ያሕዌ ጽድቃችን – የመሲሑን አምላክነት የሚያረጋግጥ ስያሜ

ያሕዌ ጽድቃችን

የመሲሑን አምላክነት የሚያረጋግጥ ስያሜ

በወንድም ሚናስ


እንደሚታወቀው ብሉይ ኪዳን፣ ስለ መሲሑ አያሌ ትንቢቶችን የያዘ መጽሐፍ ነው። በብዙኃን ዘንድ በዋነኝነት በመዝሙረ ዳዊትና በትንቢተ ኢሳይያስ ያሉ ክፍሎች በተደጋጋሚ ቢጠቀሱም፣ ሌሎች ምንባባትም ስለ መሲሑ በርካታ ትንቢቶችን እንዳሰፈሩ መዘንጋት የሌለበት እውነታ ነው። ከእነዚህም ውስጥ አንዱ የነብዩ ኤርምያስ ትንቢት ነው። ለዛሬ በምዕራፍ 23፥5-6 ያለውን ጥቅስ እንመለከታለን፦

ኤርምያስ 23፥5-6፦ “እነሆ፤ ለዳዊት፣ ጻድቅ ቅርንጫፍ(צָמַח) የማስነሣበት ጊዜ ይመጣል፤ እርሱም ፍትሕንና ጽድቅን የሚያደርግ፣ በጥበብ የሚገዛ ንጉሥ ይሆናል” ይላል እግዚአብሔር። በእርሱም ዘመን ይሁዳ ይድናል፤ እስራኤልም በሰላም ይኖራል፤ የሚጠራበትም ስም፣ ‘ያህዌ ጽድቃችን'( יְהוָה צִדְקֵנוּ) የሚል ነው።”

እንግዲህ በዚህ አነስተኛ መጣጥፍ ውስጥ፣ “ቅርንጫፍ” የሚለውን ቃል ትርጓሜ፣ እንዲሁም “ያሕዌ ጽድቃችን” የሚለው ቃል መሲሑ አምላክ መሆኑን እንዴት እንደሚያመለክት እናትታለን።

1. “ቅርንጫፍ” (צֶ֣מַח) የሚለው ቃል ትርጉም

በብሉይ ኪዳን በተለይም በትንቢተ ኤርሚያስና በመዝሙረ ዳዊት ላይ “ቅርንጫፍ” (በዕብራይስጥ፦ צֶ֣מַח “ጻማዕ”) የሚለው ስም መሲሑን ለማመልከት የሚያገለግል ተምሳሌታዊ ቃል መሆኑን ብዙ ሊቃውንት የሚስማሙበት ጉዳይ ነው[1]። ለምሳሌ መዝሙረኛው የተናገረውን እንውሰድ ፦

““በዚህም ለዳዊት ቀንድ አበቅላለሁ (אַצְמִ֣יחַ)፤ ለቀባሁትም ሰው መብራት አዘጋጃለሁ።”— መዝሙር 132፥17 (አዲሱ መ.ት)

“አበቅላለሁ” ለሚለው የገባው የዕብራይስጥ ቃል אַצְמִ֣יחַ “ኣፄሚያ” የሚል ሲሆን የ צָמַח “ጻማዕ” አንደኛ መደብ ነጠላ ሲሆን፣ ዋና ትርጉሙም “ቅርንጫፍ” የሚል ነው። ይህንን ጥቅስ ሚድራሽ ታንኹማ የተሰኘ ጥንታዊ የአይሁድ መጽሐፍ፣ ይህ ቅርንጫፍ መሲሑ ነው ይለናል፦

“ለዳዊት ቀንድን አበቅላለሁ በዚያም ለቀባሁት መብራትን አዘጋጃለሁ (መዝ. 132:17) መባሉ መሲሑን ያመለክታል።”[2]

በተጨማሪም፤ በአረማይክ ታርጉም ላይ “በዚያን ቀን የእግዚአብሔር ቅርንጫፍ ያማረና የከበረ ይሆናል”(ኢሳ 4፥2) የሚለውን “በዚያን ቀን የእግዚአብሔር መሲሕ ያማረና የከበረ ይሆናል”፤ ሲል “እነሆ፤ ባሪያዬን ቊጥቋጡን አመጣለሁ።”(ዘካርያስ 3፥8) የሚለውንም “እነሆ፤ ባሪያዬን መሲሑን አመጣለሁ።” ብሎ አስቀምጧታል።

