድሞችም ባይኖሩት ርስቱን ለአባቱ ወንድሞች ስጡ!
ባይብል ሟች ለእናት፣ ለሚስት፣ ለእህት፣ ለአክስት የመውረስ ድርሻና መብት ምንም ያስቀመጠው ነገር የለም። የሴት ውርስ ጭቆና ባይብል ላይ እያለ ቁርኣን ላይ መፈለግ የተቆላበት እያለ የተጋፈበትን መፈለግ ነው። “የምጣዱ እያለ የእንቅቡ ተንጣጣ” ወይም “ቅቤ አንጣሪዋ እያለች ጎመን ቀቃይዋን ምች መታት” ይላል ያገሬ ሰው። አላህ ሂዳያ ይስጣችሁ!
መልስ
ተረቱ ላይ እንደጎበዝከው ሁሉ ሒሳቡም ላይ ብትጎብዝ ጥሩ ነበር፡፡ ከላይ የተጠቀሰው የብሉይ ኪዳን የውርስ ሕግ መሬትን የተመለከተ እንጂ ገንዘብና ሌሎች ንብረቶችን የተመለከተ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር አምላክ የተስፋይቱን ምድር ለእስራኤላውያን ነገዶች ከፋፍሏል (ዘኁልቁ 26፡51-65)፡፡ ይህ ክፍፍል ቀጣይነት ይኖረው ዘንድ የመሬት ርስትን መውረስ ዘር በሚቆጠርባቸው በአባቶች በኩል እንዲሆን ተደርጓል፤ ነገር ግን ወንድ ልጆች በሌሉበት ሴት ልጆች ይወርሳሉ፡፡ ይህም ያ መሬት በዚያ ጎሣና በዚያ ቤተሰብ እጅ እንዲሆን ለማስቻልና በቀጣይነት የርስት ክፍፍል ግጭት እንዳይፈጠር ለመከላከል ጥሩ መንገድ ነው (ዘኁልቁ 27፡1-11)፡፡
የገንዘብና የሌሎች ንብረቶች ውርስን በተመለከተ የበኩር ልጅ ካለበት ኃላፊነት አንፃር እጥፍ እንዲያገኝ ከመደንገጉ ባለፈ (ዘጸአት 21፡15-17) መጽሐፍ ቅዱስ ማሕበረሰቡ እንደየ ሁኔታው እንዲወስን ክፍት አድርጎ ትቶታል፡፡ መሬትንም ቢሆን ወንድ ልጆች በሌሉበት ሴት ልጆች እንዲወርሱ ስለተደነገገ ሴቶችን ሙሉ በሙሉ ያገለለ አይደለም፡፡
የመሬት ርስትን የተመለከተው ትዕዛዝ መለኮታዊ አስተዳደር (Theocracy) ባለበት ሁኔታ ለእስራኤላውያን የተሰጠ ትዕዛዝ መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ከአይሁድ ዘር ያልሆነውን የኢዮብን ታሪክ ስንመለከት ከወንዶች ልጆቹ ጋር ለሴቶች ልጆቹም ርስት ሰጥቷቸዋል፡-
“እግዚአብሔርም ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛውን ለኢዮብ ባረከ፤ አሥራ አራት ሺህም በጎች፥ ስድስት ሺህም ግመሎች፥ አንድ ሺህም ጥማድ በሬዎች፥ አንድ ሺህም እንስት አህዮች ነበሩት። ደግሞም ሰባት ወንዶችና ሦስት ሴቶች ልጆች ሆኑለት። የመጀመሪያይቱንም ስም ይሚማ፥ የሁለተኛይቱንም ስም ቃስያ፥ የሦስተኛይቱንም ስም አማልቶያስ ቂራስ ብሎ ሰየማቸው። እንደ ኢዮብ ሴቶች ልጆችም ያሉ የተዋቡ ሴቶች በአገሩ ሁሉ አልተገኙም፤ አባታቸውም ከወንድሞቻቸው ጋር ርስት ሰጣቸው፡፡” (ኢዮብ 42፡12-15)