2.የሚጠራበት ስም “ያህዌ ጽድቃችን” ነው

ኤርምያስ መሲሑን “ጻድቅ ቅርንጫፍ” ብሎ ከጠራው በኋላ፣ “ያሕዌ ጽድቃችን” (ኤር 23፥6) በማለት መሲሓዊ ኑባሬውን ጠቅሷል። ይህ በግልጽ የመሲሑን መለኮትነት እየተናገረ ነው። ሆኖም የመሲሑን አምላክነት የማይቀበሉ አይሁዳውያንም ሆኑ ሌላ የእምነት ቡድኖች የሚከተለውን ሙግት አዘውትረው ይጠቀማሉ። “ያህዌ ጽድቃችን” የሚለው የያህዌ ስም አጫፋሪ ስም ሆኖ የመጣበት መጠሪያ ነው፥ “ያህዌ ” አጫፋሪ ስም ሆኖ መግባቱ አምላክነትን ካሳየ፣ “ኤልያህ” (ያሕዌ አምላኬ ነው)፤ “ኤርሚያህ”(ያሕዌ ከፍ ያደርጋል)፤ “ኢሳይያህ ”(ያሕዌ ያድናል)፤ ወዘተ… በመሰል ስሞች የተጠሩ ግለሰቦች ያሕዌ ሊሆኑ ነው” ይሉናል። ይህ ግን ድኩም ሙግት ነው፣ ምክንያቱ ደግሞ ከላይ የተዘረዘሩት መጠሪያዎች “ያህ” በሚለው የያሕዌ ምህፃረ ቃል ጋር የተጫፈሩ ስመ-ያሕዌን የተሸከሙ መጠሪያዎች ናቸውና። ይኸውም የኤልያስን፤ የኢሳይያስን ወይም የኤርሚያስን ባሕርይ ለመግለጽ የታሰቡ ሳይሆን፣ ያመኑትን አምላክ የሚገልጹ ስሞች ናቸው። ነገር ግን በትንቢተ ኤርሚያስ መሲሑ “ያሕዌ ጽድቃችን” መባሉ “ያህ” በሚል ከተጫፈሩት መጠሪያዎች ፈጽሞ የተለየ ነው። ምክንያቱ ደግሞ ኤርሚያስ በክፍሉ ባሕርዩ ጻድቅ መሆኑን እየነገረን ያለው መሲሑን እንጂ ሌላን ማንነት አይደለምና። ጥቅሱን በትኩረት እናንብብ፦

ኤርምያስ 23፥5-6 “እነሆ፤ ለዳዊት፣ ጻድቅ ቅርንጫፍ የማስነሣበት ጊዜ ይመጣል፤ እርሱም ፍትሕንና ጽድቅን የሚያደርግ፣ በጥበብ የሚገዛ ንጉሥ ይሆናል” ይላል እግዚአብሔር። በእርሱም ዘመን ይሁዳ ይድናል፤ እስራኤልም በሰላም ይኖራል፤ የሚጠራበትም ስም፣ ‘እግዚአብሔር ጽድቃችን’ የሚል ነው።” (አዲሱ መ.ት)

በአጭር ቃል ነብዩ እያለን ያለው መሲሑ በኑባሬው (በባሕርዩ) ጻድቅ ስለሆነ ጽድቅን ያደርጋል። ምክንያቱ ደግሞ እርሱ ጽድቃችን የሆነው ያሕዌ በመሆኑ ነው። ስለዚህም በትንቢተ ኤርሚያስ ውስጥ ያለው ክፍል መሲሑ መለኮት መሆኑን ያስገነዝበናል።


[1]The Moody Handbook of Messianic Prophecy, pg. 1014

[2] Midrash Tanchuma, Terumah 7:1


በእንተ ኤርምያስ 23፥5-6

ለሙስሊም ሰባኪ ስሁት ሙግት ምላሽ

ከላይ የሚገኘውን ጽሑፍ ማሕበራዊ ሚድያዎች ላይ ያነበበ አንድ ሙስሊም ሰባኪ ለጽሑፉ መልስ ብሎ የሞነጫጨረውን አንድ ወዳጄ ልኮልኝ አንብቤያለሁ። ጽሑፉ ከላይ ባለው ሐተታ መልስ የተሰጠበትን ነጥብ የሚደግም ቢሆንም የክርስቶስን አምላክነት የሚክዱ ወገኖች እንዴት ያሉ ስሁት ሙግቶችን እንደሚጠቀሙ ለማሳየት ጥሩ ምሳሌ ሆኖ ስላገኘሁት መልስ እሰጠዋለሁ። እንዲህ ሲል ይጀምራል፦ 

አብዱል፦

5፥17 እነዚያ አላህ እርሱ የመርየም ልጅ አልመሲሕ ነው ያሉ በእርግጥ ካዱ፡፡ لَّقَدْ كَفَرَ الَّذِينَ قَالُوا إِنَّ اللَّهَ هُوَ الْمَسِيحُ ابْنُ مَرْيَمَ

መሢሕ ከዳዊት እና ከእሴይ ሥር የሚያቆጠቁጥ ሰው ነው፥ ይህ ሰው ለፈጣሪ ባሪያ ስለሆነ ፈጣሪ እርሱን “ባርያዬ” ይለዋል፦
ዘካርያስ 3፥8 እነሆ እኔ ባሪያዬን “ቍጥቋጥ” አወጣለሁ።
ዘካርያስ 6፥12 የሠራዊት ጌታ ያህዌህ እንዲህ ይላል፦ እነሆ ስሙ “ቍጥቋጥ” የሚባል ሰው በስፍራው ይበቅላል።

መልስ፦
ጌታችን በመሲህነቱ  በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የባርያን መልክ ይዞ መለኮታዊ ክብሩን በመተው እንደ መመላለሱ “አገልጋይ” ወይም “ባሪያ” ተብሎ ቢጠራ ሰብዓዊ ባሕርዩን እንጂ መለኮታዊ ባሕርዩን ስለማይነካ አምላክነቱን ለማስተባበል የሚውል ሙግት ሊሆን አይችልም (ፊልጵስዩስ 2፡4-12)፡፡

አብዱል፦

የሚበቅለው “ሰው” መባሉን ልብ አድርግ! ይህ ሰው ስል
ለሚያቆጠቁጥ የማዕረግ ስሙ “ቍጥቋጥ” ተብሏል፦
ኤርምያስ 23፥5 እነሆ፥ ለዳዊት ጻድቅ “ቍጥቋጥ” የማስነሣበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል ያህዌህ።
ኤርምያስ 33፥15 በዚያም ዘመን በዚያም ጊዜ ለዳዊት የጽድቅን ቍጥቋጥ አበቅልለታለሁ
ኢሳይያስ 11፥1 ከእሴይ ግንድ በትር ይወጣል፥ ከሥሩም “ቍጥቋጥ” ያፈራል።

ኢሳይያስ ላይ “ቍጥቋጥ” የሚለው የዕብራይስጥ ቃል “ነሰር” ‏נֵ֫צֶר‎ ሲሆን ኢሳይያስ፣ ኤርሚያስ እና ዘካርያስ “ቁጥቋጦ” ብለውታል፥ ይህ መሢሕ ናዝሬት ወደምትባል ከተማ መጥቶ ሲኖር በነቢያት ማለትም በኢሳይያስ፣ በኤርሚያስ እና በዘካርያስ “ቁጥቋጦ” የተባለው ትንቢት ተፈጸመ፦
ማቴዎስ 2፥23 በነቢያት፦ “ናዝራዊ” ይባላል” የተባለው ይፈጸም ዘንድ፥ ናዝሬት ወደምትባል ከተማ መጥቶ ኖረ።

“ናዝራዊ” የሚለው ቃል በግሪኩ “ናዙራኦስ” Ναζωραῖος ሲሆን ይህም ቃል “ነሰር” ‏נֵ֫צֶר‎ ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል የተገኘ ነው፥ መሢሑ ፈጣሪ የሚያስነሳው ሰው እና ከእሴይ ሥር የሚያቆጠቁጥ “ቍጥቋጥ” ነው።///