ይህ የሚያመለክተው ሴት ልጆች የአባታቸውን ንብረት የመውረስ መብት እንዳላቸው ሲሆን የመሬት ርስትን የተመለከተው ትዕዛዝ ከእስራኤል ውጪ ባሉት ሕዝቦች ላይ እንደማይሠራ ነው፡፡ በአዲስ ኪዳን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ፆታን ሳይለይ ወላጆች ለልጆቻቸው ገንዘብን ማከማቸት እንደሚገባቸው ተናግሯል፡-
“እነሆ፥ ወደ እናንተ እመጣ ዘንድ ስዘጋጅ ይህ ሦስተኛዬ ነው፤ አልከብድባችሁምም፥ እናንተን እንጂ ያላችሁን አልፈልግምና። ወላጆች ለልጆች እንጂ ልጆች ለወላጆች ገንዘብ ሊያከማቹ አይገባቸውምና።” (2ቆሮንቶስ 12፡14)
እስልምና በየትኛውም ዘመንና በየትኛውም አጋጣሚ የሴት ልጅ ውርስ ከወንዱ በእጥፍ ያነሰ እንዲሆን በመደንገግ ለሴት ልጅ የጭቆና መንገድ ከፍቷል፡፡ አንዲት ሴት ብዙ ኃላፊነቶችን የተሸከመችና ለቤተሰቧ ብዙ አስተዋፅዖ ያበረከተች ብትሆን እንኳ ወንድሟ በፆታው ምክንያት ብቻ እጥፍ ውርስ ያገኛል፡፡ ክርስቲያኖች የሰው ልጆች የደረሱበትን ንቃተ ኅሊና ተከትለውና የየአገራታቸውን ሕግጋት አክብረው እንደየሁኔታው የውርስ ክፍፍል ማድረግ ይችላሉ፡፡ ሙስሊሞች ግን ሁኔታዎችን ሳያገናዝብ በደፈናው የሴቶችን ውርስ በእጥፍ ከወንዶች ያሳነሰውን ሕግ በመለኮታዊ መገለጥ ስም ስለተቀበሉ በዚህ ረገድ በሰባተኛው ክፍለ ዘመን በነበረው የአረብ በረሃ ውስጥ ተቸክለው ይኖራሉ፡፡
የቁርአን ደራሲ የሒሳብ ስህተት
ሙስሊም ሰባኪያን ለማብራራት ከተቸገሩባቸው የቁርአን ስህተቶች መካከል አንዱ በውርስ ጥቅሶች ውስጥ የሚገኘውን የሒሳብ ስህተት ነው፡፡ ጥቅሶቹን ካነበብን በኋላ ስህተቱን እናሳያለን፡-
“አላህ በልጆቻችሁ (ውርስ በሚከተለው)፣ ያዛችኋል፣ ለወንዱ የሁለት ሴቶች ድርሻ ብጤ አለው፤ (ሁለት ወይም) ከሁለት በላይም የሆኑ ሴቶች ብቻ ቢሆኑ፣ ለነሱ (ሟቹ ) ከተወው ረጀት ከሦስት ሁለት እጁ አላቸው። አንዲትም ብትሆን ለርሷ ግማሹ አላት። ለአባትና ለእናቱም፣ ለርሱ ልጅ እንዳለው ከሁለቱ ለያንዳንዱ ከስድስት አንድ አላቸው። ለርሱም ልጅ ባይኖረውና ወላጆቹ ቢወርሱት፣ ለእናቱ ሢሶው አላት። ለርሱም ወንድሞችና እህቶች ቢኖሩት ለእናቱ ከስድስት አንድ አላት፣ (ይህም የተባለው) በርሷ ከተናዘዘባት ኑዛዜ ወይንም ከዕዳ በሁዋላ ነው። አባቶቻችሁና ልጆቻችሁ፣ ለናንተ በመጥቀም ማንኛቸው ይበልጥ ቅርብ እንደሆኑ አታውቁም። (ይኽም) ከአላህ የተደነገገ ነው፤ አላህ ዐዋቂ ጥበበኛ ነውና።” (ሱራ 4፡11)
“ለእናንተም ሚስቶቻችሁ ከተዉት ንብረት፣ ለነርሱ ልጅ ባይኖራቸው፣ ግማሹ አላችሁ፤ ለነሱም ልጅ ቢኖራቸው ከተዉት ሀብት ከአራት አንድ አላችሁ፤ (ይህም) በርሷ ከሚናዘዙባት ኑዛዜ፣ ወይንም ከዕዳ በሁዋላ ነው። ለእናንተም ልጅ ባይኖራችሁ፣ ከተዋችሁት ንብረት፣ ለነርሱ(ለሚስቶች) ከአራት አንድ አላቸው፤ ለናንተም ልጅ ቢኖራችሁ፣ ከተዋችሁት ንብረት፣ ለነርሱ ከስምንት አንድ አላቸው፤ (ይህም) በርሷ ከምትናዘዙባት ኑዛዜ በኋላ ነው። ወላጅም ልጅም የሌለው