መልስ፦

በመጀመሪያ ይኽ ሙስሊም ሰባኪ የፈጸማቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ በኩረ ጽሑፍ የሆኑትን የዕብራይስጥና የግሪክ ቃላት ስህተቶችን በማረም እንጀምር፣ “ነሰር” ‏נֵ֫צֶר‎ ብሎ ያነበበው ቃል በትክክል ሲነበብ “ኔጼር” የሚል ነው። ምንም አይነት የ “ሰ” ድምፅ የሚሰጥ ፊደል በሌለበት ሁኔታ የ “ጸ” ድምጽ ያላትን ፊደል “ሰ” ብሎ ማንበቡ የዕብራይስጥ ፊደላትን በመሠረታዊ ደረጃ እንደማያውቅ ማሳያ ነው። ግሪኩም ቢሆን ሲነበብ Ναζωραῖος “ናዞራይኦስ” እንጂ  “ናዙራኦስ” አይደለም። ምን አለ ይህ ወገናችን በሚያውቀው ልክና መጠን ቢናገር፤ ወይም አስፈላጊ የመርጃ መሣርያዎችን ቢጠቀም? 

ወደ ሌላኛው ስሕተቱ ስንገባ “ኢሳይያስ ላይ “ቍጥቋጥ” የሚለው የዕብራይስጥ ቃል “ነሰር” ‏נֵ֫צֶר‎ ሲሆን ኢሳይያስ፣ ኤርሚያስ እና ዘካርያስ “ቁጥቋጦ” ብለውታል፥” ብሎ በተናገረው ኢሳይያስ 11፥1 ላይ የገባው የዕብራይስጥ ቃል እንደ እርሱ አነባነብ נֵ֫צֶר‎ “ነሰር” ብንል ቃሉ በትንቢተ ኤርሚያስ 23፥5 እና ኤርሚያስ 33፥15 ላይ  ጸሐፊው ያስቀመጠው የዕብራይስጥ ቃል አይደለም። በኹለቱ ምንባባት ማለትም፣ ኤርሚያስ 23፥5 እና ኤርሚያስ 33፥15  ያለው ቃል ጸሐፊው እንዳለው נֵ֫צֶר‎ “ነሰር” ሳይሆን צֶ֣מַח “ጻማዕ” የሚል ነው ስለዚህ ሙስሊሙ ሰባኪ እንዳለው  መሲሑ ናዝሬት ወደምትባል ከተማ መጥቶ ሲኖር በነቢያት ማለትም በኢሳይያስ፣ በኤርሚያስ እና በዘካርያስ “ቁጥቋጦ” የተባለው ትንቢት ተፈጸመ የሚለው ሙግቱ ሊያስኬደው አይችልም። ምናልባት ትንቢተ ኢሳይያስ 11፥1 የማቴዎስ 2፥23 ፍጻሜ ሊሆን ቢችልም፣ በኤርምያስ 23፥5 እና ኤርሚያስ 33፥15 ላይ נֵ֫צֶר‎ “ኔጼር” የሚል ነገር ስለሌለ የማቴዎስ 2፥23 ነው ለማለት አንዳች አያስደፍርም። ይህንን እውነታ ማስተዋል ያልቻለ ሰው ይህ ሙስሊም ሰባኪ በሚያሳየው ድፍረት ልክ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የመናገር ሞራል ሊኖረው አይገባም።

አብዱል፦

ክርስቲያኖች “ይህ ቍጥቋጥ እራሱ ያህዌህ ነው” በማለት ይዋሻሉ፥ እንደ ማስረጃ አድርገው የሚጠቅሱት ጥቅስ ይህንን ነው፦ ኤርምያስ 23፥6 በዘመኑም ይሁዳ ይድናል እስራኤልም ተዘልሎ ይቀመጣል፥ የሚጠራበትም ስም፦ “ያህዌህ ጽድቁኑ” ተብሎ ነው። ሲጀመር ዐውዱን በአጽንዖት እና በአንክሮት ካየነው ለዳዊት ጻድቅ “ቍጥቋጥ” መሢሑ ሲነሳ ይሁዳ ይድናል እስራኤልም ተዘልሎ ይቀመጣል፥ “የሚጠራበት” የተባለው ተባታይ አንቀጽ “እስራኤል” እንጂ ቍጥቋጥው በፍጹም አይደለም። ይህንን በተመሳሳይ ሰዋስው ሌላ ቦታ ተቀምጧል፦
ኤርምያስ 33፥16 በዚያም ዘመን ይሁዳ ይድናል ኢየሩሳሌምም ተዘልላ ትቀመጣለች፥ የምትጠራበትም ስም፦ “ያህዌህ ጽድቁኑ” ተብሎ ነው። “ኢየሩሳሌም” የሚለው ቃል “እስራኤል” በሚል ተለዋዋጭ ቃል መምጣቱን ልብ አድርግ! “የምትጠራበት” የተባለችው አንስታይ አንቀጽ እርሷ “ያህዌህ ጽድቁኑ” ተብሎ ነው፥ ስለዚህ “ያህዌህ ጽድቁኑ” ተብሎ የተጠራው መሢሑ ነው” ብሎ መሞገት እጅግ ሲበዛ የዐውድ ክፍል እና የሰዋሰው አወቃቀር በቅጡ ያልተረዳ ሰው ሙግት ነው።

መልስ፦

ክፍሉን በጥንቃቄ እንመልከት። ቍጥር 5 ላይ እንዲህ ይላል፦

“እነሆ፤ ለዳዊት፣ ጻድቅ ቅርንጫፍ የማስነሣበት ዘመን ይመጣል፤…”

ይህ ሙስሊም ጸሐፊ በቍጥር 5 የተጠቀሰው “ቅርንጫፍ” የተባለው መሲሑ መሆኑን ቢያምንም ትንቢቱ የተገባደደው በዚሁ ቍጥር እንጂ፣ በቍጥር 6 አይደለም የሚል ነው።  ስለዚህ ክፍሉን በጥንቃቄ በመፈተሽ እውነታውን እንመልከት። ነብዩ ኤርምያስ በቍጥር 5 ላይ እየተናገረ ያለው መሲሑ ስለሚነሳበት ዘመን  ነው። “ዘመን”፤ “ጊዜ”፤ ተብሎ የተተረጎመው፣ יוֹם “ዩም” የሚለው  የዕብራይስጥ ቃል በቍጥር 6 ላይ ተባዕታይ፤ ዘርፍ ሙያ በመሆን  “በእርሱም ዘመን” ተብሎ ተጠቅሷል።  “በእርሱም ዘመን” (בְּיָמָיו֙) ተብሎ የተቀመጠው የዕብራይስጥ ቃል ተባዕታይ፤ ዘርፍ ሙያ ስለሆነ “በእርሱ ዘመን” የሚል ትርጉም አለው። ይኽውም በቍጥር 5 ላይ ይመጣል ስለተባለው መሲሕ ቍጥር 6 ተጨማሪ ማብራሪያ እያቀረበ ስለሆነ፤ “የሚጠራበት ስም” የተባለው የክፍሉ ንሑስ ሐረግ የሆነውን መሲሑን እንጂ እስራኤልን አይደለም።

ሲቀጥል በአውደ ንባቡ ጽድቁ እየተነገረለት ያለው መሲሑ እንጂ እስራኤል አይደለም፣ ምክንያቱም በቍጥር 5 ላይ፦ “ጻድቅ ቅርንጫፍ (צֶמַח צַדִּיק) …በምድር ጽድቅን የሚያደርግ(וּצְדָקָה בָּאָרֶץ)…” ብሎ ከገለጸ በኋላ በቍጥር 6 ላይ ይኼ ጻድቅ የኛም ጽድቅ የሆነ መለኮት መሆኑን ለማሳየት ስሙን “ያሕዌ ጽድቃችን” ብሎ ይሰልሰዋል።  ስለዚህ በአውደ ጽሑፉ ላይ ዋናው ንሑስ ሐረጉ መሲሑ እንጂ በምንም ሁኔታ እስራኤል አይደለም።  ይኽ ብቻም አይደለም፣ ክርስቲያን ያልሆኑ እጅግ ጥንታዊ የሆኑ ስመጥር የአይሁዳውያን መዛግብት በትንቢተ ኤርምያስ ምዕራፍ 23፥6 የተጠቀሰው መሲሑ መሆኑን አስፍረዋል። የተወሰኑትን ለመመልከት ያህል፦

“እግዚአብሔር ንጉሡን መሲሕ ብሎ በስሙ ይጠራዋል። ምክንያቱ ደግሞ ስለ ንጉሡ መሲህ የሚጠራበት ስሙ ይህ ነውና ፡- ያህዌ ጽድቃችን (ኤር. 23፡6)።”[1]

“…መሲሑን በተመለከተ እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ፦ “የሚጠራበትም ስሙ ይህ ነው፤ እግዚአብሔር ጽድቃችን ነው”[2]