በጎን ወራሾች የሚወርስ ወንድ ወይንም ሴት ቢገኝ፣ ለርሱም (ለሟቹ) ወንድም ወይም እህት፣ (ከናቱ በኩል ብቻ የሆነ) ቢኖር ከሁለቱ ለያንዳንዳቸው ከስድስት አንድ አላቸው። ከዚህም (ከአንድ) የበዙ ቢሆኑ እነርሱ በሲሶው ተጋሪዎች ናቸው፤ (ይኽም ወራሾችን) የማይጎዳ ሆኖ በርሷ ከሚናዘዙባት ኑዛዜ፣ ወይንም ከዕዳ በኋላ ነው። ከአላህም የሆነ ኑዛዜ (ያዛችኋል)፤ አላህም ዐዋቂ ቻይ ነው።” (ሱራ 4፡12)
“ይጠይቁሃል፤ በላቸው፦ ወላጅና ልጅ ሳይኖረው በሚወረስ ሰው አላህ ይነግራችኋል፤ ለርሱ ልጅ የሌለው ሰው ቢሞት እርሱም እኅት ብትኖረው ለርስዋ ከተተወው ረጀት ግማሹ አላት።እርሱም ለርሷ ልጅ የሌላት እንደሆነች (በሙሉ) ይወርሳታል። ሁለት (እኅቶች ወይም ከሁለት በላይ) ቢሆኑም፣ ከተወው ረጀት ከሦስት ሁለት እጁ አላቸው። ወንድሞች (ና እኅቶች) ወንዶችና ሴቶች ቢሆኑም፣ ለወንዱ የሁለት ሴቶች ድርሻ ቢጤ አለው። አላህ እንዳትሳሳቱ ለናንተ ያብራራል። አላህም በነገሩ ሁሉ አዋቂ ነው።” (ሱራ 4፡176)
እነዚህ ጥቅሶች ብዙ ክፍተቶች አሉባቸው፡፡ ለምሳሌ ያህል ወራሽ ቤተሰብ የሌለው ሰው ውርሱን ወንድሞቹና እህቶቹ እንዲካፈሉ በቁጥር 112 ላይ የተነገረው በቁጥር 176 ላይ ሲደገም እርስ በርሱ የሚጋጭ ክፍልፋይ ነው የተሰጠው፡፡ እንዲህ ያሉ በርካታ ችግሮች ቢኖሩም ለጊዜው እናቆያቸውና የሒሳቡን ችግር ብቻ እንመልከት፡፡ ችግሩ ቁርአን ያስቀመጠው የኃብት ክፍፍል በብዙ ሁኔታዎች የማይሠራና ክፍፍሉ ሲደመር ከኃብቱ በላይ መሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው 3 ሴት ልጆቹን፣ ሚስቱንና ወላጆቹን ትቶ ቢሞት በጥቅሶቹ መሠረት የኃብት ክፍፍሉ የሚከተለውን ይመስላል፡-
3 ሴት ልጆች | 1 ሚስት | 2 ወላጆች | ድምር |
2/3 | 1/8 | 1/3 (እያንዳንዳቸው 1/6) | 2/3+1/8+1/3=1.125 ወይም 1+1/8 |
ከላይ እንደሚታየው ኃብቱ ለ 3 ሴት ልጆችና ወላጆች ብቻ የሚበቃ ሲሆን ለሚስት የተወሰነው 1/8ኛ ከአጠቃላይ ኃብቱ ውጪ ነው፡፡ ከየት አምጥተን ነው የምንሰጣት? ምናልባት ይህ ሒሳብ የአራተኛ ክፍል ትምህርት በመሆኑ ሙስሊሙ ሰባኪ ላይረዳው ይችላል የሚል ስጋት አለኝ፡፡
ሌላ አንድ ምሳሌ እንጨምር፡፡ ይህኛው በጣም ቀላል ነው፡፡ ጥቅሱ የሚለውን ተመልከቱ፡- “ለወንዱ የሁለት ሴቶች ድርሻ ብጤ አለው፤ (ሁለት ወይም) ከሁለት በላይም የሆኑ ሴቶች ብቻ ቢሆኑ፣ ለነሱ (ሟቹ ) ከተወው ረጀት ከሦስት ሁለት እጁ አላቸው። አንዲትም ብትሆን ለርሷ ግማሹ አላት።”
ወንዱ የሴቷን እጥፍ ያህል የሚወርስ ከሆነና የሴቷ ድርሻ የኃብቱ ግማሽ ከሆነ ወንዱ ጠቅላላውን ኃብት ስለሚወስድ ድምር ውጤቱ ከመቶ ፐርሰንት አልፎ 150% ነው የሚሆነው!
እውን ይህ ከሰማይ የወረደ መገለጥ ነውን?