የክርስትናን ነገረ መለኮት በመጻረር በርከት ያሉ ሙግቶችን የሚያቀርበው ይሁዲው ጌራልድ ሴጋል እንኳን በኤርምያስ 23፥2-6 ላይ የመሲሑ መለኮትነትን አያሳይም ብሎ ባቀረብው ሙግቱ እንደ ሙስሊሙ ሰባኪ በቍጥር 6 ላይ “ያሕዌ ጽድቃችን” የተባለው መሲሑ መሆኑን በመካድ አልነበረም[3]።

የኤርምያስ 33ን ዐውድ ስናነብ ደግሞ  ‘“ከዳዊት ዘር በእስራኤል ቤት ዙፋን ላይ የሚቀመጥ ሰው ፈጽሞ አይታጣም፤” (ኤር 33፡17) ይላል። ይህም ወደ መጨረሻው፣ ወደ ታላቁ የዳዊት  ዘር በሆኑ ነገሥታት አማካይነት ሊመጣ  ያለውን አካል የሚያመለክት ነው።  በኤርምያስ የተነገሩት የመጀመሪያዎቹ የባቢሎን ግዞት (ኢየሩሳሌም ስትወድቅ አይቶ) በዳዊት በትረ መንግሥት ላይ ገዢ የነበሩት በኢየሩሳሌም በዙፋኑ ላይ የተቀመጡ አለቆች ጊዜያዊ  አገዛዝ መቋረጥ እንዳለበት  ይናገራል። በእርግጥ በሁለተኛው ቤተመቅደስ ዘመን የዳዊት ዙፋን አለመታደስ በእስራኤል ውስጥ ስነ-መለኮታዊ ቀውስ ማስከተሉ በመጨረሻ ፍጻሜ ያለው መሲሃዊ ተስፋ  ምክንያት ሆኗል (ኤር 23፥5-6)። በመጨረሻም የነቢያትን  መሲሃዊ ተስፋ የበለጠ ለመረዳት ያስቻለው ይህ ቀውስ እንደሆነ መናገሩ የበለጠ የኤርምያስ 23፥5-6 ሐሳብ ያጸናል። ስለዚህ በኤርምያስ 33፥16 እና ከኤርምያስ 23፥5-6 በማዋሐድ ትንቢቱ መሲሑን ሳይሆን ሕዝበ እስራኤልን ነው ማለት፣ ስሕተት ይሆናል። መሲሑ “ያሕዌ ጽድቃችን” የተባለው ለዳዊት ቤት የተነሳ “ጻድቅ ቅርንጫፍ” በመሆኑ ሲሆን ኢየሩሳሌም በዚህ ስም የተጠራችው ከእርሱ ጋር ካላት የቀረበ ግንኙነት የተነሳ ነው። “ያሕዌ ጽድቃችን” የሚለው ስያሜ የመሲሁን ማንነት ገላጭ ሲሆን ኢየሩሳሌም ግን ከእርሱ የተነሳ ስያሜውን ተሸከመች እንጂ እንደ መሲሁ “ጻድቅ ቅርንጫፍፍትሕንና ጽድቅን የሚያደርግ …” አልተባለላትም። የሙስሊሙ ሰባኪ ሙግት ውድቅ ነው።

አብዱል፦

ሲቀጥል “ጽድቁኑ” צִדְקֵֽנוּ ማለት “ጽድቃችን” ማለት ሲሆን “ጽድቃችን” በሚል ቃል ላይ “ያህዌህ” የሚለው ስም ለማጫፈር ስለመጣ “እስራኤል” ወይም “ኢየሩሳሌም” ያህዌህ አይሆኑም፥ ምክንያቱም “እስራኤል” ወይም “ኢየሩሳሌም” ቦታ እስከሆኑ ድረስ የቦታ ስም ላይ “ያህዌህ” የሚለው ስም ለማጫፈር ይመጣል፦
ዘፍጥረት 22፥14 አብርሃምም ያንን “ቦታ” “ያህዌህ ይርኤ” ብሎ ጠራው።
“ይርኤ” יִרְאֶ֑ה ማለት “ያያል” ማለት ሲሆን “ያያል” በሚል ቃል ላይ “ያህዌህ” የሚለው ስም ለማጫፈር ስለመጣ ቦታው ያህዌህ ነውን? እንቀጥል፦ ዘጸአት 17፥15፤ ሙሴም “መሠዊያ” ሠራ፥ ስሙንም “ያህዌህ ንሲ” ብሎ ጠራው። “ንሲ” נִסִּֽי ማለት “ዓላማዬ” ማለት ሲሆን “ዓላማዬ” በሚል ቃል ላይ “ያህዌህ” የሚለው ስም ለማጫፈር ስለመጣ መሠዊያው ያህዌህ ነውን? እንቀጥል፦
መሳፍንት 6፥24 ጌዴዎንም በዚያ ለያህዌህ “መሠዊያ” ሠራ፥ ስሙንም “ያህዌህ ሻሎም” ብሎ ጠራው። “ሻሎም” שָׁל֑וֹם ማለት “ሰላም” ማለት ሲሆን “ሰላም” በሚል ቃል ላይ “ያህዌህ” የሚለው ስም ለማጫፈር ስለመጣ መሠዊያው ያህዌህ ነውን? እንቀጥል፦
ሕዝቅኤል 48፥35 የከተማይቱ ስም “ያህዌህ ሻማህ” ተብሎ ይጠራል። “ሻማህ” שָֽׁמָּה ማለት “በዚያ” ማለት ሲሆን “በዚያ” በሚል ቃል ላይ “ያህዌህ” የሚለው ስም ለማጫፈር ስለመጣ ከተማይቱ ያህዌህ ናትን?

መልስ፦

የዕብራይስጡን ቃላት ያነበበትን የተሳሳቱ መንገዶች በማረም እንጀምር። צִדְקֵֽנוּ የሚለው ቃል ሲነበብ ጸሐፊው እንዳለው “ጽድቁኑ” ሳይሆን “ጺዴቄኑ” የሚል ነው። “ንሲ” ያለው נִסִּֽי “ኒሢይ” የሚል ነው።  ወዳቀረበው “ሙግት” ስንመለስ በብሉይ ኪዳን “እግዚአብሔር ጽድቃችን” ተብለው የተጠሩ ሌሎች ነገሮችም ቢኖሩም (ኤርምያስ 33፥16) ሆኖም ይህ ለቦታዎች ስያሜ ብቻ የሚሰጥ ነው። ነገር ግን፣  ማንነት ላላቸው አካላት  የእግዚአብሔር ስም ሙሉውን አይቀመጥም። ኤልያህ ቢሆን ዘካሪያህ በስማቸው ላይ “ያህ” የሚለው የያሕዌ ምህፃረ ቃል ብቻ ያርፍባቸዋል። ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነን በዚሁ ትንቢተ ኤርምያስ ላይ ያለው “ሴዴቅያስ” የሚለው ስም ነው።  ሴዴቅያስ በዕብራይስጥ צִדְקִיָּה  “ጺዴቂያህ” የሚል ሲሆን ትርጉሙም “እግዚአብሔር ጽድቄ ነው”፣ የሚል ነው። በኤርምያስ 23፥6 ላይ መለኮታዊው ስም ሙሉ በሙሉ የተጻፈ ሲሆን ሴዴቅያስን በተመለከተ ግን ስሙ በምህጻረ ቃል እንደተጻፈ ልብ ማለት ያስፈልጋል (ኤርምያስ 21፥3)። በኤርሚያስ 23፥6 ላይ ግን መሲሑ  ጻድቅና ጽድቅን የሚከውን ስለሆነ “ያሕዌ ጽድቃችን” የሚለው ቃል ማንነቱን ስለሚገልጽ በሙሉ መለኮታዊ ስም ተጠቅሷል፦

ኤርምያስ 23፥5-6 “እነሆ፤ ለዳዊት፣ ጻድቅ ቅርንጫፍ የማስነሣበት ጊዜ ይመጣል፤ እርሱም ፍትሕንና ጽድቅን የሚያደርግ፣ በጥበብ የሚገዛ ንጉሥ ይሆናል” ይላል እግዚአብሔር። በእርሱም ዘመን ይሁዳ ይድናል፤ እስራኤልም በሰላም ይኖራል፤ የሚጠራበትም ስም፣ ‘እግዚአብሔር ጽድቃችን’ የሚል ነው።” (አዲሱ መ.ት)


ዋቢ መጻሕፍት
[1] (The Midrash on Psalms, William G. Braude, Translator (New Haven: Yale, 959), Yale Judaica Series, Volume 13, Leon Nemoy, Editor, Book One, Psalm 2.2)
[2] Talmud, Bava Batra 75b)
[3] https://jewsforjudaism.org/knowledge/articles/chapter-24-lord-righteousness